መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር

በገ/ሕይወት ባይከዳኝ

1916 ድጋሚ ኅትመት 1953

ይህንን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2000 ዓ.ም. እንዳነበብኩት ላገኘው እንደማልችል በመገመት ከዚህ በታች ያስቀመጥኳቸውን ጥቅሶች ለቅሜ በማስታወሻዬ ላይ አሣረፍኩ፡፡ ከጊዜ በኋላ መጽሐፉንም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አሳተመው፤ እኔም ጥቅሶቹ እንዳይጠፉብኝ ስለፈለኩ ኮምፒተሬ ላይ ገለበጥኳቸው፤ ከዚያም ምናልባት የመጽሐፉን ሐሣብ በተመረጡ ጥቅሶች አማካይነት ቶሎ ለመረዳትና መጽሐፉን ማግኘት ላልቻሉም ምን ዓይነት መጽሐፍ እንደሆነ ለማየት ይረዳል በሚል በዚህ ጦማር ላይ አስቀመጥኩት፡፡ ጥቅሶቹ የተወሰዱትም ከበፊት ከ1953 ዓ.ም እትም በመሆኑ የአ.አ.ዩ. ፕሬስ ካሳተመው ጋር የተጠቀሰው ገፅ ቁጥር አብሮ አይሄድም፤ ምናልባት ወደፊት ማስተካካያ አደርግበት ይሆናል፡፡ እንዲሁም እዚህ ያሉ ጥቅሶች ምንም እንኳን እኔ ጠቃሚ ናቸው በሚል የመረጥኳቸው ቢሆኑም በግል ፍላጎት ተጽእኖና የመረዳት ሁኔታ የተመረጡ ሊሆኑ እንደሚችሉና ሊስተዋሉ የሚገባቸው ሌሎች ጥልቅ አሳቦችን የሚገልጹ እንዳሉ አለመዘንጋትም ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነም ወደፊት ዝርዝር የኢኮኖሚ ትንታኔ እሰጥበታለሁ፡፡  ‹‹

!  ዛሬ ደግ የተባለው ደንብ የሕዝብ ዕውቀትና ሀብት ሲሰፋ ጥቂት ዘመን ቆይቶ የማይጠቅም ይሆናል፡፡ እንዲሁም ዕውቀት ላላቸው ሕዝቦች ጥሩ የሆነ ደንብ ዕውቀት ለሌላቸው ሕዝቦች ትልቅ ጉዳት ይሆንባቸዋል፡፡ (15)

!  ደንብ ሁሉ ምንም ቢጠቅም በተለየ ጊዜ ውስጥ ለተለየ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ (15)

!  የማንኛውም ነገር ዋጋ ሲገመት ያ ነገር እስኪገኝ ድረስ ያለው ድካም ሁሉ እንደመገመት ነው፡፡ (44)

!  ማንኛው ነገር እስኪገኝ ድረስ መሰናክሉና ድካሙ እያነሰ ሲሄድ የዚያ ነገር ዋጋው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ መሰናክሉና ድካሙ ከበዛ ግን ዋጋው ይጨምራል፡፡ (44)

!  ዕውቀት ሲበዛ ማንኛውንም ነገር ለኑሮ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት መሰናክሉና ድካ ያንሳልና የዕቃው ሁሉ ዋጋ ያንሳል፡፡ (45)

!  ዋጋ ማለት የሥራ መለኪያ ማለት ነው፡፡ (45)

!  ድሮ አንድ ብር ለማግኘት ብዙ ድካም ያስፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን አንድ ብር ለማግኘት ብዙ ድካ ስለማያስፈልግ የጤፍ ዋጋ ከድሮው ያንሳል እንጂ አይበልጥም፡፡

!  ነጋደዎች ሻጭና ገዥን የሚያገናኙ ተላላኪዎች ናቸው፡፡ (49)

!  ዕውቀት ሲበዛ የነጋዴ ጥቅም ያንሳል፤ የሠራኞች ጥቅም ግን ከፍ ይላል፡፡

!  ቀስት መጀመሪያ እስኪሠራ ድረስ ዋጋው ውድ ነው፤ የመጀመሪያው ቀስት ከተሠራ በኋላ ግን በራሱ ጊዜ ዋጋው ይቀንሳል፡፡ (50)

!  ከሠር የብረትን አፈር ለማቅለጥ ዋጋው ይወደዳል፤ መጥረቢያ ከተሠራ በኋላ ግን ይቀንሳል፡፡ መሣሪያ ሲረክስም ለኑሮ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ አብሮ ይረክሳል፡፡ (50)

!  ለኑሮ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ሲረክስ ሰው በዓለም ላይ ሙሉ ጌትነት ሲለሚያገኝ ይከበራል፤  ድካሙም ያንሳል፡፡ ስለዚህ ዕውቀት ሲበዛ ኑሮ ይረክሳል፡፡ (51)

ምሳሌ፡- አንድ ሰው መቶ ኪሎ ዕቃ 7ኪ.ሜ የሚያህል መንገድ በሰዓት ሊጎትት አይችልም፡፡ ፈረስ ግን 9 መቶ ኪ.ግ ዕቃ በሰዓት ሊጎትት ይችላል፡፡ ማለት ፈረስ ከሰው 9 እጥፍ ጉልበት አለው፡፡ ሆኖም ዕውቀት ስሌለው ሰው በዕውቀቱ አልምዶት ያሸክመዋል፡፡ የሰው ሥረውም ይፋጠንለታል፡፡ ከዚህም ይበልጥ ባቡር ይሠራል፡፡ (51)

!  ዕውቀት ከጉልበት ይከበራልና ከቤት ከዳኙ ሥራ ይልቅ የሣር አጫጁ ሥራ ይረክሳል፡፡ (52)

!  ዕውቀት ከጉልበት ይበልጣልና በዕውቀታቸው ከፍ ያሉ ሕዝቦች ዕውቀታቸው ዝቅ ያለውን ሕዝቦች በግድ ይበልጧቸዋል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እንዳይጎዳ የሚፈልግ መንግሥት አውራ ጥረቱ ትምህርትን ማስፋፋት ነው፡፡ ዕውቀቱ ሲበዛ ራሱ ይመክታልና፡፡ (52)

!  ሰው በዕውቀቱ ጌትነቱ ይሰፋል፡፡ በዚህም የሚያስፈልገውን ነገር በጥቂቱ ድካም ያገኛል፡፡ (53)

!  ዕውቀት ያለው ሰው ዕውቀት የሌለውን ሰው ድካም በትንሽ ዋጋ ይገዛዋል፡፡ (53)

!  ዕውቀት ዓለምን እንደሚገዛ የማይነቃነቅ ዘላለማዊ ደንብ ነው፡፡ (53)

!  መሬት በሰው እጅ አይሠራም ነገር ግን ዋጋ ያወጣል፡፡ ለዚያውም በመበላለጥ፡፡ ምክንያም በጥቂት ሰዎች እጅ በሞኖፖል ስለሚያዝ ነው፡፡ ሞኖፖሎችም ስለሚበላለጡ የመሬት ዋጋም ሊበላጥ ችሏል፡፡ በዚያም የሚኖር ሕዝብ አርነት የለውም፡፡ (53-54)

!  ድህነትና ጌትነት የተለየ በሰው ዕውቀት ነው፡፡

!  ቀስትን የሠራ ሰው የቀስቱ ባለሀብት ነው፡፡ መሣሪያ ካልተጠቀሙበት በእጅ ስላለ ብቻ ሀብት አይሆንም፡፡

!  የድንጋይ ከሰል በእንግሊዝ ለብዙ ዓመታት ኖሯል፤ ሀብት ሆኖ መቆጠር የጀመረው ግንባርና መርከብ መሠራ ከጀመረ በኋላ የሱ ሀብትነት ታወቀ ተወደደም፡፡

!  ለሀብት ሁለት ትርጉም አለው፡፡ ርግጠኛ ሀብትና አብላጫ ሀብት፡፡ (57)

!  የሀብት መለኪያ ሥራ ነው፡፡ ሀብት ማለት የዓለም ጌትነት መለኪያ ነው፡፡

!  ለሰው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ምድር በሆድዋ ይዛለች፡፡ ሰውም ሊጨምርበት አቅም የለውም፡፡ ማንኛውንም ነገር ሲፈልግ አንቀሳቅሶ ማጋጠም ነው ያለበት፡፡ የሚያንቀሳቅሰውና የሚያጋጥመው ደግሞ በሥራ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ዕውቀቱና ገንዘቡ ሥራ ብቻ ነው፡፡

!  ሰው ኑሮው ከምድር ጋር ሲታገል ነው፡፡ እሱ ጌታ ልሁን እሷ ደግሞ አልገዛም በማለት፡፡ ይህም ትግል ሥራ ይባላል፡፡ ሰውም አብላጫ ሀብት የሚኖረው ትርፍ አብላጫ ትርፍ የተሠራ ነገር (ዕቃ) ሲኖረው ነው፡፡ የሚታገል ሰው ባላጋራው ከወደቀለት በኋላ የመታገሉ ኃይል ይቀልለታል፡፡ ዳግመኛ ቢታገል የመታገል ስልቱ ይጨምርለታል፡፡ አንድም ሥራ መጀመሪያ ከተሠራ በኋላ በሁለተኛው አያቅትም፡፡ (የመጀመሪያ ሥራ) የሚቀጥለውን ሥራ ያቀለዋልና፡፡ (58)

!  ሀብት የጌትነት መለኪያ ነው፡፡ አንድ ሀብት ከተገኘ በኋላም መሰናክል ካላጋጠመው የበለጠ ሀብት ይከተለዋል፡፡ ተጣጥሮ ላም የገዛ በዓመቱ ጥጃ ትወልዳለች፡፡ ወንድ ቢሆን ሲያድግ እርሻ ያርስበታል፤ አዝምሮም እህል የሚተርፈው ካገኘ ሸጦ ሌላ መሣሪያ ይገዛበታል፡፡ ማረሻ ይገዛል፤ ከዚያም ሰረገላ (ለመጓጓዣ)፤ ከዚያም መጓጓዣውን (መንገድ) ያበጃል፡፡ (59)

!  ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ ነው፡፡ ሥራ የሚሠራው ደግሞ በዕውቀት ነው፡፡ በዕውቀትም ሀብት ሁሉ ከምድር ይገኛል፡፡ ሀብት የምድር ጌትነት ነውና፡፡ (60)

!  ሀብት ማለት የምድርን ግዛት መለኪያ ነው፡፡ ሀብትም የሚስፋፋ ዕውቀት ሲስፋፋ ነው፡፡

!  ሥራ የሚፋጠነው በዓይነት ሲከፋፈሉት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች አንድ ዓይነት ሥራ ከሠሩ ሊረዳዱ አይችሉም፡፡ አራት ሰዎች በአንድ ጥማድ በሬ ቢያርሱ ሥራቸው አይፋጠንም፡፡

!  ሰው ሚሽት የሚያገባው ሥራውን ተከፋፍሎ ለመሥራት መተባበሩ ነው፡፡ እሱ ሲያርስ እሷ ትጎለጉላለችና፡፡ ወይም እሷ የቤቱን እሱ የውጭውን ለመሥራት፡፡ ስለዚህ ሰው እየበዛ ሲሄድ የሥራ ክፍፍልም እየሠመረ ይሄዳል፡፡ (63)

!  ዕውቀት ባለው ሕዝብ ዘንድ ትዳሩ ሁሉ ተለዋውጦና ተከፋሎ ነውና ተቀምጦ የሚበላ የለም፤ እንካ ሥራ ሥራ አምጣና ይባላል፡፡ (64)

!  በድስት የተጣደን ለማፍላት እንጨት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰውም ለመሥራ ምግብ ይፈልጋል፡፡ ሰው ቢሠራም ባይሠራም ምግብ መፍጀቱ አይቀርም፡፡ የማይሠራውም የሠራተኛውን ድካም በከንቱ ይፈጃል፡፡ ይህም እየበዛ ሲሄድ መሬቱ ችጋርና ድህነት ይሆናል፡፡ (የማይሠራው ከሚሠራው ሲበልጥ) (64)

!  ትልቅ ሀብት የሚሠበሰብ ከትንሽ ሲጀመር ነው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ግን በላተኛው ከሠራተኛው ከበዛ የተሠራው ሥራ ሁሉ ያልቅና እንደገና ለመጀመር ጭምር ያስቸግራል፡፡

!  ሥራ የሚፋጠነው እየተባበሩ ተከፋፍለው ሲሠሩት ነው፡፡ በመላውም ሥራ ከመሠልጠን በአንዱ ሥራ መሠልጠን ይቀላል፡፡ (65)

!  የአንድ ሀገርም ወስጥ ሥራ እየተከፋለ ሲሄድ ሰውም በዚያው ሥራ ሲሠለጥን ያገሩ ሀብት እያደገ ይሄዳል፡፡ (65)

!  ሀብት መዠመሪያ ሳይመሠረት እያደገ አይሄድም፡፡

!  እንደሥራው አከፋፈል ብዛትና እንደለውጡም አፈጣጠን መጠን የሕዝቡ ሀብት ከፍ ወይም ዝቅ ይላል፡፡

!  የአንድ ሀብት እንዲያድግ መጀመሪያ ሠራተኛው ከበላተኛው እንዲያንስና ሕዝቡ ተከፋፍሎ እንዲለዋወጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

!  በአንድ ሀገር ውስጥ ነጋደ ሲበዛ ሹምም፣ ወታደርም፣ ቀማኛም ይበዛል፡፡ (ነጋዴ የሚበዛው ሠራተኞች መገናነኘት ስላቻሉ ነውና፡- በርቀት ምክንያት)

!  መሬት ማናቸውንም ነገር የምትሠጥ በብድር ነው፡፡ ብደሯን ካልመለሱላት ልክ እንደባንኮች ሁሉ ታስቸግራለች፡፡ ምክንያቱም የሚፈጠር ሁሉ ከመሬት ነውና ወደ መሬት ይመለሳል፡፡ (ዘፍ.3፡-19) ምድርም ያበደረችውን ነገር ሁሉ ካልመለሱላት ለወደፊት ሥጭኝ ቢሏት ትለግማለች፡- የወሰድከውን መልስ በማለት፡፡ እንዳውም ብድሯን ያልመለሰውን ሕዝብ በረሃብና በበሽታ ትቀጣለች፡፡ (70)

!  ያገራችን መሬት የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ፣ ቆዳ፣ ቡና፣ እህል፣ በሬ፣ ላም፣… እየሆነ ቢሄድ አሁን ባይሰማንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዝቶ መሬት ስትጠብ ጉዳቱ ይታወቃል፡፡

!  ዕውቀት ያነሰው ሕዝብ ዕውቀታቸው ከፍ ካሉ ሕዝቦች ጋር ሲገበያይ መጀመሪያ ትርፍ ጉልበት ድካም ይሠጣቸዋል፡፡ ሁለተኛም መሬቱ ወደ እነሱ ይሄዳል፡፡ ከዚያም እሱ ራሱ (ሕዥቡ) ተወስዶ ወደ እነሱ ይሄድላቸዋል፡፡ (70)

!  ያልተደከመበት ሁሉ ዋጋ አያወጣም፡፡ ደን ውስጥ ሄዶ አጋምን ለመብላት የፈለገ ከመንገድ በስተቀር ዋጋ አያወጣም፡፡ ተለቅሞ ገበያ የወጣ አጋም ለመብላት ግን ገንዘብ መከፈል አለበት፡፡ (71)

!  ያቡጀዲ ጥጥ እንጂ ሥራው ወደ ሀገራችን መጥቶ ፍግ አይሆንም፡፡ (71)

!  ዕውቀት  የሌለው ሰው ድሃና የሰው ሎሌ ነው፡፡ ሥራው አይከማችለትምና፡፡ (72)

!  አንድ ሕዝብ ድህነትና ሎሌነት እንዲቀርለት፡-

 1. እርስ በርሱ በፍጥነት እንዲገናኝ ብልሃት ይበጅለት፡፡
 2. በየሥራው እንዲሠለጥን ትምህርት ይቁምለት፡፡
 3. ሕዝቡ የሚፈልገውን ሁሉ በሀገሩ ውስጥ እንዲሠራ ለቀረጡ የመንግሥት ሹማምንት ይጠብቁት (72)

!  ዕውቀት በሌለው ሀገር ውስጥ መንገድም የምድር ባቡርም ቢሠራለት ለጊዜው ይንቀዋል፡፡ ለጊዜው ብዙ ብር ይገባለትና ሀብታም የሆነም ይመስለዋል፡፡ (ለምሳሌ) ዐሥር ሺህ ብር የተበደረን ሰው መበደሩን ያላወቀ ሰው ቢያየው ሀብታም ይመስለዋል፡፡ ያወቀ ግን ያዝንለታል፡፡ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ዕውቀታቸው ከፍ ካሉ ሕዝቦች ላይ ዕቃ ሲገዙ እየተበደሩ ነው፡፡ የሚበደሩትም ብድር ዕኩሌው ከጉልበታቸው ዕኩሌታው ከምድራቸው ነው፡፡ (72)

!  የውጭ ሀገር ሰዎች ኢትዮጵያውያንን (በግብራቸው) የሚሏቸው፡- ‹እኛ የመጣነው የሀገራችሁን ሀብት ለመውሰድ ነውና እኛ ሠርተን በመሬታችሁ ውስጥ ያለውን እንዲንወስድ እሺ አትሉንምን? እሺ የምትሉን ከሆነ ያገራችን ሠራተኞች አናመጣም፡- ዋጋቸው ይበዛብናልና፡፡ ስለዚህ (የእናንተ) የጉልበታችሁ ዋጋ እጅግ በጣም ትንሽ ነውና እናንተው ሠርታችሁ ሥጡን ለድካማችሁ ዋጋም ጥቂት ብር እንከፍላችኋለን፡፡ በዚሁ በምንሠጣችሁ ጥቂት ብር ግን የሚያስፈልገውን መሣሪያና መኪና ገዝታችሁ ልብሳችሁንና ለኑሮ የሚያሥፈልጋችሁን (ተጠቀሙ)፤ ሁልጊዜ ሌላ ዕቃ አትሥሩ፡፡…. ሁሉንም ነገር ከእኛ ግዙ፡፡ የሠጠናችሁንም ገንዘብ ከብዙ ወለድ ጋር በቶሎ መልሱልን፡፡

!  ሕዝቡ ሲሠለጥን ግን ለኑሮ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በገዛ እጁ ይሠራል፡፡ ሥራውም በጣም ይከፋፈላል፡፡ መንገድና የምድር ባቡር በመሠራቱ ሠራተኛው አጠገብ ላጠገብ ይሆናል፡፡ በመንቀሳቀስ ጊዜ አይባክኑም፤ በያዙት ሥራ ብዙ ለመሥራት ጊዜ ያገኛሉ፤ ነጋደም አይበዛም፡፡ በዚህም አዳዲስ ሥራና ብልሃት እራሳቸው መርምረው ያኛሉ፤ ትርፉም ይጨምራል፡፡ የሕዝብ ሀብትና የመንግሥት ኃይል እያደገ ይሄዳል፡፡ ሀብትም ማለት አንዱ ኃይል ነው፡፡

!  መንግሥት ቀረጥ ሲወስድ ሕዝቡን ሊጎዳ ይችላል፡፡ በሀገሩ ውስጥ የተበጀው ዕቃ ሲሸጥና ሲለወጥ በገባያው የቀረጠ እንደሆነ ዕቃውን ሠርተው የሚያለዋውጡትን ሠራተኞች እንደማራራቅ ያህል ይቆጠራል፡፡ የበለጠ ድካምንም ይጨምራል፡፡ ይህም ሥራን ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም የመለዋወጥ ፍላጎትን ይገድባልና፡፡ ሥራንም ስለሚቀንስ ሀብትን ያሳንሳል፡፡ የመንግሥት ግብርንም ስለሚቀንስ የሚያገባው ገቢ ያጣል፡፡ የተላላኪው (ነጋዴው) ደመወዝም ይጨምራል፡፡ ዕቃ ደግሞ የሚረክሰው ሻጭና ገዥ ሲቀራረቡ ነው፡፡(76-77)

!  ሕዝቦች ሁሉ መሰናክል ባያጋጥማቸው ከፍ ወዳለው የዕውቀት ደረጃ መድረስ ይችሉ ነበር፡፡ የዓለም ሕዝቦች እንዳገኛቸው መሰናክል መጠንና መሰናክሉን ማለፍ መቻል የሀብታቸው መጠን ከፍና ዝቅ ይላል፡፡ ሀብት የተሠራ ሥራ ክችት ነው፡፡ (78)

!  አርነት ያለው ሕዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ መንግሥት ብቻ ያለው ሕዝብ ማለት ብቻ አይደለም፤ ራሱንም የቻለ ሕዝብ ማለትም ነው እንጂ፡፡ (79)

!  የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከዛሬ ድረስ ራሱን አልቻለም፡፡ የሚገለገልበት ነገር ሁሉ ከሌላ ሕዝብ የመጣ ነውና፡፡ ደህናውን መንገድ መንግሥት ለክቶ ካልሠጠውና ካላሳየው እንደዚህ ዓይነት ምቾትና ድሎት የለመደ ሕዝብ መጨረሻው ክፉ ነው፡፡ ብዙ ነገር ለምዶ የለመደውን ነገር ለማድረግ ግን አቅም ያጣልና፡፡ (80)

!   በተጨማሪም በዘመናዊነት የተሠራው ዋጋው ስለሚቀንስ የውጭውን ለመግዛት የራሱን ይተዋል፤ ይረሳል፡፡ ለዚህ ዋናው መመከቻ የተደላደለ የጉምርክ ደንብና ሥራ ማሰልጠን ነው፡፡ (81)

!  ባገር ውስጥ ሥራ ሲበዛ ሕዝቡም ጭቅጭቅንና ነገርን ይጠላል፡፡ ማለትም ጭቅጭቅና ጦር ቅድሚያ  የሚበዛው ባልሠለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ነው፡፡ ሕዝቡ ሲሠለጥን የሹሞች እርዳታና ቸርነት የሚፈለግበት ምክንያት ያንሳልና፡፡

!  መሬት በጥቂት ሰዎች እጅ ሲገባ(ሲያዝ) ለሀገሩ መጥፎ ምልክት ነው፡፡ ሕዝቡ እንደደኸየና መንግሥትም እንደደከመ ያሳያል፡፡

!  መሬት አይሸጥ አይለወጥ ተብሎ ቢታወጅ ለሕዝብ የበለጠ ጉዳት ነው፡፡ ባላገሩ ያለው ገንዘብ መሬት ብቻ ነውና፤ ይህንንም ገንዘቤ ነው ያለውን ገንዘብ እንደልቡ ካልሸጠና ካልለወጠ ገንዘቤ ነው የሚለውን ነገር ፈጽሞ ያጣል፡፡ በእዳ እንኳን ቢያዝ እጁን የሚያወጣበት ነገር አያገኝም፡፡

!  እነሆ በብዙ ድካም ተለቅሞ አንዳች ነገር ሳይሠራበት ወይም ሳይሞቅ ያለቀ እንጨት በከንቱ መጥፋቱ ነው፡፡ እንዲሁም የማይሠራ ሰው የበላው እህል በከንቱ መጥፋቱ ነው፡፡ (98-99)

ከዚህ በላይ ለቀረበው የተሠጠ ማጠቃለያ (99-113)

 1. ሰው የተፈጠረው የምድር ጌታ ለመሆን ነው፡፡ ነገር ግን የምድር ተገዥ ሆኖ ነበር፡፡
 2. በኋላ ግን ዕውቀት ስለበዛ ተባዛ ተባበረ፡፡
 3. ከተባዛና ከተባበረ ዘንዳም ሥራውን ተከፋፍሎ ስለሠራ እንደሥራው መጠን መለዋወጥ ጀመረ፤ ዋጋ ማለትም የሥራ መለኪያ ነው፡፡
 4. ሀብት ማለት የዓለም ጌትነት መለኪያ ነው፡፡ ሁሉንም የምትሠጥ መሬት በመሆኗና የሰው ተግባር እሱን ማጋጠም በመሆኑ ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ ማለት ነው፡፡
 5. ማንኛውም የተሠራ ሥራ ከኃላ የሚከተለውን ሥራ ያቀለዋል፡፡ ማንኛውም ሀብትም የበለጠ ሀብት ይከተለዋል፡፡ ጅምር ወዲያው ወዲያው ሲጠፋ አንዳች ሥራ አይጠራቀምም፡፡ ዕውቀት በሌለው ሕዝብ ዘንድም በላተኛው ከሠራተኛው ይበልጣል፡፡ ሀብትም አይጠራቀምም፡፡
 6. የሕዝብ ሀብት የሚሰፋው ሕዝቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመሥራት ሥራውን በብዙ ተከፋፍሎ ሲለዋወጥ ነው፡፡ የሚለዋወጡት ከተራራቁ ግን ድካም በከንቱ ይባክናል፡፡ ለተላላኪም ሊከፍሉ ግድ ይላቸዋል፡፡ ድካምም ሲበዛ ልብ ይሠንፋል፡፡ በዚህም የሚሠራው ሥራ ያንሳል፤ ሀብትም አያድግም፡፡
 7. ሠራተኞችን የሚያቀራርቡ በመንግሥት የተሠሩ የባቡር ሀዲድና መንገድ ሲኖሩ ነው (ናቸው)፡፡ ሆኖም ግን በሀገሩ ውስጥ የሚዘዋወር ዕቃ ላይ ቀረጥ መቁረጥ ሠራኞችን ያራርቃል፡፡
 8. ለዚህ ደግሞ በሀገር ውስጥ የትምህርት መስፋፋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የጉምርክ ደንብም ጠቃሚ ነው፡- ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ለመቀረጥ፡፡ ዕቃን ሁሉ ከውጭ የሚያመጣ ሕዝብም ፍጹም ድሃ ነው፡፡
 9. ከውጭ ዕቃ በሚገባበት ሀገር ውስጥ የባላገሩ ጥቅም ያንሳል፡፡ መሬትም በሞኖፖል ይያዛል፡፡

10. የመንግሥት መሠረት እርሻ ነው፡፡ ባለርሻ የሚያገኘው ጥቅም ሲያንስ የመንግሥት መሠረትም አይጠናም፡፡

!  ያለፋ ቆዳ የሚረክስ ከከብት አራጁ ቤት ሲሆን የለፋ ቆዳ ደግሞ በቁርበት ፋቂው ቤት ነው፡፡ ጥጥም ታርሶ የሚዘራበት ቦታ ይረክሳል፤ ልብስ ከሚሠራበት ግን ይወደዳል፡፡

!  የወርቅና የብር መለዋወጫነትን የተገነዘቡ ሕዝቦች ዘንድ አጠቃቀሙን ስለሚያውቁበት ሲበደሩ እንኳን ወለዱ ያንሳል፡- ሸማ በሸማኔ ቤት እንደሚረክሰው፡፡ (114)

!  አንጨት በሌለበት ቦታ መጥረቢያ አያስፈልግምና በዕውቀት ሠልጥኖ መለዋወጥ በሌለበት ሕዝብ የወርቅና የብር ጥቅም ብዙ አይደለም፡፡ (115)

!  ላሙን ሸጦ ልብስ በመግዛት የሚያስቀምጥ ባላገር እንደማይጠቀመው ሁሉ ብርና ወርቅንም ወስዶ እቤት ቢያስቀምጡት ካልሠሩበት አይጠቅምም፡፡ (115)

!  የሀብታሞች አኗኗርና የሠራተኛው የድኸው አኗኗር ዓይነቱ ዕንበለ መጠን (ከልክ በላይ) የሚራራቅበት ሀገር መንግሥቱ ከጥፋት አፋፍ እንደደረሰ ያሳያል፡፡

!  ትምህርት በሌለበት ሀገር ለሥርዓት የሚሆን መሠረት አይገኝም፡፡ (125) አዲስ ደንብም ቢወጣ ከሚጠቅመው የሚጎዳው ይበልጣል፡፡

!  ባንክ የሚቆም በሀገር ላይ ያለ ሀብት (ወርቅና ብር) ሥራ እንዳይፈታ ገንዘብ ያለው ለሌለውና ለሚሠራው እያበደረ እንዲሠራበት ለማድረግ ነው፡፡ (125)

!  በሀገር ውስጥ ወታደርና ነጋዴ ሲበዛ ለመንግሥትም ለሕዝብም አይረባም፡፡ የመንግሥት ዋና መሠረት እርሻ ነውና፡፡

!  የማንኛውም መንግሥት ሀብትና ኃይል የሚያድግ ሕዝቡ በሥራ የሠለጠነ እንደሆነ ነው፡፡ ወለድ የሚበዛው ሕዝቡ በሥራ ባልሠለጠነለት መንግሥት ነው፡፡ (130)

!  አስተማሪው የነገረውን ቃል ተጣሮ የተማረው ነገር እውነት መሆኑንና አለመሆኑን የሚመራመር ተማሪ ከሺህ አንድ አይገኝም፡፡ (132)

!  በዚህ ዓለም የሚሠራው ሥራ አብዛኛው በእምነት ነው፡፡ ከሰው ልጅ እምነት ቢጠፋ አንዳችም ሥራ አይሠራም ነበር፡፡ ዕውቀት የሌለው ሕዝብ እርስ በእርሱ አይተማመንም፡፡ ስለዚህ የሚሠራውም ጥቂት ነው፡፡  ስለሆነም ዕውቀት ለሌለው ሰው ቸክ ሰጥተው ከባንክ ብር አውጣ ቢሉት አያምንም፤ አታለው ከቤት ሊያስወጡት ይመስለዋልና፡፡ ብሬን ቆጥራችሁ በእጄ ካልሠጣችሁኝ አላቃችሁም ይላል እንጂ! በመንግሥት ታምኖ የቆመ ባንክ መታመኑን መንግሥት ከመሠከረለት (ከተዋሰው) ዘንድ ሕዝቡም እንዲያምነው የተገባ ነው፡፡ ለዚህም ነው ባንኮች ወረቀትን አትመው መገበያያ የሚያደርጉት (በመንግሥት ትዛዝ)

!  በሀገር ድኸ ሲበዛ ለመንግሥት ጉዳት ነው መሠረቱ ይነቃነቃል፡፡ (139)

!  ሕዝቡ በመላው ብሩን የሚያስቀምጥበት ቦት አንድ ብቻ እንዲሆን ቢደረግ ደግ ይሆናል? ባገሩም ውስጥ ካንዱ ወረዳ ወደ አንዱ ወረዳ ብር ሲላክ መልክተኛው አንድ ብቻ እንዲሆን ቢደረግ ይበጃል? (139)

!  ሚዛን የሚመዛዘነው በሁለቱም ጫፍ እኩል የሚከብድ ነገር ሲደረግበት ነው፡፡ የሰውም ፀባይ እንደዚሁ ነው፡- እንስሳዊና መልአካዊ፡፡ ቀስቃስሽ ካላገኘ ሰው መልአካዊ ባሕሪውን አይከተልም ወደ እንስሳዊ ባሕሪው  ያጋድላል እንጂ!

!  የሰው አውራ ቀስቃሽ ባላንጣ ነው፡፡ ባላንጣ ያለው ሰው ክፉ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ለባላጋራውም እንደማይሣነው ስለሚያውቅ በደግ ሊያሸንፈቀው ይጥራልና፡፡ (141)

!  ዕውቀት የሌለው ሰው የዝሆንን ቁመትና መብረቅ ሲያይ የትልቅ ነጎድጓድም ጩኸት ሲሰማ የፈጣውን ሥራ ያደንቃዋል፡፡ አስተዋይ የሆነ ሃይማተኛ ግን የንብንና የጉንዳንን ትጋት፣ የሥራቸውንም ትክክልነት፣ የሥርዓታቸውንም ማማር አይቶ በዚህ ዓለም ፍጥረት ይገረማል፡፡ ከመብረቅና ከነጎድጓድ ኃይልም ይልቅ የንብና የጉንዳን ተአምር ለፈጣሪው የበለጠ ምስጋና ሆኖ ይታየዋል፡፡ (ምሳ.6፡-6) ››

Please follow and like us:
error

Leave a Reply