ሃይማኖት

የሃይማኖት ምንነት፡-

ሃይማኖት የሚለው ቃል ‹ማመን› እና ‹መታመን› የሚሉ ቃላትን ያቀፈ ፅንሰ-ሐሣብ ነው:፡ ‹ማመን› አንድ ‹ሰው› ወይም ‹አካል› የተናገረውን፣ የሠራውን፣ ያዘዘውን፣… አምኖ መቀበል ወይም በዚያ አካል ላይ እምነት ማሳደር ሲሆን ከዕለታዊ የሰዎች ለሰዎች የእርስበርስ የግንኙነት መስተጋብር እስከ አጠቃለዩ ዓለመ ፍጥረት መኖርና ጥበቃ፤ እንዲሁም ቃልኪዳናዊ ስምምነት ያለውን ሁኔታ ያጠቃልላል፡፡ በሌላ አገላለፅ ማመን ከራስ ውጭ የሚገኝ  የአንድ አካልን (ነገርን) መኖር አምኖ በመቀበል የእምነት ስምምነት ማድረግ ነው፡፡  እምነትም ‹ይሁን› ብሎ በመቀበል በስምምነት ውስጥ መግባት ወይም ስምምነትን መቀበል ነው፡- እምነት ውል መግባት ነው፡፡ ይህ  ከእግዚአብሔር ጋር ስናያይዘው መኖሩንና የሚሠራቸውን ተግባራት አምኖ በመቀበል መስማማት ይሆናል፤ ማመን፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ማመን ‹የዓለመ-ፍጥረቱ፣ የፍጥረታት፣ የዕውቀት፣ የሞራል… › መሠረት፣ አመንጪ፣ የበላይ ተቆጣጣሪና ጠባቂ አካል አለ፤ ከሰዎችም ጋር በተለያየ መንገድ ግኑኝነት ያደርጋል፤ በዚህም የቃል ኪዳን ስምምነት ገብቷል ይህም ትክክል ነው ብሎ መቀበል ነው፡፡

የሰው ልጅ ደግሞ በዓለም ላይ ሲኖር ያለ እምነት  ምንም ሊተገብር አይችልም፡፡ ዕምነት ለሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወትና የአእምሮ እረፍት መሠረት ነው፡፡ በግልጽም ሆነ በሥውር አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ግኑኝነት የሚያደርገው፣ የሚኖረው፣ … በሌሎች ላይ ዕምነት በማሣደር ነው፡፡ ሌሎች ተግባሮት ሁሉ የሚመጡት ዕምነትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ዕምነትም ከጥቃቅን ነገሮች የርስ በርስ ግኑኝነት ጀምሮ እስከ ዓለመ-ፍጥረቱ መሠረት መጠበቅ ያለውን ነገር አምኖ ይኖራል፡፡ ዕምነቱም በግልፅ ከሚያውቀው ጀምሮ እስከ ሊረዳው እስከማይችለው ያለውን ነገር ያጠቃልላል እንጂ በተጨባጭ ነገሮች ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ሃይማኖት ደግሞ ከማመንም በላይ ነው፤ መታመንን ይፈልጋል፡- ‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፤ በአፉም መስክሮ ይድናል› እንዳለ ቅ.ጳውሎስ፡፡ ‹መታመን› የሚለው ፅንሰ-ሐሣብ ማመንን እንደ ቅድመ ሁኔታ ይፈልጋል፡- እምነት ላልተጣለበት ነገር መታመን የለም፡፡ ስለዚህ ማመን ለመታመን ግማሽ ክፍል ነው፡፡ ‹መታመን› የሚለው ፅንሰ ሐሣብ የሚገልጸው ለአንድ አካል ወይም ሰው የገቡትን ቃል ኪዳን ወይም ስምምነት አክባሪ፣ ጠባቂ፣ ፈጻሚ መሆን ወይም በስምምነቱ መሠረትም ኃላፊነትን መወጣት፣ አኗኗርን መምራት ወይም ተግባራን ማከናወን ማለትን በመሆኑ መተማመናዊ ትግበራን ይገልጻል፡፡ መታመን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግኑኝነትም ‹መኖሩን፣ ድንቅ ተግባራቱን፣ ጠባቂነቱን፣ ትዕዛዛቱን፣ወዘተ… አምኖ በመቀበል መመስከር፣ ከእሱ ጋር የገቡትን ግኑኝነት በማክበር በአግባቡ ሕይወትን መምራት ማለት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት የእነዚህ የሁለት (የማመንና መታመን) ተመጋጋቢ ፅንሣተ ሐሣብ ውህድ ፅንሰ ሐሣብ ነው፡፡

አንድን ቃል ኪዳን በማመን ከአምላክ ጋር ግኑኝነት የሚያደርገው ምክንያታዊ አእምሮ ያለው ሰው ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለማቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን የሃይማኖት እየተናቀ፣ እየተንኳሰሰና እየተተቸ የሚገኝበት ጊዜ መሆኑ ለብዙዎች ግልፅ ነው፡፡ ለብዙዎችም ይህ አካሔድና ዕይታ ትክክል መስሎ ይታያቸዋል፡፡ አስተውሎታዊ ግን አይደለም፡፡

የእምነት ዓይነቶች፡-

ሃይማኖት ማመንና መታመን የሚሉ ፅንሣተ-ሐሣብን የያዘ ቃል ነው ባልነው መሠረትም ዓይነቱንም በዚህ ወሰነ ትርጉም ተመሥርቶ ይከፋፈላል፡፡ በአጠቃላይ ሃይማኖትን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

 1. በእግዚአብሔር ህልውነት ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት
 2. በእግዚአብሔር አለመኖር ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት
 3. ‹አሊለም› ሃይማኖት

1)  በእግዚአብሔር መኖር ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት፡-

 1. የእግዚአብሔር ህልውነትን በማመንና እሱን በመመሥከር እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ግኑኝነት የሚያደርግ በሥራው ፍፁም የሆነ አምላክ መሆኑን ይቀበላል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚካተቱም ብዙ የሃይማኖት ደረጃዎች ይገኛሉ፡፡

2)  በእግዚአብሔር አለመኖር ላይ የተመሠረተ አስተምህሮ፡-

 1. የእግዚአብሔርን ህልውነት የሚክድና ለዚያም አቋም ጥብቅና የቆመ ሃይማኖት መሰል አስተምህሮ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ሃይማኖት በግልፅና በተቋማዊ አደረጃጀት የማይታወቅ ቢመስልም በአብዛኛው በሳይንስና በፍልስፍና አስተምህሮ ተወሽቆ እምነቱ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲስፋፋ ጥረት ይደረግለታል፡፡
 2. የዚህ ሃይማኖት አቀንቃኞች በዋናነት ዝግመተ ለውጠኛችና ቁሳካላዊያን ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ፈርደሪክ ኒቼ፣ ማርክስ፣ ሌኒን፣ ዳሪዊን፣ ሪቻርድ ዳውኪንስና መሰሎቻቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

3)  ‹አሊለም›[1] እምነት

 1.  እግዚአብሔር አለ ግን፡-
 • ሥራው ትክክል አይደለም፡- ፍጥረቱን ሲመለከቱት ፈጣሪና ተቆጣጣሪ እንዳለው ይገልጻል፡፡ ይሁንና የፍጠረቱ አኗኗርና በችግር የሚገኝ መሆኑ ከእርሱ ጠባያት ጋር ይጋጫል፡፡ ስለሆነም እኩይነት በዓላማችን መንሠራፋቱ ትክክል አይደለም፡፡ በዚህ የተነሣም የእግዚአብሔርን ህልውነት እንጠራጠራለን የሚል አቋም ያራምዳሉ፡፡ ስለዚህ የፍጥረትን ፍጹም አለመሆን ለጥርጣሬያቸው እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡
 • ከፍጥረት ጋር ግኑኝነት የለውም፡- እግዚአብሔር ቅዱስና ከሁሉም በላይ ስለሆነ በእርኩሰትና በክፋት ከተሞላው የፍጥረቱ ሁኔታ ጋር ግኑኝነት የለውም፡፡ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ግኑኝነት ያደርጋል ማለት ከፍጹማዊ ጠባያቱ ጋር ይጋጫል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ካለ  የፍጥረቱ አካል ያልሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ አርስቶትል የማይንቀሳቀስ አንቀሳቃሽ የሚለው ይህንን አካል ነው፡፡
 1. የትኛውን ትክክል?፡- በዓለም ላይ የሃይማኖት ዐይነት ብዙ ነው፤ ትክክለኛውንም ለመለየት ያስቸግራል፡፡ ያለ ሃይማኖት ደግሞ እግዚአብሔርን መኖሩን አምኖ ማምለክና መመስከር አይቻልም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በህልውና መኖሩን አምነን ብንቀበል እንኳን በየትኛው እምነት ዓይነት (ሃይማኖት) ከእሱ ጋር ግኑኝነት ማድረግ እንዳለብን መለየት ስለማንችል ‹አለም›፣ ‹የለም› ብለን መግለፅ አንችልም፡፡
 2. እግዚአብሔር አለ ግን ከፍጥረት የተለየና ከእሱም ውጭ የሚገኝ እንዲሁም ከፍጥረት ተለይቶ ዘላለማዊ የሆነ አይደለም፡፡ ከፍጥረቱ ጋር ብቻ አብሮ የሚገኝ ነው አንጂ! በተለይ ሳይንቲስቶች ከንፁህ ኃይል (pure energy) ጋር ያይዙታል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ወስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ፈላስፎች (ም.ስፒኖዛ፣ ረሰል) እና ሳይንቲስቶች (ም. አይንስታይን፣ እስጢፋኖስ ሃውኪን…) ናቸው፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሦስት አማሮጮች ውስጥ ከመጀመሪያው በስተቀር ሌሎቹ የሃይማኖትን ትርጉም በትክክል የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ምንም እንኳን ፍልስፍና እና ሳይንስን በማመንና ለእነሱም ጥብቅና በመቆም መታመኑን የሚመሰክር ቢኾንም በውስጡ የተለያዩ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛ ፍልስፍና (በተለይ ዓለማዊ ፍልስፍና) የሚታመን መሠረት የሌለው ገና በእውን ነገር መኖርና አለመኖር ላይ የሚሟገት የንፀሮተ ዓለም ፅንሰ-ሐሣብ ነው፡፡ በእውን ነገር መሠረት መኖርና አለመኖር ላይ ጭቅጭቅ አለበት፤ በዚህ የተነሣም ከሰዎች አንጻር ብቻ የሚቃኝ አመለካከት ለመኾን ይገደዳል፡፡ ሳይንስ ደግሞ የተለዋዋጩ ዓለም ተለዋዋጭ ዕውቀት ነው፡፡ ሰዎች ለማወቅ እስከጣሩበት ያለውን በመቀበል ከዚያ ውጭ ያለውን ዕውቀት ይሸፍናል፤ መሠረቱም የሰዎች ፍልስፍናዊ ዕይታ ነው፡፡ ስለዚህ ሳይንስም የሚታመን አካልን በመሠረትነት በመቀበል ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ይሁንና ኹለቱም ለክፍላቸው የታመነ ምስክርነት አሏቸው፤ስለኾነም ነው ዕይታቸው  እንደ ሃይማኖት ሊወሰድ የቻለው፡፡ ችግሩም ያለው በመታመናቸው ሳይኾን የታመኑበት ነገር አስተማማኝ አለመኾኑ ነው፡፡ ይህ ስለኾነም በእግዚአብሔር አለመኖር ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ ሃይማኖት የሚለውን ፅንሰ-ሓሣብ በአግባቡ የማያሟላ ነው፤ በመኾኑም ተቀባይነት የለውም፡፡

ኹለተኛው አቋም ግራመጋባት የፈጠረው አስተሳሰብ ይመስላል፡፡ የአስተሳሰብ ግራ መጋባት ደግሞ የእምነት መድረሻ አይኖረውም፡፡

በዚያም አለ በዚህ ትክክለኛ ሊኾን የሚችለው አንደኛው ዓይነት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት የሚያምኑት ወይም ቃል የገቡለት አካል መኖርን ለእሱም ቃል ገብቶ መጠበቅን ይጠይቃል፤ በቃል ኪዳን የተሣሠሩት አካል ከሌለው ወይም አስተማማኝ የኾነ አካልን ቃልኪዳን ተቀብሎ ካልጠበቁ ሃይማኖት አይኖርም ወይም የተሟላ ትርጉም አይኖረውም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ አንድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ሃይማኖትም አንድ መሆን የግድ ነው፡፡ ስለኾነም ነው ቅ.ጳውሎስ ‹አንዲት ሃይማኖት› በማለት እግዚአብሔር አንድ እንደኾነ ኹሉ በሃዝ ወስኖ ያስቀመጠው፡፡

 1. በእግዚአብሔር መኖር ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ደረጃዎች፡-

1ኛ ደረጃ. በአግዚአብሔር መኖር ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ:-

 1. ፍጥረት ያለ ልዕለ ተፈጥሮ አካል ሊገኝ የሚችልበት ዕድል የለም፡፡ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ የሚያስተዳድራቸው አካል መኖሩ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም እያንዳንዷን የሰዎች እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር አይደለም፤ ከፈጠረ በኋላ ሕግና ሥርዓትን ሠርቶ በዚያ እንዲተዳደር ትቶታል፡፡ ለምሳሌ አፍላጦን፣ አርስጣጣሊስና አብዛኞቹ የግሪክ ፈላስፎች በዚህ ዕምነት አቋም ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
 2. ማስረጃቸው ተፈጥሮ ብቻ  ነው፡፡ በሐሳብ ደረጃ የሃይማኖት መጻሕፍትን በአብዛኛው አይቀበሉም፤ ከተወሰኑት የምሥራቅ ሃይማኖቶች በስተቀር፡፡

2ኛ ደረጃ. አግዚአብሔር በተለያየ ሁኔታ መገለጡን የሚያምንና የሚቀበል፡-

 1. አግዚአብሔር ፍጥረታትን ከመፍጠሩም በተጨማሪ ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያደርጋል፤ በተለይም ለሰዎች ማንነቱን ገልጽዋል ( ለምሳሌ በራዕይ፣ ሰዎችን በቀጥታ በተላያየ ነገር ላይ ተገልጾ በማነጋገርና ምልክቶችንና ታምራቶችን በማሳየት፣ በህልም…) ሆኖም እንደ እኛ ሰው በመሆን አልተገለፀም፡፡
 2. የእስልምና ሃይማኖት፤ እንዲሁም ከእነዚህና ከምሥራቅ ሃይማኖቶች ጋር የተያያዘ አስተምህሮ ያላቸው አብያተ እምነቶች፡፡ የአይሁድ ሃይማኖት በዚህ ክፍል መካተት ቢችልም ወደፊት ሰው በመሆን ይገለፃል የሚል እምነት ስለሚያራምድ ከዚህ በታች ከተገለፀው ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የበለጠ ይቀርባል፡፡ ሰው በመሆን በሥጋ ሰብዕ አልተገለፀም በማለት ደግሞ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር አብሮ ይሰለፋል፡፡ የባህዑላ ሃይማኖትም በዚህ ክፍል መመደብ ይችላል፡፡

3ኛ ደረጃ. እግዚአብሔር በሥጋ (ሰው በመሆን) አንደተገለጠ የሚቀበል፡-

 1. እግዚአብሔር ፍጥረቱን ከመፍጠሩም በተጨማሪም ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያደርጋል፡፡ በዚህ ግንኙነትም በሰውነት እስከመገለጥ ደርሷል፡፡
 2. በዚህ ሥር የሚገኙ በክርስትና ወስጥ የሚገኙ አባዛኞቹ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊሊክና ፕሮቴስታንት
 3. አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ዶግማዎቻቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አዕማዳተ ምሥጢራት የሚባሉት፡- ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡ ከእነዚህ አዕማደተ ምሥጢራት የወጣ አስተምህሮ የለም፡- ከወጣም የክርስትና መንፈስ አይኖረውም፤ ይሁንና ባስሊየሳዊያን (ኢየሱስ ብቻ) እና አርዮሳዊያን (የያህዋ ምስክሮች) የሚባሉ ይህንን አስተምህሮ በሙሉነት የማይቀበሉ አካላትም አሉ፡፡

እዚህ ላይ ጥያቄ በማንሳት መከራከር እንችላለን፡፡ በእግዚአብሔር መኖር አያምኑም የምንላቸውን ሃይማኖቶች ብንተዋቸው እንኳን በእሱ የሚያምኑት ሃይማኖቶች ለምን ተለያዩ? የሚያምኑበት አምላክ አንድ አይደለም እንዴ? ነው የሃይማኖት መለያየት ምንም ለውጥ የለውም? ለውጥ ከሌለው በተለያዩ ሃይማኖቶች ተቃራኒ የሆኑ መርሆዎች ለምን ሊኖሩ ቻሉ? ለምንስ አንዱ ሌላውን እንደተሳሳተ ይቆጥራል? አንድ ሃይማኖት ብቻ ከሆነ ትክክል ታዲያ ሌሎቹ ምን ይሠራሉ? የትኛውስ ነው ትክክል? እንዴትስ ትክክለኛውን ለይቶ ማወቅ ይቻላል?

ሃይማኖት ለምን ተለያየ?

የሰው ልጅ በዓለም ላይ ሲኖር በባህል፣ በልምድ፣ በግንዛቤ መለያየትና በቀደምት ትውልዶች አስተሳሰብ ተፅዕኖ እንደሚደረግበት ይታወቃል፡፡፡ ይህ ደግሞ የአምልኮ ሥርዓትና የዶግማ መለያየትን እንደሚፈጥር ይነግረናል፡፡ በዓለም ላይም የተለያየ ሃይማኖት መኖሩ እርግጥ ነው፡፡  ይህንን መለያየት በማየት ‹የሚመለከው እግዚአብሔር አንድ ኾኖ እያለ ለምን ሃይማኖት እንደዚህ ሊለያይ ቻለ?› በማለትም መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄም የሚከተሉትን ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል፡፡

v  በሰው ልጆች ፍላጎት መለያየት፡- ሃይማኖት ከሰዎች አመለካከት ጋር የተያያዘ በፍላጎት የሚቀበሉት ነገር ነው፡፡ በመኾኑም ሰዎች አመለካከታቸው በመለያየቱ የሚከተሉት ሃይማኖትም በፍላጎታቸው ላይ ተመሥርቶ መለያየቱ የግድ ይኾናል፡፡

v  የሰው ልጅ በነፃ አዕምሮው በመምረጥ የሚያምን መኾኑ፡- ሰዎች በፈቃዳቸውና በነፃ ምርጫው ተመሥርተው ነው ዕምነታቸውን የሚወስኑት፡፡ በነፃ ምርጫቸው በመጠቀምም የሚፈልጉትን፣ ቅርብ የኾኑለትንና ተፅዕኖ ያደረገባቸውን ሃይማኖት መርጠው ያምናሉ፡፡ ነፃ ምርጫም የኹኔታዎች ተገዥ ስለኾነ ሰዎች ተገዥ በኾኑበት ነገር ላይ ተመሥርተው እምነታቸውን እነዲመርጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ሃይማኖት እንደ ኅብረተሰቡና ሰዎች ልዩነት ሊለያይ ችሏል፡፡

v  የሰው ልጅ ስህተት ፈፅሞ የሚኖር መኾኑ፡- በክርስትና ሃይማኖት ዕይታ የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር የጀመረው ስህተትን ከፈፀመ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖርም ብዙ የዕለታዊ ሥራዎችና የታሪክ ውርሶች ተፅዕኖ ያደርጉበታል፡፡ በዚህ የተነሳም አዕምሮው እየዛገ በመሔዱ የፅሑፍ ሕግ በዕየለቱ እየተመለከተ እንዲያስታውስ ተደርጓል፡፡ በመኾኑም የሰው ልጅ ስህተትን ከፈፀመ በኋላ ያለው ሕይወቱ በስህተት የተሞላ ሊኾን ችሏል፡፡ ይህም የተለያየ ሃይማኖትንም እንዲፈጥር አድርጎታል፡፡

v  የሰው ልጅ አኗኗር በሕግና በልምድ እየተለያየ መሔድ፡- ሰዎች በመኖሪያ አካባቢያቸውና በአኗኗር ስልታቸው ይለያያሉ፡፡ በመኾኑም በዓለም ላይ አንድ ተመሳሳይ የኾነ ነገርን በተለያየ መንገድ ሊገልፁትና ሊተገብሩት ይችላሉ፡፡ ይህም ከታሪካዊ ቆይታ ጋር ተያይዞ ልምድ ይኾናል፡፡ ሃይማኖትም በዚህ ልምድና አኗኗር ሥርዓት ተገዥ ነው፡፡ ይህ በመኾኑም በዓለማችን ላይ የሃይማኖት መለያየት ሊፈጠር ችሏል፡፡

v  በሰይጣን መኖር፡- በዓለማችን ላይ ሰዎች በስህተት ጎዳና እንዲጓዙ የሚያደርግ ሰይጣን የሚባል እርኩስ መንፈስ አለ፡፡ የእሱም ዓላማ ሰዎች ከመልካምነት ርቀው ከአምላካቸው እንዲለዩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ተግባሩም የሰዎች እምነት የተለያየ እንዲኾን በማድረግ ያሳስታል፡፡ በመኾኑም በዓለም ላይ የተለያዩ ሃይማኖቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ለዚህም በአንድ መጽሐፍ ቅድስ የሚመሩ ክርስቲያኖች የተለያየ እምነት መከተላቸው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን በዓለም ላይ መኖሩ ለሃይማኖት መዛባትና መብዛት ምክንያት ነው:- ለማወናበጃነት ስለሚጠቀምበት፡፡

v  እግዚአብሔር በግደታ አምልኩኝ አለማለቱ፡- ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሃይማኖት መለያየት የቻለው እግዚአብሔር በግደታ አምልኩኝ ባለማለቱ የተነሳ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የማምለክ ሥርዓት በግደታ ላይ የተመሠረተ ቢኾን ኖሮ ሃይማኖት የፍርሃት ውጤት ስለሚኾን በየትም አካባቢ ተመሳሳይ ይኾን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የነፃነት አምላክ ስለኾነ በዚህ እመኑ በማለት አያስገድድም፡፡ በመኾኑም ሰዎች እንደ አካባቢያቸው ተጨባጭ ኹኔታና ልምዳቸው የተለያየ እምነት ሊኖራቸው ችሏል፡፡ በመኾኑም ሃይማኖት ሊለያይ ችሏል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የሃይማኖት መለያየት የእግዚአብሔርን ህልውነት መቃወም አይችልም፡፡ ከመቃወም ይልቅም  የሃይማኖት መለያየት በነፃ ምርጫ ላይ ተመሥርቶ ዕምነትን መከተል እንደሚገባ የሚገልፅ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በነፃ አዕምሮው ተጠቅሞ ከሌላው በመለየት የራሱን አመለካከት ይከተላል፡፡ በዚህ መሠረትም የራሱን አመለካከት የተከተለ ሰውም ከእሱ ጋር የሚገጥም አመለካከት ያላቸው ሰዎችን ዕምነት ይጋራል፡፡ በዚህም በፊት ከነበረው የተለየ ዕምነት መፈጠሩ የግድ ነው፡፡ ይህም ልዩነቱን ያመጡት ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች መኾናቸውን ይመሠክራል፡፡  ስለዚህ የሃይማኖት መለያየት የእግዚአብሔርን የነፃነት አምላክ መኾን ይመሰክራል፤ በራስ ፍላጎትም ተፅእኖ ሊዩነት ሊያመጣ ችሏል፡፡

የሃይማኖት ሚዛኖች

በጥቅል መልክ አንድን ሃይማኖት በሚከተሉት ሚዛኖች መገምገም  ይቻላል፡፡ እስቲ እንያቸው፡፡

1)  አንድ ሃይማኖት ትክክለኛ ነው ለመባል በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ህልውነት ላይ ሙሉ እምነት ያለው (እግዚአብሔር መሠረት የሆነው) መሆን ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ አሳማኝ የሆነ የእምነት መሠረት አይኖረውምና፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት የሁለት አካላትን ቃል ኪዳን መጠበቅና መተማመን የሚፈልግ ፅንሰ-ሐሣብ ነው፡፡ እምነት የሚጣልበት ነገርን ይፈልጋል፤ በዓለም ላይ የሚገኝ ነገር ሁሉ ደግሞ ሙሉ እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ብቻ የሆነ እምነትም ለሃይማኖት የተሟላ ወሰነ ትርጉም አያሰጥም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን መሠረቱ ያላደረገ ሃይማኖት ትክክል አይደለም፡፡

2)  የእግዚአብሔርን መታወቂያ ጠባያትም ሳያምታታና ሳይሻራርፍ በሙሉነት መቀበል መቻል አለበት፡፡ አግዚአብሔርን ልናውቀው የቻልነው በጠባያቱ ምንባብነት ነውና፡፡ የእግዚአብሔርን ጠባያት ሙሉ ለሙሉ ሳያካትት እና/ እያምታታ የሚገልጽ ሃይማኖት አስተማማኝነት አይኖረውም፤ ችግር አለበት፡፡

3)  ከእግዚአብሔር ተነገረ የተባለው ነገር በተግባር ተገልጾ መታየት (መተግበር) መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ በትንቢት መልክ የተገለጹ በተግባር ተፈጽመው፣ በምሳሌ የተገለፁም በአማዊነት እውን ሆነው መታየት አለባቸው፡፡

4)  ሃይማኖቱ ከእግዚአብሔር ለሰዎች በሰዎች አማካይነት የተገለጸ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት ከሰዎች አዕምሮ አስተሳሰብ በላይ የሆኑ ነገሮችን የያዘና የእግዚአብሔርን ሥራዎች የሚገልፅ ነው፤ እነዚህን መገለጦች በአግባቡ አውቆ ለሰዎች መግለጽ የሚችለው ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እሱም ምንም እንኳን ሰዎች ሊረዱት በሚችሉ ነገሮች ሁሉ ማንነቱን፣ ተግባራቱንና ህልውናውን መግለጽ ቢችልም በአግባቡ ሰዎች ሊገነዘቡት የሚችሉት በሰዎች ቋንቋና መግባቢያ መንገድ ሲገለጽ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ሰዎች ራሳቸው ናቸው ወይም በሰዎች በኩል ነው፤ ስለዚህ በሰዎች በኩል መገለጹ ከየትኛውም መንገድ የተሻለ ነው፡፡ እንዲሁም ሃይማኖት ከአምልኮ ተግባራት (ከጸሎት፣ ጾም…) ጋር የተያያዘ ነው (በተለይ ጸሎት ከበላይ ጋር የሚደረግ ውይይት ነውና)፤ ይህንን ደግሞ የሚፈጽሙት ሰዎች ናቸው፡፡ ይህንን አምልኮም የሚፈጽሙት እነሱ ሊገባቸውና ከስሜታቸውና ከአዕምሯቸው ጋር አገናዝበው ነው፡፡ ይሁንና መሠረታዊ ሕግጋቱ ( ለምሳሌ የእግዚአብሔር ጠባያት ፍጹምነት) አስተማማኝ መሆን አለባቸው፤ በሰዎች አኗኗር ሁኔታ፣ የግንዛቤ ደረጃና ልምድ እና ስሜታዊነት የተነሣ በየጊዜው የሚለዋወጡና የታደሱ መሆን የለባቸውም፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ምንጩ እግዚአብሔር ራሱ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ከሆነም ሃይማኖት ከእግዚአብሔር በሰዎች በኩል ለሰዎች የተገለጸ መሆን አለበት፡፡

5)  ከሰዎች ተፈጥሯዊ ሥነ ልቦና፣ የአዕምሯ ሚዛንና የተፈጥሮ ሁኔታዎች (ከሰው ውጭ የሚገኙትንም ጨምሮ) ጋር መስማማት አለበት፡፡ ምክንያቱም በሃይማኖት አምኖ አምልኮ የሚፈጽመው ሰው ነውና፡፡ ሰው ደግሞ የአዕምሮና የስሜት ሥሪት መሆኑ ይታወቃል፤ አምልኮም የሚፈጽመው በአዕምሮው አስቦና በሰሜቱ አንብቦ ነው እንጂ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶቹን አውልቆ አይደለም፡፡ እነዚህም የተፈጥሮው ሀብቶች ከውጭው ዓለም (ነገሮች) ጋር ግኑኝነት ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖቱ የእነዚህን የተፈጥሮ መስተጋብሮች በማስማማት መግለጽ መቻል አለበት፡፡

6)  ምክንያታዊ የሆነና ዓላማ ያለው መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር ግብታዊ አምላክ አይደለም፤ ስለሆነም አንዲትም ነገር በዘፈቀደ አይሠራም፡፡ በዚህ የተነሣም በሃይማኖት መኖርና መመራት ያስፈለገበት ምክንያት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለበት ግብና ግቡ ጋር መድረሻም ሥርዓትና ዓላማ ሊኖረው ይገባል፡፡

7)  እንደዘመኑና እንደሁኔታው የሚለዋወጥ መሆን የለበትም፡፡ ያለበለዚያ ከትውልድ ሁኔታ መለዋወጥ ጋር አብሮ የሚቀያየር ከሆነ ዋስትና አይኖረውም፡፡

8)  በሃይማኖቱ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት አለበት፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት በእግዚአብሔር የተገለጠና በሰዎች እሳቤ የታገዘ ስለሆነ ነው፡፡

9)  የሰው ዘሮችን ሁሉ በእኩል ዕይታ የሚያይ መሆን አለበት፡፡ ማለትም አንዱን ዘር የተመረጠ ሌላውን ደግሞ የተለየ ማድረግ የለበትም፡፡

10) በተፈጥሮ ሥርዓት ውስጥ የሰውን ልጅ የመመራመር ተፈጥሮ የሚያግድ መሆን የለበትም፡፡ የሰው ልጅ የመመራመር ተፈጥሮ ያለው ፍጡር ነውና፤ እስከቻለው ማሰብ፣ መጠየቅና የጠየቀውን መልስ ለመስጠት መሞከር አለበት፡፡

(ይህ ጽሑፍ የሚቀረው ትንታኔና መቃጫ አለ)


[1] ‹አሊለም› የሚለው  ‹አለ+የለም› የሚሉ ቃላት ጥምረት ነው፡፡

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply