ኢትዮጵያዊነት፡- ገና ከጅምሩ ነገሩ!

ሰሞኑን ይህን ድረገጽ ከፍቼ ‹ኢትዮጵያ!› ‹ኢትዮጵያ!› የሚል ጽሑፍ መለጣጠፍ ስጀምር የተመለከቱ አንዳንድ ዘመናዊያን ብሔርተኞች ‹ኢትዮጵያዊነትን› እያጣጣሉ በውስጥ መስመር አርበኛነታቸውን አሳዩኝ፡፡ ‹ጊዜውን ያልዋጀ› ጠሳብ የሚያንፀባርቅ ድረገጽ ነው የምትለጥፈው የሚል ትችትም ያቀረቡልኝ አሉ፡፡ አሁን ያለውን የብሔር ትኩሳትና ነባራዊ ኹኔታ ያልተረዳ ጽሑፍ እንደምጽፍ አድርገው የወሰዱም ቅን አሳቢዎችም አጋጥመውናል፡፡ ከዚያ ባለፍ አቅሙ ካለህ ለምን በነባራዊ ኹኔታው ላይ አትትፍም የሚል ምክረ ሐሳብም ያቀረቡልኝ አሉ፡፡

ለእኔ ዐስበውም ይሁን አይሁን መልዕክታቸው ይሰማኛል፤ እኔም በብሔር እያዋዛሁ እና በእኛና እነሱ እያነጻጸርኩና እያጋጋልኩ ጓደኛ ብሰበስብ ባንድ ሳምንት በመቶ ሸህዎች የሚቆጠሩ መወደዶችን (ላይኮችን)፣ በአሥር ሺህዎች የተመደቡ አስተያየቶችን (ኮሜንቶችን)፣ ለብዙዎች የሚደርስ ማካፈሎች (ሸሮችን) ማግኘቴና፤ ከዚያ የሚገኘውን የዝና፣ የዕውቅና፣ የጀግንነት፣ … የገቢ ትሩፋቶችን መቋደስ እንደሚያስችለኝ አላጣውም፤ ችግሩ እሱ አይደለም፤ እንዳውም ይህ በጣም ቀላሉ ፋሽን ነው፡፡

የእኔ ሐሳብ በዚህ ማጋጋል ውስጥ፣ በዚህ መፈራረጅ ውስጥ ያለው እሳት ማገዶ እየጨመርኩ ማጋጋም አለመፈለግ ኾኖ እንጂ፤ የብሔር እሳቱ እየጋመ በመኾኑ ቢቻል የሚያቀዘቅዘው ውሃ፣  የጋራ የኾነ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይሻላል በሚል ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እንዳው ዕንቁና የምሥጢር ቋት የኾነው ብርቁ ኢትዮጵያዊነት መሸርሸሩ ስለሚያሳስበኝ ነው በዚህ የተከሰትኩት፤ ጊዜና ዐቅም ቢኖረኝ በዚህ ዙሪያ ብዙ ብጽፍ በወደድኩ፤ ለሙከራ ግን ጀምሬያለሁ፡፡ እኔ የማውቃትና ታሪኳን የተገነዘብኩላት የመሰለኝ ኢትዮጵያ ለእኔ የምትደንቀኝ ኢትዮጵያ ሳትገለጽ እየተቀበረች መሔዷ ያሳስበኛል፤ ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ልዩ ነውና፤ ብችል ኖሮ በዜማ በቅኔ በሰፊው ብዘምርለት ምኞቴ ነው፡፡

በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊነትን በኹለት ዓይነት መንገድ ሊገለጽ ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡- በእንጀራና በዛፍ ምሳሌ፡፡ አዎ! ኢትዮጵያዊነት ለብዙ ዘመናት የተላቆጠ፣ የተቦካ፣ የተጋገረ እንጀራ ነው፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከእንጀራ ጋር እየጋገረ ያቀረበው ድንቅ ደራሲ አዳም ረታ ነው፤ እሱ ያየበት የራሱ መንገድ አለው፤ በእኔ ዕይታ ደግሞ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ማንነት ለማግኘትም ስንት ዘመናት አልፏል ባይ ነኝ፤ በእነዚህም ዘመናት በቅራኔዎችና በትብብሮች (በአንድነት) እየተፋተገ በዘመናት የታሪክ እሳት በስሎ እኛ ያለንበት ዘመን ላይ ደርስዋል፡፡ ስለኾነም ቅራኔዎቹን ብቻ ይዞ መነሁለል (መበጥረቅ) የአደጋ ብዛትን መጋበዝ እንጂ ዐዋቂነት አይኾንም፤ የብሔርተኝነት ችግር አንዱ ይህ ነው፤ ትብብሩንና ተዋሕዶዉን ይዞ በስንት የቅራኔና የመዋዋጥ መስተጋብር መገኘቱንም መዘንጋት ወይም መተውም የዕይታዎች መስተጋብር ዕጥረት ይኾናል፡፡

በዚያ ላይ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ዘመን ረዥምና ቀደምት እንደሆነው ሁሉ የሕዝቦቿም ማንነት  ከዘመኗ ጋር አብሮ የተለያየ መስተጋብርን እያደረገ ያለንበትን ሁኔታ ማስገኘቱን መካድም ኾነ መዘንጋት አይገባም፤ ልክ እንጀራ ከእህል መዝራት ተሰብስቦ እስከ መቦካት ብዙ ሒደቶችን አልፎ ተጋግሮ እንደሚገኘው፡፡ ወደድንም ጠላንም ግን ኢትዮጵያዊነት ዐዲሲቱ ኢትዮጵያ እንደሚባለው ገና አዲስ እየበቀለ ያለ ሰብል አይደለም፡- የብዙ ዘመናት ዶክሜንት ነው እያቆሸሽን ጣልነው እንጂ፡፡ አንድም ለየብቻው በቅሎ ዘርዝሮ፣ ተለቅሞና ተሰብስቦ፣ ከዚያም ባለፈ ተመርቶ በጥሬነት ለየብቻ የተሰበሰበ ማንነት አይደለም፤ ይለቁንም በአንድ ላይ በመከራ ተፈጭቶ፣ በአብሮነት ተቦክቶና ተጋግሮ የበሰለ እንጀራ ኾኗል፡፡ ይህም ኾኖ ግን ልክ ከተለያየ እህል ዱቄት ተላቁጦ እንደተጋገረ እንጀራ ይህኛው የዚህ ነው፤ ያኛው የዚያኛው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የእህሉ ዓይነት በዛ ወዳለበት የጤፍ፣ የዘንጋዳ፣ የዳጉሣ፣ የገብስ፣… እህል እንጀራ እያሉ እንደመጥራት በዛ ያለውን መገለጫ የያዘውን ስያሜ በመጥራት መግለጽ ልማድም አግባብም ነው፡፡ በዚህም አግባብነቱ ጥንታዊ ማንነታችን ጭምር መርምር እንድንረዳ የአስረጅ ምንጭና መኩሪያ ስለሚኾነን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለማይበላው ለማይስማማው አይኾንም፤ ለሚስማማው የሰው ልጅ (እንጀራ ለለመደ) ሌላ ምግብ ያለ እስከማይመስለው ድረስ ይወደዋል፤ ስለዚህ ምናልባትም ከተለያዩ እህሎች ተዋሕዶ የተጋገረውን እንጀራ ለያይቼ እረዳለሁ ማለት ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ የአገራችን የብሔር ፖለቲከኞች ችግር ይህ ነው፤ ከተለያየ እህሎች ተዋሕዶ ተጋግሮ እያየነውና እያረጋገጥነው፤ አንድ ንፁህ ዘር ብቻ የኾነ አስመስለው ሲናገሩ ትንሽ እንኳን ስቅጥጥ አይላቸውም፡፡ ምናልባትም መሃይምነት ሀብቴ ብለው ይኾናል፡፡

ይህ የምለው ሐሰት ነው የሚል ካለ ታሪኩን ያንብብ፣ ጥበቡን ይመርምር፡፡ የሕዝቡ ታሪኩ በጦርነት፣ በስደት፣ በረሃብና በመጋባት አንድ ላይ መጋገሩን ይረዳል፡፡ ሌላውን እንኳን ብናልፈው የአክሱም ውድቀት የፈጠረው ክስተት የሰሜኑን ወደ ደቡብ፣ የመሃሉን ወደ ሰሜን አምጥቶታል፣ ሥልጣኔውንም እንደዚሁ፡፡ ለምሳሌ የአህመድ ግራኝ ጊዜ ጦርነት፣ የኦሮሞ መስፋፋትና የዐፄ ምንሊክ ግዛት ማስፋት የመስተጋብሩ ዋና ዋና ተጠቃሾች ይኾናሉ፡፡ በእነዚህ የታሪክ ክስተቶች ያልተዋሐደ ወይም ያልተቀላቀለ ያለ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ በመቦካት ተዋሕዶ የተጋገረ ማንነት ይዞ የአንድ የኾነ ብሔር ላይ ብቻ መንጠልጠል ምን ይሉታል፡፡

2ኛ ምሳሌ፡- አንድም ኢትዮጵያዊይነት ለብዙ ዘመናት የደረጀ ዛፍ ነው፤ በዚህም ሥሩን አመቻችቶ፣ ግንዱን አደርጅቶ፣ ቅርንጫፎን አብዝቶና አስፋፍቶ ብዙ ቅጠሎችን እያረገፈና እየተካ አሁን ያለንበት ዘመን ላይ የደረሰ የታሪክ መስተጋብር ውጤት ነው፡- ኢትዮጵያዊነት፡፡ ይህ ማንነት ብዙዎች በዛፉ ሥር ተጠልለው ያመልኩት የነበረ መንፈስ ነው፤ ለዚህም ስንቶች ተሰውተውለታል፤ ደማቸውን አፍሰው አለምልመውታል፤ በዘመኑ እርዝመትና ከቅርንጫፉ ስፋትና ውስብስብነት የተነሣ ማንነቱ የደረቀና የተረሳ ቢመስልም፣ አንዳንዶችም በዘረኝነት እሳት አቃጥለው እንዲጠፋ ሊያደርጉት ቢጥሩም አሁን በህልውና አለ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነም ብዙዎች ቅርንጫፎቹ ማንነታቸውን ረስተው፤ ግንዳቸው ጠፍቷቸው ሲቸገሩ እያየን አብረን ከመደናበር የጥንቱን የማንነታቸውን ሥር፣ ግንድና ቅርንጫፍ በማያያዝ ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጂ እኛማ ማንነታችን ከግንዱ ጋር ተጠብቆ ተያይዞልናል፡፡ ይልቁንስ ባለማወቅ ንፋስ በሚያወዛውዘው ቅጠል እየተረበሽን ከመነታረክ፣ ተምታቶብንም የነፋስ ማዕበል ማድመቂያ ከመሆን የሚጠበቅን የማንነታችን ዛፍ በአግባቡ ዐውቀን ብናሳውቅ ብዙ እንጠቀማለን፡፡ የዘር ሥራችንም የያዘውን መሠረትም በመመመርመር ግንዳችን እንዲጠነክር ብናደርገው፤ እንኳንስ ነፋስ በቅጠልነት ሊወዛውዘን ይቅርና ለብዙዎች ማረፊያ ዛፍ በመሆን ብዙ ቁም ነገር በሠራን ነበር፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ሌሎች የጥንታዊት የኢትዮጵያ ማንነት ረስተው ተበትነው ማንነታቸውን ለዘነጉት የጥንቱን ከአሁኑ ጋር በማገናኘት ለመረዳት (ለማስረዳት) ከጥንት ጀምሮ የተበተኑ ዘመዶቻችንን ማግኘት አለብን እንጂ በጫፍ ላይ የሚገኝ ቅጠልን ይዘን እየተወዛወዝን በነፋስ ማዕበል እየጠመታታን መኖር የለብንም፡፡ ይልቁንም ግንዱን ጨብጠን እስከ ቅጠሉ ያለውን የማንነታችንን ተያያዥነት መመርመር ይገባናል፡፡ የዘር ሥራችን የያዘውን መሠረት (ግንድ) መርምረን በማወቅ የዘር ግንዳችን ብናጠብቀው እንኳን ነፋስ የሚያወዛውዘው ቅጠል ሆነን እርስ በራስ ልንናቆር ይቅርና ለብዙዎች የማንነት ማረፊያ ታላቅ ዛፍ በሆንን ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምልበት ምክንያት ይህ ነው፡፡ ብሔርተኞችም ይህንን ነገር ቢያስተውሉት እጅግ ደስተኛ እኾናለሁ፡፡

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply