መኑ ውእቱ ፍልሱፍ- ፈላስፋ ማን ነው?

(በካሣሁን ዓለሙ)

ፍልስፍናን እማራለሁ› ብዬ ት/ቤት ብገባ፣ መምህሩ ‹ፍልስፍና ምንድን ነው?› ብሎ መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፤ ‹ካወቅኩትማ ለምንስ ልማረው ብዬ ሒሳብ ከፈልኩ?› አልኩኝ፤

‹ታዲያ ፍልስፍናን በገንዘብ ልተገዛ ነው የመጣኸው?› ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡

‹አይ! በመማር ለማወቅ ነው የመጣሁት› አልኩት፡፡

በዚህ መሃል ግን በክፍል ውስጥ አብረን ከነበርነው ተማሪዎች መካከል አንዱ ቀለብላባ ተማሪ ‹ፈላስፋ የሚባለው ራሱ ማን ነው?› የሚል ጥያቄ አንሥቶ ገላገለኝ፡፡

መምህሩም ‹ፈላስፋ ምን እንደኾነ ንገረኝና የፍልስፍናን ምንነት አስረዳሃለሁ፤ ይባላል› አለን፡፡ ወይ ጣጣ ማብዛት! ‹ከየትኛው ነው የሚጀመር? ፍልስፍናን ከሚያወቀው ሰው ወይስ ከፍልስፍና ምንነት? ማንም ይፈላሰፈው ፍልስፍናን ካወቅነው አይበቃንም? ደግሞስ ‹የፈላስፋን ምንነት ንገረኝ› ማለት ማንነቱን ከማወቅ ያነሰ፣ አሳቢውን ሰው ወደ ቁስነት የቀየረ አነጋገር አይኾንም?› የሚል ሐሳብ መጣብኝ፡፡ አላስችል ስላለኝም ‹የፈላስፋው ማንነት እንደ ቁስ ተቆጥሮ ለምን በምንነት ይገለጻል?› አልኩት!

እሱም ጥያቄውን ወደ እኔ በማዞር ‹ሐሳቢ ሰው ምንነት የለውም ልትል ነው?› ብሎ አፋጠጠኝ፡፡

‹አይ! በቁስነቱ እየተከራከርን ጊዜ ከምናባክን በማንነቱ ተወያይተን የፍልስፍናን ምንነት ብንረዳ ይሻላል ብዬ ነው› አልኩት፡- ነገር ለማብረድ፡፡

አስተማሪው ግን በማስጠንቀቅ መልክ የዘመኑን አባባል ተጠቅሞ ‹ሲጀምር ጊዜ ከሌለህ ፍልስፍና ጋር አትድረስ፤ ሲቀጥል በፍልስፍና ትምህርት የማትስማማበትም ነገር ቢኾን ይነሳል፤ ሲቀጣጠል የፈላስፋውን ምንነት ሳታወቅ እንዴት ከማንነቱ ላይ ደረስክ? ምንነት የለውም ልትል ነው ወይስ በምንነቱ ላይ ጥያቄ አይነሳም፤ ታውቆ አልቋል ለማለት ፈልገህ ነው? ሲጧጧፍ በምንነትና በማንነት መካከል ያለው ልዩነት ገብቶሃል? ከገባህ አስረዳን፤ ካልገባህ ለማወቅ ጠይቅ እንጂ ሳታውቅ ለጥያቄው ያልተመለሰ መደምደሚያ አትስጥ!› እያለ ወረደብኝ፡፡

በመሃል ግን ቀድሞ ጥያቄ ያነሣው ልጅ በመሃላችን ገብቶ ገላገለኝ፤ ‹እኔ ጥያቄውን ያነሣሁት ፈላስፋ ልንለው የምንችለው ሰው ከሌሎች ሰዎች መካከል ምን ዓይነት ዕውቀት፣ አኗኗር እና ስብዕና ያለው ነው?› ለማለት እንጂ ስለምንነቱም አንስተን እንድንከራከር አልነበረም፤ ምክንያቱም ‹ስለ ፋላስፋ ምንነት› የምናነሣ ከኾነ ስለ ሰው ልጅ ምንነት ቀድመን ማንሳት ይገባናል እንጂ ክርክራችን ‹ፈላስፋ!› ስለምንለው ሐሳቢ የማንነት መለያ ብቻ አይኾንም፤ ምክንያቱም ክርክራችን በምንነት ዙሪያ ከኾነ የምንጋገረው ስለፍልስፍና ምንነት ሳይኾን ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ ሊኾን ነው፤ ይህም ከሐሳባችን ክበብ ውጭ ያለ ክርክር ያደርግብናል› አለናም፤ ‹ፈላስፋ የምንለው ፍልስፍናን ያወቀውን ነው ወይስ ለማወቅ የሚጥረውን ሰው?› የሚል ለመምረጥ የሚያስቸግር መንታ ጥያቄ አስከተለ፡፡

ጥያቄዋ ለመምህራችንም ግር ያሰኘችው ወይም የተመቸችው ትመስላለች፤ ‹እስቲ መጨረሻ ላይ ያነሣኸውን ጥያቄ በግልጽ አብራራው› ብሎ መልሶ ዕድሉን ሰጠው፡፡

ቀጠለ ተማሪው ‹ፈላስፋ የምንለው ፍልስፍናን የሚያውቅ ከኾነ የፍልስፍና ምንነት በፈላስፎች ታውቋል፤ የማይታወቀው መፈላሰፍ በማይችሉት ወይም ባልተፈላሰፉ ሰዎች ነው ማለት ይኾናል፤ ይህ ደግሞ ‹ፍልስፍና ጥበብን ማፍቀር ወይም መሻት ነው› ከሚለው ትርጉም ጋር አይስማማም፤ ፈላስፋ ከተባለ በኋላ ምን ዓይነት ጥበብን ለማወቅ ይፈልጋል? አይ! ፈላስፋ የሚባለው ፍልስፍናን ለማወቅ የሚጥርና የሚተጋ ነው ከተባለ ደግሞ የፍልስፍና ምንነት ገና አልታወቀም ማለት ይኾናል፤ ይህ ከኾነም ‹ፍልስፍና ማለት እንደዚህ ነው› በማለት መተርጎም አንችልም፤ ገና ምንነቱ በሐሳቢዎቹ መች ታወቀና!›፡፡

መምህሩ ተማሪውን ትኩር ብሎ እየተመለከተው ‹ፈላስፋ ማለት አንተ ነህ!› አለዋ!

ተማሪውም ጥያቄውን አስከተለ ‹በየትኛው አፈራረጅ!›

‹በጥያቄህ!›

‹ፈላስፋ ማለት ጠያቂ ማለት ነው?›

‹በትክክል! ግን አንተ እንዳነሣኸው ጥያቄዎቹ መሠረታዊና አመክንዮአዊ መኾን አለባቸው› ሲለው ተማሪው የዋዛ አልነበረምና!

‹የዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጥያቄን መጠየቅ የሚያበዛ ሕፃን ልጅ ነው፤ ስለዚህ ‹ፈላስፋ ስትል እንደሕፃን የኾነ› ማለት ይመስልብሃል› አለው፤ ‹እንደ ሕፃን ካልኾናችሁ መንግሥተ ሰማያትን አትወርሱም› ሚለውን የወንጌል ሐሳብ ጎትቶ ‹እንደ ሕጻን ዓይነት ጥያቄ ካልጠየቃችሁ ፈላስፋ ልትባሉ አትችሉም› ወደሚል የፍልስፍና ጥያቄ ያመጣው ይመስላል፡፡

መምህሩም ‹የሕፃናት ጥያቄ ተራ ነገሮችን ለማወቅ የሚያነሱትና እንዳመጣላቸው የሚጠይቁት አመክንዮዊ ተጠየቅን የማይጠብቅ ነው› አለው፡፡

‹አልስማማም ሕፃናት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተራ ይመስላሉ እንጂ በጣም ጥልቅ ናቸው፤ ለዚህም የራሴን ልጅ እንደምሳሌ ማንሳት እችላለሁ፡፡› በማለት ቀጠለ፡፡

‹አንድ የሦሰት ዓመት ልጅ አለኝ፤ ቤት ስገባ ጀምሮ በጥያቄ ያፋጥጠኛል፤ ለምሳሌ ትላንትና ማታ የእንግሊዘኛ ፊልም እየተለመከትን ‹ምንድን ነው የሚለው?› አለኝ፡፡

እኔም ‹እንግሊዘኛ ነው የተናገረው› አልኩት፡፡

‹እንግሊዘኛ ምንድን ነው?›

‹ቋንቋ!›

‹ቋንቋ ምንድነው?›

‹ሰዎች አንዱ ከሌላው ጋር በመነጋገር የሚግባቡበት›

‹ተግባብተውስ?›

‹ይጠቀማሏ!› ጥያቄው ማቆሚያ ስለመይኖረው፤ ‹በቃ! ጥያቄ አታብዛ!› አልኩት

‹እሽ!› አለና ቀጠለ፤ ‹እኛ የምናወራው ምንድን ነው?›

‹አማርኛ!›

‹አማርኛ ምንድን ነው?›

‹ቋንቋ!›

‹እንቢ! እንግሊዘኛ ቋንቋ ነው ብለኸኝ አልነበር?›

‹አዎ! ብየኸለሁ፤ ኹለቱም እንግሊዘኛም፣ አማርኛም ቋንቋ ናቸው፡፡›

‹ቋንቋ ማለት እንግሊዘኛና አማርኛ ማለት ነው?›

‹አዎ! ግን ሌሎችም ቋንቋዎች አሉ፡፡›

‹ሌላ ምን?›

‹ብዙ ናቸው፡፡›

‹በቃ! ቋንቋ ማለት ብዙ!! ማለት ነው፡፡›

‹አይ! ቋንቋ ማለት መግባቢያ ነው፤ ግን ብዙ ዓይነት አለው፡፡›

‹ለምን እውነተኛውን አትነግረኝም? መጀመሪያ እንግሊዘኛ ቋንቋ ነው አልከኝ፤ ከዚያም አማርኛም ቋንቋ ነው አልከኝ፤ ከዚያም ቋንቋ ብዙ ነው አልከኝ፤ ከዚያም መግባቢያ ነው አልከኝ፤ ለምን ታታልለኛለህ? እንቢ በቃ እውነቱን ንገረኝ፡፡›

‹አላታለልኩህም! ደግሞ ጥያቄ አታብዛ ብየሃለሁ› ብዬ ተቆጣሁት

‹አትዋሸኛ!› ብሎ ተነጫነጨና እንደገና ‹አሁን ግን ጥያቄ ቀንሻላሁ አይደል?› ብሎ ሌላ ጥያቄ ቀጠለ››

ይህን ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላም ‹አሁን ይህ ጥያቄ መሠረታዊ የማይኾነው በምኑ ነው? ተጠየቃዊስ አይደለም? ለምሳሌ ለመጀመሪያው ጥያቄ የእኔ መልስ የተሳሳተ ነበረ እንጂ እሱ የጠየቀው በፊልሙ ውስጥ የሰማው ምን ማለት እንደኾነ እንድነግረው ነበር፤ ስለ ቋንቋም አትዋሸኝ ብሎ የተነጫነጨውም ‹አታጣርስ› ማለቱ ነው› ብሎ ተከራከረ፤ ክርክሩን ሲያዩት ከሕፃን ልጁ ጥያቄ መጠየቅን የተማረና የለመደበት ይመስላል፡- ጉድ እኮ ነው! ፈላስፋን ከሕፃን ልጅ ጋር ከማመሳሰል የበለጠ ምን ጉድ ሊመጣ ይችላል?

መምህሩ ግን ‹አልፎ አልፎ ያጋጥማል፤ የዚህ ዓይነት የመጠየቅ ችሎታ ያላቸው ልጆች አሉ› በማለት ክርክሩን መዝጋት የፈለገ መሰለ፡፡

እኔም አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ትዝ አለኝና ከቀረበው ክርክር ጋር በማገናኘት ፈገግ አልኩኝ፡፡ ወሬውን ያጫወተኝ ጓደኛዬ ጓደኛው የሕግ ሰው ነው! አነጋገሩ ኹሉ ‹ይኸ ከኾነ ይኸ› ዓይነት ተጠየቃዊነትን የተከተለ ነው፤ እናም ይህ ጓደኛው አንድ የአምስት ዓመት ልጅ አለው፤ እናቱ ልታስጠናው ስትሞክር አይግባቡም፤ እንደ አባቱ ‹ይኸ ከኾነ ይኸ› ዓይነት ጥያቄውን እያሽጎደጎደ ያስጨንቃታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀን ሕይወት ያላቸውና ሕይወት የሌላቸው ነገሮችን ልታስረዳው ስትሞክር፤ ‹ሕይወት ያላቸው ነገሮች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይራባሉ፣ አንዳንዶቹም ይንቀሳቀሳሉ፤ ከዚያም ይሞታሉ፤ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች ግን አይዋለዱም፣ አያድጉም፤ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ አይሞቱም…› እያለች ለማብራራት ትሞክራለች፡፡

‹እሽ! እንደዚያ ከኾነ መኪና ሕይወት አለው ማለት ነው?› ብሎ ጠየቃት፡፡

‹የለውም!› ስትለው ከልጁ ጋር ተጣሉ ‹ሕይወት ያላቸው ነገሮች ይንቀሳቀሳሉ ብለሽኛል፤ መኪና ደግሞ ይንቀሳቀሳል› አላት፤ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ ከዚያም እናቱ ‹ኹለተኛ አሳይኝ እንዳትለኝ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ያበላሸህ እሱው ስለኾነ ራሱ ይወጣው› አለችው፡፡

‹ታዲያ ሳታውቂ ለምን ልታስረጂኝ ትፈልጊያለሽ? ኤክስ ልታስገቢብኝ ነው!› ብሎ ልጁም ተቆጣ ብሎ አጫውቶኛል፡፡

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የኾነ ታሪክ የአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራች የዙምራን የልጅነት ታሪክም እናገኛለን፡፡ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ‹ፍልስፍና ፪› በሚል መጽሐፉ ዙምራን ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ የዙምራን የልጅነት የጠያቂነት ተፈጥሮ ይመሰክራል፤ ገና በኹለት ዓመት ዕድሜው ስለ እግዚአብሔር እና የሰው ልጆች አፈጣጠር እናቱን በማፋጠጥ የጠየቃቸው ጥያቄዎች ብዙ ፈላስፎች ሲጠይቋቸው ኖረው መልስ ያላገኙላቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ ይህ ከኾነም ዙምራ ገና በሕፃንነቱ ፈላስፋ ነበር ማለት ነው፡፡ ከኾነም ‹ፈላስፋነት ከሕፃንነት የሚጀምር ነው› ያስብላልና የተማሪው መከራከሪያ ያስኬዳል፡፡

መምህሩ ግን የፈላስፋን ማንነት ከጠያቂነት ወደ ሌላ ትርጉም ቀይሮ ለማብራራት ሞከረ፡፡ ‹ፈላስፋ ለመኾን ወሳኙ ነገር ጥያቄ መጠየቅ ብቻ ሳይኾን የጊዜ መኖርም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ጊዜ የሌለው ሰው ተረጋግቶ ለማሰብ አይችልም፤ በእርጋታ ኾኖ ያላሰላሰለ ደግሞ የጥበብ ፍቅር ሊገባውና ሊመረምራት አይችልም፡፡ በዓለማችን የምታውቋቸው አብዛኞቹ ፈላስፎች የማሰቢያ ጊዜ የነበራቸው ናቸው› አለን፡፡

አሁንም ያ የቅድሙ ተማሪ በጥያቄ አፋጠጠው ‹ይህ ከኾነማ ፈላስፋ ማለት ሥራ ፈት ማለት ሊኾን ነው?› ሲለው፤

‹ልትለው ትችላለህ! ግን ማሰብ ሥራ አይደለም እንዴ?› አለው መምህሩ፡፡

‹ወደ ተግባር ያልተቀየረ ሐሳብ ምን ጥቅም ሊያስገኝ?›

‹ማሰብ አንድ ነገር ነው፤ ወደ ተግባር ቀይሮ መጠቀም ደግሞ ሌላው ነገር ይኾናል፤ መጀመሪያውኑ ተረጋግቶ በጥልቀት ካላሰበ ግን ስህተት ሊሠራ ይችላል፤ ስለዚህ ነው ፈላስፋ ማለት ጊዜ ኖሮት ባለው ጊዜ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚያሰላስል፣ ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ለማወቅ የሚጥር የሚኾነው› አለና ለመጠቅለል ሞከረ፡- መምህሩ፤ ግን አልቻለም፡፡

‹ስለዚህ ፈላስፋ ማለት ባለ ትርፍ ጊዜ ሰው ማለት ነው?› በማለት ክርክሩን  ለማስቀጠል ቋመጠ ተማሪው!

‹አዎ! ምን? ለምን? እንዴት?… የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ አስተሳሰቡን የሚያበጥረው ጊዜ ኖሮት ሲያስብ ነው›

‹ጊዜ ሊኖረው የሚችለው ደግሞ ሀብታም ከኾነ ወይም በሌሎች ትካሻ ላይ በዕርዳታ የሚኖር ከኾነ ብቻ ነው፤ ያለበለዚያ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ሲል በሥራ መወጠሩ ግድ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ችግር ብልሃትን ይፈጥራል እንጂ ትርፍ ጊዜ አስተውሎትን የሚጨምር አይመስለኝም› አለ ተማሪው፡፡

‹ያልከው ሐሳብ በተወሰነ ደረጃ ልክ ነው፤ ግን መረዳት ያለብህ በምንም ምክንያት ወይም መንገድ ይኹን ለመፈላሰፍ ተረጋግቶ ማሰብ ያስፈልጋል፤ ተረጋግቶ ለማሰብና ለመከራከር ደግሞ ጊዜ ማግኘት ግድ ነው፤ አንድ ሰው ፈላስፋ ለመኾን ጊዜ ሊኖረው ግድ ቢኾንም ጊዜ የተረፈው ሰው ኹሉ ግን ፈላስፋ መኾን ይችላል ማለት አይደለም፡፡›

‹ይህ ማለት እኮ ፈላስፋ ሥራ ፈቶ በሐሳብ ሲናውዝ የሚኖር ሰው ማለት ሊኾን ነው፤ በሐሳብ ብቻ ሥራ ፈቶ የሚኖር ከኾነ ደግሞ ፍልስፍናም የሥራ ፈቶች ጊዜ ማሳለፊያ ወይም የሰነፎች ምክንያት ሊኾን ነው፤ ይህንን ዓይነት የሥንፍና ተግባር መውደድ ደግሞ ትክክል አይመስለኝም፡፡› አለ ተከራካሪው ተማሪ፤ ክርክሩ ግን ‹የእንቢየው!› መስሎበታል፡፡

‹ይህ እንኳ ለመርታት በመፈለግ ብቻ ጫፍ ይዘህ መሟገትህ ካልኾነ መስተቀር መረዳት አይመስልም› አለው መምህሩ፤ ከተማሪው ኹኔታ በመነሣት በአስተያየቱ ኹሉም ተማሪ የተስማማ መስሎ ዝም አለ፡፡

ነገር ግን ‹ያለ ውጤት በሐሳብ ሲናውዙ መዋልና ማደር እንዴት ለፈላስፋነት ያበቃል?› የሚለው ጥያቄ ከእኔም አእምሮ አልተነሣም፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም ቢኾኑ ወይ መምህርን መሞገት ልምድ ስለላቸው በመፍራት ወይም የመሟገት አቅም ስለሌላቸው ይሁን የተማሪውን ሐሳብ ገሸሽ አድርገው የመምህሩን ‹በይሁንነት› ተስማሙ፤ ተስማማን፡፡

ይሁንና አንድ ሌላ ተማሪ የባሰ ሌላ የንትርክ  ሐሳብ አነሣ፤ ‹ፈላስፋ ማለት አስተሳሰቡ ከማኅበረሰቡ ጋር አብሮ የማይገጥም ዕብድ ነው› አለ፡፡

መምህሩም ‹ታዲያ ለምን እኛ አላበድንም?› የሚል ጥያቄ ጠየቀው፡፡

‹የዕብድ አድናቂ ከመቼ ወዲህ ነው የሚያብደው፤ እናንተ እኮ የእነሱ አድናቂና ደቀመዛሙርት ናችሁ እንጂ ‹ፈላስፋ› ለመባል የደረሳችሁ አይደላችሁም› ብሎ መለሰ ተማሪው፡፡

‹የዕብድ አድናቂ የሚኾነው ጤነኛ ቢኾን ነው ብለህ ነው?›

‹መቼም አብዶ የዕብድ አድናቂ መኾን ይችላል ለማለት አይቻልም፡፡›

‹እሽ! ይሁንልህ እንበልና! ፈላስፋ ዕብድ የሚባለው ፍልስፍናን ስላወቀ ነው ወይስ ያበደ ሁሉ ፈላስፋ ነው?›

‹ያበደ ኹሉማ ፈላስፋ መኾን አይችልም፡፡ የፍልስፍና ዕብደት ከማኅበረሰቡ ተገልሎ በራስ ዓለም መኖር ስለኾነ አስተሳሰቡን ከማኅበረሰቡ ወጣ አድርጎ ለማየት የሚሞክር የፍልስፍና ዐዋቂ ነው እንጂ!›

‹ስለዚህ ፈላስፋን የሚያሳብደው ፍልስፍና ማወቁ ነው ማለትህ ነው?›

‹ይመስለኛል!›

‹እና አንተ መቀወስ ፈልገህ ነው ፍልስፍና ልትማር የመጣኸው?›

‹እኔማ ለምን እቀውሳለሁ፤ ራሴን ጠብቄ እማራለሁ እንጂ! እኔ የምማረው ፍልስፍናን ለማወቅ እንጂ ፈላስፋ ለመኾን አይደለም፡፡›

‹ግቡ ማበድ ከኾነ ማወቅህ ምን ይጠቅምኻል? ደግሞስ ፈላስፋ የምትለው ፍልስፍናን የማያውቅ ሰው ነው እንዴ?›

‹ፍልስፍናን ሳያውቅማ እንዴት ፈላስፋ ሊባል ይችላል?›

‹ያ ከኾነማ አንተም ፈላስፋ ለመኾን ትማራለህ ማለት ነው፤ እንደዚያ ከኾነ ደግሞ እንዳትቀውስ አሁንኑ ፍልስፍና መማርህን ማቆም አለብህ›

‹እንደዚያ ማለቴ አይደለም! ለምሳሌ አንተ የፍልስፍና መምህር ነህ፤ ስለዚህ ፍልስፍናን ታውቃለህ ማለት ነው፡- መቼም ሳታውቅ አታስተምረንም፤ እና አሁን አንተ ‹ፈላስፋ› ልትባል ነው?›

‹ለምን ልባል አልችልም?›

‹ፍልስፍናን ተምሮ በማወቅና በማስተማር ‹ፈላስፋ› መኾን ከተቻለማ፤ የፍልስፍናን ትምህርት የሚያስተምረው መምህር ኹል ‹ፈላስፋ› ሊኾን ነው?›

‹ለምን አይኾንም?›

‹ይህ ከኾነማ የፈላስፋ አድናቂ ኹሉ ራሱ ፈላስፋ ነው እያልከኝ ነው?›

‹የፈላስፋ አድናቂ ኾኖ ፈላስፋ መኾን አይቻልም ልትለኝ ነው?›

የመምህሩና የተማሪው ጭቅጭቅ ሊያቆም ስላልቻለ እኔ ነገሩን ለማስቀየስ ሞከርኩኝ፤ ‹የእሱ (የተማሪው) ክርክር ‹ፈላስፋ› የሚባለው ፍልስፍናን ከማኅበረሰቡ ወግና ልማድ ወጣ አድርጎ የሚያስተውል ሰው ነው ለማለት ፈልጎ መሰለኝ!› አልኩኝ፡፡

‹ከማኅበረሰቡ ወጣ ብሎ ማየት ፈላስፋ ያስብላል እንዴ?› በማለት ጥያቄውን ወደ እኔ አዞረው፡- መምህሩ፤ እኔም የፈለግሁት ይህንን ነበር፡፡

‹ከዚያ ወጣ ያለ አስተሳሰብና አስተውሎት ከሌለውማ ምኑን ፈላስፋ ኾነው?›

‹ያንኑ የማኅበረሰቡን ወግና ልማድ በማሻሻልና በማስተካከል ቢቀርፀውስ ፈላስፋነትን ማግኘት አይችልም?›

‹እንደዚያ ማድረግ ይችላል እንጂ! እኔም እኮ የምለው ይኸንን ነው፤ እነሱ ተቀበሉትም አልተቀበሉትም ሕዝቦች የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሐሳብን የሚያፈልቅና የሚያቀርብ ብልህ ሰውን ነው ፈላስፋ ማለት ያለብን፡፡›

‹በአንተ አስተያየት ፈላስፋ ማለት ‹ብልህ ሰው› ማለት ሊኾን ነው፡፡›

‹አዎ! ይመስለኛል›

‹ይህ ከኾነም ብልሆች ኹሉ ፋላስፎች ሊኾኑ ነው፡፡›

‹ኹሉም ላይኾኑ ይችላሉ፤ ግን ‹ፈላስፋ› ለመባል ብልህ መኾን አስፈላጊ ይመስለኛ፡፡›

‹እና ቅድም ‹ዕብድ ነው› እያለ የተከራከረው ይህንን ለማለት ፈልጎ ነው የምትለኝ፡፡›

‹ይመስለኛል!›

‹ይመስለኛል! ‹ብልህ ማለት ዕብድ ይመስልሃል!››

‹እንደዚያ ማለቴ አይደለም› አልኩኝ፤ ‹ሳላስበው በየት በየት ዞሮ መጣብኝ› የሚል ሐሳብ እያሰብኩኝ!

‹ያልከውን ልትክድ ነው? የተነሳኸው የእሱን ክርክር ለማገዝ አይደለም?›

‹እሱን የደገፍኩት ‹ፈላስፋ የሚባለው የተለየ አተያይ ያለው ሰው ነው› ለማለት በመፈለግ የተናገረ ስለመሰለኝ እንጂ ብልህነትን ከዕብደት ጋር ለማያያዝ አይደለም፤ ደግሞም እኮ ዕብድ ማለት የአእምሮ መናወፅ ያጋጠመው ማለት እንጂ አእምሮው ሰልቶ ብልሃትን የታደለ ማለት አይኾንም፡፡›

‹ሐሳብን እርስ በራሱ እያጣረስከው ነው፤ ቀድሞውንም የእሱን ሐሳብ የምትቃወም ከኾነ የክርክሩ ደጋፊ ኾነህ ለመከራከር መሞከር አልነበረብህም፤ ማወቅ የሚኖርብህም መቼም ቢኾን ለመከራከር በመጀመሪያ አቋምን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ከዚያም መከራከሪያ ማስረጃዎችን ማቅረብ አግባብ ነው፤ አንተ ግን አቋምህም ከየት እንደኾነ አይለይም፤ የመከራከሪያ ማስረጃዎችህም እንዴት ክርክርህን ሊያግዙልህ እንደሚችሉ የገባህ አትመስልም፡፡›

እኔም ከዚህ በኋላም መሄድ ስላልቻልኩ ዝም አልኩ፡፡

ኾኖም በዚህ ኹኔታ ላይ እያለን አንድ ኮሰስ ያለ የሚመስል ተማሪ እጁን አወጣና ‹እንደ እኔ እንደ እኔ እስካሁን ካነሣችሁት ክርክር ተነስተን ስንጨምቀው ፈላስፋነት ወደ ባለቅኔነት ያደላ ይመስለኛል፣ ስለዚህ ፈላስፋ መባል ያለበት  የሀገራችን የቅኔ ሊቅ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡›

‹እንዴት ኾኖ? እስቲ! የሀገራችን ባለቅኔዎች ፈላስፎች መኾናቸውን አብራርተህ አስረዳን? ብቻ ‹ዕብድ› እና ‹ብልህ› እንዳምታታው አንተም ‹ፈላስፋ› እና ‹ባለቅኔም› ተምታተውብህ እንዳይኾን› ብሎ እንደማሾፍም ቃጣው፡-መምህሩ፡፡

‹ግዴለም ሐሳቤን ስማውና ካልተመቸህ ትነቅፈዋለህ፡፡ እንግዲህ አንተ ካቀረብከው ሐሳብ ብንነሣ ‹ፈላስፋ ማለት ጊዜ ኖሮት የሚያስብ ሰው ነው› ብልኻል›፤ ሸጋ ሐሳብ ነው፤ ፣ብልህ ሰው ነው› ብሎ የተከራከረም አለ፤ ይህም ሸጋ ነው፤ ‹ዕብድ ነው›፤ ‹ሕፃን ነው› ብሎ የሞገተም አለ፡፡ እነዚህ ሐሳቦች የሀገራችንን ባለቅኔዎች ማንነት ብንረዳ ይታረቃሉ እንጂ አይጣሉም፤ ‹ሊቃውንት መጻሕፍትን ባያስታርቋቸው ኖሮ እርስ በራስ ዱላ አንስተው ይጫረሱ ነበር› እንዲሉ፤ ሊቅ ማለት ሐሳብን ከሐሳብ እያስታረቀ፣ ፍሬውን ከገለባው እየለየ የሚያስረዳ እንጂ የሐሳብ ጠብ ጫሪነትን የሚያጋንን መኾን የለበትም፡፡›

‹ማንዛዛቱን ተውና ፍሬ ነገሩን በአጭሩ አቅርብ፤ እንዴት ኾኖ ነው የሀገራችን ባለቅኔዎች ፈላስፎች ሊኾኑ የሚችሉት?›

‹ይቅርታ መምህር እኔ እንኳን ‹ውሃ ከጥሩ ነገር ከሥሩ› እንዲሉ ለሙግቴ መሠረት መጣሌ ነበር፤ ካንዛዛሁት ይቅርታ! ለማንኛውም እንደ አንተ አቀራረብ ከኾነ ፈላስፋ ማለት ‹ጊዜ ኖሮት ጥልቅ ሐሳቦችን ማብሰልሰልና መረዳት የሚችል ሰው ነው› ብልሃል!

‹አዎ!›

‹በዚህ በኩል ደግሞ የሀገራችን የቅኔ ተማሪዎችና ሊቃውንትን የሚያህል አይገኝም?›

‹እንዴት?›

‹በሀገራችን የቅኔ ሊቅ ለመኾን ቅኔን ቆጥሮ ያለፈ ተማሪ መኾን ያስፈልጋል፤ የቅኔን ትምህርት መማር የሚቻለውም ከቤተሰብ ተለይቶ የንብረትና የቤተሰብን ጉዳይ ዘንግቶ፣ ለቁመተ ሥጋ ብቻ በመለመን፣ ጊዜ ሠጥቶ በማሰብ ነው፡፡ አብዛኛው የቅኔ ተማሪ ትምህርቱን እየተማረ ቅኔን የሚቆጥረውና የሚቀኘውም ኹሉ ነገር ጭር ባለበት፣ የሚያውክ እንቅስቃሴ በማይታይበትና በማይሰማበት በሌሊት፣ ነቂኸ ሕሊናን በመክፈት ወይም ከሰው ተለይቶ ጫካ ውስጥ ገብቶ በጥልቀት በማሰብ ነው፤ ስለዚህ አንተ ባልከው መሠረት ፈላስፋ ማለት ጊዜ ኖሮት በዚያ ጊዜ ውስጥ በጥልቀት ማሰብ የሚችል ከኾነ፤ ፈላስፋ ሊባል የሚገባው የሀገራችን ባለቅኔ አይደለምን?›

‹ምናልባት ሊኾን ይችላል፤ ማወቅ ያለብህ ግን በዓለማችን ላይ ብዙ ባለቅኔዎች አሉ፤ ምንም እንኳ ቅኔያቸው ፍልስፍና የለውም ማለት ባይቻልም፤ ፈላስፋዎች ብሎ መጥራት ግን ያስቸግራል፡፡ የሀገራችን ባለቅኔዎችም የተለዩ አይደሉም፤ እንዳውም በሀገራችን ባለቅኔ የሚባሉት በሃይማኖት ቀኖና እና በነገሥታት ውዳሴ ተሸብበው የሚቀኙ ስለኾኑ ፍልስፍናን ያውቃሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ እንዲሁም መለየት ያለብህ ባለቅኔ ማለት ገጣሚ ነው፤ ገጣሚ ደግሞ አንድ የሚነሽጠው ነገር ሲያገኝ ቤት በሚመታ ስንኝ ሐሳቡን የሚገለጽ ጸሐፊ ነው፤ ፈላስፋ ግን ገጣሚውን መኾን አስፈላጊው አይደለም፤ ነገሮችን በጥልቀት ነው የሚያስበው፤ በተጠየቅ ወይም በምክንያት ነው  የሚከራከረው፡፡›

‹ይቅርታ መምህር! የእኔን ነጥብ የሳትከው መሰለኝ› አለና ተማሪው ምክንያቱን ማብራራት ጀመረ ‹የኔ ነጥብ› አለ ‹አንደኛ ቀድመህ ካነሣኸው ‹ፈላስፋ ማለት ጊዜ ሠጥቶ ማሰብ የቻለ ነው› ባልከው መሠረት የሀገራችን ባለቅኔዎች ጊዜ ስጥተው ከቤተሰብ ተለይተው፣ የዓላማዊ አስተሳሰብን ንቀው፤ ሰጥ ረጭ ያለ ሥፍራና ጊዜን መርጠው የአንድን ነገር ተፈጥሮ፣ ክስተት፣ ታሪክና ባህል ከሌላው ወይም ከመንፈሳዊ ነገር ጋር በማነጻጸር አውጥተው አውርደው የሚቀኙ በመኾናቸው አንተ ያነሣኸውን የፈላስፋነት መስፈርት መከራከሪያ የሚያረጋግጡ ናቸው ማለቴ ነው፡፡

ኹለተኛም እኔ በዓለም ላይ ያሉ ገጣሚዎች ኹሉ ፈላስፎች ናቸው አልወጣኝም፤ ያቀረብኩትም የዓለማችንን ባለቅኔዎች የሚመለከት ሳይኾን የሀገራችንን የግዕዝ ቅኔ ሊቃውንትን የሚመለከት ነው፤ የክርክሬ ማጠንጠኛም የሀገራችን የቅኔ ሊቃውንት ትምህርቱን ጀምረው እስከሚጨርሱ የሚያልፉበት ሥርዓት አንተ ያነሣኸውን ‹ጊዜ ሠጥቶ የማሰብ መርህን› የሚተገብር ነው፤ ይህ ከኾነም ፈላስፎችም ብለን ልንጠራቸው ይገባናል የሚል ነው፡፡ ፈላስፋ ገጣሚ አይደለም ያልከው ግማሽ ትክክል ነው፤ እንዲሁም ከሀገራችን ሊቃውንት አንጻር ምንም እንኳን ቅኔያቸውን በግጥም ቢያቀርቡም ባለቅኔ ማለት ገጣሚ ላይኾን ይችላል፤ ቅኔንም በግጥም አድርገው የሚቀኙት ዕምቅና አይረሴ አድርገው በዜማ ለመግለጽ ስለሚመቻቸው እንጂ የቅኔ መገለጫውና አገልግሎቱ  ግን ብዙ ነው፤ ይህንን ለይቶ ማወቅም ይጠቅማል፡፡

የሀገራችን ባለቅኔዎች ከሌሎች ሀገሮች ባለቅኔዎች የተለዩ አይደሉም ያልከውን ያለማወቅ ስለመሰለኝ ለይተህ እስክታውቀው መጠበቅ ያስፈልጋል፤ በጥቅሉ ግን አባቶቻቸን ከሚሉት ልነግርህ የምችለው ከጥንት ጀምሮ ራሱን የቻለ የትምህርት ሥርዓት ያለው፤ ቀድሞ የሰዋሰው ሥርዓትን በአግባቡ መማርን የሚጠይቅ፣ ምሥጢርን በግልጽ ውስጥ አስገብቶ እየደበቀና እየፈለቀቀ፣ በተምሣሌትና በንጽጽር ቃላትን በቃላት ደራርቦ ሲገልጽ ግርምትን የሚፈጥር፣ ትምህርቱ ለሌሎች ትምህርቶች ማጥኛና መመርመሪያ መሣሪያ የሚኾን፣ የተጠየቅ ልጠየቅ የሙግት ጥበብን ለማወቅ መሠረት የኾነ፣ የፍጥረታን ውህዳዊ ተፈጥሮ የጠበቀ (ሥጋዊነትንና መንፈሳዊነትን፣ ሰማያዊነትንና ምድራዊነትን፣ ግልጻዊነትንና ምሥጢራዊነትን፣…  ያዋሀደ)፣… ቅኔ ያለው ኢትዮጵያ ነው፤ ሌሎች ጋር አለ ካልክ በምሳሌ አምጣና ዐሳየን፤ አነጻጽረን እንቀበላለን፡- የሌሎቹ ቅኔ ለግዕዝ ቅኔ ‹የስም ይጠጌው› ነው እንጂ ‹የእውነት ይደርሴው› አይደለም፡፡ ደግሞም የሌሎች ሀገሮች ባለቅኔዎች የሚባሉት ‹ነሸጠን› በማለት ግጥም የሚደረድሩትን ሲኾን የሀገራችን ግን በአብሰልስሎሽ ምሥጢር የሚራቀቁ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ‹በሃይማኖት ተሸብበውና ነገሥታትን እያወደሱ› የሚለው መከራከሪያህ የዕውቀት ሳይኾን የስሜት ነፀብራቅ ያስመስልብሃል፡፡ ‹ምናልባት በሃይማኖት ውስጥ ፍልስፍና የማይታወቅ ከመሰለህ› ሌላ ርዕስ ስለኾነ እንለፈው፤ በሃይማኖት ውስጥ ፍልስፍና መኖሩን ሳታውቅ የፍልስፍና መምህር ትኾናለህ ብዬ ግን አልገምትም፡፡ ሊቃውንቱ ለነገሥታቱ ቅኔ የሚቀኙትና የሚያቀርቡትም የድሮዎቹ ነገሥታት ራሳቸው የቅኔን ምንነትና የዕውቀትነቱን ደረጃ ስለሚያውቁ ትልቅነቱን ማስመስከራቸው ነው፤ ከባህላቸው አንጻር ነገሥታትን ማወደሳቸውም ነውርነቱም አይታየኝም፡፡ ይቅርታ! መልስ ለመሥጠት ብዬ ከክርክራችን ነጥብ ወጣሁ መሰለኝ፡፡› ብሎ አቆመ፤ ያደረገው ግን ንግግር እንጂ ክርክር አይመስልም፤ ለዚያም ይመስለኛል መምህሩም በመሃል ላይ ሊያስቆመው ያልፈለገው፡፡

ኾኖም ‹መጀመሪያ ንግግርህን አርም፤ የንግግርህ ድምፀት አልተመቸኝም፤ ያቀረብከውም የእናንተን የደብተራዎችን አስተሳሰብ ነው፤ ‹ፈላስፎች ነን› ለማለት የምትመኙት ምኞት ይመስላል፡፡› አለው መምህሩ፡፡

‹መምህር ለምን ሌላ ነገር ውስጥ እንገባለን? ይልቁንስ የያዝነውን ነጥብ ብናበሰል አይሻልም? እሺ! ሌላውን ኹሉ እንተወውና ‹ፈላስፋ ማለት ጊዜ ኖሮት በጥልቀት የሚያስብ ነው› አላልክም?›

‹ብያለሁ! ግን አንተ እንዳልከው አይደም፡፡›

‹እሺ! ምንም ይሁን ‹ባለቅኔዎችም ጊዜ ወስደው በማሰብ የሚቀኙ ከኾነ የክርክርህ ማዕቀፍ ባለቅኔዎቻችንን ያካትታል ማለት ነው፤ ይህ ከኾነም ከእኔ አቀራረብ ጋር መስማማት አለብህ፤ ከተስማማህ እንዴት ባለቅኔዎቻችንን የፈላስፋነት ማዕረግ እንነፍጋቸዋለን? ካልተስማማህ ‹ከዚህ በተለየ ጊዜ ሰጥቶ በጥልቀት የሚያስብ ሰው ፈላስፋ ሊኾን የሚችልበትን ምሥጢር ገልጸህ አብራራልኝ?›

‹እኔ የደብተራዎችን ድግምት ፍልስፍና ብዬ ለመውሰድ ይቸግረኛል? የተጻፈውን የዳዊት መዝሙርና ውዳሴ ማርያም ምናምን እያላችሁ የምትደግሙትን በምን አግባብ ነው ፍልስፍና የምለው? አሁን እዚህ አንተ ጊዜ ሰጥተው በማሰብ እያልክ የምትከራከርላቸውን ሰዎች እኮ እናውቃቸዋለን? ‹ሸምድድ እንዳትረሳ› የሚል ስልትን በመከተል ከተጻፈላቸው ቃል ውጭ ማሰብ እንደማይችሉ እናውቃለን፤ ይህ ለእኔ ፍልስፍናን የፍልስፍና ተቃራኒ አድርጎ መረዳት ይመስለኛል፤ እንደዚያ ካልኾነ በስተቀር የሀገራችን ባለቅኔዎች የምትላቸው ፈላስፎችም መባላቸው አይገባኝም?›

‹እሺ! መምህር ካልገባህ ይቅርብህ!› ብሎ ዝም አለ ተማሪው፡፡ መምህሩም የተበሳጨ እየመሰለ፤ ክፍሉን ጥሎ ወጣ፡፡

እና! ፈላስፋ ማን ነው? መልሱን ለፈላስፎች እንተውላቸው፤ ምናልባት እነሱም ‹ፍልስፍናችን ለጥያቄ እንጂ ለመልስ አያደላም› ይሉን ይኾን እንዴ? በሉ ‹ከፈላስፋ ያወቀ ቡዳ ነው› እንዳትሉኝ ‹ቡዳ ፈላስፋን ይበልጠዋል ወይ?› ብዬ እጠይቃችኋለሁና፡- ለመፈላሰፍ ወይም ሕፃን ለመኾን!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply