ሃይማኖት፣ ፍልስፍ እና ሳይንስ ያላቸው ግንኙነት (በዲያግራም)

(በካሣሁን ዓለሙ)

(የጽሑፉ ሐሳብ ከዲያግራሙ ጋር የተናበበ ስለኾነ እያስተያዩ እንዲያነቡት ይጋበዛሉ፤ ጽሑፉ ‹ቅኔ-ዘፍልሱፍ› በሚለው መጽሐፌ ውስጥም ተካቶ ይገኛል፡፡)
ሀደሀፈ
የትኛውም የዕውቀት ፅንሰ-ሐሳብ ከዚኽ ድያግራም እንደማይወጣ ማስተዋል ጠቃሚ ነው፤ ማለትም አንድ ሰው እዚኽ ከተጠቀሱት ስምንት አማራጮች ውስጥ አቋሙን ሊያንፀባርቅ የሚችለው በአንደኛው ነው፡፡ ከድያግራሙ ክበባት ውጭ የሚገኘው ስምንተኛው (ተ.ቁ. 8) አማራጭ ግን የሌለና በአማራጭ አቋምነትም ሊወሰድ የማይችል ነው፤ ምክንያቱም በዚኽ አቋም ላይ የሚገኝ ሰው አንድም ስለተባሉት (ስለ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ) ምንም ዕውቀት የሌለው ኾኖ በተለምዶ የሚኖርና፣ ዕውቀቱ ከሌሎች ኅብረተሰቦች ጋር ያልተነካካ ሲኾን፣ አንድም የአእምሮ በሽተኛ በመኾኑ ስለሃይማኖት፣ ስለፍልስፍናም ኾነ ስለሳይንሳዊ ዕውቀቶች ያለው ዕይታ ነፃ ከኾነ ነው፤ ይኽንን ደግሞ ዕውቀታዊ አድርጎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡

አንድ ሰው ምናልባትም ኹሉንም በየፈርጁ የመረዳት ችሎታ ያለው ሊኾን ይችላል እንጂ፤ በየትኛውም ቢኾን ከድያግራሙ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና እና የሳይንስ ክበባት የወጣ ዕውቀት አይኖረውም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰው የዕውቀት ኹሉ መሠረትና አእምሮን ለአስተውሎት የሚቀርፅ ፍልስፍና እንጂ ሃይማኖት ተረታ ተረትን ከማውራት ያለፈ ጥቅም የሌለው እንዳውም አእምሮ እንዳያስብ በእምነት ዶግማ ሸብቦ የሚይዝ፤ ሳይንስ ደግሞ በልዩ የዕውቀት ክልል ተሸብቦና በዚያውም ላይ በጥርቅሞሽ ላይ በተመሠረተ መላምት ተጠምዶ የሚኖር እንጂ ምንም ዓይነት ከፍልስፍና ጋር የሚገናኝ ጥቅም የሌለው አድርጎ ሊወስደው ይችላል፤ ይኽ አቋም በዲያግራሙ ተ.ቁ. ‹7› ‹ፍልስፍናን ብቻ› በሚወክለው ሥፍራ ተቀምጧል፡፡
በሌላ በኩልም ሳይንስን አግዝፎ ሌሎቹን የዕውቀት (የአስተሳሰብ) ክፍሎች አንኳሶ ወይም ሙሉ ለሙሉ ‹አይጠቅሙም፤ አያስፈልጉም፣ ትርጉምም የላቸውም› በሚል ዕይታ ቃኝቶ፤ ሃይማኖትን ጊዜው ያለፈበት ዕውቀት የሌላቸው ወይም ሳይንስን ያላወቁ ሰዎች አስተሳሰብ፣ ፍልስፍናንም በፍተናና በአስተውሎታዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ መረጋገጥ የማይችልና ለነባራዊ ዓለም ጥቅምና አገልግሎት የማይሠጥ ዕውቀት አድርጎ በመደፍጠጥ የሚያምን ይኖራል፤ ይኽ አቋምም በዲያግራሙ ተ.ቁ. ‹6› ‹ሳይንስን ብቻ› በሚወክለው ክፍል ተገልጿል፡፡
በተቃራኒው ሌላው ሰው ደግሞ ኹሉም ከሃይማኖት ውጭ ያለው ዕውቀት ትርጉም አልባ የኾነና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላ፤ ማለትም ፍልስፍና ከሃይማኖት ጋር የሚጋጭ፣ ሳይንስም ከሃይማኖት ጋር ሊገናኝ የማይችል አድርጎ ሊወስድ ይችላል፤ ይኽም ‹ሃይማኖትን ብቻ› በሚወክል አቋም በተ.ቁ. ‹5› ተጠቅሷል፡፡
እነዚኽ ሦስት አቋሞች ለየራሳቸው በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የተያዙና ‹የሌላው ክፍል ካክሽ ነው› የሚል አመለካከት ያለባቸው ናቸው፡፡ ይሁንና ሦስቱም በአንድ የሰው ልጅ አእምሮ የሚታሰቡና የሚብሰለሰሉ በመሆናቸው ግንኙነት አይኖራቸውም ለማለት ይከብዳል፤ ጽንፋዊ አስተሳሰቦቹ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋርም ተስማምተው የሚሄዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖተኛ ሆኖ የማይመረምርና ጥያቄ የማያነሳ ዝም ብሎ አእምሮውን አደንዞ የሚያምን ሰው አይኖርም፤ ካለም ጤነኛ አይደለም፡፡ ሳይንቲስትም ወይም የሳይንስ አፍቃሪ የኾነ ሰውም የሳይንስን መሠረታዊ እሳቤዎች ለመገንዘብ የማይጥር አይገኝም፤ የማይጥር ከኾነም ሳይንስ ገና አልገባውም፤ እሳቤዎቹን ለመረዳት ከጣረ ደግሞ ፍልስፍናን ፈለጋት ማለት ነው፡፡ ፈላስፋ ነኝ የሚል ሰውም ወይም የፍልስፍና አቀንቃኝ የኾነ ወዳጇ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ አመጣጥና የአኗኗር ኹኔታ የማይጠይቅና የማይመረምር፣ ስለ እግዚአብሔር ሀልዎት፣ ጠባያትና ተግባራት የማይሟገትና ስለ ዘላለማዊነትና ጊዜያዊነት ኹኔታ ጥያቄ የማያነሳ አይኖርም፤ የሳይንስንም መልስ ያለገኘላቸውን ጥያቄዎች ለምንና እንዴት እንደኾነ የማይመረምር አይኖርም፤ ካለም ፍልስፍና ገና አልገባውም፡፡ በሌላ በኩል ዐሳቢዎቹ በራሳቸው ችግር እንዳለባቸው ዕያወቁ ጽንፈኝነታቸውን የሚያጸኑ ከኾነ ደግሞ ችግሩ ያለው ከዐዋቂዎቹ (ከሰዎቹ) እንጂ ከዕወቀቶቹ ፅንሳተ ሐሳብ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚኽ በዲያግራሙ በተ.ቁ.5፣ 6 እና 7 የተወከሉት አቋሞች የፅንፈኝነት ችግር ያለባቸው ናቸው ማለታችን ትክክል ነው፡፡
ከጠቀስናቸው ጽንፈኝነቶች በተቃራኒ በተ.ቁ. 1 የተወከለው የድያግራሙ ክፍል ሦስቱን አቋሞች አስማምቶ የሚገኝ ነው፤ ሦስቱም በመሠረታቸው የተያያዙና የማይነጣጠሉ መኾናቸውን ይገልጻል፡፡ በዚኽ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ዐሳቢ ሳይንቲስት ኾኖ ሃይማኖተኛ ወይም ሃይማኖትን የሚያከብር፣ ለፍልስፍና ልዩ ክብርና ፍቅር ያለው፣ ሦስቱን አጣጥሞ የሚገኝ ሰው ነው፡፡ ለእሱ ሦስቱን ለየብቻ ለያይቶ አንድነታቸውን በማፍረስ መረዳት ከባድ ስህተት በመኾኑ ትኩረቱ ያለው የሦስቱ መስተጋብር ላይ ነው፡፡
የተ.ቁ.1 ማዕቀፍን አልፈን ወደ ኹለተኛው ክፍል (ተ.ቁ.2) ስንገባ ሳይንስ ትርጉም አልባ አስተሳሰብ ተደርጎ እናገኘዋለን፤ በዚኽ ማዕቀፍ መሠረት ከኾነም ዕውቀት በሃይማኖትና በፍልስፍና ውስጥ የሚገኝ የኹለቱ መስተጋብር እንጂ ሳይንሳዊ ስልትን የሚፈልግ አይደለም፤ የሳይንስን ዕውቀት ማዳበርም ጥቅም የሌለው የማያስፈልግ ነገር ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተ.ቁ. 3 የሚገኝ ሐሳቢ ፀረ-ሃይማኖት የኾነ አስተሳሰብ አለው፡፡ በዚኽ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ሳይንቲስትም ኾነ ፈላስፋ እንደ መምህሮቹ ኒቼና ማርክስ ሃይማኖትን አምርሮ የሚጠላ፤ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት የዕውቀትም ኾነ የመልካምነት ጥቅም የማያስገኝ አድርጎ የሚከራከር ነው፡፡ ለእሱ ዕውቀት ሊባል የሚገባው ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ሳይንስ ኾኖ ከሃይማኖት ቀኖና የተፋታ ሲኾን ነው፡፡ ስለኾነም ‹ሃይማኖት የሰው ልጆች የዕውቀት ጠላት ነው› የሚለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዚኽ ማዕቀፍ አስተሳሰብ ማንፀባረቂያ ናቸው፡፡
እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖትንና ሳይንስን አክብረው፣ ሃይማኖትን ለነፍሳቸው መዳኛ፣ ሳይንስን ለኑሯቸው መቃኛ አድርገው ከወሰዱ በኋላ ግን ፍልስፍናን ጥቅም የሌለው ወይም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን አድርገው የሚረዱ አሉ፡፡ እነዚኽም በተ.ቁ.4 የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምናልባትም ፍልስፍናን እንዲጠሉ ወይም ከፍልስፍናዊ አስተሳሰብ እንዲለዩ የሚያድርጋቸው ፍልስፍና የሚታወቀው በምንፍቅናዊ ስልት ስለመሰላቸው ሊኾን ይችላል ወይም ፍልስፍናን ሲጎረጉሩ መኖር ለሥጋም ለነፍስም የሚያመጣው ጥቅማዊ ውጤት አይኖርም ብለው ስለገመቱ ሊኾን ይችላል (Dogmatists እና Pragmatists ይኾናሉ) ወይም የፍልስፍናን ምንነትና የማወቂያ ጥበብ ማወቅ ካለመቻል ሊኾን ይችላል ወይም የፍልስፍና በምንፍቅና መጠቃትና ሃይማኖትን እንደ አሽሽ የሚወስዱ ፈላስፎች መብዛት ፍልስፍናን ከመሠረቱ እንዲቃወሙ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው ሊኾን ይችላል፡፡ በምንም ምክንያት ይሁን በዚኽ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙት ሊቃውንት ፀረ-ፍልስፍና አቋም የያዙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የዲያግሙን አስተሳሰቦች ተዘርዝሮ ሲታይ ካለው ነባራዊ ኹኔታ አንጻር የየራሳቸው ድክመትና የአስተሳሰብ መሠረት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በእኔ እምነት የቅራኔያቸውን አጽናፍና መስተጋብራዊ ግንኙት ከተረዳነው አንድ አስተሳሰብ ምንን መነሻ አድርጎ እንደሚቀርብ መገንዘብ ያስችለናል፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው የተገንዛቢው ሰው የራሱ አቋምና የዕይታ ልማድ ነው፡፡
Please follow and like us:
error

Leave a Reply