ሙግት በእግዚአብሔር ጠባያት

(በካሣሁን ዓለሙ)

(ማስታወሻ፡- ከዚህ በፊት በሀልዎተ-እግዚአብሔር ዙሪያ በሻይ ቤት የተደረገ ሙግት በሚል ርዕስ ከአንድ ኢ-አማኝ ጋር ባደርግነው ውይይት ባለመግባባታችን ተለያይተን እንደነበር፤ ከዚያም  በኢ-ሜይል አድራሻዬ እግዚአብሔር በምን እንደሚታወቅ እንድጽፍለት ጠይቆኝ ጠባያተ-እግዚአብሔር በሚል ርዕስ የጻፍኩትን የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት እንደላኩለት ገልጬ ነበር፡፡ ከዚያም በኢ-ሜይል በእግዚአብሔር ጠባያት ዙሪያ ያደረግናቸውን ሙግቶች ለማቅረብ ቃል በገባሁት መሠረት በአንድነት ሰብስቤ አቅርቢያቸዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ጽሑፍ ረዥም እንደሆነ ቢሰማኝም፤ ከሚቆራረጥ አሳቡን ለማያያዝ በአንድ ላይ ቢሆን የተሻለ ስለመሰለኝ ነው፡፡ መልካም ንባብ!)

                እሱ፡-

ያ ወዳጄም የላኩለትን ጽሑፍ ካነበበ በኋላ በመልስ ደብዳቤው “የጻፍክልኝ የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት እርስ በርሳቸው የሚምታቱ (የሚጣረሱ) እና አሳማኝነት የሌላቸው ናቸው፡፡” አለኝ፡፡

                እኔ፡-

እኔም አለመኾናቸውን ለማስረዳት “‹የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያትን ‹ትክክል ናቸው›  ብለን ካልተቀበልንማ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለየትኛውም ነገር ማውራትና መናገርም አንችልም፡፡ ባለፈው እንደገለፅኩልህ ቋሚ የኾኑ ሕጎችን በመሠረታዊነት “ትክክል” ብሎ መቀበል በየትኛውም የዕውቀት ዘርፍ የተለመደ መነሻ ነው፡፡ እስቲ ቆይ ልጠይቅህ ቋሚ የኾኑ መሠረታዊ ህግጋት (postulate or axiom) የሌሉት የዕውቀት ዘርፍ አለ? አለ ለማለት የምትደፍር አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የትኛውም ዕውቀት በመሠረታዊ ሕግ (postulate) ላይ ይመሠረታልና፡፡ ከሌለ ደግሞ ለምን ታዲያ ከውቅያኖስ የሰፉትንና የጠለቁትን የእግዚአብሔር ጠባያት በዶግማነት “ትክክል ናቸው” በማለት አንቀበላቸውም?”  ብዬ የመልስ ጽሑፍ ላኩለት፡፡

                እሱ፡-

እሱም “አትሳሳት በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች ‹መሠረታዊ ሕግጋት›  (postulate) በመኾን የሚወሰዱት ምንም ጥያቄ የማይነሳባቸው ሲኾኑ ነው እንጂ እርስ በርሳቸው በተቃርኖ የተሞሉ ኾነው አሳማኝነት የሌላቸው ከኾኑ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ አንተ ጽፈህ የላክልኝ የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ደግሞ የትኞቹም አሳማኝነት የሌላቸው ፣ በጥያቄ የተከበቡና እርስ በራሳቸው የሚጋጩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው ፣ ዘላለማዊ ነው፣ ኹሉን ያውቃል፣ ወዘተ እያልክ ጽፈህልኛል፡፡ ለመኾኑ እግዚአብሔር ዘላለማዊ አምላክ ከኾነ እንዴት ዘላለማዊነት የሌለውና የሚጠፋ ፍጥረት ፈጠረ? ዘላለማዊነቱንስ እንዴት ዐወቅን? ምናልባት መልስህን በፍጥረቱ እንዳትል ፍጥረቱ ዘላለማዊ አይደለም ብለኻል፡፡ ከፍጥረቱ ውጭ ባለ አካል ካልክም እኛ ፍጡራን አይደለንም ወይ? እንዴት ከፍጥረቱ ውጭ የሚገኝ አካል ሊያሳውቀን ቻለ? ከፍጥረቱ ውጭ ያለውን የእግዚአብሔር ጠባያት (ዘላለማዊነት ፣ ኹሉን አዋቂነት ፣ ፈጣሪነት….) ሌላ አካል ነገረን የምንል ከኾነ ሌላ እግዚአብሔር አለ ማለታችን ነው?”

           እኔ፡-

 “ከጥያቄዎችህ መረዳት የቻልኩት የአንተን የመረዳት ችግር እንጂ የእግዚአብሔርን ጠባያት መምታታት አይደለም፡፡ የጻፍኩልህን የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት በማስተዋል ማገናዘብ ሲያቅትህ ወይም በፊት ስለ እግዚአብሔር ከጠጣኸው የአጉል ፍልስፍናና የክህደት ማጥ ውስጥ መውጣት ሲሳንህ በዚያው ታንቀህ ግራ ከምትጋባ በነጻ አእምሮ ሁንና አስተውለህ መርምራቸው፡፡ ልብ አድርግ ኹሉም ጠባያቱ የእግዚአብሔርን ፍጽምና ይመሰክራሉ ፤ ኹሉም ጠባያቱ በከሀሊነቱ ውስጥ ይካተታሉ እንጂ አይቃረኑም፡፡ ወደ ጥያቄዎችህ ልግባና፡፡

“‹እግዚአብሔር ዘላለማዊ አምላክ ከኾነ እንዴት ዘላለማዊነት የሌለውና የሚጠፋፋ ፍጥረት ፈጠረ? የእሱን ዘላለማዊነትስ እንዴት ማወቅ ቻልን?› የሚሉ ጥያቄዎች ጠይቀኸኛል፡፡ ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር ኹሉንም ፍጥረት ዘላለማዊ አድርጎ በሌላ እግዚአብሔርነት ለምን አልፈጠረውም ነው? የፍጥረቱ በጊዜ ወሰን ውስጥ መፈጠር ከእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ጋር ይጋጫል ነው? እንደተረዳሁህ ከኾነ የእግዚአብሔርን ጠባያት ከፍጥረት ጋር የማምታታት ችግር አለብህ፡፡ ስለኾነም ወይ ቀድመህም እግዚአብሔር ከፍጥረት ጋር በጊዜ ገደብ ውስጥ ተገኝቷል ብለህ ገምተሃል ወይም የእግዚአብሔርን ጠባያት መለየት አልቻልክም፡፡ በዚህ የተነሳ ከዓለመ-ፍጥረቱ መገኘት በፊት ፈጣሪ ይኖራል ለማለት ተቸግረሃል፡፡ በአጠቃላይ ስለ ፍጥረት ስናወራ ግን ስለ ኹለት ነገሮች እየተናገርን መኾኑን አስተውል፡፡ ፍጥረት ማለት ራሱ ተፈጣሪ ወይም የተሠራ ፣ ሥሪት ማለታችን ነው፡፡ ይህም ተደራጊነትን ይገልጻል፡፡ ተፈጣሪ ወይም ተሠሪ ነገር ባለበት ደግሞ የፈጣሪ አድራጊነት ወይም ሠሪነት መኖሩ የግድ ነው፡፡ ስለኾነም በተደራጊው አካል ወይም ነገር ውስጥ አድራጊውንም እያወራን ነው ማለት ነው፡፡ በዚህም የፈጣሪንና የተፈጣሪን ልዩነት መረዳት ይቻላል:: ይህንን ልዩነት ከተረዳህም “ዘላለማዊ አምላክ ኾኖ እንዴት ዘላለማዊ ያልኾነ ፍጥረትን ፈጣረ?” የሚለው ጥያቄህ የስንፍና ጥያቄ መኾኑ ይገባሃል፡፡ አስቸጋሪ የሚኾነውም በጊዜ ገደብ ተይዞ ዘላለማዊ ነገር ማስገኘት ወይም የራስን እኩያ ነገር መፍጠር ነው እንጂ ዘላለማዊ ኾኖ ዘላለማዊነት የሌለው ፍጥረት መፍጠር ምክንያታዊ የኾነ የፈጣሪነትና የፍጡራን ልዩነት መታወቂያ ነው፡፡ በመኾኑም የፍጥረቱ በጊዜ ገደብ ውስጥ መፈጠር ከእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ጋር አይጋጭም፡፡ የእግዚአብሔርን ከሀሊነት (ሀሉን ቻይነት) ይመሰክራል እንጂ!

“‹በፍጡርነት በጊዜ ተወስነን እንዴት የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ማወቅ ቻልን?› ላልከው የእግዚአብሔር ጠባያት እሱነቱን የምናውቅባቸው ፊደላት ናቸው፡፡ እሱነቱን አንብበን እንረዳባቸዋለን፡፡ እነሱም የሚገለጹት በፍጥረቱ ነው፡፡ ፍጥረቱን “ፍጽምናህ የት ጋር ነው?” ብለን ስንጠይቅ የእግዚአብሔር ጠባያት ጋር ይወስደናል፡፡ ይህንንም በኹለት ዓይነት መንገዶች ማወቅ እንችላለን፡፡

“እንደምናውቀው የሰው ልጅ አዕምሮ ያለው ፍጡር ስለኾነ የቻለውን ያህል ይመራመራል፤ እስከቻለው ይጠይቃል፤ የመሰለውንም መልስ ይሰጣል፡፡ የሰው ልጅ በሚያደርገው አስተውሎታዊ ምርምርም የፍጥረትን ምንነት ፣ ህልውና እና ከጊዜ ጋር ያለውን ግንኙነት ይፈትሻል፡፡ በዚህም አንድ የኾነ ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡ የፍጥረቱን አኗኗርና ከጊዜ ጋር ያለውን ማስተጋብራዊ ግንኙነት ሲያጠናም ፍጥረቱ በጊዜ እንደሚገደብ እና ኹለቱ እንደማይለያዩ ማወቅ ይችላል፡፡ እንዲሁም ከፍጥረት ግድግዳ ወሰን በማለፍም አስገኚ ይኖረው ይኾናል በማለት እንዲገምት ይገፋፋል፡፡ እንደገናም አስገኚ ካለው ‹አስገኚው  በጊዜ የተገደበ ይኾን ያልተገደበ?› ወደሚል እሳቤ ይወስደዋል፡፡ በጊዜ የተገደበ ይኾናል የሚለው መልስ አሳማኝነት ስለማይኖረው ዘላለማዊ የኾነ መኾን አለበት የሚለው ግምቱ የተሻለ ኾኖ ያገኘዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አስገኚው ከፍጥረት ተለይቶ ለብቻው በተወሰነ ሥፍራ የሚገኝ ይኾን ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ኾኖም ይህ ግምቱ ስለማያስኬደው ፍጥረቱን ያስገኘ አካል ጠባቂውም መኾን አለበት ወደሚል ግምት ይወስደዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ሌሎች ጥያቄዎችንም እየጨመረ ሊመራመርና ከገመትነው አቅጣጫ በተቀራኒውም ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‹ፍጥረቱን ፈጥሮ ለእኛም አእምሮ ጠባይዕ ሰጥቶ እንድንመራመር ካደረገን በአብዛኛው መልሱን በትክክል ላላገኘናቸው ጥያቄዎች ራሱ መልስ የማይሰጠን ለምንድነው?› የሚል ጥያቄን በመጠየቅ ሊጨነቅ ይችላል፡፡ ለዚህ መልስ የሚኾነው ደግሞ የፈጣሪ መገለጽ ነው፡፡ ይህም ወደ ኹለተኛው የእግዚአብሔርን ማንነትና ሥራ ማወቂያ መንገድ ይወስደናል፡፡

“እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያለው በሕግና ሥርዓት እያስተዳደረ የሚኖር በመኾኑ ራሱን በተለያየ መንገድ ለፍጥረቱ ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ በራዕይ ፣ በህልም ፣ በተለያዩ ፍጥረቶች ላይ በመታየትና በመሳሰሉት ራሱን ለሰው ልጆች ይገልጣል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ለተወሰኑ ሰዎች ራሱን ገልጾ ስለ እራሱ ማንነትና ፣ ፍጥረትን መፍጠርና እየጠበቀ በሥርዓት ማስተዳደር የሚገለፁ መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲመዘገቡ ማድረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ ዓለመ-ፍጥረቱን ስለመፍጠሩ ‹እግዚአብሔር በመጀመሪያው ቀን ሰማይና ምድርን ፈጣረ፡፡› ተብሎ ተገልጻል፡፡ ይህም ጊዜና ሥፍራ በአንድነት መፈጠራቸውን እሱ ግን የእነዚህ ክስተቶች አድራጊ ስለኾነ ከእነሱ በላይ መኾኑን ያስረዳናል፡፡ በዚህም በራሳችን ምርምር ብቻ ተጉዘን ማግኘት የማንችለውን መልስ ነግሮ አሳመነን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስለእግዚአብሔር ዘላለማዊነትና ፈጣሪነት በአእምሯችን የማሰብ አቅም ተጠቅመን እንገምታለን በእሱው ገላጭነት ደግሞ እንገነዘባለን፡፡ ከእነዚህ ውጭ ደግሞ ሌላ ልናውቅበት የምንችል መንገድ የለም፡፡

“ስለኾነም ወንድሜ የመገንዘብ አቅም ውሰንነትና የመረዳት ችግር ስላለብን የእግዚአብሔርን ጠባያት እርስ በርስ እናጋጫቸዋለን እንጂ መሠረታቸው አንድ ከሀሊነት ስለኾነ አይጣረሱም፡፡ በመኾኑም በጠባያቱ ትክክልነት ተስማምተን በፍጥረቱ አኗኗርና ሥነ-ሥርዓት ኹኔታ ላይ ብንወያይ ይሻላል፡፡››

              እሱ፡-

“አይደለም፡፡ በመጀመሪያ እርስ በራሳቸው የማይስማሙና ተቀባይነት የሌላቸው ጠባያትን በትክክልነት በማመን ብቻ ተቀበሉ ማለት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አታስቡ እመኑ ብቻ ማለት ይመስላል፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ደግሞ እኛ ስለፈለግን ብቻ ትክክል አይኾኑም፡፡ እርስ በርስ የሚቃረኑ ከኾነም ምንም ብንላቸው መጋጨታቸው አይቀርም፡፡ መጋጨታቸውን ደግሞ በግልፅ እያየን ነው፡፡ እስቲ የተወሰኑትን በማሳያነት እንመለከታቸው፡፡

“እግዚአብሔር ኹሉንም ነገር ፈጥሯል ማለትና ኹሉንም ያውቃል ማለት የሚጋጩ ገለጻዎች ናቸው፡፡ ከቅድስናው ጋርም ይቃረናሉ፡፡ እንበልና እግዚአብሔር ኹሉንም ነገር የፈጠረ ነው ካልን መልካሙንም ኾነ መጥፎውን የፈጠረው እሱ ነው ማለታችን ነው፡፡ መጥፎውን ነገር ደግሞ የፈጠረው እያወቀ ነው መባሉ የእሱን ባህርያዊ ጠባያት እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡ እንዴት እያወቀ መጥፎ ነገርን ይሠራል? ይህንን መቼም ሕጻን ልጅም አያደርገውም፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ቅዱስና ትክክለኛ ፈራጅ ነው መባሉ የበለጠ ችግርን ይጎለጉላል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚኾነን የአዳም ታሪክ ነው፡፡

“እንደሚባለው ከኾነ እግዚአብሔር አዳምን በገነት ፈጥሮ ሲያኖረው አንዲት ዕፀ በለስን እንዳይበላ ከመከልከል ያለፈ የፈጠረው መጥፎ የኾነ ዲያብሎስ የሚባል ፍጡር መኖሩን አልነገረውም፡፡ ዲያብሎስንም አዳምን እንዳያሳስት አልከለከለውም፡፡ አዳም ግን በዚህ ፍጡር (በዲያብሎስ) ተታሎ እንደሚሳሳትና የሞት ፍርድም እንደሚፈረድበት እግዚአብሔር ያውቅ ነበር፡፡ ይህንን እንግዲህ ምን እንበለው? ትክክለኛ ፍርድ? በመጀመሪያ መጥፎ የኾነ ዲያብሎስን ፈጠረ፤ አዳምን እንደፈለገ እንዲያስተውም ተወው፡፡ አዳምን ፈጥሮ ግን በሕግ አሠረው፡፡ ከዚያም ዲያብሎስ አታሎ ሲያስተው ግን በአዳም ላይ ፈረደበት፡፡ ከኹሉም የሚገርመው ደግሞ ይህ ኹሉ እንደሚኾን እግዚአብሔር ኹለቱንም ሳይፈጥራቸው በፊት ጀምሮ የሚያውቅ መኾኑ ነው፡፡ እና እያውቀ የተሳሳተው ማን ነው? እግዚአብሔር ወይስ አዳም? አዳም ለእግዚአብሔርና ለዲያብሎስ ኳሳቸው (አሻንጉሊታቸው) ነው እንዴ አንዱ አሳሳች ሌላው ተሳስተሃል በማለት ፈራጅ በመኾን የሚጫወቱበት? ይህ ዓይነት የእግዚአብሔር ሥራ የድመት ጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ምን ይባላል የጠገበች ድመት አይጥ ተያዘች አትበላትም፤ ኾኖም ግን አይኗን አውጥታ ሜዳ ላይ በመልቀቅ እያራወጠች ትጫወትባታለች፡፡ ይህም ከዚያ አይሻልም፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔር ቅድስና የሚታወቀው እርኩስ ዲያብሎስን በመፍጠር ነው እንዴ? ከፈጠረውስ ለምን አላጠፋውም? በእሱ እርኩስነት የሰው ልጅ ለምን ይሰቃያል? ዲያብሎስ በእርኩሰቱና በክፋቱ እንዲኖር ከፈቀደለት እንዴት ኾኖ ፈቃዱ ከፈጣሪነቱ ፣ ኃያልነቱ ፣ ኹሉን አዋቂነቱ ፣ ኹሉም ሥፍራ መገኘት መቻሉ ፣ ትክክለኛ ፈራጅነቱና ቅድስናው ጋር ይስማማል?

“እነዚህ ኹሉ የዘረዘርኩልህ ጥያቄዎች የሚያሳዩት የእግዚአብሔርን ጠባያት አለመስማማት ነው፡፡ ካልተስማሙ ደግሞ ትክክል አይደሉም ማለት ነው፡፡ ትክክል ያልኾኑትንም ማንኛውም ሰው “ትክክል ናቸው” በማለት መቀበል የለበትም፡፡ ስለኾነም ብትችል አንተም ይህንን ስህተት ሲባዛ ስህተት እኩል ይኾናል ትክክል የመሰለ አቀራረብከን ብታስተካክል ጥሩ ነው፡፡”

          እኔ፡-

 “የእግዚአብሔርን ጠባያት ለማጋጨት መጣርህ ይገርማል፡፡ ይህንን ያህል ለማጋጨት ከምትጥር ‹ከፍጥረቱ በስተጀርባ ምን ይገኛል?› በማለት ለመጠየቅ ብትሞክር የእግዚአብሔርን ፍጹማዊ ጠባያት ከፍጥረታት የአኗኗር ኹኔታ ጋር እያምታታህ ለማጣረስ አትጨነቅም ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፣ ኹሉን አዋቂነት ፣ ትክክለኛ ፈራጅነትና ቅድስና ያጋጨው የዕይታህ ውስንነትና የመልካም እሳቤ ችግርህ ነው እንጂ በትክክልም የእግዚአብሔርን ማንነት ለማሳየት የሚረዳ የእሱነቱ መገለጫዎች መኾናቸው ግልጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው ስንልም ኹሉንም የፈጠረው በሕግና ሥርዓት አድርጎ ነው ማለታችን ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ኹሉንም በማወቅ ነው፡፡ በዚህ ሕግና ሥርዓት መሠረትም ፍጥረቱ ተዋዶና ተያይዞ ይኖራል፡፡ ፍጥረቱ የተሠራለት ሕግና ሥርዓትም በገደብ ውስጥ ስለኾነ ያንን ሲተላለፍ ቅጣት ያገኘዋል፡፡ ምክንያቱም ከሚኖርበት ተፈጥሮ ውጭ ያለው የእሱ አይደለምና፡፡ ለምሳሌ ሰው በውሃ ውስጥ እየዋኘ ወይም በእሳት ውስጥ እየተቃጠለ መኖር አይችልም፡፡ ዓሣም በየብስ ላይ እየተራመደና እየዘለለ መኖር አይችልም፡፡ ሰውም ኾነ ዓሣ ከተሠራላቸው የአኗኗር ተፈጥሮ ዝንፍ ሳይሉ ይኖራሉ፡፡ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓትምም እንደ ፍጥረቱ የተለያየ ነው፡፡

“እስቲ የሰጠኸውን የዲያብሎስንና የአዳምን ምሳሌም እንመልከተው፡፡ በእነሱ ዙሪያ ያነሣኸቸው ጥያቄዎች ‹እግዚአብሔር ዲያብሎስ አዳምን እንደሚያስተው ፣ አዳምም እንደሚሳሳት እያወቀ ለምን ፈጠራቸው? ዲያብሎስንስ አዳምን ሲያሳስተው እያወቀ ለምን ዝም አለው? ለምንስ ዳቢሎስን አላጠፈው? ዲያብሎስ እርኩስ ከኾነ እንዴት በቅዱሱ እግዚአብሔር ተፈጠረ? ወዘተ›  የሚሉ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹንም እንመርምራቸው፡፡

በመጀመሪያ ግን እግዚአብሔር የሚሳሳት ፍጥረት አዳምንም ኾነ ዲያብሎስን መፍጠር የለበትም ማለት የራሱ ችግር እንዳለበት መገንዘብ አለብን፡፡ አንደኛ የሚሳሳት ፍጥረት መፍጠር አልነበረበትም ማለት እንደ ራሱ እግዚአብሔር ፍጹም የኾነ ወይም ኅሊና አልባ ፍጥረት ብቻ መፍጠር ነበረበት ማለትን ይገልጻል፡፡ ይህ ደግሞ አያስኬድም፡፡ ኹለተኛ እግዚአብሔር ፍጥረቱን በሕግና ሥርዓት ፈጥሮ ማስተዳደር የለበትም የሚል አንድምታን ያሰማል፡፡ ፍጥረት የኾነ ኹሉ ደግሞ የሕግና ሥርዓት ገደብ አለበት፡፡ ከገደቡ በሚወጣ ሰዓትም ስህተት ይሠራል፡፡ ሦስተኛ እግዚአብሔር አእምሮ ላላቸው ፍጥረቶች ነፃ ፈቃድ መስጠት አልነበረበትም የሚል አስተሳሰብ አለበት፡፡ ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት ግን ምርጫ አለው፡፡ በምርጫውም ስህተት ሊፈጽም ይችላል፡፡ በመኾኑም የማይሳሳት ፍጥረትን ብቻ መፍጠር የሚለው ዕይታ የፍጥረታትን በሕግና ሥርዓት መፈጠራቸውን ያላስተዋለ የአዕምሮ ጠባይ ላላቸው ለሰውና መልአክት ደግሞ ነፃ ፈቃዳቸውን የሚያሳጣ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአዳምና የዲያብሎስ መሳሳትም የሚያያዘው በፈቃዳቸው ሕግና ሥርዓትን ከመጣስ ጋር ነው፡፡

‹የዲያብሎስን አፈጣጠር በተመለከተ እርኩስ ኾኖ በእግዚአብሔር እንዳልተፈጠረ ፣ እግዚአብሔር በሕግና ሥርዓት አክብሮ ፈጥሮት  እንደነበርና ዲያብሎስ ግን በምርጫው ሕግ ስለተላለፈ የተፈጠረበትን ቅድስና እንዳጣ ይተረካል፡፡ ይህም ማለት የዲያብሎስ እርኩሰት የተፈጠረበትን ቅድስና ማጣት እንጂ ሲፈጠር ጀምሮ በእርኩሰት የተሠራ ፍጡር አልነበረም ማለት ነው፡፡ በመኾኑም የዲያብሎስ እርኩስነት በነፃ ፈቃዱ ተጠቅሞ የተሠራለትን የሞራል ሕግና ሥርዓት ተላልፎ መኖር ነው፡፡

‹የአዳምም ቢኾን የሕግና ሥርዓት መተላለፍ ኹኔታና ደረጃው ይለያያል እንጂ ከዲያብሎስ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አዳምም የተፈጠረው ዐዋቂ ተደርጎ ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረው ሕግና ሥርዓት ሰርቶ ዕውቀትና ነፃ ፈቃድ ሰጥቶ ነው፡፡ ለዚህም የፈለገውን መርጦ መፈጸሙ ምስክር ነው፡፡

‹እዚህ ላይም ያነሳኻቸውን ጥያቄዎች እንመልከታቸው፡፡ ጥያቄዎችህም ‹ዲያብሎስ አዳምን ሲያስተው ለምን ዝም አለው? ለምን ዲያቢሎስን አላጠፋውም? ሌላው ሲያሳስተው እያየ ዝም ማለቱ ትክክል ነው እንዴት ይባላል?› የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ ግን አዳምን ዕውቀትና ፈቃድ አልባ ያስመስለዋል፡፡ ለአዳም ሕግና ሥርዓት ሠርቶ ሰጥቶት የለም እንዴ? ዲያብሎስን መከልከል ለምን ያስፈልጋል? አዳም የፈጠረው እግዚአብሔር መኾኑን አውቆ የለም ወይ? ዕፀ በለሷን እንዳይበላ የሚያግደው ሕግ እኮ የሰጠው ሊያመጣበት የሚችለውን ችግር ጭምር በመግለጽ ነው፡፡

“ይህንን ጉዳይ አስተውለን በማየት መረዳት አለብን፡፡ አዳም እኮ የተሳሳተው በነጻ ፈቃዱ በመጠቀም ከተነገረው የማስጠንቀቂያ የአምላክ ቃል (ሕግ) ይልቅ የሌላ የማያውቀውን የዲያብሎስን ምክር ሰምቶ በመምረጥ ይሁንብኝ በማለት ነው፡፡ በዚህ ጥፋቱ ዋና ተጠያቂው አዳም ራሱ እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ዲያብሎስም ቢኾን ለአዳም የሰጠው አማራጭ ምክር እንጂ የማስገደድ ሥራ አይደለም፡፡ በአስገዳጅነት ቢኾን እንኳን አዳም ዕውቀትና አቅም አንሶት በመሸነፍ ተሳሳተ ይባል ነበር፡፡ አዳም ግን የአምላኩ የማስጠንቀቂያ ትእዛዝ አቅም ኾኖ ሊረዳው ይችል ነበር፡፡ በመኾኑም ድርጊቱን የፈጸመው የአምላኩን ማስጠንቀቂያ አቃሎና ንቆ የዲያብሎስን ምክር ግን አክብሮ በመምረጥ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ ራሱ እንጂ እግዚአብሔር ወይም ሌላ አካል ሊኾን አይችልም፡፡ ቆይ! እግዚአብሔር ነፃ ፈቃድን ሰጥቶ ፣ ሕጉን በግልጽ ሠርቶና ተናግሮ ፣ የሚያስፈልገውን ነገር አሟልቶና ዕውቀቱን አበልጽጎ ከመፍጠር የበለጠ ምን ያድርገው? ነፃ ፈቃዱን ቀምቶ እንዳይመርጥ ማድረግ ነበረበት?

“‹እሺ ታዲያ አዳም እንደሚሳሳት እያወቀ ለምን ፈጠረው?›  ለሚለው ጥያቄህ መልሱ ‹የሚሳሳት ፍጥረት መፍጠር የለበትም› የሚለው አመለካከት ካለበት ችግር ጋር ይያያዛል፡፡ አዳምን በሚመለከት እንደሚሳሳት እያወቀ የፈጠረበትን ምሥጢር የሀገራችን ሊቃውንት ከአምላክ ሰው መኾን (በሰውነት መገለጥ) ጋር ያያይዙታል፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹አዳም እንጂ ፍጠረኝ ሳይለው እንደሚስት እያወቀ ለምን ፈጠረው ቢሉ ለእዚያም እኮ ነው ሰው ኾኖ ያዳነው፡፡› እንዲሁም የአዳም መሳሳት ጠቀመው እንጂ አልጎዳውም ምክንያቱም አምላክ ሰው ሲኾን እሱም በዘሩ አምላክነትን ገንዘብ ማድረግ ችሏልና› በማለትም ይከራከራሉ፡፡ ምናልባት ይህ አገላለጽ ግን የእግዚአብሔርን መኖር ለሚጠራጠር ሰው ተረት ተረት ሊመስለው ይችላል፡፡ ለእሱ ምንም ይምሰለው ለእኛ አምላክ ሰው በመኾን ዘመዳችን ሆኗል ፤ የሞት እዳችንን አስወግዶልናል ፤ አምላክን በተጨባጭ ዐወቀን እንድናመልክ አድርጎናል ፤ ወዘተ፡፡ በአጭሩ የአዳም መሳሳት ከአምላክ ሰው መኾን ጋር ይያያዛል ፤ የመፈጠሩ አንድ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

“ሌላ የጠየቅከኝ ጥያቄ ‹ዲያብሎስንስ ለምን ፈጠረው? ከፈጠረውስ በኋላ በስህተቱ ዓለምን ከሚያረክስ ለምን አላጠፈውም?› ያልከው ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የምሰጥህ መልስ ላያጠግብህ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም ዲያብሎስ ለምን እንደተፈጠረ የሚገልጽ ያለኝ መረጃ ውስን ነው፡፡ ምናልባትም እግዚአብሔር ያልገለጸልን ምስጢርም ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በውስን ግምት ግን የሰው ልጆችን ሊያስተምርበት የፈለገ ይመስላል፡፡

“‹ለምን አላጠፈውም?› የሚለው ጥያቄህ ግን የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በሃይማኖት እንደሚታመነው ከኾነ ዲያብሎስ የተፈጠረው መልአክ ኾኖ ነው፡፡ መልአክትን ደግሞ እግዚአብሔር እንዳይጠፉ (እንዳይሞቱ) አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ ስለኾነም ዲያብሎስን ተሳሳተ ብሎ ማጥፋት ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ አንደኛ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተለዋዋጭ ያደርገዋል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድም ፍጥረቱ በተፈጠረበት ሕግና ሥርዓት እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓትን የጣሰም ፍጥረት በጥፋተኝነት ይቀጣል፡፡ ከዚህ ውጭ አጠፋህ ብሎ ማጥፋት ግን ከፈጠረበት ዓላማ ውጭ ያደርገዋል፡፡ በመኾኑም ተለዋዋጭ ፈቃድ ያለው ያስመስላል፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔርን ኹሉን ዐዋቂነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ምክንያቱም እንደሚሳሳት ሳያውቅ ቀርቶ መሳሳቱን ሲያይ አጠፋው ማለት ይኾናል፡፡ በሌላ በኩል መልአክትንም እንዳይሞቱ አድርጎ የመፍጠሩን ኹኔታ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ‹ዲያብሎስን ካጠፋው ለምን ቅዱሳን መልአክትስ ሳይጠፉ ይኖራሉ? ዲያብሎስን የሚያጠፋው ቅዱሳኑን ለማስፈራራት ጭምር ነው?›  ስለኾነም ዲያብሎስን አለማጥፋቱ ትክክል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እኛ የማናውቀው ተጨማሪ ምክንያትም ይኖረው ይኾናል፡፡

“ሌላ ‹የዲያብሎስ በርኩሰት መኖር ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር እንዴት ይስማማል?› የሚል ጥያቄም ጠይቀኸኛል፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን የቅድስና ጠባይ ያለመረዳት ችግር እንጂ ዲያብሎስ ከእግዚአብሔር ጋር ተሳትፎ የሚያደርግበትን ሕግና ሥርዓት ሲያፈርስ ቅድስናውን አጥቷል፡፡ እርኩሰት ማለትም የቅድስና ተሳትፎን ማጣት ወይም ከቅድስና መለየት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለዲያብሎስ እንጂ በእግዚአብሔር ቅድስና ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ የለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕግና ሥርዓትን  በማፍረስ የሚመጣ ርኩሰትም ከእሱ ቅድስና ጋር የሚፎካከር ወይም ቅድስናውን የሚያጠፋ አይደለም፡፡ በመኾኑም ዓለምን የሞላት የዲያብሎስ እርኩሰት ክብደት ኖሮት የእግዚአብሔርን ቅድስና አያጠፋም፡፡››

             እሱ፡-

 “አንዳንድ ጊዜ መልስህን ሳስተውለው ትገርመኛለህ የምትሰጠኝ መልስ ማድበስበስ ነው ወይስ ማምታታት? ነው ጥያቄዬ ሳይገባህ ነው ልታስረዳኝ የምትሞክረው? እስከአሁን ስትተርክልኝ የነበረው ታሪክና የሰጠኸኝ መልስ ምን ያህል ፍሬ ነገር የሌለውና የተምታታ እንደኾነ ተረድተኻል? በአጠቃላይ ስለ እግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት የነገርኸኝ የሃይማኖት ተረትና እርስ በእርሳቸውም የሚጋጩ ናቸው፡፡

“ከዚህ በፊት በጠየቅኩህ ‹እግዚአብሔርን ፍጹማዊ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ዲያብሎስ ደግሞ ሕግና ሥርዓትን ያፈረሰ እርኩስ› ብለኻል፡፡ ይህ ዓለምም በእርኩስትና በክፋት የተሞላ መኾኑን ተናግረኻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹እግዚአብሔር በኹሉም ሥፋራ ይገኛል› ብለኻል፡፡ ትልቁ መጋጨት ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ‹ይህ ዓለም በዲያብሎስ እርኩሰትና ክፋት የተሞላ ከኾነ እንዴት ኾኖ ነው የሚጣጣመው? እንዴት ፍጹማዊ ቅዱስ ኾኖ በሚገኝበት ሥፍራ እርኩሰት ነገሠ?  ነው እግዚአብሔር እርኩሰት ያለበት ሥፍራን እየለቀቀ ይሸሻል? ነው እንደቦታው ኹኔታ ራሱን እየለዋወጠ ነው የሚኖረው? ማለት ዲያብሎስ ባለበት ቦታ ከእርሱ ጋር እየተመሳሰለ እርኩሰት በሚበዛበት ሥፍራ ያንን ገንዘብ እያደረገ በመስማማት ነው የሚኖረው? እንደዚያ ከኾነስ እንዴት እግዚአብሔርን ቅዱስ፣  የማይለዋወጥ፣ ኹሉም ሥፍራ የሚገኝ፣ ኹሉንም የሚያውቅ ወዘተ.›   እያልን መናገር እንችላለን?››

                 እኔ፡-

“ማስተዋል ብትችል እኮ! የዚህንም መልስ ቀደም ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡ ይህንን የእግዚአብሔርን ጠባያት መጋጨት የፈጠረው የእኛው የመረዳት አቅምና ምናባዊ አንግል መኾኑን ነግሬኻለሁ፡፡ ምክንያቱም አዕምሯችን በተቃራኒ ሐሳቦች የተሞላ ስለኾነ የትኛውንም ነገር ሳያቃርን ትክክለኛ ምንነቱን ለመረዳት ይቸግረዋል፡፡ የአንዲት ነጠላ ሐሳብን ምንነት በቀጥታ ወስዶ ምንነቷን፣ ከሌሎች ጋር ያላትን ዝምድና፣ መሠረቷ ምን እንደኾነ ከመረዳት ይልቅ ከሌላ ነገር ጋር በማቃረን ማጋጨት ይቀለዋል፡፡ ለምሳሌ ልክ እንዳንተ አረዳድ “ቅድስና” የቅድስናን ምንነት፣ደረጃና ምንጭ ከመመርመር ይልቅ ‹እርኩሰትን› ቀድሞ በማምጣት ያቃርነዋል፡፡ ይህ ደግሞ አዳም ከተሳሳተ ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች አስተሳሰብ መላሸቅ የተነሳ የተፈጠረ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጠባያት ከፍጡራን ኹኔታ ጋር ስናምታታቸው የመረዳት አቅምና ስልታችን የበለጠ ይወሳሰብብናል፡፡ የአንተም ዋና ችግር ይኸ ይመስለኛል፡፡

“የእግዚአብሔርን ጠባያት በሚመለከትም ደጋግሜ እንዳልኩህ ችግሩ የእኛው የመረዳታችን ኹኔታ ነው እንጂ፤ ጠባያቱ የሚጋጩ ኾነው አይደለም፡፡ አንተ የጠቀስካቸው ጥያቄዎችም በድምሩ ሲቀመጡ ‹እግዚአብሔር በቅድስና በኹሉም ሥፍራ የሚገኝ ከኾነ እና ዲያብሎስ ደግሞ በእርኩሰቱ በዚህ ዓለም ላይ ከነገሠበት እንዴት እግዚአብሔር ባለበት በዚህ ዓለም የዲያብሎስ እርኩሰት ነገሠ? እግዚአብሔርስ ለምን ፈቀደለት›” የሚሉ ናቸው፡፡

“የእኔ መልስ ደግሞ ቅድም እንደጠቀስኩልህ ነው፡፡ የዚህ ዓለምና የዲያብሎስ እርክሰት ከእግዚአብሔር ቅድስና የሚያቃርናቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሕግና ሥርዓት ደንጋጊና ሠሪ ስለኾነ የእሱ ቅድስና በዚህ ክበብ የሚመዘን አይደለም፤ ፍጹም ነው እንጂ! በተቃራኒው የዲያብሎስ እርኩሰት ደግሞ በሕግና ሥርዓት ተመዝኖ በደረጃ የተሰጠውን ቅድስና መተው ወይም የማጣት ውጤት ነው፡፡ በመኾኑም የዚህ ዓለም መርከስ ወይም የዲያብሎስ እርክሰት የሚጋጨው ወይም የሚቃረነው ከዚህ ዓለም ቅድስና ጋር ነው፡፡ በዚህ መሠረት የዲያብሎስ እርኩሰት በሕግና ሥርዓት የተሰጠውን ቅድስና በመተው መጻረር ከኾነ እንዴት ብሎ ነው ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ተወዳድሮ የሚቃረነው?

“ይህንን ነጥብ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብርሃንና ጨለማ አሉ፡፡ አንዱ ባለበት ሌላው አይኖርም፡፡ እኛም በብርሃን ጊዜ እናያለን በጨለማው ጊዜ ደግሞ ለማየት እንቸገራለን፡፡ ምክንያቱም የዓይናችን የማየት ተፈጥሮ በዚህ ዓለም የብርሃን ጊዜ እንዲያይ በጨለማ ጊዜ የማየት አቅም እንዳይኖረው ወይም እንዲያንሰው ተደርጎ የተፈጠረ ነው፡፡ ይህንን ይዘን ‹እግዚአብሔር ፀሐይ ሳትወጣ ወይም ብርሃን ሳይበራ እንዴት ማየት ይችላል?› ማለት የእግዚአብሔርን ጠባይ ያለ መረዳት ችግር ወይም ድንቁርና ከመባል ውጭ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ የዚህ ዓለም እርኩሰትና ቅድስናም ከጨለማና ብርሃን ጋር ተነጻጻሪ አንድምታ አላቸው፡፡ የእግዚአብሔር የቅድስና ጠባይ ደግሞ ከብርሃን ምንጯ ከፀሐይም በላይ ነው፡፡

“ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹እንዴት እግዚአብሔር ባለበት ሥፍራ ዲያብሎስ ሊኖር ቻለ?› የሚለው ጥያቄህም የእግዚአብሔርን መንፈስነት (ረቂቅነት) ያለመረዳት ችግር ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የትኛውም ነገር ውስጥ ሰርጾ መኖር የሚችል አካል እንዳለው ልትረዳ ይገባል፡፡ የእሱ አካል የመንፈስነት ፍጽምና ከፍጥረት ግዝፈትና እርቅቀት ጋር በማቃረን የምንረዳ ከኾነማ ለምን በዚህ ብቻ እንገታለን፤ የስንፍና ጥያቄዎቻችንን አንጨምርም? ለምሳሌ ይህ ‹ዓለም በፍጥረት የተሞላ ስለኾነ ባዶ ሥፍራ የለበትም እንዴት እግዚአብሔር በኹሉም ሥፍራ ይገኛል እንላለን? ቦታውን ኹሉ አየሩ ፣ አፈሩ ፣ ውሃው፣ ድንጋዩ ፣ እጽዋቱ ፣ እንስሳው ሞልቶት የለም እንዴ? ሰውስ ቢኾን ውስጡ በአጥንት ፣ በደም ፣ በሥጋና በአየር ተሞልቶ እንዴት የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው እንላለን?› እያልን በስንፍና ጥያቄዎችን መጨመር እንችላለን መረዳት አይኾንም እንጂ! ለመረዳት ፈልገህ ከኾነ ግን ልብ አድርግ እግዚአብሔር ከየትኛውም ንፁህ ኃይል (pure energy) የረቀቀ ነው፡፡ እርቅቀቱንም (መንፈስነቱን) ምንም እርቅቀት ኾነ ግዝፈት አይወስነውም፡፡ እንደዚሁም የእሱን ቅድስና የሚወስን እርኩሰት የለም፡፡››

            እሱ፡-

“ይህ ያብራራሃው መልስም ቢኾን ሌሎች ጥያቄዎችን ይጎላጉላል እንጂ አጥጋቢነት ያለው መልስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹የእዚህ ዓለም (የዲያብሎስ) እርኩሰት የዚህ ዓለም ሕግና ሥርዓትን መጣስ ወይም የዚህ ዓለም ቅድስና መተው ነው› ካልን የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፈራጅነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባብናል፡፡ ‹እንዴት?› ካልክ ‹የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፈራጅነት በዚህ ዓለም ተግባር ወይም ሥራ ላይ አይደለም ወይ? የእግዚአብሔርን ቅድስና የማይጸራር ከኾነ ለምን በዚህ ዓለም ጥፋት (እርኩሰት) ላይ ይፈርዳል?  ትክክለኛ ፈታሒነቱስ የሚታወቀው በዚህ ዓለም ኹኔታ ላይ በመፍረድ ወይስ በሌላ?› ‹በዚህ ዓለም ሥራ ላይ አይደለም› ካልክ ‹የእዚህን ዓለም እርኩሰት በሠሩ ሰዎች ላይ ለምን ይፈርድባቸዋል› ይባላል? ኃጢያትስ የዚህ ዓለም ቅድስናን መጻረር ነው ወይስ የአምላክን? በዚህ ዓይነት ግራ መጋባትስ እንዴት የእሱ ጠባያት አይጋጩም ይባላል?››

               እኔ፡-

“እስካሁን ድረስ መሠረታዊ ነጥቦችን አልተረዳህልኝም መሰለኝ፡፡ እኔ የምልህ ደግሞ እግዚአብሔር ይህንን ዓለም የፈጠረው በሕግና በሥርዓት አድርጎ ነው፡፡ ስለኾነም ፍጥረት ኹሉ ከተፈጠረበት ሕግና ሥርዓት ውጭ ሲኾን በሕጉ እና በሥርዓቱ የተሰጠውን ፀጋ ያጣል፤ ይህ ደግሞ ከተፈጥሮው ጋር ስለማይስማማ እርኩሰትና ቅጣት ይኾንበታል፡፡ ለምሳሌ አዳምን እንውሰድ ከተፈጥሮው ጋር የተያያዘች አንዲት የቃል ሕግ ተሰጠችው፡፡ ‹ይህችን የበለስ ፍሬ ከበላህ ትሞታለህ› የምትል፡፡ ተላልፎ በላ ሞተ፡፡ ምክንያቱም የመብላቱ ውጤት ሞት ነው ተብሏልና፡፡ በልቶ ባይሞት ግን እግዚአብሔር ውሸታም፤ የተናገረውን የመፈጸም አቅም የሌለው፤ ሕጉም የማይሠራ ያደርገው ነበር፡፡ እሱ ግን ሕጉም ትዕዛዙም እውነት ስለኾነ ለአዳም የፈለገውን ሰጠው፡፡ ሞት ማለትም መለየት ማለት በመኾኑ ከእግዚአብሔር ፀጋ ተለየ፡፡ በመኾኑም አለመታመንን፣ ከሐዲነትን፣ ከተሰጠው ውጭ መፈለግን፣ አመፀኛነትን፣ ስግብግብነትን ገንዘብ አደረገ፡፡ ይህ ደግሞ ከተፈጠረበት ሥርዓት ውጭ መኾን ስለኾነ ቅጣት ኾነበት፡፡ የዲያብሎስም እርኩሰት ተመሳሳይ ነው፡፡

“ይህንን የአዳምን ጉዳይ በተለይ ልብ ብለን ማስተዋል የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ሕግ እኮ ዕፀ በለስን እንዳይበላ መከልከል ብቻ አይደለም ቅዱስ ኾኖ እንዲኖር ሕግና ሥርዓትን በአእምሮው ውስጥ ቀርጾ ከተሰጠው የቅድስና ፀጋ ውጭ ከወጣም ጥፋት እንደሚኾንበት የዕውቀት ሚዛን በአእምሮው ውስጥ ጽፎ ነው የፈጠረው፡፡ በተጨማሪም ነፃ ፈቃድን አድሎታል፡፡ በመኾኑም ከተሰጠው የሕግ ሥርዓት ቅድስና ወጭ አልፎ በመሄድ እርኩሰትን የመረጠው አዳም እንጂ እግዚአብሔር መቼ ዝም ብሎ ፈረደበት፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ ማለትም እኮ ሰዎች የፈለጉትን መስጠት ማለትም ነው፡፡ አዳምም ሕግ መተላለፍን መረጠ ሰጠው፡፡

“ኃጢያት ማለትም የተፈጠሩበትን ዓላማ በሳተ መንገድ በመሔድ ከሕግ ውጭ የኾነ ሥራ መሥራት ማለት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የሰው ልጅም አራት ነገሮችን መዘንጋት የለበትም፡፡ አንደኛ ፍጡር መኾኑን ፣ በፍጡርነቱም በሕግና ሥርዓት ገደብ ውስጥ የመኖር ግዴታ እንዳለበት፡፡ ኹለተኛ ዕውቀት የተሰጠው በመጠን ተወስኖ መኾኑን ዕውቀቱንም በቅደም ተከተልና በደረጃና በሥርዓት መረዳት እንደሚኖርበት፡፡ ሦስተኛ ገደብ ያለበት ነጻ ፈቃድ ያለው መኾኑ፡- በፈቃዱ የሚመርጠውን ነገር ከራሱ ተፈጥሮ ጋር እያገናዘበና እያስተዋለ መኾን እንደሚገባው፡፡ አራተኛ በስሜት የታሠረ ፍጡር መኾኑን፡- በዚህም ስሜታዊነት አስፈላጊ ቢኾንም የአእምሮ አስተሳሰባችንን ከተቆጣጠረው ግን ችግር ስለሚፈጥር መጠንቀቅ እንደሚኖርበት መረዳት አለበት፡፡ እነዚህን አራት ነጥቦች ያልጠበቀ ሰውም ከሕግና ሥርዓት ውጭ በመውጣት በተቃራኒው ነው የሚኖር፤ በዚህም ከተፈጥሮው ውጭ ስለሚወጣ ቅጣት ያገኘዋል፡፡

 “ወደ ዋናው ነጥባችን እንመለስና እግዚአብሔር በዚህ ዓለም እርኩሰት ላይ ይፈረድበታል ማለት የዚህ ዓለም ፍጥረት (ሰው) ቅድስናውን በማጣቱ እርኩሰትን ገንዘብ ያደርጋል፤ የእርኩሰት ደሞዝንም ይወስዳል ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል እግዚአብሔር የሠራው ሕግ ሲጣስ ሕጉ ራሱ በጣሰው ሰው ላይ ቅጣቱን ይበይንበታል ወይም ይፈርድበታል ማለት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

  “ስለዚህ እግዚአብሔር እርኩሰት በሠሩት ላይ ይፈርደባቸዋል ማለት ያፈረሱት ሕግ ቀጪ ኾኖ የቅጣት ደሞዛቸውን (ዋጋቸውን) ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ይፈርድላቸዋል ማለት ከጠበቁት ሕግ ተጠቃሚ ይኾናሉ ማለት ነው፡፡››

                  እሱ፡-

“እሺ ሌላውን እንኳን ብንተወው እግዚአብሔር ዓለመ-ፍጥረቱንና በእሱ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረቶቹን የሚያስተዳድረው በሕግና ሥርዓት ነው ማለትና ከዘላለማዊ ፈቃዱ ለሰው ልጆች ነፃ ፈቃድን አድሏቸዋል ማለት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የራሱ የኾነ ፈቃድ ኖሮት ከዚያም ለፍጥረቱ ሰጥቶ በሕግና ሥርዓት የሚያስር ከኾነ የሰጣቸው ነፃ ፈቃድ የታለ? ይህ ‹እንዳይበላ ግፋው እንዳይተወው ሳበው› ዓይነት ሥጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፍጥረቱን ነጻ ፈቃድ እንዳሳጣው ነው የሚያሳየው፡፡ ‹ለምን?› ብትል ምንም ያህል ነፃ ፈቃድ ቢኖር ሕግና ሥርዓት ባለበት አድርግና አታድርግ የሚባል ማሠሪያ አለ፡፡ አድርግና አታድርግ በማለት ማስተዳደር ደግሞ ነፃነትን መግፈፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው እግዚአብሔር ፍጥረቱን በሕግና ሥርዓት አሥሮና ቀፍድዶ የቅኝ ግዛቱ ማድረጉን እንጂ የፍጥረቱን ነፃነት አይደለም፡፡

“እንደገናም አንድን ሰው ‹በፈቃዱ ነው የተፈረደበት ኩነኔን ፈልጎ ነው ሕግ የጣሰው› በማለት መቅጣት ነፃነትን ሲፈልግ ወህኒ በመውረድ መቀጣት አለበት እንጂ ነፃ መውጣት የለበትም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጨቋኝና አንባገነን ገዥዎች የሚፈጽሙት የማን አለብኝ ሥራ ነው፡፡ እንዳውም ጨቋኝ መሪዎች ሕዝቦችን በመጨቆን የሚያሰቃዩት ምናልባት ከእሱ ተምረው ይኾን እንዴ? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚሰጠውንም ፍርድ ትክክል ነው በማለት መቀበል ያስቸግራል፡፡ እንዴት ራሱ ፈቃድን ሰጥቶ የሰጠውን ፈቃድ ግን በሕግና በሥርዓት ተብትቦ አፈረሳችሁ በማለት መቅጣት ትክክለኛ ፈራጅ በኾነ አካል ይሰጣል ? ሳያውቅ ቀርቶ ነው አይባል ‹የማያውቀው የለም› ብለሃል፡፡ እንዴት እያወቀ ቀድሞ መከልከል ወይም ሕግና ሥርዓቱን አለመስጠት ሲቻል አውቆ ሰጥቶ በጥፋተኝነት ይቀጣል? እውነት እልኃለሁ እግዚአብሔር እያወቀ እንደዚህ የሚያደርግ ከኾነ እንኳን በእሱ ዕውቀት በእኛም ቢኾን ትክክል አይደለም፡፡››

           እኔ፡-

“ጥያቄዎች እግዚአብሔርን እንዴት ልስደበው በማለት የተዘጋጀህባቸው ይመስላሉ፡፡ እግዚአብሔርን መስደብ የማወቅ መለኪያ መስሎህ እንደኾነም እንጃ፡፡ ለእኔ ግን ትክክል አትመስለኝም፡፡ ፍጥረታትን በሕግና ሥርዓት ማስተዳደር ጨቋኝነት ነው ማለትም ስህተት ነው ፡፡ ነፃነትንም ቢኾን ገደብ ልክ ሊኖረው እንደሚገባ የሚጠፋህ አይመስለኝም ፡፡ ሕግና ሥርዓትም የአዕምሮ ወይም የዐዋቂ አካል ሥራ መኾኑ የግድ ነው ፡፡ በዓለመ-ፍጥረቱ  የሚገኘው ፍጥረት ኹሉ በሕግና ሥርዓት ባይኾን የሚኖረው በህልውና መገኘትም አይችልም   ነበር፡፡ እንዴት ኾኖ!

‹‹እንዳው ይሁን ይኑር ብንል እንኳን ያለ ሕግና ሥርዓት ውጥንቅጡና ድብልቅልቁ የወጣ ይኾን ነበር እንጂ አንድም ፍጡር በተስተካከለና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ መገኘት አይችልም ነበር፡፡ ይህም እግዚአብሔርን ፍጥረቱን በሕግና ሥርዓት ማኖር ያቃተውና ዕውቀቱ ምሉዕ ያልኾነ ነው ለማለት እንገደድ ነበር፡፡ ሕግና ሥርዓት አልባነትም የአዕምሮ አልባነት፣ የዝረውነት መገለጫ እንጂ፤ የዐዋቂነት መታወቂያ አይደለም፡፡ ፍጥረቱን ስንመለከት ግን የፈጠረው አካል በጥበብ በተሞላ ዐዋቂነት፣ ሕግና ሥርዓት አስይዞ እንደሠራው እንጂ በግለደለሽነት የሚነሮ አለመኾኑን መረዳት እንችላለን፡፡ የፍጥረታት አኗኗራቸው በሕግና ሥርዓት መሠረት የሚመራ ነውና፡፡

‹‹አንተ እንደተናገርከውም ‹ነፃ ፈቃድን በሕግና ሥርዓት ሳይገድቡ ለፍጥረታት በተለይም አዕምረ ላላቸው ሰውና መላዕክት መስጠት ነበረበት› ማለትም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እንደምገምተው ይህንን አስተያየት የሠጠኸው ከአጉል ምኞት፣ ፍጡር መኾንን ከመዘንጋትና ካለማስተዋል የተነሣ ይመስለኛል፡፡ ያለበለዚያማ ‹ነፃ ፈቃድን ለምን በሕግና በሥርዓት ወስኖ ይሰጣል? ነፃ ፈቃዳችን ለምን ያለ ገደብ አልኾነም?› ማለት እግዚአብሔር ለምን ሌላ እግዚአብሔር አድርጎ አልፈጠረንም ማለት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ባልተወሰነ ፈቃድ ባለቤትነት ከሕግና ሥርዓት በላይ መኾን ከተቻለ እግዚአብሐየርነትን ገንዘብ ማድረግ እንጂ ፍጡር መኾን አይደለም፡፡ ስለዚህ በሕግና በሥርዓት ገድቦና ነፃ ፈቃድን መሥጠቱ ትልቅ ፀጋ ነው፤ ፍጡር ነንና፡፡

‹‹እና ነፃ ፈቃድን በሕግና በሥርዓት መሠረት መሠጠቱ አግባብነት ያለው ከኾነም በተሠጠው መሠረት መኖር ሲቻል ያንን ጥሶና አልፎ የሚሔድም የተሠጠውን ናቂና ሥጦታውን አልፈልግም ባይ በመኾኑ የፈለገውን ከተሠራለት ሕግና ሥርዓት ውጭ ያለውን ዋጋ ማግኘት አለበት፡፡ ከተፈቀደለት ሕግና ሥርዓት ውጪ ያለው ደግሞ እሱ ካለው ተፈጥሮ ጋር ስለማይስማማ ዋጋው ቅጣት ይኾንበታል፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሕግ ጣሹ የፈለገውን በመሥጠቱ የነፃነት አምላክ ነው፡፡ ለተቀባዩ ግን ከተሠጠው ሕግና ሥርዓት ውጪ ያለውና ፈቃዱ ባለመጣጣማቸው በውጤትነት የሚያገኘው ደመወዝ (ዋጋ) ቅጣት ይኾንበታል፡፡ ይህም አምላክ አስገዳጅ አለመኾኑን ያስረዳናል፡፡ ከተፈቀደላቸው ሕግና ሥርዓት ውጪ በመሔድ መኖር ሲፈልጉ በመፍቀድ ደመወዛቸውን አልከለከለምና፡፡

 ‹‹ደግመህ ደጋግመህም ከመፈጠር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ጠይቀኸኛል፡፡ ይኸውም ‹ኹሉን ያውቅ የለም ወይ? እንዴት አዳምና ሔዋንንስ እንደሚያጠፉ እያወቀ ፈጥሮ ይቀጣቸዋል?› የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ግን ደግሞ የሠጠሁህን መልስ አስታውስ፤ አሥር ጊዜ ለተመሣሣይ ጥያቄ ተመሣሣይ መልስ መሥጠት ትርፉ መደናቆር ነው፡፡  ኾኖም እዚህ የጥያቄዎችህን አንድምታ ያስተዋልካቸው አልመሰለኝም፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ‹ዓለመ-ፍጠረቱ ከመኖር ወደ አለመኖር እንደሚለወጥ እያወቀ ለምን ፈጠረው? አንድ ነገርስ ለምን ሳይለወጥ ባለበት አይረጋም? ለምንስ ሰው ተወልዶ አድጎ ይሞታል? ፍጥረት ኹሉስ ለምን በዚህ ሕግና ሥርዓት ይገዛል? ለምንስ የፍጥረቱን ህልውና ይወስነዋል? ለምሳሌ ሰውን በአስተሳሰቡ፣ በአካሉና በፈቃዱ ለምን ወሰነው? ለምንስ አንድ አንድ ጊዜ ፈጥሮ ብቻ ሳይሞት እየተራባ እንዲኖር አላደረገውም?› የሚሉና የመሣሠሉ የአንድምታ ጥያቄዎችን ያሰማሉ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ፍጥረቱን እንዴት በሕግና ሥርዓት አጠባብቆና አስተሣሥሮ ፈጥሮ እያኖረው እንደሚገኝ ያለማስተዋል ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡

የሚሠጡት አንድምታም ምን ያህል ችግር እንዳለበት ለማሳየት ሰውን እንደምሳሌ በመውሰድ መመልከት ይቻላል፡፡ ‹የሰው ዘር ለምን ተወልዶ አድጎ ይሞታል? ለምንስ በቦታ፣ በጊዜ፣ በአስተሳሰብና በፈቃድ ይወሰናል?› ማለት አንድምታው ‹ለምን ሰው አንድ ብቻ ኾኖ አልቀረም? ለምንስ መዋለድና መባዛት አልቀረልንም?› ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ያልተወሰነ ፈቃድ፣ ዕውቀት፣ ህልውና ያለው ሰው ካለ ያ ኹሉንም ጠቅልሎ ይይዘዋል፡፡ ይህ ከኾነ ደግሞ ሌሎች ሰዎች የመኖሪያ ቦታና ጊዜ አያገኙም፡፡ በዕውቀትና በፈቃዱም የአምላክነትን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎችህን አስተውለህ አንድምታቸውንም እያየህ አግባብነታቸውንም እየመዘንክ ቢኾን ጥሩ ነው፡፡

‹‹ምናልከባት ለመረዳት ያስቸገረህ የሕግና የሥርዓትን ምንነትና አስፈላጊነት ካለማወቅ ከኾነ ያንን ለማወቅና ለመረዳት መጣር እንጂ ባልተረዱት ነገር ላይ ተነስቶ እንኳን እግዚአብሔርን ሰውንም መስደብ ትክክል አይመስለኝም፤ አግባነትም የለውም፤ ዐዋቂነትም አይደለም፡፡ የሕግና የሥርዓት ምንነትን ለመረዳት ከፈለክ ግን በዚህ አተረጓጎም ሕግና ሥርዓት ሲባል ምን ማለት እንደኾነ ማየት ይቻላል፡፡

‹‹ሕግና ሥርዓት ተመሳሳይነትና ተያያዥነት ያላቸው ተመጋጋቢ ፅነሣተ-ሐሣብ ናቸው፡፡ ሕግ እግዚአብሐየር ፍጥረቱን ኹሉ እንደ አኗኗሩ (ሀልዎቱ) በመጠን፣ በዓይነት፣ በርቅቀት፣ በጊዜና በቦታ ተወስኖ እንዱ ከሌላው ጋር በመመጣን፣ በመጠባበቅና በመስማማት የሚኖርበት የፈቃድና የክልከላ ወሰን ሲኾን ሥርዓት ደግሞ የአኗኗሩ ስልት ወይም የፍጥረቱ የሀልዎት መጠባበቂያ ስልታዊ ቁጥጥር ወይም አስተዳደራዊ ስልት ማት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜም ኹለቱን አንድ አድርጎ የማየት ነገርም አለ፡፡ ኾኖም ሕግ ሲባል ድንጋጌውን፣ ሥርዓት ደግሞ የድንጋጌውን አፈጻጸም ወይም አሠራር ማለት ይኾናል፡፡

‹‹ሕግና ሥርዓትን በአንድነት ወስዶ በኹለት መክፈልም ይቻላል፡- የተፈጥሮና መንፈሳዊ በሚል፡፡ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ፍጥረት የተባለ ነገር ኹሉ ተገድቦ፣ ተጠባብቆና ተስማምቶ እየተካካና እየተመጋገበ የሚኖርበት ስልት ሲኾን፤ መንፈሳዊ የሚባለው ደግሞ በተለይ ኅሊና ባላቸው ፍጥረታ (በሰውና በመላእክት) ተጽፎ የሚገኝ ከፈቃድና ካስተሳሰብ ጋር የተያያዘ፣ ትክክል ያልኾነውን እንዲተው፣ መልካም ትክክለኛ የኾነ አኗኗርና ሥርዓትን ብቻ እንዲፈጽሙ በመውቀስና በመፍቀድ የሚጠብቅና የሚመራ ሀብት ነው፡፡ በኹለቱም (በተፈጥሮም ኾነ በመንፈሳዊ) ከሕጉና ከሥርዓቱ ውጭ መኾን ጥፋትና ቅጣትን ያስከትላል፡፡

‹‹የኹለቱንም ሕግና ሥርዓት በምሳሌ በማነጻጸር ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓትን (የመሬት ስብተ ሕግና የመንቀሳሰቅ ሥርዓትን) መመልከት ሐሣባችንን ግልጽ ያደርግልናል፡፡ መሬት በላይዋ ላይ የሚኖሩ ፍጥረቶቿን ይዛ የምትኖረው በስበት ሕግ የተነሣ ነው፡፡ መሬት የምትንቀሳቀሰውም (በራሷ ዛቢያም ላይ ኾነ በፀሐይ ዙሪያ በምትዞርበት ምህዋሯ) በዚህ ሕግ የተነሣ ነው፡፡ በተለይ በፀሐይ ዙሪያ በምህዋሯ ላይ የምታደርገው ዙረት በኹለት የስበት ኃይሎች የተነሣ ይከናወናል፡- በገፍታሪ ኃይል (centrifugal force) እና በጎታች ኃይል (centripetal force) መመጣን፡፡ በእነዚህ ኃይሎች የተነሣም መሬት ከምህዋሯ አፈንግጣ ወደ ፀሐይ በመቅረብ ሣትቀልጥና ሳትነድ ወይም ከፀሐይ በመራቅ ሳትቀዘቅዝና በበረዶነት ሙሉ ለሙሉ ሳትሸፈን የጎዳና ሚዛኗን ጠብቃ በመንቀሳቀስ ትኖራለች፡፡ ስለኾነም መሬት በሚገዟት መያዣና መንቀሳቀስ ሕግጋትና ሥርዓታት መሠረት የመኖር ግደታ አለባት፡፡

‹‹የመሬት ሕግና ሥርዓት ግን የተፈጥሮ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የሚመለከታቸው በጥቅሉ ሕይወት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ፍጥረታ ሲኾኑ በተለይም ማሰብ የሚችሉት ሰውና መላእክት ናቸው፡፡ እነዚህ ፍጥረታትም (ሰውና መላእክት) በአእምሯቸው መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት ተጽፎባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እውነት፣ ፍቅር፣ ጥሩ፣ ሐቅ፣ ቅድስና፣ ለሌሎች መስዋዕት መኾንና የመሳሰሉት የመንፈሳዊ ሕግ መሠረቶች ናቸው፡፡ በተለይም ለእኛ ለሰው ልጆች እነዚህ መንፈሳዊ ሕግጋት በአእምሯችን ተጽፈው ከፈቃዳችን መሻትና ከስሜት ሕዋሶቻችን ጋር ግብግብ በመፍጠር ኾኖም ተስማተው ይኖራሉ፡፡

‹‹ይህም መሬት በተፈጥሮ ስበት (ገፍታሪና ጎታ) ኃይሎቿ ግብግብ ዛቢያዋንና ምህዋሯን ጠብቃ እንደምትንቀሳቀስ መኾኑ ነው፡፡ ለምሳሌ መሬት ከምህዋሯ አፈንግጣ ወደ ፀሐይ በጣም ብትጠጋ ሙቀቷ ጨምሮ እንደምትቀልጠው፣ ሰውም ከተፈጥሮው አልፎ አምላክ ልኹን ቢል በጥፋ ይቀጣል፤ የተፈጥሮ ውስንነት አለበትና፡፡ በሌላ በኩልም መሬት ከምህዋሯ በማፈንገጥ ከፀሐይ በጣም ርቃ ብትሔድ በበረዶ ተሸፍና ምንም ሕይወት ያለው ነገር እንደማይኖርባት ሰውም ያለውን የአዕምሮ ሀብት (መንፈሳዊ ሕግ) ሳይጠቀምበት በተቃራኒው መጥፎ ተግባራትን ቢሠራም የተሠጠውን ፀጋ ያጣል፤ ይህም በተቃራኒው ቅጣት ይኾንበታል፡፡ ስለዚህ የተፈጥሮ ሕግጋት ሲጣሱ አካላዊ ቅጣት እንዳለበቸው ኹሉ መንፈሳዊ ሕግጋም ሲጣሱም የአእምሮ ወቃሽነት፤ ከዚያ መንፈሳዊ ቅጣት አለባቸው፡፡ በመኾኑም መንፈሳዊ ሕግጋት ሰዎች በእምነት፣ በእግዚአብሔር ፀጋ ሥርዓትን ጠብቀው በሰላም እንዲኖሩ አስችለዋቸዋል፡፡

‹‹በዚህ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት ሰዎችን ማስተዳደር ደግሞ ነፃነትን መግፈፍ ሳይኾን የሰዎችን የአኗኗር ኹኔታ ሥርዓት ባለው መልኩ ማድርግ ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ምን ያህል ዐዋቂና ጥበበኛ ሞራላዊ አምላክ መኾኑን ይመሠክራል፤ ለሰዎች አእምሮ ጠባይን አድሎ የዕውቀትና የሞራል ሀብታም ተጠቃሚ አድርጓቸዋልና፡፡››

                      እሱ፡-

  ‹‹አረ! እንዳው ኹሉንም ነገርልተወውና ስለሞራላዊነት በጻፍክልኝ ‹እግዚአብሔር ሩህሩህና ትክክለኛ ፈራጅ ነው ብለሃል፡፡ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል? ምክንያቱም ርህራሄ ካለ ሊታዘንለት የሚገባ አካ (ሰው) አለ ማለት ነው፤ ማዘንና መውደድ ባለበትም ማዳላት ይፈጸማል፡፡ ማዳላት ባለበትም ትክክለኛ ፍርድ (ፍትሕ) ይኖራል ማለት አይቻልም፡፡ እንዴት ታዲያ እግዚአብሔር ‹ምራላዊ አምላክ ነው› ልንለው እንችላለን?

                       እኔ፡-

      ‹‹ ከኹሉም በፊት እግዚአብሔር ስንል ‹በኹሉም ጠባያ ፍጹማዊ የኾነ አምላክ› ማለታንን አትዘንጋ፡፡ ፍጹም የኾኑ ጠባያቱም አንዱ ካንዱ የተለያዩ ሳይኾኑ በአንድነት ተስማምተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ፈታሒነት ምንድነው? ለተጎዳ ማዘንንና ጎጂን አካል መቅጣትን የሚያጠቃልል፤ ኹሉን ዐውቆም ትክክለኛ ፍትሕን መስጠት ነው፡፡ ስለኾነም እግዚአብሔር ትክክለኛ ፈራጅ ነው ስንልም ኹሉንም በማወቅ ነው፡፡ ሩህሩህ ነው ስልም ኹሉንም በማወቅ ለኹሉም እንጂ እንደ ፍጡራን ሳያውቅ ቀርቶ ተጎጅውንና ጎጅውን ሳይለይ የውጫዊ ገፅታን ብቻ በማየት ወይም በስሜትና ብግል ፍላጎት ተጭበርብሮ በመታለል አይደለም፡፡ ስለኾነም እግዚአብሔር ለፍጥረት ኹሉ ይራራል፤ በማንኛውም ፍጥረት ላይ በማንም ምንም ዓይነት ያልኾነ ነገር ሲደረግበት አይደሰትም፡፡ይህም ማለት የአንድ ሰው ተግባር እግዚአብሔርን እንዲራራ ያደርገዋል፤ ባጠፋውም ላይ ይፈርድበታል፤ ለተጎዳው ደግሞ በአግባ ይፈርድለታል፡- የሚፈርደው ኹሉንም በማወቅ ነውና፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር የሞራላዊነት ጠባያት ፍጥረቱን የሚነብባቸውና የሚግባባቸው ስሜቶች ናቸው፤ ስለኾነም   የእግዚአብሔር ከፍጥረት ጋር ግኑኝነት ማድረግ ስንናገር ፍጹማዊ ጠባያቱን ከፍጥረቱ ኹኔታ ጋር የሚያስማማው በሞራላዊ ጠባያቱ አማካኝነት ነው ማለታችን ነው፡፡››

                      እሱ፡-

‹‹ምን ፍፅምና፣ ፍፅምና ትለኛለህ? እግዚአብሔር በሞራላዊ ጠባያቱ ፍጹም ነው በማለት ከማድስበስ ለምን በትክክል የዓለምን ሥቃይና ችግር አታስተውልም፡፡ እስቲ በመጨረሻ ጥቅል ነገርን ሞራላዊነት ካልከው ጋር በማያያዝ በተጠየቅ ላቅርብልህ፡፡ እንደ አንተ አገላለፅ፡-

 1. እግዚአብሔር ኹሉንም ነገር ያውቃል ፡- እውነት ከኾነ፡፡
 2. እግዚአብሔር ኃያል አምላክ ነው፡- እውነት ከኾነ፡፡
 3. እግዚአብሔር የፍጥረት ኹሉ ፈጣሪ ነው፡- እውነት ከኾነ፡፡
 4. እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ አምላክ ነው ፡- እውነት ከኾነ፡፡
 5. ዓለም የሥቃይና የመከራ መድረክ ናት፡- እውነት፡፡ ዓለም ላይ እይኖርክ ይህንን የምትክድ አትመስለኝም፡፡ በዚህ የምትስማማ ከኾነም ከዚህ በላይ የጠቀስካቸውን የእግዚአብሔር ጠባያት ስፈትሻቸው ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም የሚከተሉትን አማራጭ መደምደሚያዎች ለመስጠት እንገደዳለን፡፡

  1ኛ. አማራጭ፡- እግዚአብሔር ኹሉን ያውቃል፤ ነገር ግን የዓለም ሕዝብ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ይህ ከኾነ እግዚአብሔር የዓለምን ሕዝብ የሥቃይ ምንጮች ለማጥፋት ወይ ፈቃደኛ አይደለም ወይም ፈቃደኛ ቢኾንም ለማጥፋት አቅም የለውም ወይም ሥቃያቸው የማያሳዝነው ጨካኝ አምላክ ነው፡፡

2ኛ. አማራጭ፡- እግዚአብሔር ኹሉን ነገር ማድረግ የሚችል ኃያል አምላክ ነው፤ ነገር ግን የዓለም ሕዝብ በመከራ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ይህ ከኾነም ወይ እግዚአብሔር ሥቃዩን ከዓለም ላይ ለማስወገድ ፈቃደኛ አይደለም ወይም የሥቃዩን መኖር አያውቅም፡፡

3ኛ. አማራጭ፡- እግዚአብሔር ኹሉንም ነገር ፈጥሯል፤ ነገር ግን በዓለም ላይ ሥቃይና መከራ ተንሰራፍተዋል፡፡ ይህ ከኾነም እግዚአብሔር ወይ ኹሉን ነገር አያውቅም ቢያውቅም ለማጥፋት ፈቃደኛ አይደለም ወይም  መከራና ሥቃይን ዐውቆ የፈጠረ ኃላፊነት የማይሰማው አምላክ ነው፡፡

በእነዚህ አማራጮች መሠረትም ‹ሥቃይና መከራ መኖር አልነበረባቸውም ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ስላሉ የእግዚአብሔር ጠባያት ትክክል አይደሉም፤ (ሐሰት) ናቸው፡፡› የሚል መደምደሚያ ለመስጠት እንገደዳለን፡፡ ስለዚህ በዓለም ላይ ሥቃይና መከራ ተንሰራፍቶ መገኘቱ ኃላፊነት የሚሰማው ሞራላዊ አምላክ አለመኖሩን መስካሪ ነው፡፡›

   እኔ፡-

‹ይገርማል አሁንም እዚያው ነህ? እንዴት ይኾን የአስተሳሰብህን መሠረትና ቅርንጫፍ መለየት የምትችለው? አቀራረብህን ሳስተውለው እግዚአብሔርን በመቃወም ዓለምን ከመካራና ሥቃይ  የተላቀቀች አድርገህ ለመፍጠር የምትጥር ይመስላል፡፡ እስቲ መጀመሪያ ልጠይቅህ ‹ዓለም የሥቃይና መከራ መድረክ ብቻ ከኾነች?› ለምን መሞትን ትፈራለህ? ከመኖር መሞትን ለምን አልመረጥክም? ምክንያቱም የመኖርህ አስፈላጊነት በመከራ ለመሠቃየት ከኾነ አጭር መንገድ መሞት አለልህ አይደለም እንዴ? በሥቃይ የመኖርህ ትርጉሙና ጥቅሙስ ምንድን ነው? በሥቃይህስ ተጠያቂ የምታደርገው ማንን ነው? እግዚአብሔርን አትል ሥቃይና መከራ ካለ የለም ብለህ ደምድመሃልና፡፡

 ዓለም ግን አንተ አንደምትለው የሥቃይና የመከራ መድረክ ብቻ አይደለችም፤ ደስታና ተድላም አሉባት እንጂ! እንዲሁም የመከራና ሥቃይ ኹኔታም አንተ እንዳቀረብከው አይደለም የመኖራቸው ምሥጢር፡፡ ደግሞም  የዓለም ሥቃያት (ችግሮች) የምንላቸው ርሃብ፣ ጦርነት፣ በሽታ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና መንሸራተት፣ ቃጠሎ፣ በአጠቃላይም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ናቸው፡፡ የእነዚህ ችግሮች ኹሉ ጉልላቱ ደግሞ ‹ሞት ነው› በማለት የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ ሌሎቹ እሱን የሚያፋጥኑና የሚያዘገዩ ግብዓቶቹ ወይም የሞት አገልጋዮች መኾናቸው አይጠፋህም፡፡ መቼም ከሞት የበለጠ መጥፎ ነገር ይኖራል በማለት መከራከር የምትችል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከሃይማኖት ዕይታ ውጪ ኾነን ‹የሞት መኖሩ እስፈላጊ ነው ወይስ አይደም?› በማለት ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ ‹ነው› የሚል በመኾኑ የምትስማማ ይመስለኛል፡፡

ሞት ምንም እንኳን ለሰው ልጆች እጅግ መጥፎው የህልውናቸው ፀር ቢኾንም ያለ እሱ የሰዎች መዋለድና የመኖር ትርጉም ምን ይመስል እንደነበረ ስናስተውለው እንኳን ኖረ ማለታችን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሞት ካልኖረ የትውልድ መተካካት አያስፈልግም፡- ትርጉምም አይኖረውም፡፡ ልጅና ሽማግሌ ኾኖ ማለፍ አይኖርምና፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚኖሩ የአኗኗር ኹኔታዎችም መኖር አስፈላጊ አይኾንም፡፡  ነገር ግን የሞትን መኖር የምትቀበልና የምትደግፍ ከኾነም ሌሎቹ የሰው ልጅ በመሬት ላይ ሲኖር የሚያሰቃዩት የተለያዩ ችግሮች ከሞት ያነሱና ለእሱም ግብዓት የኾኑ ናቸው፤ ሥቃያቸውም የሚጎዳን ለሞት እኛን ሲያዘጋጁ በሚፈጥሩብን ተፅእኖ ዓይነት፣ ኹኔታና ቆይታ የተነሳ ነው፡፡ ሥቃያቸው ከሞት በላይ ቢኾን ኖሮማ ሰው የመሞት መብት ስላለው ከመኖር መሞትን በመምረጥ ሥቃይ እንዳያገኘው ማድረግ ወይም ከሥቃይ መገላገል ይችል ነበር፡፡ ይህ መኾኑ ከሞት በላይ የኾነ ሥቃይ ወይም መጥፎ ነገር አለመኖሩን ይመሰክራል፡፡ በሞት መኖር አስፈላጊነት ላይ ከተስማማህም የእሱ ግብዓት የኾኑት ችግሮች መኖራቸውን መቃወምህ አግባብ ቢኾንም በመገልበጥ ከሞት አስበልጠህ መኾን የለበትም፡፡

በዓለም ላይም ደስታ እንዳለ ኹሉ ሐዘንም አለ፤ ተድላ እንዳለ ኹሉ ችግርም ይኖራል፤ ሰላምና ፍቅር እንዳለ ኹሉ መከራና ሥቃይም መኖራቸው ግልፅ ነው፡- ይህን የምትክድ አይመስለኝም፡፡ ለዚያውም የመጥፎ ነገሮች መጠንና የማሰቃየት ደረጃ ከመልካሞቹ ነገሮች  ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ ቆይ ሰው ከሚታመምበት ጊዜ የጤነኛነቱ ዕድሜው አይበልጥም ትላለህ? አብዛኛውን ዕድሜውን የሚኖረውስ በሰላምና በፍቅር ኾኖ አይደለም እንዴ? የሚያጋጥመው  የመጥፎ ነገሮች ብዛትስ ከጥሩዎቹ ጋር ሲነጻጸር ይህንን ያህል መቼ ነው? ስለዚህ መጥፎ ነገሮች በመጠን፣ በዓይነት፣ በአጋጣሚና በመከሰት ቆይታቸው ከጥሩ ነገሮች አኳያ በጣም ውስን መኾናቸውን ልብ ማለት አለብህ፡፡

እንዲሁም አንተ እንዳልከው ሳይኾን ብዙ የዓለም ክስተቶችና ችግሮች ምንም መጥፎዎች ቢኾኑም ጠቀሜታ አላቸው፤ ጥሩ ነገሮችንም አነጻጽሮ ለማወቅና ለማጣጣም ያገለግላሉ፡፡ ከዚህ በላይ እንደተጠቀስውም ከሞት የበለጠ መጥፎ ክስተት የለም፤ ይሁንና ሞት ባይኖር ኖሮ ፍጥረት ምን ዓይነት ገፅታ ይኖረው እንደነበር ስናስተውል ‹መጥፎ የሚባል ነገር ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለት ይኾን?› ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡  መጥፎ ነገሮች የምንላቸውም ለጥሩ ነገሮች ማጠፈጫ፣ እያነጻጸሩ መማሪያ እንዲሁም የራሳቸውም መልካም ጠቀሜታ ያላቸው መኾናቸውም በዕውቀት የተፈጠረ ሥርዓት ማሳያ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡

በሥርዓቱ መሠረት ከኾነም የትኛውም ነገር ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ እሳት አቃጣይና ብዙ ነገሮችን አጥፊ ነገር መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና እሳትን በአግባቡና በጥንቃቄ ከተጠቀሙበት ለሰው ልጆች ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ልክ እንደሳት መጥፎ የምንላቸው ነገሮች በተፈጥሯቸው አግባብ የሚገኙ ከኾነ ጠቃሚ እንጂ ጎጂዎች አይደሉም፡፡ ይህ ከኾነም መጥፎ ነገሮች ከእግዚአብሔር ሞራላዊነት የርህራሄና የቸርነት ጠባያትም ጋር የሚያቃርን ነገር የለባቸውም፤ ምክንያቱም ከመጥፎነታቸው ይልቅ የሚገኙት በጥሩነት ነውና፡፡ ለሰውም መጥፎ የሚመስሉት ነገሮች በሥርዓታቸው መሠረት በአግባቡ ከኾኑ ጠቀሜታቸው የጎላ ነውና፡፡

እንዲሁም ለአንዱ መጥፎና የሥቃዩ ምንጭ ኾነው የሚታዩ ለሌላው ግን እጅግ አስፈላጊና የመኖሩ ዋስትና ኾነው የምናገኛቸው ክስተቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሥጋ በል የኾኑ እንስሳት ሣር በል እንስሳትን በመመገብ ይኖራሉ፡፡ በዚህም የሣር በሎቹ እንስሳት ሥጋት፣ ሥቃይና የህልውናቸው ማጣት ምክንያት ለሥጋ በል እንስሳት ግን የመኖራቸው ዋስትና መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ሥቃይ በማለት የምንላቸው ነገሮች እኛ እንደሚመስለን ሥቃይ ብቻ ሳይኾኑ የራሳቸው የኾነ ምክንያት የሚኖራቸው አስፈላጊ ነገሮችም ናቸው፡፡ የፍጥረት እርስ በርስ ተጠባብቆና ተመግጋቦ የመኖሩ ማሳያም ናቸው፡፡

በሌላ በኩል መጥፎ ነገሮች በመጠናቸውና በአስከፊነታቸውም ከጥሩዎቹ አንጻር ሲታዩ በእግዚአብሔር ጠባያት ላይ የሚፈጥሩትም የማጣረስ ወይም የማቃረን ክብደትና ተፅእኖ አይኖርም፤ መጥፎ ነገሮች የሕግ መተላለፍ ውጤትም ናቸውና፡፡ የእግዚአብሔር ጠባያት ደግሞ ከሕግጋት በላይ  ፍጹማን ናቸው፡፡ ስለኾነም የመጥፎ ነገሮች በሕግ መተላለፍ መከሰት ሕግ በማይገዛው ላይ መሥራት አይችልም፤ የሌሎች ክስተቶችም ኹኔታ እንደዚሁ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጠባያትን መቃረን አይችሉም፡፡ ይህም የአንተ ዋናው ችግርህ የእግዚአብሔርን ጠባያት ከተፈጥሮ ክስተትና አኗኗር ጋር ማምታታትህና ማጋጨትህ ነው፡፡ በጥቅሉ እንኳን ዓለም ማለት የተፈጠረ ክስተት በሕግ የተወሰነ በመኾኑም ጉድለት ያለበት፤ እግዚአብሔር ደግሞ የሕግጋት ሠሪና ተቆጣጣሪ መኾኑን መለየት አለብህ፡፡

‹ በምንስ ቢኾን ታዲያ መጥፎ ነገሮች እግዚአብሔር እንዲኖሩና ሰዎችን እንዲያስመርሩ ለምን ፈቀደ?› ብለህ ብትጠይቅ ግን አግባብ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ኹለት መልሶች ይኖሩታል፡፡ አንደኛ ከዚህ በፊት አንደገለፅኩልህ መጥፎ ነገሮች የተሟላ ጥሩ ነገር አለመኖር ወይም የጥሩነት ጉድለት መኖሩን ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሽታ የተሟላ ጤንነት አለመኖር፣ ጦርነት የተሟላ ሰላም ማጣት፣ ጥላቻ የፍቅር መጥፋት፣ ስህተት የተሟላ ትክክለኛነት አለመኖር፣ ክፋት የተሟላ መልካምነት ማጣት… ናቸው፡፡ እግዚአብሔርም ፍጥረትን ሲፈጥር በፍጽምና ሳይኾን በሕግና ሥርዓት በፀጋ መኾኑን ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከፍጥረት ጠባይ አንዱ መተዋቂያ ተለዋዋጭነት ነው፡፡ ከዚህ ከፍጥረት ፍፅምና ምሉዕ አለመኾንና ተለዋዋጭነት የተነሳ መጥፎ ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በፀጋነት ያልተፈጠረ ፍጡርም አይገኝም፡፡

በሌላ በኩል በዓለም ላይ የሚገኘው ከሞራል ጋር የተያያዘ መከራ ወይም ሥቃይ ኹሉ በሰው መሳሳት የመጣ የፈቃድ ውጤት መኾኑንም ማስታወስ ይኖርብሃል፡- አዳምና ሔዋን በፈቃዳቸው ይሁንብን ብለው ያመጡት የነፃ ምርጫ ውጤት ነው፡- ክፉ የምንለው ነገር፡፡ በአዳምና በሔዋን መሳሳት መከራና ሥቃይ የእነሱም መደምደሚያ የኾነው ሞት በዓለም ላይ መጣ፡፡ ይህም በዘራቸው ኹሉ ላይ ስለተላለፈ ድሃ፣ሃብታም፣ ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ ሴት፣ ወንድ… በማለት የትኛውንም ሰው ሳይመርጥ የመከራው ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ምናልባትም ለአንዳንዱ በጣም ከባድ የኾነ መከራ፣ ለሌላው ደግሞ አነስተኛ ሥቃይ የሚያጋጥመው ቢኾንም ኹሉም በሞት ይስተካከላል፡፡ ስለኾነም በዓለም ላይ ሥቃይና መከራ መንሰራፋታቸው  የሕግ መተላለፍ ውጤት ነው፡፡

በተጨማሪም ለታላቅ ዓለማ ተብለው የሚፈጠሩ ለእኛ መጥፎ የሚመስሉን ነገሮች መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የመሬት መንሸራተትና መንቀጥቀጥ፣ የሱናሚ ክስተት፣ ጎርፍ፣ በሀገራችን በአፋር ክልል አልፎ አልፎ የሚከሰት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ… ሰው በፈቃዱ አመጣቸው ለማለት አይቻልም፡፡ ይሁንና የእነዚህ ክስተቶች መፈጠር ደግሞ የራሳቸው ታላቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ እዚህ ከገለፅነው በተለየ ልናውቀው ያልቻልነው የራሱ ዓለማና ምክንያት ይኖረዋል፡- እግዚአብሔር እንዲኖሩ የፈቀደበት፡፡

በአጠቃላይ በዓለም ላይ ያለውን የመከራ ሥቃይ በተመለከተ የሚኖር የመደምደሚያ ሙግት አንተ እንዳቀረብከው ሳይኾን የሚከተለውን ይመስላል፡፡

 1. ፍጥረት በራሱ ሙሉዕ የኾነ ፍጹማዊ ተፈጥሮ የለውም፡- እውነት፡፡
 2. በዓለም ላይ የተወሰነ ሥቃይና መከራ አለ፡- እውነት፡፡ (ዓለም በሙሉ የሥቃይ መድረክ ናት ማለት ስህተት ነው)
 3. በዓለም ያሉ ችግሮች የፍጡራንን ፍጹም አለመኾን የሚያሳዩ ናቸው፡- እውነት፡፡ (ውስንነት፣ ተለዋዋጭነትና ጥገኝነት ስላለባቸው)
 4. እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍጹማዊ የኾነ አምላክ ነው፡- እውነት፡፡ (ኹሉን አዋቂነት፣ ኃያልነት፣ ፈጣሪነት፣ ሞራላዊነት…የእግዚአብሔር ባሕርይ መታወቂያ ጠባያት መኾናቸውን አስተውል፡፡)
 5. የፍጡራን ፍጹም አለመኾን የእግዚአብሔርን ፍጽምና አያጠፋም፡- እውነት፡፡ (በተ.ቁ. 1 እና 4 መሠረት)
 6. ስለኾነም በዓለም ላይ የተወሰነ ችግር መኖር የእግዚአብሔርን ፍጹማዊ ጠባያት አይቃወምም፡- እውነት፡፡ (በተ.ቁ. 3 እና 5 መሠረት)
 7. የእግዚአብሔር ጠባያትም ያለ ህልውነቱ አይኖሩም፡- እውነት፡፡
 8. ስለዚህ እግዚአብሔር አለ፡፡››
Please follow and like us:
error

4 COMMENTS

 1. የባህርይ የአካል ና የህላዌ ልዩነቱ አንድነት ግልጽ አይደለም? የሦስቱም ሁነት እንዴት ነው? ጥያቄዬን ግንበጥክክልመግለጽአልቻልኩም …

 2. የባህርይ የአካል ና የህላዌ ልዩነቱ አንድነት ግልጽ አይደለም? የሦስቱም ሁነት እንዴት ነው? ጥያቄዬን ግንበጥክክልመግለጽአልቻልኩም …

 3. ወንድሜ ያነሣኸው ጥያቄ ከምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) ጋር የተያያዘ ነው፤ኾኖም ግንዜቤ ከሰጠኽ ጠቅለል ያለ አስተያየት ከዚህ በታች አቅርቢያለሁ፡፡ ሰፋ አድርገህ ለማጥናት ከፈለክ ‹ቅኔ ዘፍልሱፍ› የሚለው መጽሐፍ ላይ ለማብራራት ሞክሪያለሁና፤ እዚያ ላይ ምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) በሚል ንዑስ ርእስ የተቀመጠውን ብትመለከተው መልካም ነው፡፡
  ህላዌ፣ አካልና ባሕርይ
  ህልውና (Existence) ‹ሀለወ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተወሰደ ሲኾን የሚገልፀውም መገኘትን ወይም መኖርን ነው፤ ስለዚኽ ‹ህልው ነገር› ማለትም የተገኘ ወይም የሚኖር ነገር ማለት ይሆናል፡፡ ህልውነት አካል (Body) እና ባሕርይ (Essence) በሚሉ ነገሮች (ፅንሳተ-ሐሳብ) የተሠራ ክስተት ነው፤ አንድ ‹ህልው ነገር› የራሱ ባሕርይና አካል ይኖረዋል፡፡ ህልውና ኖሮት የሚገኝ ነገር ኹሉ ባሕርይና አካል ሊኖሩት የግድ ስለኾነም ህልውነትን ከባሕርይና ከአካል ውጭ አድርጎ መረዳት አይቻልም፡፡
  ምናልባት ‹አካልና ባሕርይ የሚባል ነገር የለም› የሚል ተከራካሪ ካለ፤ እስቲ ቆይ እንጠይቅ! አንድ ነገር ‹ህልው ነው› ስንል አካል የለውም ልንል እንችላለን ወይ? ‹የለውም› ልንል ከቻልን፤ ታዲያ በምን ማስረጃ ወይም ኹኔታ ህልው መኾኑን ማወቅ ቻልን? ‹አዎ! ያለ አካል ሊከሰት የሚችል ነገር አይኖርም› በሚለው ከተስማማን ግን ባሕርይ የሌለው ‹አካላዊ ነገር› ሊኖር ይችላል ወይ? አእምሮ በረቂቅነት አንብቦ የማይተረጉመው አካል ሊኖር አይችልም፤ ባሕርይም የአካል መሠረታዊ ነገር፣ ያ አካል ተለይቶ የሚታወቅበት መነበቢያው ወይም የሥሪቱ ምክንያት ነው፡፡ ያ ከኾነም እንዴት አካሉ በሥሪተ-ነገሩ ሳይነበብ ወይም ባሕሪው ሳይገልጽልን ልናውቀው እንችላለን?
  በእውነታው ከጥንት ሊቃውንት ጀምሮም ህልውነትን ከባሕርይና ከአካል ጋር አያይዞ መረዳት የተለመደ ነገር ነው፤ አንድ ነገርም ያለ እነዚኽ ነገሮች በህልውና ሊከሰት አይችልምና፡፡ ህልውና ከአካልና ባሕርይ ጋር አያይዞ በመግልፅ በኩል ግንባር ቀደም የኾነው ፕላቶን ነው፤ ኾኖም ፕላቶን ባሕርይን ሰማይ ላይ ሲሰቅለው፤ አካልን ደግሞ ከዚያ ተቀድቶ የተከሰተ የመገለጫ ነፀብራቅ አድርጎ ወስዶታል፤ በዚኽ የተነሣም ህልው ነገርን በአካል ላይ የሚንፀባረቅ ሰማያት ውስጥ የተደበቀ ቅርጸ-ባሕርይ (Form) አድርጎታል፤ በሰማይ ህልው ኾኖ የሚገኘው ነገርም ጥላው በመሬት ላይ ተከስቶ እናገኘዋለን ባይ ነው፤ ስለዚኽ አካል የሰማዩ ነገር ጥላ (Shadow) ኾኖ የተገለፀ ስለኾነም በመሬት ላይ የሚገኘው ህልው ነገር ኹሉ ትክክለኛው እውን ነገር ሊኾን አይችልም፡፡
  ይኽንን የፕላቶንን የሰማያት ስቅለት በመቃወም ‹ባሕርይማ ከአካል ተለይቶ አይከሰትም፤ ስለዚኽም አንድ ህልው ነገር አካልና ባሕርዩ ሳይነጣጠሉ የሚገኙበት ክስተት ነው› በማለት የተከራከረው ተማሪው አርስጣጣሊስ ነው፡፡ የሀገራችን ሊቃንውትም የህልውናን ጉዳይ እንደ አርስጣጣሊስ በባሕርይና በአካል አለመነጣጠል መርህ ነው የሚገነዘቡት፡፡ መርሁም ‹ባሕርይ ያለ አካል አይከሰትም፤ አካልም ያለ ባሕርይ ተለይቶ አይታወቅም› የሚል ነው፤ ስለኾነም በሀገራችን ሊቃውንት ዘንድ ‹ህልውና›፣ ‹ህላዌ›፣ ‹ባሕርይ›፣ ‹አካል›፣ ‹ኩነት› የሚባሉ ቃላት ጥልቅ ትንታኔ ያላቸው ተገናኝና ተመጋጋቢ አስተሳሰቦች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ህልውና፣ ህላዌና ባሕርይ በኩነት በመገናዘብ አንድነት ያላቸው ናቸው፤ የሚገለፁትም በአካል አማካይነት ነው፡፡ ስለኾነም ነው ሁለቱ ባሕርይና አካል ተለያይተው አይከሰቱም የምንለው፡፡ ረቂቅ ወይም ግዙፍ ሊኾን ይችላል እንጂ አካል ሳይኖረው የሚከሰት (የሚገኝ) ህልው ነገርም አይኖርም፤ አንድ ነገርም አካል ነሥቶ በመከሰት የሚታወቀው በባሕርዩ ነው፤ ያለ ባሕርይ ማንነቱ (ምንነቱ) ሊታወቅ ወይም ሊለይ አይችልም፡፡ ስለዚኽ አንድ ህልው ነገር በአካሉ መገለጫነት፣ በባሕርዩ አሳዋቂነት (ገላጭነት) ተከስቶ ይታወቃል፡፡
  አሁን እዚኽ ላይም ቢኾን ‹አካልና ባሕርይስ ለየራሰቸው ምንድን ናቸው?› የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ላይገለጽልን ይችላል፡፡ ስለኾነም የተወሰነ ማብራሪያ መስጠት ይጠቅማል፤ ምርምራችን እንቀጥል፡፡
  ባሕርይ
  ከላይ እንደጠቀስነው ባሕርይ ማለት የአንድ ህልው ነገር ጥንተ መሠረት ወይም የተፈጥሮው ምክንያት ማለት ነው፡፡ ባሕርይ በአካል ህልው ኾኖ ከአካል ሳይለይ የአካልን ጠባይ ወይም ስሜት ይገልጻል፡፡ በመኾኑም አንድ በአካል ተለይቶ የተከሰተ ነገር የሚታወቀው ባሕርዩ በስውር አብሮት ኾኖ ማንነቱን ወይም ምንነቱን ሲያንጸባርቅለት ነው፡፡ ኾኖም ባሕርይ በረቂቅነት በሕሊና ይጻፋል እንጂ ይኽ ነው ተብሎ በስሜት ሕዋሳት አይገለጽም፡፡ ባሕርይ ጥንት መሠረት ወይም የተፈጥሮ ምክንያት ነው ስንልም ህልው ነገሩ የተፈጠረበት መሠረተ ነገር ነው ማለታችን ነው፡፡ ይኽም የሚገለጸው በሚከሰተው አካሉ ተንጸባርቆ ነው፡፡ ይኽን ይዘን ‹አካል እንዴት ነሽ?› እንበል!
  አካል
  አንድ ህልውና ያለው ነገር ህልውነቱ ተለይቶ የሚገለጸው በአካሉ ነው፤ አካል ስንልም ባሕርይ በስውር የሚገለጽበት ነገር ማለታችን ነው፤ ይኽም አካል ረቂቅ (መንፈስ) ወይም ግዙፍ ሊኾን ይችላል፡፡ የትኛውም ቢኾን የባሕርይ መገለጫ ህልው ነገሩ የሚያካትታቸው ነገሮች በሙሉ የሚገኙበት ነገር ወይም ‹እኔ ባይ›፣ ‹በእሱነት› ተጠቅሶ የሚገለጽ ነገር ነው፡፡ አካል እንደ ዓይነቱና ምንነቱ ወይም ማንነቱ ወጥነት ያለው አንድ ዓይነት ሊኾን ወይም በመልክ፣ በአጠቃላይ ግን የሰው አካል ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ያለውን ሰብዓዊ መገለጫ ያጠቃልላል፤ ‹እኔ ባይ› ወይም መጠሪያ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አካልም በኹለት መልኩ ሊገለጽ ይችላል፤ በርቅቀት ወይም በግዝፈት፣ በውስንነት ወይም ባለመወሰን፣ በተለዋዋጭነት ወይም በዘላለም ቀዋሚነት፣ በሙሉት ወይም በጎዶሎነት ይገለጻል፡፡
  የአንድ ህልው ነገር ባሕርይም ወጥ ነው አይለዋወጥም አካሉ ግን በቅርጽ፣ በኹኔታ፣ በመልክና በጊዜ ቆይታ ሊቀያየርና ሊለያይ ይችላል፡- ባሕርዩ ቢቀያየር ወይም ቢለዋወጥ ኖሮ ግን አንድን ሰው ወይም ነገር የአካሉ ገጽታ በተቀያየ ጊዜ እሱነቱን ለመለየት እንቸገር ነበር፡፡ ስለዚኽ የየትኛውም ነገር አካሉ የህልው ነገር ባሕርይ የሚገለጽበት፣ ህልው ነገሩም በዓይነት፣ በመልክ፣ በቅርጽ፣ በኹኔታና በጊዜ ተለያይቶ የሚዘረዘርበትና በረቂቅነት ወይም በግዙፍነት የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ስለዚኽ ህልው ወይም እውን ነገር ስንል በአካል የተገለፀ በባሕርዩ ተለይቶ ማንነቱ ወይም ምንነቱ የሚታወቅ ነገር ማለታችን ነው፡፡

 4. ወንድሜ ያነሣኸው ጥያቄ ከምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) ጋር የተያያዘ ነው፤ኾኖም ግንዜቤ ከሰጠኽ ጠቅለል ያለ አስተያየት ከዚህ በታች አቅርቢያለሁ፡፡ ሰፋ አድርገህ ለማጥናት ከፈለክ ‹ቅኔ ዘፍልሱፍ› የሚለው መጽሐፍ ላይ ለማብራራት ሞክሪያለሁና፤ እዚያ ላይ ምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) በሚል ንዑስ ርእስ የተቀመጠውን ብትመለከተው መልካም ነው፡፡
  ህላዌ፣ አካልና ባሕርይ
  ህልውና (Existence) ‹ሀለወ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተወሰደ ሲኾን የሚገልፀውም መገኘትን ወይም መኖርን ነው፤ ስለዚኽ ‹ህልው ነገር› ማለትም የተገኘ ወይም የሚኖር ነገር ማለት ይሆናል፡፡ ህልውነት አካል (Body) እና ባሕርይ (Essence) በሚሉ ነገሮች (ፅንሳተ-ሐሳብ) የተሠራ ክስተት ነው፤ አንድ ‹ህልው ነገር› የራሱ ባሕርይና አካል ይኖረዋል፡፡ ህልውና ኖሮት የሚገኝ ነገር ኹሉ ባሕርይና አካል ሊኖሩት የግድ ስለኾነም ህልውነትን ከባሕርይና ከአካል ውጭ አድርጎ መረዳት አይቻልም፡፡
  ምናልባት ‹አካልና ባሕርይ የሚባል ነገር የለም› የሚል ተከራካሪ ካለ፤ እስቲ ቆይ እንጠይቅ! አንድ ነገር ‹ህልው ነው› ስንል አካል የለውም ልንል እንችላለን ወይ? ‹የለውም› ልንል ከቻልን፤ ታዲያ በምን ማስረጃ ወይም ኹኔታ ህልው መኾኑን ማወቅ ቻልን? ‹አዎ! ያለ አካል ሊከሰት የሚችል ነገር አይኖርም› በሚለው ከተስማማን ግን ባሕርይ የሌለው ‹አካላዊ ነገር› ሊኖር ይችላል ወይ? አእምሮ በረቂቅነት አንብቦ የማይተረጉመው አካል ሊኖር አይችልም፤ ባሕርይም የአካል መሠረታዊ ነገር፣ ያ አካል ተለይቶ የሚታወቅበት መነበቢያው ወይም የሥሪቱ ምክንያት ነው፡፡ ያ ከኾነም እንዴት አካሉ በሥሪተ-ነገሩ ሳይነበብ ወይም ባሕሪው ሳይገልጽልን ልናውቀው እንችላለን?
  በእውነታው ከጥንት ሊቃውንት ጀምሮም ህልውነትን ከባሕርይና ከአካል ጋር አያይዞ መረዳት የተለመደ ነገር ነው፤ አንድ ነገርም ያለ እነዚኽ ነገሮች በህልውና ሊከሰት አይችልምና፡፡ ህልውና ከአካልና ባሕርይ ጋር አያይዞ በመግልፅ በኩል ግንባር ቀደም የኾነው ፕላቶን ነው፤ ኾኖም ፕላቶን ባሕርይን ሰማይ ላይ ሲሰቅለው፤ አካልን ደግሞ ከዚያ ተቀድቶ የተከሰተ የመገለጫ ነፀብራቅ አድርጎ ወስዶታል፤ በዚኽ የተነሣም ህልው ነገርን በአካል ላይ የሚንፀባረቅ ሰማያት ውስጥ የተደበቀ ቅርጸ-ባሕርይ (Form) አድርጎታል፤ በሰማይ ህልው ኾኖ የሚገኘው ነገርም ጥላው በመሬት ላይ ተከስቶ እናገኘዋለን ባይ ነው፤ ስለዚኽ አካል የሰማዩ ነገር ጥላ (Shadow) ኾኖ የተገለፀ ስለኾነም በመሬት ላይ የሚገኘው ህልው ነገር ኹሉ ትክክለኛው እውን ነገር ሊኾን አይችልም፡፡
  ይኽንን የፕላቶንን የሰማያት ስቅለት በመቃወም ‹ባሕርይማ ከአካል ተለይቶ አይከሰትም፤ ስለዚኽም አንድ ህልው ነገር አካልና ባሕርዩ ሳይነጣጠሉ የሚገኙበት ክስተት ነው› በማለት የተከራከረው ተማሪው አርስጣጣሊስ ነው፡፡ የሀገራችን ሊቃንውትም የህልውናን ጉዳይ እንደ አርስጣጣሊስ በባሕርይና በአካል አለመነጣጠል መርህ ነው የሚገነዘቡት፡፡ መርሁም ‹ባሕርይ ያለ አካል አይከሰትም፤ አካልም ያለ ባሕርይ ተለይቶ አይታወቅም› የሚል ነው፤ ስለኾነም በሀገራችን ሊቃውንት ዘንድ ‹ህልውና›፣ ‹ህላዌ›፣ ‹ባሕርይ›፣ ‹አካል›፣ ‹ኩነት› የሚባሉ ቃላት ጥልቅ ትንታኔ ያላቸው ተገናኝና ተመጋጋቢ አስተሳሰቦች ናቸው ፡፡ ለምሳሌ ህልውና፣ ህላዌና ባሕርይ በኩነት በመገናዘብ አንድነት ያላቸው ናቸው፤ የሚገለፁትም በአካል አማካይነት ነው፡፡ ስለኾነም ነው ሁለቱ ባሕርይና አካል ተለያይተው አይከሰቱም የምንለው፡፡ ረቂቅ ወይም ግዙፍ ሊኾን ይችላል እንጂ አካል ሳይኖረው የሚከሰት (የሚገኝ) ህልው ነገርም አይኖርም፤ አንድ ነገርም አካል ነሥቶ በመከሰት የሚታወቀው በባሕርዩ ነው፤ ያለ ባሕርይ ማንነቱ (ምንነቱ) ሊታወቅ ወይም ሊለይ አይችልም፡፡ ስለዚኽ አንድ ህልው ነገር በአካሉ መገለጫነት፣ በባሕርዩ አሳዋቂነት (ገላጭነት) ተከስቶ ይታወቃል፡፡
  አሁን እዚኽ ላይም ቢኾን ‹አካልና ባሕርይስ ለየራሰቸው ምንድን ናቸው?› የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ላይገለጽልን ይችላል፡፡ ስለኾነም የተወሰነ ማብራሪያ መስጠት ይጠቅማል፤ ምርምራችን እንቀጥል፡፡
  ባሕርይ
  ከላይ እንደጠቀስነው ባሕርይ ማለት የአንድ ህልው ነገር ጥንተ መሠረት ወይም የተፈጥሮው ምክንያት ማለት ነው፡፡ ባሕርይ በአካል ህልው ኾኖ ከአካል ሳይለይ የአካልን ጠባይ ወይም ስሜት ይገልጻል፡፡ በመኾኑም አንድ በአካል ተለይቶ የተከሰተ ነገር የሚታወቀው ባሕርዩ በስውር አብሮት ኾኖ ማንነቱን ወይም ምንነቱን ሲያንጸባርቅለት ነው፡፡ ኾኖም ባሕርይ በረቂቅነት በሕሊና ይጻፋል እንጂ ይኽ ነው ተብሎ በስሜት ሕዋሳት አይገለጽም፡፡ ባሕርይ ጥንት መሠረት ወይም የተፈጥሮ ምክንያት ነው ስንልም ህልው ነገሩ የተፈጠረበት መሠረተ ነገር ነው ማለታችን ነው፡፡ ይኽም የሚገለጸው በሚከሰተው አካሉ ተንጸባርቆ ነው፡፡ ይኽን ይዘን ‹አካል እንዴት ነሽ?› እንበል!
  አካል
  አንድ ህልውና ያለው ነገር ህልውነቱ ተለይቶ የሚገለጸው በአካሉ ነው፤ አካል ስንልም ባሕርይ በስውር የሚገለጽበት ነገር ማለታችን ነው፤ ይኽም አካል ረቂቅ (መንፈስ) ወይም ግዙፍ ሊኾን ይችላል፡፡ የትኛውም ቢኾን የባሕርይ መገለጫ ህልው ነገሩ የሚያካትታቸው ነገሮች በሙሉ የሚገኙበት ነገር ወይም ‹እኔ ባይ›፣ ‹በእሱነት› ተጠቅሶ የሚገለጽ ነገር ነው፡፡ አካል እንደ ዓይነቱና ምንነቱ ወይም ማንነቱ ወጥነት ያለው አንድ ዓይነት ሊኾን ወይም በመልክ፣ በአጠቃላይ ግን የሰው አካል ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ያለውን ሰብዓዊ መገለጫ ያጠቃልላል፤ ‹እኔ ባይ› ወይም መጠሪያ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አካልም በኹለት መልኩ ሊገለጽ ይችላል፤ በርቅቀት ወይም በግዝፈት፣ በውስንነት ወይም ባለመወሰን፣ በተለዋዋጭነት ወይም በዘላለም ቀዋሚነት፣ በሙሉት ወይም በጎዶሎነት ይገለጻል፡፡
  የአንድ ህልው ነገር ባሕርይም ወጥ ነው አይለዋወጥም አካሉ ግን በቅርጽ፣ በኹኔታ፣ በመልክና በጊዜ ቆይታ ሊቀያየርና ሊለያይ ይችላል፡- ባሕርዩ ቢቀያየር ወይም ቢለዋወጥ ኖሮ ግን አንድን ሰው ወይም ነገር የአካሉ ገጽታ በተቀያየ ጊዜ እሱነቱን ለመለየት እንቸገር ነበር፡፡ ስለዚኽ የየትኛውም ነገር አካሉ የህልው ነገር ባሕርይ የሚገለጽበት፣ ህልው ነገሩም በዓይነት፣ በመልክ፣ በቅርጽ፣ በኹኔታና በጊዜ ተለያይቶ የሚዘረዘርበትና በረቂቅነት ወይም በግዙፍነት የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ስለዚኽ ህልው ወይም እውን ነገር ስንል በአካል የተገለፀ በባሕርዩ ተለይቶ ማንነቱ ወይም ምንነቱ የሚታወቅ ነገር ማለታችን ነው፡፡

Leave a Reply