መቀነትሽን አጥብቂ

IMG0193A

(የኮተቤው የሻው ተሰማ)
የዕድሜሽን ተውሳክ-ተቀጥላ፣ በመሐፀንሽ ስትቋጥሪ፣
ያበሳሽን ቀነ ገደብ፣ ስትቀንሽ- ሰትደምሪ፣
በትኩስ-በበራዱ፣ ቃር ማቅለሽለሽ… ስትጀምሪ፣
ዶሮ መረቁ ቢያርብሽ፣ ወጡ በቅመም ባይጥም፣
‹ቅሪት ያምራታል› ተብሎልሽ፣ ለደንታሽ ደንታ ባይሰጥም፣
ፍሪዳ ባይጣልልሽ፣ ዕድል ባይጥፍሽ ለቅልጥም፤
አቅበጥብጦ ሲያስፋሽክሽ…፣ ሲያስመልስሽ የበላሽው፣
ቃሪያ ጎመኑ… ውል ሲልሽ ያኔ ነበር የጀመርሽው፡፡
ከባጥ በላይ ፅኑ ፍዳ፣ በልጅ ስቃይሽን መቁጠር፣
በኪነ ጥበቡ ትንግርት፣ ቅጥያሽ ሆኜ ስፈጠር፡፡
በመዓልት-ሌሊት ተራክቦ፣ ሲኳኳል የአዋርኅ ቀመር፣
ቀናትን ሣንምት ውጧቸው፣ ሣምታትን ዘጠኝ ወር፣
በወርኀ ማዕዶት ሽግሽግ፣ ለዓመት ሦሰት ወር ሲቀር፣
እንደ ልሳኑ ስያሜ፣ ‹ቅሪት› ነበርሽ ቀደም ሲል፣
ነፍስ ስዘራ ስጠራቀም፣ ከ‹ፅንሰነት› ተብዬ ‹ሽል›፣
ከደምሽ ደም እየሞላሁ፣ እድገቴን ባንቺው ሳሻሽል፣
በዚያ የሸክም ወራት፣ ሲያበራይሽ የልብ ጋር፣
ነፍስሽ ሕቅታን ስትቃዥ፣ ተሠርታ በሞት አውታር፣
ላይ ቅጽበት እፎይታ አጥተሸ፣ ሲያባዝትሽ ሰቀቀኑ፣
በብጽዓት እየማለድሽ፣ በምልጃ በጧፍ- በጣኑ፣
ነገ የሰማይ ያህል- እየመጠቀ ቀኑ፣
ቁም ስቅልሽን እያሳየሁ፣ ‹ነፍሰጡር› ሆነሽ ተጦሬ፣
ባፍንጫሽ እያስቃተትሁ፣ ልክ ዘጠኝ ወር ቆጥሬ፣
በመጣሁ-ቀረሁ ሕማማት፣ የቀናት ለጠፍ ደምሬ፣
የአራስ ቤት ወግ ላሳይሽ፣ ስበቃ ለምስልሽ ፍሬ፤
ደሜን ከደምሽ በመድፈቅ፣ አጥንቴን ካጥንትሽ አጋጥሜ፣
‹የምጥ ማርያምን› ሲማልድ፣ ምጥሽን ሲያምጥ አዳሜ፣
አስደግድጌው እንደ ጃን፣ ወንድ ሴቱን አስቁሜ፣
ኮኮቤ ሲቃናልኝ- ፍካሬው ሲያምር ሕልሜ፣
በሽርት ውሃ ብሥራት-መርዶ፣ ተሸጋገርኩ ለሌላ ዕድሜ፡፡
…..
የጣረ ሞት ምሥል ጉሙ፣ ሲገፈፍ ጥቁር ጨለማ፣
የአራስ ጥሪ ወጉ አይቀርም፣ ልብሽ ሐሴት ሲያሰማ፡፡
የደም ካሣ በልቶ ላይጠግ፣ አካል እም አካልሽ ደማ፣
ተቀጥላ ላበቀልሽ፣ ጥሪት ሀብትሽን የሚሻማ፣
አንባረቅሽ አሉ በዕልልታ፣ ገምገም ዙሮ እስኪሰማ፡፡

አንቺማ ምን ታደርጊው፣ የወረስሽው ነው ከእናትሽ፣
በጅማትሽ ድር ተደርቶ፣ የተማገ በሕይወትሽ፡፡
እንደ ተወጠርሽ ቃተሸ ተርገብግበሽ መሞትሽ፡፡
ግትሽን ብገጠግጠው፣ ወሸሽ ተመጦ እስኪደማ፣
ጆሮሽ መዝሙሬን እንጂ፣ ማንቋረሬን እንዳልሰማ፣
ፍዳን እንደበረከት መታረዝን እንደሸማ፣
ችጋርን እንደሲሳይ፣ ጥምን እንዳልተጠማ፣
አሜን ይሁን እንድትይው፣ ልብሽ እንዳያቅማማ፣
ታቻችይው ዘንድ ቸሮሻል፣ በረበበብሽ ግርማ፡፡
ደግሞ እኮ!…
ከጽንስ እስከ ሕርስ ቀን፣ መልክ ያጣው ስቃይሽ አንሶ፣
ከዳዴ እስከ ድክድክ፣ በደግሞ ባናት ተመልሶ፣
ከጉንፍሽ እስከ ጀርባሽ፣ አካሌ አካልሽን ዳሶ፤
ጽዱው ገላሽ ሲበሸቅጥ፣ በምናምኔ ርሶ፣
ሥቄ ስጫወት ፈክተሸ፣ ሳለቅስ ሆድሽ ተላውሶ፤
ስንፎለፎል ተፍነክንከሽ፣ ሲከፋኝ አንጀትሽ ጨሶ፣
አጸፋን መመለስ እንጂ፣ እንደ ቅጥንብሬ ጣጣ፣
ሆድሽ ከሁዳድ ሰፍቶ፣ ብሶት የማይቆጣ፣
የንባብ-ትርጓሜው ሰምና ወርቅ፣ ምሥጢሩ ጠፋኝ ጨርሶ፣
የማልሽው ኪዳን ምንድነው፣ በ´ናትነትሽ ደርሶ?

ይመጡንሻል ቃላቱ፣ ብልሽ ‹እምዬ እናቴ›
የመልኬ ምሥል መቅረጫ፣ ራሴን ማያ መስተዋቴ?
ሳትበይው ከምትከፍይው፣ ከዘጠኝ ወር ሸክም ዕዳሽ፣
ከጭንቅ አጥቢያ እስከ ማግስት፣ ከምጥ ዋይታ ምሬት ፍዳሽ፡፡
ሥጋሽ አልቆ-ጥላሽ ቀርቶ፣
ደስታዬ እያረካ፣ ትኩሳቴ ሲጎዳሽ፣
ገላሽን ችፌ በጣጥሶት፣ እከክ አንፍሮት ቆዳሽ፣
ፊትሽ መጋፊያ መስሎ፣ አንድ ቀን እንኳን ሳይጸዳሽ፡፡
ሌሊት ቁንጫ ግጦሽ፣ መዓልት በቅማል ተልተሸ፣
በጥም አጎዶ ከስለሽ፣ በጠኔ ጣር ተላግተሸ፡፡
የእርሜን እንጥፍጣፊ፣ ለኔ ወተትሽን ግተሸ፡፡
ራስሽን ለኔ መግበሽ፣ አንቺን አሮብሽ ጎመን፣
የዘጠኝ ወር ሸክም ፍዳው፣ ሳይበቃሽ የምጡ ጣመን፣
የሐሩር ንዳድ አንፍሮሽ፣ ጽልመት አውሮሽ ዳፈን፡፡
ደቂቁ ሊቅ ተብዬ፣ ትሩፋትሽ ሰው እንድሆን፣
የዋተትሽበት ምሥጢር፣ መስታወቴ ምን ይሆን?

አይ አንቺ እምዬ እናቴ፣
አንድ ሆነሽ ምዕልፍቴ!
ሥገጠግጠው ሥጋሽን፣ እስኪነጥፍ የወረርሽ ጠል፣
በጀርባሽ አሞላቀሽ (አሟቅለሽ) ስትውይ፣ ትከሻሽ እሲከገነጠል፡፡
ጭኖችሽን ዱካ አድርጌ፣ በደረትሽ ስንጠላጠል፣
አንቺ በለፋሽበት፣ እኔ ደልቶኝ ስቀማጠል፡፡
ለግብርሽ የሚመጥን መስታወቴን ማ` ልበል?

ለዚህ ወለታሽ አጸፋ እናት ይልሻል አገሩ፣
እኔም እናቴ ብልሽ፣ መች ሊመጥንሽ ዳሩ፡፡
ለማንም ባልቴት እንስት፣ ከተቸረ እንደዋዛ፣
ኅብረ ቀለሙን አወይቦ ካደረገብኝ ደብዛዛ፣
አሕዛብም ብሆን-አዋማ፣ ሰልሳላ ማተቤን በጥሼ፣
እንደ ናቡከደነፆር፣ ሣር ብበላ አጎንብሼ፤
‹እናት› ብዬ አልጠራሽም ከሌሎች ጋር ደምስሼ፡፡
አንችነትሽ ምጥቅ ነው፣ እናት ከመባል ይልቃል፣
የግብርሽ ስንክሳር-ዚቁ፣ በስያሜ መች ያልቃል፡፡

ግን ታዲያ መስታወቴ፣…
ምናብሽን ፍቅር ቸፍችፎበት፣ ንቁ አእምሮሽ ዶለዶመ፣
ነገን መተንበይ ተስኖት… ግምት በውስጥሽ ጨለመ፡፡
ያበው ተረት አልሰማሽም፣ የያቀበሉን ሊቀባበሉ፣
የዛሬ ልጆች ሠልጥነው፣ ‹ምሳሌ› ይሉታል አሉ፡፡
ስለናትና ልጅ ፍቅር፣ አብጠልጥለው ሲተርቱ፣
ለኔ አስመስለው ፈርደው፣ አንቺን ለይስሙላ ´ረቱ፡፡
የናትና ልጅ ፍቅር፣ እንደ ጀማ ውሃ ሁሉ፣
ከታች ወደ ላይ አይፈስም፣ ከላይ ወደ ታች እንጂ አሉ፡፡
ሲያጎርፍም ሆነ ሲጎድል፣ ከላይ አያቋርጥም፣
ከታች ያለው ግን ተቀብሎ፣ ያጸፋ መልስ አይሰጥም፡፡
ሲያፈስ ይኖራል እስከ ሕልፊት፣ የላይ ከበላይ ተቀብሎ፣
የላይኛው ሞልቶት ተርፎት፣ የታች አያውቀም ጎሎ፡፡
ያለ የሌለው አሟጦ፣ የላይ ለበታች ይሰጣል፣
የታችኛው ጉግማንጉግ ግን፣ ተቀብሎ ያሰምጣል፡፡
ከላይ ነውና አድራሻሽ፣ አንቺም እንደ ጀማ ውሃ፣
የቤዛነትሽ ወሮታ፣ የተለገሰሽ አምኃ፣
ጠፍቶሽ ከሆነ ምሥጢሩ፣ ነገ ቢመለስ ብለሽ፣
ጉድ ተቀብጥረሻል እሙ፣ የማን ያለህ ትያለሽ!?

ያኔ ሳነሆልልሽ፣…
በኮልታፋው ልሳኔ፣ በጥዑም አንደበቴ፣
ልቦናዬ ቂም ሳይደቅል፣
በፍቅርሽ ፍቅር ላበቅል፣
ጠርቼ አልጠግብም ነበር፣ ስምሽን መስታወቴ፡፡
ሲያልፍ ተረት ይመስላል፣
አንቺን ብቻ እንደምወድ፣ እንደምጦር ስገዘት፣
ቃሌ ስለታም ነበር፣ ያላጠቆረው ዝገት፡፡
ትንቢትን በጨቅላ ምናብ፣ በኩሸት-ግነት ከስቼ፣
እንደመድረክ መነባንብ፣ ስተርክ አስፋፍቼ፤
ሆድሽ ብሽ እንዳይለው፣ እህል-ውሃውን አስማምቼ፣
ምች እንዳይጋረፍሽ፣ የድባብ ምጽላል ገዝቼ፤
ቆፈን እንዳይጎዳብኝ፣ ፀሐይ በሰፌድ አግብቼ፤
‹እጦርሻለሁ› እል ነበር፣ የቅዱሳን ስም ጠርቼ፡፡

መስከረም በቀልድ አይጠባም፣
ከፈጩበት የጋፉበት፣ የመሰልሽበት ተስፋ፣
ከምድር ላቆየሽው ብድር፣ አቁረሽ ከሆነ አጸፋ፣
የደቀንሽውን ቋት አብሽው፣ዱቄት ሳይሞላ ተደፋ፤
እንደማምንሽ ባላመንሽኝ- ምነው ድራሼ በጠፋ፡፡
የፍቀርሽ ማጠንት ያጠነው፣ የልቤ ፀዓዳው ቀፎ፣
ያዳም-ሄዋን ግብር ሆነና፣ ያለቦታው ተሸክፎ፣
በአካል ዘ`ማካሉ ላይ፣ የናርዶስ ሽቶ አርከፍክፎ፣
እማኝ-ውል ሰሚ… ጠርቶ፣ የገባልሽን ቃል ገድፎ፤
ለባዕድ ጽጌ ሆኗል፣ ከሄዋን ሥር ተወትፎ፡፡
ሰው አፈር ነው ታጥቦ አይጠራም፣ ከክፋት ድቤ ተደባልቆ፣
ከትስብእት ባህርዬ ይልቅ የአውሬነቴ ባሕርይ ልቆ፤
እጅሽ ሲያጥር ዐይቼ፣ ውስጤ በንዋይ ቀልጦ፣
እንደ ሸንኮራ መጥጬ፣ ተንገፈገፍኩሽ እንደ ፌጦ፡፡
እናም እምዬ እናቴ፣
አንድ ሆነሽ ምዕልፊቴ፡፡
ያነጣጠርሽው ስቶ፣ ያቀባበልሽው ከሽፎ፣
ራዕይሽ ቅዠት ሆኖ፣ ከሚቀር ጥላሽን ገፎ፣
በሸንጎ ዐውድ ከሚጥለኝ፣ ልብሽ ፀፀት አትርፎ፣
አምሳለ እንጎቻ ከንፈርሽ፣ ከሚስም እኔን አቅፎ፣
ሲሳይ ወመድኅን ጡትሽ፣ ትን ባለኝ ተወትፎ፡፡
ወይ በጨነገፍኩልሽ፣ ውሃዬ በቀረ ሰፍፎ፡፡
ለሰሚው ግራ ነገር፣
ወይ አይበላ ጥሞ፣ ወይ አይደፋ አጸይፎ፤
ግራ አጋብቼሽ ከምቀር፣ እጅ- እጅ እንዳለ ገንፎ፣
ወስላታው ልቤ በነደለ፣ በማንጉርጥ ተቦትርፎ፡፡
አንቺም ምርኩዝሽን ባመንሽ፣ ይራዳሽ ነበር ደግፎ፡፡
ለነገሩማ እምዬ አንቺው ባንቺው ስትፈርጂ፣
የቁም-ስቅልሽን ያየሽው፣ መቼም ፈርዶብሽ እንጂ፣
እኔ በዕድሜ ድርብ ሳሻቅብ፣ አንቺ ቁልቁል ስትወርጂ፤
ባራት እግርሽ ስትቆሚ፣ በሦስት እግርሽ ስትሔጂ፣
ለጉሮሮሽ ደጅ ሰጠኝ፣ ለ`ህል-ውሃ ስትማልጂ፤
የዶሮ ሙቀት ሲያተኩሽስ፣ በነፋስ ሽውታ ስትበርጂ፤
የቅድሙን አሁን ረስተሸ፣ ወግ ደርሶሽ ስትጃጂ፤
ዕድሜ ግዳይ ሲጥልሽ፣ እንድጦርሽ ነው ስታረጂ?!
ድንገት እንድህ የሆንሽው፣
ንቁ አእምሮሽ ሲነሆልል፣ ንስር ዐይኖችሽ ሲጨልሙ፣
ከራራው ጅማትሽ ሲረግብ፣ እጅ `ግሮችሽ ሲካክሙ፣
እንዳቀፍሽኝ አስተኝቼ፣ እንዳጠባሽን መግቤ፣
ጦሬ እንድቀብርሽ ይሆን፣ እንዲራራልሽ ልቤ

እምዬ…
ጠግቦ ባደረም ይሁን፣ ወይ ተርቦ በዋለ፣
አልጋ በተለወጠ፣ ወይ ዘመን ባጋደለ፣
ተበልጦ.. ልጁን ዘንግቶ፣ ሆድሽ ለሆዱ እንዳላለ፣
ልብሽ እንዳልሾከተ፣ ግብርሽ እንዳልታጎለ፣
ትልቅ-ትንሹ ዋቢሽ ነው፣ ከኔ ነው የጎደለ፡፡
ዶሮና ጫጩቷ ልብ ይሏል፣
ጩ -ጩ- ጩ- ጩ- ጩ- ጩ- እያሉ፣
በክንፏ ተከልለው፣ ያፏን ነጥቀው እንዳልበሉ፣
ራሳቸውን ባካል፣ ብልጥ ሲሉ
በየፊናቸው ኮብልለው፣ ትተዋት ኮበለሉ፡፡
ወላድ ይፍረደነኝ ብለሽ ባይዋጥልሽም ቅሉ፣
ባንቺ ልቀት፣ በኔ ድቀት፣ ፍች አያገኝም ቃሉ፤
ለኔ በዝቶ ላንቺ ያንሳል፣ እናትና ልጅ መባሉ፡፡

እንግዲህ መስታወቴ፣
ምኞትሽ አልቦ ሆኖ፣ የመሐን ዕድል ካስቸረ፣
እንደ ሸኮኮ ጸሎት፣ ፍጻሜው ካላማረ፣
ሆድሽን ሆድ አስብሽው፣ ልጄን ብለሽ አትነፍርቂ፣
ውላጅሽ ገደል ይግባ፣ መቀነትሽን አጥብቂ፡፡
(የሻው ተሰማ፣ የጥቁር አፈር ትሩፋ፣ ገጽ 79-87)

Please follow and like us:
error

Leave a Reply