አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለ ፊደል…

የተላከ ከግስ ከመዝገበ ቃል፣

ትርጓሜ አፈታት ሐተታ ፊደል፣

ይድረስ ከወዳጀ ከሕፃናት ልብ፣

ከግእዝ ሰራዊት ካማርኛ ሕዝብ፣

ከናቴም ከጦቢያው ካፍሪካ ባላልጋ፣

እጆቿን ወደ እግዜር ከምትዘረጋ፡፡

ሰላምታ አቀርባለሁ ለፊደል ጸሐፍት፣

ላተሞች ሳይቀር እጅ በመንሳት፡፡

ስለተጠማችኹ የፊደልን ዜና፣

ከሥሩ ከምንጩ ላመጣው ነውና፤

ምናልባት ስትቀምሱት ስታጣጥሙት፣

ጠላ ነው ብላችሁ ስም እንዳትሰጡት፡፡

ጥሩን ቃል ውሃ ጠላ ነው ብትሉ፣

ይታዘባችኋል የሚቀምሰው ኹሉ፡፡

እነ ምን አለበት እነ ኹሉ ቀኙ፣

በትግረኛ መንፈስ ፊደልን ሲቃኙ፣

ከግእዝ ለይተን ዐማርኛን ኹሉ፣

ባ፩ ‹አ› ባ፩ ‹ሀ› (ሰ፣ጸ) እንጣፍ የሚሉ፣

አላወቁም ይኾን ቋንቋ እንዲበላሽ፣

ንባቡም ምሥጢሩም እንዲኾን ብላሽ፡፡

እንደነሶምሶም ዐይኑ ከወጣማ፣

ጥፈቱም ቋንቋውም ይኾናል ጨለማ፡፡

ዐወቀች፣ ዐወቀች፣ዐወቀች ቢሏት፣

መጣፏን ዐጠበች የሚሉት ተረት፣

ላየው ላስተዋለው ላይናማ ደብተራ፣

ሠምና ወርቅ ነው፣ ከዚህ ምኞት ጋራ፡፡

የፊደልን ገላ ደፍሮ ለመቁረጥ፣

ሐኪም መኾን ያሻል በአፍአ በውስጥ፣

አፍአው ዐማርኛ፣ ውስጡም ግእዝ ነው፣

ትምርቱ እንደ ገደል ያልተደፈረው፡፡

ለቋንቋ በሽታ ለጥፈት ሕማም፣

ከትምርት በቀር መድኃኒት የለም፡፡

እንደምን ይቻላል በቀንጃ ፊደል፣

የቋንቋውን ሞክሼ ማወቅ መነጠል፡፡

ጥንቱን ፊደልችን ሴማዊ በገና፣

ኹለት ኹለት ኾኖ ለምን ተሠረና፡፡

ዐማርኛችንስ በጥፈት ጎዳና፣

ካባቱ ከግእዝ መቼ ይለይና፡፡

የትምርቱስ ችጋር የዕውቀቱ ቀጠና፣

ፊደል በማሳነስ መቼ ይለቅና፡፡

በሴማያን ዘንድ በያፌት ልጆች፣

ይህ ነገር ቢሰማ ያሰኛል ሞኞች፡፡

(መዝገበ-ፊደል፤ ገጽ 28-32)

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

Please follow and like us:
error

Leave a Reply