በ20ኛ መ/ክ/ዘ 2ኛው አጋማሽ የኢትዮጵያዊያን አካሔድ ዋና ሕጸጽ (ክፍል 1)

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የምትገኝና የዲሞክራሲ ሥርዓት ያልሰፈነባት ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግም ልጆችዋ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡- መስዋዕትነት ከተባለ፡፡ ይሁንና  አልቻሉም፡፡ ይህ ሀገሪቱን የማዝበን እንቅስቃሴ በግልፅና በቆራጥነት መቀንቀን የጀመረውም በዋናነት ከ1950ዎቹ ጀምሮ መሆኑና የሀገሪቱ ችግሮችም የበለጠ እየተወሳሰቡና እየባሱ የመጡት ከዚያ በኋላ መሆኑ የእንቅስቃሴውን ሕጸጽ (ጉድለት) ፈትሸን ማየት እንዳለብን ይጠቁመናል፡፡

በእኔ እምነት ከ1950ዎቹ በኋላ ኢትዮጵያን ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የተሞከሩ የትጥቅም ይሁኑ የሰላማዊ ትግሎች ጭብጣቸውን የሳቱ ይመስሉኛል፡፡ የእነዚህን ትግሎች መዳረሻ ግባቸውን ስንፈትሸው፣  የሔዱበትን አቅጣጫ ስንቃኘው፣ የመነሻ ምክንያታቸውን ስንመረምረውና አንዳንድ የተገኙ የአዎንታ ወይም የአሉታ ታሪካዊ ውጤት ስንገመግም ግልፅ የሆነ ነገር አናገኝባቸውም፡፡ ይህንንም ከሥነ-አመክንዮአዊ ሕጸጻት አንጻር ብንተነትነው የጭብጥን መሣት ሕጸጽ (Missing the point) ተፈጽሞበት እናገኘዋለን፡፡ እስቲ ለማሳያ የሚሆኑ የተወሰኑ ታሪካዊና ነባራዊ አስረጅዎችን እንመልከት፡፡

  1. 1.  ታሪካዊ ጭብጥን መሣት፡

ኢትዮጵያ ታሪካዊት ሀገር መሆኗን የሚክድ ብዙም የለም፡- በታሪክ ዘመን ርዝመቷና አመጣጥ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፡- በታሪካዊነት ትሸፍነው የነበረው ቦታ ቢያጨቃጭቅም፡፡ ችግሩ ያለውን በዋናነት ባለቤት የሆንበትን ታሪክ መጠቀም አለመቻልም ይመስለኛል፡፡ ይህም ጫፍ ላይ በተንጠለጠለ የታሪክ ባለቤትነት ላይ ሲሽከረከር የበለጠ ችግሩን ያጎለዋል፤ አጉልቶትም ይገኛል፡፡

ከ1950ዎቹ በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ ከቀድሞዋ ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ተጣልቷል ማለት ይቻላል፡፡

ምንም እንኳ በዐፄ ቴዎድሮስ ሙከራና በተከታዮቻቸው ነገሥታት ጥረት በ19ኛው መ/ክ/ዘ ዘመናዊነት በሀገራችን ተጀምሮ በተለይም በዐፄ ምኒልክ መሠረቱ የተጣለ ቢሆንም፤ ዐፄ ኃይለ ሥላሴም ሕገ መንግሥት እስከ ማርቀቅ ደርሰው ሀገሪቱን ለማዝመን ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም እስከ 1950ዎቹ ድረስ ኢትዮጵያ በባህላዊና በልምድ አሠራር እየተፏንቀቀች የምትገኝ ሀገር ነበረች፡፡ ከ1950ዎቹ በኋላ ግን የተማሩት ልጆቿ በሀገራቸው ኋላቀርነት ቁጭት ተነሳስተው የአስተዳር ችግሮች እንዲስተካከሉና ፊውዳላዊ ያሉት የአገዛዝ ሥርዓት እንዲስተካልና በማርክስታዊ ርእዮተ ዓለም አዲስ ኢትዮጵያን ለመፍጠር (ለመገንባት?) ከፍተኛ መስዋዕትነት በማድረግ ጣሩ፡፡ ጥረታቸው ግን በአካሔድም፣ በግብም ውል አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም፡-

የቀድሞውን የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት፣ የአንድ ብሔር የፊዳላዊ አገዛዝ ሥርዓት ጨቋኝነት ታሪክ አድርጎ የመፈረጅ አባዜ ነበር፡፡

ሀገሪቱ በውስጥ እርስበርስ በሚደረግም ሆነ ከውጭ ሉዓላዊነትን በመድፈር በሚደረግ ጦርነት ተወጥራ የኖረች መሆኗ እውነት ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም ታሪካችን ጦርነት ነው ብሎ መፈረጅና በባህል መስተገብሮች፣ በሥልጣኔ አስተዋጽኦና በነፃነት አርዓያነት ያበረከተችውንና ያላትን ትልቅ የታሪክ ሀብት ሳይመረምሩ ወይም በፊዳላዊ ሥርዓት ፈርጆና ንቆ በመተው በጦርነት ዙሪያ ብቻ ማቀንቀን ግን ዘርፈ ብዙዋን ኢትዮጵያን መዘንጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ በመሆን ለዓለም ኅብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓን ብዙ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች የመሠከሩት መሆኑን የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑት ምሁራን ከ20ኛው መ/ክ/ዘ መጀመሪያ ጀምሮ ሲያቀነቅኑት እንደነበር ታሪካዊ መዛግብትን ማገላበጥ ብቻ ይበቃል፡፡ ለምሳሌም ‹ የጥንቱ የኩሽ ግዛት አስገራሚዎቹ ኢትዮጵያዊያውያ› (እ.ኤ.አ.1926) የሚለውን የድሩስላ ዲ. ሆስቶን ና ‹ኢትዮጵያ እና የሥልጣኔ ምንጭ› (እ.ኤ.አ.1939) የሚለው የዮሐንስ ጃክሰን መጻሕፍት በመመልከት ብቻ ሀገራቸውን የኢትዮጵያ የሥልጣኔ አስተዋኦ መረዳትና ይህንንም እንደአንድ የታሪክ ግብዓት በመውሰድ ሀገራቸውን ለማበልፀግና ታላቅ ሀገር መሆኗንም ለማሳየት ይችሉ ነበር፡- የ1950ዎቹና 1960ዎቹ ተማሪዎች፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አባቶቻችን ለነፃነት የከፈሉትን መስዋዕትነት በማስተዋል የታሪክ ኃላፊነትን ለመወጣት ያለውን የባህልና የማኅበረሰብ ልምድና ማንነት እንደነበረ በመጠበቅ ኢትዮጵያ የምትዘምንበትን ስልት ነድፈው መጣር ነበረባቸው፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩት የተማሪ ምሁራኖች ግን ከጦርነት ውጭ ምንም ታሪክ እንዳልነበራት አድርገው በመውሰድና የነበረውን የአገዛዝ ሥርዓት በማጣጣል አፈርሰው አዲስ ኢትዮጵያን ሊፈጥሩ ነው የጣሩት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ለማን እንደታገሉ እና እንደሚታገሉ ባይታወቅም ንግግራቸውና ገድላቸው ሁላ የተጋድሎ ሆኗል፡፡ እየተገዳደሉም የመገዳደል ገድልን አወረሱን፡፡

ልብ ብሎ ላስተዋለው ገድላቸው ሁሉ አፍራሽና አስፈራሽ ሆነው እርስ በርስ የተደባደቡበት ነው፡፡ ታሪኩ በድብድብ እንዲቀጥል የፈለጉም ይመስላሉ፡- ለዚህም ንግግሮቻውንና መጻፎቻቸውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ከ1950ዎቹ በኋላ ያለው የታሪክ ፍረጃ የኢትዮጵያን የጥንታዊ የሥልጣኔ ምንጭነት የካደ፣ የኅበረተሰቦቿን የባህልና የማንነት መስተጋብር የረሳና አባቶቻችን ለነፃነት ያደረጉትን መጋደል ለአልሆነ ፕሮፓጋንዳ ከማዋል ያለፈ ክብር ያልሰጠ በመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታሪካዊ ፍሰትንና ጭብጥን የሣተ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሌላው የዘውጋዊነት ፖለቲካን እንደ እስትራቴጂ ወስዶ ሕዝቦችን ለማናከስ መጣር የሚንፀባረቅበት እንቅስቃሴ ‹አደገኛው› የሚባለው ከ1960ዎቹ በኋላ የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ የሚገርመው ግን እነዚህ ለዘውግ ፖለቲካ ሌት ተቀን የሚተጉት ምሁራን ‹እውን ብሔራቸውን ያውቁታል?› ብለን ጥያቄ ብናነሣ ከቁጣ ያለፈ መልስ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ላለማስቆጣት ዝም ይባላል እንጂ! ለምሳሌ ሕወሓትና ኦነግን ወስዶ ማየት ይቻላል፡፡ ሕውሐት በትግራይ ክልል ታግሎ በማሸነፍ የሀገሪቱን ሥልጣን ይዞ የሚያስተዳድር ታጋይ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፤ ኦነግም የኦሮምን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ነጥሎ የራሱን ሀገር ለመመሥረት የሚጥር ድርጅት እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ ሕውሐት ለምን ትግል አካሔደ? ለትግል የተነሣበትስ ምክንያት አግባብ ነበር? መጨረሻስ የተነሣበትን ዓላማ ከግብ አደረሰ ወይስ ቀየረ?…

ለምን ትግል አካሔደ ብለን ስንጠይቅ ‹ትግራይ ተጨቁና ስለነበር ነጻ በማውጣት ራሷን የቻለች ሀገር ለማድረግ› የሚል ዓላማ እንደነበረው ከተመዘገቡ የታሪክ ሰነዶች ማግኘት ይቻላል፤ በአጭሩ ትግራይን ራስዋን የቻለች ሀገር ለማድረግ ማለት ነው፡፡ እና ይህ አጥጋቢ ነበር? ለመሆኑ ዐፄ ዮሐንስ ጣሊያንን ትግራይ ውስጥ ጥለው መተማ ድረስ በመሔድ መስዋዕት የሆኑት ለማን ብለው ነበር? መቼም ለትግራይ ብለው እንደማይመልሱ እገምታለሁ፤ ካልመለሱ ታዲያ ማንን ነው የሚታገሉት የአበቶቻቸውን ዓላማ ሁሉ? ግን ግን ትክክለኛው ዓላማቸውን በመያዝ ግባቸውን መቱ? ዓላማቸውን አሳክተው ግባቸውን ቢመቱ ትግራይ ተገንጥላ ነበር፤ ትግራይ ግን በአትዮጵያ የታሪክ መሠረትነቷ ስላለች የተነሱበትን ዓላማ አላሳኩም ማለት ነው፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ዓላማቸውንማ ወደ ኢትዮጵያዊነት ለውጠውታል ከተባለ በፊት መጀመሪያ ይዘውት የተነሱት ዓላማ ስህተት ነበር፤ ለትግራይ ብቻ ብለውም አልተዋጉም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነም ሌላ ጥያቄ እናነሳለን ‹ለምን የመጀመሪያውን ዓላማ መቀየር አስፈለጋቸው? ስህተት ስለነበር ወይስ በሌላ ምክንያት? ስህተት ስለነበር ከተባለ በስህተት ሀገርን በማወካቸው ተጠያቂ ናቸው፡፡ ከእነሱም ይልቅ ‹ገንጣይ፣ አስገንጣይ› ይል የነበረው ደርግ ትክክል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በስህተት ሀገር ለመገንጠል ሲታገሉ ምን ያድርግ አገሪቱን ከመገነጠጣል አደጋ የማዳን ኃላፊት የለበትም እንዴ? በሌላ ምክንያት ከተባለ ምንድን ነው ይህ ምክንያት? እሽ! ምንም ይሁን ‹በሌላ ምክንያት ነው› በሚለው የሚስማሙ ከሆነ አሁንም የተነሱበትን ‹ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዓላማቸውን› ይዘውታል ማለት ነው? በዚህ መልክ የኦነግንም መገምገም ይቻላል፡፡

የኦነግ ትግል የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጨቋኞች ነፃ አውጥቶ ኦሮሚያ የምትባል ሀገርን ለመመሥረት ነበረ፤ ነውም መሰል፡፡ ይህ ለዛ ባለው ፈሊጣዊ አማርኛ ቢገለፅ ‹ኦነግ የሚታገለው ግንድን ቆርጦ ቅርንጫፍ ለመትከል ነው› ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ከሆነም ወይ ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ አያውቀውም ወይም ሌላ ምክንያት አለው ለማለት ያስችላል፡፡ ምክንያቱም እነ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን እንዳረጋገጡትና ያለው ነበራዊ የኦሮሞ ባህል ከጥንት የግብጥ ታሪክና ባህል ጋር ሲነፃፀር እንደሚያስረዳው፤ እንዲሁም የጥንቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ መጽሐፍም እንደሚጠቁመው ከሆነ የኦሮም ሕዝብ የጥንት የኩሽ ዋና ግንድ የነበረና አሁንም ያንን ባህል ጠብቆ የሚገኝ አስደናቂ ሕዝብ ነው፡፡ ይህም ማለት የኦሮም ሕዝብ ማንነት በአሁኗ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ከአፍሪካ ሕዝቦች የታሪክ አሻራ ጋር የተያያዘ መሠረት ያለው ነው፡፡ በተጨማሪም ኦሮሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ባለው መልካም ባህል ተዋህዶና ተደበላልቆ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ እና ይህንን ሕዝብ የሚያውቁት ከሆነ እንዴት ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ይታገላሉ; ‹የኦሮም ሕዝብ በሌሎች ስለተጨቆነ ከዚያ ነፃ ለማውጣት ነው› የሚል አስተሳሰብ ሲያራምዱ ይደመጣሉ፡፡ የታሪካዊ መሠረትነቱ ይቅር ብንል እንኳን ‹የኦሮሞ ሕዝብ በሌሎች በመጨቆኑ ነው ይገንጠል የምንለው› የሚሉትም ቢሆን አያስኬዳቸውም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ለመገንጠል ምክንያት የሆናቸው ጭቆና ከሆነ ጭቆናውን ያካሔደው ግማሽ ክፍል የኦሮሞ ሕዝብ አካል የነበረ ነውና (የሸዋ ኦሮሞ ባብዛኛው አለበት) የመገንጠል እስትራቴጂያቸው ግማሹን የኦሮሞ ሕዝብ አያካትትም ማለት ነው፤ በተጨማሪም አሁንም የኦሮሞ ሕዝብ በሌሎች እየተገዛ ነው በማለት ያጠነጥናል፤ ይህ ደግሞ የበለጠ ሌሎች ጥያቄዎችንና ምስቅልቅሎችን የያዘ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ምናልባት ኦነግን መሪዎቹ ሳያውቁት የሌሎች ተልዕኮ መፈፀሚያ እንዲሆን አድርገውታል በማለት እንዲንጠረጥረው ያደርገናል፡፡

የኢትዮጵያን የጥንት ሥልጣኔ መሠረትነት ኦሮሞ በባህሉ ጠብቆት ስለሚገኝ ይህንን ለማጥፋት የሚጥሩ አካላት ‹ኦነግን ባላወቀው አንጀቱ ውስጥ ገብተው በመጎዝጎዝ› መጠቀሚያቸው እንዲሆን አድርገውታል በማለት መጠርጠራችን ምክንያታዊነት አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኦሮምኛ ፊደል የኢትዮጵያን የጥንት ሥልጣኔ ፊደል እንዳይጠቀም መደረጉ የጥርጣሬያችን ማሳያ ይሆናል፡፡ ይህ በታሪክ ጥናት የሚተነተን በመሆኑ ብንተወው እንኳን ኦነግ ‹የኦሮም ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥዬ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር እምሠርታለሁ የሚለው የ1960ዎቹ ትኩሳት ያጋለውና የታሪካዊ፣ የባህላዊና የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክና ጥንታዊ የኢትዮጵያ መሠረትነት ያላገናዘበ (ያለወቀ ማለት ነው የሚቀለው) ነው፡፡  በጥቅሉ ግን ኦነግም ሆነ ሕውሐት የ1960ዎቹ ተማሪዎች የታሪክ ጀማሪነትና የጎሠኝነት ልክፍት ውጤቶች ናቸው፤ ለጎሠኝነት ትግል ውል አልባ መሆን ማሳያዎችም ይሆናሉ፡፡

በአሉታ ዙሪያ የማቀንቀን ጥንውት የተላበሰ ነው፤

የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ችግር የነበረንን ታሪክ አጉልቶ በአግባቡ አለመጠቀም ብቻ አይደለም፡፡ የተከናወኑ የታሪክ ክፍተቶችን በመፈለግ በአሉታ መጠለዝም እንጂ! በዚህም ታሪክ ማለት ማንነትን ማወቂያና የተሻለ ልምድን መቅሰሚያ መሆኑ ቀርቶ መዋቀሻና ስህተትን ነቅሶ ማራገቢያ ማለት እስኪመሰል ድረስ ‹እከሌ የተባለው ንጉሥ ይህንን ሠርቶታል፣ የእንትናን ኃጢያት መሬት አትችለውም…› ዓይነት አቀራረብን የተከተለ ነው፡፡ ለዚህ እሩቅ ሳንሔድ የተጻፉ የተጋዳላዮቻችንን የጦርነት ገድላት ማየት ነው፡፡ ከገድላት ውጭ ያሉትም ቢሆኑ መንፈሳቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ‹ሥልጣን፣ ባህልና አገዛዝ፣ ፖለቲካና ምርጫ› በሚለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን የአገዛዝ ሥርዓትና ባህል በገዥና ተገዥነት፣ በባርነትና በጌታነት፣ በጦርነት… የፈረጁበትን አቀራረብ መመልከት ይበቃል፡፡ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለተወሰኑ ሣምታት ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋር ተያይዞ በንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ፣ በአጼ ምኒልክ፣ በአጼ ቴዎድሮስ፣ በአጼ ዮሐንስና በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዙሪያ የተደረገው ክርክራዊ ማጠልሸት እንደማሳያ ሊሆን ይችላል፤ የተመለከትነው የድገፋ ካራቴና የአሉታ ጥለዛ ነበር፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ በጓደኛሞቹ በበዕውቀቱ ስዩምና በዓለማየሁ ገላጋይ መካከል በዐፄ ቴዎድሮስ ዙሪያ የተደረጉ ክርክር መሰል ጭቅጭቆችም ቢሆኑ የአሉታ ጥለዛን የሚያቀነቅኑ ነበሩ ለማለት ያስደፍራል፡፡ በአጠቃላይም አሰተውለን ከመረመርነው ከ1950ዎቹ ወድህ ያለው ታሪካችን በጎሣ ፖለቲካ የጠለሸ፣ በቅርብ ጊዜ የታሪክ ክስተቶች ወቀሳ የተቃኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡

2. የኢትዮጵያን የታሪክ ፍሰት የተቃረነ ወይም ታሪካዊ ግኑኝነት የሌለው ትግል ማካሔድ፡-

ከቅርብ ጊዜያት ታሪካችን የትግል እሮሮ የበዛበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወይ በትጥቅ ወይም በስድድብና በሲቪል ግብግብ የተሞላ ነው፡፡ ግን ይህ መሥዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ከኢትዮጵያ የታሪክ ልምድና አመጣጥ አንጻር ምን ያህል ተክክልነት አለው ብለን ብንፈትሸው በአብዛኛው የታሪክ ተመጋጋቢነት የሌለው መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ እንዳውም የታሪካዊ ማንነት ተቃራኒ የሆነ አካሔድም ይስተዋልበታል፡፡ ለምሳሌ፡-

የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የታሪክ ባለቤት የሆነውን የዘውዳዊ ሥርዓት ማጥፋትና ማጥላላት

በኢትዮጵያ ከተፈፀሙ የታሪክ ሰህተቶች የነበረንን ጥንታዊ የንግሥና ሥርዓት እንዳልባሌ መጣሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከተቀበልነው ከ5000 ዓመታት በላይ ባንቀበለው የ1000 ዓመታት በንጉሣዊ አገዛዝ ሥርዓት ስትተዳደር የነበረች ሀገር ነበረች፡፡ የንጉሥና ሥርዓትም በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍልም የሚንፀባረቅና የተለመደም ነበር፡፡ በዚህ ሥርዓትም ቢያንስ ነፃነቷን አስከብራ መኖር ችላለች፤ ባህሉዋንም ጠብቃለች፡፡ የዚህን ዓመታት የንጉሣዊ አገዘዝ ሥርዓት እንደ አሮጌ እቃ በመጣል የፎከረ ምሁር ያለባት ሀገርም ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በአንድ ንጉሥ ስህተቶች (ስህተት ከተባለ) አጠቃላይ ሀገሪቱ የነበራት ታርካዊ የአገዛዝ ሥርዓት ገርስሶ መጣል ከተሠሩ ሰህተቶች ከፍተኛውን ይይዛል ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ (ምናልባት በዚህ ጉዳይ ላይ ንጉሡም ራሳቸው ተጠያቂ ይመስሉኛል)፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን የራስን ስህተት ለመደበቅ ሲባል የፊውዳሉን ሥርዓት ማጠልሸት አሁንም ቢሆን የሚቀነቀን መሆኑ ግርምትን ይፈጥራል፡፡

ወደ ራስ ታሪክና ማንነት ያለመመልከት አባዜ፡-

ከ1950ቹ በኋላ ያለው ትውልድ የራሱን ታሪክ፣ ባህልና የሥልጣኔ አሻራ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ ለማወቅ ጥሯል ብለን ብንጠይቅ መልስ ለመስጠት የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር የተናገረው ነው፡፡ ስብሐት ስለ ዳኛቸው ወርቁ ‹አደፍርስ› መጽሐፍ አስተያየት ሲሠጥ ‹አደፍርስን እስካነብ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ መጻፍ የሚቻል አይመስለኝም ነበር፤ አደፍርስን  ካነበብኩኝ በኋላ ግን በእንግሊዘኛ የጀመርኩትን ‹ሌቱም አይነጋልኝ› የሚለውን መጽሐፌን ቀይሬ በአማርኛ ጻፍኩት› የሚል ዐይነት አስተያየት መስጠቱን ብዙ ጊዜ የምንሰማው ነው፤ ዘነበ ወላም በማስታወሻው ጽፎታል፡፡ ይህንን አባባል ከ1960ዎቹ ተማሪዎች ሁኔታ ጋር አያይዘን በብንመለከተው ልዩ ትርጉም የሚሠጠን ይመስለኛል፡፡ ምክንያም በማንበብ ባህሉ አርአያችን የምንለው ስብሐት በዚያን ጊዜ የተጻፉ የፍቅር እስከ መቃብርን ዓይነት የልብ ወለድ መጽሐፎችን አለማየቱ፣ ‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር› የሚለውን የገብረ ሕይወት ድንቅ መጽሐፍ ሳያነብ መቅረቱ፣ የገድላትን አጻጻፍ ያልቃኘ መሆኑ፤ የዘርያዕቆብን የፍልስፍና መጽሐፍ አለማየቱ፣ የዕጓለ ገ/ዮሐንስ ‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ› ሳያነበው መቅረቱ… ምን ማለቱ እንደሆነ አስቡት፤ እነዚህን ሀገራዊ መጽሐፎች ያልተመለከተ ምሁር ምን ያህል በራሱ ባህል ምን እንዳለና ምን መጻፍ እንዳለበት ያውቃል ማለት እንችላለን;  ይህን ጉዳይ ያነሣሁት ስብሐትን ለመውቀስ ብዬ ሳይሆን የዚያት ዘመን ትውልድ ምን ያህል የራሱን ባህል ይመረምር ነበር የሚለውን ለማሳየት ብዬ ነው፡፡ አንድ ያጋጠሙኝም የ1960ዎቹ ምሁርም ሁኔታ መጥቀስ እዚህ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሰውዬው መጽሐፍን ሲበሉ የኖሩ፤ የመጽሐፍ ቀመኛ ናቸው፤ በተለይም ያለነበቡት የፍልስፍና መጽሐፍ የለም ማለት ይቻላል፡- ከፕሌቶ ‹ዘሪፐብሊክ› ከሚለው መጽሐፍ ጀምሮ ያሉ ፍልስፍናዊ ሥራዎችን በሙሉ አንብበዋል፡፡ እናም እኝህን ሰው ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ስለሚገኘው ‹አንጋረ ፈላስፋ› ስለሚለው መጽሐፍ አነሳሁባቸው፤ እንደማያውቁት ነበር የነገሩኝ፡፡ ልብ ብላችሁ አስተውሉልኝ፤ የሰውየውን የዕውቀት ደረጃና ያነበቡትን መጽሐፍ ብዛት አይታችሁ፤ ለምን የሀገራቸውን ታዋቂ የፍልስፍና መጽሐፍ ሳያነቡ ቀሩ ብላችሁ ጠይቁልኝ፤ መልሱን ታገኙታለችሁ፡፡ የራስን አቅሎ የማያት ዝቅጠት አታዩባቸውም;

አረ እንዳውም እውነት እንነጋር ከተባለማ ‹የዚያን ጊዜ ትግል ምን ለመፍጠር ነበር? በተወላገደ የሶሻሊዝም አመለካከት በመቃኘት የነበረንን ጨዋ ባህል ለማጥፋት አልነበረም? ሶሻሊዝምን እንደ ጽንፈኛ ሃይማኖት የሚያቀነቅን ትውልድ አልነበረም? መመዘኛውና ማጣቀሻው ሁሉ ማርክስ፣ ሌኒን፣ቼኮቬራ፣… አልነበሩም? ይህ ምን ማለት ነው? …› ለመሆኑ ምን ያህሉ ተማሪ ነበር የጥንት ኢትዮጵያን አስተምህሮና ባህል አውቆ ለመጠበቅ የጣረ? ማን ነው እጓለ ገብረ ዮሐንስ የአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ ሲከፈት ያቀረበውን የሬድዮ ንግግር አድምጦ ወይም የጻፈውን መጽሐፍ አንብቦ ጠቃሚ ነው በሚል የጠበቀው? የንጉሡን አደራስ ያከበረ@…. ለመሆኑ ምን ያህሉ ተማሪ ነበር እኛ እኮ የራሳችን ጥንታዊ ታሪክ አለን፤ ስለዚህ መጀመሪያ የራሳችን ታሪክ ከራሳችን ምንጭ በየገዳሙ ዞሮን ትውፊታዊ ማስረጃዎችን ዳስሰን ማየት አለብን ብሎ የተሟገተ? ለማሐይምናን ወታደሮች አሳልፈው በመስጠት ሀገሪቱን የደም መሬት ያደረጓት ራሳቸው ምሁር ነን የሚሉት የጊዜው ተማሪዎች አይደሉም እንዴ?… ብቻ ይቅር እንጂ! ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተጉበትን ትምህርት ገደል የሰደዱት እኮ ምሁራን ተማሪዎቹ ራሳቸው ናቸው? እሳቸው ምን ያድርጉ ‹መጣንበዎት! ልናጠፋዎት ነው! ወዮወሎት!; ሲባሉ ያቅማቸውን እንቢ አሉ፡፡ ምን ያድርጉ የጥንታዊት ኢትዮጵያን ቀጣይነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብኝ እንጂ ዝም ብዬ በሶሻሊዝም ፕሮፓጋንዳ ስትጠፋ አላይም አሉ፤ ምን ያድርጉ?

ሀገራዊ የታሪክ ምንጮችን በተረትነት የመፈረጅ አባዜ፡-

ከ1950 በኋላ ባለው ታሪካችን ትልቁ አደጋና ውስብስብ ችግርን የፈጠረው ‹በገዳማት የሚገኙና እምነት ነክ ሆነው የተጻፉ መጻሐፎችን ሁሉ የያዙትን በተረትነት የመፈረጅ ወይም በሥነ ተረት መርህ መመዘን ነው፡፡ ነጮች ትንሽ የታሪክ ቀዳዳ ካገኙ ያንን መሠረት አድርገው ታሪኩን የራሳቸው ለማድረግ ይጥራሉ፤ የእኛዎቹ ደግሞ ስንት ማስረጃ ያለውን የታሪክ ምንጭ በሃይማኖት እያሳበቡ ተረት ነው ይሉናል፡፡ ለምሳሌ የጀርመን ቱሪስቶች የላሊበላ ውቅር አቤያተ ክርስቲያናት ላይ የናዚን አርማ የሚመስል ቅርጽ በማየታቸው ‹ይህንን የሠሩት ጀርመኖች ናቸው› ብለው ነበር፤ ዘርዓ ያዕቆብ እሱ በነበረበት ጊዜ ነጮች በኢትዮጵያ የነበሩ መሆናቸውን በመጥቀሱ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን አንድ ፈረንጅ ነበር ብለውታል ራሱን (እሱ ከጻፈው ታሪክ ይልቅ ነጮቹ የገመቱት ታሪክ ትክክል ሆኖ) ፤ ሌላም ሌላም፡፡ የእኛዎቹ ደግሞ ዘርዓ ያዕቆብንም አያቁትም፡፡ ቢያውቁትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን ሃይማኖትን ለመስደብ በማጣቀሻነት ለመጠቀም ነው፡፡ ለአብዞዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን የአክሱም ሐውልት እንዴት ተሠርቶ ቆመ? የላሊበላ ውቅር አቤያተ ክርሰቲያናት እንዴት ተሠሩ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የላቸውም፤ ቢኖራቸውም ውጭዎች የነገሯቸው ግምት ነው፡፡ ምክንያቱስ ቢሉ? በኢትዮጵያ የሚነገረው ተረት ነውና፡፡ በጊዜው ከነበረ የታሪክ ማስረጃ ይልቅ የአንድ የታሪክ ኤክስፐርት አስተያየት ሲታመን አይገርምም?

በአጠቃላይ ከዚህ በላይ እንደተገለተጠቀሰው ከ1950ዎቹ በኋላ የኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ውጥንጥቅጡ ወጥቶ ይገኛል፡፡ ይህንንም ልብ ብሎ ላስተዋለው የታሪካዊ ጭብጥን የመሳት ሐጸጽ ነግሶበት ያገኛል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ አሁን ላለንበት ነበራዊ ሁኔታ ዋና መሠረቱ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን የሚገኘው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አራንባና ቆቦ መቆም፣ የባህል መላሸቅ፣ የራስን ማንነት ማጣጣል… የ1960ዎቹ ምህራን ያመጡብን ውዥንብር ውጤት ነው፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply