ንጉሥ አምደጽዮን – ጀግናው ኢትዮጵያዊ

ethiopiankingamdetsion

በመሪራስ በላይ ተጻፈ። ከታላቅ ምስጋና ጋር የአፄ ይኩኖ አምላክ የልጅ ልጅ የአፄ ውድም አርእድ ልጅ አምደጽዮን ስመ መንግሥታቸውን ሣልሣዊ ገብረመስቀል (ንጉሥ ላሊበላ) ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው በአንድ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ስምንት (1298) ዓ.ም. ነገሡ።

የቀደማዊው ምኒልክን (ምንይልክ) ዘርና የነገሥታቱን ታሪክ ለማጥፋት ሮማውያንና አረቦች በሚልኳቸው መልእክተኞቻቸውና ጳጳሳቶች ከአዳም እስከ ምኒልክ የተጻፈው መጽሐፈ ሱባኤ መጽሐፈ አበው ከምኒሊክ እስከ አልአሜዳ ዘመን የተጻፉት መጽሐፍት ተለቅመው ጠፍተው በምትካቸው በአረብኛ ቃል የተጻፉ ተተክተው ሳለ እንዲሁ አይሁዳዊ የሆነቸው የአረቦች ጠላት ዮዲት ተነስታ የአረብኛን መጻሕፍቶችና አዋቂዎችን ስታቃጥል እንዲሁ አብሮ የነበረው በግእዝ የተጻፈው መጻሕፍ ሁሉ የሚበልጠው ተቃጥሎ ነበር።

ስለዚህ አፄ አምደጽዮን በነገሡበት በአንደኛው ዘመነ መንግሥታቸው የነገሥታትን ታሪክና የመንፈሣዊን መጻሕፍት የሚጽፉትንና መተርጎም የሚችሉትን ሊቃውንት በመሪራስ ተድላዓለም በኩል ጥሪ አደረጉ።

ሊቃውንቶችም በአፄ አምደጽዮን ጥሪ መሰረት መጻሕፍቶቻቸውን ይዘው ወደ ተጉለት ተሰበሰቡ። እነዚህም የታሪክና የጽሕፍት ባለቤት የሆኑት ሊቃውንት የመጡበት አገር፦

ቤተማል

ቢተግራማል

ቢተግአ

ቤተዋልሻ (ዋሸራ)

ቤተሃማራ (አማራሳይንት)

ቤተእንዳ (አንዳ ቤት)

ቤተ አባይ (አፈርዋናት)

ቤተ አሹር (ወገራ-ራስዳሽ)

ቤተጉድረት

ቤተ እንዳት

ቤተሳህል (ጣና ሐይቅ)

ቤተ ሃጌ (ሐረርጌ ድዋሮ)

ቤተወንጂ (አሩሲ)

ቤተቂዳር ዛይላ

ቤተ መቅደስ (ሙቃድሾ) ናቸው። ከእነዚህ አገሮች የመጡ ሊቃውንቶች ጸሐፊዎች በዳጎ ሲቀመጡ ቀለም የሚቀምሙና ከፈረስና ከበቅ ብራና ፍቀው የሚያወጡ በሞረት በግራርጌ በአፈርዋናት በአንዳቤት ቀለብና የሚፈልጉት የብራና መፋቂያ መስሪያ ቀርቦላቸው ሥራቸውን ጀመሩ።

የጸሐፊዎች አለቃና መጽሐፍት ተረካቢ መሪራስ ዘጉባኤ ሲሆን አስተናጋጁና ቀለብ ሰፋሪ መሪራስ ተድላ ዓለም ሙሉ ስልጣን ተሰጣቸው። ለየራሳቸው ሦስት መቶ ተላላኪዎች ነበሯቸው።

በዳጎ ለጽሕፈት የተዘጋጁ አምስት መቶ ሊቃውንቶች ነበሩ።

1 ኛ – በዚህን ጊዜ መጽሐፈ ሱባኤ በዳንግዣ ከደንገቦች ስለተገኝ አሥራ ሁለት መጽሐፍቶች ብቻ ተጻፈ የሚገልጽ ነው።

2 ኛ – መጽሐፈ አክሱማይ ሲራክ፡ ከመጽሐፈ ሱባኤ ጋር የተያያዘ ሲሆን እርሱም ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ዮዲት የነገሡትን የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ የያዘና የተጻፈውም በኑብያ ውስጥ በአክሱማይ ሲራክ ተጽፎ በላሊበላ ወደ ኢትዮጵያ ገባ።

3 ኛ – መጽሐፈ ፍጥረት፡ በመላእክትና በሰው ልጆች በእንስሳትም የሚሰለጥኑትን ባህርያትና ጠባያት   የሚገልጽ፡

4 ኛ – መጽሐፈ ኢያስጼድ ሲራክ የጻፈው የድንጋዮች አይነትና በድንጋይ ውስጥ ስለሚገኘው የጥበብ ኃይል፡

5 ኛ – ፍካሬ ክዋክብትና አውደ ነገሥት ስለ ሰው ፀባይና ስለክዋክብት የሚመራ፡

6 ኛ – መጽሐፈ ጥበብ በድንጋይና በእንጨት ቤትም ሆነ ቤተመንግሥት ለመስራት፡

7 ኛ – መጽሐፈ ቀኖና ዘሱባኤ ስለ ሥጋ ስለ ነፍስ ስለመንፈስ አንድነትና ሦስትነት ስለአለው ልዩነት፡

8ኛ – መጽሐፍ መናፍስት በሰው ልጆች ላይ የሚሰለጥኑትንና የሚታዘዙትን ለይቶ የሚያስረዳ፡

9 ኛ – ክብረነገሥትና ብእለነገሥት የተባሉትንና በአንዳንድ ሊቃውንቶች የተደረሱትን የቅኔና የአገባብን ሙያ የሚገልጹ ነበሩ። ሌሎችም መጻሕፍት ቅዱሳን መጻሕፍተ ነቢያት ወሐዋርያት ወመዝሙረ ዳዊት ወመጽሐፍተ ሰሎሞን የተባሉ ሁሉ ለየገዳማቱና ለየአድባራቱ በግእዝ ተጽፈው ተልከዋል። ለጻፉትም የማእረግ ስምና ልዩ ልዩ ሽልማት ሰጥተው ወደየሃገሮቻቸው ከመሕፍቶቻቸው ጋር በሰላም አሰናብተዋቸዋል።

በዚህን ጊዜ ከግብፅ የመጡት ጳጳስ አባ ያዕቆብ፡ በአፄ አምደጽዮን መልካም ተግባር እንዲሁም የኖረውንና የተደበቀውን መጻሕፍት ሁሉ አሰባስቦ በመጻፉ ተናደዱና በየገዳማቱ በየአድባራቱ ለሚኖሩ መነኮሳትና መምህራን ጥሪ አድርገው እኛን ሳያማክር ሳይጥይቅ ወደየገዳማቱ መጻሕፍቶችን ልኮአልና እንዲቃጠሉ ምእመናኑም ለአፄ አምደጽዮን እንዳይገዙ አውግዙ ብለው የኤጲስ ቆጶስነት ማእረግ እየሰጡ ላኩዋቸው። አላማቸውም አፄ አምድጽዮን የአጻፉትን መጻሕፍት እንዳይቀበሉ ለማውገዝ ነበር።

በዚህን ጊዜ የጳጳሱን ፍቅድ ለመሙላት ብለው አባ አኖሪዎስና አባ ፊልጶስ የደብረ ሊባኖስን መነኮሳት አስከትለው ንጉሠ ነገሥቱ አፄ አምደጽዮን ከሚኖሩበት ዳጉ ሂደው በድፍረት ስር ማሽና ቅጠል በጣሽ አስማት ደጋሚ ደብተራ ሰብስበህ እግዚአብሔር የማይወደውን መጽሐፍት አጽፈህ በየገዳማቱ ልከሃልና በቶሎ ሳይራባ እንዲቃጠል አድርግ አሉት።

አፄ አምደጽዮንም እኔ የፃፍኩት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን  የአደረገላቸውን ተአምርና ቃልኪዳን እንዲሁ   በዘመናቸው የሆነውን ሁሉ ለትውልድ ታሪካቸው እንዲተላለፍ እንዳይረሳ አጽፌአለሁ እንጂ እናንተ እነደምትሉትና እንደምታስወሩት አይደለም አላቸው።

አባ አኖሬዎስም ታሪክ ብትፈልግ ከግብጽ ለኛ ብለው የመጡትን ጳጳስ ቃል በሰማህና የሚሉህን ባደረክ ነበር፡ ግን አሁን በራስህ ፍላጎት ያደረከውን ስህተት አምነህ መጽሐፍቱን አሰብስብህ ባታቃጥለው አውግዤሃለሁ አገርም አይገዛልህ ብለው ተናገሩት።

ንጉሥ አምደጽዮንም አባ አኖሪዎስን በገበያ ላይ በጅራፍ እንዲገረፉ አዘዘ። በዚህን ጊዜ የቤተ ክህነቱ ወገን በአባ አኖሬዎስ መገረፍ አጉረመረመ፡ ስሙንም ለማጥፋትና ለማቆሸሽ የአባቱን እቁባት እህቱንም አገባ ከሃዲም ነው ብለው መነኮሳቱ እየፃፉ በየገዳማቱ ላኩ አስወሩበትም፡ ነገር ግን ውግዘቱም ሆነ ሐሰተኛው ወሬ አምደጽዮንን ከክብራቸው ከመንግሥታቸው ሊያወርዳቸው ቀርቶ እንዲያውም በጦርነትም ይሁን በመንፈሳዊ ሥራቸው የእግዚአብሔር መንፈስ አልተለያቸውም፡ ከቀን ወደቀን መንግሥታቸው እየጸና እስከ ውቅያኖስ ባሕር ድረስ ባሉ ጎሣዎች ተከበሩ ታወቁ።

በአፄ አምደጽዮን መንግሥት ላይ የሚያምጽና መንግሥታቸውን የሚገለብጥ ሌላ ሰው እንዲነግሥ ቤተ ክህነቱ ተማከረ፡ በጻጻሱ በአባ ያእቆብ አሳሳቢነት በሚፈለጉበት የቱርክና የግብጽ የየመን ሱልጣኖችና ሸሆች በኢትዮጵያው በክርስቲያኑ መንግሥት ላይ እንዲያምጹና እንዲወጉት ለባላባቶች የጦር መሣርያና የጦር አሰልጣኞች ለወላስማዎች ላኩላቸው። የተላኩትም ከባላባቶች ጋር መጥተው ተቀላቀሉ።

በዚህን ጊዜ በንጉሥ አምደጽዮን በኩል ያለውን ኃይል የሚገልጽ ሰላይ እየላኩ ለይፋቱ ባላባት ለሃቅ አድዲን እንዲያምጽና እንዲዋጋ በአረብኛ ጽፈው ላኩለት። እርሱም ከአዳሉ ባላባት ጋር ተማክሮ ለአምደጽዮን እንደማይገብር አስታወቀ።

እንደዚህም ሆነ፡ ሃቅ አድዲን በወላስማ ላይ የበላይ እንደሆነ ኢትዮጵያንም ጠቅልዬ የክርስቲያን መንግሥት አጥፍቼ የእስላም መንግሥት በምትኩ አስቀምጣለሁ ብሎ ክርስቲያኖችን መግደል ዓብያተ ክርስቲያናትን ማፍረስ ጀመረ። እንዲሁም ንጉሥ ነገሥቱ እንደሚያደርጉት በኢትዮጵያ አገሮች የሚሾሙትን ሱልጣኖችና ኢማሞች ከሊፋዎችንም እየሾመ ይዘጋጅ ጀመር።

አፄ አምደጽዮንም ይህንን ወሬ በሰሙ ጊዜ በ1300 ዓ.ም ከተጉለት ወደ ይፋት ሄደው በወንድሙ በደራደርና በሐቅ አድዲን እየተመራ የሚመጣውን ሠራዊት ድል አድርገው ደራደርን በፈረሱ ላይ እንዳለ በጦር ወግተው ገደሉት። የእስላሞች ጦር መሪ ባላባት ሐቅ አድዲን ወደ ግዞት ወደ ጎጃም ተላከ። በእርሱ ፈንታ የወላስማን ማዕረግ ለወንድሙ ልጅ ለሰበን ሰጥተው የአመጸውን ሽረው ያላደመውን ሹመው በሰላም ወደ ዳጎ ተጉለት ተመለሱ።

አፄ አምደጽዮን በነገሡ በአሥራ ስምንተኛው ዘመነ መንግሥታቸው በወላስማ ስብረዲን የሚባል እስላም ተነሳና ለአምደጽዮን የሚገዛውንና የሚገብረውን ሁሉ አጥፍቶ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥሎ በምትኩ ጃሚዎችንና መስጊዶችን ማሰራት ክርስቲያኖችን መግደል ጀመረ።

አፄ አምደጽዮንም ሊቀ አፍራስ ዘየማን ሊቀ አፍራስ ዘጸጋም ሊቃውንተ ሃራ ዘፄዋ የሆኑትን ሁሉ ጥሪ አድርገው ከሾሙና ከሸለሙ በኋላ ሰብረዲን (ሰበር-አደዲን)ወደሚኖርበት ወደ አዳልና ወደ ሞራ አገር ላኳቸው።

ከተላኩትም የቀኝ ፈረሰኞች የግራ ፈረሰኞች የጨዋ ሠራዊት አለቆች ከሰበር አደዲን ሠራዊት ጋር ገጥመው ድል አድርገው ብዙ ህዝብ ከማረኩና የታሰሩትን ከአስፈቱ በኋላ በመንደሩ ብዙ ወርቅና የዳሉል ሉል ድንጋይ ከአረብ አገር የተላከለት የጦር መስሪያ ሰይፍና ጦር ከሰብር አደዲን ቤት አግኝተው ወሰዱ። ሰብር አደዲን ግን አስቀድሞ ስለሸሸ ሊያገኙት አልቻሉም።

በአፄ አምደጽዮን ላይ ጠላት ሁነው የተነሱት የቤተክህነቱ ባለስልጣናት በየገዳማቱና በየአድባራቱ ህዝቡ አንገዛም እንዲልና እንዲያምፅ ሰብከውት ስለነበር በሰሜን በፀለምት በጠገዴ በወገራ በደንቢያ የተሾሙ ሁሉ አመፁባቸው።

በዚህን ጊዜ አፄ አምደጽዮን ቸንከር ሰቀልት ጎንደር ሃደር አይደር ከረን ኮረም ዳሞት የሚባሉትን የፈረሰኛንና የእግረኛን ወታደሮች በጦር በአጋዙ በጸጋ ክርስቶስ አንተሁን እየተመሩ የአመጻውን አገር ቀጥተው የጠፋውንም አገር እንዲያለሙ ወደ በጌምድር ላኳቸው። እነዚህም የአምደጽዮን ሠራዊት በሄዱበት አገርና በሰፈሩበት አምባ በስማቸው ስሙ ያው ሆነ፤ ይሄውም በቸንከር ሠራዊት ስም ቸንከር በሰቀልት በጎንደር ሠራዊት ስም ሠፈሩ ጎንደር ተባለ፤ ይሄም ሠራዊት እራሱ ለፍቶ ጥሮ በጉልበቱ ስለሚያድር በጎንህ እደር ሲሉ ጎንደር ተባለ።

እንደዚሁ በሳምሮና በሰቆጣ በአዘቦ በሣምሬ ገጽሃን የሚባል ተነሳና ንጉሥ ነኝ ብሎ በአፄ አምደጽዮን መንግሥት ላይ አመጸ። በመልአከ ባህርና በሊቀ ሐመር የሚመራውን ሠራዊት ስሙም የዋግድልናይ የዳህና በለው የሰርቄት ስብስብ ክበብ ማዕከል ተዋዛት ተብሎ የሚጠራውን ሠራዊት ላኩት። እርሱም ከቡግና እስከ ዙላ የአለውን አገር አቅንቶ አፄ አምደጽዮን ለአነገሱት ንጉሥና ለሾሙት ለትግሬ ሹም ለዋግሹም ለደህናሹም እንዲገዛና እንዲያስገብር የአመፀውንም እንዲያጠፋ ላኩት፤ እርሱም እንደተባለው አደረገ።

እንደዚሁ በመልአከ ባህር የሚታዘዝ የኩናማ የብሌን የትግሬ ሠራዊት ከሐማሴን ተነስቶ ጠላትን እያሳደደ የአመነውንም እያስገበረ ገብረመንፈስ ቅዱስና ተክለሃይማኖት በክርስትና ሃይማኖት ወደ አሳመኑት አገር ተላከ። ከዚያም ከሰባት ተከፍሎ ሰባት ቤት ጉራጌ ተብሎ አገር እያለማ ከባላባቱ ጋር በጋብቻ ተቀላቅሎ ኖረ። “ጉራ” ማለት ግራ ሲሆን “ጌ” ደግሞ ሃገር ማለት ነው። ጉራጌ የግራው ሠራዊት አገር ማለት ነው። ይህ ሠራዊት ጥንት ወደመጣበት አገር በሰይፈ አርእድ ጊዜ ተመልሶ ሰልፍ ያሳየበትን አገር ጉራእ ተብሏል። “ሶዶ” ማለት ጠላቱን ሰዶ እራሱ የግራው ሠራዊት ሠፈረበት ማለት ነው።

አፄ አምደጽዮን የሃድያን ነጋሽ፡ የጎጃምን ነጋሽ፡ የቋራን ነገሽ፡ የትግሬን ነጋሽና የእናሪያን ነጋሽ የተባሉትን አምስት ነገሥታት ጥሪ አደረጉ። አሥራ ሁለት እራሶች ማለት መልከኃይል ሲባል የነበረው ራስ የሚባል የስልጣን ስም ተሰጥቶ ነበርና እነዚህ ሁሉ ከያሉበት አምባቸው እንዲመጡ ትዕዛዝ በየአገሩ በየአምባው ተላከ። ሁሉም በአንድ ላይ በደብረ ደጎ ተጉለት ተሰበሰበ። አፄ አምደጽዮን ወደ አዳል አገር ከመዝመታቸው በፊት አስራ ሁለት በሮች በአሉበት በአምባ ጽዮን በተድባበ ማርያም በእየሱስ ክርስቶስ እጅ ለቅዱስ ማርሔር የተሰጠው ሰይፍ አለት የሚሰነጥቅ ድንጋይም የሚከፍል ስለነበርና በክብርም ይኖር ስለነበር የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ስላሳያቸው ልከው አስመጡት። ይህም ሰይፍ ከመምህር ያሬክ በትር ጋር ሲኖር የነካው ሰው ሁሉ ከደዌው ይፈወሳል፡ ወደ ጦርነትም የሚሄድ በሰይፍ ታሽቶ ሲሄድ የጠላት ሰይፍና ጎራዴ ጦርም አይነካውም። ከሁሉም ስለሚጠበቅ ካህናቱን ልከው አስመጡት፡ ከዚያም በክብር ከታቦቱ ጋር በሚሄዱበት በድንኳን እንዲቀመጥ ተደረገ።

አፄ አምደጽዮን ለነገሥታቱና ለራሶች በወርቅና በብር በነሃስ የተጌጡትን ቀስትና ጦር ሰይፍና ጎራዴ ጋሻና የብረት ልብሶች ከሸለሙና ሰራዊቶቻቸውንም ከአስደሰቱ በኋላ የከዳውን አገርና እያደባ ክርስቲያኑን እየገደለ ንብረቱን እየዘረፈ ወደሚሸሽበት የአዳል አገር ለጦርነት ጉዞ አደረጉ።

የአፄ አምደጽዮንና የነገሥታቱ ሠራዊት መምጣታቸውን የሰሙ የአዳል የሞራ የጢቆ የበከላይ የወገር የገለባ አለቆችና ሰዎች ከመቶ ሺህ በላይ ሆነው ሌሊት መጥተው ከበቧቸው።

አፄ አምደጽዮን የጦር መሣሪያቸውን ልብስ ለብሰው ሰይፋቸውን ይዘው ከድንኳናቸው ወጡና በረቅ ከሚባለው ፈረሳቸው ሁነው ገጠሟቸው። ከፊታቸው የሚቆምና የሚመከት ጀግና ጠፋ ከአንድ ሺህ በላይ ሰውም ገደሉ።

እነዚህ የእስላም ሰራዊት አምደ ጽዮንን የሜወጋ ቀስትና ጦር ወይም ሰይፍ እንደማይነካቸው እንደማያርፍባቸው አይተው ተሸንፈው ሸሹ።

እንደዚሁ በሌላ ቀን እያዘናጉ ቢመጡም በአፄ አምደጽዮን ከመውደቅና ከመገደል በቀር በአምደጽዮን በኩል አንድ ሰው እንኳ ገድሎ ሰለባ ማድረግ አልቻሉም።

አፄ አምደጽዮንም በ1316 ዓ.ም ስኔ 25 ቀን ለጦር አለቆችና ለነገሥታቱ እንዲህ ብለው ተናገሩ። ጎጃም ቋራም ደንቢያም ወገራም ዳሞትም ሓድያም ባፎም ድሆኖም ዋግም ሌሎችም ሁላችሁ ስሙኝ፡ እነሆ ሁልጌ ሊወጉን መጥተው ተወግተው ብዙዎችን ስንገድል ትንሽቶችም ትልቆችንም አለቆቻቸውንም ማርከናል ይህንን ሁል ድል ያገኘነው በእኛ ኃይል ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል በልጁም በእየሱስ ክርስቶስ እርዳታ ነው፡ አሁንም እግዚአብሔር ስለእኛ ይዋጋልና እነዚህን ከሐዲዎች አትፍሩ በእግዚአብሔር ጽኑ እንጂ አትጠራጠሩ፡ በሰይፍ ቢመጡባችሁ ሰይፍ አላችሁ፡ በቀስትና በጦር ቢመጡባችሁ እንደዚሁ አላችሁ። እግዚአብሔርም ከእኛ ሠራዊት ቁጥር በላይ ምርኮን ሰጣችሁ፡ ሊወጉን ከመጡት የሚበልጡት ሞቱ እንጂ አልተመለሱም ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ልጅ እየሱስ ክርስቶስን የካዱና በእርሱ ያመኑትን ምእመናን ለመግደልና ለማጥፋት በትምክህት መጥተዋልና ተዋርደው ወደቁ።

እነዚህ አረመኔዎች የሚሉትን ቃል አልሰማችሁምን? ክርስቲያኖች በጦርነት ቢገድሉን በሰማይ መልካቸው ያማረ ቆንጆዎች ሴት ልጆችን መላእክት ይዘው ይቆዩናል፡ ማርና ወተት ወዳለበት ጀነት ያስገቡናል፡ እኛ ደግሞ ክርስቲያኖችን ብንገድልና ብናጠፋ እስከ ሰባት ዘር የሆኑ ልጆቻችን ሁሉ ሳይቀሩ እናጸድቃለን ብለው ነው የመጡና በከንቱ የሚጠፉ ከንቱ ቢሶች ፍጥረቶች ናቸው።

እናንተስ አብና ወልድን መንፈስ ቅዱስም በአንድ የተጠመቃችሁ በደሙ የተቀደሳችሁ ሳላችሁ ለምን ከሃዲዎችን ትፈራላችሁ? አሁንም እውነተኛይቱን ሃይማኖቱን ለማጽናት ለህጋችሁም ተገዢ ለመሆን ክብርን ለመቀዳጀትና አገራችሁን ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በርቱ ሰይፋችሁን ታጠቁ ልባችሁንም አጽኑ ነፍሳችሁንም አታስደንግጡ፡ ይህም ጦርነትና ግድያ አገርን ለመጠበቅ በህጋችን በሃይማኖታችን አይደልም፡ ምክንያቱም እምነታችን በህጋችንን ለመጽናት ለመጠበቅ ነው። የህግን ሥራ ፈጽሞ ማድረግና ሕግን አለመተላለፍ ፍጹምና ብቁነት ነው፡ ነገር ግን የሕግን ሥራ አለመፈጸም ክርስቶስን መቃወም ነው፡ እርሱ ሕግን ፈጽሞአልና። የሕግ መሠረቱ መንግሥታችን ነው የመንግሥታችንም ክብር ሕግ ነው። እንግዲህ በሕግ እምነታችንን እናቆማለን፡ በእምነታችንም ህግአችን እናጸናለን እንጂ አንሽርም።

ዳዊት በእግዚአብሔር ታምኜአለሁ የሰው ልጅ ምን ያደርግልኛል ብዬ አልፈራም እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ ጠላቶቼን እመለከታለሁ እንዳለው እናንተ በእግዚአብሔር ታምናችሁ ጽኑ ደግሞም አህዛብ ሁሉ ከበቡኝ በእግዚአብሔር አሸነፍኳቸው ብሏል።

አሁንም ልባችሁ ወደነበረበት ወደጦር አድርጉት እንጂ ወደኋላ ለመሸሽ አታስቡ፡ ፍርሃትን ከልባችሁ አስወግዱ እኔ ግን አምላኬ በእግዚአብሔር አብ ልጅ በእየሱስ ክርስቶስ ኃይል እነዚህን ከሃዲዎች ሳላጠፋ ክረምት ሆነ በጋ ወደ ከተማዬ ላልመለስ በእግዚአብሔር ስም ምያለሁ ልቤንም በክርስቶስ አጽንቼአለሁ አሉ።

አፄ አምደጽዮንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የእግዚአብሔር ኃይል ከእናንተ ጋር ይሁን፡ ሥልጣኑም በውስጣቸው ይደር፡ ሰይፋችሁም ወደጠላት ልብ ይግባ፡ ጦርና ፍላፃም ወደልባቸው ሥር ይቀርቅር፡ ጎራዴአችሁም የጠላትን አንገት ይምታ፡ ለሃገራችሁ ለእምነታችሁ የጸናችሁትን ሰራዊቱን ሁሉ እግዚአብሔር እስከ ፍጻሜው ድረስ በጋሻው ከልሎ ከጠላት አይንና እጅ ይሰውራችሁ፡ አሸናፊነቱን ይስጣችሁ፡ ድል ለእናንተ ይሁን አሉ።

ሁሉም ሠራዊት እንደቃልህ ከመንፈስህ ጋር ይሁንልን አሜን አሉ። ያም ስፍራ ድል ለናንተ ተባለ። እንዲህም ሆነ ከግንቦት ወር እስከ ሃምሌ ድረስ ጦርነት ሌትም ሆነ ቀን አላቋረጠም ይኽውም አፄ አምደጽዮን እንደሌሎቹ ነገሥታት ሠራዊት ብቻ ልከው አላዋጉም። እራሳቸው በእግዚአብሔር ኃይል ተዋግተው ድል አድርገዋል። ይህም አገር ምስራቁና ምዕራቡ አይታወቅም ውሃውም የፋራ ምንጭ ከጉድጓድ የሚገኝ  ነው፡ ሰዎቹም ፈጣን ጨካኞች ናቸው።

በዚህን ጊዜ እንደነቢይ የሚያከብሩት በጠጉሩ ወገቡን የሚታጠቅ ከባሕር ማዶ የመጣ ስሙ ቃዚ ሳልህ የተባለ ሰው የአዳልን የበከላን የሃገራን የፈደሴን የግዳድን የነጉበን የዙባባን የሃርላን የሆባትን የተርሳን የአይሞን የአልብሮን የዚልአን የእሴትን የደዋሮን ሸሆችና ከሊፋዎች ለጀሃድ ጦርነት ጥሪ አድርጎ ሁሉንም ሰበሰበ።

የመጡት ከሁለት ሺህ መስጊዶች ለጦርነት በይማሞችና በሼሆች የተሰበሰቡ አምስት መቶ ሺህ ከባህር ማዶ የመጡት አንድ ሺህ ነበሩ።

በአፄ አምደጽዮን በኩል ስልሳ ሺህ አራት መቶ ሰራዊት ነበር። እነዚህም የቀኝና የግራ የኋላ ደጀንና የፊት ጦር ሰራዊት ፈረሰኛ እግረኛ ብረት የለበሱ ቀስተኛና ጦረኛ ባለ ሰይፍ ባለ ጎራዴ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ አምደጽዮን እምነትን የጣሉባቸው የሚተማመኑአቸው ነበሩና ለጦርነት ንጉሠ ነገሥቱ ከአሉበት ርቀው ሄዱ።

አፄ አምደጽዮን በወባ በሽታ ታመው በአልጋ ተኝተው ለሰባት ቀን እህል አልበሉም ውሃም አልጠጡም ነበር። በዚህን ጊዜ ምድርን አንበጣ እነደሚሸፍናት ጉምም መሬትን እንደሚያለብስ ሁሉ የእስላሞች ጦር ሰራዊት እየተርመሰመሰ እንደጉዳንዳ እንደ አንበጣ ሆኖ መጣ።

ከአፄ አምደጽዮን ጋር የነበሩት ሠራዊት በሊቀ ንኡሳን የማኑ የሚመሩት ትንሾች ነበሩና ደንግጠው ፈሩ። በዚህን ጊዜ አፄ አምደጽዮን ከመኝታቸው ተነስተው የቀኝና የግራ ጋሻ ጃግሬአችው የጦር ልብሳቸውን እንዲያለብሷቸው አዘዙ ወገባቸው እየተንቀጠቀጠ መቆም አቃታቸውና ወደቁ፡ አይሆንሎትም ቢሏቸውም እኔ እንደፈሪ ወይም እነደሴት ከአልጋ እንደተኛሁ አልሞትም እንደተጋዳይ አርበኛ አሟሟቴን አውቃለሁ አሉና /ከተድባበ ጽዮን/ ከተድባበ ማርያም የመጣውን የማርሄርን ሰይፍ እንዲሰጧቸውና የካህናቱን አዝዙ። ካህናቱም እንደተባሉት ሰይፉን አምጥተው ሰጡአቸው።

ንግስት ዣን መንገሣ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይና ታለቅስ ጀመር። አፄ አምደጽዮንም ወደ ሰማይ እንጋጠው በእጃቸው ሰይፍና ጋሻቸውን ይዘው መሐሪውና ሐያሉ እግዚአብሔር ሆይ ሕዝብህን በኃጢአቱ ብዛት አታጥፋው ለጠላቱም አሳልፈህ አትስጠው በምህርተህ ማረው እንደቸርነትህም ብዛት ኃይልህን ስጠው፡ እኔን ግን ደስ የሚልህን አድርግብኝ ሞቴ ስለህዝብህና ስለ አገልጋዮችህ ይሁንብኝ አሉ። ይህንንም ቃል የተናገሩ አገልጋዮችህ ይሁንብኝ አሉ። ይህንንም ቃል የተናገሩ “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” ብሎ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ሁሉ እንዲሁ አፄ አምደጽዮን ለሕዝባቸው እንጂ ለራሳቸው አልጸለዩም።

በዚህን ጊዜ ጠላቶቻቸው በአራቱ ማእዘን ሆነው ሰይፋቸውን እያብለጨለጩ ቀስታቸውንም ደግነው ነፋስ እንዳናወጠው ባህር ማእበልና በዝናብ ጊዜ እንደሚጮህ ነጎድጓድ ቃላቸውን እየሰሙ መጡባቸው።

አፄ አምደጽዮን በአጠገባቸው ያሉትን ሠራዊት በእግዚአብሔር ታመኑ አይዞአችሁ እነዚህን የእስላም ሰራዊት ከብዛታቸው አይታችሁ አትፍሩ የእግዚአብሔር ኃይል ካልተጨመረበት በስተቀር ብዙ ሠራዊት በብዛቱ ማሸነፍ ትንሽም ሠራዊት በማነሱ ሊሸነፍ አይችልም አሏቸው። ነገር ግን የአፄ አምደጽዮን ሠራዊት ፈርተው ወደ ኋላ ሸሹ።

አፄው ግን ለሚሸሹት እንዲህ አሉ እንደገና ትንሽ ቆማችሁ እንዴት እንደምጋደልና እንደምሞት ተመልከቱ ወይም እግዚአብሔርን በእጄ ላይ ሆኖ የሚሠራውን አስተውላችሁ እዩ አሉ። እነርሱ ግን ሽሽታቸውን ቀጠሉ ወዴት ትሸሻላችሁ የትም ልትሄዱ ልትደብቁ አትችሉም ነገር ግን በእግዚአብሔር ታምናችሁ ታግላችሁም ሙቱ በውርደት ከመሞት እንደጀግኖች አሙዋሙዋት በክብር ሙቱ ብለው በጥቁር አረብ አስፈሬ ከሚባለው ፈረሣቸው ላይ ወጡ፡ ከዚያም የንጉሥ ሣፍስገድን ልጅ ዘነአስፈሬን ንጉሥ ተክሉን ንጉሥ ወናግረአድን ወደ እስላሞች ጦር መካከል እንዲገቡ አዘዙ።

አፄ አምደጽዮን የጠላት ሠራዊት ወደበዛበት በኩል ገብተው ፍላጻውና ጦሩ እንደበረዶ እየወረደባቸው ከመሃል ገብተው የበረሃ ሰው ጥሻውን እንደሚጥስ በቱጊ እንደሚመነጥር አርእድ በሚባለው ሰይፍ ቆራረጡአቸው።

አፄ አምደጽዮን በሄዱበት መሬት የጠላት በድን ሸፍኖት ከበድኑ ላይ በድን ወድቆበት ይታይ ነበር፡ አፄ አምደጽዮን አንድ ግዜ ከፈረስ ላይ ሆነው አንድ ግዜ ከመሬት ሆነው የጠላትን አንገት ሲቀጩትና ሲቆርጡት ፈረሱም ሲከተላቸው ይታይ ነበር።

በዚህን ጊዜ የእስላም ሰራዊት ሽሽት ሲጀምር የጠላትን ወታደሮች ሠራዊት ምርኮና ሰለባ ሴቶቹ ይውሰዱ እናንተ ግን ሸሽታችሁ የነበራችሁ ያልሞቱትን የሸሹትን አባራችሁ ግደሉ አሏቸው። እንደተባሉትም ተከታትለው ብዙ የጠላት ሠራዊት ገደሉ።

ይህን የመሰለ ጦርነት በአለፉት ነገሥታት አልተደረገም። ጦርነቱም ከስድስት ሰዓት እስከ ፀሐይ ግባት ነበረ። ሲዋጉ የዋሉበት እጃቸው በደም ከሰይፉና ከጋሻቸው ጋር ተጣብቆ በግድ ነው ያላቀቁት።

በአፄ አምደጽዮን እጅ የእግዚአብሔር ኃይል ይገለጥ ዘንድ የፄዋ ጦር ሠራዊት በሌለበት በእግዚአብሔር ኃይል ጠላቶቻቸውን በትንሽ ሠራዊት ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተገደሉ።

በአፄው በኩል ፈርሰው ሲሸሹ ሁለት መቶ ሃምሳ ሲሞቱ አንድ ሺህ ሁለት መቶ በአለቆቻቸው የሚመሩ ሰባት መቶ ንጉሠ ነገሥቱን የሚጠብቁ ነበሩ።

አፄ አምደጽዮን በድል አድራጊነት ታቦቱ ወደ አለበት ገብተው ለእግዚአብሔር ምስጋና ተንበርክከው አቀረቡ። ከመሸም በኋላ በሌላ አገር የዋለው ሠራዊት መጣና ትልቅ ደስታ ሆነ፡ ሲነጋም የሞተው በድን እየሸተተ ሰለአስቸገረ አፄ አምደጽዮን ለጨዋ ሠራዊታቸው እንዲህ አሉ፡ እንግዲህ ሳትፈሩ ንገሩኝ ወደፊት እንሂድ ወይስ እንቅር? አንድ ሰው ብቻ በፈቀደው መደረግ የለበትም ማናቸውም ነገር ያለምክር የተደረገ እንደሆነ በፍራቻ የተጀመረ እንደሆነ ይፈርሳል ፍፃሜው አያምርም አሏቸው።

በዚህን ጊዜ ሕዝበ እግዚአብሔር የሚባል ካህን እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔር በትናንትናው ቀን ከጠላት እጅ አድኖሃል የያዝከውም ሰይፍ የሰውን ገላ እንደሳር ሲያጭድ ሲቆራርጥ የጠላትንም ሰይፍና ጦር ሲሰባብር አይተናል ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ሰይፍ ባይሆን ኖሮ ሁላችንም አልቀን ሙተን ነበር፡ አሁንም ጌታዬ ሆይ ስማኝ ትናንትና ያየነው ሕዝብ ከሞተው ያልሞተውና የሸሸው አይን አይዘልቀውምና አሁን ብንመለስና ወደ ሃገራችን ብንሄድ ይሻላል አላቸው።

አፄ አምደጽዮንም ሰማህ ወዳጄ ሆይ ስማኝ ፈርተህ ሌላውን እንዲፈራና እንዲጠራጠር ታደርጋለሁ እግዚአብሔር እንደሆነ ትናንት ተረድቼዋለሁ ዛሬ ግን አልረዳም የሚል አይምሰልህ በፍጹም ልባቸሁ እግዚአብሔርን እመኑ፡ በርትታችሁም ታገሉ አትጠራጠሩም በየጊዜው አባቶቻችንን ለረዳቸው እኛንም ለጠበቀ ለረዳን ለእግዚአብሔር ተገዙ፡ ስሙንም በክብር አንሱ ዘምሩለት፡ ቅኔውንም ተቀኙለት፡ እግዚአብሔር በእኔ ክንድ ላይ ሆኖ በብዛታቸው ተመክተውና ተባብረው የመጡትን ጠላቶቻችንን ከእሬሳ ላይ እሬሳ እንደክምር እስከሚሆኑ ድረስ ገደልኳቸው ሰይፉም ጨርቅን እንደሚቀድ እንጂ የሰውን ገላ እንደሚቆርጥ አይመስለኝም ነበር፡ ይህም የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ የእኔ ክንድ አይደለም። አሁንም እኛ የመጣነው አረመኔን ለማጥፋት በምትካቸው ሰላማዊውን ሰው ለማስቀመጥ እስከሆነ ድረስ በየሃገሩ ሹም ሽር አድርገን ብዙ ሃገር እናቀናለን አሉ። ሠራዊቱም እንስማማለን ትናንትናም በእግዚአብሔር ኃይል ያዳንከን አንተ ዛሬም ሆነ ነገ የምታድነን አንተ፡ በአንተ ልብ በአንተ አሳብ በአንተ ትእዛዝ እንሄዳለን፡ ከአንተ ማንም አይለየን አሏቸው።

ከዚያም ተነስተው ዜባ ወደምትባል አገር ደርሰው ሹም ሽር አደረጉ፡ ከዜባም ተነስተው ተአረርክ ሰፈራቸውን አደረጉ፡ በዚያም ያመጸውን አጥፍተው ያመነውን አስገብረው ወደ ዶቤ ሄዱ፡ ከዶቤም ዘሶይ ከዘሶይ ተለግ ሄደው የተቃጠለውን ቤተክርስቲያን አሰርተው በምርኮ ሰልመው የነበሩትን ሁሉ ወደ ክርስትና እምነት መልሰው ሹም ሽር አድርገው አኳ የሚባለውን ወንዝ ተሻግረው መርመጎብ ከሚባለው አገር ደረሱ። በዚያም ጦርነት አድርገው በጠላት በኩል አምስት ሺህ ሰራዊት ገደሉ።

አፄ አምደጽዮን ነሐሴ 11 ቀን በላስጌ አገር መስጊዱን አፍርሰው የዮሐንስን ቤተክርስቲያን ተከሉ፡ ከዚያም ዝርአት የሚባል ወንዝ ተሻግረው እራቴ ከሚባል አገር ሰፈራቸው አደረጉ።

በዚህን ጊዜ ጆሮአቸውንና ብልታቸውን የተቆረጡና የተሰለቡ ሰዎች ወደ አምደጽዮን ቀርበው ውሃ ልንቀዳ ስንሄድ ድንገት ደርሰው ቆርጠውን ይሄዳሉ በጣም ፈጣኖች ናቸው አሏቸው። ንጉሠ ነገሥቱም ቁስላቸውን አይተው በጣም አዘኑና ለሠራዊታቸው እኔ መለከት እያስነፋሁ ነጋሪት እያስመታሁ ነገ ጠዋት እሄዳለሁ እናንተ ደግሞ ግራና ቀኝ አሸዋውን ለብሳችሁ ተደበቁ ወደ ሰፈር ሲመጡ ግደሉአቸው አሉ። ሠራዊቱ እንደተባሉ አደረጉ። ብዙ የኢሳ ነገዶችን ገደሉ። ከሞቱትም በአግልግላቸው ውስጥ የሰለቡትን ብልትና ጆሮ አገኙ፡ ለአፄ አምደጽዮን አሳዩ።

አፄ አምደጽዮን የጠፋውን አገር እያለሙ ሹም እየሾሙ ብልቃዜር ከሚባል አገር ደረሱ፡ በዚያም የእስላሞችን ሼህ አብደላን አስመጥተው ያሰለምካቸውን ክርስቲያኖች አምጣ ብለው አዘዙት፡ እርሱም እንደተባለው አመጣቸው፡ እነርሱንም ወደ ክርስትና እምነት መልሰው የቀጡትን ቀጥተው የእስላሞችን መሪ ሽረው ለወንድሙ ለነስረዲን ስልጣኑን ሰጡበት። በዚያም የመስቀልን በአል አክብረው የዋሉበትን አገር አመራአምባ – አምባ አማራ አሉት በኋላም ዘመነ ስሙን ካራአማራ የአሉት አገር ነው። እርሱም የአማራ ሰራዊት እንዲቀመጥበት ተደረገ።

አፄ አምደጽዮን ለኢትዮጵያ የባሕር በር ወደሆነው ወደ ዛይላ ሄደው የኢትዮጵያን ውቅያኖስ ባሕርን የግዛቷን ዳርቻ አይተው በባሕር ዳር የሚኖሩት ጎሣዎች ከክርስትና እምነት ወደ እስልምና እምነት ተዛውረው ሃይማኖታቸውን ቀይረው ነበርና ሁሉንም ሰብስበው ከመከሩና ከአስተማሯቸው በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። በዛይላም የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን አስተከሉላቸው።

አፄ አምደጽዮን ከዛይላን የአብርሃ አጽብሃ ተክል የሆነች መቅደስ ማርያም የምትባለውን እስላሞች አፍርሰው መስጊድ ሰርተውባት ነበርና እርሳቸውም እንዲሁ መስጊዱን አፍርሰው የማርያምን ቤተክርስቲያን አሰሩ፡ ስሟንም መቅደስ ተሰየመች። ከዚያም በጎጃም ነጋሽ የሚመራውን የበረንታንና የሸበልን ሰራዊት እንዲሰፍርበትና አገሩን እንዲጠብቅ ሙሉ ዋስትና ሰጡት። በዚህን ጊዜ ዋቢ-ኃላፊ መሆኑን ለመግለጽ የሸበሌዎች ዋቤነት ለማለት ወንዙን ዋቢሸበሌ ብለው ሰየሙት፡ እስከዛሬ ድረስ ስሙ ያው ሆነ።

አፄ አምደጽዮን ከዚያም ወደ ደዋሮ ተመልሰው ከሐረራ በሄዱበት ሠራዊት ስም ደዋሮን /ሐረርጌ/ የተዋጊዎች አገር ለማለት ሐረርጌ አሉት፡ ስሙም ያው ሆነ፡ ቤተሃጌ ሁሉ እንዲሁ ሐረርጌ ተብሏል።

እንደዚህም ሆነ በደዋሮ በአሁኑ ስሙ ሐረርጌ በተባለው አገር በዘመነ ኦሪት ጀምሮ የእግዚአብሔር ስም የሚጠራበትና የሚመሰገንበት ይባላል፡ ይህም ስም የተሰጠው አዳም ሳይባል አድማኤል ኪሩብ በሚባልበት ጊዜ ከኤዶም ወደዚሁ ተራራ ወርዶ ለአራዊትና ለእንስሳት ስማቸውን የሰየማቸው ንጉሣቸው መሆኑን የነበረበት ስፍራ ነው።

ስለዚህ በትንቢተ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል ስለአዳም ይናገራል፦ “በእግዚአብሔር ገነት በኤደን ነበርህ የከበረ እንቁስ ሁሉ ስርጽዮን ቶጻዝዮን/እንቁዮጵያ ግዮን/አልማዝ ቢረሌ መረግጽ ኢያስጲያ ስንፔር በሉር/ድሉል የሚያብረቀርቅ እንቁ ወርቅ ልብስህ ነበር የከበሮህና የእንቢልታህ ስራ በአንተ ዘንድ ነበር በተፈጠርክበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሻ-ህ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላልሰህ ከተፈጠርክ ቀን ጀምሮ በደል እስከሚገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ በንግድህ ብዛት /ከሣጥናኤል ጋር በመነጋገሩ/ ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ ስለዚህ እንደርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ በውበትህ ምክንያት ልብህ ኮርቶአል ከክብርህ የተነሳ ጥበብህን አረከስህ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገስታት ፊት /በልጅ ልጆቹ/ ሰጠሁህ በበደልህ ብዛት /እፀ በለስን  በመብላት/ በንግድህም ኃጢአት/የሰይጣን ቃል በመስማቱ/ መቅደስህን /ሰውነቱን/ አረከስክ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርሷም በልታሃላች በሚያይህም ሁሉ በምድር ላይ አመድ አድርጌአለሁ” [ሕዝቅኤል 28:13-20]

ስለዚህ ይህ ተራራ አዳም በተባለው በኩሩብ ደብረ ኪሩብ ተብሏል። ይህ ደብረ ኪሩብ የሚገኘው በቤተ ኃጌ ደዋሮ ሲሆን ነገዶቹም ሞራራ ሸሆ ኢሳ ሱላጤ ሌሎቹም ይኖሩበታል።

በቀዳማዊ ሚኒልክ ዘመነ መንግሥት ከፈንታሌው ነገድ የቢንያስ ልጅ ማታን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደተራራው ወጥቶ ቤተ እግዚአብሔርን አሰርቶ ከጨረሰ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን የሆነውን ጽላት በታቦተ ሕጉ ውስጥ አስቀምጦ ስሙንም በራእይ እንዳየው ደብረ ኪሩብ አለው። በዚሁ የእግዚአብሔርን ስም የሚያመሰግኑ ካህናትን አስቀመጠበት፡ በኋላ ዘመንም በክርስቶስ ደቀ መዝሙር በበርተሎሚዎስ ተጠምቀው ኑሪዎች ክርስቲያን ሆነው ነበር፡ በኋላ ግን የእስላም እምነት ተከታዮች ወጥተው ከተራራው ክርስቲያኖችን ገደሉአቸውና ጠፍ ሆነ።

ነገር ግን ፩ኛ፤ በአፄ ይኩኖ አምካክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ አባ ተክለጽዮን የሚባሉ መናኝ ባሕታዊ የሚኖሩበትንና የፈራረሰውን ቤተ መቅደስ እንደገና አንጸው ብዙ ባሕታዊዎች በስውር ከኢሣ ተደብቀው ይኖሩበት ነበር። ፪ኛ፤  ከደብረ ኪሩብ ወደ ቤተ ሐጌ በኩል ማለት ወደ ደቡብ ከደብረ ኪሩብ ተነስቶ ወደ ደብረ ወገግ የሚያርፍ ብርሃን ስለሚታይና እረቂቅን መላእክት ስለሚወርዱበት ወገሣ ወገግታ ስለታየበት ደብረ ወገግ ተብሏል። እርሱም የዛሬው አሰቦት ነው። ይህ ተራራ በዘመነ ኦሪትም ለእግዚአብሔር መስዋእት የሚዘጋጅበት ሥፍራ አለው፡ ብዙ መናንያን ባሕታዊያኖች ይኖሩበት ነበር፡ በኋላ ግን እንደ ደብረ ኪሩብ አረመኔዎች ስለአቃጠሉትና ስለአወደሙት ጠፍ ሆኖ ሲኖር የአቡነ ተክለሃይማኖት ደቀ መዝሙር የነበሩ አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ የተባሉ የቡልጋ ሰው ወደተራራው ወጥተው የፈራረሰውን ቤተ መቅደስ እንደገና አድሰው ሰሩ። ገዳሙን እንዳቋቋሙ ብዙ መናንያን መጥተው ይኖሩበት ነበርና በዚህን ጊዜ አፄ አምደ ጽዮን ወደ ተራራው ወጥተው መነኮሳቱን አጽናንተው ቤተከርስቲያኖችን በሰፊው አሰርተው የውኃ ጉድጓድም አስቆፍረው ሄደዋል።

አፄ አምደጽዮን ለነዚህ ገዳሞች ጠላት የሆኑትን አረመኔዎችና አለቃቸውንም ኃይደራን ገድለው በምትኩ ሌሎችን ረሺድንና ፈቂህን ሾመው ሸልመው የሳርካንን ሹም ዮሴፍን አስረውና ይዘው ኤረር ሂዱ፡ በዚያም በምርኮ በተገኘው ወርቅ ለአድአጽዮን ቤተክርስቲያን ማደሻ ሰጡ። አድአጽዮንም መንበረ ወርቅ ተሰራላት፡ ጉልላቱም እንዲሁ በወርቅ ተሰራ።

አፄ አምደጽዮን እግዚአብሔር አምላካቸውን የሚያመሰግኑ ስሙንም የሚቀድሱ ካህናትን እየሾሙ ሸለሙ ነገር ግን በጳጳሱ በአባ ያዕቆብ ስብከት የተወናበዱ ካህናት አሁንም ስም ማጥፋታቸውንና ማደማቸውን ስለሰሙ ብዙ ካህናት ተገርፈዋል ታስረዋልም። ለዚህም ሁሉ የሚያሳድሙትን ጳጳስ አባ ያዕቆብን ወደ ግብጽ መልሰው ላኳቸው።

አፄ አምደጽዮን ካህናቱንና ሊቃውንቱን ጥሪ አድርገው እንግዲህ ለተዋህዶ ኃይማኖታችን መሪና አባት የሚሆን እናንተው ከናንተው መካከል ብጹዕ እና ቅዱስ የሆነውን ምረጡና ሹሙ፡ አይሆንም ካላችሁ ለዘመነ መንግሥቱ ከግብጽ ጳጳስ ማስመጣት ቀርቶ ከዚህ እንኳን መንፈሣዊ ሕይወቱና የአስተዳደጉ ታሪክ እምነቱም ሳይመረመር ዳባ በመልበሱ ቆብ በመድፋቱ የኃይማኖት አባት መሆን አይችልም ብለው ተናገሩ።

በዚህን ጊዜ አፄ አምደጽዮን ሞግዚት ሆና ያሳደገቻቸውና አባታቸው አፄ ውድም አርእድ ፈቅደው ያጋቧቸውን ዳዲን ሲነግሡ ዣን ሞገስ ብለው ሰይመው ነበር፡ በኋላ ዣን ሞገስ መካን በመሆኗ አፄ አምደጽዮን ያለልኝ እንዳይቀሩ ብላ ሌላ ሚስት እንዲያገቡ ስላስገደደቻቸው ወደ ዙላ ሂደው ሳለ ከብሌን ነገድ ድርሂት የምትባል አገቡ፡ ስሟንም ዣን ሳባ ተብላ ተሰይማለች።

ዣን ሳባ የተባለችው ድርሂት በአምደ ጽዮን ፈቃድ የትግሬ ንግሥት ከመበሏ ሌላ በኃማሴን ውስጥ ይባሩአ (ደብሩዋ) የተባለውን ከተማ ቆረቆረች ደባሩአ ወይም ይባሩዋ ከሚባለው ከተማ የሚቀመጥ በሥራዋ መላከ ኃይል በልአከ ባሕር መባሉ ቀርቶ ባሕር ነጋሽ ትግሬ ነጋሽ የቤተ ክህነቱ ደግሞ አቃቤ በአት እንዲባል አድርጋለች።

እንዲሁ በግራ ባልቲሃት በንግሥቲቱ ትእዛዝና በአምደ ጽዮን ፈቅድ ከሰባት ነገዶች የተውጣጣው ሰራዊት በምድረ ከብድ ከሐማሴን ወጥቶ ስለሰፈረና ባለእርስት ስለሆነ ሰባት ቤት ጉራጌ ተብሏል። ይኽውም የግራይቱ ወይም የግራው ሰራዊት አገር ማለት ነው።

አፄ አምደጽዮን በዘመነ መንግሥታቸው ኢትዮጵያን ከባሕር ጠረፍ እስከ ባሕር ጠረፍ እስከ ግብጽ ድረስ ባሉ ነገሥታት ላይ ገዝተዋል። የጠፋውንም አገር አልምተዋል። በዘመናቸው ግዛታቸውን የደፈረ አልነበረም፥ በሰላሳ ዘመነ መንግሥታቸው በተወለዱ በአምሳ ሰባት ዓመታቸው ባልታወቀ ህመም ታመው አረፉ።

ከአፄ አምደጽዮን ቀጥሎ ልጃቸው ንዋየ ክርስቶስ ስመ መንግሥቱ አባቱ አምደጽዮን አክብሮ ይዞት በነበረው ሰይፈ አርእድ ተብሎ በአንድ ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ስምንት /1328/ ዓ.ም. ነገሠ።

ሠይፈአረእድ የተባለበት ምክንያት ይህ ሰይፍ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለማርሄር በግብፅ ምድር ሳለ “ኃይል ሆይ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ” ብሎ የሰጠው በተድባበ ማርያም ይኖር ነበርና የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እንዲታጠቁት ለአምደጽዮን በራእይ ነገራቸው፤ አፄ አምደጽዮንም ባህር ተሻግሮ የመጣን የእስላምን እምነት ተከታይ ሰራዊት ድል አድርገው አጥፍተውበታል። ሰይፉ የአረፈበት አለቱን ይሰነጥቀዋል፤ ድንጋይም ይሁን እንጨት ይበታተናል፤ የሰውን ገላ እንደጨርቅ ይቀደዋል፤ ስለዚህ አረቦች ይህ ሰይፍ ከአላህ የመጣ እንጂ በሰው እጅ የተሠራ አይደለም ይላሉ። ተሹመው በመጡት ጳጳስ ለማሰረቅ ተሞክሮ ሳይሆን ቀረ፤ እንዲሁ አፄ ልብነድንግል ለመታጠቅና ከግራኝ ጋር ለመዋጋት ፈልገው ሲሄዱ እግዚአብሔር ስለአልፈቀደ ከተድባበ ማርያም ወደሌላ ዋሻ ውስጥ በድብቅ እንዲቀመጥ ተደረገ።

ስለዚህ ይህ ሰይፍ ከተድባበ ማርያም ወደሌላ ከመሄዱ በፊት ለንዋየ ክርስቶስ ስለአስታጠቁት ስመ መንግሥቱ ሰይፈ አርእድ ተባለ።

አፄ ሰይፈአርእድ በአምስተኛው ዘመነ መንግሥቱ ወደ እናቱ አገር ሂዶ ገዳሞችን ጎብኝቷል፤ እንዲሁ ከአባ መድኃኒነ እግዚእ ከሚባሉት ባህታዊ ቡራኬ ከተቀበለ በኋላ እግዚአብሔር የሚወደውን ለማድረግ እፈልጋለሁና ይምከሩኝ አላቸው። አባ መድኃኒነ እግዚእም በግብፅ የሚኖሩትን ክርስቲያኖችና ጳጳሳት እስላሞች እያሰቃዩአቸው ነውና ሂደህ የታሠሩትን በሰላም ወይም በጦርነት አስፈታቸው ብለው መርቀው ወደ ግብፅ ላኩት።

አፄ ሰይፈአርእድም ሰራዊቱን ክተት ብሎ ወደ ጉርአ ከሚባለው ላይ ሰልፉን አሳይቶ ወደ ኑብያ ሄደ። በዚህን ጊዜ የኑባው ንጉሥ ስናር የደንካን የዳንቡልንን የገሰናን ጎሣዎች እስከ አለቆቻቸው ሠላሳ ሺህ ቀስተኝ ሠራዊት ይዞ ቆየው።

አፄ ሰይፈአርእድም ለግብጹ ሱልጣን የአሰርካቸውን ክርስቲያኖች ክርስቲያኖች ካልፈታህ የአፈረስከውን ቤተ ክርስቲያን መልሰህ ካልሰራህ አንተንና ሠራዊትህን ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፡ ባህር ማዶ የአለው ጌታህ ሊያድንህ አይችልም የሚል ደብዳቤ ተላከለት።

የግብጹም ሱልጣን የተላከለትን መልስ ሳይሰጥ ለጦርነት ተዘጋጅቶ ወደ አማርና መጣ፤ ከዚያም በአስዋን ከጠዋት እስከማታ ከተዋጉ በኋላ የግብፅ ሰራዊት ድል ሆነና ሸሸ፤ በዚህን ጊዜ ከአምስት ሺህ በላይ የእስላም እምነት ተከታይ ሰራዊት አለቀ፤ በኑብያና በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ሺህ ሞተ።

አፄ ሰይፈአርእድም ካይሮን ለመውረርና የታሰሩትን ለማስፈታት ሲዘጋጅ የግብጽ ከሊፋዎችና ሼሆች አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ለአፄ ሰይፈአርእድ የታሰሩትን ክርስቲያኖችና ጳጳሳቱን እንደሚፈቱና ወደፊት ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ጋር የፍቅርና የሰላም ውል በሊቀ ጳጳሱ በአባ ጴጥሮስ በኩል እንደሚይደርጉ ታስረው የነበሩትን ምክትል ሊቀ ጳጳሱን አባ ማርቆስንና ሌሎችንም መንኮሣት ላኩበት። አፄ ሰይፈአርእድም ከጳጳሱ ቡራኬ ከተቀበለና ከግብጽ ሱልጣኖች ጋር ውል ከተዋዋለ በኋላ ኢትዮጵያ ጳጳስ አልነበራትምና አባ ሰላማ የሚባል መነኩሴ ተሰጥቶ ከምክትል ሊቃነ ጳጳስ ማርቆስ በሰላምና በፍቅር ተሰነባበተ።

ከዚያም ያመጸውን አገር ወግቶ ድል አድርጎ ሹም እየሾመ ለአመነውም አለቃ እየሸለመ በእናሪያ ከፋ አድርጎ በሰላም ተጉለት ገባ።

አፄ ሰይፈአርእድ የተባለው ነዋየ ክርስቶስ በ፪፰ ዘመነ መንግሥቱ በኢትዮጵያ አገርየተቅማጥ በሽታ ገብቶ ብዙ ሕዝብ ከጨረሰ በኋላ መጨረሻ እራሱ ታሞ ሞተ።

አፄ ውድም ፍሬ   (ንዋየ ማርያም)

ከንዋየ ክርስቶስ (አፄ ሰይፈአርእድ) ቀጥሎ በፈንታው ልጁ ነዋየ ማርያም ስመ መንግሥቱ ውድም ፍሬ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ /በ1356/ ዓ.ም. ነገሠ።

በአፄ ውድም ፍሬ ዘመነ መንግሥት በመላ ኢትዮጵያ እርሃብና በሽታ ሆኖ ስለነበር ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የሚዘዋወር ሰው አልነበረም። በዚህን ጊዜ የወላስማን መንበር ይዤ የክርስቲያኑን መንግሥት አጥፍቼ በሸሪያ ሕግ የእስላም መንግሥት አቋቁማለሁ ብሎ ሃቅ አድዲን አህመድ ለጦርነት ተነሳ፤ መጀመሪያ የይፋቱን ገዢ አጎቱን አቦበከር አሊን ገደለ፤ ከዚያም ተዘጋጅቶ መምጣቱን የሰማ አፄ ውድም ፍሬ የተባለው ንዋየ ማርያም ተዋግቶ ገደለው፡ ሃቅ አድዲም ከሞተ በኋላ ለዘጠኝ ዓመት ያህል አገሩ ሰላም ሆነ።

እንደዚህም ሆነ፡ እንደ ግብፃውያን ዳግማዊ ሰላማ እንደ ኢትዮጵያውያን ሳልሳዊ ሰላማ ማለት ከሣቴ ብርሃን የተባሉትን ሰላማን ግብፃውያን ከእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ በጊዜው ከነበሩት ከአትናትዮስ የጵጵስና ስልጣን እንዳልተሰጣቸው ስለሚያምኑና ስለፃፉ ነው፤ ነገር ግን ከሣቴ ብርሃን ሰላማ በኋላ ማቴዎስ የሚባለውን በአፄ ዋዜብ ዘመነ መንግሥት ሊቀ ጳጳሱ ቄርሎስ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ስም አዲሱ ሰላማ ብሎ ሹሞ ልኮት ነበር፤ እርሱንም ኢትዮጵያውያን ነዑስ ሰላማ ብለውታል፤ የኢትዮጵያን የቀደምት መጽሐፍትን ያስጠፋና በምትኩ የአረብኛን መጽሐፍት ያበዛና ያስተማረ ነበረ።

ይህ ግብጻውያን ዳግማዊ ሰላማ ያሉት ጳጳስ በንዑስ ሰላማ የተጀመረውን የመጽሐፍት ትርጉም፡ ማለት በእስክንድራውያን መጽሐፍት ከአረብኛ ብቻ እንደተቀዱ የሚያስተምርና በአፄ አምደጽዮን ዘመነ መንግሥት የተጻፉትን መጽሐፍት መነኮሳትና ቀሳውስቱ እንዲያነቧቸው ያደረገ ነው።

ስለዚህ ስሙን ካልእ ሰላማ ወይም ዳግማዊ ሰላማ ተብሎ ተሰይሟል። እርሱም ለአርባ ዓመት ያህል የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መርቷል፤ ነገር ግን በአባ ሰላማ ሰላማ ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት የአገር ድንበር መጠበቅ ቀርቶ ለራሳቸው እንኳን ስማቸውን የሚያስጠራ ከተማ አልቆረቆሩም። ከእነርሱም መካከል ስማቸው የታወቀው አፄ ዘረያእቆብ ደብረ ብርሃንን ቢቆረቁሩም በደራሲነታቸውና የደረሷቸው መጽሐፍት እስከዛሬ ድረስ በየአድባራቱ ስለሚገኙ ነው እንጂ አባ ሰላማ የእስላም እምነትን የሚከተሉትን ወገኖች ሲረዳና ሲመክር የነበረ በኋላም ጥላቻውና ጠቡ እያየለ ሄዶ ግራኝ መሐመድን ያስነሳ ነው።

እነዚህን በመሰሉ ጳጳሳት ከይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ልብነ ድንግል የነበሩ ነገሥታት ለአገራቸው እንደ አክሱማይ የአክሱምን ሐውልት እንደ ቅዱስ ላሊበላ ከአንድ ወጥ ድንጋይ አለት የጠረቡ አብያተ ክርስቲያናት ሳይሰሩ አልፈዋል።

አፄ ዳዊት   (ንጉሥ በቃል)

አፄ ውድም ፍሬ የተባለው ነዋየ ማርያም በነገሠ በአስረኛው ዘመነ መንግሥቱ በተቅማጥ በሽታ ታሞ ስለሞተ ወንድሙ ዳዊት የተባለው ይበቃል ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ በ1366 ዓ.ም. ነገሠ።

በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ሣልስ ሠላማ ወይም ካልዕ ሠላማ የተባለው ጳጳስ በዘመነ ጵጵስናው ኢትዮጵያ ለግብጽ ሙሉ በሙሉ የኃይማኖት ጥገኛና በእስክንድርያ ስር ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ውል እንዲዋዋሉና አፄ ዳዊትን ደህና አድርጎ በመስበኩና በማሳመኑ ግብራቸውንም ገጸ በረከታቸውንም እንዲያቀርቡ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ምእመናን በዘመነ ኦሪት ከቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ በሌዋውያን ካህናት አማካኝነት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉትን አምልኮተ እግዚአብሔር ሥርአትንና ትእዛዛቶችን በሚፈጽሙበት ጊዜ ለማስተው የተለያዩ ጽሁፎችና ስብከቶች አዘጋጅቶ ነበር ሳይሆን ቀረ።

በሳልስ ሠላማ አስፈላጊ እንዳልሆነ ከተሰበኩት መካከል ጥቂቶች ለአብርሃም የታዘዘውን ግዝራት በሙሴ ሕግ የተጻፈውን የመብል ስርአት የእግዚአብሔር ቃላት የተጻፈባቸውን ጽላቶችና ታቦተ ሕጉት በቅዱስተ ቅድሳት መቅደስ ውስጥ ማስቀመጥ በአዲስ ኪዳን ስለተሻረ አያስፈልጉም እያለ አስተምሮአል ጽፎአል፤ ነገር ግን በእየሱስ ክርስቶስ በባለቤቱ ቃል “እኔ ሕግና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም” ባለው መሠረት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት የብሉይ ኪዳንና የአዲስን ኪዳን በተዋህዶ አዋህደው አጽንተው ኑረዋል።

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

  1. “A nation is a society united by a delusion about its history and common hatred to its neighbors.” ብሎ ነበር
    ሾፐንአወር

  2. “A nation is a society united by a delusion about its history and common hatred to its neighbors.” ብሎ ነበር
    ሾፐንአወር

Leave a Reply