መንግሥት፣ ሕዝብና ሥርዓት

ተቀበልነውም አልተቀበልነው ዓለም የተሠራችው በፖለቲከኞች ነው፤ አገሮችም የተመሠሩትም በእነሱ ፍላጎትና ድርድር እንጂ ፖለቲከኞች ባይኖሩ ኖሮ አገር የሚባል ክልል አይኖርም ነበር፡፡ በአገራትም ተቋማት የተመሠረቱትና አሁን ባሉበት ሥርዓት እንዲገኙ ያደረጋቸው የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ አገሮችም በሚፈጥሩት በብዙ ሺህና ሚሊዮኖች የሚቀጠሩ ሰዎች ሕይዎታቸው የተቀጠፈውና የአካልና የሥነ ልቦና ተጎጂ የኾኑት፣ እንዲሁም ስደተኛና ተገላቺ የኾኑት፣ የዓለም ስንትና ስንት ንብረት፣ ቅርስና አካባቢ የወደመው ፖለቲኮኞች በሚፈጥሩት አለመስማማትና መጣላት ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ የዓለም ሠሪዋም፣ አጥፊዋም ኾኖ ለዘመናት ኖሯል፤ ወደፊትም አልሚ ወይም አጥፊ ከመኾን የሚገታ አይመስልም፡፡ አልሚነቱ አገርን ሲያበልፅግ፣ የሰው ልጆችን አነዋዋር ኹኔታ ሲያሻሽልና ዓለም አሁን ያለበትን ኹኔታ እንዲያገኝ ሲያደርግና ለዕድገትና ለፍትሕ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሲያሟላ ኖሯል፡፡ በተቃራኒው ግን የዓለም የብጥብጥና የምስቅልቅል መድረክ የጦርነት ቀጠና በመኾን ለዘመናት ለብዙ ሕዝቦች መጥፋትና መንገላታት ቀዳሚ በመኾን የፈጠረው ችግር ልክ ወደር የለውም፤ ለምሳሌ የአገራት ወረራ፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ፖለቲካ የሚወልደው ነው፤ በአገራችን የቀሽብርና ነጭ ሽብር መቅሰፍ የፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ በተለይ ለዓለም ሕዝቦች የስቃይና የብጥብጥ ችግሮች የሚኾኑት ለተወሰነ ሕዝብ የተለየ ጥቅም እናስገኛለን በሚሉ ፖለቲከኞች ነው፤ እነዚህ ፖለቲከኞች የአስተሳሰባቸው መነሻ ራሱ ችግር አለበት፤ ምክንያቱም ዕሳቤያቸው የሚነሣው የሰውን ልጅ በማክበር ሳይኾን በመገልበጥ የተወሰነ ቡድንንና አካባቢን የእነሱ ወገን ሲያደርግ፣ ሌላውን ተቃራኒ ተቀናቃኝ በማድረግ መድቦ ነው፤ በዚህም ሰውነትን የቡድን አገልጋይ ወይም መሣሪያ ያደርጉታል፡፡ በዚህ የተነሣም የሚወክሉትን ቡድን ለመጥቀም ሌላውን ሲጎዱ ሰብዓዊነትን ይሽራሉ፤ በዚያ ተቃራኒ ያለው ወገንተኛ ደግሞ በተመሳሳይ መብቴን ላስከብር በሚል ወደ መቀናቀን ይሄዳል፤ የዚህ ፍጥጫ ውጤቱም ብጥብጥ ይኾናል፤ የብጥብጡም ውጤት የጠላትነት መንፈስ ማጎልበት፣ ሲበዛም መተላለቅ ሊኾን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክም በዚህ መስተጋብር ያለፈ ነው፤ አሁን ባለንበት ጊዜ ችግሩን የበለጠ ያወሳሰበው የታሪክ መስተጋብሩ ሳይቀር በዚህ የፖለቲካ መነጽር የሚስተዋልና የሚሠራ መኾኑ ነው፡፡

መንግሥት የፖለቲካ ውጤት ነው፤ አሁን ባለንበት ዘመንና የሰው ልጆች የአኗኗር ደረጃ ለዓለምም ኾነ ለአንድ አገር መንግሥት ማስፈለጉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ዋናው የፖለቲካ ጩኸት የሚሰማው ግን በአገራት ዙሪያ ነው፡፡ የአገራትን መንግሥት መኖር አስፈላጊ በመኾኑ ላይ ስምምነት አለ፤ ዓለም በታሪክ ሂደት ይዞት የመጣው ልማድ የሚመሰክረው ይህንን ነው፡፡ በዚህ ልማድ ውስጥ ከመንግሥት ጋር የሚያያዙ ኹለት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡- ሕዝብና ሥርዓት፡፡ ስለዚህ ለአንድ አገር (1) ሕዝብ፣ (2) መንግሥት፣ (3) ሥርዓት ያስፈልጋታል፤ እነዚህ ሦስት ነገሮችም ያለ አገር የራሳቸው ህልውና ስለማይኖራቸው እርስ በራስ አንዱ ሁለቱን በአስፈላጊነት ይፈልጋቸዋል፤ ሦስቱም ተገናኝተው በመስማማት የሚኖሩበት አገርን እንደነበረ በመቁጠርና በሀገር ህልውና ላይ ጥያቄ ባለማንሳት ነው፤ ልክ አንድ ሰው ስለሚረግጠው መሬት ብዙም እንደማይጨነቀው፡፡

የመጀመሪያው (ሕዝብ) ሰፊና ለረዥም ዘመናት በቅጥልጥሎሽ እየተዋለደ የሚኖር ሲኾን፣ ኹለተኛው (መንግሥት)  በጊዜ ሒደት ዓይነቱን እየቀያየረ የሚኖር ነው፤ ሦስተኛው (ሥርዓት) የኹለቱ የሕዝብና መንግሥት ማስተሣሠሪያ ገመድ ወይም የግንኙት ኹኔታ ነው፡፡  ያለ ሕዝብ የሚቆም መንግሥት የለም፤ ሕዝብና መንግሥት የሚገናኙት ደግሞ በሥርዓት ነው፤ ‹ሥርዓት ከሌለው ብዙ ሕዝብ ሥርዓት ያላት ትንሽ ከተማ ብዙ ሙያ ትሠራለች› ይላሉ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፤ ስለዚህ መንግሥት ሕዝብን በሥርዓት የሚመራና መንገዱንም የሚያመቻች ተቋም ነው፤ ይህንን የሚያደርግበት ስልት ነው በሥርዓት የሚገለጸው፤ ስለዚህ ኹለቱም ሕዝብና መንግሥት በሥርዓት መመራት አለባቸው፤ ሥርዓት ያከብራሉ፤ ያስከብራሉ፤ በሥርዓቱ መሠረትም ግንኙነታቸው ይሠምራል፤ ሥረዓቱ በአንደኛው ተፅእኖ ውስጥ ሲገባ ወይም የአንደኛው ሚዛን ሲያይል ወይም ሲደክም አለመስማማትና ግጭቶች ይበዛሉ፡፡ እነዚህ ሦስት አስፈላጊ ነገሮች የተስማሙለት አገር ግን ሰላሙ የተጠበቀ፣ በልማት ጎዳና የሚጓዝ፣ የአንዱ ለሌላው በአስፈላጊነት የተናበበለት ይኾናል፡፡

የአንድ አገር ሕዝብ ሲባልም ቀላል ነገር አይደለም፤ የብዙ ቡድኖችና የፍላጎቶች ክምችትን የያዘ ነው፤ የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ባሕሎችና ታሪካዊ ዳራዎች ይኖሩታል፡፡ በሕዝብ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ቡድኖችም ይኖራሉ፤ አንድ ቡድን የተለየ ፍላጎት ያለው የጋራ ማንነት ነው፤ ከሌሎች ቡድኖች ፍላጎት ጋር የመስማማት ብቻ ሳይኾን ያለመስማማትም ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ የሰው ልጆች ቡድናዊ ህልውና ተፈጥሯዊ ነው፤ ከቤተሰብ ጀምሮ ያለው የቡድናዊ ማንነት መቅረጫ ልማድ ወሳኝነት አለው፤ ይህን ቡድናዊነትም ቤተሳባዊነት (በዘር)፣ ማኅበረሰባዊነት/ ብሔረሰባዊነት በቋንቋና በታሪክ መስተጋብር ወይም በሃይማኖት ይፈጥሩታሉ፡፡ ቤተሰባዊነት ከደም ጋር ይያያዛል፤ ብሔረሰባዊነት ደግሞ ከመግባባት ባህልና ከታሪክ መስተጋብር ጋር የተቆራኘ ነው፤ ሃይማኖታዊነት ደግሞ ከእዚህኛው ዓለም ባለፈ ያለውን የመኖር ተስፋ በአብሮ የመጋራት የተስፋ አስኳል በውስጡ አለው፡፡ ሰዎች ቡድናዊነትን የሚያጎለብቱ በጎ በማሰብ እንጂ ለክፋት አይደለም፤ ለምሳሌ አንድ ሰው የዘር ቡድን ወይም የቤተሰብ አባልነቱን የሚያጠነክረው ለወገኖቹ በመቆርቆር ነው፤ ወገኖቹን ከሥጋት ለመከላከልና ደኅንነቱን ለመጠበቅ ወይም እንዲጠበቅለት በመፈለግ ነው፤ ይህንን በአዎንታ ዕይታ ካየነው አስፈላጊና ጠቃሚ እንጂ ጎጅነቱ መሠረት አይኾንም፤ ጎጂ የኾነ ነገር ዘለቄታ አይኖረውምና፡፡ በቋንቋውም ቢኾን ከሚግባባው ሰው ጋር ቡድን መመሥረቱና በዚያም መኖሩ በጎ መነሻ አለው፤ ሃይማኖትም ሰዎች የሌላውን ዓለም ሕይወት ጭምር እንዲያገኙ በማሰብ የተፈጠረው ወይም አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው የሕይወት ማሻገሪያ ቡድንን የያዘ ተቋም ነው፤ ይህም እንኳን በዚህ ዓለም ለወዳኛው ዓለም ጭምር በሰዎች በማሰብ የሚደረግ ተቆርቋሪነት አለበት፡፡ ‹ይኸ ኹሉ የቡድናዊነት አመሠራረት በበጎ ከኾነ ለምን የሰው ልጅ ለግጭትና ለብጥብ ይዳረጋል?› የሚል ጥያቄ በውስጣችን መፈጠሩ አይቀርም፤ መልሱን ቀስ በቀስ እያገኘነው እንሄዳለን፡፡

የሰው ልጆች በየአኗኗር ልማዳቸውና ዕድገታቸው ያጎለበቷቸውና የያዟቸው ብዙ የአኗኗር ዘይቤዎች አሉ፤ የዕውቀት ክምችት፣ የማኅበረሰብ ልማድ ጠባቂነት፣ የታሪክ ትርክት፣ የቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ቅጥልጥሎሽ፣… አሏቸው፡፡ በዚህም ውስጥ ‹የእኔ› ወይም ‹የእኛ› የሚሉትን ለመጠበቅ የራስን እንደ ብቸኛ እውነት፣ የሌሎች ደግሞ እንደ ሐሰትና እንደማይረባ ነገር አድርገው የመውሰድ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ የአስተሳሰቡ መሠረት የራስ የሚሉትን መልካም የአኗኗር ዘይቤ መጠበቅና ማቆየት ቢኖርበትም የሌሎችን በራስ መነጽር አለማየት ወይም በሌሎችም ዘንድ ሌላ እውነት ሊኖር ይችላል ብሎ ያለማሰብ ችግርም አለበት፡፡ በዚህ መነጽር ማየቱ ብቻ ሳይኾን የራስን ቡድን ባህልና ወግ ክብር ሲሰጡ የበላይ አድርጎ ዝናን ለማጎናፀፍ የሚደረግም ምኞት አብሮ ይኖራል፤ በዚያ ላይ ከአእምሯቸው ይልቅ ክንዳቸው የሚፈጥን ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፤ የእነሱም የማኅበረሰብ መከታነት ሌሎችን በማሸነፍ ላይ ይመሠረታል፤ ይህም አጸፋን ከሌሎች ሲያጋጥመው ግጭትና ብጥብጥ ይከሰታል፡፡ በዚያ ላይ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ የመግባቢያ ቋንቋና የሃይማኖት መለያየት ሊኖርበት ይችላል፤ እንዲሁም የሀብት አለመመጣጠንም በሕዝቦቹ ወይም በግለሰቦቹ መካከል መፈጠሩም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ ኹሉ ሥርዓት ሚዛኑን ካልጠበቀው ከጉልበተኞች የጡንቻ አስተሳሰብ ጋር ተዋሕዶ ግጭትና ብጥብጥን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ስለዚህ ሕዝብ ስንል ይህንን ኹሉ ልዩነት አካቶ የያዘ ነው፤ እነዚህ ልዩነቶች ለማጣጣም ብዙ ብልሃትና ትግዕሥት ይጠይቃል፤ መንግሥትና ሥርዓት ያስፈለጉትም እነዚህን ልዩነቶች ለማጣጣም ነው፡፡ ለምሳሌ በአገሩ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች ፍላጎታቸው ከመለያየቱ የተነሣ አንዱ ከሌላው ጋር ላይስማማ፣ ከዚያም ባለፈ ሊቃረንና ሊያጣላቸው ይችላል፤ የትኛውም ቡድን የእሱ ፍላጎት በተለየ እንዲጠበቅለትና እንዲሟላለት ይፈልጋል፤ የአንዱ ፍላጎት መሟላትም የሌላውን ቡድን ፍላጎት ሲጎዳ በመስተጋብሩ አለመጣጣም ይፈጠራል፡፡ የአንዱ ባህልም ከሌላው ጋር ተቃራኒ ከመኾኑ ጋር ተያይዞም የቡድኖች ፉክክር ይኖራል፤ አለመስማማትም እንደዚሁ፤ ኹሉም ቡድን የራሱ ባህል የበላይ እንዲኾንለት ይፈልጋል፤ ይህ በአንድነት ላይ የሚፈጥረው ጫና አለ፤ ስለዚህ ይህን የባህል ተጽዕኖዊ መስተጋብር አጣጥሞና አስማምቶ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰባት ታሪካዊ ዳራቸው የተለያየና ምናልባትም አንዱ ሌላውን በማጥቃትና በጦርነት በተፈጠረ መቆራቆስ የተፈጠረ የታሪክ ዳራ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንዲሁም በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰባት የተለያዩ ቋንቋዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፤ በተለይ እነዚህን ቋንቋዎች የሚያስተሣሥር የጋራ የኾነ መግባቢያ ከሌላቸው ከመግባባት ይልቅ መለያየትን መፍጠር ይቀላቸዋል፤ በመለያየት ውስጥ ደግሞ ቢያንስ መቆራቆስ ይኖራል፡፡ በተጨማሪም የሃይማኖት ልዩነት እየሰፋ መሔድና የፉክክርነት መንፈስን መዳበር የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖም ከፍተኛ ነው፤ በተለይ ሃይማኖት የወገናዊነት ስሜቱ ጥልቅ፣ ዕሳቤ ሰፊ፣ ዕይታውም ተሻጋሪ ስለኾነ ጠብና አለመስማማቱም የከረረ የመኾን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በዜጎችና በቡድኖች መካከል የሚኖርና የሚፈጠር የሀብት ልዩነትም ማኅበረ መስተጋብሩን ሊጎዳው መቻሉ የማይስተባበል እውነት ነው፡፡ ስለዚህ የአንድ አገር ሕዝብ ስንል የእነዚህ ልዩነቶችና ማንነቶች መስተጋብርን የያዘ የሕዝብ/ቦች ስብስብ ነው፡፡

እነዚህን የተወሳሰቡና የተለያዩ ማንነቶችና መገለጫዎች ጠብቆና አስማምቶ ማስተዳደር እንዲቻል ነው መንግሥት የተፈጠረው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው መንግሥት ከኾነም ይህ አካል የሕዝቦችን የጋራ ማንነት ጠብቆና መስተጋብሩን አስተባብሮ በማስማማት የሚያኖር አካል/ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ሥርዓታዊ ተቋም አመሠራረትም እንደ ሕዝቡ ባህል፣ ታሪክ፣ ልማድና አስተሳሰብ ይለያያል፡፡ መንግሥት አንድም በሕዝብ ፍላጎት የማስተዳደር ፈቃድ ያገኘ አካል ሊኾን ይገባል፤ አንድም በኃይልና በጉልበት የሕዝቡን ፍላጎት ለማስተዳደር የተደራጀ አካል ሊኾን ይችላል፤ አንድም በታሪክ የመግዛትና የማስተዳደር ኃላፊነትና ፈቃድ የተሰጠን ነን የሚሉ ሰዎች በዘር እየተወራረሱ የሚመሩበት ሥርዓታዊ ተቋም ሊኾን ይችላል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹የሕዝብ ነን› ሲሉ እኩዩንም ኾነ በጎውን ሲሠሩ በሕዝብ ፈቃድ ያላክካሉ፤ ‹ሕዝቡ› ማለት መገለጫቸው ነው፤ ለዚህም በሕዝቡ ዘንድ በአግባቡ ትርጉማቸው የማይታወቁ ‹ዴሞክራሲ›፣ ‹ሪፐብሊክ› የመሰሉ ስያሜዎች ሽፋን ኾነዋቸው ይሠራሉ፡፡ ኹለተኞቹ ‹ጨፍልቀው›፣ ‹ቁረጠው›፣ ‹ፍለጠው›፣… የሚሉና የራሳቸውን ፍላጎትና አስተሳሰብ በሌላው ላይ በመጫን አድራጊ፣ ፈጣሪ የሚኾኑ ሰዎች የተሰበሰቡባቸው ናቸው፤ በእነዚህ የአስተዳደር ሥርዓት ሕዝብ ውስጥ ለውስጥ ያማል እንጂ በግልጽ የመቃወምና ሐሳቡን የመግለጽ መብቱ ሲበዛ ውስን ነው፤ ስለኾነም ‹አንባገነን› ይሏቸዋል፤ ‹አንባ ላይ ገናና› ወይም ‹የኹሉም የባላይ ነኝ ባይ› እንደማለት ነው፡፡ ሦስተኞቹ የማስተዳደር ሥርዓትን ከዘርና ከሃይማኖት ጋር በመያያዝ ‹ባለመብት ነን› የሚሉ ናቸው፤ እነዚህም ሃይማኖት ማደንዘዣቸውና መሸፈኛቸው፣ በዘር የመግዛት ልማድ የሞራል ኃይላቸው ይኾኗቸዋል፤ ሕዝቡም በልማድ ስለሚታሠር ተስማምቶ የመተዳደር ባሕልን ሊያዳብር ይችላል፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥት ዓይነቶች ‹መንግሥት ሕዝብን በሥርዓት እንዴት ይምራ?› በሚል አስተሳሰብ ላይ የሚፈጠር ልዩነት የሚለያያቸው ናቸው፤ የትኛው ይሻላል ቢባል ለሕዝቡ የሚጠቅመው መባሉ የማይቀር ነው፤ ችግሩ ግን አንዱ ሌላውን እየኮነነ ኹሉም ‹ጠቃሚ እኔ ነኝ› የሚል መኾኑ ነው፡፡ የመንግሥቱን ጥሩነትና ጠቃሚነት የሚያስተዳድርበት ሥርዓት ይወስነዋል፡፡

ሥርዓት የምንለው በጥቅሉ የአስተዳደር ሥርዓት ሲኾን ሲዘረዘር ግን ካስተዳደርም ያልፋል፡- የሕዝቡን ሥነ ልቦናዊ ዳራ፣ ባህል፣ ታሪካዊ ዕድገት፣ የሃይማኖት አስተሳሰብ፣… ያካተተና ያጣጣመ መኾንን ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንድ ሥርዓት ከሕዝቡ ሥነ ልቦና ጋር የሚስማማ፣ ባህሉን የጠበቀ፣ የማኅበረሰቡን ታሪካዊ አመጣጥ ያገናዘበና ያስማማ፣ ከሃይማኖቱና ከልማዱ ጋር የማይጋጭና የተስማማ መኾን ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ከአገሪቱ ሕዝቦች ውጭ ያሉ ማኅበረሰቦችን ሥርዓቶች ያገናዘበ ሲኾን የበለጠ ተስማሚና ጠቃሚ የመኾን ዕድሉ ይጨምራል፡፡ በዚህ መስተጋበር የሚሠራው ሥርዓት ማጠንጠኛው ሕግና ፍትሕ የጠበቀ እና በመልካምነት የተቃኘ  መኾን አለበት፤ በሕጉ ቁጥጥር ይደረጋል፣ በፍትሑ ደግሞ እኩልነትና አግባባዊነት ይሠራል፤ በመልካምነቱም በጎነት ይጠበቃል፣ ጠቃሚ ተግባራትም እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች የተስማሙለት አገር መንግሥቱ መልካም፣ ሥርዓቱ ከሕዝቡ ሥነ ልቦናና ባህል ጋር የተስማማ ይኾናል፡፡ የኢትዮጵያ ኹኔታ ምን ይመስላል? (ይቆየን! ያቆየን! ይቀጥላል…)

Please follow and like us:
error

Leave a Reply