ሕጸጽ (Fallacy)

ልብ አንለውም እንጂ ንግግሬቻችን፣ ውይይቶቻችን፣ ክርክሮቻችን እና እነዚህን የምናቀርብባቸው መንገዶች በስህተት የተሞሉ ናቸው፤ ይህንን ልማድ በማስተዋል ማረም ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ የሚያግዘው ተጠየቃዊ አስተሳሰብን ማጎልበትና የተዘበራረቁ አቀራረቦችን ማስተካል ነው። እኔም ለዚህ ያግዛል በማለት “መሠረታዊ ሎጂክና ሕጸጽ” ከሚለው መጽሐፌ ስለ ሕጸጽ የሚያትተውን ክፍል በተከታታይ ለማቅረብ አስቤያለሁ፤ የአገራችንን ፖለቲካና የሚድያ አጠቃቀም ለመገምገምና የራስ ሐሳብንም በአግባቡ ለማቅረብ ያግዛል ብዬ አምናለሁ፤ በተለይ ደግሞ መደበኛ ያልኾኑ ሕጸጻትን (Informal fallacies) ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው።  ለዛሬው ግን የሕጸጽን መሠረታዊ ምንነት ላቅርብ!

ሕጸጽ ምንድን ነው?

ሕጸጽ (Fallacy) የሚለው ቃል የተወሰደውም ከግዕዝ ቋንቋ ሲኾን ‹ሐጸጸ› ከሚለው ግሥ የወጣ ጥሬ-ዘር ነው፡፡ በአማርኛም ቀጥታ ተወስዶ ያገለግላል፡፡ የቀጥታ ነጠላ ትርጉሙም ጉድለት ወይም አለመሟላት ማለት ነው፡፡ ይህም የሚያስረዳው የተገለፀው ነገር አለመሟላቱን፣ ተስተካክሎ አለመገኘቱን፣ የተሳሳተ ነገር መከሰቱን፣ እውነታው አጥጋቢ ወይም አሳማኝ አለመኾኑን ወይም የመደበላለቅና የመምታታት ኹኔታ በመከሰቱ የተጠቀሰው ነገር እንከን ያለበት መኾኑን ነው፡፡

ሥነ-አመክንዮአዊ (Logic) ትርጉሙም ይህንነ መሠረታዊ ትርጉም ይይዛል፡፡ ሥነ አመክንዮ ደግሞ በቋንቋና በክርክር የተሠራ ጥበብ ነው፤ ክርክር የሐሳብ መነሻና መቋጫ ያለው የአስታሰብ ፍሰት ሲኾን እውነት ወይም ሐሰት መኾን በሚችሉ ዐርፍተ ነገራት ይሠራል፤ የዐረፍተ ነገሮቹን እውነት ሐሰት መኾንም በትክክለኛ የቋንቋ አጠቃቀምና የቃላት ፍች ይወሰናል፡፡ በዚህ ሂደትም ሕጸጽ በክርክር መዋቅር ወይም ይዘት ተጠየቃዊ ፍሰት (inference) ውስጥ ችግር መፈጠሩን ወይም ጉድለት መከሰቱን ይገልፃል፡፡ ይህ ከኾነም ክርክሩ ሕገ-ወጥ (Invalid) ወይም ድኩም (Weak) ለመኾን ይገደዳል፤ አንድ ክርክርም ሕገ ወጥ ወይም ድኩም ከኾነ ለሕጸጽ ይጋለጣል፡፡

ሕጸጽ ምንጩ ኢ-አመክንዮአዊ ክርክር (Ilogical argument) ነው፡፡ ኢ-አመክንዮአዊ ክርክርም በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተለይም በስሜታዊነት፣ በግል ዕይታ፣ በድንቁርና እና በመሳሰሉት ተፅዕኖዎች የተነሣ ይፈጠራል፡፡ ምክንያቱም ስሜታዊነት በውስጥ ፍላጎትና ምኞት ወይም ብስጭትና ጥላቻ ወይም ራስ ወዳድነት የተነሣ ምክንያታዊነትን ይሸፍናል፤ በነዚህ የስሜት ነፀብራቆች የተሸፈነና ነፃ ዕሳቤውን ያጣ ሰው ደግሞ አንድን ነገር (ክርክር) በአመክንዮአዊነት ለማየትና በስምም ዕይታ ለመግለፅ አይችልም፡፡ በግል ዕይታ የሚመራ (የሚመለከት) ሰውም የስሜታዊነት ጫና ያርፍበታል፤ ዕይታውም ከሌሎች ሰዎች ዕይታ ጋር ሊቃረን ይችላል፡፡ በመኾኑም ለኢ-አመክንዮአዊነት ይጋለጣል፡፡ ድንቁርናም ቢኾን የዕውቀት ፀር ነው፡፡ ድንቁርና የነገሠበት ሰውም የመረጃ ዕጥረት፣ የአቀራረብ ችግር፣ የተጠየቃዊነት ፍሰት ስልት ድህነት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህ በመኾኑም ለኢ-አመክንዮአዊነት ይጋለጣል፡፡ በነዚህ የተነሣም ሕጸጽ ይፈጠራል፡፡

ሕጸጽ ዐውቆ በሚፈጸም ወይም ሳያውቁ በሚገጥም የክርክር ስህተት ሊከሰት ይችላል፡፡ ማለትም አንድ ተከራካሪ እያወቀ በተለያየ ስልት ሕጸጽ እንዲፈጸም ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡-

  • ክርክሩን በማድበስበስና ትክክለኛ ማስረጃ ያቀረበ በማስመሰል፣
  • ክርክሩን ባልኾነ አቅጣጫ በመምራትና አጠማዞ ተጠቃሚውን ግራ በማጋባት (ለምሳሌ የቃላት ጨዋታ በመጠቀም)፣
  • ሐሰቱን ከእውነት ጋር አባልቆ በማቅረብና በማምታታት፣
  • የክርክሩን ተቃዋሚ ጥያቄ እንዲነሳበትና ግራ እንዲጋባ በማድረግ፣
  • ስሜታዊ የኾኑ ቃላትን ተጠቅሞ ሥነ ልቦናዊ ጫና በመፍጠር ወተ… ሊኾን ይችላል፡- ሕጸጽን የሚፈጸመው፡፡

በሌላ በኩል ግን ባለ ማወቅ የሚፈጠረው ሕጸጽ በተከራካሪው በራሱ ድክመት የተነሣ የሚፈጸም ስህተት ነው፡፡ ይህም ለምሳሌ ተከራካሪው፡-

  • የክርክሩን ይዘት (መዋቅር) እያወቀ የቋንቋ ዕውቀት እጥረት ወይም የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ሲያጋጥመው፣
  • የክርክሩን ማስረጃና ጭብጥ በውል በማቀናጀትና በመልክና በሥርዓት ማቅረብ ሲያቅተው፣
  • የክርክርን ሕግጋት፣ ሥርዓትና ስልት ሳያውቅ ሲከራከር ወዘተ… ሕጸጽ ለፈጽም ይችላል፡፡

ተከራካሪው ዐውቆ የሚፈጽማቸውም ይኹኑ ሳያውቅ የሚከሰቱት ሕጸጻት መፈጠሪያ ሥፍራ የክርክር ተጠየቃዊ ፍሰት ይገባኛል ጥያቄዎች (claims) ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጸጻት በክርክር መንደርደሪያዎች እና መደምደሚያ መገናኛ ላይ የሚሽከረከሩ የክርክር ባላንጣዎች ወይም ችግር ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ችግር የሚፈጥሩትም ሐሰትን በእውነት ውስጥ በመሸሸግ፣ መጥፎን ከጥሩ ጋር በማደባለቅ፣ የስህተትን መርዝ በትክክል ማር በማላስ ነው፡፡ ለዚህ ሕጸጽ (ሕጸጻት) የሚል ስም የተሠጣቸው፡ በየትኛውም መመዘኛ ጉድለት እንጂ ምሉዕነት የላቸውምና፡፡

የሕጸጻት ዓይነት

  የሕጸጻት ዓይነት በዋናነት በኹለት ሊከፈል ይችላል፡፡ እሱም መደበኛ (Formal) እነ ኢ-መደበኛ (Informal) ሕጸጻት ናቸው፡፡ መደበኛ ሕጸጻት በአጠይቆት ክርክር ብቻ የሚከሰቱና በመዋቅር ብቻ ጥገኛ የኾኑ ሕጸጻት ናቸው፤ የክርክር መዋቅርን በመጣስ ይታወቃሉ፤ማለትም የክርክሩ መንደርደሪያ መደምደሚያውን ለማገዝ በሚያደርገው የተጠየቃዊ ፍሰት ይገባኛል ጥያቄ የመዋቅሩ ሕግጋት ተጥሰው ስህተት ሲፈጸም ሕጸጻቱ ይፈጠራሉ፡፡ የመደበኛ ሕጸጻት የክርክር መንደርደሪያና መደምደሚያ እውነትነት ከመከሰት አያስጥላቸውም ወይም ሐሰትነት እንዲፈጸሙ አያደርጋቸውም፡፡ የክርክሩ መዋቅር ሕገ ወጥ መኾን ግን ሕጸጻቱ አእንዲፈጸሙ ያደርጋቸዋል፤ ስለዚህ የመደበኛ ሕጸጻት በክርክር ሕጋዊነት ይባረራሉ፤ በሕገ ወጥነት ግን ይነግሣሉ፡፡

የኢ-መደበኛ ሕጸጻት በዕለት ተዕለት የክርክር ጽሑፎች እና ንግግሮች ውስጥ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በተለይም ክርክርን ባልኾነ አቅጣጫ በመምራት ወይም አድበስብሰው በመደበቅና በማምታታት ብዙ ሰዎችን ያታልላሉ፡፡ ለይቶ በማያውቃቸው ሰውም የሕጸጽ ካባቸውን እንደለበሱ በእውነትና በትክክል መሳይነት እያሞኙ ጓደኛቸው የሚያደርጉ ሕጸጻት ናቸው፡፡ ስለኾነም ኢ-መደበኛ ሕጸጻት በዋቅር ተለይተው አይታወቁም፤ የመዋቅር አይገዛቸውምና፡፡

ኢ-መደበኛ ሕጸጻት ከመደበኛ ሕጸጻት ጋር ከተነጻጸሩ አስቸጋሪነታቸው ያመዝናል፡፡ የሚከሰቱትም በጥሩ ልብስ ተጀቡነው አርተፊሻል ወርቅ አጥልቀው ነው፤ የነገሡበት ክርክርም ‹ትክክል ነኝ› ብሎ የሚፎክርና የሚያቅራራ ሊኾን ይችላል፡፡ የክርክሩ ይዘት ተመርምሮ የተሸፈኑበት ልብስ ሲገለጥና ያጠለቁት ወርቅም አርቲፊሻልነቱ ሲታወቅ ግን በትክክለኛነት ያቅራራወውና የፎከረው ክርክር ተዋርዶ ቁጭ ይላል፡፡ መደበኛ ሕጸጻት ግን ከክርክር መዋቅር ጋር የተጣበቁና ሕግጋቱ ሲጣሱ የሚከሰቱ ናቸው፡፡

የኢ-መደበኛ ሕጸጻት መጥፎ ገጽታቸው ብዙ ነው፡፡ እንበልና አንድ ክርክር በአመክንዮአዊነት ሲታይ ትክክል አይደለም፤ ስህተት ነው፡፡ ኸኖም ሕጸጻቱ ትክክል በማስመሰል ታዳሚው እንዲቀበል በማድረግ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ‹ስህተት የኾነ ክርክርንማ ማን ይቀበላል?› የሚል ተሟጋች ይኖር ይኾናል፡፡ ነገሩ ሌላ ነው፤ ታዳሚው የሥነ-ልቦና ጫና እንዲፈጠርበት ይደረጋል፡፡ በዚህ ጫናም ተቃዋሚ የነበረው ታዳሚ ምናልባት የሕጸጻቱ ደቀ መዝሙር ሊኾን ይችላል፤ የክርክሩን ትክክለኛነት በመመስከር፡፡ ይህንን የሚፈጽሙትም ስሜት በሚኮረኮሩና በሚስቡ ቃላት ተጠቅመው ነው፡፡

ኢ-መደበኛ ሕጸጻት መጥፎ ተግባራቸው የሚፈጸምበት ስልትም አደገኛ ነው፡፡ እንበልና የክርክሩ አድማጭ ወይ አንባቢ የአደገኛ ስሜት ቀስቃሽ ቃላት ተግባራትን ነቅቶ በፊት ለፊት በር በተጠንቀቅ ይጠብቃል፤ እናጅሬው ሕጸጻት ታዲያ ምንም ሳያንኮሻኩሹ በጓሮ በር በኩል ሾልከው ወደ ቤት መግባት ይችላሉ፡፡ ለዚህም አንዱን ተከራካሪ ተብዬ ለመደምደሚያ የሚኾን ትክክለኛ ማስረጃ ሳይዝና አስፈላጊ የኾነውን ተጠየቃዊነት ሳይጠቀም ክርክሩን በሽንገላ ቃላት ጀቡኖ ታዳሚውን እንዲያደርቅ ይልኩታል፡፡ እሱም የክርክሩን ማስረጃና ጭብጥ እያማታ በማቅረብ የሕጸጻቱን በጓሮ በር በኩል መግባት ይሸሸጋል፡፡ በዚህም ታዲያ ታዳሚው የተከራካሪውን ኹኔታ እያየ ከእሱ ጋር ሲደርቅ ሳያውቀው ቤቱ የሕጸጻቱ መፈንጫ ይኾናል፡፡ በተለይ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚገረመው የታዳሚው መታለልና መሸወድ ብቻ አኤደለም፤ ተከራካሪው ተብየውም ተልዕኮውን መፈጸሙን እንጂ ሕጸጻቱ ቤት መግባታቸውን አያውቅ ይኾናል፡፡

የኢ-መደበኛ ሕጸጻት መፈጸሚያ ስልታቸው ስለሚቀያየር በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስቸግራል፡፡ እንበልና ታዳሚው ሕጸጻቱ በየትኛውም ስልት መጥተው ወደ ቤቱ እንዳይገቡ ነቅቶና ተጠንቅቆ እየጠበቀ ነው፤ ተታሎ የሚያታልለው ተከራካሪም እሱ ጋር ድርሽ እንዳይልብ አባሮታል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜም ቢኾን እናጅሬ ሕጸጻት አይተኙለትም፡፡ በቅርብ ሩቅ ኾነው ታዳሚው እንዲሰማቸው በማድረግ ‹እንዲህ አይደለም እንዴ? ለምንስ ይኸ ይኾናል?› በማለት የሚያቀርቡት የጥያቄ ክርክር በጆሮው መጥቶ ጥልቅ ይልበታል፡፡ በዚህም ታዳሚው ጥያቄ ተቀስቅሶበት ወይ ግራ ይጋባል ወይም የእነሱው ዘመድ ይኾናል፡፡ ከዚህ በላይ አደገኛ አለ?

ኢ-መደበኛ ሕጸጻት በቁጥራቸው ብዙ  ናቸው፡፡ ዓይነታቸውን ዘርዝሮ ለማወቅና ጠባያቸውን በትክክል መረዳትም ያስቸግራሉ፡፡ ኾኖም ግን ምሁራኑ በዓይነትና በመልክ ቁጥራቸውን በመዘርዘር ለማስቀመጥ ከመሞከር አልቦዘኑም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የሕጸጻቱን ዓይነት ሥርዓት ለማስያዝ በመሞከር የሚታወቀው አርስጣጣሊስ (አርስቶትል) ነው፡፡ የሥነ-አመክንዮ አባት የሚባለው አርስጣጣሊስ 13 የኢ-መደበኛ ሕጸጻቱን በመለየት በኹለት ክፍላት ከፋፍሎ ለማስቀመጥ ሞክሮ ነበር፡፡ ከእሱ በኋላ የተነሡ ፈላስፋዎችም ሕጸጻቱን በዓይነታቸው በመከፋፈል ብዛታቸውን ለማሳወቅ ብዙ ጥረዋል፡፡ እንዳውም በአሁኑ ጊዜ ወደ 120 ገደማ የሚደርሱ የኢ-መደበኛ ሕጸጻት ዓይነቶች ተለይተው እንደታወቁ ይነገራል፡፡ ቢንስ ግን በደንብ ተለይተው የታወቁትን ሕጸጻት ማወቅ እጅግ ጠቀሜታው የጎላ ስለሚኾን እነሱን እየዘረዘርን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ይቆየን! ያቆየን!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply