በኢትዮጵያ የተጀመሩ ዋና ዋና የሥልጣኔ ማሳያዎች

የኢትዮጵያውያን የሥልጣኔ ምንጭነት በየፈርጁ ማየት ይቻላል፡፡ ይሁንና በየፈርጁ በማብራራት ማስቀመጥ ሰፊ ጊዜና ማስረጃዎችን እያነጸሩ ማየትን ይጠይቃል፡፡ በጥቅሉ ብናስቀምጠው የሚከተሉት ሥልጣኔዎች ምንጮቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

  1. በፊደልና ሥነ ጽሑፍ፡- ብዙዎቹ የግብፅ ጥናት ምሁራን የግብፆችን ጽሑፍ ከኢትዮጵያ የተወሰደ መኾኑን ይቀበሉታል፡፡ ለብዙ ዘመናትም በኢትዮጵያውያ መጻፊያ በመኾን ያገለግል እንደነበር የጠቆሙም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሎሬት ፀጋዬ  ‹የኢትዮጵያ ሄሮግሊፊክ ፊደል› በማለት ይገልጻል፤ አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስም ‹ቅዱስ ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ነው፤ የተዋሕዶ አንበሳም መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው› በሚለው መጽሐፋቸው ‹በኢትዮጵስ ፊደል› የተጻፈው በማለት  የግብፅን ሄሮግሊፊክ ጽሑፍ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም የግብፆች ሄሮግሊፊክ ጽሑፍ ከኢትዮጵያውያን የተወሰደ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ እንዲሁም ድሩሳላ ዱንጂ ሆስቶን የተባለችው የታሪክ ምሁርም ‹የግብፆች ሄሮግሊፊክ ከግብፅ በበለጠ በኢትዮጵያውያን በተራው ሰው ዘንድ ሳይቀር ይታወቅና ይነገር ነበር› ብላለች፡፡

በጽሑፍ ሰፍረው ከሚገኙ አንዳንድ መረጃዎችም በመመሥረት የጽሑፍ ፊደል በኢትዮጵያውያን የተጀመረ መኾኑን መገመት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያዊው ንጉሥ ሰብታህ ጊዜ የነበረው ‹ኃይልዋን› የተባለው የጽሑፍ አስፋፊና ተቆጣጣሪ (በአሁን ዘመን አገላለጽ የሥነ ጽሑፍ ሚኒስቴር) ‹ጽሑፍ በእኛ ተመሥርታ እንዳጀማመራችን አላደግችም፡፡ ጥበብን ከኛ የተቀበሉት አሦሪውያን ለወጥ ባለ መልክ በማዘጋጀት ከኋላችን ተነሥተው ብዙ ሥራ ሠርተውበታል፡፡ እኛም እንደየችሎታችን ሠርተን ቀደምትነታችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡› በማለት መናገሩ በታሪክነት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ (አእምሮ ንጉሤ፤ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ ከቅራት- ዘመናዊ ፖሊስ፣ ገጽ 21)፡፡

በሌላ በኩል የግብፅን የሥዕል ፊደሎችን ከእኛ ከግዕዝ ፊደሎች ጋር እያነጻጸርን ብናስተያያቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ኾነው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ የግዕዝ ፊደል መጀመሪያ የኾነው ‹ሀ› ምልክትነቱ የሚወክለው ‹ሆይ› ብሎ መጸለይን ነው፡፡ በዚህ ጋር ተያይዞም የ‹ሀ› ፊደል ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ያለውን የዳዊትን ቃል ወክሎ የሚኖር ፊደል ነው፡፡ ይህንን ፊደል በግብፅ ሄሮግሊፊክስ ፊደል ውስጥ የ‹ሀ›ን ምልክት እንደያዘ ka  (ካ) ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ይህንንም ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን የ‹ሥላሴ›ን አስተምህሮ ከግብፃዊያን አማልክት ካባሳ (ka-ba-sa) ጋር በማያያዝ ባብራራበት መጣጥፉ የ‹ካ›ን ፊደል ‹ሃ› በማድረግ በመጠቀም ‹ካባሳ›ን ሀበሻ በማለት ተርጉሞታል፡፡ ፀጋዬ በብዙ ጽሑፉ ‹ካም› የሚለውን የተፅውኦ ስም ‹ሃም› በማለት ይጠቀማል፡፡ ለዚህም የሠጠው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ‹ከ› የሚለውን ፊደል እንደ ‹ሀ› ይጠቀሙበታል የሚል ነው፡፡ (Africa Origin of Major World Religion: The Origin of the ‘Tirinity’ and Art (Ethiopian Origin to Egypto-Greek and Hebrew), page 102) ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በኾነ መልኩ ዶ/ር አየለ በክሬም ‹ሀ›ን ከሄሮግሊፊክሱ ‹ካ› ጋር ያመሳስሉታል፡፡  ከፊደል ጋር በተያያዘ ሌላ ምሳሌ እንጨምር፡፡

 በሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ በቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አማካይነት የተዘጋጀው ስለ ግዕዝና አማርኛ ቋንቋ ታሪክ የሚያትተው መጽሐፍ በገጽ 12 የ‹ፈ (ፌ)› ፊደል ውክልና ሲገልፅ ‹የአፍ ሥዕል የተከፈተ አፍ መስሎ ከመላስ ጋር ይታያል፡፡› ብሎ አስቀምጧል፡፡ ስለ ፊደሎች የቅጠል አቀያየር ታሪክ ሲናገርም ‹ጥንት ግን ቅጠላቸው በቀኛቸው በኩል ነበር፤ እነ ‹ፈ› ፊታቸው በቀኝ በኩል ነበር ይባላል› ብሏል (ገጽ 15)፡፡ ከእነዚህ የትርጉምና የታሪክ ጥቆማዎች ተነሥተንም የ‹ፈ›ን ፊደል ከግብፁ የሄሮግሊፊ ፊደል ‹ታ›   ጋር ብናጻጽረው አንድ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ሌሎቹንም የሄሮግሊፊክ ፊደሎች ከእኛ ፊደላት ጋር ብናጻጽራቸው ተመሳሳይ ውጤቶችን እናገኛለን፡፡ ለዚህም ይመስላል እነ ሎሬት ፀጋዬ እና እነ አባ ተስፋ ሥላሴ ሞገስ የግብፅን ሄሮግሊፊ ‹የኢትዮጵያ ፊደል› የሚሉት፡፡ እነዚህ ኹሉ ምስክሮች ሲደመሩ እና እላይ ከጠቀስናቸው ማስረጃዎች ጋር ሲያያዙ ፊደልና ጽሑፍ በኢትዮጵያ የተጀመሩ መኾናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

2. በፍልስፍና ጥበብ፡- በአውሮፓውያንና በቅኝዎቻቸው አስተምሮ መሠረት ፍልስፍና የተጀመረው በግሪክ አዮናውያን በሚሏቸው በእነ ጣለስ ነው፡፡ ‹ጣለስ ምልዓተ ዓለሙና ፍጥረታቱ ከምን መጡ ለሚለው ጥያቄ ከአንድ ነገር ፡-ከውሃ፡- የሚል መልስ በመስጠት ምክንያቱን ያስቀመጠ የመጀመሪያው ፈላስፋ ነው፤ በእሱ መነሻነትም ፍልስፍና ተጀምራ በግሪክ በልፅጋለች፡፡› የሚል አስተምህሮ ዓለማችንን ይመራል፡፡ ይሁንና ፍልስፍና በግሪክ መበልፀጓ እውነት ቢኾንም የተጀመረችው ግን ግሪክ ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፍልስፍና ጥያቄን በማንሳት እንደ መጀመሪያ ፈላስፋ የተወሰደው ጣለስ ግብፅ በመሄድ የሒሣብ፣ የጂኦሜትሪ፣ የሥነ ፈለክና የመሳሰሉ ትምህርቶችን መማሩ ተረጋግጧል፡፡ እንዲሁም ዓለም ከውሃ የተገኘ ነው የሚለው ትምህርቱ ከግብፅ ያገኘው መሆኑ እርግጥ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግብፆች ኹሉ ነገር ከውሃ የመጣ ነው በማለት አምልኳቸውን ጭምር ከውሃ ጋር ያያይዙ የነበሩ መኾናቸው ጥሩ ምሰክር ነው፡፡ የጥንት ግብፆች አምልኳቸውን በውሃ ይፈጽሙ የነበረበት ሥርዓት አሁንም በሀገራችን በኦሮሞዎች የኢሬቻ በዓል አፈጻጸም ጋር ተመሣሣይ መኾኑን ሎሬት ፀጋዬ በጻፈው መጣጥፍ አብራርቶ አስቀምጦታል፡፡ (Africa Origin of Major World Religion:… page 100)፡፡ ይህ ከኾነም ጣለስ ‹ኹሉም ነገር የተገኘው ከውሃ ነው› የሚለውን ፍልስፍናውን ከእነ ምክንያቱ የወሰደው ከግብፅ ነው፡፡

ይህም ብቻ ሳይኾን ብዙዎቹ የግርክ፣ የሮማና የሌሎች ፈላስፎችም የተጠቀሙባቸው መጻሕፍት ከግብጽ መጽሐፎች የተወሰዱ እንደኾኑ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ የአፍላጦን (ፕሌቶ) እና የአርስጣጣሊስ መጽሐፎች ከጥንት የግብፅ ጽሑፎች የተወሰዱ እንደነበሩ ሙግቶች ተነሥተዋል፤ የእነዚህን ሙግቶች ማስረጃዎቹ በማነጻጸርና ማመሳከር የትኛው ትክክል እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል:: በተለይ የፍልስፍና ዋና ዋና ፅንሣተ-ሐሳብና ማጠንጠኛ ነጥቦች ‹በሥርቆት› ሊባል በሚችል ደረጃ ከግብፅ ‹የምሥጢር ጥበባት› መጻሕፍት የተገለበጡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ዙሪያ Stolen Legacy: Greek Philosophy is Stolen Egyptian Philosophy የሚለውን መጽሐፍ መመልከት ብቻ ጠንከራ መከራከሪያ ይሠጠናል፡፡

እንዲሁም ከግሪኮች በፊት በግብፅ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመው የተለያዩ ትምህርቶች ይሠጡ እንደነበር ከተገኙ የጽሑፍ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ A companion to African philosophy የሚለው መጽሐፍ (ገጽ 35-36) ኢምሆትፕ(Imhotep)፣ ሆር-ዠድ-ኢፍ(Hor-Djed-Ef)፣ ካገምኒ(Kagemni) እና ፕታህ-ሆትፕ(Ptah-Hotep) የሚባሉትን በ3ኛው ሥርዎ መንግሥት (2668-2649) የግብፅን ባህላዊ ፍልስፍናን የጀመሩ ናቸው ይላቸዋል፡፡ ለምሳሌም ከዚህ በታች ያለውን በመጥቀስም ማስረጃዎችን ያሳያል፡፡

Books of wisdom (i.e. philosophy) were their pyramids,

And the pen was their child . . .

Is there anyone here like Hor-Djed-Ef?

 Is there another like Imhotep?

They are gone and forgotten,

But their names through their writings cause them to be remembered.

(Papyrus Beatty IV, Verso)

‹የጥበብ መጽሐፎች (ፍልስፍና) ፒራሚዶቻቸው ነበሩ፤

ብዕሩም ልጃቸው ነበር፤

እውን ሆር-ዠድ-ኢፍን የመሰለ ሰው ይኖራል?

ኢምሆተፕን የመሰለስ ሌላ ይገኛል?

እነሱም  ከዚህ ዓለም ያልፋሉ፤ ይረሳሉ፤

በሥራቸው አማካኝነት ግን በሥማቸው ሲታወስ(ሱ) ይናራል(ሉ)፡፡›

ሌላው ከፍልስፍና ጀመሪዎች መካከል በአስደናቂ ፍልስፍናው የሚታወቀው ኤራቅሊጰስ ኢትዮጵያዊ የነበረ መኾኑን የሚጠቁም ፍንጭ መገኘቱ ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ጥናት የሚያስፈልገው (በትክክል እሱ ስለመሆኑና አለመሆኑ፤ ለዚህም የሚኾን አስተማማኝ ማስረጃ ስለመገኘቱ) ቢኾንም እሱ ጽፎታል የተባለው መጽሐፍ ግን በዋልድባ ገዳም እንደሚገኝ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ የጻፈው መጽሐፍም በራሱ ስም ‹መጽሐፈ-ኤራቅሊጰስ› ይባላል፡፡ በእሱ መጽሐፍ እንደተገኘው መረጃ ከኾነ በጥንት ጊዜ በሌሎች ሀገራት በጠቢብነትና በነብይነት ታዋቂ የኾኑት አብዛኞቹ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው (አእምሮ ንጉሤ፤ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ ከቅራት- ዘመናዊ ፖሊስ፣ ገጽ 40)፡፡ ኾኖም በግሌ እሱ ሊኾን ይችላል የሚለው ግምቴ እጅግ ዝቅተኛ ነው፤ የጻፍኩት ለጥቆማ ብቻ ነው፡፡

ከዚያም ባለፈ የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና ምን እንደሚመስል ብንመለከት ጥንታዊ አስተሳሰብንና ጥበብን የተላበሰና የተፈጥሮ መሠረትን ያለቀቀ ኾኖ ይገኛል፡፡ ይህንን በሌላ ጽሑፍ ስለምንመለከተው አለመነካካት ይሻላል፡፡ በጥቅሉ የፍልስፍና ጥበብ አስተምህሮው የተጀመረው በጥንታዊት ኢትዮጵያ (ወይም በኢትዮጵያ ሥር በነበረችው ግብፅ) መኾኑን በጠቀስናቸው ነጥቦች ተመሥርቶ መገመት ይቻላል፡፡

3. በሥነ ፈለግ ጥናት፡- የሥነ ፈለግ ጥናትን የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ስለመኾናቸው ማስረጃዎች ይናገራሉ፡፡ ከምንም በላይ በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያዊው ሄኖክ እንደተጻፈ የሚታመነው መጽሐፈ ሄኖክ በዚህ ዙሪያ ያሉ የምርምር ሁኔታዎችን በአግባቡ መዝግቦ መገኘቱ ይህንን ሐቅ ይመሰክራል፡፡ መስፍን አረጋ የሚባሉ የጦቢያ ሊቅ ‹ራማ ሉል› በሚል ርዕስ በጻፉት መጣጥፍ ስለ መጽሐፈ ሄኖክ የሚከተሉትን ነጥቦች ጠቁመዋል፡፡ እሳቸው ከመጽሐፉ  ወስደው በማሳያነት ያስቀመጧቸው ነጥቦችን እነሆ!

  • ‹ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና የምታበራውም የፀሐይን ብርሃን በመፀብረቅ (reflect) እንደኾነ ለመጀመሪያ የተገነዘበው ሄኖክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ም.22 ቁ.5
  • የፀሐይና የጨረቃ ዘዌያዊ ገማዘንግ (angular diameter) በቅርበዛ (approximately) እኩል እንደሆነና ሄንዳላዊ የፀሐይ ግርዶሽ (total solar eclipse) የሚከሰተውም በዚሁ ምክኒያት እንደሆነ የገለጸው ሄኖክ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ ም.21 ቁ.57
  • ወደ አድማስ በጭራሽ ሳይዘልቁ ምድርን የሚሖሩ ኮኮቦች (በዘመናዊ አጠራር ሠቅዋልታዊ (circumpolar) የሚባሉ ኮኮቦች) እንዳሉ የጻፈው ሄኖክ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ ም.23 ቁ.14
  • የጨረቃ ሻጃወች (phases) ማለትም መልኮች እየተቀያየሩ ጨረቃ ሙሉ (full)፣ ሐኔ (crescent)፣ ሰኒም (gibbous) የምትሆነው የፀሐይ ብርሃን የሚያገኘው የጨረቃ ፊት ከምድር ስለሚዟዟር እንደሆነ ያብራራው ሄኖክ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ ም.26
  • ፈለኮች (planets) ፀሐይን እንደሚሖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘበውና እነዚህ ፈለኮች ለፀሐይ የተገዙ መሆናቸውን ለማሳየት በግዕ ቅኑይ (የተገዛ፣ የተነዳ) ብሎ የሰየማቸው ሄኖክ ነው፡፡ ም.24 ቁ.8
  • የራማዊ አካላትን በተለይም ደግሞ የፀሐይንና የጨረቃን ሑሰት (motion) ለመግለጽ ይረዳወ ዘንድ ራማ ሉልን (celestial sphere) ማለትም ጠፈርን ለተለያዩ መስኮቶች (በዘመናዊ አጠራር ቀኝ እርገት (right ascension) እና ዝቅዝቀት (declination) ለሚሉት) ለመጀመሪያ ጊዜ የከፋፈለው ሄኖክ ነው፡፡
  • ዓመትን ለ364 ዕለታት የከፋፈለው ሄኖክ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ ም.23 ቁ.20
  • እያንዳንዱ ዕለት ለ 18 ሸንሽኖች የሸነሸነው (በዘመናዊ አጠራር ለሃያ ዐራት ተሸንሽኖ ሰዓት ለሚባለው) ሄኖክ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ ም.21 ቁ.18-22
  • ባጠቃላይ ሲታይ ‹ዘመናዊ ጠፈርሲን› (Modern Astronomy) ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይኾን ‹መጽሐፈ ሄኖክ› በተለይም ደግሞ ከምዕራፍ 21 እስከ ምዕራፍ 25 ያሉትን ክፍሎች አብራርቶና አስፋፍቶ እንደገና መጻፍ ማለት እንጅ ሌላ ምንም ዐዲስ ነገር የለውም፡፡ በርግጥም ብልሁ ንጉሥ ‹ከፀሐይ በታችም ዐዲስ ነገር የለም› (መጽሐፈ መክብብ ም.1 ቁ.10) ያለው መጽሐፈ ሄኖክን አንብቦ ወይም ስለ ይዘቱ ተነግሮት መኾን አለበት፡፡›

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርና ጊዜያትን የማስላት ጥበብ ደግሞ የተመሠረተው በሄኖክ መጽሐፍ ነው፡፡ የሄኖክ መጽሐፍ ተጽፎ የተገኘው በግዕዝ ቋንቋ በሀገራችን ነው፤ በታላቅ ቅዱስ መጽሐፍነት ተቀባይነት ያለውም በተለይ በኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የሥነ ፈለግ ጀማሪዎቹና ምንጮቹ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ነው፡፡ የቀን መቁጠሪያችንም በአብዛኛው በእሱ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህም ብቻ ሳይኾን ‹ዐውደ ነገሥት፤ ወፍካሬ ከዋክብት›ን የመሳሰሉ አስደናቂ የሥነ ከዋክብት መጻሕፍት ኢትዮጵያውያን ምን ያህል በጥበብ ይራቀቁ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡ የመጽሐፎቹን የምርምር ስልትና ጥበብ ማስተዋል ጠቃሚ ነው፡፡  በተለይ በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያውያን ዕውቀት በጣም ጥልቅ እንደነበር በሚያደርጓቸው የመተት ሥራዎች (ጥበባት) መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የአስረስ የኔሰውን ‹የካም መታሰቢያ› እና ‹ትቤ አክሱም መኑ አንተ?› የሚሉ መጽሐፎች መመልከት የጥበባቸውን ጥልቀት ዐይቶ ለመደነቅ ይበቃል፡- ካልበቃም በመመራመር መጨመር ነው፡፡ እንዳውም የጠፈር አካላት አብዛኞቹ ስሞችም ከጥንት ኢትዮጵያውያን እንደተወሰዱ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ ረ.ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጥንታዊ ግሪኮች እሳቤ› በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 8 ‹እነሆ ዛሬ የሰማይ ከዋክብት የሥነ ፈለክ ካርታ የሦስቱ ኢትዮጵያውያን  ማለትም  የካስዮጵያ (ከ1890-1871 ከክ.ል.በ በኢትዮጵያ ነግሣ የነበረች)፣ የአንድሮሜዳና የሴፊየስ ስሞች የኮከብ መጠሪያ ኾነው በሳይንስ ዘርፍ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡› በማለት አስቀምጠዋል፡፡ ‹ሄርኩለስ› የተባለው ግዙፍ የአሜሪካ አውሮፕላን መጠሪያም በግሪኮች ተረት የተፈጠረ ኢትዮጵያው ጀግና ነው፡፡ እነነዚህ ኹሉ ማስረጃዎች የሚጠቁሙት ኢትዮጵያውያን በጥንት ሥልጣኔያቸው በሥነ ፈለግ ጥናት የዳበረ ዕውቀት ባለቤቶች እንደነበሩ ነው፡፡ ከኢትዮጵያም የቀደመ የሥነ ፈለግ ሥልጣኔ የተመዘገበበት ሀገር ነበረ ለማለት አያስደፍርም፡፡ የትኛው ሀገር?

4. በሐውልትና በሕንፃ ሥራ፡- የዓለማችን የመታሰቢያ ሐውልቶች ተመሣሣይ ቅርፅና አሠራር ይታይባቸዋል፡፡ ይህንንም የዓባይን ወንዝ ተከትሎ ከኑቢያው ወይም ከግብፁ…. እስከ አክሱም ከዚያም እስከ ዘመናችን የሰማዕታት ሐውልት በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ አሠራርም በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ ብቻ ሳይኾን በደቡብ አሜሪካ በማያና በኢንካ፣ በእስያ በህንድና ቻይና፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካም የሚታይ ሐቅ ነው፡፡ ስለ አጀማመሩም ከግብፁ (ሜርዌ) ሐውልት የሚቀድም የለም፡፡ ይሁንና የሐውልቱ ሥራ ከዚህ ተነሥቶ፣ ልምድ በመኾን በዓለማችን የጥንትና የቅርብ ሥልጣኔዎች ተንሠራፍቷል፡፡ ይህ የሐውልት ሥራ በግብፅ የተጀመረው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ (ፈርኦን)… ግብፅን ጭምር ያስተዳድር በነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ለዚያም ነው ቀጣይ በኢትዮጵያ የነገሡት ዘሮቹ ሐውልትን በአክሱም በማቆም አባታቸው የጀመረው ጥበብ እንዳይረሳ እና ለእነሱም መታሰቢያ (መታወሻ) እነዲኾናቸው በእክሱም የገነቡት፡፡

እንዲሁም ሐውልቶችና የግብፅ ፕሪያሚዶች እንዴት እንደተሠሩ ልዩ ጥቆማ የሚሠጠው የአባ ተስፋ-ሥላሴ ሞገስ ‹ቅዱስ ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ነው…› የሚለው መጽሐፍ የግብፅ ፕራሚዶችና ሐውልቶች በኢትዮጵያውያን መሠራታቸውንና ሰዎች ሊያዩዋቸው የማይችሉ የተቀበሩ ፕራሚዶች በኢትዮጵያ በዘጠኝ ሥፍራዎች እንደሚገኙ እስከነ ዓይነታቸውና መገኛቸው ከዋልድባ የብራና መጽሐፍ በተገኘ ማስረጃ ተመሥርቶ ይገልጻል፡፡ ይህም የሐውልትና የሕንፃ ሥራ ጥበብ በኢትዮጵያውያን ቀጥሎ እስከ ዘመናችን መድረሱ ይታመናል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሀገራት የሐውልትንና የግንባታ ሥነ ጥበብን የተማሩት በጥንት ኢትዮጵያውያን ነው፡፡  የሚገርመው ደግሞ የጥንት ሐውልትና ሕንፃ ዐሠራር ጥበብን ቴክኖሎጅ ከፍተኛ በደረሰበት በዚህ ዘመን እንኳን በአግባቡ መረዳት ሳይቻል መቅረቱ ነው፡፡ ለምሳሌም የአክሱምን ሐውልት፣ የግብፅን ፕራሚድ፣ የላሊበላን ውቅር አቤያተ ክርስቲያናት አሠራር ማስታወስ በቂ ነው፡፡

5. እዚህ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ በተለያዩ የጥንት የዓለም ሥልጣኔ መገለጫዎች ዙሪያ ወይም በጥንት ጊዜ በተጀመሩ የጥንት ሥልጣኔዎች የኢትዮጵያ ጀማሪነት የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በግብራና (በእርሻና በከብት ዕርባታ)፣ በመርከብ ጉዞ (በባህር ላይ ንግድ)፣ በአምልኮ ሥርዓት፣ በመንግሥት ሥርዓት፣ በኪነ ጥበባት፣ በኅብረት መሥራትና መኖርና በመሳሰሉት በጥንት ጊዜ በተጀመሩ ሥልጣኔዎች ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አሻራቸውን ጥለዋል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ርዕስ ብዙ አጨቃጫቂ ጉዳይን የሚዳስስና ሰፊ ጥናትና ምርምርን የሚፈልግ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይሁንና የራስን ቀድሞ በማክበር ማጥናትና ለራስ የጋራ የታሪክ ሀብት መቆጨትና ለዚያም መሟገት ግደታ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት በላቀና በተለየ የሥልጣኔና የጥበባት ምንጭና ባለሃብት መኾን መታደል እንጂ ትርጉም አልባ ነገር ላይ መዳከር አይደለም፡፡ ይህ ከሆነም የጥንታዊ ቀደም ሥልጣኔያችንን በአግባቡ ማስተዋልና ‹ለምን?› ብለን በመጠየቅ መቆጨት ይኖርብናል እንጂ ‹ተረት ነው› ከሚሉት ጋር አብረንና የእነሱ አፍ በመኾን መተረት የለብንም፡፡ ለመሆኑ ተረቱ ከየት መጣ? በዓለም የሥልጣኔ ታሪክስ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ተለይቶ ተረት የሚኾንበት ምክንያት ምንድን ነው? ቀደምት ስለሆነና የሥልጣኔው ማማ ከፍታ ለማመን ስለሚከብድ ነው? ከእነ ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ውጭስ በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትንና ዋሻዎችን ፈትሾ የጥንት ኢትዮጵያን ታሪክ ለመዳሰሰስ የሞኮረ ዘመናዊ ምሁር የትኛው ነው? ይህ ባልሆነበትስ ቀድሞ ታላቁን የሥልጣኔ መሠረት የሆነ ታሪክን በተረትነትና በትርጉም አልባነት ለመፈረጅ እንዴት ይቻላል?… ጥያቄዎችን መደርደር ይቻላል፤ ዋናው ነገር ያለው ግን የሚያስማማ መልስ ለማግኘት መሞከሩ ላይ ነው፤ የአቅማችንን ተቆጭተን ብንደፋደፍበት አይከፋም፡- ለመልሱ፡፡ ለማንኛው ታላቁ ምሁር ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን በአንድ ግጥሙ፡-

‹አስቀድሞ ሰው ሲፈጠር በዘፍጥረት በአፍሪካ አገር፣

እዚህ አሁን ባለንበት፣ በኖርንበት ክልል ነበር፡፡

ቀጥሎም ቋንቋና ፊደል፣ ልሣንም የፈለቀበት፣

የዓለም የሥልጣኔ እንብርት ይህችው የኛው ጦቢያ ናት፡፡› ብሏልና፤

(ጦቢያ አምስተኛ ዓመት ቁ.3፣ መጋቢት 1989)

ሌሎቻችንም እንደእሱ የሀገራችን ጥንታዊ ሥልጣኔ ቅናቱ ይኑረን፤ አሜን!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply