አበሳ መምህር

ብዙውን ጊዜ ስለመምህር  ሲነሳ የሚጠቀሰው

“አዬ የመምህር ያለበት አባዜ፣

አስተዋይ ተማሪ ባጋጠመው ጊዜ”

የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም ነው፡፡ እኔን  ያጋጠመኝ ግን ሌላ አበሳ ነው፡፡ እስቲ ለማሳያ እንዲኾነኝ በፊዚክስ ትምህርት ተመርቄ ማስተማር የጀመርኩበትን የመጀመሪያዋን ክፍለ ጊዜ ኹኔታ ብቻ ልጥቀስ፡፡

ገና ክፍል ውስጥ ስገባ ጨነቀኝ ቢኾንም እንደምንም ራሴን አረጋግቼ የዕወቁኝ ሰላምታ “Good Morning!” ማለት፡፡

መልስ ታዲያ ምን ኾነ “ከጉድ ያወጣን!”

እኔም ገና በመጀመሪያ ቀን ክፉ አልናገርም በማለት ችዬ ዝም አልኩኝ፡፡ ባይኾን ትምህርት ከመጀመሬ በፊት አንዳንድ የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን ላሳውቃቸው “Abcent is not allowed” ብዬ ጻፍኩኝ፡፡

ወዲያው አንዱ ተማሪ እጁን አውጥቶ “ቲቸር!” አለኝ

“አቤት!”

“ሥዕል ነው ጽሑፍ?”

እርር! ነው ያልኩት እርር! “ጽሑፌ ለእኔ ይነበበኛል እንዴት ሥዕል ያደርገዋል” ብዬ፡፡ ኾኖም መቼስ ምን አደርጋለሁ ስጠየቅ መመለስ አለብኝ እንጂ በማለት “ኧረ! ጽሑፍ ነው “ማንም ተማሪ እንዳይቀር ለማለት ነው፡፡” አልኩኝ፡፡

“እሺ! ጽሑፍ ከኾነ በአማርኛ ነው የተጻፈው በእንግሊዘኛ?” ብሎኝ ቁጭ!

“ኧረ! በእንግሊዘኛ ነው!”

“እሺ! እስፔሊንጉን ንገሪን የመጀመሪያው ምንድ ነው?”

“A”

“ቀጥሎስ”

“B”

“ከዚያስ?”

“C”  ኾኖም “ስፔሊንጉን”ን መሳሳቴን አወቅኩ፡፡

ነገር ግን በዚህ ጊዜ ከጎኑ የተቀመጠው ልጅ እጁን አውጥቶ “በቃ! በቃ! ቲቸር እያንዳንዱን ስፔሊንግ በመዘርዘር ከምትለፊ ከ”A” እስለ “Z” በራሳችን እንጻፍ?” አለኝ፡፡

በዚህም ቢኾን እርር! ነው ያልኩት እርር! “እኔ የ10ኛ ክፍል የፊዚክስ መምህርት እንጂ የመዋዕለ ሕጻናት  A, B, C, D አስቆጣሪ አደረገኝ እንዴ?” ብዬ፡፡ ነገር ግን ምን አደርጋለሁ መልስ ከመስጠት ውጭ! “የተጻፈው A, B,C, D ሳይኾን ” “Absent is not allowed” የሚል ነው አልኩት እስፔሊንጉንም አስተካክዬ፡፡ እነሱም እግዜር ይስጣቸው ይኹን! ይኹን! ብለው ተስማማን፡፡

ከዚያም ያንን አጥፍቼ የእለቱን ትምህርት መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ይኹንና ወሬያቸው አላጽፍ አለኝ፡፡ በተለይም ከኋላ ጥግ ከዳርና ዳር አካባቢ ጨዋታው ደራ፡፡ ከቀኝ ጥግ በኩልም አንድ ተማሪ “ተቀበል!” አለ፡፡

“እሺ! ጀምር” አለው ከግራ ጥግ በኩል የተቀመጠ ተማሪ፡፡ እኔም “ምንድነው?” ብዬ ዘወር ስል ተቀባዩ ተማሪ እየተዘጋጀ “ቆይ! አንዴ ቲቸር!” አለኝ፡፡

“ና ውጣ ና ውረድ ሲል እየሰማነው” አቀባዩ

“ና ውጣ ና ውረድ ሲል እየሰማነው” ተቀባዩ፡- በዜማ

“ወደ ላይ ወደ ታች አርሶት አገኘነው በለውማ!”

“ወደ ላይ ወደታች አርሶት አገኘነው፡፡”

ነገሩ ገባኝ፤ ቢገባኝስ ምን አደርጋለሁ እርር! ድብን ከማለት ውጭ! ጸሑፌ መስመሩን ስቶ ወደ ታች መውረዱን መንቀፋቸው ነውና፡፡ በዚህም ክፍሉ በሣቅና በጭብጨባ ቀውጢ ኾነ፡፡ እኔማ ምን እላለሁ? አፍሬና ደንግጬ ዝም ነው እንጂ! ይባስ ብሎ ሌላ ጉድ አጋጠመኝ የተወሰኑት እየሣቁ በመኸከለኛው እረድፍ ከኋላ ወንበር የተቀመጡት ሴትና ወንድ ተማሪዎች ጨዋታ ጀምረዋል፡- የሴትና የወንድ የከንፈር ጨዋታ! የሚገርመው ደግሞ ፊት ለፊታቸው ተገትሬ እንደፊልም ቀራጭ ቆጠሩኝ መሰለኝ ወይ እፍር! ወይ ድንግጥ!

ቢቸግረኝ እኔ አፍሬ ፊቴን ወደ ብላክቦርዱ አዞርኩኝ፡፡ ግን ደግሞ የክፍሉን ሥነ-ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነትም አለብኝ፡፡ ስለዚህ ኮስተር ብዬ ወደ ተማሪዎቹ ዞርኩኝ፡፡ ሁለቱ ልጆች ጨዋታቸውን አድርተውታል፡፡ የተጋባባቸውም ጀማምረዋል፡፡ ገርሞኝ ዝም ብዬ እመለከታቸው ጀመር፡፡ እነሱ ግን “ማፈርና መደንገጥ ድሮ ቀረ” ያሉ ይመስላሉ፡፡

ይባስ ብሎ የጀመረው ልጅ “ቲቸር ምን ያስፈጥጥሻል ከፈለግሽ አንቺም ከአንዱ ጋር ተጫወቺ ወይም ዘወር በይልን ሙዳችንን አታጥፊው” ሲለኝ ድንግጥ ነው ያልኩት ድንግጥ! ብልስ ምን አመጣለሁ አልመታው ቢያንስ ይበልጠኛል፡፡ እንዲሁም የተማሪን ዝንብ “እሽ!” ያለ መምህር ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ ውልቅ፡- ልብሱን የነካ ወደ እስር ቤት፤ አካሉን ያቆሰለ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ….” የሚል ማስጠንቀቂያ አለ ሲባል ስለሰማሁ ችዬ ዝም!

ግን ደግሞ የክፍሉን ሥነ-ሥርዓት የመቆጣጠር ኃላፊነቴንም መወጣት አለብኝ፡፡ ባይኾን እስቲ ከሰሙኝ ልምከራቸው በማለት በጥያቄ መልክ “ይህ ዘመን ጥሩ እንዳልኾነ ታውቃላችሁ አይደል? ” ማለት፡፡

“በትክክል እንጂ “HIV/AIDS ወጣቱን እየቀጨው ይገኛል” የሚለውን ስብከት ልትነግሪን አይደል? ” አለኝ አንዱ ተማሪ እጎኑ ከተቀመጠችው ተማሪ እንብርት በኩል የሰደደውን እጁን ለመሰብሰብ እየሞከረ፡፡

“እሺ ሌላው ኹሉ ይቅርና  HIV/AIDS በምን በምን እንደሚተላለፍ ታውቃላችሁ?” አልኩኝ እኔን እንኳን ባያፍሩና ባይፈሩ አጅሬን እንዲጠነቀቁ ልመክራቸው፡፡

ለካ ልጅቱ ተናዳ ኖሮ “እስከ ዛሬ ድረስ ” HIV/AIDS መተላለፉን የማውቀው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ነው፡፡ እሱም ስልችት ብሎኛል፡፡” አለችኛ! በዚህም መምህር የኾንኩበትን ቀን ብቻ ሳይኾን የተወለድኩበትንም ቀን ልረግም ፈልጌ ነበር፡፡ ግን ባልወለድና መምህር ባልኾን መቼ ይህንን ጉድ እሰማና ዐይ ነበር ብዬ ቻል!

መቼስ ምን አደርጋለሁ ቢቸግረኝ ሣቅ ብዬ ወደ እነሱ በመመልከት ሥነ-ልቦናቸውን ለመማረክ እየሞከርኩኝ “እሺ!” አኹን ወደ ዋናው ትምህርታችን እንመለስ!” አልኩኝ፡፡

ኾኖም ሣቅ ብዬ ወደ ተማሪዎቹ መመልከት ሳበዛ ነው መሰለኝ ከፊት ለፊት ብቻውን የተቀመጠው ደህና የሚመስል ልጅ “ይመችሽ! ክፍሉን እኮ ፍቅር በፍቅር አደረግሽው”  ብሎ በዓይኑ አይመታኝም! “ወከክ!” ነው ያልኩት ወከክ!፡፡ ከመደንገጥ ሌላ ምን አደርጋለሁ? እንዳው ድንግጥ ነው እንጂ ዝም ብሎ ድንግጥ!

ይኹንና እንደምንም ድንጋጤዬን በመቋቋም “ከቻልኩ እስቲ ልምከራቸው”  ብዬ “አረ ተዉ እባካችሁ የድሮ ተማሪ እኮ እንዲህ አልነበረም፡፡ መምህሩን ያከብራል፡፡ ነውርም አይሠራም፡፡” ማለት፡- ታሪክ ልጠቅስ ፈልጌ፡፡

“አዬ!” አለኝ የዘንዶ ምስል በዩኒፎርሙ ላይ የሣለው “ድሮ ባህዮቹ ዘመን ነው? በዚያን ጊዜ ‹ተማሪ ለመምህሩ ባሪያው ነበር› ሲሉ ሰምተናል፡፡ አኹን ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ መምህሩ እንቢ ካለ ያው ነው፡፡” ብሎ ቀበቶው ውስጥ የሰካትን ሴንጢ አያሳየኝም! የምገባበት ጠፋኝ፡፡ ምን ላድርግ ክፍሉን ትቼ እንዳልወጣ ክፍለ ጊዜው ገና አላለቀም፡፡ ፍርሃቴ  በጥፍ ቢጨምርም ችዬ ዝም!

“ቲቸር ምነው ፊትሽ ከቾኩ ጋር ተመሳሰለ? ” አለኝ ሰንጢ ከያዘው ልጅ ጎን የ2PAC ቲሸርትን ለብሶ የተቀመጠው ልጅ ፊቴ ሲነጣ አይቶ ፍርሃቴን አውቆብኝ ነው መሰል፡፡

ሱሪው ላይ የጊንጥ ምስል የሳለው ልጅ ደግሞ እግሮቹን አነባብሮ ከዘረጋበት ዴስክ ላይ ሰበሰበና “ይህ ዴስክ እንኳን ሲመቱን ይናገራል አንቺን ምን ይዘጋሻል?” ብሎኝ ሲነሳ ተደወለ፡፡ ልጁም ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ሌሎችም ተከትለውት ሲወጡ ገርሞኝ፡- ‹አዬ! የመምህር ያለበት አበሳ› አልኩኝ፡፡

“አዬ! የመምህር ያለበት አበሳ

ሆ!ሆ!

ይቅር አይነሳ ይቅር አይነሳ

ሆ!ሆ!

ይቅር አይነሳ ይቅር አይነሳ

ሆ!ሆ!… ”

እያሉ ዳንስና ጭፈራውን አቀለጡት፡፡

መቼስ ምን አደርጋለሁ ቀስ ብዬ ሽልክ ብዬ ወጣኋ!!!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply