አድዋ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?

268135_10200223072073445_1761812899_n‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ፡፡›

የ117ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ሳስብ ባለፈው ዓመት በ116ኛው ዓመት በዓል ዙሪያ ‹የአድዋ ድል ምናችን ነው?› የሚል ዓይነት ክርክር ተነስቶ ዓይቼ ስለነበር ያ መነሻ ሆኖኝ ክርክሬን በጥቅል መልክ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለማድረግ ፈለግሁ፡፡ ሆኖም የሙግቴ አካሔድ አቋሞችን በመገምገም ዙሪያ እንጂ ማስረጃዎችን በማንጠርና በመሰግሰግ ላይ ያተኮረ አይደለም፤ ስለዚህ አንባቢዎቼም በዚህ ዕይታ ቢረዱልኝ ጥሩ መግባባት ይኖረናል የሚል ግምት አለኝ፡፡

እንደኔ አረዳድ የአድዋ ድል ለነፃነት መስዋዕት የተከፈለበት የታሪካችን የማዕዘን ድንጋይ ስለሆነ ልዩ ክብር ይገበዋል፡፡ አድዋ በታሪኩ ብዙ የሆነ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የኩራት መንፈስ የተመዘገበበት ታሪክን የያዘ የጋራ መግባቢያ መድረክ ነው፡፡ እንኳን ሌላ የጥንት ታሪካችን እንዲታወስ ሁሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ከሆነ በአድዋ ጦርነት ዙሪያ የሚነሱ የክርክር አቋሞችና ጥያቄዎች ይህንን መንፈስ እንዳይሸረሽሩት መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ላድዋ ድል ልዩ ክብር መስጠት እነኳን ለኢትዮጵያውያን ለሌሎች አፍሪካዊያን ያስፈልጋል ባይ ነኝ በግሌ፡፡

እንዳው ይሁን እስቲ ብለን ብንከራከር እንኳን መከራከሪያዎቻችን ከማወናበድ ያለፈ አሳማኝነት የሚኖራቸው አይመስሉም፡፡ ለማንኛውም በአድዋ ጉዳይ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ መከራከሪያዎችን በአራት መደቦች ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ማለትም በአቋም ደረጃ፡-

1ኛ. በጦርነቱ መካሔድ ላይ ባለመስማማት መከራከር

2ኛ. በጦርነቱ ሳይሆን በውጤቱ ላይ ባለመስማማት መከራከር

3ኛ. ጦርነቱንም ሆነ በጦርነቱ የተገኘውን ውጤት በመቀበል፤ የድሉ ታሪክ ለሌላ ጥቅም ውሏል ብሎ መከራከር

4ኛ. ከአድዋ ጦርነት ድል ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር አልነበረም፤ ይልቁንስ ትልቅ ፋይዳ አስገኝቶልናል ብሎ መሟገት

እንደ እኔ ግንዛቤ በአድዋ ጉዳይ የተነሣ የትኛውም ክርክር ከእነዚህ መከራከሪያ ጭብጦች ውጭ ሊወጣ ዐይችልም፡፡ ይህ ከሆነም የትኛው የመከራከሪያ አቋም ትክክል እንደሆነ በተጠየቅ እየቃኙ መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡ ከመጀመሪያው እንነሣ፡፡

  1. በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን መውጋታችን ስህተት ነው

ይህን አቋም ይዞ የሚከራከር ሰው በጦርነቱ ውጤት መስማማት አይችልም፡፡ (መንስኤውን በማንሳት መከራከር አስፈላጊ ስላሆነ እንለፈው፡፡) የዚህ አቋም መከራከሪያ ‹ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር ሆና ከመኖሯ ይልቅ ቅኝ ግዛት ተገዝታ ቢሆን ይሻል ነበር› የሚል አንድምታን ያሰማል፡፡ ኢትዮጵያዊ አይደለም አፍሪካዊ ሆኖም ቢሆን ይህንን አቋም በመያዝ የሚከራከር ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ‹ጦርነቱ ቅኝ ግዛት ይዘን እንግዛችሁ› በሚሉ ጉልበታም ቅኝ ገዥዎች እና ‹በጉልበት ቅኝ አትገዙንም፤ እንቢ!› በሚሉ ጭቁን አንገዛም ባዮች መካከል የተካሔደ ስለሆነ አፍሪካዊ ሆኖ፤ ለዚያውም ‹ወይ ቅኝ ግዛት ሳንገዛ ቀረን› በማለት የሚቆጭ ሰው አይኖርም፡፡ ይህንን አቋም ይዞ የተሟገተም እስከዛሬ አልሰማሁም ወይም አላጋጠመኝም፤ ምናልባት ወደ ፊት ከተነሣ ብሎም መሟገቻ ነጥቦችን እያዘረዘሩ መነታረክም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምናልባት ‹የአድዋውን ጦርነት ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛት ለመያዝ የቋመጠውን ጣሊያንን ለመመለስ የተደረገ የጦርነት ድል አይደለም› የሚል ትውልድ እስካልመጣ ድረስ!

  1. የጦርነቱ ድል አግባብነት የለውም

በሁለተኛው ነጥብ ዙሪያ ያለው አቋም የአድዋ ጦርነት ቅኝ ገዥዎች ለመመከት የተደረገ ተጋድሎ መሆኑን በመቀበል፤ በውጤቱ ላይ የተከሰቱ ችግሮች ድሉን የተሟላ አላደረጉትም ወይም የታሰበው የድል ውጤት ትክክል አይደለም የሚል ሙግት ነው፡፡ በዚህ አቋም ዙሪያ ተሰልፈው የሚቃነቅኑት በተለይ ኤርትራዊያንና የእነሱ ድምፅ የሆኑ ‹ዘመን ወለድ› ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ‹ዐፄ ምኒልክ በአድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ካደረጉ በኋላ ወደ ኤርትራም በመሄድ ጣሊያን ቢያንሰ  መዋጋት፤ ቢቻል ደግሞ ተዋግተው ማባረር ሲጋባቸው፤ ትተውት ስለተመለሱ የአሁኗ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ተገንጥላ በጣሊያን ሥር በቅኝ ግዛት እንዲትቆይ ስላደረጉ ትልቅ በደል ሠርተዋል፡፡› የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እንዳውም ኤርትራ አሁንም ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ራሷዋን በመቻል ለመኖር እንዲትገደድ ያደረጓት ዐፄ ምኒልክ ስለሆኑ ተጠያቂ ናቸው› የሚል አቋምም ያራምዳሉ፡፡

ይህ መከራከሪያ ግን በሁለት ምክንያቶች የተነሣ አሳማኝ አይመስልም፡፡ አንደኛ ዐፄ ምኒልክ የዚያን ጊዜ ጦርነቱን ከአድዋ ድል በኋላ ለመቀጠል የማይችሉባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ የርሃብ ዘመን ስለነበር የስንቅ ችግር ነበረባቸው፣ የወታደር ኃይላቸው ተዳክሞ ነበር፣ ጣሊያንም ምጽዋ ላይ እራሱን በማጠናከር ጦርነቱን እንደገና ለመግጠም እየተዘጋጀ ነበር፤ ያም ብቻ ሳይሆን አዲስ ኃይልም በማስመጣት ተጠናክሮ ነበር፡፡ ይህ ሐቅ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ዐፄ ምኒልክ ወደፊት በመግፋት ተዋግቶ ድል ማድረግ ይችሉ ነበር ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፤ እንዳውም በአድዋ ላይ ያገኙትንም ድል ሊያጡት ይችሉ ነበር ማለት የተሻለ አሳማኝ ይመስላል ፡፡ ሆኖም ድሉ ቢቀርም ምንም አይደል ዋናው የሀገር ሉዓላዊነት ስለሆነ እስከመጨረሻው በመግፋት መታገል ነበረባቸው ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፤ ግን የጠቀስናቸውን መከራከሪያዎች ከተቀበልን አቅምን አይቶ መታገልም አንዱ የጦርነት ስልት ነውና ግራና ቀኙን አመዛዝኖ የተሻለውን አማራጭ መምረጥ የአንድ ብልህ መሪ ተግባርና ኃላፊነትን የመወጣት ብቃት ነው፡፡ የምኒልክም ኤርትራን ሳያስመልሱ መመለሳቸው በዚህ መልክ ይታያል፡፡ እዚህ ላይ ግን ኤርትራዊያን ‹ከኢትዮጵያዊነት ፍቅራቸው ጥብቀት አንጻር› ከኢትዮጵያ ተለይተው በጣሊያን ለመገዛታቸው ምክንያት አድርገው ማቅረባቸው እውነታነት የለውም ማለት አይቻልም፡፡ እውነታው ከምኒልክ አቅም በላይ የሆነ ይመስላል ለማለት እንጂ!

ኤርትራዊያን ግን ‹አሁንም ከኢትዮጵያ ተለይተን ለመሔዳችን ምክንያታችን ዐፄ ምንልክ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ለጣሊያን ስለተውን ነው፡፡› የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ከሆነ አያስኬዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ‹ከኢትዮጵያ ተለይተው በጣሊያን ለመገዛታቸው ምክንያታቸው ምኒልክ ከሆኑና እሳቸውንም በዚህ ተሳስተዋል› ካሉ አሁን ከኢትዮጵያ የሚለዩት ምኒልክ የተሳሳቱትን ተግባር መልሰው በራሳቸው ላይ ራሳቸው ጭምር እየፈፀሙ ነው? ምኒልክስ ኤርትራን ሳያስመልሱ ለመምጣታቸው ከዚህ በላይ የተጠቆሙት ምክንያቶች አሏቸው ኤርትራዊያ ግን አሁን ላሉበት ሁኔታ ምኒልክን ተጠያቂ የማድረግ አግባባዊ ምክንያት የላቸውም፡፡

እሺ ይሁን ምኒልክ ኤርትራ ተገንጥላ በጣሊያን ሥር ለመቆየት ተጠያቂ ናቸው ብለን ብንስማማ እንኳን የአድዋን ድል ውጤት በደረጃ የበለጠ ከፍ ሳያደርገው ይቀር ይሆናል እንጂ በተገኘው የጦርነት ድል ላይ ላለመስማማት በቂ አይደለም፡፡ ክርክሩ የሚሆነው ‹የአድዋ ድል በአግባቡ የተገኘ አስደናቂ ድላችን ነው፤ ከዚያም በላይ ጣሊያን ከኤርትራም ሙሉ ለሙሉ ተባሮ ኤርትራዊያንም እንደ ሌሎች የኢትዮጵያውያን መሆን ቢችሉ ኖሮ ድሉ የበለጠ ያኮራ ነበር› የሚል ነው፡፡  ይህ ደግሞ በአድዋ ድል ከተገኘው የበለጠ ድል መቀዳጀት ይቻል ነበር ብሎ መቆጨት እንጂ የተገኘው ውጤት ትክክል አለመሆኑን ማሳያ አይሆንም፡፡

ምናልባት ውጤቱን የማይቀበሉ ወገኖች ያዩበት አንግል ከድል አድራጊው አንጻር ሳይሆን ድል ከሆነው ከጣሊያን አንጻር ተመልክተውት ቢሆንም አንኳን አሳማኝነት የሚኖረው አይሆን፡፡ ምክንያቱም ጣሊያኖችም በአድዋ ጦርነት መሸነፋቸውን የመሰከሩት ጉዳይ ነውና፡፡ ያንን የሽንፈታቸውን ታሪክ ለመቀልበስ መሰለኝ ከአርባ ዓመት በኋላ በመርዝ ጭስ የተበቀሉን፡፡ የእነሱ መሸነፍ ትክክልና ተቀባይነት ያለው ከሆነም ኢትዮጵያውንም ማሸነፋቸው፤ በዚህም ክብር ይገባቸዋል ማለት ትክክል ነው፡፡ አንድ ነገር መጠርጠር ግን ይቻላል፤ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች በአድዋን ጦርነት የተገኘውን ድል የሚያንኳስሱት የድሉ ኃያልነት እንዲደበዝዝ የፈለጉ አካላት የእጅ አዙር ተጽዕኖ አድርገውባቸው ይሆን እንደ? በጥቅሉ ግን አንድ ተከራካሪ የአድዋን ድል ትክክልነት ከተቀበለ ውጤቱን ለመቀበል ይገደዳል፤ ምክንያቱም ድሉ የታወቀው ባስገኘው ውጤት ነውና፡፡ በድሉ መልካም ውጤት ከተስማማም ስለ አድዋ ጦርነት ነቀፌታው አግባባዊነት አይኖረውም፤ ማስረጃም አያግዘውም፡፡

  1. ውጤቱስ ትክክል ነው ድሉ ለሌላ መጨቆኛ መሣሪያ ሆነ እንጂ!

ይህ መከራከሪያ የአድዋን ጦርነት እስከ ውጤቱ የተቀበለ ነው፡፡ ከውጤቱ በኋላ ግን ለሌላ የጭቆና ተግባር መሣሪያ ሆኗል ብሎ ይወቅሳል፡፡ ማለትም ‹ዐፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ያገኙትን የድል ውጤት ለሌላ ብሔረሰቦች መጨቆኛ ሽፋን ተጠቅመውበታል፤ ወይም የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች የታደጋት ቢሆንም የውስጥ ጭቆናን ግን ጨምሮላታል፡፡ የውጭ ኃይሎችን ድል ብናደርግስ በሀገራችን ተጨቋኝ ብሔሮች (ሕዝቦች) ሆነን ከኖርን ምን ይሠራልናል? የጨቋኙ ዓይነት እንጂ መጨቆናችን አልቀረለን፤ ይህ ከሆነ የአድዋ ድል ምናችን ነው?› የሚል መከራከሪያን ይቅርብበታል፡፡

ይህንን መከራከሪያ ዝም ብለው በድፍኑ ሲመለከቱት ትክክል የመሰለ ነገር ቢኖርበትም አምታችነት የተጠናወተው ነው፡፡ ምክንያቱም የአድዋን ድል በቀጥታ አይቃወምም፤ ‹ጭቆና ነበር› የሚለውም አሳብ እውነታን የያዘ ነው፡፡ ‹እውን ግን ጭቆናው ከአድዋ የድል ውጤት ጋር በትክክል የሚያያዝ ወይም በአድዋ ጦርነት አሸናፊ መሆን ያመጣው ነው ወይ?› ብለን ስንጠይቅ ብዙ አጠያያቂ ነገሮች ያጋጥሙናል፡፡ እንዲሁም በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ዙሪያ አንዣበው የነበሩትን የቅኝ ገዥዎች ዓላማ፣ አካሔድና ሊያስከትሉት የነበረው የተጽእኖ መጠንና የኢትዮጵያን ብተና አላስተዋለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልክ ሲታይ በመከራከሪያው አቋም ዙሪያም ብዙ ችግሮች እንዳሉበት መገንዘብ አያቅተንም፡፡ እንዳውም የአቋሙን አተያይና አንድምታ ሰፋ አድርገን አንየው ካልን ብዙ የማይስኬዱ ነገሮችን ጎልጉለን ማውጣት እንችላለን፡፡

አንደኛ የጭቆናንና የነጻነትን ትርጉሞች ያለ መጠንና ልክ ዘርጥጦ የመጠቀም ችግር አለበት፤ በግል ትዝብት እንደታየውም የሚመዝነው በአሁኑ ጊዜ የድሞክራሲ ሥርዓት መርሆዎች ዕይታ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ በዐፄ ምኒልክ ጊዜ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ በዚያን ጊዜ ሊያደርጉት ከሚችሉትና መሆን ስለነበረበትና ስላልነበረበት መዝኖ ሳይሆን በቀጥታ ይህንን አድርገዋል ይህ ከሆነ ደግሞ ጭቆና ወይም መብትን መጣስ ስለሆነ አግባብ አይደለም፤ ‹ጨቋኝ ናቸው› የሚል አቀራረብ ይንፀባረቅበታል፡፡

ሁለተኛ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት መገኘቷን በውስጠ ታዋቂነት ይቃወማል፤ ዐፄ ምኒልክ ግዛታቸውን ባያስፋፉ ኖሮም በእሳቸው አገዛዝ ሕዝቦች አይጨቆኑም ማለትንም ያሰማል፤ ምከንያቱም ዐፄ ምኒልክ በአድዋ ድል ባያደርጉ የመስፋፋት አቅማቸው ይቀንስ ነበር በሚል ግምት! በዚህም በቅኝ ገዥዎች ተይዞ መሰልጠን ይገኝ ነበር የሚል አጉል አረዳድም አለበት፡፡

ሦስተኛ የሀገር ሉዓላዊነትን ከውስጥ የአሠራር ችግር ጋር አደባልቆ የማምታታት ችግር አለበት፡፡ የውስጥ አስተዳደራዊ ችግርና የነበረውን የማይፈለግ የጭቆና ሥርዓት መቃወም አንድ ነገር ነው፤ የሀገር ሉዓላዊነት ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡

አራተኛ የጥንት የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ምንጭነት የዘነጋና ሁሉንም ነገር ሁሉ ከዐፄ ምንሊክ አገዛዝ በኋላ የተከሰተ አስመስሎ የፈረጀ ነው፤ ጥንታዊት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት በላይ ሰፊና ሥልጡን የነበረች ሀገር እንደነበረች በቀላሉ የታሪክ ሰነዶች በማገላበጥ መረዳት ይቻላል፤ የዚህች ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር ሕዝቦች መሆናችን ብቻ ዐፄ ምኒልክም ይሁኑ ሌላ ንጉሥ ወይም መሪ አንድነቷን ማስጠበቁ አስፈላጊ ነበር፤ የምኒልክም መስፋፋት የጥንቷ ኢትዮጵያ ማስመለስ እንጂ አዲስ ሀገረ-መንግሥትን መፍጠር አይደለም፤ ስለዚህ ኢትዮጵያን ከዐፄ ምኒልክ መስፋፋት በኋላ ብቻ የተገኘች አድርጎ ማየት ኢትዮጵያን ያለማወቅ ችግር ነው ፡፡

አምስተኛ የአድዋን ድል አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማምታታት ችግር አለበት፡፡ በዚህም ድሉን ከሌላ ጉዳይ ጋር በማምታታት የማጣጣል ሥራ ይንፀባረቅበታል፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ግን በአሁኑ የዓለምና የሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ የዚያን ጊዜው ሥርዓት በዘመኑ የአኗኗር ልምድና ሥርዓት መመዘን ይኖርበታል እንጂ አንዱን በሌላው መጠለዝ አግባብ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ዐፄ ምኒልክም ይሁኑ ሌሎች መሪዎች ለፈጠሩት ‹ጭቆናም ይሁን ሌላ መጥፎ ተግባር› የድሉን ታላቅነትና አስፈላጊነት አይቀለብሰውም፤ ባይሆን መጠየቅ ያለባቸው አግባባዊ ያልሆነ ነገርን በእሱ ታከው ከሠሩ በእዚያ ተግባራቸው ነው፡፡ በዚህም ቢሆን ለምሳሌ ዐፄ ምኒልክ ‹የአድዋን ድል ውጤት ለሕዝቦች መጨቆኛ አድርገውታል› ሲባል በምን ዓይነት መልኩ? የሚል ጥያቄ ይነሣል፡፡ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች በመስፋፋታቸው ነው? ከተስፋፉ በኋላ በአስተዳደር ሥርዓት ሕዝቦችን ስለበደሉ ነው? ነው በሌላ? በመጀመሪያው ‹ባደረጉት መስፋፋት› ከተባለ ‹መስፋፋታቸው አስፈላጊ ነበር ወይስ አይደለም?› የሚል ጥያቄ ይከተላል፤ በአስፈላጊነቱ ላይ ከተስማማን ችግሩ ያላው ከመስፋፋቱ በኋላ ባለው የአስተዳደር ሥርዓት ነው ማለት ነው፡፡ በዐፄው መስፋፋቱ አስፈላጊነትና አግባብነት ካልተስማማን ግን ‹ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ፈልገን ነበር?› የተከፋፈለች? የተከፋፈለች ኢትዮጵያስ እኛ በፈለግነው መልኩ ትገኝልን ነበር? ለምሳሌ ኦሮሚያን እንውሰድ ዐፄ ምኒልክ በመስፋፋት አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ባያስጠብቁልን ኖሮ አሁን የሚገኘው ኦሮሚያ በአንድነት ይገኝልን ነበር? ሌላ የውጭ ወይም የውስጥ ኃይልስ እኛ በምንፈልገው መልኩ ኦሮሚያን ሊያስገኝልን እንደሚችል ዋስትና ይኖረናል? ከሌለ በመጠኑም ቢሆን ምኒልክን ማመስገን የኦሮሞዎች ፋንታ ይሆናል፤ ይህ ለሌሎችም ብሔረሰቦች ይሠራል፡፡ በሌላ በኩል ‹ዐፄ ምኒልክ በኃይልም ይሁን በሰላማዊ ማግባባት ተስፋፍተው የኢትዮጵያን አንድነት ከማስጠበቁ ሌላ አማራጭስ ይኖራቸው ነበር?› ካለ ምን? ከሌለ ትንሹን ችግር ለትልቁ ጥቅም ማጥፊያ በማድረግ ማጣጣል የለብንም፡፡

እሽ! በመስፋፋታቸው ተስማምተን ያልተስማማንበትና የተማረርንበት ጉዳይ ከዚያ በኋላ በተፈጠሩ የአሠራርና የአስተዳደር ችግሮች ነው እንበል፤ ይህ አግባብ ይሆናል፡፡ ባይሆን መፈተሽ የሚገባው እየመዘን ያለነው በዚያን ጊዜ በነበረው አስተሳሰብና ልማድ ነው ወይስ አሁን ቢሆን ኖሮ ብለን በተመኘነው የሥርዓት አሠራር ነው? አሁን በምንመለከተው የዴሞክራሲም እንበለው የነፃነት ሥርዓት ሚዛን ከሆነ ችግሩ ያለው ከሚዛናችን ሊሆን ይችላል፤ በዴምክራሲ ሥርዓት ሚዛን ለምን አላስተዳደሩም የምንለው ጥያቄ ትክክል ቢሆን እንኳን ‹ይችሉ ነበር ወይ?› የሚል ጥያቄንም ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ሌላ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው ‹ዐፄ ምኒልክ ሕዝቦችን ያንገላቱ ጨቋኝ ናቸው› ስንል የምንከሰው ሥርዓቱን ነው ወይስ የአንዳንድ ግለሰቦችን የአስተዳደር ችግሮች ወስደን ነው የዘፈዘፍንባቸው? የአገዛዝ ሥርዓታቸውን ነው የምንል ከሆነ ዕቅድና ፖሊሲ ነድፈው (በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ) ጭቆናል አካሂደዋል ማለታችን ይሆናል፤ አይ በዚያ መልክ አይደለም የምንል ከሆነ ግን በአስተዳደር ክንውን ውስጥ በተፈጠረ ጥፋት ነው የምንከሳቸው ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ምንም እንኳን መልካም የአስተዳደር ሥርዓት አለመኖሩ ቢያስጠይቃቸውም ከነበረው ነበራዊ ሁኔታ አንጻር ሚዛን አይደፋም፤ ምክንያቱም ያለ እንከን የማስተዳደር አቅማቸውና ልምዳቸው ውስን ነበርና፡፡

በጥቅሉ ሕዝቦችና ብሔረሰቦች መጨቆን አልነበረባቸውም በሚለው ብንስማማም የአድዋ ድል ለሌላ መጨቆኛ መሣሪያ ውሏል የሚለውን ሙግታችን የሚደግፍልን አይደለም፡፡ የዐፄ ምኒልክን መስፋፋት ተጠያቂ እንዳናደርግ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በእሳቸው ሥር የነበረው ከጦርነቱ በፊት ነበር፤ ከጦርነቱ በኋላ ባለው ጊዜ ቀሪዎቹ በአንድነት ጥላ ሥር መግባታቸው አድዋ የተለየ ኀይልን ለምኒልክ ስላጎናፀፋቸው ብሎ ለመከራከር በቂ ማስረጃ ያለው ምክንያት አይደለም፤ እንዳውም በአድዋ ጦርነት ባይዳከሙ ኖሮ የበለጠ ኃይል ያገኙ አልነበረም ወይ? ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ የአድዋ ድል በአንድነት የማስተባበር ኃይልን ስለሰጣቸው በሚል እንዳው ይሁን ብለን ብንስማማ እንኳን የአድዋን ድል ኃያልነት የሚቀንሰው አይሆንም፤ ምክንያቱም የአድዋ ጦርነት ከውጭ ኃይሎች ጋር የተደረገ ወራሪን የመመከት ትግል ነው፤ በዐፄ ምኒልክ የተደረገው ጭቆና ግን በሀገራችን መንግሥት ወይም በመንግሥታችን የአስተዳደርና የአሠራር ችገር የደረሰብን በደል ነው፡፡ በሌላ በኩልም የአድዋን ድል ከአስተዳደር ችግር ጋር ልናያይዝ የምንችልበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም በአድዋ ጦርነት አልተሳተፍክም ተብሎ ወይም በአድዋ ጦርነት ከጠላት በኩል ሆነሃል ተብሎ የደረሰ የጭቆና በደል የለም፤ በሌላ ሊሆን ይችላል እንጂ! የአድዋ ድል ኃያልነት ግን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያ ሁሉ ኩራት የሆነ የአባቶቻችን የጋራ ትግላቸው ውጤት ነው፤ ባለቤት የሆንበትን የጋራ ኩራት ደግሞ ገለልተኛ በመሆን ማየትና ማንኳሰስ አግባብ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ‹አድዋ ድል የመጨቆኛ መሣሪያ ስለሆነ ትልቅ ክብር ሊሠጠው አይገባም› የሚል አቀራረብ አግባባዊነት ያለው መከራከሪያ አይደለም፤ ትልቁን በትንሹ መናድ ወይም ‹አልተገናኝቶም› ይሆናልና፡፡

  1. የድዋ ድል የኢትዮጵያ ልዩ ክብር

ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ነጥቦች በአስተሳሰብና በዕይታ አድማስ ችግር አለባቸው ብለን ከተስማማን፤ የቀረውን ትክክልነት ማየት ይኖርብናል፤ የአራተኛው መከረከሪያ ነጥብም ‹የአድዋን ድል ለኢትዮጵያ ጥቅም እንጂ ያመጣው ችግር የለም› በሚል መከራከሪያ ላይ የሚሽከረከር ነው፡፡፡ በሀገሪቱ ላይ ጉዳት  (ችግር) አምጥቷል የምንል ከሆነ ‹ምን?› የሚል ጥያቄን መልስ መስጠት አለብን፤ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውን ችግሮች (መከራከሪያዎች) አንስተን እንዳንመልስ አጥጋቢ መከራከሪያዎች አለመሆናቸውን ተመልከተናል፡፡ ከእነሱ ውጭ ሌላ መከራከሪያዎችን በማንሳት ለመሟገት ደግሞ ሚዛን የሚደፋ መከራከሪያ ማግኘት የምንችል አይመስልም፡፡ ስለዚህ የአድዋን ድል ከጥቅም ውጭ ያመጠው ችግር (ጣጣ) የለም የሚለውን በመደገፍ ያስገኛቸውን ፋይዳዎች መመልከት ይገባናል፡፡ በዚህ መልክም የምንሟገትበትን የአድዋ ድል ምናችን እንደሆነ እንይ፡፡

1)  ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያገናኘ (የታሪክ መበጠስ እንዳይፈጠር ያደረገ) ነው፡-

በጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች (ለምሳሌ ሄሮዱተስ፣ ዲዮርዳኖስ፣ የግሪክ፣ የሮምና የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች) እና በሀገራችን እስከዛሬ ተገትረው ምስክርነትን በሚያውጁ ሐውልቶች፣ አቤያተ ክርስቲያናትና አቤያተ መንግሥታት፣ እንዲሁም በየገዳማቱ በሚገኙ የብራና መጻሕፍት ሕያው ማስረጃነት ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ታሪክ በአድዋ ድል አማካይነት ቀጣይነት እንዲኖረውና እንዲታወስ ሆኗል፡፡ የአድዋ ድል ባይገኝ ኖሮ ግን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የዓለም ሥልጣኔም ምንጭ መሆኑ በጥቁር ሕዝቦች አይቀነቀንም፤ በራሳችንም በሆን ታሪኩ ከተረት ያለፈ አክብሮት አያገኝም ነበር፤ ቢያገኝም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊነገር የሚችል አይሆንም ነበር፤ እንዳውም የታሪክ አስተሳሰባችን እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሠረቱ የጠፋበት ላለመሆኑ ዋስትና አይኖርም፡፡ ስለዚህ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ተበጥሶ እንዳይቀርና ተያይዞ እንዲቀጥል ያደረገልን ልዩ ክስተታዊ ኩራታችን ነው፡፡

2)  የጥንቶቹን አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር የተመሰከረበት የጦርነት ድል ነው

3)  ባህላችን ተጠብቆ እንዲኖር አስችሎናል፡- ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በባህል ቅኝ ግዛት ብንወረርም

4)  የኢትዮጵያን አንድነት እውን ለማድረግ ያስቻለ ነው

5)  ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ መድረክ እንድትታወቅና እንድትከበር ምክንያት የሆነ ነው

6)  ነጻነታችንን አስከብረን መኖር እንደምንችል አስመስክረንበታል፣

7)  ለሌሎች ሀገራት ሕዝቦች አርአያ ሆኗቸዋል፡- ለነፃነታቸው በቁርጠኝነት እንዲታገሉ ምሳሌ በመሆን ለዓለም የነፃነት ትግልና ክብር ምሳሌ ሆኗል፡፡

8)  የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለማቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በአፍሮ አሜሪካዊያንና በአፍሪካዊያን እንዲቀነቀንና እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል

9)  ጥቁር ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚችል (የሰው ዘር ሁሉ እኩል እንደሆነ) አውሮፓውያን ትምህርት ያገኙበት ድል ነው፡- በመሆኑም ቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል

10) ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረትና ጥንካሬ አድዋ ምክንያት ሆኗል

11) ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ በዕውቅና እንዲረጋገጥና ድንበሯን በአግባቡ ለመከለልም ጭምር አስችሏታል…

ይህንን መከራከሪያ አስፋፍቶ ማቅረብና በመረጃዎች ማስደገፍ ይቻላል፤ ዋነው ግን የክርክሩ አተያይና ክብደት ስለሆነ በዚህ መቋጨት በቂ ይሆናል፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው ነጥቦች ደግሞ በዓለም ሀገራትም ሆነ በሀገራችን ልዩ ትርጉምና ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እነዚህን ነጥቦች ተመልክቶና ተረድቶ የአድዋን ድል ማጣጣልና ማንኳሰስ አይገባውም፤ አግባብና አስተዋይነትም አይሆንም፤ የመልካም እሳቤ ችግር ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይልቁንስ የዐድዋ ድል ባስገኘው ውጤት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የትብብር፣ የአንድነት፣ የኩራት እና የክብር ምንጭ የሆነ፤ ለሀገራችንም ዓለም አቀፍ ዝናንም ያጎናጸፈ ልዩ የአባቶቻችን የመስዋዕትነት በረከት ነው፡፡

ለማንኛውም ካስተዋልነው የአድዋ ድል! የማንነታችን ማሳያ፣ የኩሩ ታሪካችን ማስመስከሪያ፣ ኢትዮጵያን ከነጮች የባህል ብረዛ የታደገ፣ ለጥቁሮች ነፃነት ማቀጣጠያ ክብሪት የሆነ፣ የአንድነታችን ማጥበቂያ፣… ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለም አድዋ ድል የእኛ ብቻ አይደለም፤ የጥቁር ሕዝቦች ሁላ እንጂ! አድዋ በውጤቱ ብዙ ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክም ምንም ይሥሩ ወይም ያጥፉ ካድዋ ጋር ተያይዞ ግን አፍሪካዊያን ሁሉም ሊኮሩባቸው የሚገቡ መሪ ናቸው፡፡

‹ምኒልክ ማለፉን የምትጠይቁኝ፤

ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ፡፡›

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply