እልፍ አንድ ሺህ ወይስ ዐሥር ሺህ?

read in pdf

፩. ምክንያተ ጽሕፈት

ይስማዕከ ወርቁ በቅርብ ጊዜ ባሳተመው ‹ተከርቸም› በሚለው 6ኛ መጽሐፉ ‹እልፍ(፼) ዐሥር ሺህን ሳይኾን አንድ ሺህን ይወክላል› የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ እኔም በመጽሐፉ ያቀረበውን የእልፍ(፼) ቁጥር አስተያየት ከተመለከትኩ በኋላ መስተካከል ያለበት ጉዳይ መስሎ ስለተሰማኝ ይህንን ጽሑፍ በተወሰነ ደረጃ ሞነጫጭሬ አስቀምጨው ነበር፤ በዕንቁ መጽሔት ተጠይቆ የሰጠውን መልስ ከተመለከትኩ በኋላ ግን መከራከሪያ ነጥቦችን ማቅረብ አስፈላጊ መስሎ ታየኝ፡፡

ምክንያቱም በእኔ ዕይታ የይሰማዕከ የ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ውሳኔያዊ መጣጥፍና አጠቃቀም ሁለት አንድምታዎች አሰምቶኛል፡፡ አንድኛ ከዚህ በፊት የታተሙት የሊቃውንት መጻሕፍት የግዕዝ ቁጥር አጠቃቀም ስህተት መኾን ይጠቁማል፡፡ ይህ አንድምታም  ‹የሀገራችን ሊቃውንት የግዕዝ ቁጥር ዕውቀት የላቸውም› የሚል ትርጓሜንም ያመጣል፡፡ ይህንን ደግሞ ‹እነዚህ ሕዝቦች እስከ ሺህ ድረስ አልቆጠሩም እንደ?› ያስብለናል እና ‹ቀና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ› የሚሉት የይስማዕከ አገላለጾቹ ምስክር ናቸው፡፡ ስጋቱ ቢገባኝም ‹ከኛ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው› ዓይነት አቀራረቡ ግን አስተዋይነት ያለው አልመሰለኝም፡፡ ስለዚህ ጥረቱ መልካም ቢኾንም ያላስተዋላቸው ነጥቦች ስላሉ እንዲያጤናቸው እና ሌሎችም ትክክል መስሏቸው የቁጥር አጠቃቀማችን እንዳያዛቡ በሚል አመለካከት ይህንን አስተያየት አቀረብኩ፡፡

፪. በእንተ ይስማዕከ

በመሠረቱ በግሌ ይስማዕከን ከሚያከብሩትና ከሚያደንቁት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፎቹ የሚያቀርባቸው ሀገራዊ ዕይታዎች ይማርኩኛል፡፡ ለምሳሌ ‹ደርቶጋዳ› የሚለውን መጽሐፉን እንዳነበብኩ ‹ከፍቅር እስከ መቃብር ቀጥሎ 2ኛ ምርጥ የልብ ወለድ መጽሐፍ› ብዬ ለመናገር ደፍሬ ነበር፡፡ ይኸኛው ‹ተከርቸም› የሚለው መጽሐፉም ቢኾን በውስጤ የሚያስቆጨኝን ሐሣብ ይዞ ስለቀረበ ነው መሰል አስደስቶኛል፡፡ እስቲ ለማሳያ እንዲኾነኝ ከዚህኛው መጽሐፍ ልጥቀስ፡-

‹‹ከግድግዳው ጥግ አፉን የከፈተውን ትልቅ ጉድጓድ አይተው፡

‹ስብሐት ለአብ! የምን ጉድጓድ ነው?› አሉ፡፡

‹ለጋን ማስቀመጫ ብዬ ነው፡፡›

‹ታዲያ ይህንን ያህል?›

‹ጋኔ ትልቅ ነው፡፡ ለነገሩ ይህንን ያህል መቆፈር አልፈለኩም ነበር፡፡ ትንሽ ስቆፍረው ተደረመሰና ሰፊ ኾነብኝ፡፡›

‹እንዲያስ ከኾነ በደንብ በቆፈርሽ!›

‹እንዴት?›

‹ብር ወይም ወርቅ ተቀብሮበት ቢኾንስ!›

ኧረ? ማን ሊቀብረው እዚህ ላይ!›

‹አይ ልጄ አባቶቻችን’ኮ ብዙ የቀበሩልን ሀብት ነበር፡፡ ነገ ዛሬ ሲሉ ሳያሳዩን አለቁ እንጂ! ሞት ቀደማቸው! ታሪካችን፣ ሀብታችን ሁሉ እንደ አፅማቸው መሬት ውስጥ ኾነ፡፡ ለማን ይናገሩት? ትውልዱ ሁሉ መና ኾነባቸው፡፡ እኛማ እንኳንስ ለነገ ልንቀብር የዕለት ከርሳችን ከረጢት አልሞላ እያለን ስንዛግጥ እንውላለን፡፡ ስንታክት ኖረን ሳይሳካልን መትነን! ኸረ ወዲያልኝ!› አሉ ጭራቸውን ሽው አድርገው፡፡››

የሚገርመው ታዲያ ቆፋሪዎቹ ጉድጓዱ ያዘጋጁት ሰውየውን (አባ ሰባጋዲስን) ሊቀብሩበት መሆኑ  ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መለኩሴው ቅርስ አላዘርፍ ስላሏቸው ደብዛቸውን በማጥፋት እና የቅርስ ቤቱን  ቁልፍ ወስደው ቅርሱን በመዝረፍ ለፈረንጆች ለመሸጥ ነው፡፡ በዚህም ይስማዕከ ቅርሶቾቻችንና አባቶቻችን የሚገኙበትን ህልውና ምን እንደሚመስል በሚጥም ምሠላና መቼት ማሳየት ችሏል፡፡ የይስማዕከን ማጠንጠኛ በእውን የሚታይ ክስተት መሆኑን ለማረጋገጥ  የአብነት ትምህርት ቤቶችን ሁኔታ መቃነኘት ብቻ ይበቃል፡፡ አባቶቻችን ያከማቹትን ዕውቀትና በምስጢርነት የያዙትን ሀብት ተረካቢ ሰው በማጣቸው ይዘውት እየተቀበሩ ወይም በዘራፊዎች እየተነጠቁ መሆናቸውን ለመረዳት ያስችላል፡፡ እንዲሁም የታሪካችንን አመጣጥ ዞር ብሎ መዳሰስም በሀጋራችን ዋሻዎችና መሬት ውስጥ ብዙ የተቀበረ ቅርስና ሀብት ሊኖረን እንደሚችል ለመገመት ያስችለናል፡፡ እናም ይህንን ትልቅ ሀገራዊ የታሪክ ቀውስና የቅርስ ዝርፊያ ሁኔታ ነው ይስማዕከ በ‹ተከርቸም› ምጥን አድርጎ የነገረን፡፡ እንደ እኔ ከሆነ የቅርስ ጥበቃ ተቋማት ለማስተማሪያ ቢጠቀሙበትም መልካም ይመስለኛል፡- ይህንን መጽሐፍ!፡፡

 ምንም እንኳን የ‹እልፍ›ን ውሳኔ በሚመለከት ከታች የገለጽኩትን ትችትና ማስተካከያ ባስቀምጥም እንደ ሥራዎቹ ከኾነ ግን ይስማዕከ ‹‹ይበል!› ሊባል የሚገባው ልጅ ነው› የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለእኔ እንዳውም ዐጼ ኃ/ሥላሴን ሳይቀር ‹ልጁን ጥዬ አልሄድም!› እስከማለት ካደረሳቸው  ከወጣቱ የማይጨው ጀግና ‹አብቹ› ጋር ተመሳስሎብኛል፡፡ በእውነት በዚህ በኩል መመስገን ሲያንሰው ነው፡፡ እንደ! የቀሚስ ግልቢያ አቀንቃኝ በበዛበት በዚህ ዘመን እኮ ነው እንቁዎቻችንን (icons) ተጠቅሞ የራሳችንን ማንነት፣ ባህልና ሥልጣኔ እንድንመረመር እየታገለ ያለው፡፡

‹ሰው ማለት ሰው ማለት፣

ሰው ኾኖ ሲገኝ ነው ጀግና በጠፋለት፡፡› ነው የተባለው ልበል?

በጥቅሉ ይህንን ብልም ችግሮች የሉም ማለቴ ግን አይደለም፡- ፍጹም መኾን አይቻልምና፡፡ በተለይ በሥነ ጽሑፍ ሐያሲነት ጎራ የተሰለፉት ብዙ እንደሚያወሩ አውቃለሁ፡፡ በግሌም እንደታዘብኩት የልጅ አውቃለሁ ባይነት የሚንጸባረቅበት ይመስለኛል፡፡ ይህንን ለማለት ያስደፈረኝም ስንት ሊቃውንት የተስማሙበትን የእልፍ ምልክት ዐሥር ሺህ መኾን ስህተት ነው በሚል ላርማችሁ ማለቱ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ያቀረበው መከራከሪያም አጥጋቢነት ያለው አልመሰለኝም፡፡ ምናልባት ወደፊት የተሻለ ጥናታዊ ማስረጃዎችን የሚያቀርብ ከሆነም (በዕንቁ መጽሔት እንደጠቆመው) በዚያን ጊዜ የሚታይ ይሆናል፡፡ ለጊዜው ግን ከላይ ካነሳሁት አንድምታ አንጻር አስተያየት መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግንቸዋለሁ፡

፫. የይስማዕከ ክርክር ማጠንጠኛ፡-

ከሁሉም በፊት መታወቅ የሚኖርበት ‹እልፍ(፼) አንድ ሺህ ነው፡፡› በማለት የተጠቀመ ይስማዕከ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ መ.ይትባረክ ገሠሠ መራ የተባሉ አባት የኢትዮጵያ ቁጥር አስመልክተው ባዘጋጁት ‹ሰዋሰወ ቀመር› በሚል ጥናታዊ መጽሐፋቸው ስለ እልፍ ውሳኔ የተወሰኑ ሊቃውንትን ጠይቀዋል፡፡ በጥናታቸው ከጠየቋቸው ሠላሳ አምስት ሊቃውንት መካከልም ሦስቱ ‹አንድ ሺህ› እንደሚሉት አስቀምጠዋል፡፡ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ የተለየ መረጃዎችን በማቅረብ የታወቁት መሪ ራስ አማን በላይ በ2000 ዓ.ም ባሳተሟቸው መጽሐፎች እልፍን እንደ አንድ ሺህ ወስደውት ይገኛል፡፡ ኾኖም ከይስማዕከ በስተቀር ሌሎቹ ‹እልፍ(፼)›ን አንድ ሺህ ያሉበትን ምክንያት አላቀረቡም፡፡ (ምናልባትም ማቅረብ አይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡) ለምሳሌ መሪ ራስ አማን በላይ ‹መጽሐፈ ብሩህ ዣንሸዋ ቀዳማዊ› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 184 እልፍን አንድ ሺህ ካሉ በኋላ እንደ አማራጭ ዐሥር ሺህ ብለው አስቀምጠውታል፡፡ ይህ ደግሞ ግራ ያጋባል፡፡ በዚህ በኩል ‹እልፍን አንድ ሺህ ነው› የሚል መከራከሪያ ያቀረበ ይስማዕከ ብቻ ነው፡፡ የይስማዕከስ መከራከሪያ ምንድን ነው?

‹አንድ ሺህን ዘሎ ለዐሥር ሺህ የ፼(እልፍ) ምልክት (symbol) መስጠት አግባብ አይደለም› የሚለው ሐሣብ ለይስማዕከ ዋና መከራከሪያው ነው፡፡ የእሱን ቃል እንደነበረ ብንጠቀሰው መከራከሪያ ነጥቡ ግልፅ ይኾንልናል፡፡

‹የግዕዝ አቆጣጠር… ለእያንዳንዱ መራሂ ቁጥር (ለምሳሌ ፲፣፳፣፴…፻…) የራሱ ምልክት አለው እንጂ (ከመሠረታዊ ቁጥሮች በቀር) ቁጥሮችን በማገጣጠም አይጠቀምም፡፡ ለመቶ (፻) ምልክት እንዳለው ሁሉ ለሺህም ምልክት ያበጃል እንጂ ዐሥር(፲) እና መቶ(፻) አጣምሮ ምልክት አያበጅም፡፡ ለሺህ ምልክት ሳያበጅ ለዐሥር ሺህ ምልክት ያበጃል ብሎ ማመንም አጉል ነው፡፡ እንደዚያ ከኾነማ ለሃያ ሺህም ቀጥሎ ላሉትም ምልክት ሊያስፈልግ ነው፡፡ ሺህን ዘሎ ለዐሥር ሺህ ፼(እልፍ) የሚባል ምልክት (symbol) ያበጃል ብዬ ማመንም በግሌ ይቸግረኛል፡፡ የሚያሳምነኝም አጥቼ ትቸዋለሁ፡፡› በማለት የራሱን ማሰማኛ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡

በተለይም፡-

1)  ‹በመጽሐፍ ቅዱስ ‹እልፍ› የሚለው ቁጥር አንድ ሺህም ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ እብራይስጥ፣ ዐረብና ትግሬም እልፍ ብለው የሚጠሩት አንድ ሺህን ነው፡፡› የሚለውን የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ሐሣብ እና

2)  ›እልፍን ዐሥር ሺህ እየተባለ መጠቀም የመጣው የጥንታዊ ትምህርታችን እየተዘነጋ፤ የተዘበራረቀ አጠቃቀም ተለምዶ ነው፡፡› የሚሉ ነጥቦችን መከራከሪያዎቹ አድርጓቸዋል፡፡

፬. ባቀረባው መከራከሪያ ላይ የሚኖረኝ ትችት

‹የግዕዝ አቆጣጠር ለሺህ ምልክት ሳይሰይም ለዐሥር ሺህ እልፍ(፼) ምልክት ማበጀቱ ትክክከል ነው ወይስ አይደለም?› የሚለውን መከራከሪያ ከታች አሳማኝ ማረጋገጫዎችን የማቀርብበት ስለኾነ ላቆየውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላነሳቸው የመከራከሪያ ጥቅሶች ማስተካከያ ነጥቦች ላቅርብ፡፡

 1. መጀመሪያ መታወቅ የሚኖርበት እልፍ አንድ ጊዜ አንድ ሺህ ሌላ ጊዜ ዐሥር ሺህ ተብሎ መጠቀሱ ግልፅ የኾነ አጠቃቀስ አለመኖሩን ያመለክታል እንጂ ‹አንድ ሺህ› ለመሆኑ ማስረጃ አይኾንም፡፡ ይህም ትክክለኛውን መርምረን ለማወቅ እንድንጥር ይጋብዘናል:: ለክርክሩ ከኾነ ግን አእላፍንም ‹አንድ ሺህ ነው› ብሎ መሟገት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ይስማዕከ እንዳስቀመጠው ከኾነ  በ‹ዘጸአት ፳፬፥፯ ‹ወይገብር ምሕረተ ላዕለ አእላፍ› (ምህረቱን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ…) ስለሚል አንድ ሺህ አእላፍ ተብሎ ተገልጽዋልና፡፡ እንዲሁም መ. ይትባረክ ባደረጉት ጥናት ውስጥም እልፍን መቶ ሺህ(ሰዋሰወ ቀመር ገጽ 31) ነው በማለት ያስቀመጡ አባት አሉ፡፡  ስለዚህ የእልፍ በተለያየ መልክ መጠቀስ የአበውን የቁጥር አጠቃቀም ስልት እንዲንመረምር ይጋብዘናል እንጂ ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ብለን ለመወሰን በቂ ምክንያት አይኾንም፡፡ እና አበው ለምን አንድ ሺህን እልፍ እያሉ ይጠሩታል?
 1. እልፍ፣ አእላፍ… የመሳሰሉት አሐዞች ብዙን ጊዜ ብዛትን አመልካች ኾነው ይቀርባሉ፡፡ ለዚህም በትንቢተ ዳንኤል ፮፥፲ ‹ወየአውድዎ እልፍ ወትእልፍተ አእላፋት› ማለትም ‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ አእላፈ አእላፋትም በፊቱ ይቆሙ ነበር፡፡› በሚል የተገጸው የብዙህነት ማሳያ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ እንዲሁም አለቃ ክዳነወልድ ክፍሌ ለ‹እልፍ› አማራጭ ትርጉም ሲሰጡ ‹ብዙ፣ እጅግ፣ ዐያሌ› ማለት ነው በማለት እንደማሳያ በዘዳግም ፯፥፲ ‹ወእገብር ምሕረተ እስከ እልፍ ትውልድ ለእለ ያፈቅሩኒ› ማለት ‹ለሚወዱኝም… ምሕረቴን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የምጠብቅ…› የሚለውንና ሌሎች ጥቅሶችንም በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በተለይ ‹እልፍ›ን ብዙ ለማለት ‹የአንድ ስንደና የገብስ ዛላም ከፍሬው ብዛት የተነሣ እያንዳንዱ ራስ እልፍ ይባላል፡፡› በማለት ‹የስንደ ዛላ እፍኝ ይሞላ፡፡› የሚለውን ተረት ተርተዋል፡፡ በመሆኑም ‹እልፍ› ኾነ ‹አእላፍ› የሚለው ብዛትን ለማመልከት አንድ ሺህን ሊወክል ይችላል፡፡
 1. በግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እልፍ አንድ ሺህን ወክሎ የተገኘበት ምክንያት ምናልባት በመጻሕፍት ትርጓሜ ጊዜ የእብራስጥ ወይም የዐረብ ቋንቋ ተጽዕኖ መኖሩን ማሳያ ኾኖ የቀረ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የተተረጎመበትን ቋንቋ በመጠቀም የመጻሕፍት አተረጓጎም ምሥጢርን ለመጠበቅ የሚደረግ ስልት ነው፡፡ ይህንንም በመዝሙረ ዳዊት ፻፲፱(119) የተቀመጡትን የአምላክ መጠሪያ ስሞች (በእብራይስጥ) በቀጥታ ተወስደው (በቁም) መተርጎማቸውን እንደ ምሳሌ ወስዶ በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ከተተረጎበት ቋንቋ ተጽዕኖም አንጻር ይታያል፡፡
 1. ድፍረት ባይኾንብኝ ይስማዕከ አውቆም ይሁን ሣያውቅ (በታይብ ስህተት የተነሣም ሊኾን ይችላል) ትክክለኛውን ትርጉም ወይም አገላለጽ  በአግባቡ ያልላስቀመጠባቸው አገላለጾችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-

v  በአግባቡ የተተረጎሙትን እንደተሳሳቱ በመቁጠር፡- ‹ነገሥት ካልዕ ፲፱፥፴፭ ‹ወቀተለ፡ እምተዓይኒሆሙ ለአሦር ዐሥርተ ወስምንተ እልፈ  ወሃምሣ ምዕተ፡፡› (ሰረዝ የተጨመረ) የሚለው በአሐዝ ሲጻፍ ፲ወ፰፼ወ፶፻ ይሆናል፡፡ የአማርኛው ትርጉሙም ይስማዕከ እንዳስቀመጠው ‹ከአሦራዊያን ወገን መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፡፡› ማለት ነው፡፡ እና በዚህ ‹እልፍ› ዐሥር ሺህ ነው ወይስ አንድ ሺህ? በግልፅ ዐሥር ሺህን ወክሎ ነው የተጻፈው፡፡ ይስማዕከ ግን አንድ ሺህን እንደሚገልጽ አድርጎ ነው ያብራራው፡፡ ምንም እንኳን ምሳሌውን ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወሰድኩት ቢልም ትክክል አይደለም፤ አለቃ እንደማስረጃ የወሰዱት ሌላ ነው፡፡ እንዲህ ይላል አለቃ የጠቀሱት (እልፍ አንድ ሺህ ተብሎ የተጠቀሰበት) ማስረጃ ‹‹ከዐረብ ቋንቋ የተቀዳው መጽሐፈ ቄርሎስ በመዠመሪያው ክፍል ‹ምእተ ወሰማንያ ወኀምስት እልፈ› ይላል፡፡›› (ሰረዝ የተጨመረ)፡፡ ትርጉሙም ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፡- መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ፡፡  የሁለቱን አገላለጽ ልዩነት ግን ልብ ይሏል፡፡ በሁለተኛው ጥቅስ ትርጉሙ ላይም የዐረብኛ ተፅእኖ መኖሩን መረዳት ይቻላል፡፡

v  አግባባዊ ያልኾነ ጥቅስ አጠቃቀም፡- በራዕይ ዮሐ. ፯፥፭ ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፡፡ የሚለውን በግዕዙ ‹እም ውስተ ሕዝበ ይሁዳ ፪፼ ወ፳፻› ይላል በማለት አስቀምጦታል፡፡ እኔ የአገኘሁት የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‹እለ እምውስተ ሕዝበ ይሁዳ ፼ወ፳፻…› ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ይህ አሐዝም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን ለሁሉም ነገደ እሥራኤል ዐሥራ ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ እስከ ቁጥር ፰ ድረስ ተጠቅሷል፡፡ የቁጥሩ የአማርኛ ትርጉምም ‹አሥራ ሁለት ሺህ› ማለት ነው፡፡ የዚህን ምሥጢር ደግሞ አስረስ የኔ ሰው ‹የካም መታሰቢያ› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 11 ፈታተው አሳይተውታል፡፡  ስለዚህ ይስማዕከ የተሳሳተ የግዕዝ ቁጥር ተጠቅሟል ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም እሱ ወደሚፈልገው እየጎተተው ነው እንዴ? ለማለት ሁሉ ዳድቶኛል፡፡ ምናልባት ትክክል ነው የሚል ከኾነ ከየትኛው የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ እንደጠቀሰው ቢጠቁመን ስህተቱ ከምን እንደኾነ ለመመርመር ያስችለናል፡፡ የታይፕ ስህተት ከኾነ ግን ይቅርታ! ማስተካከል ግን ይገባል፡፡

 1. ይስማዕከ ያቀረባቸው የመከራከሪያ ጥቅሶች አብዛኞቹ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍል ‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› መጽሐፍ (ገጽ ፪፻፳፬) የተወሰዱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ደግሞ እልፍ(፼) ዐሥር ሺህ መሆኑን በማብራራት የጻፉ ናቸው፡፡ በእብራይስጥና በዐረብም ‹እልፍ አንድ ሺህ ነው› ያሉት የእነዚህ ቋንቋዎች ሊቅ ስለነበሩ አነጻጽረው ለማስረዳት ነው፡፡ ስለዚህ ይስማዕከም ይህንን በአግባቡ ቢመለከተው መልካም ይመስለኛል፡፡

፭. እልፍ(፼) ዐሥር ሺህ ስለመሆኑ ማሳመኛዎች፡-

በትክክልም ይስማዕከ እንደጠቀሰው እልፍ(፼) ‹አንድ ሺህ ነው› ወይስ ‹ዐሥር ሺህ› የሚለው አከራካሪ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን የተወሰኑ ግራ መጋባቶች ቢኖሩም በግልፅ የምናያቸው መረጃዎችና የግዕዝ ቁጥር አፈጣጠር ግን በትክክል የሚያስረዱት የእልፍን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ ለዚህም ከዚህ በታች የተጠቀሱት ማሳያዎች ማረጋገጫ ይኾኑናል፡፡

 1. የግዕዝ አሐዝ ዕድገት የራሱ የኾነ አመክንዮአዊ አካሔድ አለው፡፡ እልፍም ይህን አሐዛዊ አመክንዮ ተከትሎ መጠሪያውን ያገኘ ነው፡፡ ሺህ የተባለው የቁጥር ስያሜ ግን ከዐረበኛው (ከሌሎች) የቁጥር አጠቃቀም ጋር ለማጣጣም ተብሎ ኋላ የተሰየመ ይመስላል እንጂ የግዕዝ ቃል አይደለም፡፡ ለዚህም ‹ሸ› የሚባል የፊደል ‹ሆሄ› በግእዝ የፊደል ገበታ ውስጥ አለመኖሩ ምስክር ይሆናል፡፡

የግዕዝ አቆጣጠር አካሔድ ማሳያ ሰንጠረዥ

አኀዝ በግዕዝ ሲነበብ በአማርኛ ትርጉሙ አመክንዮአዊ አካሔዱ
አሐድ (አሐዱ) አንድ 1
ክልኤት ሁለት 2
ሠለስት ሦስት 3
አርባዕት አራት 4
ኀምስት አምስት 5
ስድስት ስድስት 6
ሰብዐት ሰባት 7
ሰመንት ስምንት 8
ተስዐት ዘጠኝ 9
የአንድ ቤት ጨረሰ፡፡ በኢትዮጵያ ዜሮ (አልቦ) የሌለ ነገርን ስለሚወክል ተቆጣሪ ኾኖ ውክልና አልተሰጠውም ማለት ይቻላል፡፡
ዐሥርት ዐሥር 1X10
ዕሥራ ሃያ 2×10
ሠላሳ ሠላሳ 3×10
አርብዓ አርባ 4×10
ኀምሳ ሐምሳ 5×10
ስሳ ስልሳ= ስድሳ 6×10
ሰብዓ ሰባ 7×10
ሰማንያ ሰማንያ 8×10
ተስዓ ዘጠና 9×10
ምእት መቶ 10×10=100
እዚህ ላይ ዐሥር እጥፍ በመሆኑ የአንድ ቤትን በዐሥር ቤት ማብዛት ዝርዝርነቱን ጨርሷል፡፡ ስለዚህ ዝርዝር የኾነውን የአንድን ቤት በውስጠ ታዋቂ ይዘን የዐሥር ቤት እስከሚያልቅ (እጥፍ እስከሚኾን) ቀጥለን እንይ፡፡
፲፻ ዐሥርቱ ምእት ዐሥር መቶ= ሺህ 10×100
፳፻ ዕሥራ ምእት ሃያ መቶ=2ሺህ 20×100
፴፻ ሠላሳ ምእት ሠላሳ መቶ=3 ሺህ 30×100
፵፻ አርብዓ ምእት አርባ መቶ=4ሺህ 40×100
፶፻ ኀምሳ ምእት አምሳ መቶ=5ሺህ 50×100
፷፻ ስሳ ምእት ስልሳ መቶ=6ሺህ 60×100
፸፻ ሰብዓ ምእት ሰባ መቶ=7ሺህ 70×100
፹፻ ሰማንያ ምእት ሰማንያ መቶ=8ሺህ 80×100
፺፻ ተሰዓ ምእት ዘጠኝ መቶ=9ሺህ 90×100
፻፻=፼ እልፍ መቶ መቶ=10ሺህ 100×100=10000
እዚህም ላይ መቶ እጥፍ መኾን መቻሉን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ የተነሣ አዲስ ስያሜ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚያም ነው ዐሥር ሺህ  ‹እልፍ› የተባለው፡፡ ከዚያ በፊት ባሉት (ለምሳሌ በሺህ) ስያሜ (ምልክት) መስጠት አያስፈልግም፤ እጥፍ መኾን አልቻለምና፤ ዐሥርቱ ምእት(፲፻) የሚለውም መወከል ችሏልና፡፡

ከሰንጠረዡ አመክንዮአዊ የመራሔ ቁጥር አሰያየምና የቁጥር ዕድገት ስልት መረዳት የምንችለውም እልፍ የዐሥር ሺህ ምልክት መኾኑን ነው፡፡ የግዕዝ አቆጣጠር ከእልፍ በላይ ባሉት ቁጥሮች አጨቃጫቂነት ይታይበታል፡፡ አስተማማኝ ጥናትም ስለሚጠይቅ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቢያለሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ተነሣሁበት ነጥብ በመመለስ እልፍ ዐሥር ሺህ መሆኑን ወደሚያረጋግጥ ተጨማሪ ነጥብ ልለፍ፡፡

 1. በግዕዝ ቁጥር ውስጥ ትልቁ ነፃ (ነጠላ) ምልክት ያለው ቁጥር መቶ(፻) ነው፡፡ የእልፍ ምልክት(፼) የሁለት መቶዎች (ምእታት) ብዜት እንጂ ራሱን የቻለ ነጠላ ምልክት አይደለም፡፡ ከሌሎቹ ተጣማሪ ምልክቶች የሚለየው በአንድነት መታሠሩ (፻፻=፼) እና መጠሪያው ነው፡፡ ከሌሎች በተለየ የተጣመረበት ምክንያት ምናልባት በጥንት ጊዜ አጻጻፍ በተከታታይነት ከሚቀመጡ ሁለት የመቶ አሐዞች ጋር እንዳያምታታ በሚል ጥቅም ላይ የዋለ ይመስላል፡፡ ለዚህም የኢዛና ሐውልት የአሃዝ ጽሑፎችን (ለምሳሌ፡ Ö፼â፻፻á=25140) ማየት ማረጋገጫ ይሆነናል፡፡ ስለሆነም እልፍ የሚለው የሁለት መቶ አሐዞች ጥምረት መቶ ጊዜ መቶ መሆኑን በግልጽ ይመሰክራል፡፡ ምናልባትም የይስማዕከም ስህተት እልፍ የሁለት መቶዎች ጥምረት መሆኑን ያለመገንዘብ ችግር ይመስለኛል፡፡ እንደ እኔ ግንዛቤ ይህንን የተረዳ ሰው የእልፍ ምልክት አንድ ሺህን ይወክላል ብሎ ለመከራከር አይደፍርም፡፡ ስለዚህ እልፍ ዐሥር ሺህ መኾኑን በዚህ ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
 1. የተደረገ ጥናትም የሚያረጋግጠው የእልፍ(፼)ን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ በመ.ይትባረክ ገሠሠ መራ የተዘጋጀው ‹ሰዋሰወ ቀመር› በሚለው የጥናት መጽሐፍ የተጠየቁት መምህራን ይህንን አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህ የእልፍ ዐሥር ሺህ መኾንን በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የመጻሕፍት፣ የቅኔና የቁጥር መምህራን የተስማሙበት ነው፡፡ የጥናት ውጤቱንም በጥቅል መልክ በሰንጠረዥ ስናስቀምጠው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ (መጽሐፉን ያገኘ ከገጽ 21-44 ያለውን ይመልከት)

የሊቃውንት የእልፍ ውሳኔ ማሳያ ሰንጠረዥ

ተ.ቁ ጥናቱ የተካሔደበት ሥፍራ ብዛት እልፍ ላይ ያለው ውሳኔ
አንድ ሺህ ዐሥር ሺህ
1 አክሱም 3 2 1
2 ተምቤን 1 0 1
3 መቀሌ 1 0 1
4 ደሴ 2 0 2
5 ሐዋሳ 2 0 2
6 ሐረር 2 0 2
7 ድሬደዋ 3 0 3
8 ደብረ ማርቆስ 1 0 1
9 ባህር ዳር 2 0 1 (አንዱ መቶ ሺህ ነው ብለዋል፡፡)
10 ዲማ 2 ? 1
11 ጨጎደ፣ አዳማ 1 0 1
12 ጎንደር 5 1 3 (አንዱ አባት ውሳኔያቸውን ሳያሳውቁ ሞተዋል)
13 አዲስ አበባ 7 0 7
14 ቤተ ክህነት 3 0 3
ድምር 35 3 29
ያልተወሰነ 3

ከዚህ በላይ ባለው ሰንጠረዥ መረዳት እንደሚቻለው ከተወሰኑት (9%) በስተቀር አብዛኝቹ መምህራን(83%) ‹እልፍ ዐሥር ሺህ ነው› የሚለውን የሚደግፉ ናቸው፡፡ በእውነት የራሳችንን ምኞት እንከተል ካላልን በስተቀር ከእነዚህ የቅኔ፣ የመጻሕፍትና የቁጥር ሊቃውንት የበለጠ ስለ ግዕዝ ቁጥር አመጣጥና ስለ እልፍ አሰያየም ዐውቀን ለማረም የምንችል አይመስለኝም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እነ አስረስ የኔሰው፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበጊዮርጊስ እና መሰል የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሊቃውንት በየመጻሕፍታቸው የእልፍን ዐሥር ሺህነት መሰከሩ እንጂ አንድ ሺህ ነው በማለት አልጻፉም፤ አልተከራከሩም፡፡ ለምሳሌ አስረስ ኔሰው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ‹የጥንት ፊደላችን በአልፋ ቤት (አ) ይጀምር ነበር› ብለው መጻፋቸውን ነቅፈው በሀሌታ ‹ሀ› መጀመሩን ለማሳየት መጽሐፍ ጽፈዋል፡- ‹የካም መታሰቢያ› እና ‹ትቤ አክሱም መኑ አንተ?› የሚሉ፡፡ በእልፍ ጉዳይ ላይ ግን የነበራቸው አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ደግሞ እንደ ተራ ምሁር የሚታዩም አይደሉም፡- የዕውቀት ውቅያኖሶች እንጂ፡፡ ስለዚህ በእልፍ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም የነበራቸው ከጥንት ጀምሮ የእልፍ ምልክት(፼) ዐሥር ሺህን መወከሉ የተረጋገጠ ስለነበር ነው፡፡

 1. የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አጻጻፍም የሚነገረን የእልፍ(፼)ን ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡  የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ዓመተ ዓለምን እስከ ስምንት ሺህ ዓመተ ምህረትን ደግሞ እስከ ሁለት ሺህ ድረስ አድርሶታል፡፡ በእኒህ የዓመታት አጠቃቀስም ሺህን እልፍ በማለት ያስቀመጠ የለም ማለት ይቻላል፤ ይልቁንም በምእት(በመቶ) ቤት (ለምሳሌ ፲፻፣ ፳፻፣ ፴፻…) ነው የሚገለጸው፡፡ በተለያዩ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎች በእልፍ የተገለጸ የዓመታት አጻጻፍ አይታይባቸውም፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ በቀላሉ እንኳን በዐጼ ቴዎድሮስ (የእነ አለቃ ዘነብን)፣ በአጼ ምኒሊክ (በአማርኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ሰዋሰው፣ የአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስን ጦቢያ…)፣ በንግሥት ዘውድቱ (መንፈሳዊ መጻሕፍት) የንግሥና ዘመናት እንዲሁም በቀ/ን/ነ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያዎቹ የንግሥና ዓመታት የታተሙ መንፈሳዊና ዓለማዊ መጻሕፍትን የኅትመት ጊዜ አጻጻፍ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እልፍ አንድ ሺህ ቢኾን ኖሮ ፲፰፻፣ ፲፱፻… እያሉ ከመጻፍ ይልቅ ፼፰፻፣ ፼፱፻… እያደረጉ መጻፍ በተለመደ ነበር፡፡ ልብ ይበሉ እልፍ(፼) ለዓመታት መጻፊያ ኾኖ ያልተጠቀሰው ከስምንት ሺህ በላይ በመውጣት በዐሥር ሺህ የሚጻፍ ዓመት ስለሌን ነው፡- በመንፈሳዊ አቆጣጠር፡፡ ደግሞስ ዓመተ ምሕረትን ብቻ እንኳን በሺህ መጻፍ ከጀመርን ከሺህ ዓመት በላይ ኾኖን ሳለ ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ እልፍን አንድ ሺህ አድርገን ካልጻፍን ብለን እንዴት እንዳአዲስ ልንሟገት እንችላለን?
 1. ከዓመታት አጻጻፍ ሌላ ከዐሥር ሺህ በላይ የኾኑትን አብዛኞቹን ቁጥሮች ግን በእልፍ ተጽፈው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌም ዮሐ.ራዕይ ፯፥፬ ‹ወሰማዕኩ ኁልቆሙ ለእለ ተኀትሙ ፲ወ፬፼ወ፵፻›፡- ትርጉሙ ‹ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።›፤ ዘዳግም፲፪፥፴፯ ‹ወግዕዙ ደቂቀ እሥራኤል እምራምሴ ውስተ ሰኮታ ፷፼›፡- የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ።፤ ራዕይ ዮሐንስ ፯፥፬-፰ ያሉ ቁጥሮች…የመሳሰሉት ጥቅሶች  ዐሥር ሺህን በእልፍ ምልክት መግለፅ የተለመደ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
 1. ከኹሉም በላይ በአፄ ኢዛና የድል ሐውልት ላይ ተጽፈው የሚገኙ የግዕዝ ቁጥሮች የእልፍን ዐሥር ሺህ መኾን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌም ‹…ለስድስቱ ነገሥት ፪፼፶፻፻፵ ለህመ› ይላል፤ ይህንንም ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ‹…ለስድስቱ ነገሥታት 25140 ሠንጋ ሠጠን፡፡› ብለው ተርጉመውታል፡፡ እንዲሁም ሌላ ‹…ምህርካ ፫፼፲፻፱፻፶፯ ለህም…› የሚል አሐዝ አለ፤ ይህም ቁጥር ‹30957›ን የሚወክል መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡  በሐውልቱ ላይ ሌሎች የግዕዝ ቁጥሮች ስላሉ የበለጠ በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ኾኖም ከላይ በተ.ቁ. 2 እንደተጠቀሰው ከአሁኑ አጻጻፍ ጋር ልዩነት መኖሩንም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስናቸው የሐውልት ቁጥሮች በአሁን ጊዜ አጠቃቀም የተጻፉ ቢኾኑ ኖሮ የመጀመሪያው ፪፼፶፩፻፵፣ የሁለተኛው ደግሞ ፫፼፲፱፻፶፯ ዓይነት አጻጻፍ ይኖራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ የእልፍ(፼) ቁጥርን ዐሥር ሺህ መኾን ታሪካዊ ማስረጃዎች ሁሉ ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡

በእኔ በኩል ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች እልፍ ዐሥር ሺህ ለመሆኑ አሳማኝ መከራከሪያዎችን ያቀረብኩ ይመስለኛል፡፡ አሳማኝ መከራከሪያ እንኳን ማቅረብ ባልችል እልፍን አንድ ሺህ አድርጎ ለመጠቀም ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ውድቅ የሚያደርግ ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ያለበለዚያ የእኛን የቁጥር አካሔድ በውጭዎች ስልት እየመዘንን መለዋወጡ አግባብ አይመስለኝም፡፡

  ፮.ማሣረጊያ

እኔ እንደማምነው ከኾነ ምንም እንኳን አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም የባህላዊ አስተምህሯችን በትውፊት ተያይዞ እኛ ጋር ደርሷል፤ የእልፍ  ትክክለኛ ስያሜ ምልክትም እንደዚሁ፡፡ አሁን ያለው የሀገራችን የአስተምህሮ ችግር ከዐጼ ምኒልክ በኋላ የዘመናዊ ትምህርት አስተምህሮ ውጫዊ (የአውሮፓን አስተምህሮ መሠረት ያደረገና ሀገር በቀል የሆኑ ትምህርቶችን ያቃለለ) መኾን ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ይህ ግን በዘመናዊ አስተምህሮ አካባቢ ያለውን አካሔድ የሚመለከት እንጂ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የበረዘ (ተጽዕኖው ቢኖርም) አይመስለኝም፡፡ የእኛ የጥንታዊ አስተምህሮ ደግሞ ያለው በእነዚህ ተቋማት (በአብነት ት/ቤቶች) ነው፡፡ እንዲሁም  የተለያዩ የቆዩ የብራና መጽሐፎች በውጭም ኾነ በሀገር ውስጥ መኖራቸው የጥንታዊ የቁጥር ስያሜ በአግባቡ ተመዝግበው ስለመገኘታቸው ማረጋገጫ መኾን ይችላሉ፡፡ የእልፍ አሐዝ ስያሜም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የእልፍን ስያሜ ድንገት ዛሬ ተነስተን የፈጠርነው አለመሆኑን መረዳት አለብን፡፡

ይስማዕከም በጥቅሉ እልፍ አንድ ሺህ ነው በማለት የመከራከሪያ ነጥብ ማንሳቱ መልካምና የሚደገፍ ቢኾንም ጥናት ላይ ሳይመሠረት በራሱ ውሳኔ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ግን ትክክል አይመስልም፡፡ ምክንያቱም የእልፍን አንድ ሺህነት የሚያመለክቱ የመጻሕፍት የኅትመት መግለጫዎች የሉም፡፡ የቆዩ የብራና መጻሕፍትም ዓመተ ዓለምንና ዓመተ ምህረትን በእልፍ (አንድ ሺህ አድርገው) የገለጹ አይመስለኝም፡፡ የጥንት የብራና መጻሕፍትም እልፍን አንድ ሺህ በማድረግ ቢያስቀምጡ ኖሮ ቢያንስ ዐጼ ኃ/ሥላሴ እያስተረጎሙ እንዲታተሙ ባደረጓቸው የአንድምታ መጽሐፎች ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ መጽሐፎቹ የሚመሰክሩት የእልፍን(፼) ዐሥር ሺህ መኾን ነው፡፡ ስለዚህ የ‹እልፍ› ምልክት(፼) ዐሥር ሺህን መወከል የታመነባትና አግባብነት ያለው ነው፡፡ ለማንኛውም ይሰማዕከ ይህንን ጉዳይ በማንሳቱና እኔም እንድጽፍ ምክንያት ስለኾነኝ እግዜር ይስጠው፡፡

Please follow and like us:
error