ምሲዮኖችና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ምንና ምን ነበሩ? ከአለቃ አያሌው ታምሩ ታሪክ የተቀነጨበ

‹‹የላይኛውን ዓይኔን ወስዶ የውስጡን አበራልኝ› የሚሉት አለቃ አያሌው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ በሊቅነታቸው ከሚታወቁት ሊቃውንት አንዱና ግንባር ቀደሙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የእኝህን ታላቅ ሊቅ የሕይወት ታሪክ ልጃቸው ሥምረት አያለው አዘጋጅታ አሳትመዋለች፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ውስጥም በዘመናዊ የከፍተኛ ትምህርት አጀማማር ውስጥ የምስዮኖች ተጽዕኖ ምን ይመስል እንደነበር ያሳያል ያልኩትን ቀንጭቤ እዚህ አቅርቤዋለሁ፡፡IMG_20150819_143156
‹‹አባቴ በግርማዊነታቸው ፊት ከተቀኘ በኋላ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የነሣውን የዘመኑን ወጣት ኢትዮጵያውያ ሁኔታ አስመልክቶ የሚከተለውን አቤቱታ ለጃንሆይ አሰማ፡፡
‹… ጃንሆይ! ሃይማኖት እየጠፋ ነው፡፡ ጀስዊቶች በገቡበት አገር ሁሉ ያልተገለበጠ መንግሥት፣ ያልተናወጠ አገር… ያልተለወጠ ሥርዓት ያለመኖሩን ከእኔ የበለጠ ጃንሆይ ያውቃሉ፡፡ ሁሉ እየተነሣ ኃይለ ሥላሴ ይሙት… ኃይለ ሥላሴ ይሙት እያለ የአባቱ ማሳረፊያ ቢያደርግዎ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ ወጣቱን ትውልድ አዳሪ ትምህር ቤት ሰብስበው እያስተማሩ ነው፡፡ አስተማሪዎች ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን ታሪክ፣ እምነትና ባህል ከሚነግሩት በቀር የራሱን ታሪክ የሚያስተምረው የለም፡፡ እነዚህ ነገ ሲወጡ ጉድጓድ ውስጥ ያደገ የውሻ ግልገል መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ክፉ ነገር ቢመጣ እንኳን ደሙን የሚያፈስልዎ ውሃ የሚረጭልዎ አያገኙም…፡፡› በማለት ስለ ጊዜው ሁኔታ የነበረውን ሥጋትና ወደፊት ሊመጣ ይችላል ብሎ ልቡ የሰጋበትን ተናገሯል፡፡
ይህንን ንግግር ያደረገው ሥራዬ ብሎ በዓላማ ደረጃ ከያዛቸው የማስተማሪያ መንገዶች አንዱ ባለሥልጣናትን በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ መምከርና ማንቃት ተገቢ ነው ብሎ ያምን ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ሰያደርግ ደግሞ ከእነሱም ሆነ ከሌላው ‹የእኔ ዕውቀት ይበልጣል› በማለት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተሰጠው መንፈሳዊ ጸጋ የተነሣ ሌላው ሰው ከርቀት የማያየውን ነገር እርሱ በዓይነ ትንቢት የመገንዘብ ስጦታ ስለነበረው ጭምር ነው፡፡ በዚህ ዕለት አባቴ ያደረገው ንግግር ብዙዎች ከድፍረት ቢቆጥሩትም ንጉሠ ነገሥቱ ግን ችላ ብለው አላለፉትም፡፡ ይልቁንም ምን እንዲያደርጉለት እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡
እሱም ‹የዓለምን መጻሕፍት ለመመርመር የምችልበት፣ ዕውቀት የማገኝበት፣ እኔም በዐቅሜ ከአገሬ ዕውቀት የተማርኩትን ትምህርት ለዘመኑ ወጣቶች የማካፍልበት የመማርና የማስተማር ዕድል እንዲሰጠኝ ነው፡፡…› በማለት መለሰላቸው፡፡
ጃንሆይ ተጨማሪ ጥያቄዎች ነበሯቸው፡፡
‹ከየት ነው የመጣኸው?› ሲሉ ጠየቁት፡፡
‹ከጎጃም ክፍለ ሀገር ከሚገኘው ከታላቁ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡› በማለት መለሰ፡፡
‹የዓይንህን ብርሃን ባታጣ ኖሮ ምን ለመሆን ትመኝ ነበር?› ሲሉት፤
‹ምኞቴ ምናልባት ወታደር መሆን ነበረ፡፡› ሲል መለሰላቸው፡፡
‹እንኳን ዓይንህ ጠፋ፡፡› አሉ ጃንሆይ፡፡
‹እንዲህ ባይሆን ጠንክረህ አትማርም ነበር፡፡ ደግሞ ወታደርነቱም አልቀረብህም የክርስቶስ ወታደር ነህ፡፡ አይዞህ በርታ፡፡› ብለው ወደ ማስተማሩ ሥራ እንዲያተኩር መከሩት፡፡ በማስከተልም በቀዳማዊ ኃይለ ሥለሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያስተምር መፍቀዳቸውን ገለጡለት፡፡ እዚያው አጠገባቸው የነበሩትን አቶ ከበደ ሚካኤልንም ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ አዘዟቸው፡፡ በዚሁ መሠረት በዩኒቨርስቲው እያስተማረ በወር አንድ መቶ ሃያ አምስት ብር እንዲከፈለው የተፈቀደ መሆኑን የሚገልጥ ደብዳቤ ለትምህርት ሚኒስቴር ሒሳብ ክፍል ተጻፈለት፡፡
በርከት ባሉ ዘመናዊና መንፈሳዊ ምሁራን የተከበቡት ንጉሠ ነገሥት የቅኔ መምህር በአገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ በነበረው የትምህርት ተቋም ውስጥ እንዲያስተምር ሲፈቅዱ ሁኔታው ካስደሰታቸው ይልቅ ያስከፋቸው ይበልጡ ነበር፡፡ ከተከፉት መሐል አንደኛውና ግንባር ቀደሙ የዩንቨርስቲው ዲን ካናዳዊ የጀዌስዊት ሚሲዮን ቄስ ዶክተር ማት ነበሩ፡፡
….
ዩኒቨርስቲው ሲቋቋም አመራሩን የተረከቡት ቄስ ሉቺያ ማት ሲሆኑ በእርሳቸው ይመራ የነበረው የጀስዊትስ ቡድን የቀዳማዊ ኃይለ ሥልሴን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅን ለመምራት ከመመረጣቸው አስቀድሞ በዚያን ጊዜ ተፈሪ መኮንን እየተባለ ይጠራ የነበረውን ትምህርት ቤት በማስተዳደር ላይ ይገኙ ነበር፡፡
እነ ቄስ ማት… ከዘመናት ሕልምና ረጅም ዕቅድ በኋላ የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ የሚሆኑ ወጣት ምሁራንን ለማብቀል የተዘጋጀውን ዩኒቨርስቲ በብልኀት ተቆጣሩት፡፡ በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ ያገኟቸውን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ሥልጡን ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ወደ አበሻ ፈረንጅነት እየለወጡ ቀንና ሌሊት ያለ ዕረፈት ይሠሩ በነበረበት ወቅት ያገሬን ወጣቶች ሃይማኖታቸውንና ታሪካቸውን እኔ አስተምራለሁ የሚል ደፋር መሪጌታ ሲመጣባቸው በቀላሉ አላዩትም፡፡ በመሆኑም አባቴ በዩኒቨርስቲ እንዲያስተምር ከግርማዊነታቸው የተሰጠውን ትእዛዝ ለማስለወጥ በቤተ መንግሥቱ አካባቢ ተሰሚነት በነበራቸው ኢትዮጵያውያን በኩል ሙከራ አደረጉ፡፡
‹መሪጌታ አያሌው ወታደሮችን እንጂ ተማሪዎችን ማስተማር የለበትም› እስከ ማለት የደረሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በጃንሆይ ፊት ተቃውሟቸውን የገለጡ በእምነታቸው ጄስዊቶቹን የሚመስሉ ዘመናዊ ትምህር የተማሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ነበሩ፡፡ ነገር ግን የንጉሠ ነገሥቱን ትእዛዝ ማስለወጥ አልቻሉም፡፡
በመሆኑም ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ሳይወድ በግድ ማሰተማሪያ ሰዓትና ቦታ ስለ ፈቀደለት በግንቦት ወር ፩፱፻፵፱ (1949)ዓ.ም. ማስተማር ጀመረ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ‹የማስተማሪያ ጊዜ ስለተሸማህብን በቀኑ ክፍለ ጊዜ ያኝተን ትምህር ማስተናገድ አንችልም፤ ከፈለግህ ማታ ማታ እየመጣህ ማስተማር ትችላለህ› አሉት፡፡ እሱም በተሰጠው ጊዜ መጠቀምን ስለመረጠ ማታ ማታ ማስተማሩን ቀጠለ፡፡ በርቱዕ አንደበቱና በተብራራ ትምህርቱ የተማረኩት ወጣት ኢትዮጵያውያ ትምህርቱ ከቀን ወደ ማታ በመለወጡ አልተከፉም፤ አልቀሩም፡፡ እንዲያውም ወደ አዳዲስ ሃይማኖት ተወስደው የነበሩ ሁሉ እየተመለሱ ትምህርቱን በከፍተኛ ንቃት መከታተል ጀመሩ፡፡ አንዱ አንዱን እየሳበ ከቀን ወደ ቀን እየበረከቱ ጉባኤውን አጠናከሩት፡፡ ከዚህ የተነሣ የተመደበላቸው ፵፭ (45) ደቂቃ አልበቃ እያለ እስከ ምሽቱ ፬ (4) ሰዓት ድረስ ማምሸት ጀመሩ፡፡
የማታው ክፍለ ጊዜ ካሰቡትና ካቀዱት ውጪ የሆነ ውጤት ያስከተለባቸው እነ ቄስ ማት አባቴ አንድ ዓመት ካስተማረ በኋላ ደግሞ ሌላ ነገር አሰቡ፡፡ ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ በ፩፱፻፶ (1950)ዓ.ም. የክረምት ዕፍት ተዘግቶ ቆይቶ ሲከፈት አባቴ የሚያስተምረው መንፈሳዊ ትምህርት ከዋናው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ግቢ ወደ ምህንድስና ኮሌጅ እንዲዛወር መወሰኑን ነገሩት፡፡ የምህንድስና ኮሌጁ በዚያን ጊዜ ተግባረዕድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ግቢ ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡
በ፩፱፻፶፩ (1951)ዓ.ም. የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ላይ አባቴ ከዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ምህድስና ኮሌጅ ሄደ፡፡ ኮሌጁን የሚመሩት አሜሪካዊ ዘንድ ቀርቦ ሥራውን ለመጀመር ሲያኘጋግራቸው ከምሽቱ ፩ (1) ሰዓት ጀምሮ ፵፭ (45) ደቂቃ የሚቆይት ክፍል እንደሚሰጡት ነገሩት፡፡ የእርሱን ትምርህት የሚፈልግ ተማሪ ካለ ገብቶ ቢማር ተቃውሞ እንደሌላቸው ገልጠው እሳቸው ግን የሚማሩ ተማሪዎችን እንደማይመድቡለት አሳወቁት፡፡
‹ተማሪ ሳይመደብልኝ ማንን አስተምራለሁ?› ብሎ ቢጠይቃቸው፤
‹ክፍል ስጠው እንጂ ተማሪ መድብለት አልተባልኩም› የሚል መልስ ሰጡት፡፡ ትእዛዛቸውን ተቀብሎ ወጣ፡፡ ምናልባት የሚመጡ ተማሪዎች ባገኝ ብሎ በተሰጠው ጊዜና ቦታ ጠበቀ፡፡ ለተማሪዎቹ ስለ ሁኔታው የተገለጠላቸው ነገር ስላልነበር ወደ እርሱ ክፍል የሚመጡ ተማሪዎች ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ለተወሰኑ ቀናት በተሰጠው ባዶ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ የሚመጡ ተማሪዎች ሲጠብቅ ያመሽና የተመደበለት ሰዓት ሲያልቅ ወጥቶ ይሄድ ነበር፡፡ የትምህር ቤቱ አስተዳደር ለተወሰኑ ቀናት ሁኔታውን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ‹ወደ አንተ ክፍል የሚመጣ ተማሪ ስሌለ ወደ ግቢው መግባት አያስፈልግህምና ከዚህ በኋላ እንዳትመጣ፡፡› ብሎ ወደ ግቢው እንዳይገባ በጥበቃ ሠራተኞች አሳገደው፡፡
እሱ ግን እንዲህ አሉኝ ብሎ አልቀረም፡፡ በተመደበለት ቀንና ሰዓት ወደ ትምህርት ቤቱ እየሄደ ከግቢው ውጪ ይቆምና ልክ ፵፭ (45) ደቂቃዋ ስታልቅ ተመልሶ ይሄድ ነበረ፡፡ ይህንን ትዕይንት በተደጋጋሚ ሲከታተል የነበረ አንድ ተማሪ ትኩረቱ ተሳበ፡፡ ይህ ሰው አስፋው በላይ የተባለ የተግባረ እድ ትምህርት ቤት (ተማሪ) ነበረ፡፡ ተማሪው ሁኔታው ስላስገረመው ከዕለታ በአንዱ ቀን ጠበቀው፡፡ በሰዓቱ መጥቶ ከበሩ አጠገብ ሲቆም ተጠግቶ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ ለምን በየጊዜው እየመጣ እንደሚቆም ጠየቀው፡፡
አባቴም ንጉሠ ነገሥቱ በፈቀዱለት መሠረት እንደ ምን ለማስተማር እንደ ተመደበና ወደ ተግባረ እድ ትምህር ቤት እንዴት እንደ መጣ ነገረው፡፡ ሆኖም ተማሪዎች ስላልተመደቡለት ማስተማር አለመቻሉን በመጨረሻም ክፍሉን እንደቆለፉበትና ወደ ቅጽረ ግቢውም እንዳይገባ እንዳገዱት ነገረው፡፡
በሁኔታው የተገረመው ተማሪ አስፋው ‹ታዲያ በሩ ከተዘጋብዎ ለምን አይሀዱም? ለምንስ ይቆማሉ?› በማለት መልሶ ጠየቀው፡፡ አባቴም ‹ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ሂዱና አስተምሩ ሲላቸው፤ ባይሰሟችሁ እንኳን የእግራችሁን አቧራ አራግፋችሁ ሂዱ ብሏቸው ነበር፡፡ እም ጊዜዋ እስክታልፍ ጠብቄ የእግሬን አቧራ አራግፌ ለመሄድ ነው የቆምኩት› ብሎ መለሰለት፡፡ የዚያን ጊዜው ተማሪ የአሁኑ አዛውንት አቶ አስፋው ከሃምሳ ዓመት በኋላ ስለዚያች ቀን ትዝታቸው በጻፉት ማስታወሻ ላይ አባቴ ይህን መልስ ሲሰጣቸው የተሰማቸውን እንደሚከተለው ገልጠውታል፡፡
‹… ከሰጡኝ መልስ በመነሣት በሳል ዕውቀት እንዳላቸው ብገምትም የተዋሕዶ ሃይማኖት ርቱዕ አስተማሪ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም ነበር፡፡ ከተለያየን በኋላ እርሳቸውን የሚያውቁ ተማሪዎች ስጠይቅ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥነ መለኮት ሊቅ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡…›
ተማሪ አስፋው ስለ ሁኔታው ከተረዳ በኋላ ወደ ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ዘንድ ቀርቦ፤ ‹የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች አስተማሪዎች እየገቡላቸው ይማራሉ የእኛን ሃይማኖት እንዲያስተምሩ የተመደቡት መምህር ለምንድነው የተከለከሉት? እንደ ሌሎቹ ጓደኞቻችን እኛ ስለ ሃይማኖታችን ማወቅ ስለምንፈልግ መምህር ይመደብልን፡፡› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡
በዚህ ጥያቄ ምክንያት አባቴ እየገባ እንዲያስተምር ተፈቀደለት፡፡…››
(አባቴና እምነቱ፡- የአለቃ አያሌው ታምሩ የሕይወት ታሪክ፤ ከገጽ 90-101 ካለው ታሪክ የተወሰደ)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply