በቀለ ተገኝ ስለፊደል

በቀለ ተገኝን ‹‹የምዕራባውያ ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ ፩›› በሚል በ1985 ዓ.ም› ባሳተመው፣ በከፍተኛ የአማርኛ ቋንቋና የሥነ-ጽሑፍ ችሎታው የIMAG4856ተራቀቀበትን መጽሐፉን እየተገረመ ያነበበ ያውቀዋል፤ መጽሐፉን ያላነበበ ካለ ግን ትልቅ ቁም ነገር ቀርቶበታል፡፡ ለማንኛው እኔ እዚህ ስለ በቀለ ተገኝ ምንም ማለት አልፈለኩም፤ አልችልም፤ ሆኖም በመግቢያነት ከጻፈው ውስጥ ስለ ፊደላችን ያተተውን ብቻ (በተለይ ከገጽ 50-57 ካለው ውስጥ) መርጨ አቅርቤላሁ፡- በዚያው አጻጻፉንና በፊደላት መቆነጻጸር የነበረውን ቁጭት ማየት ይቻላል በሚል!

‹‹… ከፊደላቱ አቀራረፅ ጀምሮ እስከ ልሳነ ጥበቡ አወቃቀር፣ ከቅርቦቹም ይበልጥ፣ የጥንቶቹ አባቶቻችን በተራቀቀ ጥበብ አሣምረው የቀመሩልንን ብልሃት፣ ባርከውና መርቀው እንደአወረሱን አዙረን ማየት አቅቶናል፡፡ … እሊያ የጥንቱ ሊቃነ ልሳናችን መቸና እንዴት እንደሆነ ምንጩን እንዲነግሩን ከእኔ ለሚበልጡ፣ የታሪክ ሊቃውንት ፈንታውን ልተውላቸውና፤ ሊሆን እንደሚገባው፣ ከሕንፃው ነደቅታችን፣ ከሠዓሊያኑና ከአምሳለተ ቅርፁ ጠበብታን፣ ከቅኔ ዘረፋው፣ ከመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜው፣ ከመኅሊዩ ዜማና፣ ከየዕውቀቱ የአእምሮ ምጥቀት በመጠቀም፣ በመመካከርና በመተጋገዝ ፊደላችንን ፈጥረውልን ነበር፡፡ … በዓለም ዙሪያ በተተከሉት ከማነ ምስባካት ሁሉ የሚደነቅልንን፣ የፊደል ገበታችንን፣ ተጨንቀው፣ ተጠበው ቀምረውልን ነበር፡፡ ከዚያ ወዲያም፣ ያን ረቂቅ የፊደላችንን ጥበብ፣ ከእናትና ልጁ፣ ከግእዝና ከአማርኛው ቋንቋዎቻችን ጋር፣ በተለይ በቤተክህነት ሊቃውንታችን ባለአደራነት፣ በጸጋ አውርሰውን፣ በክብር አልፈው ነበር፡፡ …

… በበኩሌ እንደ ልማደ ደንቡም፣ አፍአዊ ፈሊጡን ወይም ብሂለ ነገሩን ለየሀገረ ሰብኡ ጥበበልሳን ልተወውና ከሥነጽሑፋቱና ከሥነልሳናቱ፣ ከሥነአጠይቆቱም አኳያ፣ በቅድሚያ ከፊደልቻንን ያለ አግባቡ መቆነጻጸልና መመናዘር እጅምራለሁ፡፡ … ሌላው ቀርቶ በጽሕፈት ላይ ከአንዱ የፊደል ዘር፣ ለምሳሌ ግዕዙና ራብኡ ያለቦታቸው እንዳይገቡ የምንከላከልበት፣ ረስተነው እንጂ፣ በደንብ የተጠና የፊደል አጠቃቀም ሥነሥርዓት ነበረን፡፡ ይህ ሥርዓት የመነጨው ከቋንቋችን ወልጋዳነት ወይም ኋላቀርነት የተነሣ የሚመስላቸው፤ የብልሃቱ ምሥጢሩ በዕውነቱም እንዲያ አለመሆኑን፣ ከፊደል ቆጠራ ሲወጡና ገና ዘፈቲነ ብርዕ (ብዕር?) ብለው መጻፍ ሲጀምሩ፣ ደንቡን በውል ያልተማሩት፣ ወይም በጥፋታቸው ስለማይቀጡበት፣ አያሌ አገር አጥፊዎች ምሁራን መኖራቸውን፣ በእንተ ሃፍረቱ ደባብቄው አላልፍም፡፡ በዚህ ረገድ አቤ ጉበኛው በእኛ ቋንቋም እንደሌላው፣ የፊደላት በቃላት አግባብ፣ እንዲሁ በሆታ ብቻ መጣስ የሌለበት፣ የሥነልሳናት ሕግና ደንብ እንደ አለው፣ የአስጠነቀቀበት የብልህ ሰው ምክሩ፣ ሰሚ ጆሮ እንደአጣ በመቅረቱ፣ የማዝንለትን ያህል፤ በትክክለኛ አቋሙ ግን፣ በዚህ አጋጣሚ ነፍሱን ይማር እያልሁ ታላቅ አድናቆቴን ስገልጽለት፣ የልብ ደስታ ይሰማኛል፡፡…

ፊደላችን አንድያውን የተንኮታኮተውና ብሔራዊ ቋንቋችንም አብሮት የዳሸቀው፣ ደርግን የሚያስመሰግነው አንዱ፣ ታላቁ ሥራው፣ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻው እንደመሆኑ፣ በዚያው ሰበብ ግን ከድንቁርናው ብዛት፣ በአማካሪዎቹ ምሁራንም የአዋቂዎች ጥፋት፣ ያለበቂ ጥናትና ምርምር ሥርዓተ ፊደላችንን አፋልሶ፣ ገበታውን ጭምር በሰባበረውና በጣለው ጊዜ ነበረ፡፡ … ፊደላችን ከመጀመሪያው ፈሩን የለቀቀበት ስሕተት መንሥኤው፣ ከደርጉ ዘመነ መንግሥትም ጥቂት ፈቀቅ ማለቱን አታጡትም፡፡ በዚህ ሳቢያም (በፍቅር እስከመቃብር እንደተጻፈው) የደርጉ አማካሪዎች ሳይቀሩ፣ ለሽፍናቸው መሸፈኛ ጭምር የሚበጃቸውን ጥሩ ምህኛት አገኙና፤ በጉዳዩ ሌላው ቢቀር የሥነጽሕፋቱና የሥነልሳናቱ ጠበብታችን፣ አሳባቸውን ተጠይቀው፣ ሳይመክሩበትና ሳይዘክሩበት፣ ልክ እንደችግሮኞቻችን ፍልሰትና መንደር ምሥረታው፣ የዱር ምንጠራና የቀየ ነቀላ ሁሉ፣ በስም አብዮት ወአድኅሮት፣ በጥንታዊው በክቡሩ ባህላችንና በቅዱሳኑ ሃይማኖቶቻችንም ላይም ሳይቀር፣ ከነጭኑና ከቀዩ ሽብሮች አከታትለው የድምሰሳውን አዋጅ ተጣለብን፡፡ …. ከዚያ ወዲያማ በቅጽበት ሌሊት ወመዓልት፣ የኢትዮጵያ ጸሓፍት በሁሉም ልሳናት፣ እስከዛሬም ድረስ የተራቀቁበትን ጥበብ ምን ብዬ ብገልጽላችሁ፣ ትክክለኛው ሥዕል እንደእኔው ይታያችሁ ይሆን? መራቀቅ ሌላ፣ መዘባረቅ ሌላ፡፡ ስለሆነም የፊደል ገበታችን በጠቢባኑ ከተፈቀዱት ዐረቢ ቀለማት ውጪ፣ የሥነልሳናቱና የሥነአጠይቆ ሕግጋቱ ሁሉ ተጣጥሰው አበቁ፡- ማለት አይበቃም፡፡ ከሀ እስከ ፐ ድረስ ከላዩም ከታቹም፣ ከፊቱም ከኋላው ጭረትና ጅራት ወይም ዛጎልና መስቀል የሚያስቀጥል ጫፍና ጎን ያለበት ፊደል ሁሉ፣ በዚሆኒቱ ኩምቢና በአህያይቱ ሎምቢ፣ በግመሯ ዝንጀሮ ደኅራና በፊየሊቱ ጭራ፣ በአጋዛኒቱ ጆሮና በሰጎኒቱ እግረ ጭራሮ፣ (ያጎደልኩትን አቃቂር ከፈለጋችሁት አምሳለ ፍጥረት ጋር አነፃፅሩት) እየተዥጎረጎሩና እየተሞናቀሩ፣ በየወረቀቱ ላይ የተሞነጫጨሩልን፡፡ አንዳንዶቻችንማ ከአንድ ሥመጥር የልብወለድ ድርሳን ጸሐፊ ሊቃችን በስተወር፣ በማንኛውም ሊቃነ ሥልጣናት ሳይባረክልን፣ ከክልስም ሥሉስ ዘር ካላቸው ፊደሎቻችን መካከል፣ ውቃቤያችን ያስወደደንን እንደአፈቀደን እያስነካን፣ ያስጠላንን ደግሞ፣ ሌላው ጸሐፊ ቢፈልጋቸው፣ ባይፈልጋቸው ከቆሻሻው ማጣራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ከከተትናቸው ሰንብተናል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ የገበያ ግርግር መሀል፣ እምዬ ኢትዮጵያ በየአውደ ዕውቀቱ በያዝነው ምእተ ዓመት ብቻም እንኳ፣ ስንትና ስንት ዕዳ ችላ፣ እንደ አትክልተኛ ኮትኩታና ተለባኝታ ያሳደገቻቸው የየሙያው ጠቢባንዋና ሊቃነሥልጣናትዋ ሁላ፣ የት ደረሱ? ዋእ! ውሸት አታናግሩኝ! ያጭራቁ ደርግ፣ ሁሉንም ውጦ አልጨረሳቸውም፡፡ ለፍርጃው ብሎልን እኔና ብኜዎቼ ይሄው እስከአሁንም ከመዓቱ ተርፈን አለና! እኒያ የተረፉትሳ ሃይ አይሉም እንዴ? እኛማ ታየልንኮ! ከዚያም ከዚያም ምንጭ እያናጠቅን በየጽሕፈቱና በየዕለታቱ እንደጋዜጠኞቹ ‹የምንፈበርከውና› እረኞቹን ባለሥጣኖቻችንን እየተከተለን ‹የምንተገብረው› አዳዲስ ቃል ውይ ማማሩ! …››

Please follow and like us:

Leave a Reply