በደርግ አብዮታዊ አገዛዝ ዙሪያ የተደረጉ የደራሲያን ሥላቆችን ምንያህል ያውቃሉ?

ለአብነት ያህል የአለቃ እንባቆም፣ የአቤ ጉበኛ፣ የጳውሎስ ኞኞን እና የመንግሥቱ ለማን ሥላቆች እናስታውስ እስቲ፡፡ ሥላቃቸውን በተራ ንግግር ሳይሆን በግጥም ያቀረቡት አለቃ እንባቆም ናቸው፡፡ ግጥማቸው እንዲህ ይላል፡
‹ንገረው ለተጉለት ንገረው ለቡልጋ፣
አገሬን ወረራት የዝንጀሮ መንጋ፤
ይሠረዝ ይደለዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ይደለዝ ይሠረዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ሰው ከተፈጠረ ገና ሦስት ዓመቱ፡፡›
ይህ ሥላቃዊ ግጥም የተገጠመው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደው አንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት ሥልጣን ያዙ በተባለበት ጊዜ ነበር፡፡ ገጣሚውም ግጥማቸውን በሬድዮ ካነበቡ በኋላ ሌላ ትርጉም እንዳይሠጥባቸው ‹አገሬን ወረራት ያልኩት የዝያድ ባሬን ወታደር ነው› ብለዋል፡፡ እውነታው ግን በአገራችን እንደተለመደው ባንድ ሰው መመራት ቀርቶ በአንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት መመራቷ ገርሟቸው የተቀኙት ቅኔ ነው ይባላል፡፡ የሁለተኛው ስንኝም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፤ ሦስተኛውም የአብዮት በዓል ሲከበር አብዮቱን አሞገሰው ሰው በእግዚአብሔር ሳይሆን ኤንግልስ እንዳለው በሥራ የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው እንዲናገሩ ስለታዘዙ ‹የአገራችን ሰው የተፈጠረው ከአብዮቱ በኋላ ብቻ ነው› በሚል አንድምታ ሰው በኦሪት ጊዜ ተፈጠረ የሚለውን እንደ ስህተት የቆጠሩት መስለዋል፡፡ ይህም ለሚገባው ሶሻሊዝምን ያመሰገኑ መስለው ኦሪትን ማወደሳቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግጥሙም በባሕርዩ ንጽጽራዊ ሥላቅ ይባላል፡፡
ደራሲው አቤ ጉበኛ በመጨረሻ ዘመኑ ላይ ባሕር ዳር የድርና ማግ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለጎጃም ነጋደዎች ያከፋፍል ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን ግን ድርና ማጉን ለጎንደር ነጋደዎችም ስለሸጠላቸው፤ ጎጃሜዎች ኮታችንን ለሌላ ሰጠብን በሚል ከሰሱት አሉ፡፡
እናም ደኛው ‹አቶ አቤ ይህንን ለምን አደረግህ?› ሲለው፤
‹ጌታየ የጎንደር ነጋደዎች ኢትዮጵያውያን መስለውኝ ነበር፤ ወደፊት አልሸጥላቸውም› አለ ይባላል፡፡
አቤ አሁንም እዚያው ባሕር ዳር እንዳለ ካድሬዎች እየተመለመሉ የካቲት አሥራ ሁለት ት/ቤት ይገባሉ፤ በሦስት ወራት ውስጥ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን እየተማሩ ይመረቁና ባሕር ዳር ይመለሱ ነበር አሉ፡፡ እናም ‹ማርክስና ኤንግልስ ደደቦች ስለሆኑ ፍልስፍና ሲያጠኑ ሠላሳና ዐርባ ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ የእኛ አገር ካድሬ ግን በሦስት ወር ውስጥ እየላጠው መጣ› ብሎ እንደተሣለቀ ይነገራል፡፡
አንድ ወቅት ላይ ጳውሎስ ኞኞ ‹ሠርቶ አደር ጋዜጣን ትወደዋለህ ወይ?› ተብሎ ተጠይቆ ነበር አሉ፤ ጋዜጣው ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የበላይ ጠባቂነት የሚዘጋጅ ነው፤ ታዲያ ጳውሎስም ምሳሌ በመጠቀም ተሣልቆባቸዋል፤ እንዲህ አለ ‹አንድ ገዚ አንዱ ‹ማርያም ትወዳታለህ?› ተብሎ ሲጠየቅ ለምንድ አልወዳት ከግን የሚያላትም ልጅ እያላት አለ፤ እኔም ሠርቶ አደር ጋዜጣን አልወደውም ብል ከግንድ ጋር ስለሚያጋጨኝ እወደዋለሁ› ብሏል፡፡
ንግግራቸው ሁሉ በቀልድ የሚታጀበው መንግሥቱ ለማም ባህል ሚኒስቴር ውስጥ እያሉ አንድ የባህል መምሪያ ኃላፊ ‹ጓድ መንግሥቱ አርንጓደው ዘመቻ ተጀምሯል፤ በዚህ ዙሪያ ድርሰት ይጻፉ› ይላቸዋል፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ ስብሰባ ሲሄድ ጠርቶ ‹ድርሰቱ ከምን ደረሰ?› ይላቸዋል፡፡
መንግሥቱም ታዲያ ‹ወንድም ትቀልዳለህ ወይስ የምርህን ነው?› ይሉታል፡፡
ኃላፊውም ‹በአብዮትማ ቀልድ የለም› በማለት ትካሻውን ይነቀንቅባቸዋል፡፡
መንግሥቱም ‹አንተ ደደብ ደነዝ ነህ እኔ ድርሰት እንደ ልብስ ስፌት አድርስ ተብዬ ስለ አረንጓደው ዘመቻ አልጽፍም፡፡ ይህንን ከፈለግህ አራት ኪሎ ሄደህ ለአለቆችህ ንገራቸው፤ ስትነግራቸውም ከግንድ ጋር አስደግፈው በሣንጃ ይወጉኛል፤ ያን ጊዜ ስለ አረንጓደው ዘመቻ ሳይሆን ሳንጃው በመቀመጫዬ ስለመግባቱ ድርሰት እጽፋለሁ፤ ምክንያም ያመኛላ!› ብለውታል ይባላል፡፡
(ምንጭ፡- ታደለ ገድሌ፣ ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply