ቅኔ የፍልስፍና ላዕላይ ጥበብ

(በካሣሁን ዓለሙ)

መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣዉ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ብሩህ ዓለምነህ የተባለ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› የሚል መጽሐፍ ደራሲ ‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?› በሚል ርዕስ በቅኔ ፍልስፍናነት ላይ ትችት አቅርቧል፡፡  በእውነቱ ያነሳው ሐሳብ ስለ ፍልስፍና ጥሩ አገራዊ የክርክር መነሳሳትና ዕይታን የሚፈጥር ስለሆነ የበለጠ ትጋትንና የዕውቀት ብልፅግናን ያድልልን እላለሁ፡፡

እኔም በተነሳው ሐሳብ ላይ የራሴ የጥናት ጅማሮ ስላለኝ ምልከታየን ላከፍል ፈለኩ፡፡ ይሁንና በጽሑፌ የብሩህን መጽሐፍ ለመተቸት አልተነሣሁም፤ የኢትዮጵያ ፍልስፍናን ይዘትም ማሳየት ማጠንጠኛዬ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ቅኔን ከደረጃዋ አውርደን በአመድ ላይ እንዳናከባልላት ከፍተዋን በመጠኑ ለማሳየትና ለመሞገት ነው፡- አነሣሤ፡፡ ካስፈለገ የብሩህ መጽሐፍን ለመሔስና የኢትዮጵያን ፍልስፍና ይዘት ለማሳየት በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡

የብሩህ ክርክር ማጠንጠኛም መቋጫም ‹በተለያዩ ቅኔዎች መካከል በየጊዜው የሚገነባ አንድ ወጥነት ያለው የሐሳብ ሥርዓት መዘርጋት ስለማይቻል፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ከቅኔነት ውስጥ ማውጣት አይቻልም፡፡› የሚለው ነው፡፡ በዚህ መደምደሚያ ግን እኔ አልተስማማሁም፤ ባለመስማማት ካልተቀበልኩት ደግሞ የመንደርደሪያ ማስረጃዎቹን በመፈተሸ ክርክሩ ያለበትን ችግር መለየትና ማረም ይኖርብኛል፡፡ ይህን ላድርግ ካልኩ ግን የብሩህ ሐሳብ ላይ እየተሸከረከርኩ መቅረቴ ነው፡፡ ያ እንዲሆን አልፈልግም፤ ስለዚህ የራሴን ክርክር በአዲስ መልክ በማዋቀር የቅኔን ልዕለ-ፍልስፍናነት ለማሳየት ሞክሬያለሁ፤ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅኔነት በዚያው ውስጥ አለ፡፡

አሁን የብሩህን ክርክር መሠረታዊ ስህተት ነው የምለውን በማሳየት ልነሣ፡፡ ‹ችግሩ ያመለካከት ነው› እንዲል ካድሬ ለእኔ የብሩህ ክርክር ዋና ስህተት ያለው በዕይታው ላይ ነው፤ ዕይታው ከማዶ ስለሆነ ወዲህ ማዶ ያለው በአግባቡ ዐልታይ ያለው ይመስላል፡፡ ማስተዋል የሚገባው ግን የአገራችን ፍልስፍና የዕይታ ማጠንጠኛው ልክ እንደፊደላችን ከአውሮጳውያን ይለያል፡፡ ምን ማለቴ ነው?

ሁለቱ የግዕዝ ፊደላት እና የእንግሊዘኛ አልፋቤቶች ተፈጥሮን በሥዕልነት በመወከል አቅማቸው፣ በአናባቢና በተነባቢ ተዋሕዷቸው፣ በቅርጻቸው፣ በድምፅ አወጣጣቸው፣… ይለያያሉ፡፡ ስለሆነም አንድ ሐሳብ ስንጽፍባቸውና ስናነብባቸው ከተፈጥሯቸው ጋር የተገናዘበ ስሜትና ግንዛቤን ነው የሚሰጡን፡፡ የተጻፉ ጽሑፎችን ከማንበብ በፊትም ፊደላቱን/አልፋቤቱን ማወቅም ይቀድማል፡፡ ለምሳሌ የግዕዝን ፊደል ያላወቀ የእንግለዘኛ ሊቅ በዚያ የተጻፈ ጽሑፍን ሊያነበውና ሊጽፍበት ስላልቻለ ቢተቸው ትርጉም አይሠጥም፡፡ የኢትዮጵያ ፍልስፍናም ሆነ የቅኔ ፍልስፍናነት ተፈጥሮ ከፊደል ምሳሌ ጋር ይናበባል፡፡ ቅኔነት በኅብርነት፣ በዕምቅነትና በለዛዊነት የተሠራ ስለሆነ በደረቅና በነጠላ ሐሳብ ከሚገነባው እና የአሻሚነት ትርጉም ከማይስማማው የአመክንዮ ፍልስፍና ጋር አንድ አይደለም፤ ዕይታውም መንገዱም ይለያል፡፡ ስለዚህ የቅኔን ፍልስፍናነት የምናይበት እና ደረቁን የአውሮጳ ፍልስፍና የምናይበት ዕይታ ልዩነቱንና አመሠራረቱን መገንዘብ የዕይታ አድማሳችንን ይቀርጸዋል፤ ሚዛናችንንም እንደዚሁ፡፡ አሁን እየተቸገርን ያለነው የግዕዝ ፊደል ባሕርይ የያዘውን የኢትዮጵያን ፍልስፍና በእንግሊዘኛ አልፋቤት እያነበቡ የተረዱ ምሁራን ጋር መላተማችን ነው፡፡

እዚህ ላይ ‹የኢትዮጵያን ፍልስፍና› የምንገመግመው ከአምክንዮ መርህ አንጻር ከሆነም ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና ከተጠየቅ ልጠየቅ ጥበብ› ጋር በማገናዘብ መከራከር ይቻላል፤ ተጠየቅ ልጠየቅ ራሱ ከቅኔ የፈለቀ የክርክር ጥበብ ነውና፤ ዋና ግን አይደለም፡፡ በብሩህ መከራከሪያ የማልስማማውም ቅኔን በፍልስፍና አወቃቀርና በሐሳብ ሥርዓታዊ ትሥሥር (ፍሰት) አንጻር ብቻ ስላየው ነው፤ በተጠየቅ ስልት ማለት ነው፡፡ የአገራችን የቅኔ ጥበብ ግን የሐሳብ ሥርዓትንና ትሥሥርን የሚፈጥረው በዋናነት በሰምና ወርቅነቱ እንጂ በአምክንዮአዊነቱ/በተጠየቃዊቱ አይደለም፤ ለዘመናት ሊቃውንቱ የተለያዩ ስልቶችን በመፍጠርና በመጠቀም ሲማሩትና ሲያስተምሩት የኖሩት በኅብርነት ወይም በሰምና ወርቅ መነጽር ነውና፡፡ ይህን ብልም በተለመደውና በተማርነው መሠረት ስላልሆነ እንጂ ምክንያታዊ ትሥሥር የሌላቸው ቅኔዎች የሉም፡፡ ቅኔዎቹን ወደ አመክንዮአዊ ክርክር በመቀየርም የዐረፍተ ነገሮቹን ምክንያታዊ ትሥሥር እየተነተኑ ማሳየት ይቻል፡- ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ:: አሁን ይህን ነጥብ እናቆየውና እስቲ ቅኔን ፍልስፍና አድርገን እንድንወስድ የሚያደርገን ዋናው መከራከሪያ ምን እንደሆነ ለማሳየት ልሞክር፡፡

ቅኔ በመደነቅ ላይ የተመሠረተ ጥበብ ነው፤ ማጠንጠኛውም ምሥጢር እየፈለቀቁ ማውጣት ነው፤ ፍልስፍናም እንደዚሁ አይደለም ወይ? የቅኔ ዓላማ የእውነትን ምሥጢር መግለጥ ነው (ወርቅ የሚለው ‹እውነት!› ሲል ነው)፤ ፍልስፍናም መዳረሻው እውነትን ማግኘት ነው (ማንም እውነተኛ የፍልስፍና ዐዋቂ ይህን አይክድም)፡፡ ፍልስፍና እና ቅኔን የምመዝነው በእነዚህ መሠረታዊ ዕሳቤዎች ላይ ተመሥርቼ እንጂ ከቅርንጫፉ ጀምሬ ወይም በመንገዳቸው ላይ እየተንገዳገድኩ አይደለም፡- በስልት ከሆነ አመክንዮ አንድ የፍልስፍና የአተዋወቅ ስልት ነው፤ ሰምና ወርቅነት ደግሞ የቅኔ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ በአመሠራረታቸው ሳይሆን በአተዋወቅ ስልታቸውና በይዘታቸው ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ መዳረሻቸውና አመሠረራታቸው ግን ያገናኛቸዋል፡፡

አዎ! የቅኔ ይዘት ሰምና ወርቅን ማዋደድ ሲሆን ዋና ስልቱም ሰምን ተጠቅሞ ወርቅን በማንጠር ምሥጢሩን ማግኘት ወይም የተደበቀውንና የተሠወረውን ማውጣትና ዕንቆቅልሹን መፍታት ነው፡፡ ቅኔ ተፈጥሮን በቅርብ ነው የሚያነባት፤ ምክንያቱም ተፈጥሮ የተሠራችው በኅብርነት፣ በዕምቅነት፣ በዜማና በውበት ነው፤ የቅኔም ሥሪትና ጠባይ እንደዚሁ ነው፡፡ ቅኔ ለተፈጥሮ ባላው ቅርበት የተነሣም በእውነት ዕንቆቅልሽ ላይ ይሽከረከራል፤ ለዚያም ነው የሰምና ወርቅ ሥሪት፣ የእውነት አመሠራረት፣ የማይፈታ የምሥጢር ቤት የሆነው፡፡ የቅኔ ፍልስፍናነትም የሚሸለቀቀው በዚህ መልኩ እንጂ የዕውቀት አወቃቀሩና ፍሰቱ ከፍልስፍና ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ አይደለም፡፡

ፍልስፍና ‹የእውነትን፣ የዕውቀትንና የእሴትን› መስተጋብር በአምክንዮ መርሆዎች እያበጠረና እያዋደደ መጎርጎርና የእውነት መዳረሻን ማግኘት ነው፡- ማጠንጠኛው፡፡ ፍልስፍና አተዋወቁ በአመክንዮ መሆኑ ለዕውቀት እንዲያደላ፣ ከዕውቀት ተነሥቶ እውነትን ወደ መፈለግ እንድያንጋጥጥ፣ የእውነትና የዕውቀት እሴቶችን ከአመሠራረተቻው ጋር ለማጣጣም እንዲተጋ፣ በዚህ የተነሣም እውነትን ቆፍሮና በዕውቀት አበጥሮ ለማውጣት ሲለፋ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ በእውነቱ የቅኔነትን ጠባይ ከተረዳን ፍልስፍና በቅኔ የተቃኘ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ላብራራው!

የፍልስፍና ማጠንጠኛዎች ‹እውነት፣ ዕውቀት እና እሴት› የሚሉ ፅንሳተ ሐሳባት መሆናቸውን ገልጫለሁ፤ እነዚህ ‹እውነት፣ ዕውቀትና እሴት› የሚባሉ ፅንሳተ ሐሳቦች በአመሠራረታቸው በቅኔነት ተፈጥሮ የተቃኙ መሆናቸውንም እንደዚሁ፡፡ እውነት በምንነቷና በአተዋወቁዋ ዕንቆቅልሽ (ምሥጢር) እንደሆነች አለች፤ የሰው ልጅም እስከዛሬ ድረስ እየቆፈረ የኖረው የእውነትን ሰሞች እንጂ ዋና ምሥጢር የሆነችውን ወርቋን አላገኛትም (የእውነት ምሥጢርነት ቢፈታ ኖሮም ፍልስፍና አይኖርም ነበር)፤ ይህም ነው እውነትን ቅኔ ያደረጋት፡፡ ዕውቀትም ቢሆን ከምንጯ፣ ከስፋቷ፣ ከጥልቀቷ፣ ከመዋቅራዊ ሥርዓቷ አንጻር እስካሁን ምሥጢሯ ሊፈታ አልቻለም፤ ይህም ዕውቀትን ቅኔ ያደርጋታል፡፡ የእሴትም አንድምታ ተመሳሳይ ነው፤ የእውነትና የዕውቀት ኤሴቶች ጉዳይ፣ የዉበት፣ የግብረገብ (የሞራል)፣ የማኅበራዊ መስተጋብር እና” የአኗኗር ሥርዓት ምሥጢሩ ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ እንደሆነ አለ፤ የእሴት ቅኔ ማለት ይህ ነው፡፡ እነዚህ እውነት፣ ዕውቀትና እሴት ደግሞ ፍልስፍና የተሠራባቸው ናቸው ብለናል፤ ይህም ማለት ፍልስፍና ጥልቀቱና ምጥቀቱ የተመሠረተው በቅኔ ላይ ነው ማለት አይደለም ወይ? ስለዚህ ቅኔ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የዕሴት› ንጣፍ ላይ (ንጣፍ የሚትለዋን ቃል ከብሩህ ነው የወስድኳት) የሚሽከረከር የፍልስፍና ላዕላይ ክፍል ነው ብንልስ ዐበልን ወይ?

የቅኔን ልዕለ-ፍልስፍናነት ለማስረዳት ከአገራችን ልውጣንና የአውሮጳ ታዋቂ ፈላስፎች (ምንም እንኳ ከአገራችን ቅኔ ቢለይም) ‹እጃችሁ ከምን?› ብዬ ልጋብዛቸው፤ ምን ላድርግ? ሙግቱ ሁሉ ‹በከመ ይቤ› ሆነብና! ባይሆን እንዳትሰለቹብኝ ሐሳቤን ቀለል አድርጌ በወዘና ለማቅረብ ልሞክር፡፡

በመጀመሪያ የግሪኮቹን ሶቅራጥስን፣ ፕላቶንና አርስቶትልን ልጋብዛቸው ስል ሶቅራጥስ ‹መጀመሪያ ራስህን ዕወቅ› አለኝ፣ ፕላቶን ‹ይህን ቅኔ የሚባል የተረት አስተሳሰብ ይዘህ መምህሬን ምን አድርግ ነው የምትለው?› ብሎ ሲያፈጥብኝ፣ ለካ ይህንን ያለው ቅኔና ፍልስፍናን እያደባደበ ስለነበረ ነው፡፡ አርስቶትል ግን በማስተዛዘን ‹ቅኔ እንደፍልስፍና ባይሆንም ከታሪክ የተሻለ ሐሳብ ነው› ብሎ ሸኘኝ፡፡ አኳይነስ ጋር እስከምደርስ ድረስ የሮማውያኑም መልስ ከፕላቶንና ከሶቅራጥስ የተቀዳ ነበር፤ በተለይ አውጉስጢን የጣኦት ማምለኪያ ብሎ ነው ቅኔን ያንቋሸሸብኝ፤ ምስክር ለማግኘት በማደርገው ጥረት ተስፋ አልቀረጥኩም፡፡

አኳይነስ ሲያረጋጋኝ፤ ቪኮ የተባለው ኢጣሊያዊ ፈላስፋ የዕውቀት ምጥቀትና የፍልሰፍና መሠረት ቅኔ መሆኑን ተከራከረልኝ፤ ከዚያማ አቶ ካንት፣ አቶ ሄግል፣ አቶ ኬርከጋርድ፣ አቶ ኒቼ፣ አቶ ሄደጌር፣… (ወይ! አቶ አልኩኝ የፕሮፌሰሮቹን ፕሮፌሰሮች እኮ ነው!) ከፍልስፍና አልፈህ ወደ ቅኔ ልዕልና ከፍ ከፍ በል አሉኝ፡፡ ካንት ከአድማሱ ባሻገር (Noumenon) ያለው ዓለምን ለመረዳት የሚያበቃው ቅኔ እንጂ ምክንያት አቅሟ አይፈቅድም በሚል Critique of Jugdement የሚለውን መጽሐፉን ጋበዘኝ፤ ጥሩ ትዝብት አለው፡፡ ሄግል ተቀብሎ ‹የፍልስፍና ሁሉዓቀፋዊ ውህደት የሚገኘው በቅኔ ነው በሚል በPhenomenology of Spirit መጽሐፉ ሞገተኝ፡፡ ቀጠለ ኬርከጋርድ ፈላስፋ ሳይሆን ‹ባለቅኔ› ብለህ ጥራኝ አለኝ፤ በዚህም Absurdity የማለቱ ምሥጢር የአመክንዮ ፍልስፍና የተፈጥሮን ዕንቆቅልሽ መፍታት እንደማትችል ስለተረዳ መሆኑን አብራራልኝ፡፡ ‹እሺ ከሐዲው ኒቼስ ምን ትላለህ?› ብዬ ልጠይቅ ስል በሶቅራጥስ ‹እስጥአገባ› (Dialectic) ክርክር ሲበሣጭ አገኘሁት ‹ምነው?› ስለው ‹በቅኔ ላይ በሠራው ወንጀል ሞት ሲያንሰው ነው› ብሎ መለሰልኝ፤ ኒቼ ደግሞ ከተበሳጨ እግዜርንም ከመግደል እንደማይመለስ ስለማውቅ ቀዝቀዝ ብዬ ‹ይህንን የምትልበት እጅህ ከምን?› ስለው The Birth of Tragedy የሚለውን መጽሐፉን Gay Science ከሚለው ጋር እያስማማ ስለ ቅኔ ልዕልና ሞገተኝ፤ ‹ድንቅ ነው› ብዬ ተለየሁት፡፡ ወደ አገር ቤት ልመለስ ስል፣ ‹ሄደገር!› ከካንትና ከኒቼ የተቀበለውን እየተቸና እያሰፋ ‹ሥነ-ኩነትን› (Beingness) መግለጽ የሚችለው ቅኔ ስለሆነ ካድማሱ ባሻገር የተደበቀውን የኩነት ጥበብ ማሳያም መሆን ይችላል አለኝ፤ ለማረጋገጥ ‹ምክንያትስ?› ስለው ልኳ አፍጥና አግጥን ማቀናበር ስለሆነ ከግድግዳው ወዲያ ማሰብም ማሳሰብም አትችልም አለኝ፡፡ ከዚህ በላይ የቅኔ ልዕልና ምሰክርስ ከየት ላምጣ? ለካ! አመክንዮ ፍልስፍናን ቅኝ ግዛት ይዛ ብዙ ምሥጢር ደብቃብናለች እያልኩ ወደ አገር ቤት!፡፡

ወደ አገር ቤት ስመለስ አገናኝ ድልድይ ፈለኩ፤ ማን አገኘሁ? እጓለ ገ/ዮሐንስን፡፡ እሱም ‹ቅኔ ስንል… ጨርሶ ሌላ ነገር ነው፡፡ ከባድ ነው፡፡ ምሥጢር የተመላ የረቀቀ ፍልስፍና የተከማቸበት ማለት ነው፡፡ ባለቅኔውም ሰሚውም በሕሊና ርቀት የተራመዱ ናቸው፡፡ ሁለቱ ሲገናኙ አንደኛው ገና ከመጀመሩ ኹለተኛው ይበል! ይበል! እያለ ቃሉ ተማርኮ ነው፡፡ የሕሊና ርቀትና የቃል አንደበት ጉልበት በቅኔ ትምህርት በጣም ተስፋፍቶ ይታያል፡፡› አለኝ (እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ 2003 ዓ.ም 2ኛ እትም፣ ገጽ 71)፡፡

ከዚያም ከአገራችንን ባለቅኔዎች ‹ቅኔን እንዴት ነው የሚያዩት?› የሚል ጥያቄ ይዤ ወደ እማሆይ ገላነሽ ስጠጋ ‹ቅኔን ይቀኙታል እንጂ ዐያዩትም!› ሲሉኝ ጥያቄው ራሱ ጠፋብኝ፡፡ ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ግን ‹ቅኔ ሕሊናን (አእምሮን) ለምሥጢር የማስገዘት ጥበብ ነው› ብለው እጥር ምጥን አድርገው አስቀመጡት፤ ‹ማብራሪያ!› እንዳልል ‹ጨዋ!› ይሉኛል ብዬ ‹ሕሊና›፣ ‹ምሥጢር›፣ ‹ማስገዛት› የሚሉትን ቃላት እያብሰለሰልኩ አለሁ፡፡ እስቲ አብረን እናስብ፤ ሕሊናን ለምሥጢር ከማስገዛት በላይ ምን ጥበብ ይገኛል ትላላችሁ?

እንደ ጉርሻ ጠቅለል ሳደርገው፣ የቅኔ ጥበብ ተግባር የዕቆቅልሹን ዓለም ምሥጢር መፍታት በመሆኑ ከፍልስፍናም በላይ ልዕልና ያለው ነው፡፡ ቅኔን ፍልስፍና የምናደርገውም በሐሳቡ ስፋት፣ ምጥቀት፣ ጥልቀትና ድንቀት፣ እንዲሁም ዕንቆቅልሽዋን እውነት መመርመሪያ ልዩ ጥበብ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ አእምሯችንን ከፍ ከፍ በማድረግ የፍልስፍና ዘውጎች መሠረት ወይም ንጣፍ የሆነውን ቅኔነትን ወደ መረዳት እንደግ፡፡ አይበቃኝም? (ኧረ! አራት ነጥብ ወዴት ነሽ? ሰውየው ይዘውሽ ሄዱ እንዴ!)

 

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply