በሀልዎተ-እግዚአብሔር ዙሪያ በሻይ ቤት የተደረገ ሙግት

(በካሣሁን ዓለሙ)

አንድ ቀን ፒያሣ በሚገኝ አንድ ኬክ ቤት ውስጥ የሃይማኖት መጽሐፍ እያነበብኩ ቁጭ ባልኩበት አንድ ዕድሜው በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ወጣት አጠገቤ መጥቶ በመቀመጥ ጨዋታ ጀመረ፡፡ የማነበውንም መጽሐፍ ‹እስቲ ልየው› ብሎኝ አሳየሁት፡፡ ከመጽሐፉ ጋር ተያይዞ ባነሳቸው ጥያቄዎችና ነቀፌታዎች የተነሳ የሚከተለውን ክርክር ተጨቃጭቀን ተለያየን፡፡

ልጁ ክርክሩን የጀመረውም “አሁን ይህንን መጽሐፍ ብለህ ታነባለህ?” በሚል ነበር፡፡

እኔም ተናድጄ “ለምን አላነበውም መጽሐፍ አይደለም?” ብዬ በጥያቄ መለስኩለት፡፡

“ማለቴ በዚህ መጽሐፍ ጊዜህን ከምታባክን ለምን የተሻለ እውቀት ያላቸውን መጻሕፍት አታነብም?”

“ምን ዓይነት መጻሕፍት ናቸው የተሻለ ዕውቀት ያላቸው?”

“ለምሳሌ የፍልስፍና መጻሕፍትን አታነብም? ሰዎች ለጥቅማቸው ሲሉ እግዚአብሔር ፣ ሰይጣን፣ ኃጢያት፣ ጽድቅ፣ ኩነኔ ምናምን እያሉ የጻፉትን ተረታተረት ከምትለቃቅም?” አለኝ እያጣጣለ፡፡

“የፍልስፍና መጻሕፍት ኹሉ እግዚአብሔርን ይቃወማሉ እንዴ የሃይማኖት መጻሕፍትን እንደዚህ አምርረህ የምትቃወመው?”

“እንዴ! እግዚአብሔር እኮ! በድሮ ጊዜ ነገሥታትና ካህናት ለጥቅማቸው ሲሉ የፈጠሩት እንጂ የሌለ ነገር ነው፡፡ ይህንንም የፍልስፍና መጻሕፍት ብታነብ መረዳት ትችላለህ፡፡”

“እስቲ መጽሐፉን ተወውና አንተ እንደዚህ ለማለት የደረስከው የእግዚአብሔርን አለመኖር እንዴት ማወቅ ችለህ ነው?”

“እስከ ዛሬ ድረስ መኖሩን ማንም ሰው ሊያረጋግጥ አልቻለማ!”

“ትገርማለህ!”

“እንዴት! መኖሩ ያልተረጋገጠ ነገርን ባለማመኔ ነው?”

“አይ! እንደዚያ ሳይኾን የእግዚአብሔርን መኖር ሰዎች በዕውቀታቸው አረጋግጠው የሚያምኑት አድርገህ መረዳትህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምናምነው ሙሉ ለሙሉ ዐውቀን በማረጋገጥ ከኾነማ ምኑን እግዚአብሔር ኾነው? የተወሰነ ቁስ አካል እንጂ! በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ሰው መኖሩን ማረጋገጥ አለመቻሉ እግዚአብሔርን ከመኖር አያግደውም ነበር፤ አለ፤ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ያልበሰለ ፍልስፍና ይዘህ ባልገባህ ነገር ላይ እየዘላበድክ ባትቸገር መልካም ነው፡፡

“አለመብሰሉን ተወውና አሁን አንተ ‹እግዚአብሔር አለ› ብለህ ታምናለህ?”

“በትክክል!”

“ታሳዝናለህ?”

“እንዴት?”

“መኖሩ እርግጠኛ ያልኾነ ነገርን ማመንህ ነዋ!”

“አንተ አለመኖሩን በምን አረጋገጥክ አልኩህ እኮ!”

“ስለአለመኖሩ እርግጠኛ ባልኾንም መኖሩን ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ስለዚህ እንኳን ላምንበት እንዳንተ የሚያምኑ ሰዎችም ያሳዝኑኛል፡፡”

“አንተ መኖርን እንዴት ትገልጸዋለህ?”

“አንድ ነገር መኖሩ በትክክል መረጋገጥ ከቻለ ‹አለ› ይባላል፡፡ ይህም ማለት አንድ ‹አለ› የሚባል ነገር ሰዎች መኖሩን በሐሳባቸው አምነውበት ብቻ ሳይኾን በአመክንዮአዊ ህግጋት መኖሩ መረጋገጥ የሚችል መኾን አለበት፡፡ አመክንዮአዊ ሕግጋትን የሚቃረን ነገር ኹሉ ትክክል አይደለም፡፡ ትክክል የማይኾን ነገርን ደግሞ መጠራጠር ይገባል እንጂ አምኖ መቀበል ወይም መስማማት አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ አንድ አለ የሚባል ነገርም አመክንዮአዊነትን የሚቃረን ወይም ከሕግጋቱ ጋር የማይስማማ ከኾነ መኖሩ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ መድኃኒቱ መጠራጠር ነው፡፡ ከተጠራጠርክ የምታምንበትን ነገር ‹ለምን?› ብለህ በመጠየቅ ትክክል መኾን አለመኾኑን ቀድመህ ታረጋግጣለህ፡፡ አንተም ‹እግዚአብሔር አለ› በማለት ያመንክበትን እምነት ብትጠራጠር ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ማስረጃዎች አለመገኘታቸውን ታረጋግጣለህ፡፡“

“ጥያቄን ግን በአግባቡ አልመለስክልኝም፡፡ የእግዚአብሔርን መኖር ተወውና አንተ ራስህ መኖርህን በምን አረጋገጥክ? ማለቴ ያንተን መኖር ማረጋገጥ የቻልከው በአመክንዮ ህግጋት ነው ወይስ መኖርህን ስላመንህ?”

“ይህማ ቀላል ጥያቄ ነው፡፡ ስለማስብ!”

“እኸ! የአንድን ነገር መኖር የምታረጋግጠው በማሰቡ ነው?”

“ካላሰበማ የሚታሰበው ነገር መኖሩን በምን ያውቃል ብለህ ነው?”

“እንዲህ ከኾነማ በዙሪያችን የሚገኙ ነገሮች እንደ ድንጋይ ፣ አፈር ፣ ውኃ ፣ አየር ፣ እጽዋት ፣….. የመሳሰሉት ስለማያስቡ የሉም ማለት ነው?”

“ስለመኖራቸውም ኾነ አለመኖራቸው እርግጠኛ መኾን አይቻልም፡፡”

“ታዲያ እንዴት እርግጠኛ ባልኾነ ነገር ላይ እየተንቀሳቀስክ በመኖር ትሠራለህ?”

“የምኖረው እያሰብኩ እኮ ነው!”

“የምትኖርበትም ኾነ የምታስበው ነገር ከእነሱ ጋር የተያያዘ መስሎኝ?”

“እኔ እኮ! እያልኩህ ያለሁት እኔ ስለማስብ መኖሬን አረጋግጣለሁ፡፡ ባላስብ ግን እነሱም ለእኔ አይኖሩም ነበር፡፡ ላውቃቸው የቻልኩት በማሰቤ ነውና፡፡ ለምሳሌ ድንጋይን ብንወስድ ስለማያስብ ለእሱ መኖሩም አለመኖሩም ልዩነት የላቸውም፡፡ ስለእራሱ የሚያውቀው ነገር የለምና፡፡ ስለዚህ ነው ማሰብ የመኖር መሠረት ነው ያልኩህ፡፡”

“እና እያልከኝ ያለኸው ከእኔ ውጭ ሌላ ነገር ይኑርም አይኑርም እርግጠኛ አይደለሁም ነው ወይስ አንድ ነገር ካለሰበ የለም ነው?”

“ካላሰበ መኖሩን እንዴት ያውቃል? እኔስ የሌላውን መኖር እንዴት ማረጋገጥ እችላለሁ?”

“እሺ! እኔ ለአንተ አለሁ የለሁም?”

“ካላሰብክ ልትኖር ትችላለህ?”

“የማስብ ከኾነ ግን አለሁ ማለት ነው?”

“ለምን አትኖርም?”

“የእኔን ማሰብ ግን አንተ እንዴት ልታውቅና መኖሬን ልታረጋግጥ ትችላለህ?”

“የአንተ መኖር የአንተው የማሰብ ውጤት እንጂ የእኔ አይደለም!”

“በዚህ አያያዝህ ከአንተ ውጭ ያለውን ነገር በሙሉ መኖሩን እርግጠኛ ስላልኾንክ ስለ እግዚአብሔርም መኖር አለመኖር መናገር አትችልም፡፡ እንዲያውም እንደ አባባልህ ከኾነ የማያስብ የአካል ክፍልህም መኖሩን መጠርጠርህ አይቀርም”

“እና አሁን አንተ የእግዚአብሔርን መኖር በምን ልታረጋግጥልኝ ትችላለህ?”

“በእምነት ነዋ!”

“መጀመሪያ መኖሩ ባልተረጋገጠ ነገር ላይ ማመን ትክክል ነው?”

“ለየትኛውም ነገር መኖር እርግጠኛ መኾን የምትችለው ቀድመህ እምነት ስታሳድር ነው?”

“እንዴት ይኾናል? መጀመሪያ የተገመተ ነገርን አምነህ ነው መኖሩን ለማወቅ የምትሞክረው ወይስ የዚያን ነገር መኖር ዐውቀህ ነው የምታምነው?”

“ለዕውቀት እምነት መሠረቱ ነው፡፡”

“ቀድመህ ካመንክ እንዴት ትመራመራለህ? የማወቂያ መንገድህን በእምነት ዘጋኸው አይደለም እንዴ?”

“ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ የትኛውም ሰው ለሚያስበው ነገር መነሻ አለው፡፡ መነሻ ሐሳቡን አምኖና ተስማምቶ ነው ምርምር የሚያደርገው፤ ንድፈ ሐሳብ የሚነድፈው፡፡ የመነሻ ሐሳቦች ስምምነት የሌለው ምርምር ወደፊት እየጠየቀና እየፈተሸ ማወቅ አያስችልም፡፡ የዚህን ሐሳብ ትክክልነት ለማረጋገጥ ከፈለክ የትኛውንም ንድፈ-ሐሳብ ተመልከት ‹እነዚህን መሠረታዊ መርሆዎች ትክክል ናቸው ብሎ በማመን ላይ የተመሠረተ ነው› የሚል ይዘት ታገኝበታለህ፡፡ ለምሳሌ የአንስታይንን አንጻራዊ ንድፈ-ሐሳብ ብትወስድ ‹ከብርሃን ፍጥነት የበለጠ የፍጥነት መለኪያ የለም› በሚልና ‹እንቅስቃሴ አንጻራዊ እንጂ ወጥ አይደለም› በማለት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ያለዚህ መሠረታዊ ዕምነት የአንስታይን አንጻራዊ ንድፈ ሐሣብ የለም፡፡ ስለዚህ ቀድመህ አምነህ ነው ወደ ቀጣይ ወይም ጥልቅ ምርምር ልትገባ የምትችለው፡፡”

“እኸ! እንደ አባባልህ ከኾነ የእግዚአብሔርን መኖር ማረጋገጥ የምንችለው በእምነት እንጂ የምናውቀው ስላለ አይደለም፡፡”

“በእምነት ላይ በመመሥረት ስለ እሱ ብዙ ነገሮችን መመርመር እንችላለን፡፡”

“በእምነት ላይ ተመሥርተህ የምታደርገው ምርምር እኮ ኹለት አማራጭ መልሶችን ይዞብህ ሊመጣ ይችላል፡፡ ወይ ትክክልነቱን ማረጋገጥ ወይም አለማረጋገጥ፡፡ ትክክልነቱ ከተረጋገጠ ምንም አይደለም ይሁን፡፡ ካልተረጋገጠ ግን መጠርጠርህ አይቀርም፡፡ በመጀመሪያው ጥርጣሬን መሠረት አድርገህ ብትጠይቅ ግን ወደ ዕውቀት ታመራለህ፡፡ በዕውቀትህም ትክክለኛነቱን ስታረጋግጥ ማመን ትችላለህ፡፡”

“እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?”

“በእስካሁን ተስማማን”

“ከዚያው ጋር የተያያዘ ነው?”

“ምን?”

“የዕውቀትህ መነሻ ምንድነው?”

“ማለት አልገባኝም?”

“የሐሳብህ መነሻ ምንድነው? ከምታውቀው ነገር ላይ ተመሥርተህ ነው የምታስበው ወይስ ከማታውቀው ነገር ላይ ተነስተህ?”

“በማውቀው ነገር ላይ ተመሥርቼ የማላውቀውን ነገር ኹሉ እመረምራለሁ፡፡”

“ጥሩ! ይህ ማለት ለሐሳብህ መነሻ አለህ ማለት ነው”

“ትክክል!”

“ማሰብህን ከምታውቀው ነገር ላይ የምትጀምረው በማመን ነው በመጠራጠር?”

“እያሰብኩ ማመንን ምን አመጣው?”

“እና ሐሳብ መነሻ አለው እንዴ?”

“የማውቀው ነገር ለሐሳቤ መነሻ ይኾነኛል አልኩህ እኮ!”

“ሳታስብ አውቀህ ከዚያ ታስባለህ ማለት ነው?”

“የማውቀውማ አስቤ ነው፡፡”

“ይህማ አስበህ ታውቃለህ ማለት ነው፡፡”

“ትክክል!”

“ይህ ከኾነም የምታውቀው ነገር ለሀሳብህ መነሻ አልኾነህም፡፡ ምክንያቱም ልታውቅ የቻልከው አስበህ ነው፡፡”

“እሺ! ይሁን ልስማማ!”

“በዚህ ከተስማማህ ሐሳብህን ከምታውቀው ነገር ላይ አትጀምርም ማለት ነው፡፡”

“እ! እንደዚያ መኾኑ ነው፡፡”

“ይህ ከኾነም በማታውቀው ነገር ላይ ተመሥርተህ የምታውቀውን ነው የምታስበው ወይስ የማታውቀውን?”

‹የማስበው እኮ ለማወቅ ነው!›

“ለማወቅ ታስባለህ እንጂ ማወቅህን እርግጠኛ መኾን አልቻልክም፡፡”

“አካሄድህ አልገባኝም በማሰብ ማወቅ አይቻልም ለማለት ነው?”

“አልወጣኝም!”

“እና! ምንድነው የምታወራው?”

“እኔ የምልህ ስለማስብ አለሁ ብለኸኝ ነበር፡፡”

“አዎ!”

“‹እግዚአብሔርን ሳላውቀው እንዴት አለ ብዬ አምናለሁ?› ብለኸኝ ነበር?

“ትክክል!”

“ማወቅ የምትችለውም አስበህ መኾኑን ተናግረሃል?”

“አዎ!”

“የሐሳብ መነሻንም ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ የሚታወቅ ነገር ነው ብትልም ኋላ ላይ ግን እምነትን በመሸሽ የማይታወቅ ነገር ነው ብለሃል፡፡”

“እና! ማመን አለብኝ?”

“ይህ የራስህ አቋም ነው፡፡ ኾኖም በተነጋገርነው መሠረት የምታስበው በማይታወቅ ነገር ላይ ከተመሠረተ በማሰብህ መኖርህን እንዴት ልታረጋግጥ ቻልክ? በዚህ አኳኋንስ እንዴት መጀመሪያ እግዚአብሔርን ዐውቀህ መኖሩን ማረጋገጥ ትችላለህ? ደግሞስ ኹለቱ ሐሳቦች አይጋጩም?

“በመጠራጠር ነው የማስበው ብየሃለሁ እኮ!”

“መጠራጠር ማለት ማምታታትና ማጣረስ ማለት ነው እንዴ?”

“እንደዚያ ሳይኾን እውነት ነው ብለህ ቀድመህ አለመቀበል ማለት ነው፡፡”

“ይህ ከኾነ በጥርጣሬ መነሻ ሐሳብ ላይ በመስማማት የአንድን ነገር እውነትነት ማረጋገጥ አይቻልማ!”

“መነሻውንም ቢኾን መጠራጠር ያስፈልጋል፡፡”

“በዚህ ዓይነት እኮ! የአንድን ሐሳብ መነሻ እውነት ብሎ መቀበል ካልተቻለ ትክክለኛ መቋጫ ላይ አይደረስም፡፡”

“ድሮውንስ ትክክል ባልኾነ ነገር ላይ መስማማትን ምን አመጣው?”

“ትክክል ነህ፡፡ ትክክል ባልኾነ ነገር ላይ መስማማት አይገባም፡፡ ኾኖም ኹሉንም ነገር ከተጠራጠርክና የሐሳብ ስምምነት መነሻም ከሌለህ እንዴት የአንድን ሐሳብ ትክክልነት ማረጋገጥ ትችላለህ?”

“ወይ ጉድ! መነሻ መድረሻ ብሎ ነገር የለም፡፡ ኹሉንም ነገር እጠራጠራለሁ፡፡ በጥርጣሬም ትክክል የሚባል ነገር ቦታ የለውም፡፡”

“ይህ ከኾነማ አስተሳሰብህ ለአመክንዮ ሕግጋትም አይገዛም ማለት ነው፡፡”

“የአመክንዮ ሕግጋትንም መጠራጠር ይቻላል፡፡”

“እንዲህ ከኾነ ስለ ዕውቀትህም ኾነ ስለ አንተ መኖር ወይም ስለምታስበው ነገር ትክክልነት እርግጠኛ ኾነህ መናገር አትችልም ማለት ነዋ!”

“እያሰብኩ!”

“ሐሳብህን አትጠራጠረውም እንዴ?”

“ስንት ጊዜ ልንገርህ እየተጠራጠርኩ አስባለሁ አልኩህ እኮ!”

“ይቅርታ አድርግልኝና በዚህ ኹኔታ ምንም ልንስማማ አንችልም፡፡ ክርክራችንም ‹የደንቆሮ ለቅሶ› እንደሚባለው መደጋጋምና የዶሮና የዕንቁላል የትኛው ቀዳሚነትዓይነት ኾነብኝ፡፡ እያቀረብክልኝ ያለው ሐሳብም እርስ በርሱ የተጣረሰ ነው፡፡ ቆይ! መጀመሪያ የዕውቀትን ትክክልነትና የአንድን ነገር መኖር በአመክንዮ ሕግጋት ማረጋገጥ ይቻላል አልከኝ፤ አዙረህ ደግሞ የአመክንዮ ሕግጋትንም ተጠራጠርካቸው፡፡ እንዲሁም መኖሬን የማረጋግጠው በማሰቤ ነው አልከኝ፤ ማሰብህንም ተጠራጠርከው፡፡ እንዲህ ከኾነ ያለው ጥርጣሬህ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ኹኔታህም ስለ እግዚአብሔር መኖር ባለማመንህ አትገርመኝም፡- መኖርህንም ተጠራጥረኸዋልና! ለማንኛውም እኔ እምመክርህ መጠንና ውል በሌለው ጥርጣሬ ባትቸገር ጥሩ ነው፡፡ ያለበለዚያ ተጠራጣሪው አእምሮህ ተምታቶበት ውል ስቶ እንዳትጠራጠርም እንዳያደርግህ መጠንቀቅ አይሻልም ትላለህ”ብዬው ከቦታው ተነሳሁ፡፡

ኾኖም “በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ብፈልግ እንድጽፍልህ ኢ-ሜልህን ስጠኝ?” ብሎ ስለጠየቀኝ ሰጥቸው ተለያየን፡፡

(ይህ ጽሑፍ ‹ሀልዎተ-እግዚአብሔር› ከሚለው መጽሐፌ በምዕራፍ አንድ ‹የሻይ ቤት ሙግት› በሚል የተካተተ ነው፤ ማጽሐፉን ያላገኙ የማኅበራዊ ድረ-ገፅና የብሎግ ተከታታዮች እንዲመለከቱት እዚህ ለጥፍኩት፤ ቀጣይ የሙግት ጽሑፎችም ወደፊት ይወጣሉ፤ ካክብሮት ጋር አንዲከታተሉ ተጋብዘዋል!፤በፈለጉት አቅጣጫ ተመልክተው አስተያየትዎን ቢሠጡም ውለታወን አንዘነጋም፡- ለቀጣይ ሥራ ያግዘናልና፤ ቢተቹት ደግሞ የበለጠ! )

Please follow and like us:
error

8 COMMENTS

Leave a Reply