ትኩርት ያላገኘው ባህላዊ የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር ጥበብ

በካሣሁን ዓለሙ

(ይህ ጽሑፍ በውይይት መጽሔጽ ቁ.19 ታትሞ የወጣ ነው)

  1. መንርደሪያ

እኛ ኢትዮጵያዊያን በባህላችን የሚደነቁ ጥበባትን በተለይም የዳበረ የራሳችን ባህላዊ (ልማዳዊ) የትችትና የክርክር ባህል ያለን ሕዝቦች ብንኾንም በተለያየ ማኅበረሰቦች የዳበሩት የባህላችን ማሳያዎች ተጠንተውና ተገናዝበው ለዘመናዊ ትምህርትና ፍትሕ ግብዓት እንዲኾኑ ፍልስፍናቸውና ሥነ አመክንዮአዊ ጥበባቸው አልተመረመረም፡፡

ምንም እንኳን በብዙ የሀገራችን ክፍሎች ዘመናዊ ትምህርትና የፍርድ ቤት አሠራር የጥንቱን እያጠፋውና በነበር እያስቀረው ቢኾንም (በተለይ ከ1923ቱ ሕገ መንግሥት ከወጣና የዘመናዊ ፍ/ቤቶች ከተቋቋሙ በኋላ) በአንዳንድ ሥፍራዎች ‹የተጠየቅ ልጠየቅ› እና ‹የበልሃ ልበልሃ› ክርክሮች ልምድ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ማሳያዎች አሉን፡፡ ለምሳሌ በመንዝ አካባቢ እስከ ቅርብ ጊዜ ይሠራበትና እዛፍ ሥር እየተሰበሰቡ መሟገት የተለመደ እንደነበር እና በጨዋታ በመከራከር የሚፎካከሩበት ሰዎች መኖራቸውንም በዚያ አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ በማስተማር ላይ የቆየ ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ የተጠየቅ ልጠየቅ ስልትን የመሠለ የሙግት ጥበብ እያለን፣ ለዚህም የተመዘገቡ የክርክር ማሳያዎች ሞልተውን፣ ከሥነ አመክንዮ ዕውቀት አንጻር (ተክለ ማርያም ፋንታዬ ‹ተጠየቅ› በሚል ርዕስ በ1953 ከጻፉት መጽሐፍ ውጭ) አለመመርመሩ ያስቆጫል፡፡

  1. የልማዳዊ (በልሃ ልበለሃ፣ ተጠየቅ ልጠየቅ) ሙግት ምን ይመስል ነበር?

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል በጥር 27፣ 1958 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ባህል ጥናት አቅርበውት በ1961 ዓ.ም በሳተሙት ‹ባለን እንወቅበት› በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 18 ላይ ‹ሕዝባችን ብልህ ነው፤ ፈጥኖ የመረዳትና የማስረዳት ችሎታ አለው፤ የነገርን አካጌድ ይመረምራል፤ የአስተዳደር ምክር፣ ክርክር፣ ዳኝነትና ፖለቲካ የተፈጥሮ ገንዘቡ ናቸው፤ ስዚህ ብዙ ሰው ያለ ትምህርት አእምሮ ብስሎ ይታያል፡፡› በማለት ያስቀመጡት የታመቀ እውነት የያዘ ገለጻ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ መመራመር ሳያስፈልግ በቅርስነት የሚታወቁትን ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችን ማየት በቂ ነው፡፡ እነዚህን የንግግር ለዛዎችና ያላቸውን የመልዕክት ዕምቅነት ሳናስተውላቸውም በእየዕለት ንግግራችን እንጠቀምባቸዋለንና ልለፋቸው፡፡ ይህ ሊኾን የቻለው ግን በሊቃውንቱ አስተውሎታዊ ሥርዓት አሠራርና የባህል ቀረጻ መኾኑን ማስታወስ ግን ጠቃሚ ነው፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ሊቀ ሥልጣናት ሀ/ማርያም ወርቅነህ (አኹን አቡነ መልከጸዴቅ) እንዳስቀመጡት ከኾነ ‹ሊቃውንቱ ችግራቸውን ሳያስቡ ከመሥራታቸው የተነሣ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ለይተው የዕውቀት ደሴት፣ የቅኔ አደባባይ፣ የዜማ መዲና፣ የንግግር ስልት መገኛ› ስላደረጓት በክርክርና በሙግት ስልትና ልምድም የተካኑበት ነበሩ (ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፣ ገጽ 13):: ክርክር በኢትዮጵያውያን የትልቅነት መለኪያ ያዋቂነት ማስመስከሪያ ልምድ ነበረ፡፡ በመኾኑም በሸንጎ አደባባይ ከጭቃ ሹምም ኾነ ከንጉሥ ዘንድ ቀርቦ ሐሣብን በተመጠነና በጣፈጠ ቃላት በማቅረብ ንግግር አዋቂነትንና የመከራከር ችሎታን ማስመስከር የትልቅነት ማሳያ ነበር፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝም ያገራችንን ሹማምንት ‹ውሏቸውም ሥራን ትተው በክርክርና በሙግት ብቻ ነው፡፡› በማለት የተቹት ሲገለበጥ ሹማምንቱ ጊዜያቸውን ሙግትና ክርክርን በመመልከትና በማድነቅ ይጠመዱ እንደነበር ምስክር ይኾናል (መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ 1953፣ ገጽ 28)፡፡

በክርክር ጊዜ ያለውን የሙግት ፈሊጣቸውንና የአመላለስ ቅልጥፍናቸውን አስደናቂነት ግን ምሳሌ ጠቅሶ ማሳየት ግድ ይለኛል፡፡ ስለሺ ለማ የተባሉ ምሁር ‹ልማዳዊ ሙግት ለዛን፣ ደፋርነትን፣ ንቃትን፣ ብልሃትንና ጮሌነትን ይጠይቅ ስለነበር ተሟግቶ ለመርታት ረትቶም እርካታን ለማግኘትና በሌሎችም ዘንድ ለመወደስ በቅድሚያ የእነዚህንና የመሳሰሉትን ሙያዎች ባለቤት መኾን አስፈላጊ› መኾኑን ይገልጻሉ (ተጠየቅ፣ ገጽ 24)፡፡

 ይህንንም ‹የኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕግ፡ ሌባ ሻይ› የሚል መጽሐፍ ያዘጋጁት ከበደ ሀብተማሪያም (ፊታውራሪ ዶ/ር) ‹የበልሃ ልበልሃ ሥርዓቱ በጽሑፍ የተመዘገበ ይመስል በአእምሯቸው    ቀርፀው ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ከፈገግታና ከደም ግባት ጋር የሚሰጡ ወይንም የሚያስተምሩ የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶች በዚህ አጋጣሚ ሳይደነቁና ሳይመሰገኑ አይታለፉም፡፡› (ገጽ 47) ካሉ በኋላ ፈርንሳዊው ማረብ (ዶ/ር) ‹ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯቸው ጠበቆች ናቸው፡፡› (ገጽ 50)፣ ‹የሃበሾችን የሙግት ሥርዓት ለመናገር ከተፈለገ ጥንታዊነቱ ብቻ አይደለም የሚጠቀሰው አስደሳችነቱም ጭምር ነው የሚያስገርመው› (ገጽ 29) ከማለቱም በተጨማሪ የሙግት ሥርዓቱ በፊልም ሳይቀረፅ በመቅረቱ መቆጨቱን ጠቁመዋል፡፡

የሙግት ሥርዓቱም፡

‹በዛፍ ሥር ወይንም ቅልጥጥ ባለው ሜዳ በሚካሄደው ሙግት ከሳሽ ረዥም ዘንጉን እያንቀጠቀጠ ተከሳሽን ተጠየቅ እያለ (ሲያጣድፍ ተከሳሽ በበኩሉ ልጠየቅ) ያጤ ሥርዓቱን የመሠረቱን በመለት ጭብጡን ለማስቀመጥ ከፊት ወደ ኋላ ፈግ-ፈግ ከወደ ኋላ ወደ ፊት ደር-ደር ማር በቅሎ ፈረስ ወቄት ወርቅ ወዘተ እሰጥ ማለቱ› ልዩ ስሜት መፍጠሩን ነው የገለጹት (ገጽ 2)፡፡

ስለሽ ለማም፡-

‹ተውኔታዊ ባሕርይ የነበረው የከሳሽና የተከሳሽ አለባስ፣ አቋቋም፣ ዘንግ አያያዝ፣ የሰውነት እንቅሰቃሴ፣ የነገር አቀራረብና ባጠቃላይም ሞቅና ደመቅ ያለው ጥምር የአሞጋገቱ ስልት ነው፡፡ ተሟግቶ ለመርታት፣ ረትቶም እርካታን፣ ዝናና ክብርን ለመቀዳጀት በቅድሚያ የተሟጋቹን ንቃት ብልህነትና ብርታት ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የተነሣ ከሰውነት እንቅስቃሴው ሌላ በተለይ የመሟገቻው ቋንቋ በተዋቡ ቃላት፣ በምሳሌያዊ አነጋገር፣ በተረት፣ በአፈታሪክ፣ በእንቆቅልሽና በመሳሰሉትዘዬዎች የበለፀገና ለዛማ መኾን ይገባው ነበር፡፡ የእንዚህ ሁሉ ውሁድ የችሎት ነፃ ትርኢት ነው እንግዲህ ወጪ ወራጁን አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ይማርክና ያማልል የነበረው፡፡› (ተጠየቅ፣ ገጽ 15)

ሙግቱም በአገረ ገዥዎች/በወንበሮች/በዳኞች/… ‹ፀሐይ ጮራዋን ስትፈነጥቅ በዛፍ ጥላ ሥር ወይንም ቅልጥጥ ባለው ሜዳ የጀመሩትን ችሎት ጀምበር ስትጠልቅ› እንደሚያቆሙ ይገልጻሉ (የኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕግ፡ ሌባ ሻይ፣ ገጽ 25)፡፡

  1. የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር አቀራረብ

ተጠየቅ ልጠየቅ ሲቀርብም ሥርዓት አለው፡፡ ስለኾነም በሥርዓቱ የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች አሟልቶ መቅረብ (ለምሳሌ ከሣሽ ከቀኝ ተከሣሽ በግራ መቆም፣ እማኝ ማንሣት፣ የሥራትና የበስላ ዋስ መጥራት፣…)፣ የተሟጋቹ በአለባበሱ ማደግደግ (ኩታ ወይም ሸማ በትካሻ ዞሮ ወገብ ላይ በመጠምጠም የኩታውን አንዱን ጫፍ በቀኝ ወይም በግራ ትከሻ ማውረድ)፣ በአነጋገሩ የሙግት ሥርዓቱን ጠብቆ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር ሥርዓት መሠረትም እማኞችና ዳኞች ‹ይፍረድብኝ! ይፍረድብኝ! ባደላም ያድላብኝ፣ በጌታዬ ጠላት ሠይፍ ሞት ይፍረድበት፣ የራቀውን በመድፍ የቀረበውን በሰይፍ አርዶ ፈርዶ ይጣለው በሚል አነጋገር› ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ (ይጋባሉ) (ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል፣ ባለን እንወቅበት፣ ገጽ 45)፡፡

ተከራካሪው ሲያቀርብም የውርድ አነዛዝ ሥርዓትን ተከትሎ ያቀርባል፤ ለዚህም ተደጋግመው የሚጠቀሱ ቃላት/ሀረጋትን ይጠቀማል እንጂ ዝም ብሎ በፈለገው መንገድ አይጀምርም፤ ‹እግዜር ያሳየዎ፣ መልአኩ ያመልክተዎ…› ብሎ ያመለክታል፡፡ ውርድ ሲነዛም ችሎታው ያለው ከኾነ በግጥምና በምሳሌያዊ ንግግሮች አስውቦ ያቀርበዋል፤ ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችም እንደ ሕግ አንቀጽ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ባብዛኛው ግን በውርድ ጊዜ ተዘውትረው የሚባሉት ይታወቃሉ፡-

በላ ልበለሃ የዐጤ ሥርዓቱን፣

የመሠረቱን፣

የአብርሃም ራቱን፣

አልናገርም ሐሰቱን፣

ሁል ጊዜ እውነት እውነቱን

(ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል፣ ባለን እንወቅበት፣ ገጽ 46-47)፡፡

ከዚያም በተጠየቅ ክርክሩን በማቅረብ ውርድ ይነዛል፤ ‹ውርድ መንዛት ማለትም አንድ ተሟጋች በጥያቄ ጊዜ ያስተማመነውንና ከሌላው ቃል ያገኘውን መልስ ለክርክሩ እንዲደግፈው የሚያብራራበትና የራሱን ቀጥተኛነትና እውነተኛነት የሚገልፅበት ዘዴ› ነው (ስለሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ ገጽ 91)፡፡ በውርድ መንዛት ወቅትም በማር ማገጃ ተይዞ ‹እሰጥ! አገባ!› በመባባል እማኞች እየተቹትና፣ ‹ፍጆታ› እና ‹ወስደህ መልስ› በሚሉ መቀባባያ ቃላት እየተፈራረቁ ሙግቱን ከሣሽና ተከሣሽ (ጠበቆች) ያቀርቡታል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን ክርክሩ ገና ሲጀመር ከሣሽ ‹ተጠየቅ› ሲል ተከሣሽ ‹አልጠየቅም› በማለት ሊሞግት ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ በአባትና በልጅ መካከል የተደረገ  ዝነኛ ሙግትን ለማሳያነት እንመልከት፡፡

ልጅ፡- ‹ተጠየቅ!›

አባት፡- ‹አልጠየቅም!

ሰማይ አይታረስ፣

ውሃ አይታፈስ፣

መሬት አይተኮስ፣

ብረት አይርስ፣

አባትም አይከሰስ፡፡›

ልጅ፡- ‹ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል፣

ውሃም በእንሥራ ይታፈሳል፤

መሬትም በማረሻ ይተኮሳል፣

ብረት በከሰል ይርሳል፣

አባትም በጥፋቱ ይከሰሠሳል፡፡›

አባት፡- ሰማይ ያለ ዓመት ነጎድጓድ አያወርድ፣

ፈጣሪ ያለ ክህደት ገሃነም አይሰድ፣

ያለ እርሻ በመሬት ላይ እሳት አይነድ፣

ሴትም ያለ እንሥራ ውሃ አትወርድ፣

አባትም ያለ ጥፋቱ ልጁን አይክድ፡፡

አባት ለልጁ ዳኛ፣

አትሞግተኝም ዳግመኛ፡፡

በዚህ ክርክርም አባትዬው ‹አባት አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› የሚለውን የሙግቱ ማጠንጠኛ በማድረግ ‹እሰጥ!› ‹አገባ!› የሚለው ውስጥ ሳይገባ በሥርዓቱ መሠረት ‹አባት አይከሰስምና› ‹አልጠየቅም› በማለት ረተውበታል ይባላል፤ ‹ሥርዓት ልክ ነው› እንዲል የክርክሩ ጭብጥ ራሱ ጥልቅ ፍልስፍና ይዟል፡፡ ይህም የኾነው ተከሳሹ ከጥብቁ (ከተከሰሰበት ሙግት) ውስጥ ሳይገባ መኾኑ ልብ ይሏል፤ የፈጠራውን፣ የፍጥነቱን፣ የችሎታውን፣… ጉዳይም የሚደንቅ መኾኑንም እንደዚሁ፡፡

  1. የተጠየቅ ልጠየቅ ሙግት ስልቶች

የበልሃ ልበልሃ እና የተጠየቅ ልጠየቅ ሙግቶች የሚካሄዱትም በተለያዩ መንገዶች ነው፤ መንገዶቹን በመፈረጅ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢኾንም ከተሟጋቾቹ ኹኔታ፣ ከሚቀርበው ሙግት ዓይነትና ደረጃ፣ ከጠበቆቹ ችሎታ፣ ልምድና ምርጫ አንጻር እና ከእማኞችና ከዳኞች/ወንበሮች/አገረ ገዥዎች/ አኳያ የሚፈረጅ ይኾናል፡፡ ስለሺ ለማ በማብራራት፣ ስድብ በመሰንዘር፣ ራስን ወይም ዳኞችን በማሞጋገስ፣ ችሎታን በመፈተን እና ሂስ በመሰንዘር በሚል በስድስት በመክፈል ስልቶቹን ለማሳየት ምክረዋል፡፡ በእውነትም አብዛኛውን ጊዜም ክርክሩ የሚካሄደው በግጥም በመከሸንና በምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮች በማስጌጥ፣ ድንገቴና ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ የተደበቀ እውነትን በቃላት ስንጠቃ በማውጣጣት፣ ችሎታን በማስመስከር፣ ዳኞችን በማሞጋገስ፣ ተቀናቃኝ በማንኳሰስና በመስደብ… ነበር፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን ጭብጦች ተትተው፣ ችሎታዎችና መደናነቆች ዐይለው ከክሱ ውጭ በኾነ ምክንያት ያልተጠበቀ ፍርድ ሊሰጥ ይችላል፤ ዳኞችም ላሞገሳቸውና የተሻለ መተያያ ላቀረበ ሊያደሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ለአንድ ዳኛ ከሣሽና ተከሣሽ አንዱ ብር፣ ሌላው ደግሞ በቅሎ ጉቦ ሠጥተው ፍርዱን ይጠብቃሉ፤ ዳኛውም በቅሎ ለሰጣቸው ይፈርዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተፈረደበት ‹ምነው ጌታዬ በጠዋት ብር ብዬ መጥቼ ጉዳዬን ነግሬዎት እንዲህ ያደርጉኛል› ብሎ ዳኛውን ሲጠይቃቸው ‹ታዲያ መጪ ብሎ በበቅሎ ቀደመሃ!› ብለውታል ይባላል፡፡

በልጅ ኢየሱ ጊዜ ደግሞ አንድ ቀኛዝማች ሶርሱ የተባሉ ዳኛ ጠበቃው በሚከተለው መልኩ ስላወደሳቸው ‹እስቲ ድገመው› ብለው ላሞገሳቸው አስደልተው ፈርደውለታል ይባላል፡፡

‹በላ ልበልሃ

ቀኛዝማች ሶርሱ፣

ወርቅ ነው ትራሱ፣

ሐር ነው ግላሱ፣

ተድፍን ሐበሻ መርጦ የሾመው ኢያሱ፤

ቀኛዝማች ሶርሱ ለወደደው፣

ከእሳት ያወጣል ከነደደው፤

ቀኛዝማች ሶርሱ የፈረደው፣

ያዳል ጩቤ ያረደው፤

እርዱም አይንፈራገጥ፣

ፍርዱም አይገለበጥ፡፡›

በዚህ ዓይነትም በዳኞች ችግር፣ በተሟጋቾች ችሎታ መለያየት፣ በሙገሣና በብልጠት ፍርድ ሊዛባ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተሟጋቹ የሌላውን የጠበቃ ችሎታ የማይቋቋመው ሲኾንበት ፍርድ እንዳይዛባበት ‹በእንተ ማርያም ፈራጅ› ብለው ይጠይቃል፡፡ ኾኖም ግን በአገራችን የአደባባይ ሰው መኾን የትልቅ ሰውነት መለኪያ ስለኾነ የትኛውም ጠበቃ መረታትን አይፈልግም፤ በዚህ የተነሣ ከሣሽና ተከሣሽ በጥብቅና ችሎታቸው የተደነቁ ጠበቆችን መርጦ መሟገት የተለመደ ነበር፤ በዚህ ችሎታቸው የሚተማመኑ ጠበቆችም ትዕቢታቸው አይጣል ነበር፤ ግን ደግሞ ባልጠበቁት ኹኔታ መዋረድም ያጋጥማል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚኾን ምሳሌ ልጥቀስ፡፡

በዐፄ ምኒልክ ጊዜ ነው፤ ሸንኮራ አካባቢ ትኖር የነበረች አንዲት ሴት ለዓመታት የዘለቀ ክርክር ነበረባት፡፡ ባላንጣዎቿ ታዋቂ ጠበቃ ቀጥረው አዳክመዋታል፤ የቀራትም ዐፄ ምኒልክ ችለት ላይ የሚቀርብ አንድ ቀጠሮ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ጭንቅ ውስጥ እያለች ግን ዘመዶቿ አቶ አቦዬ የሚባሉ ዝነኛ ጠበቃ ባሪ ማርያም በሚባል ቦታ እንዳሉና እሳቸውን ይዞ እንድትቀርብ ይመክሯታል፤ እሷም እንደተባለችው አቦዬን ለምናና በክፍያ ተዋውላ ይዛ ትቀርባለች፡፡ በችሎትም ግራ ቀኝ እንደተቋቋሙ የተቀናቃኞቿ ጠበቃ ‹እንግዲህማ ምን አለ! የባሪው አቦዬ ተመጣ ተረታሁ ማለት ነዋ!› ብሎ በማሽሟጠጥ ተናገር፡፡ ይች ቃል አቦዬ ጆሮ ጥልቅ እንዳለች ‹ዐፄ ምኒልክ ይሙት ረታሁ› ብለው መልስ ሰጡ፡፡ ጠበቃውም ‹የለም አልተረታሁም!› በማለት መለሰ፡፡

አቦዬም እየተቁነጠነጡ፡- ከጠጅ ወዲያ አስካሪ፣

ከራስ ወዲያ መስካሪ፡፡

አንተ በለምለም ምላስህ፣

በሠላሳ ጥርስህ፤

እጌታዬ እምኒልክ ችሎት ላይ ‹የባሪው አቦዬ ተመጣ እንግዲህ ተረታሁ› ብለህ እንዳመንክልኝና ተረተህ መሬቱን ለቀህ እንደምትሄድ ቡሎ ፈረስ እሰጥ› በማለት ውርድ ይነዛሉ፡፡ እማኞችና ሌሎች ተችዎች አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ ዐፄ ምኒልክም ግራ ቀኙን ዐይተውና ኹኔታውን መዝነው ለሴትዬዋ ፈርደውላታል ይባላል (ስለሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ ገጽ 85-88)፡፡

የተጠየቅ ሙግትን በግጥም ከሽኖ ችሎታን በማስመስከርና ወንበሮችን፣ እማኞችንና ታዛቢዎችን በማማለል መርታትም የተለመደ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ ላሙ የጠፋችበት ሰውና ላሚቱን አርዶ በልቷል ተብሎ በመጠርጠር የተከሰሰ ሰው በግጥም መልክ ያደረጉት ሙግት ምን እንደሚመስል እንመልከት፡፡

ከሳሽ፡- ‹ተጠየቅ!›

ተከሳሽ፡- ‹ልጠየቅ!›

ከሳሽ፡- ‹ላሜ ጠፍታብኝ ከደጋ፣

      ስፈልግ መጣሁ በደም ፍለጋ፣

      በፍለጋ ብደርስ ከደጅህ፣

      ሙዳ ሥጋ ይዟል ልጅህ፣

      ስለዚህ ላሜን ትከፍላለህ፡፡›

ተከሳሽ፡- ላምህ ብትጠፋ ከደጋ፣

አንተም ብትመጣ በደም ፍለጋ፣

ከደጀም ብታገኝ ሙዳ ሥጋ፣

ከቤቴ በላይ አለ ተራራ፣

መዘዋወሪያ የጅብ የአሞራ፣

ከቤቴ በላይ ዛፍ አለ

በመንገዱ ጅብ ይሄዳል፣

በዛፉም ላይ አሞራ ያርፋል፤

አሞራና ጅብ ሲናተፉ፣

 ሙዳውን ሥጋ ቢተፉ፣

ነፍስ ያላወቀ ልጅም ያንን ቢያነሳ

      አያስከስሰኝምና ነገርህን አትርሳ፣

      ንግግርህን አንሳ፡፡›ብሎ መልስ ሰጠው፡፡

የክርክሩ መንፈስና አካሄድ የገባቸው ደኛም፡

ለተከሳሹ፡-

ሥጋን ሥጋንና በልተሻል፣

 ክርክርሽ ግን ያዋጣሻል፡፡› ብለው በክርክር ችሎታው ምረውታል ይባላል፡፡ (ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 22-23)

እዚህ ላይ የዳኛው ፍርድ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን እንተወውና የክርክር ችሎታቸው ተደናቂነትና ክብርን የሚያሰጥ እንደነበር፤ እንዲሁም ተማጋቾቹም ወረቀት ሳይዙና ምን ዓይነት ጥያቄ እንደሚጠየቁ መረጃው ሳይኖራቸው በአስደናቂ ፍጥነት በግጥምና በምሳሌ ከሽነው በማቅረብ የመሞገት ክህሎትና ልምድ እንደነበራው መረዳት እንችላለን፡፡

አንዳንድ ጠበቆች ደግሞ ድንገቴና ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ባላንጣቸውን የአደባባይ (የሙግት) ሰው አለመኾኑን በማሳየት ይረታሉ፤ ባይረቱት እንኳን የበላይነታቸውን ያስመሰክራሉ፡፡ ግን ሁልጊዜ አይቀናም፤ በጠየቀው ጥያቄ የሚመታና የሚረታም ይኖራል፡፡ በሚያነሱት የድገቴ ጥያቄና መልስ ውስጥም የዕውቀት ውድድርና አስተውሎት አለበት፡፡ ምሳሌ እንጥቀስ፤ አንድ ጊዜ አንድ ጠበቃ ተከሣሹን በአላዋቂነት አፋጦ መልስ በማሳጣት ለመርታት የሚከተለውን አስቸገሪ ጥያቄ ጠየቀው፡፡

‹የሰማይ ኮከብ ስንት፣

የምድር አንብርት ወዴት?›

ተከሳሹ ደግሞ መልሱን በፍጥነትና በግጥም ወዲያው አቅርቦ አዋቂነቱን ማስመስከር አለበት፡፡ መላሹም ታዲያ፡-

‹‹የሰማይ ኮከብ ስንት› ላልከው

አንድ ቁናን ጤፍ ቆጥረህ ድረስበት›

‹የመሬት እንብርት ወዴት› ላልከው

እነሆ! አንተ የቆምክበት›› በማለት በፍጥነት መልሱን ሰጠው፡፡

የዚህ ዘመን ምሁር ቢኾን ኖሮ ምን ይመልስ ነበር? ማጣቀሻ ሲያገላብጥ በጭንቀት ይቀውስ ነበር፡፡ (ኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕግ፡ ሌባ ሻይ፤ ገጽ 40)

ውርድ በመንዛት የተደበቀ እውነትን በማውጣጣት ከኹሉም የሚደንቅ የሙግት ጥበብ ነበር፡፡ በዚህም ጠበቆቹ በአቀራረብ ችሎታቸው ጥንቁቅና የማይዘላብዱ መኾናቸው ብቻ ሳይኾን እማኞችን ምስክር አድርገው፣ ወንበሮቹን አሳምነው፣ ተዛቢውን አስደንቀው የሚያደርጉት ክርክር ኢትዮጵያዊያን ሙግት በመስማት ጊዜያቸውን ቢያባክኑ አይደንቅም፡፡ እስቲ በክርክር በኩል ያላቸውን ችሎታና የአቀራረብ ፍሰት ጥንቁቅነት ለመታዛብም ኹለት የታወቁ የክርክር ማሳያዎችን እንመልከት፡፡

አንድ ጊዜ ‹ሁለት ሰዎች በርስት ምክንያት ተጣልተው ሲሟገቱ ከኖሩ በኋላ አንደኛው ይረታል፡፡ የተረታው ግን ቂም ይዞ አንድ ቀን በምሽት መንገድ ላይ ጠብቆ ይገድለዋል፡፡ ምንም እንኳን እሱ እንደገደለው ቢታወቅም ሲገድለው ያየ ሰው ባለመኖሩ ጉዳዩን ወደ ዳኛ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡ የሟች ወንድምም በአፈርሳታ (በአውጫጭኝ) ጉዳዩን ለማግኘት ቢጥርም ሳይሳካለት ይቀራል፡፡ ሆኖም የሟቹ ወንድም ዝነኛ ጠበቃ ስለነበር ተጠርጣሪውን ሰው እንደ ምንም ብሎ እዳኛ ጋር በማቅረብ በሙግት እውነትና ሐሰቱን ለማውጣት ቆርጦ ይነሳል፡፡ ተጣርጠሪውም ተከሶ በአፈ ቀላጤ ችሎት ላይ ከቀረበ በኋላ የሟች ወንድም ዳኛውን አስፈቅዶ ሙግቱን በተጠየቅ ሥርዓት ይጀምራል፡፡› ሙሉ ሙግቱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ከሳሽ (የሟች ወንድም) ‹ተጠየቅ›

ተከሳሽ ‹ልጠየቅ›

ከሳሽ ‹አንድ ስጠይቅህ አንዷን፣ ሁለት ስጠይቅህ ሁለቷን መልስ፤ ከዚህ ብታልፍ ማር ያግድህ! ታፍ ታፍህ ማር ይቀዳል›

ተከሳሽ ‹እባክህ ለሱ ግድ የለህም! ብቻ ነገርክን ቀጥል›

ከሳሽ ‹ተጠየቅ!›

ተከሳሽ ‹ልጠየቅ!›

ከሳሽ ‹ሥራት ልክ ነው?›

ተከሳሽ ‹ልክ ነው፡፡›

ከሳሽ ‹ከሥራት ያለፈ ይቀጣል፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ይቀጣል፡፡›

ከሳሽ ‹ሚስት ለባሏ መታዘዝ ይገባታል፡፡›

ተከሳሽ ‹ባልም ሚስቱን ማክበር ያሻዋል፡፡›

ከሳሽ ‹አጣረስክ! እጥብቁ ስለገባ ዋስ በለው!› አለው ለዋስ አጋቹ (ተከሳሹ ያልኾነ መልስ በመመለሱና ነገር በማዛባቱ ነው፤ ምክንያቱም ላለማጣረስ በማር እግዱ ቀድሞ ተስማምቷል፤ ባልም ሚስቱን ማክበር ይገባዋል አይገባውም ሌላ ክርክር ነው)

ተከሳሽ ‹‰ረ ምን ቢያግድ! አላጣረስኩም፡፡›

ከሳሽ ‹እንዳጣረስክ ሰጋር በቅሎ እሰጥ!›

ተከሳሽ ‹ለበቅሎህ አገባ!›

ከዚህ በኋላ እማኞች ‹አጣርሷል› ወይም ‹አላጣረሰም› (ማለት ከሳሽ ለጠየቀው ጥያቄ እቅጩን መልስ ሠጥቷል አልሰጠም) ብለው ይፈርዳሉ፡፡ የተረታውም ወገን መቀመጫውን ይከፍልና ሙግቱን እንደገና ይቀጥላል፡፡

እዚህ ላይ ከሳሽ ሚስት ለባሏ መታዘዝ ተገቢ ስለመኾኑ ለሰነዘረው አስተያየት ተከሳሽ የአዎንታ ወይም የአሉታ መለስ እንደመስጠት ‹ባል ሚስቱን ማበር ያሻዋል› ብሎ መመለሱ ከቀረበው ጥያቄ ጋር የማይጣጣም ስለመኾኑ ነገሩን እንዳጣረሰ ተቆጥሮ ይቀጣበታል፡፡

ከሳሽ ጠይቆ ካበቃ በኋላ ተከሳሽም በተራው ‹ፍጆታ!› (የጥይቁን ተራ ስጠኝ) በማለት የመጠየቅ መብት እንዲሰጠው ያመለክትና ጥይቁን ይጀምራል፡፡

ከሳሽ ‹ፍጆታ!›

ከሳሽ ‹ወስደህ መልስ!›

ተከሳሽ ‹ተጠየቅ!›

ከሳሽ ‹ልጠየቅ›

ተከሳሽ ‹አንድ ስጠይቅህ አንዷን፣ ሁለት ስጠይቅ ሁለቷን፣ ከዚች ዝንፍ ብትል ማር ያግድህ!›

ከሳሽ ‹በጄ› (እሺ)

ተከሳሽ ‹ተጠየቅ!›

ከሳሽ ‹ልጠየቅ!›

ተከሳሽ ‹ሥራት ልክ ነው፡፡›

ከሳሽ ‹ልክ ነው፡፡›

ተከሳሽ ‹ከሥራት ያለፈ ይቀጣል፡፡›

ከሳሽ ‹አዎን ይቀጣል፡፡›

ተከሳሽ ‹ሰውን ያለ ጥፋቱ የወቀሰም የከሰሰም ቅጣት ያሻዋል፡፡›

ከሳሽ ‹አዎን ያሻዋል፡፡›

ተከሳሽ ‹አንተም ያለ ጥፋቴ ከወቀስከኝ፣ ከከሰስኝ ቅጣት ይገባሃል፡፡›

ከሳሽ ‹ያለ ጥፋትህ ስላልከሰስኩህ ቅጣት አይገባኝም፡፡›

ተከሳሽ ‹ያለ ጥፋቴ እንደከሰስከኝና ለዚህም ቅጣት እንዲገባህ ፈረስ እሰጥ!›

አኹንም በዚሁ ቅጥያ ሙግት ላይ ውሳኔ ይሰጥና ወደ ዋናው ጉዳይ ይመለሳሉ፡፡

ከሳሽ ‹ተጠየቅ›

ተከሳሽ ‹ልጠየቅ›

ከሳሽ ‹ሰውን በግፍ የገደለ ወንጀለኛ ነው ይቀጣል፡፡›

 ተከሳሽ ‹አዎን ይቀጣል›

ከሳሽ ‹ባንተና በወንድሜ በአቶ ዘርፉ መካከል የርስት ሙግት ነበር፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ነበር›

ከሳሽ ‹በዚህ የተነሣ ከወንድሜ ጋር ጠበኞች ነበራችሁ፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ነበርን›

ከሳሽ ‹በመጨረሻም አቶ ዘርፉ ረታህ፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ረታኝ›

ከሳሽ ‹ስለረታህ ቂም በቀል ይዘህ ሌሊት እመንገድ ላይ ጠብቀህ የገደልከው አንተ ነህ፡፡›

ተከሳሽ ‹አረ! ባዛኝቷ ምን በወጣኝ እባክህ!›

ከሳሽ ‹ስትገድለው ያዩህ የዓይን ምስክሮች አሉ፡፡›

ተከሳሽ ‹አረ! ማንም የለም!›

ከሳሽ ‹እማኞች ንቁ!› ይላል፡፡

ከሳሽ ይህንን የተናገረው የመጨረሻዋን ቃል ልብ ብለው እንዲያጤኑለት ነው፡፡ ይህንንም በመመርኮዝ እንዲህ ብሎ ውርድ ነዛ፡፡

‹ሰውን በግፍ የገደለ ወንጀለኛ መኾኑን አምነኸል፤

ከወንድሜ ጋር ሙግት እንደነበርህና በመጨረሻም እንደረታህ አምነሃል፤

በዚህም ቂም ‹ወንድሜን ገድለኸዋል› ስትባል አሌ ብትልም፤

‹ስትገድለው ያዩህ ሰዎች አሉ› ብልህ ‹አረ ማንም የለም› ስላልክ ወንድሜን እንደገደልከው እውነቱን አውጥተኸልና በነፍሰ ገዳይነት መቀጣት እንዳለብህ ሰጋር በቆሎ እሰጥ!› አለ፡፡

(ሽበሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ 69-74)

እዚህ ላይ ዳኞች ምንም ይፈረዱ የክርክሩን ፍሰትና ድብቅ ድርጊቶችን የማውጣጣት ስልት ስናይ ምን ያህል ኢትዮጵያውን የዳበረ የሙግት ልምድ እንደነበረን መገንዘብ ያስችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ኹለተኛው ነጥብ ስለ ሴት ተሟጋች ነው፤ ሴቶች በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ወጥተው እንደ ወንዶች እንዲሟገቱ አይበረታቱም ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአደባባይ መከራከር ግን ለሴቶችም እንዳልተከለከለና ‹ሴት በማጀቷ ወንድ በችሎቱ› የተባለውን አባባል የሚያፈርስ እና በችሎታቸውም የተደነቁ ተሟጋች ሴቶች እንደነበሩም ምስክሮች የሚኾኑ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም በዐፄ ምኒልክ ዘመን ወ/ሮ አስካለ ወንድምነህ የተባሉ ጠበቃ ያደረጉትን ሙግት እንመልከት፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡-

‹ወ/ሮዋ ከወንድማቸው ከአቶ ዘለቀ ወንድምነህ ጋር በአንድነት ኾነው አዛዥ ኪዳኔ ተክሉ ይባሉ ከነበሩ ሰው ጋር በረስት ጉዳይ ይሟገቱ ነበር፡፡ አዛዥ ኪዳኔ አቶ ዘለቀን ከእህታቸው ነጥለው በድብቅ ሰለታረቋውና እህታቸውን ስላስከዷቸው፣ በእህትና በወንድም መካከል ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ በቀጠሮው እለትም ሙግቱ ሲካሄድ አቶ ዘለቀ ከእህታቸው ጋር አብረው እንደመቆም ፈንታ ፈንጠር በማለት ቁጭ ብለው ኖሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ወ/ሮ አስካለና አዛዥ ኪዳኔ በችሎት ላይ ጥቂት ከተወዛገቡ በኋላ ሴትዮዋ የዳኞችን ፈቃድ በማግኘት ሙግታቸውን በተጠየቅ ሥርዓት ይቀጥላሉ፡፡

ከሳሽ (ወ/ሮ አስካለ) ‹ተጠየቅ!›

ተከሳሽ (አዛዥ ኪዳኔ) ‹ልጠየቅ!›

ከሳሽ ‹አንድ ስጠይቅህ አንዷን፣ ሁለት ስጠይቅህ ሁለቷን ከዚህ ብታልፍ ትታገዳለህ!›

ተከሳሽ ‹በይ በጄ (እሺ)›

አፄ ምኒሊክ የሥጋ ዘመዶች አሏቸው?›

ተከሳሽ ‹አዎ›

ከሳሽ ‹የተመረጡትን ምኒልክ አስካጂ አስክዷቸው፣ ዘመዶቻቸው ቢክዷቸው፣ ከከሀዲዎቹ አስከጂው ይበልጥ ሊቀጣ ይገባዋል?›

ተከሳሽ ‹አዎ!›

ከሳሽ ‹ወንደሜና እኔ የከሰስንህ አብረን ነበር?›

ተከሳሽ ‹አዎ!›

ከሳሽ ‹እንዳውም ከእሱ ጋር ኩርፍ ነበራሁ?›

ተከሳሽ ‹አዎ!›

ከሳሽ ‹ዛሬ ግን አደባባይ ሲመጣ ነወር ብለኸዋል?›

ተከሳሽ ‹አዎ!›

ከሳሽ ‹እንግዲያው ያስካድከኝ አንተነሃ!›

ተከሳሽ ‹ምን ፍቅር አለኝና? ‹ጎበዝ በአደባባይ አያምባትርም፣ እበርሃም አይለቅም› እንደሚባለው ነወር ብለው የት ተገናኘንና? እኔ አላስካድሁም፡፡›

ከሳሽ ‹የተመረጡትን ምኒልክ ዘመዶቻቸው ቢክዱ፣ ከከጂዎቹ አስካጂው ይበልጥ መቀጣት እንደሚገባው ካወቅህልኝ፣ ከወንድሜ ጋር አብረን እንደከሰስንህና ኩርፍም እንደነበራችሁ ዛሬ ግን ነወር እንዳልከው ካመንከኝ… ‹የበሶው ስልቻ አፉ ተፈትቶ ሰውዬው አፉ ነጥቶ ከተገኘ ባይበላም እንደበላ ይቀጠራል፡፡› እንደሚባለው እስከዛሬ ተኳርፋቸሁ ዛሬ ግን ነወር ካልከው

ሰው ሳይሰማ

ታርቃጭሁ በጨላማ

በእናት በጡት፣

በአባት በአጥንት

የምንገናኘውን ወንድሜን እንዳስካዳኸኝና መቀጣት እንደሚገባህ ንጉሥ ዓይናቸው የሚጥሉባት ለወርቅ መረሻት የሚመኟት ራስ ደጃዝማች የሚደነቁባት፣ የት ተፈጠረች የምትባል በቅሎ እሰጥ!›

ተከሳሽ ‹አገባ!›

በመጨረሻም ከሳሽና ተከሳሽ ከተወዛገቡና እማኞችና ዳኞችም በጉዳዩ ላይ ከተቹበትና ከተወያዩበት በኋላ ለወ/ሮ አስካለ ወንድምነህ ፈረዱ ይባላል፡፡›

(ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 75-78)

ከዚህ በላይ የተመከትናቸው ኹለት ምሳሌዎች ያላቸውን ምክንያታዊነት እና የሙግት ጥበብ ሳያደንቁ ለማለፍ አይቻልም፤ ይህም የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር በኅብረተሰቡ ውስጥ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እየዳበረ እንዲመጣ እንዳደረገ ለመረዳት ያስችላል፡፡ የክርክራቸው ፍሰትም የአጠይቆት ሥነ አመክንዮ (Deductive Logic) መንገድን ይመስላል፡፡ የሚገርመው ግን ይህንን የመሰለ ፍትሐ ነገሥትን እንደ የሕገ መንግሥት ደጀን፣ ምሳለያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችን የሕግ አንቀጾች በማድረግ የምክንያታዊ ሙግትና ልማዳዊ ሕግ የነበረን ሕዝቦች መኾኑ ምንም ሳይመስለን እና ሳናስተውለው የምንኖር መኾናችን ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን አልጠቀስነውም እንጂ የተከራካሪን ማንነት፣ ዘር፣ ችሎታ፣ ቤተሰብ… አንንኳሶ በማዋረድና በዚያ መሠረት ተከራካሪውን አሸማቆ መርታት የተለመደ የሙግት ስልትም ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከዘመናዊ ክርክር አንጻር ሲመዘኑ ብዙ ክርክሮች በሕጸጽ የተሞሉ ነበሩ ለማለትም ያስደፍራል፡፡ ይህ ግን በጥናት የሚጠቅመው ከማይጠቅመው ተለይቶ እየተመረመረ በትችት እየነጠረ ሲወጣ አገራዊ የሙግቱ ጥበብን ለማሳደግ ትልቅ አተዋፅኦ ይኖራዋል እንጂ መልካሙን የሚያጠፋ አይኾንም፡፡ እንዳውም ሰፋ ተደርጎ ከታየ በክርክር የሚፈጸሙ ሕጸጾችን በምሳሌ እያስደገፉ ለማስረዳት ጥሩ ግብዓት የሚኖረው እንደሚኾን ይሰማኛል፡፡

በጠቅላላው ግን የአገራችንን ጥበባትና የመከራከር ባህል ሊቃውንቱ በ‹በልሃ ልበልሃ›፣ በ‹ተጠየቅ ልጠየቅ› እና በቅኔያቸው አዳብረውታል፤ ይህም በባህልነት በማኅበረሰቡ የንግግርና አጨዋወት ልምድ እንዲንፀባረቅ አድርገው ስለሠሩት ነገረ አዋቂነትንና አስተዋይነት የኢትዮጵያዊያን ሀብት ሊኾን ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ በምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮች፣ በሕዝብ ግጥሞች፣ በበላ ልበልሃና በተጠየቅ ልጠየቅ ድርጊቶችና ልምዶች ተንጸባርቆ ይገኛል፡፡ ይኹንና ይህ ጥበብ ሳይመረመርና ሳይበለጽግ እንደዘበት መተውና መዘንጋቱ ይቆጫል፡፡

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply