ተቃውሞ ስብዕና ክርክር (Argument against the person- Argumentum ad Hominem)

(ካሣሁን ዓለሙ)

‹አህያውን ፈርቶ ዳውሉን› እንዲሉ ብዙውን ጊዜ ሰዎች የክርክር በቂ ማስረጃ ወይም ምክንያት ማቅረብ ሲያቅታቸው ክርክሩን ይተውና የክርክሩን አቅራቢ አካል (ሰው) ሰድበው በማዋረድ ወይም በማሸማቀቅ መርታት ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ሰፈር ቤት ውስጥ የሚውሉ ሴቶች ሲጣሉ ‹አላውቅሽምና ነው፤ አንቺ ምንትስ!› በመባባል በስድብ ይቧነናሉ፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የሚሳደቡት ስድብ በተጣሉበት ጉዳይ ጋር አብሮ የማይሔድ ይኾናል፡፡ የዚህ ሕጸጽ አፈጻጸምም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

የተቃውሞ ስብዕና ክርክር ሕጸጽ ተከራካሪዎች የሚሳተፉበትና ክርክሩም መጀመሪያ ባቀረበው ሰው ላይ የስድ ውርጅብኝ በመንዛት የሚፈጸም ሕጸጽ ነው፡፡ ማለትም በዚህ ክርክር በመጀመሪያ አንድ ተከራካሪ የክርክሩን ፍሬ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ኾኖም ኹለተኛው ተከራካሪ ለቀረበው ሐሳብ መቃወሚያ የሚኾን ማስረጃ ወይም ምክንያት ማቅረቡን ይተውና የመጀመሪያውን ሰው ስብዕና ቀጥታ ይቃወመዋል፡፡ በዚህ ትክክለኛ ማስረጃ ያቀረበ በማስመሰል ይደመድማል፡፡ የመጀመሪያውንም ሰው ወይ በቀጥታ በመስደብ ወይም የሥራውን ኹኔታ በማጣጣል ሊቃወመው ይችላል፡፡ በዚህ ሦስት የተቃውሞ ስብዕና ሕጸጽ ዓይነቶች የታወቁ ናቸው፡፡

  1. ሰውየውን በቀጥታ በመስደብ (Fallacy of ad Hominem Abusive

የዚህ ክርር ሕጸጽ የሚፈጸመው ኹለተኛው ተከራካሪ የመጀመሪያውን ሰው የክርክር ሐሳብ በመተው ሰውየውን ራሱን በስድብ ውርጅብኝ ሲያጦዘው ነው፡፡ የስድብ ውርጅብኝን የሚነዛውም የሰውየውን ጠባይ፣ የቤተሰቡንና የሕይወቱን ገፅታ፣ መልኩን፣ ሞራሉን፣ የሚገኝበትን አኗኗር ወይም ደረጃ በመጥቀስ ሊኾን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‹ጭሣም›፣ ‹ማስጠሌ›፣ ‹ሸርሙጣ›፣ ‹በሽተኛ›፣ ‹ባሪያ› እና የመሳሰሉትን ስድቦች በመጥቀስ ሊኾን ይችላል፡፡ ሰዳቢው ተከራካሪም ዋና ዓላማውም በስድቡ ተከራካሪው ተሸማቆ ወይም ተናዶ የክርክሩን ጭብጥ ወይም እንዲስት ወይም ማስረጃውን እንዳያስተውል ማድረግ ነው፡፡

አስረጅ፡- አበበ ‹ወሲብ ቀስቃሽ ጽሑፎች በት/ቤት ውስጥ መታየት የለባቸውም› ብሎ ይከራከራል፤ አበበ ራሱ ማነው? ጠዋት ማታ ሴተኛ አዳሪ ቤት የሚገኝ ሸርሙጣ አይደለምእንዴ! እንዳውም አበበ በሠፈሩ ውስጥ የሚታወቁ በግብረ ሶዶማዊ ተግባሩ ነው፡፡

በዚህ አስረጅ ውስጥ የተጠቀሰው የአበበ ክርክርና የተዘረዘሩት መጥፎ ጠባያት አብረው የሚሔዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አበበ ያቀረበው ዋና ሐሳብ ‹ወሲብ ቀስቃሽ ጽሑፎች በት/ቤት ውስጥ መግባት የለባቸውም› የሚልነው፡፡ በኹለተኛው ተከራካሪ የቀረቡት የመቃወሚያው ማስረጃዎች ደግሞ ‹የአበበ ሴተኛ አዳሪ ጋር ሁልጊዜ መሔድና ግብረ ሰዶማዊ ተግባር መፈጸሙ› ናቸው፡፡ በመንደርደሪያነት የቀረቡት የስድብ ማስረጃዎች ሲመረምሯቸው የቀረበውን የክርክር ሐሳብ አያግዙም፡፡ ኾኖም በሥነ ልቦና ጫና አበበን አዋርደው ሐሳቡ ተቀባይነት እንዳያገኝና አፍሮ ዝም በማለት ክርክሩን እንዲያቆም የማድረግ ተፅእኖ አላቸው፡፡

ይህ ዓይነት የክርክር ሕጸጽ በሀገራችን በድሮ የበልሃ ልበልሃ ሙግት የተለመደ ተከረካሪን መርቻ ስልት ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ አንድ ተሟጋች በባላንጣው ላይ አውርዶት የነበረ የስድብ ውርጅብኝ ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡

በልሃ ልበልሃ

ያጠየ ሥርዓቱን

የመሠረቱን

አልናገርም ሐሰቱን፣

ሁልጊዜ እውነት እውነቱን፣

ሚስቲህ ዐመዳም

ካራህ (ቢለዋህ) ጎማዳም

የቤትህ በታች አጋም፣

ያንተ ብጤ ልጋጋም፣

የቤትህ በታች አፋፍ፣

ንዳንተ ያለ ልቅ አፍ፣

እራትህ ቆሎ፣

የካራህ እጀታ ኮሸቶ፤

ሚስትህ አርጣጣ፣

ሜዳ (ሽንት ቤት) እማትወጣ፡፡

(ሽበሺ ለማ፣ 1985፣ ገጽ 110-111)

ይህ የስድብ ውርጅብኝ መዓት ተሟጋቹ የባላንጣውን ስሜት በስድብ በማዋረድና በማሸማቀቅ ፈርቶ እንዲረታለት ያደረገበት ታክቲክ ነው፡፡ ከዋናወ ሐሳብ ይገባኛል ጥያቄ ጋር ግን አብሮ አይሔድም፡፡ ምክንያቱም ለመሰዳደብ ብሎ የሚካሰስ ሰው የለምና፡፡

  1. 2. የሰውየውን ኹኔታ በመጥቀስ (Fallacy of Hominem

                 Circumstantial)

የሰውየውን ኹኔታ በመጥቀስ የሚፈጸም ሕጸጽ ኹለተኛው ተከራካሪ የመጀመሪያውን ተከራካሪ በቀጥታ በመስደቡ የሚፈጸም ዐይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ የኹለተኛው ተከራካሪ የመጀመሪያውን ሰው ኹኔታ የሚቃወመው ‹ያቀረበው የይገባኛል ጥያቄ ስህተት ነው፤ምክንያቱም በዚያ ቦታ/ኹኔታ ላይ የሚገኝ ሰው ይህንን ሐሳብ ማቅረብ (መደገፍ) አይችልምና፡፡› ወይም ‹የራሱ ኹኔታ እውነት ወይም ትክክል የኾነ ነገርን ለመናገር አያስችለውም› በሚል ይዘት ነው፡፡ የሰውየውን ኹኔታም በመመልከትና እንደማስረጃ በመጠቀም የክርክሩን ዋና ሐሳብ ዋጋ የለሽና ትርጉም አልባ በማስመሰል ያሰፍረዋል፡፡ ክርክሩንም እንዳይቀጥል መስመሩን ይዘጋበታል፤ በዚህም ክርክሩ የተወደደለት ይመስለዋል፡፡

አስረጅ ‹አየለ ‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ የበዓላት ቀናት ስለበዙ መቀነስ አለባው›ብሎ ይከራከራል፡፡ ለመኾኑ አየለ ማነው? የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ዲያቆን አይደለም እንዴ! ስለዚህ የአየለን ክርክር መቀበል አያስፈልግም፡፡

በዚህ አስረጅ ተከራካሪው የተጠቀመው ስልት የአየለን ሐሳብ በማስረጀ መቃወም ሳይኾን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ዲያቆን መኾኑን በመጥቀስ ‹የሃይማቱ ተከታይ ዲያቆን ከኾን መቃወም አጥችልም› በሚል የማሳጣት ዘዴ፣ የአየለ ክርክር እንዳይደገፍ ማድረግ ነው፡፡

 

  1. አንተው ራስህ ሕጸጽ (You too Fallacy or to quoque)

  ይህ አንተው ራስህ ሕጸጽ የመመጻደቂያ ክርክር ሕጸጽ ነው፡፡ የሚፈጸመውም ኹለተኛው ተከራካሪ ቀድሞ ክርክሩን ያቀረበውን ሰው እንደሠራው አድርጎ በማቅረብና ሊቃወመው እንደማይችል በመንገር ሲሳፍረው ነው፡፡ በዚህም ‹አንተ ራስህ የሠራኸውን ነው የፈጸምኩት›በሚል ስሜት ተጀቡኖ ይመጻደቃል፡፡ ‹አንተ ራስህ ስለፈጸምከው እኔን መቃወም አትችልም፡፡› የሚልመሸፈኛን ለክርክሩ ያቀርባል፡፡

 አስረጅ፡- ‹አንድ እናት ልጃቸው ከተለያዩ ወንዶች ጋር መማገጥ እንደጀመረች ይሰማሉ፡፡ አንድ ቀንም ጠርተው፣ ድርጊቷን እንድታቆም እንዲህ በማለት ለመምከር ይሞክራሉ፡፡ ‹አረ ተይ ልጄ ይኸ የምሰማው ነገር ጥሩ አይደለም፤ ዘመኑም መጥፎ ስለኾነ ይቅርብሽ› ይሏታል፡፡ ልጅቱም ተቆጥታ ‹ለእኔ ሲኾን ለምን ያስቆጣሻል? አንቺ ራስሽ በወጣትነትሽ ጊዜ ‹አለ የተባለ ጎበዝ› እንዳላመለጠሸ ስንቱ ጎረምሣ ሲደባደብብሽ እንደነበር ስትናገሪ አልነበም?› በማለት መልሳላቸዋለች ይባላል፡፡

 

በዚህ አስረጅ ልጅቱ ያቀረበችው ማስረጃ እነቷ ካቀረቡት ሓሳብ ጋር በአመክንዮአዊነት አብሮ አይሔድም፡፡ እናቷን ግን ‹አንቺው ትሠሪው ነበር› በማለት አሳፍራ በድርጊቷ መቀጠል ትችላለች፡፡ የተግባሯን ትክክለኛት የሚያስረዳ የተቃውሞማስረጃ ወይምምክንያት ግን አላቀረበበችም፡፡

በአጠቃላይ ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው ኹሉም የተቃውሞ ስብዕና ሕጸጽ ዓይነቶች ዓላማቸው የመጀመሪያወን ተከራካሪ ስብዕና ወይም ኹኔታ መጥፎ ገጽታ በማላበስ ያቀረበው ክርክር ዋጋ እንደሌለው አድርገው መርታት ነው፡፡ ኾኖም ግን የክርክሩ መንደርደሪያና መደምደሚያ አግባባዊ ግንኙነት አይኖራቸውም፤ የመጀመሪያወን ተከራካሪበማሸማቀቅ ግን የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን የተቃውሞ ስብዕና ክርክር ከአንዳንድ ሰው ድርጊት ወይም ጠባያት ጋር ተያይዞ ከቀረበ ሕጸጽ ላይፈጸምበት ይችላል፡፡

አስረጅ፡- ‹ከበደ ኃላፊነት የጎደለው ጨካኝ ሰው ነው፡፡ምክንያቱም ባለፈው ዕሁ በመኪና ውስጥ ቦንብ አፈንድቶ 12 ንፁሃን ሰዎችን ገድሏልና፡፡

በዚህ አስረጅ የከበደ ኃላፊነት የጎደለው ጨካኝ ሰው መኾን በመኪና ውስጥ ቦንብ አፈንድቶ 12 ሰዎችን ከመግደሉ አረመኔያዊ ድርጊት ጋር አመክንዮአዊ ግንኙነት ጋር ስላለው ክርክሩ ሕጸጽ አልተፈጸመበትም፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply