‹ቅኔ-ዘፍልሱፍ› መጽሐፍ ምን ይዞ መጣ? ምንስ ይጎድለዋል?

ከጥበብ ፈለቀ

ብሎብኝ ፍልስፍና ነክ የሆኑ መጽሐፎች ለማንበብ ይማርኩኛል፡፡ ለዚህ በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ ማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በመተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች በፍልስፍና ዙሪያ የሚሠጡ አስተያየቶችን ቀድሜ ለመመልከት ጉጉት ያድርብኛል፡፡ ሰሞኑንም ‹ቅኔ-ዘፍልሱፍ› የሚል መጽሐፍ ገዝቼ አነበብኩ፤ በእውነቱ ጥሩ መጽሐፍ ነው፡፡

ከጸሐፊ ጋር በፌስቡክ የማኅበራዊ ሚዴያ ጓደኛሞች ስለሆንን የሚጽፋቸውን መጣጥፎች እመለከታለሁ፡፡ በተለይም ፍልስፍናን ከኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ጥበባት ጋር ለማያያዝ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ያስደስቱኛል፡፡ ስለሆነም ‹ቅኔ-ዘፍልሱፍ› የሚል መጽሐፉም ለእኔ ብዙ የተማርኩበትና የተለዩ ሐሳቦችን የያዘ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በመጽሐፉ ላይ የለኝን ትዝብትና ትችት ጨምሬ አስተያየት ለመስጠት የፈለኩትም ለዚያ ነው፡፡ ሆኖም ወደመተቸቱ ያደላሁም ይመስለኛል፤ ለማንኛውም መልካም ምንባብ፡፡IMG_20171028_185337

መጽሐፉ ከርዕሱ ጀምሮ ለየት ያለ አዲስ ነው ለእኔ፡፡ ይሁንና ግን ስለ ርዕሱ ጸሐፊው ያስቀመጠው ማብራሪያ የለም፡፡ ‹ቅኔ-ዘፍልሱፍ› ምን ማለት ነው በሚል ግዕዝ የሚያውቅ ሰው ለመጠየቅ ሞክሬ ነበር፡፡ አንድ ጓደኛዬ ‹የፋላስፋ ቅኔ› ማለት መሆኑን ነግሮኛል፡፡

እኔ መጽሐፉን ጠብቄ የነበረው ጸሐፊው ባዘጋጀው መልኩ አልነበረም፡፡ ከርዕሱ ጋር በተያያዘ ‹ፍልስፍና የእውነት የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ› በሚል የተጠቀሰውን ‹ቅኔ የተፈጥሮ ምሥጢር መፍቻ ጥበብ› ማለቱን በማያያዝ ‹የቅኔ ፍልስፍና ምንድን ነው?› ለሚል ጥያቄ መልስ ሰጪ መጽሐፍ ነበር የጠበኩት፡፡ ይህ የጠበቁትን እንዳልያዘ ግን ጸሐፊው ገና በመቅደሙ ‹መጀመሪያ መጽሐፉን ሳዘጋጀው የፍልስፍናን ቅኔነት እና የቅኔን ፍልስፍናነት የሚዳስስ ባለሁለት ክፍል አድርጌ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ክፍልም በዚህ መጽሐፍ የቀረበው ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ለብቻው ራሱን የቻለ መጽሐፍ ሆኖ ቢታተም የተሻለ ይኾናል በሚል አማራጭ ሐሳብ እዚህ ሳላካትተው ቀርቻለሁ› የሚል ሐሳብ አቅርቦ ሳነብ ቅር አለኝ (ገጽ 7)፡፡ ነገር ግን ጸሐፊው ‹በቅድሚያ የፍልስፍናን ቅኔነት ቃኝቼ ወደ አስደናቂዎቹ የኢትዮጵያውያን ጥበባት መጥለቅ የተሻለ ሆኖ ተሰማኝና ይህን መጽሐፍ አዘጋጀሁ፡፡› (ገጽ 7) ይላልና በኢትዮጵያ ጥበባት ዙሪያ ለማሳተም ያዘጋጃቸው ሥራዎች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የፍልስፍናን ቅኔነት እኔ ባየሁበት መንገድ የተመለከተው የለም ስለሚልም ‹ምን የተለየ ነገር ይዟል?› የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ነገር ግን የተለየ መሆኑን መመስከር ያለበት ጸሐፊው ሳይሆን ሐያሲ ወይም አንባቢው መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ እንደገናም የፍልስፍና ቅኔ ከተባለ የፍልስፍናን እና የቅኔን ግንኙነት ማሳየት፣ በተለይም ከቅኔ ዘይቤያዊነት አንጻር ፍልስፍና እንዴት ሊስማማ እንደሚችል ማስረዳት የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ጸሐፊው ግን ‹የቅኔን ፍልስፍና› መጽሐፉ እንዳማያካትት ሲገልጽ የዘነጋው ቁምነገር ፍልስፍናን ቅኔ ነው ብሎ ከተከራከረ ቅኔ እንዴት ከፍልስፍና ጋር እንሚስማማ ማያያዝ ማስፈለጉን ነው፡፡ የቅኔን ፍልስፍና ለብቻው ማሳተም የጸሐፊው መብት ነው፤ ግን ለእኛ የተቆረጠ ሐሳብ የያዘ መጽሐፍ የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡

በአቀራረብ በኩል የመጽሐፉ መግቢያ ይማርካል፤ ዓላማውም ‹የፍልስፍናን ቅኔነት በመሞገት ኢትዮጵያዊ ይትበሀል አላብሶ ለማሳየት› ነው ስለሚል ‹ፍልስፍና በኢትዮጵያዊኛ ምን ዓይነት ነች?› የሚል ጥያቄም ይጋብዛል፡፡ ጸሐፊው ፍልስፍና በኢትዮጵያዊኛ የሚገለፀው በቅኔ ቅኝት ነው ይለናል፡፡ እዚህ ላይ ግን ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚጨነቁ ወጣት ደራሲያን እየመጡ መሆናቸው የሚያስደስ ነው፡፡ ለምሳሌም በቅርቡ ለንባብ የበቃውን የብሩህ ዓለምነህ ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› መጽሐፉ ለዚህ አባባሌ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ደራሲው ካሣሁን ዓለሙም ፍልስፍናን ከቅኔ ጋር ለማስማማት ያደረገው ጥረት ከዕይታው ጀምሮ አገራዊ የፍልስፍና ተቆርቋሪነት እንዳለው ይገልጻል፡፡ ይኸ ጥሩ ጅምር ሆኖ ይሰማኛል ለእኔ፡፡

በመዋቅር ደረጃ መጽሐፉ ካካተታቸው አራት ምዕራፎች፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ መንደርደሪያና ማሳረጊያ ተብለው የቀረቡትን ጨምሮ ‹ፈላስፋ ማን ነው?› የሚል የት/ቤት ክርክር እና ‹የፍልስፍና የእውነት ዕውቀትና መልካምነት ቅኔ መሆን› የሚሉ ይዘቶችን ያካትታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስለፈላስፋ ማንነት የሚያትተው አቀራረቡ በውይይት መልክ የቀረበ ነው፡፡ ከሌላው ክፍል አቀራረብ ተለይቶ ለምን በዚህ መልክ እንደቀረበ ግልፅ አይደለም፡፡

ፍልስፍና የእውነት፣ ዕውቀትና መልካምነት ቅኔበሚል ንኡስ ርእስ የቀረበው ሃይማኖታዊ ጫና ቢያይልበትም ዕይታው ተመችቶኛል፡፡ ጸሐፊው በመቅድሙ ላይባለእግዜር ሰው ነኝስላለ ሃይማኖታዊ ጫናውን ከሚያይበት መስታወት አንጻር መቀበል ይቻላል፡፡ ፍልስፍናን ከእምነትና ከቅኔ ጋር ለማዋሐድ ያደረገው ጥረትም ለእኔ አዲስ ሆኖብኛል፡፡ በገጽ 76-77 ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ የመጽሐፉን ማጠንጠኛ የያዘና የምዕራፉም ዋና አስኳል ይመስለኛልና አብረን እንመለከተው፡፡

ጥበብ ማለት ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋሕዶ ናት› ብለናል፤ ፍቅርን ደግሞ ‹ማግኔተ-ተዋሕዶ› በሚል ተስማምተናል፡፡ በዚኽ መሠረት ፍቅር የኹለት ነገሮች የተዋሕዶነት ማግኔት ከኾነ፤ ጥበብም ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋሕዶ› ከኾነች፤ የፍቅር ማግኔጢስነት ተዋሕዶን ለማምጣት ነውና፤ ‹ተዋሕዶ› የሁለቱ የፍቅርና የጥበብ የጋራ ባሕርያቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይኽ ከኾነም ‹ፍቅረ-ጥበብ› ወይም ፍልስፍና ስንል ‹ማግኔጢሳዊ የኾነ የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋሕዶ› ማለታችን ይሆናል፡፡ እንዲሁም ‹ፍቅር፣ ተዋሕዶና ቅኔ በምሥጢር አንድ ናቸው፤ በአሐዳዊነት ይገናዘባሉ› ብለናል፤ ምክንያቱም ሦስቱም የውሕደትን ምሥጢርና ጥብቀት የሚገልጹ ናቸው፤፤ ማለትም የፍቅር ግብ ተዋሕዶነትን እውን ማድረግና መጠበቅ ነው፤ ተዋሕዶ ደግሞ የኹለት (የብዙም ሊኾን ይችላል) ነገሮች አንድ የመኾን ምሥጢር ነው፤ ይኽም ምሥጢራዊ አንድነት ቅኔ ይኾናል፤ ቅኔ የምሥጢር ጉድጓድ የኾነ የድንቀት ቋት ነውና፡፡ በዚኽ መሠረት ፍልስፍና ስንል ጠለቅ/መጠቅ ካደረግነው ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ› ማለታችን ይሆናል፤ ጥበብ ድግሞ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋሕዶ› ናት ስላልን ፍልስፍና ስንል ‹ጥበበ-ቅኔ› (የቅኔ ጥበብ) ማለታችን ይኾናል (በቅኔ ውስጥ ፍቅር፣ ተዋሕዶ፣ ምሥጢር፣ ድንቀት፣… አብረው አሉና)፡፡

ግን በአገራችን የእውነት አተረጓጎም ግልጽ ስላልሆነ እውነት ሲል Truthን ነው የሚያመለክተው ወይስ Reality ማለቱ ነው? ዕውቀትንስ በknowledge ትርጉሙ ነው ወይስ Epistemology ማለቱ ይሆን? መልካምነት ሲልም በእንግሊዘኛው Good የሚለውን ቃል መጠቆሙ ግልጽ ነው፡፡ ግን የእሴቶች (Values) ማጠንጠኛ መልካምነት ብቻ ነው ወይ? Right ወይም Wrong የሚሉ ቃላት እንደ መልካምነት እኩል ዋጋ አላቸውና፡፡ በሌላ በኩል ለኒቼ Power፣ ለሾፐሐወር Will የእሴቶች ማጠንጠኛዎች ናቸው፡፡ ይህም መታየት ነበረበት፡፡ እነዚህን ነጥቦች የጠቀስኩት በቀጣይ ምዕራፎችም ሳይብራሩ የተቀመጡ መሆናቸውን ስለታዘብኩ ነው፡፡

ምዕራፉ ሁለት በአጠቃላይ ስለእውነት እና በተወሰነ ደረጃ ደራሲው ምሥጢረ-ፍጥረት (Metaphysics) እና ምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) ብሎ ስለሰየማቸው ነጥቦች ያነሣል፡፡ ስለ እውነት (Truth) የተለያዩ ትርጓሜዎች ንድፈ ሐሳቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዘኛው (1) Correspondence Theory፣ (2) Coherence Theory፣ (3) Pragmatic Theory እና (4) The Redundancy Theory… ምሁራን የሚከራከሩባቸው የእውነት ንድፈ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ጸሐፊው ግን እውነትን የተረጎመው ከCorrespondence Theory አንጻር ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እጓለ ገ/ዮሐንስ እውነት ‹ሕሊና የሚሰጠው ፍርድ ከገዛ ራሱ ሕግጋት ጋር የሚስማማ ሲኾን ነው፡፡› ያለውን እንደመነሻ በመውሰድ ‹እውነት ማለት የህልው ነገር በሐሣብነት በአእምሮ በትክክል መወከል ነው› የሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ እንደ ንጽጽር ግን አማራጮችን በማስቀመጥ መተርጎም ይጠበቅበት ነበር፡፡ ያለበለዚያ ክርክሩን ወይም ትርጓሜውን የተሟላ አያደርገውም፡፡

ሌላው መታየት ያለበት ስለ ህልውና (Existence) ያቀረበው ነው፡፡ ጸሐፊው ህልውና ከባሕርይና አካል አንጻር ብቻ መተርጎም አለበት የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ በዚህ የተነሣም ዘመናዊያን የህልውና ፈላስፎችን ክርክር ሳይቀበል የጥንቶቹን እነ አርስቶትልና የቤተክህነት ሊቃውንት አተረጓጎም ነው የተጠቀመው፡፡ ጥያቄው ግን የእነ ሶሬን ኬርጋርድ፣ ፈርደሪክ ኒቼ፣ አልበርት ካሙ፣ ሳትረ… ክርክሮች ያልተካተቱበት የህልውና ክርክር ምን ዓይነት ነው? ይህ ጥያቄ እንዳፈጠጠ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ መልሶ ወይም መከራከሪያውን በአግባቡ አቅርቦ ቢያሳምነን መልካም ነበር፡፡ ሆኖም ጸሐፊው ክርክሬ በኢትዮጵያዊ ዕይታ የተቃኘ ነው ስለሚል ምን ያህል የኢትዮጵያዊ አተረጓጎምን ማሳየት ችሏል የሚለውን ለመመለስ ለእንደ እኔ ዓይነቱ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ምዕራፍ ሦስት ስለ ሥነ-ዕውቀት (epistemology) የሚያብራራ ነው፡፡ በዚህም ሦስት ንዑስ ርእሶች ተካተውበታል፡፡ የመጀመሪያው ‹ዕውቀት የእውነት፣ የእምነትና የአመክንዮ (ምክንያት) ቅኔ› ነው ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ› ያላቸውን ግንኙነት የሚከራከር ሲሆን ሦስተኛው ንዑስ ርእስ ‹ልቦና፣ ሕሊና እና የስሜት ሕዋሳት› ስላላቸው ግንኙነት የሚከራከር ነው፡፡ በአጠቃላይ ምዕራፉ ዕውቀትን በእውነት፣ በእምነትና በምክንያት እንደተሠራ እና ስፋቱም በሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ እንደሚጠቃለል፣ እንዲሁም ከልቦና ፈልቆ በሕሊና እንደሚታሰብ ይሞግታል፡፡

ምንም እንኳን የሃይማኖት ጠበቃነት ቢንፀባረቅበትም ከፍልስፍና እና ከሳይንስ ጋር እያነጻጸረ ያቀረበበት መንገድ ተመችቶኛል፡፡ በተለይም ደግሞ በድያግራም አስደግፎ የሰዎችን አስተሳሰብ ከሃይማኖት፣ ከሳይንስና ከፍልስፍና አንጻር የቃኘበት መንገድ የሰዎች አስተሳሰብ በምን ላይ እንደሚመሠረት ይሞግታልና ማንኛውም ሰው የራሱን አስተሳሰብ ሳይቀር ይመዝንበታል፡፡ ይህ በጣም የወደድኩት አቀራረብ ነው፡፡

ከልቦና፣ ሕሊና እና የስሜት ሕዋሳት ጋር በተያያዘ ያቀረበው ሐሳብ ብዙ የሚያሟግት ይመስለኛል፡፡ ‹እውን ግን ልቦና የሐሳብ መመንጫ መሆን ይችላል? እንዴት ነው ሕሊና ከልቦና ተቀብሎ የሚያስበው?…› የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውና ማከራከራቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ይህም ከአሁን በፊት በአግባቡ ያልተዳሰሰ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡

ምዕራፍ አራት ስለ መልካምነት የሚያትት ነው፡፡ ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር ይህንን ያህል በሰፊው ተብራርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ገለጻዎቹ ግን ጥልቀት አላቸው፡፡ ሆኖም መልካምነት በማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያለው ሚና ብዙ አልተገለጸም፡፡ ከሥነ ምግባር ወይም ግብረገብነት ጋር ተያይዞ የመልካምነት ማጠንጠኛዎች የተጠቀሱ ቢሆንም በኪነ ጥበብ፣ በሥነ ውበት፣ በሥነ መንግሥት፣… ያለው ሚና ተጠቅሶ ብቻ ነው የታለፈው፡፡ ከዚያ ይልቅ ጸሐፊው መልካምነትን ከሃይማኖት ጋር በማያያዝ ‹ያለ እግዚአብሔር መኖር መልካምነት ትርጉም አይኖረውም› የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡

ጸሐፊው ‹ባለእግዜር ሰው ነኝ› ያለውን ለማስረገጥ ይመስላል ሃይማኖታዊነቱ ተጭኖታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ በአጠቃላይ ግን መጽሐፉ የፍልስፍናን ቅኔነት ለመሞገት መሞከሩ መልካም ቢሆንም ቅኔነትን ከማሳየት ይልቅ ሃይማኖታዊ ጠበቃነትን ለማሳየት የተጣረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የቅኔን ፍልስፍና አለማካተቱ የተሟላ መከራከሪያ እንዳይኖረው ያደረገው ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም የመጽሐፉ ቃላቶች ከባድ ናቸው፡፡ የተጠቀመበት የጽሕፈት ፎንት ለማንበብ ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ ‹ሰ› እና ‹ለ›ን ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በተለይ የፎንቱ ጉዳይ በሁለተኛ እትም መስተካከል ይኖርበታል፡፡

እነዚህ ድክመቶቹ እንዳሉ ሆነው ግን መጽሐፉ አገራዊ ቃና ያለው መሆኑ አይካድም፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ የፍልስፍናን ዕውቀት ወደ አገር እየቀየሩ ለማሳየት መሞከርም ዕውቀቱን በአገራዊ መንፈስ መረዳት እንዲቻል ያደርገዋል፤ ፍልስፍናንም በእኛ መቃኘት እንደምንችል ምስክር ይሆናል፡፡ እንዲሁም ፍልስፍናን ቅኔ ነው ብሎ መሞገት አዲስ አሳብ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ላይ የፍልስፍና ምሁራን ምን እንደሚሉ ለመስማት ጓጉቻለሁ፡፡ በተጨማሪም የእኛን የፍልስፍና ልማድ ለሌሎች ለማሳወቅ ወደ ራሳችን አምጥተን ማየታችን መልካም ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር ጸሐፊ ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ እኔ በተሰማኝ መሠረት ይህንን ብያለሁ፤ ሌሎችም መጽሐፉን በማንበብ እንደ መወያያ አጀንዳ ቢያደርጉት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply