ለምን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና…?

ለምን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና…? 

በካሣሁን ዓለሙ 

‹የጥንታዊ ኢትዮጵያን ጥበብ› የሚዳስሱ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ስውተረተር ‹Encarta 2009›ን ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደያዘ ጠየቅኩት:: የአውሮፓ ነው ያለውን ከጥንታዊት ግሪክ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ አሜሪካ ድረስ ያሉ የፍልስፍና  ዓይነቶችን ዘርዝሮ አቀረበልኝ፤ ወደ ህንድና ቻይናም ሔዶ አማረጠኝ፤ ወደ መካከለኛው የእስልምና ዓለም ፍልስፍናም ወስዶ አስጎበኘኝ፡፡ ሆኖም ምንም እሱ በዚህ መልክ ቢያማርጠኝም እኔ ‹ጥያቄዬ አልተመለሰም› አልኩት፤  ሐቀኛው Encarta እንኳን በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአፍሪካ ፍልስፍና መኖሩን እንዳማያውቅ እቅጩን አረዳኝ፡፡ ይህም የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የተናገሩትን አስታወሰኝ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ ለአሜሪካን ኮንግረስ የአፍሪካ ክፍል በአቀረቡት የመወያያ ሐሣብ እንዳሉት ከሆነ በእ.ኤ.አ.1958 በካይሮ ላይ ‹Mutual appreciation of western & Eastern cultural values› በሚል ርዕስ በተካሔደ ጉባኤ የአፍሪካ አስተምህሮ አለመነሳቱ አስገርሟቸው ‹አፍሪካ የት ናት?› የሚል ጥያቄ ለመጠየቅ መገደዳቸውን አንስተው የተሰጣቸው መልስ ‹አፍሪካ ያላት ማሐይም ማኅብረሰብ ነው› የሚል ዓይነት እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ እኔም Encarta ሐቀኛ መልሱን ከነገረኝ በኋላ የበለጡ ጥያቄዎች ተግተለተሉብኝ መጡ፡፡ ‹ለምን የእኛ ዕውቀት ሳይመዘገብ ቀረ?› የሚል!

እንዲሁም Encyclopedia of Philosophy የሚለውን ባለ አሥር መድብል የዕውቀት መዝገብ አገላበጥኩት፡- ‹ከየት ላምጣልህ?› የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት፡፡ ጉድ! ብላችሁ አዘን እንዳትቀመጡ፤ ሰጋሁ፡፡ ቢያንስ እነ ዘርዓ ያእቆብን አለማወቁ አይገርማችሁም? እውን ኢትዮጵያ የእኔ ነው የምትለው የራሷ ጥበብ የላትም? ነው እንዳይታወቅ የተፈለገበት ምክንያት አለው? ግን ለምን? ኢትዮጵያ አሁን እንዳለችበት ሳትሆን በፊት በተለይም በጥንት ዘመናት የሥልጣኔዎች ምንጭ የነበረች ሀገር ናት፡፡ በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱ ጉድፈቶችን ለመዛግብተ ቃሎቻቸው ማብራሪያ እንደምሳሌ ለማስቀመጥ የፈጠኑ፤… አውሮፓዉያን ለምን በአጠቃላይ የአፍሪካን በተለይም የኢትዮጵያን ፍልስፍና መዝግበው ለማሳወቅ ሳይችሉ ቀሩ? ከእነ ደካርተስ ጋር የሚያመሳስለውን የዘርዓ ያዕቆብን ፍልስፍና ያላካተቱበት ምሥጢሩ ምንድነው? አለማወቅ? ዘረኝነት? ወይስ ሌላ ጉዳይ? ግን ለምን ይህንን አደረጉ?

ከዚያም ‹ራሱ ፍልስፍና ምንድን ነው?› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ በጣም የከነከናችሁን ጥያቄ ስትጠይቁ  መልሱን ቶሎ ካላገኛችሁ የበለጠ ጥያቄ ይጎለጎልባችሁ የለ? ስለዚህ የፍልስፍና ምንነት ማብሰልሰል ጀመርኩ፡፡ ፍልስፍና በነጠላ ትርጉሙ ‹ጥበብን ማፍቀር› የሚል እንደኾነ ደግሞ መጀመሪያ ቃሉን ተናገረው ከተባለው ከፊጣጎረስ (Pythagoras) መረዳት ችያለሁ፡፡ ሶቅራጥስም የፍልስፍና መሠረቱ መደነቅ መቻል መኾኑንም ነግሮኛል፡፡ በጥበብ ፍቅር ተነድፎ በመደነቅ ምርምር የሚደረገውም ትክክለኛው እውነት ጋር ለመድረስ መሆኑንም ተረድቻለሁ፡፡ እና ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው የዚህ ዓይነት ጥበብ አልነበራቸው?  ይህንን ለማረጋገጥም የኢትዮጵያውያንን የጥንታዊ የትምህርት መስኮች (ጉባኤያት) መዳሰስ አስፈላጊ ኾኖ አገኘሁት፡፡ በዚህም ‹የኢትያጵያ ፍልስፍና ምን ዓይነት ነው?› ለሚለው ጥያቄ መልሱን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ከዚያም የሚከተሉት ነጥቦች የኢትዮጵያውያን ጥበብ ዋና ዋና ማጠንጠኛዎች መስለው ታዩኝ፡፡

1) መሠረቱ ዕውቀት ሳይሆን ሃይማኖት (እምነት) መሆኑን ተረዳሁ፤ ስለሆነም ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡› ይላል፡- በኢትዮጵያ የተመለከትኩት ፍልስፍና፡፡ በዚህ ግን ‹በእግዚአብሔር መኖር ላይ ተማምኖ መፈላሰፍ ይቻላል? ወይስ አይቻልም?› የሚለው ጥያቄ መጥቶ ድንቅር አለብኝ፡፡ ለዚህ የሚሆን መልስ ሳፈላልግም አዛብኛቹ የጥንታዊት ግሪክ ፈላስፎች የአንድ አምላክ መኖርን የሚደግፉ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ እነ ኤራቅሊጠስ፣ ዜኖፎን፣ ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶ፣ አርስጣጣሊስና ሌሎችም አጠራራቸው ቢለያይም በእግዚአብሔር መኖር ግን እንደሚስማሙ ሳያብሉ መሰከሩልኝ፡፡ ለማጠናከር ብዬ ወደ ሮማያውያን ተሸጋገርኩ እነ አውግስቲን ኋላም እነ ቶማስ አኩነስ የፍልስፍናችን መሠረትና ጉልላት የእግዚአብሔር መኖር ነው ብለው መለሱልኝ፡፡ ምስክር በሦስት ይፀናል ብዬ ወደ ዘመናዊያን ፈላስፎች ተጠጋሁ፤ እነ ደካርተስ፣ በርክሌይ፣ ካንትና መሰሎቻቸው የፍልፍናችን መሠረት እግዚአብሔር ነው አሉኝ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዳውስ የኢትዮጵያውያንም ጥበብ መሠረቱን ‹እግዚአብሔርን መፍራት› ማድረጉ ከፍልስፍና ውጭ አያስወጣውም አልኩኝ፡፡ በእምነት ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና አይኖርም ያለው ማን ነው?

እንዳውም ፍልስፍና በእምነት ላይ ሲመሠረት አሳማኝነት ይኖረዋል ብዬ ገመትኩ፤ እምነት አልባ ፍልስፍና ግን መሠረቱ አጨቃጫቂ ነውና፤ አጨቃጫቂ ነገርም ተቀባይነት አይኖረውም፡- የሚልው እምነት ሰረፀኝ፡፡ ምክንያቱም የፍልስፍና መሠረት እምነት ነው ካልን፤ የእምነት ዋናው መሠረትም የእግዚአብሔር መኖር ነው፤ እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርዩ ፍጹም ስለሆነ ሌላ አያስፈልገውም፤ የአስተሳሰብ ሁሉ መደምደሚያ ነው፡፡ ነገር ግን ፍልስፍና የእምነት መሠረት ከሌለው በምን መነሻ መስማማት ይቻላል? ስለዚህ የኢትዮጵያውያንም ፍልስፍና በእምነት ላይ መመሥረቱ አስተውሎታዊ ነው እንጂ አለማወቅ አይደለም፤ ብዬ ወሰድኩት፡፡

2) ሁሉም ጥበባቸው በሥነ-ምግባር የተቃኘ መሆኑን ዐየሁ፤ ለዚህም የተረጎሟቸው የታዋቂ ፈላስፎች ጽሑፎች ሳይቀሩ በምስክርመት አረጋገጡልኝ፡፡ አንጋረ ፈላስፋን (የፈላስፎች አነጋገር) አገላብጬ ተመለከትኩት የብዙ ፈላስፎች ሥነ ምግባራዊ ንግግር ወይም መልካም ምክር በኢትዮጵያውያን መንፈስ ተቃኝቶ ተሰብስቦበታል፤ እንዳውም አብዛኞቹ የመጽሐፉ ጥቅሶች ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የራሳቸውን ፍልስፍና ደብቀው በሌሎች ፈላስፎች ስምና ባልታወቁ ፈላስፎች መልክ የሰገሰጉባቸው መሆናቸውን ጠረጠርኩ፡፡ ጥርጣሬ ያለምክንያት አይደለም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትህትና ስለሚያጠቃቸው ዐዋቂ ሰው መስለው መታየት እንደማይፈልጉ በጻፏቸው የሃይማኖት መጽሐፎች ተመልክቻለሁ፡፡ ስለዚህ ይህም ጥርጣሬ የኢትዮጵያውያንን የትህትና ልምድ በማየት የመጣ ነው፡፡

በተጨማሪም የዘርያዕቆብና የወልደሕይወትን ፍልስፍናዊ መጣፎች ተመለከትኩ በዋናነት በሥነምግባር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ወይም በሥነ ምግባር ፍልሰፍና የተቃኙ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ሥነ-ምግባር ደግሞ አንዱና ዋናው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መሆኑን ዐውቃለሁ፡፡ እንዳውም ሥነ-ምግባር አልባ ፍልስፍና ስብዕና አልባ ዕውቀት እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ስለዚህ የጥንት ኢትዮጵያውያን ፍልስፍና በሥነ ምግባር ገመድ መሸበቡ መልካምና ጥሩ ፍልስፍናዊ ዕይታ ሆኖ አገኘሁት፡፡

3) ፍልስፍናቸው በዋናነት በኅበር ትርጓሜያት የሚፈታ መሆኑንም የተመለከትኩት መለያው ነው፡፡ ይህንንስ በጥቅሉ ዘረዘር ላድርገው መሰል፡፡ በመጀመሪያ ቅኔዎቻቸውን ተመለካከትኩ የሚደንቁ ዕይታዎችንና ልዩ አቀራረቦችን ሳገኝ ‹ይህማ የትም የማይገኝ የኢትዮጵያውያን ብቸኛ ፍልስፍና ነው› እስከማለት ደረስኩ፤ ተደንቄ፡- መፈላሰፍ ልጀምር!፡፡ ቅኔያቸው ሥጋና ነፍስ የተዋሐዱበት እንጂ በአጥንትና ሥጋ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ሰው ሕይወት ዘርቶ የሚንቀሳቀሰው ነፍስ ያለው ከሆነ ነውና፡፡ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትልቁ ፍልስፍናቸው ቅኔያቸው መስሎ ስለተሰማኝ በምሳሌ ላሳይ መሰል፡፡

በምንት ቆመት ማሪያም እኅተ ሙሴ ወዮሳ፣

ሰማይ ወምድር እስመ ተፀውሩ በከርሳ፡፡

ትርጉም፡-

‹ሰማይና መሬት በሆዷ ውስጥ በተሰወሩ ጊዜ የሙሴና የዮሳ እህት የሆነቸው ማሪያም በምን ላይ ቆመች?›

የዚህን ቅኔ ቆዳውን በማንሳት ሥጋውን እንበልተው፤ ባለቅኔው እንዲህ ይላል ‹አስቡት እስቲ ሰማይና ምድር በአንዲት ሴት ሆድ ውስጥ የተቀመጡ ቢሆኑ ሴትዮዋ በምን ላይ ትቆማለች? እንዴትስ ወደ ሰማይ ቀና ልትል ትችላለች? እስቲ መልስ አምጡ?› ብሎ በመጠየቅ ሰማይና መሬት በምን ላይ ቆመው ሊገኙ እንደቻሉ እያሰበ በአምላክ ሥራ ይደነቃል፡፡ እና! አዮናዊያንና አቴናዊያን የግሪክ ፈላስፎች ከዚህ የበለጠ ምን ጠየቁ? እንዳውም እጥር ምጥን በማለት ይህ ፍልስፍና አይበልጥም አንደ? ይህ ግን ለኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንት ሥጋውና ፊት ለፊት የሚታየው አካል ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ነፍስ የሌለው ሥጋ የሞተ ነው፤ የ‹ጨዋ ሰው› ነው፡፡ ስለዚህ ዋናውን የቅኔውን ፍልስፍና መንፈስ መመርመር ግድ ይላል፡- በምርመር ቅኔ አነጋገር ከገለጽነው ‹ወርቁ›ን ማለት ይሆናል፡፡

የባለ ቅኔው ወርቅ የሆነው ፍልስፍና አንዲህ ነው ያለው ብዬ ግምቴን ላውራ መሰል!፤ ምን ላድርግ ግምቴን እንጂ ትክክለኛውን ነው ካልኩማ፡- ‹የማያቁትን (ያልተቀኙትን) ቅኔ መተርጎም ያለሳደጉትን ውሻ መቆንጠጥ ነው› ይሉብኛላ!፤ ስለዚህ ግምቴ መሆኑን ያዙልኝ፡፡ እንደ ግምቴ ከሆነ ባለቅኔው የእግዜር ሰው ነው፤ ሰማይን ያለ ባላ ምደርን ያለ ካስማ ያቆመ አምላክ ባደረገው ሥራ የሚያምን፤ እግዜር ከሠራው ድንቅ ተግባር ውስጥ ደግሞ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው መሆኑ አስደንቆ እንቅልፍ ነስቶታል፡፡ ይህንን የሚደንቀውን የአምላክ ሥራ ታዲያ በቅኔው ከሸነው፡፡ እንዳውም ሊቃውንቱ በተሰበሰቡበት ለመምህሩ (ጓደኞቻቸው) ይመስለኛል በቅኔው ምጥንጥን አድርጎ ጠየቀ፤ በተጠየቅ ቢቀመጥ፡-

‹ለመሆኑ እናንተ ሊቃውንት ሁሉ ጥያቄ አለኝና ተጠየቁ› አለ፡፡

‹ጠይቅ!› አሉ መምህሩ፡- ተማሪ ሲጠይቅ መልስ መስጠት ወግ ነውና፡፡

‹ሰማይና መሬት በእግዚአብሔር ተፈጥረው፤ በመግቦቱና ጥበቃው ይኖራሉ እያላችሁ ታስተምራላችሁ?›

‹አዎ!› አሉ ሊቁ መምህር፤

‹ማሪያም ደግሞ በመሬት ላይ ቆማ ትሔድ የነበረች እንደኛ ዓይነት ሰው ነበረች›

‹እንደኛ ዐይናት ተራ ሳትሆን አምላክ የመረጣት ነበረች እንጂ ሰውማ ነበረች!› አሉ ሊቁ ምን ሊያመጣ ነው ብለው፡- ምናልባት ሰይጣን እንደ አሪዎስና ንስጥሮስ ለምንፍቅና ዳረገው እንደ! ብለውም ይሆናል፡፡

‹አያጣርሱ የኔታ!› አለ ባለቅኔው ‹አንድ ስጠይቀዎት አንዷን ሁለት ስጠይቀዎት ሁለቷን ከዚህ ያለፍ ማር ያግደዎት› አለ ደፍሮ፤

‹አሁን ባለ ቅኔን ማን ይናገረዋል፣

እንዳሻው ሊናገር ሥልጣን ተሰጥቶታል›

የሚለው ትዝ ሳይላቸው አይቀርም ለመምህሩ፤ ሊቅ ስለሆኑ ማጣረሳቸው ገባቸው ወደ ሙግት  ሳይሔዱ አመኑና ‹ቀጥል!›አሉ በዐይን ጥቅሻ፡፡

‹አምላክ ከማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ፤ ከደሟ ደም ውስዶ በማህፀኗ አደሮ ተፀንሷዋል ብለው ዐሥተመውረኛል?› አለ ባለቅኔው፤ ወደ መምህሩ እያመለከተ፡፡

‹አዎ! አምላክ በግርማ መለኮቱ እንዳለ የሰው ፍቅር አገብሮት ከማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆን ተፀንሷል፣ ዘጠኝ ወር ካምስት ቀን ሲሞላውም ኅቱም ድንግልናዋ እንደተጠበቀ ተወልዶ አድኖናል ብዬ ማስተማሬን አምኜ አገባ!› አሉ፤ ለሙግት እየተዘጋጁ፡፡

‹እሺ ካመኑልኝማ!› ብሎ ከላይ የጠቀስነውን የቅኔውን ውርድ ነዛዋ፡፡ ምሥጢሩ ሲገለፅ ይህንን ይመስላል፡-

‹ሰማይና መሬትን እሱ በጥበቡ ይዟቸው የሚኖሩ መሆናቸውን ካመኑ፤ ማሪያምም አምላክን በማኅፀኗ ወስናው ከነበረ እሷ የት ላይ ቆማ ያዘቸው? ማለት ሰማይና መሬትንስ ይሁን እሽ! እሱ ይዟቸው ነው አልን፤ በእሷ ማኅፀን በአደረ ጊዜ እነሱን ማን ወይም ምን ያዛቸው? እሷስ በምን ላይ ቆማ ወሰነችው? …› በማለት አፋጠጠ፡- ከላይ ባለው ቅኔው ነው፡- ታዲያ!

ሊቁም ‹በሰማንያ የተረታ፣ መኸል አናቱን የተመታ› ሆኖባቸው የቅኔውን ጥልቀት ለማስረዳት የቅዱስ ያሬድንና የአባ ኤፍሬምን ውዳሴ፣ የአባ ሕርያቆስን ቅዳሴ … ቢጠቅሱም ስላልበቃቸው ለባለቅኔ ልጃቸው መልሳቸው ‹ዕፁብ! ዕፁብ! ይበል! ይበል!› አሉ፡፡ አበው በቅኔ ቤት ‹ዕፁብ! ይበል!› ካሉ ምሥጢር ተፈልቅቆ ቦግ ብሏል (ድንቅ ፍልስፍና ይዟል) ማለት ነው፡፡ አዩልኝ የሊቃውንቱን የቅኔ ፍልሰፍና ሊቅነት! የዕይታቸውን ምጥቀት! ከመቅናት ውጭ ምን ማድረግ ይቻላል? ምንም!

የትርጓሜ መጻሕፍታቻውን ቃኘሁ፤ እያጋጩና እያነጻጸሩ ሲያብራሩና ትክክለኛውን አንድምታ አንጥረው ሲያወጡ ዐይቼም ‹እና ከዚህ በላይ ፍልስፍና ምን ዓይነት ነው?› ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፤ ለምንስ ትርጉም አስፈለገ አልኳቸው በጨዋነቴ ‹ፊደል ይገላል፤ ምሥጢር ግን ሕይወትን ይሠጣል› ብለው የተሸፈነውን ነፍስ የሆነውን መልዕክት ለመረዳት መተርጎም እንደሚኖርበት አስረዱኝ፡- አዬ! ‹የልጅ ነገር አሁን ይኸ ይጠየቃል› ብለው እኮ ነው!፡፡

እንዲሁም አባባሎቻቸውንና ምሳሌያዊና ፈሊጣያዊ ንግግሮቻቸውን፤ እለታዊ ጨዋታቸውን በማየት ድንቅ ለዛቸውንና ዐስተውሎታዊ ንግግራቸውን በዐጭሩ እነሱ ‹እንደ ወርቅ አንከብሎ እንደሸማ ጠቅልሎ› እንደሚሉት ሆኖ አገኘሁት፡፡ በዚህ ላይ ወሬ አምሮኝ በልጅነት ጠጋ ጠጋ ብላቸው እኮ ለልጅ በሚገባ መልኩ ‹ዕንቆቅልህ!› ማለታቸው አይቀርም! እኔማ ምን እመልሳለሁ ‹ምን ዐውቅልዎት!› ብዬ ራሴው መመለስ እንጂ!

ወይ ጉድ! ምሥጢር እየሣበኝ እኮ ብዙ ወሸከትኩ፡፡ በጥቅል ላውራ፤ አዎ በጥቅሉ በኢትዮጵያውያን ፍልስፍና መንፈሳዊነት የሌለው አስተያየት የለም፤ መንፈሳዊነቱም ያለ ሥጋዊ ግዙፍ ነገር አይገለጽም፡፡ ስለዚህ ኅብረ-ነገር (ኅብረ-ፍልሰፍና) የኢትዮጵያውያን ዕውቀት ድረ-ማግ ነው፡፡

4) ከዚህ ሌላ ስለ ደብተራዎች ድንቅ ግበር (አስማተ-መተት) አንሰቼ አላወራ ይቅር እንጂ እነሱን እኮ ጠላት አይደፍራቸውም! አልተወራላቸውም እንጂ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረችው  በእነሱ የመተት ጥበብ ጭምር ነው! … ካላመናችሁ ባለ ቅኔ ‹ገሞራው›ን ምስክር ልጥራ፡- የደብተራውን ግብር ያውቃልና እንዲህ አለ፡-

‹…በሩቅ አነጣጥሮ- በራዳር አስማቱ፣

ቶርቦዶ የሚያደርግ- ባንደርቢ ድግምቱ፣

ካድማስ የሚያወርድ- ሳተላይት ምትሃቱ፣

ድባቅ የሚመታ- ባዙቃ አንደበቱ፣

ድምጥማጥ አብንኖ- ጠላት አርጊ ከንቱ፣

ታላቅ ግብር(Role) ነበረው- ደብቴ ታጋይ ብርቱ፣…..›

(አቢሲኒያ መጽሔት ቅጽ 1፣ ቁጥር 16 ጥር 1993)

በሞቴ ስለ ደብተሮች አንድ ታሪክ ላውራ! የልጅ ወሬም ቢሆን ያዳምጡኝ፤ ወሎ ውስጥ ነው አሉ፡- ላስታ አካባቢ፡፡ አንድ መሪጌታ ናቸው፡- ድብትርናቸው ያልታወቀባቸው ሊቅ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን የቀለም ቀንድ ያደርጉታል፤ አጅሬው ከሳቸውም አልፎ መሪጌትነትን ይዞ እቤቱ ‹ከች!›፡፡ አንድ ቀን ታዲያ እናቱ ክሽን ያለች ዶሮ ወጥ ላባዋራዋ ትሠራለች፤ አባት ግን ከልጅ ጋር መሻማት አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ ልጃቸው ከቤት የሚወጣበትን ዘዴ ቀይሰው ዘመድ ጋር መልዕክት ይልኩታል፤ ይች ዘዴ የገባችው ልጅ ደግሞ በድግምቱ ድስቲቷን ቆልፏት ይሔዳል፤ ማን ወንድ ይክፈታት፡፡ አባት ተናደዱ ልጁም መልክቱን አድርሶ መጣ፤ የተናደዱት አባት ግን ልጃቸው ገና በሩ ላይ ሲገባ ዐሠሩት፡- መውጣት አይችል መግባት አይሆንለት የበር መዝጊያ መስሎ ቆመ፡- እንሞካከር ማት እኮ ነው በደብተራኛ፡፡

እሱስ ቢሆን ያስመሰከረ ሊቅ አይደለ? አባቱን ዐያቸው፤ ፊት ለፊቱ በአንድ እግራቸው መሬት እረግጠው በሌላው ደግሞ ካልጋው ጠርዝ ላይ አንፈራጠው ይመለከቱታል፡፡ ሊቁ ልጅም ጦርነቱን ዝም ብሎ አልተሸነፈም፤ አባቱን ከመሬትና ካልጋ ጋር ጠፈራቸው፡- መዘዋወር የለ! መንቀሳቀስ፡፡ አሁን ተግባቡ በል ልጄ ፍታ! ልፍታ! አሉ አባት፤ ተፈታተው አብረው በሏታ! ክሽንዋን የዶሮ ወጥ፡፡ ጎበዝ ለጎበዝ ከተገናኘ ይከባበራል፡፡ አዩልኝ ይህንን ጥበብ! የመስተፋቅር ጥበባቸውንማ ሁሉም የሚያውቀው ነው? ምን አወረዋለሁ!፡- ካስነኩ በቃ!

5) በሊቃውንቱ ዕውቀት መዋቅራዊ ጥበብ ተገረምኩ፡፡ ከፊደል ገበታ ጀምሮ እስከ ሰዋሰዋዊና አጠቃላይ የቋንቋ መዋቅር ስልታቸውን ሳይ መልሴ ምን ሆነ? ‹ዕፁብ! ዕፁብ! ውእቱ!›፡፡  የፊደል ገበታ እኮ የኢትዮጵያ ማንነት የተጻፈበት ካርታ ነው፡- የሚያነበው ቢገኝ:: ስለሆነም ነው ሊቁ አስረስ የኔሰው ‹“ፊደል ሐውልት ነው … ፊደል መልክ ነው … ፊደል አባት ነው … ፊደል ልጅ ነው … ፊደል ወሰን ነው … ፊደል ዓላማ ነው … ዓላማም የኩራት ምልክት ነው፡፡ ኩራትም ነፃነት ነው፡፡ … የማንኛው ነገር መጠቅለያ ፊደል ነው፡፡” ብለው የመሰከሩት፡፡ (አስረስ ኔሰው፤የካም መታሰቢያ የኢትዮጵያ ፊደል መሠረትነት መታወቂያ 1951 ዓ.ም)፡፡ አረ ለመሆኑ! የእኛን ፊደል የሚያስንቅና የሚቀድም የዓለም ፊደል (አልፋ ቤት) ይምጣና ይወዳደር እስቲ ብዬ ልፎክር እንዴ? ይኸው ፎከርኩ!

የሰዋሰው መዋቅሩም እኮ የተፈጥሮ ግልባጭ ነው፤ ምን ልበል!:- ሰማይና መሬት በዕውቀት የተገናኙበት መሰላል ማለት እንጂ፡፡  በአዕማዳት ቆሞ፣ በአለቃ ተደራጅቶ፣ በሠራዊት የሚጠበቅ፣ በመራሂያን የሚፍታታ፣ በዓቢይና በንዑስ አግባባት እየተዋሐደና እየተበተነ የሚታሠር አስደናቂ የዕውቀት ድርጅት ነው እኮ ሰዋሰዋችን! ስለዚህ የዕውቀት ድርጅት እኔማ ምን እላለሁ ሊቃውንቱ ቢያወሩት ይሻላል እንጂ! የእኔ ግብር ‹አባ በሌሉበት…› ዓይነት ነው፡፡

በአጠቃላይ ስለ ባህላቸው ልናገር እንደ? ስለ ትውፊታችን ልመስክር እንደ? ሰለ ገዳ ሥርዓት፣ ስለ ሥነ መንግሥት፣ ስለ ዘመን አቆጣጠራችን፣ … ስለተጠየቅ ልጠየቅ፣ ስለ በልሃ ልበለሃ ክርክር ላውራ እንዴ? ጊዜ አይበቃማ! ባላዋቂነት ይበላሻላ! አቅም የለማ!… በዐጭሩ የኢትዮጵያውያን የሚያስደንቅ ፍልስፍና ተመልክቼ ጥበበኛነታቸውን ማረጋገጥ ቻልኩ፡፡ ከዚያም እንዲህ አልኩ ‹እኔ የዚህን ያህል ዐይቼ ፍልስፍናቸው ከማረከኝ ዐስተዋይ የፍልስፍና ሊቅ ቢፈትሸውማ! ምን ሊል ነው?› ግን እስከዛሬ በአግባቡ ያልተፈተሸ ለምንድን ነው? መልሱን በአጋባቡ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በወፍ በረር የሞካከሩት እንዳሉ ግን መመልከቴን አልሸሸግም፡፡

ሐሣቤን ልቋጭና ልሰናበት፡፡ በእኔ አቅም የኢትዮጵያውያንን አስገራሚ አስተውሎቶች፣ የጥበብ ፍቅር፣ እውነት ለማግኘትና ለማረጋገጥ የሚሔዱበትን እርቀት ዐይቼ ተደንቄያለሁ፡፡ እኔ እንደተረዳሁት ኢትዮጵያውያን የሥልጣኔው ምንጭ ነበሩ፡፡ የሥልጣኔ ምንጭ ለመሆን የቻሉት ደግሞ የራሳቸው ዐተያይ፣ አስተምህሮና የዕውቀት ክምችት ስለነበራቸው ነው፡- ገና ጥንት፡፡ ሊኖራቸው ከሚችለው ዕውቀት ውስጥ ደግሞ ፍልስፍና ቅድሚያውን ይይዛል፡፡ ስለዚህ ‹ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ፍልስፍና ያዳበሩ ሕዝቦች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው ብዬ ደመደምኩ፡፡

ሆኖም ለተፈጠረብኝ ‹ለምን?› ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የእኛን ፍልስፍና ዓለም አቀፍ መዝገበ ቃላትና ዕውቀተ መዝገብ የማያውቀው ማሳወቅ ስላልቻልን ነው ወይስ የእኛ ፍልስፍና እንዳይታወቅ ተፈልጎ ማዕቀብ ተደርጎብን? እስቲ መልስ አምጡ፡፡ ለምንም እንደሆነ ጨምራችሁ፡፡

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply