ቀ/ኃ/ሥላሴ እና አሥመራ

“አሥመራ ያደገችው በቀ/ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና በደጃዝማች ሐረጎት ዐባይ ከፍተኛ ጥረት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሐቅን ለመሸፈን ካልተፈለገ በስተቀር፡፡
ለምሳሌ የአሥመራ ኤክስፖ በ1961 ዓ.ም የተካሄደውንና በግልጽ የተቀመጠውን ‹አሥመራ ኤክስፖ› በሚል መጽሐፍ ገጽ 47 በ5 ዓመት ውስጥ የተከናወኑትን ሥራዎች ለማስረጃ ያህል እንዳለ አስቀምጫለሁ፡፡
1ኛ የአሥመራ ምፅዋ አሰብ፣ ከረን፣ አቆርዳት፣ መንደፈራ፣ ደቀመሐረ፣ ተሰነይ፣ ዐዲኳላ እና የጊንዳዕ ማዘጋጃ ቤቶች ከሐማሴን ሠራዬ አከለጉዛይ ምፅዋ አሰብ፣ ከረን፣ ሣሕል፣ አቆርዳት ጋሽና ሰቲት አውራጃ ገዥዎች ጋር ሆነው 25 ሚሊዮን 694 ሺህ 735 ሰዎች አዲስ የንግድ ኢንዱስትሪ የተግባረ ዕድ የመጓጓዣ የሥራ ፈቃድ ሰጥተዋል፡፡
2ኛ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በአሥመራ ከተማ ቁጥራቸው 35 ሺህ 807 መኖሪያ ቤቶች በ5 ሚሊዮን 735 ሺህ ብር፣ እንዲሁም 8 ሺህ 103 የንግድ ቤቶችና የኢንዱስትሪ ህንጻዎች በ2 ሚሊዮን 425 ሺህ ብር የተሠሩ ሲሆን የአባ ሻውል የገዛ ብርሃኑና የማዕከላይ ሠፈር ቀበሌዎች በደንበኛ ዘመናዊ ዕቅድ እንዲሠሩና ለከተማ መልክ እንዲኖራቸው ለማድረግ በታቀደው ፕላን መሠረት በፈረሱ ምትክ መኖሪያ ቤቶች እየተሠሩባቸው አዳዲስ ቀበሌዎች ተጨምረዋል፡፡
3ኛ በምፅዋ ከተማ 15 ሚሊዮን 37 ሺህ 973 ብር ከ40 ሣናቲም ወጪ የተደረገባቸው መኖሪያ ቤቶች ቪላዎችና የኢንዱስትሪ ቤቶች በድምር 433 ሕንፃዎች ተሠርተዋል፡፡
4ኛ በዓዲ ኳላ ለ71 ሕንፃዎችና ለማዘጋጃ ቤቱ ልዩ ልዩ ሥራ 312 ሺህ 115 ብር ከ85 ሣንቲም ወጪ ተደርጓል፡፡
5ኛ በመንደር አዳዲስ ሕንፃዎች ተሠርተዋል፡፡ ለዚሁም ሥራ ግለሰቦች ለገዛ ጥቅማቸው ማዘጋጃ ቤቱ ለሕዝብ አገልግሎት ወጪ ያደረጉት ገንዘብ 237 ሺህ 385 ብር ከ52 ሣንቲም ነው፡፡
6ኛ በደቀመሐሪ 305 ሺህ ብር የፈጁ 25 አዳዲስ ሕንፃዎች ተሠርተዋል፡፡
7ኛ በከረን ከተማ በ1 ሚሊዮን 498 ሺህ 100 ብር አዳዲስ ቤቶች ሲሠሩ ለከተማው ልዩ ልዩ ሥራ 173 ሺህ 777 ብር ከ57 ሣንቲም ወጪ ሆኗል፡፡
8ኛ በአቆርዳት ከተማ ከሕዝብና ከግለሰብ ገንዘብ 1 ሚሊዮን 106 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ 86 አዳዲስ ሕንጻዎች ተሠርተዋል፡፡
9ኛ በተሠነይ አዳዲስ ለተሠሩ 17 ቤቶችና ለማዘጋጃ ቤት ሥራ 247 ሺህ 700 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡
10ኛ በአሰብ ከተማ አዳዲስ ለተሠሩ 28 ሕንጻዎች ለሕዝብ አገልግሎት ሥራ 2 ሚዮን 380ሺህ 600 ብር፣ እንዲሁም ለንግድ መርከቦች ሥራ 46 ሚሊዮን ወጪ ተደርጓል፡፡ ይህ የገንዘብ ቁጥር በአሁኑ የገንዘብ ስሌት እና ዋጋው ቢተመን በቢሊዮን የሚቆጠር ይሆናል፡፡
… የኤርትራ ሕዝብ ቀ/ኃ/ሥላሴን በጣም ይወዳቸው እንደነበርረም በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ አሥመራንለመጎብኘት ሲመጡ ሕዝቡ ማንም ሳያስገድደው ከአሥመራ ቤተመንግሥት ጀምሮ እስከ ሰንበል አራተኛ ዮሐኝስ አይሮፕላን ማረፊያ ድረስ ያለውን መንገድ ግራ ቀኝ ተሰልፎ ይቀበላቸው ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በቀበሌ ሳይገደድ ጥሩንባ ሳይነፋና ሳይታዘዝ በራሱ ፈቃድነ ስሜት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ የሕዝብ ፍቅር ምን አለ ትላላችሁ? እንዲያውም ጀንሆይ ከመጡ ዝናብ ይዘንባል እየተባለ ይነገርላቸው ነበር፡፡”
(ይትባረክ ግደይ፣ የቅኔ ቤት ባህልና የሕይወቴ ገጠመኝ፣ ገጽ 79-82)

Please follow and like us:
error

Leave a Reply