እኔ አምላክን ብኾን

(በካሣሁን ዓለሙ)

እኔ አምላክን ብኾን

የሚበላ የሚጠጣው፣

የሚያይ የሚያደንቀው፣

ሰማይና ምድርን የያዙትን ኹሉ፣

ረቂቅ ግዙፋን ፍጡራን የተባሉ፣

አዘጋጅቼለት!

ባፈር ቡኮ ጭቃ በጄ አሠማምሬ፣

እስትንፋሰ ነፍስን ማወቂያ ጨምሬ፣

ክፋት ደግነትን ለማመዛዘኛ፣

አእምሮ አበልፅጌ አድርጌም መለኛ

ሰው አልፈጥርም ነበር!

እኔ አምላክን ብኾን!

 

እኔ አምላክን ብኾን!

እኔ አምላክን ብኾን!

ብፈጥረውም እንኳን እንደዚህ አድርጌ፣

ፈጣሪን ከፍጡራን፣

መለያ የሥልጣን፣

አልሰጠውም ነበር ትዛዜን ደንግጌ፤

እኔ አምላክን ብኾን!

 

እኔ አምላክን ብኾን

እኔ አምላክን ብኾን!

ምናልባት አክብሬ ትዛዜን ብሰጠው፣

የእኔን ቃል አቃሎ፣

ቆሻሻ ላይ ጥሎ፣

የፈጣሪነቴን ኪዳን ካፈረሰው፣

እንኳን ሰውንና የጣሰውን ሕጌን፣

የቅዱስ ኪዳኔን፣

ትክክል መንገዴን፣

አናንቆ አርክሶ ያቀለለ ክብሬን!

ለእሱ የተሠራ፣

በእሱ የተጠራ፣

ፍጡር የተባለ፣

ለድንቀት ለምግብ ለሰው ልጅ የዋለ፣

አጠፋበት ነበር ካለም ላይ እንዳለ፤

እኔ አምላክን ብኾን!

 

እኔ አምላክን ብኾን

እኔ አምላክን ብኾን!

ባላጠፋው እንኳን የጠፋን/ያጠፋን/ ፍለጋ፣

አይወሰን ክብሬን ምሉዕ ኩሉ ፀጋ፣

ከአርያም በላይ

ከበርባሮስ በታች የሚገኝ አካሌን

በሙሉዕ እንዳለ ወስኜ በሥጋ፣

ሰው አልኾንም ነበር!

እኔ አምላክን ብኾን!

እኔ አምላክን ብኾን

እኔ አምላክን ብኾን!

ጭራም ሰውን ኾኜ ጥፋቱን ነግሬ፣

በፍቅር በእውነት ክብሩን አስተምሬ፣

ታምር እየሠራሁ ከፊት እየመራሁ፣

የበጎ ምግባርን ሠርቼ እያሳየሁ፣

ወደ እኔ ለጠራው?

ጭራሽ! ፍቅሬን ጠልቶ እውነቴን አብሎ፣

ታምሬን አዋርዶ መንገዴን አጥፍቶ፣ ክብሬን አጣጥሎ

የሽፍትነት ተግባር በእኔው ላይ ሲሠራ፣

ይዞ አሥሮ በጥፊ ሲመታኝ ሳይፈራ፣

በጨከነ ስሜት በደነደነ ልብ፣

አካሌን ሲያቆስል ይዞም ሲደበድብ፣

ሰቅሎም በመስቀል ላይ፣

በጦር እየወጋ ምራቅ እየተፋ ሲዘብትብኝ ሳይ፤

ችዬ ዝም ልለው?

ጭራሽ! በእኔው ቁስል ባካሌ ደም መፍሰስ፣

ቆስዬ ደምቼ እሱኑ ልፈውስ?

‹ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰባቅታኒ› ብዬ በጽሞና፣

ይቅር እንዲባል ስል ላቀርብ ልመና?

እያየ እያሰበ የሠራውን በደል፣

በሚስማር ቸንክሮ ፈጣሪውን መስቀል፣

ሳያውቅ ነውና ይቅር ከራሴው ልል?

በሠራሁት ሸክላ ባበጀሁትም ገል

መሥዋዕቱ ኾኜ በራሴው ልገደል?

እኔ አምላክን ብኾን!

 

እኔ አምላክን ብኾን

እኔ አምላክን ብኾን!

እንኳን ሰውን ኾኜ ሞቸለት ልቀበር፣

በእኔ የሚዘብት የሰው ልጅ በማፍቀር፣

በጠቅላላ ነገር፣

ሰው አልፈጥርም ነበር

እኔ አምላክን ብኾን

እሱ ግን!…

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !

አሜን!

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply