እውን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም? (2)

(ባለፈው ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና መኖርና ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም› የሚሉ ተከራካሪዎች የሚቀርቡትን መከራከሪያ በጥቅል በማቅረብ ጽሑፉ አቁሞ ነበር፤ ከዚያ የቀጠለው ተከታይ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1.  የመተቻቸትና የመወያየት ባህል አለመኖር

  1.   በአፍሪካ ውስጥ በፍልስፍና ዙሪያ በሀገሮች መካከል የሚደረግ የመተቻቸትና የመከራከር ባህል የለም፡፡
  2. የመተቻትና የመከራከር ባህል በሌለበትም ፍልስፍና አይኖርም፡፡
  3. ኢትዮጵያም ውስጥ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡
  4. ስለሆነም የፍልስፍና ባህል በአፍሪካ ውስጥም ሆነ በኢትዮጵያ የለም፡፡

ይህ ክርክር ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም› የሚሉ ምሁራን አመክንዮአዊ አቀራረብን የተከተለ አንደኛው መከራከሪያቸው ነው፡፡ እውን ግን ይህ አሳማኝ ነው? አሳማኝነት ያለው ለመሆን የአቀራረብ ትክክልነት ብቻ ሳይሆን ይዘቱም እውነት መሆን ይኖርበታል፡፡ እውን የቀረበው ትክክልና እውነት ነው ወይ? ብሎ መፈተሸ ግድ ነው፡፡ በአጭሩ እውን የመተቻቸትና የክርክር ባህል የለንም ወይ? የትችትና የክርክር ባህል ያለን ከሆንን ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም› የተባለበት ምክንያት ስህተት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ባህል የሌለን ከሆንም ፍልስፍና ለመኖር የትችት ባህል መኖር ዋሳኙ መሆኑ ወይም አለመሆኑ መመዘን አለበት፡፡

ከተነሳሁባት ርዕስ አንጻር ፍልስፍና በአፍሪካ ምን ዓይነትና አተያይና መመዘኛ እንዳለውና ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ፈልቆ በግብፅ በመፍሰስ ዓለማችንን እንዴት እንዳጥለቀለቀ ከታሪካዊ ማስረጃዎችና ፅንሣተ ሐሣባት ማሳያዎች ጋር በማነጻጸር በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ የዚህ ሙግት እንብርትም ‹አፍሪካ የፍልስፍና ምንጭ ነበረች አይደለችም የሚል ሳይሆን በአፍሪካ የትችትና የክርክር ባህል ባለመኖሩ ፍልስፍና የለም› የሚል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ‹እንኳን የክርክርና የትችት ባህል የለንም ሊባል ዋናዋ የፍልስፍና እና የሥልጣኔ መነሻዋና አስተማሪዋ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ሀገራችን አይደለችም ወይ?› የሚል አተያይ ትልቁ መከራከሪያ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ካለ በአፍሪካ ያለውን የፍልስፍና አተያይና ልምድ መዳሰስ ሰፊ ሐተታ ስለሚፈልግ በሌላ ጊዜ መመለስ የተሻለ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩልም ቢሆን ‹የሥልጣኔና የፍልስፍና አስተምህሮ ምንጫ አፍሪካ አይደለችም› ከተባለም ክርክሩ የጥንታዊ መዛግብትንና ሌሎች ማስረጃዎችን ማየትንና የተጠየቅ ሙግትን ስለሚጠይቅ ራሱን ችሎ ማየቱ ተመራጭ ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ለጠቅላላ ግንዛቤ Stolen Legacy: Greek Philosophy is Stolen Egyptian Philosophy  እና A companion to African philosophy  የሚሉ መጽሐፎችን ማየት ጠቃሚ መመሆኑን ጠቁሜ በማለፍ የአፍሪካን ጉዳይ እዚህ ጋር አቁሜ ወደ ኢትዮጵያችን ልመለስ፡፡

በመጀመሪያው መጣጥፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸው ዶ/ር ፍቅሬ እንደታዘቡት የ‹የለም› ተሟጋቾች ትችት የራስን ሳይረዱ የማንኳሰስና ቀድሞውንም ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም ብሎ የመገመት አባዜ የተጠናወተው ሆኖ እንጂ እነሱ እንደሚሉት የትችትና የክርክር ባህል የሌለን ሕዝቦች አይደለንም፡፡  ለዚህ የሚሆኑ ማሳያዎች የሚሆኑ ነጥቦችን ላቅርብ፡፡

ከዚያ በፊት ግን መታወቅ ያለበት የመተቻቸት ባህል ከዕይታዎች ውስጥ የተሻለውን አንጥሮ ለማውጫና የተሻሉ ዕይታዎች እንዲገኙና እንዲዳብሩ ለማድረግ ይረዳል እንጂ ትችት ከሌለ ወንበር ያለው ፍልስፍና ሊኖር አይችልም ማለት ገልብጦ መናገር ይሆናል፡፡ ትችት የፍልስፍና ዕድገትና ሁኔታ መመዘኛ ነው እንጂ ብቸኛው የፍልስፍና መኖር ወሳኝ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ አስተውሎትና ልምድ ያለ ትችት አስደናቂ የፍልስፍና ዕይታዎችን ሊያስገኙ ይችላሉ፡፡ የመተቻቸት ባህል ስላላደበርን የሀገራችን ፍልስፍናዊ አስተምህሮ ነጥሮ መውጣት አልቻለም ማለት አንድ ነገር ነው፤ ስለማንተቻች የራሳችን ፍልስፍና ሊኖረን አልቻለም ማለት ደግሞ ሌላ ነው፤ የሁለቱ አቀራረቦች የቅርንጫፍና የግንድን ወይም የመሠረትና የግድግዳ ያህል ልዩነት አላቸው፡፡ ‹መተቻቸትና የክርክር ባህል ስለሌለን የራሳችን ፍልስፍና የለንም› የሚለው ገለጻ ቅጠል ከሌለው ግንድ አለ ማለት አይቻልም ማለት ዓይነት አቀራረብ ነው፡፡ ምክንያቱም ትችት የፍልስፍና መበልጸጊያና ማበቢያ ቅርንጫፍ እንጂ የመኖሩ ዋስትና ግንድ አይደለም፡፡ ‹ለፍልስፍና መበልጸግ መተቻቸትና መከራከር አስፈላጊ ነው› ማለት ግን የግንዱን ግርማ ሞገስና ጠቀሜታ ነው የሚገልፁት፤ እንዲሁም ዛፉን የሚያሳድጉትና የሚያወፍሩት ቅርንጫፎቹ፤ በተለይም ቅጠሎቹ ናቸው ማለት ነው፤ አግባብም ነው፡፡ ስለዚህ ትችት ለፍልስፍና መኖር ወሳኙ ሳይሆን ለመበልጸጉ ጠቃሚውና መሣሪያው ነው፡፡

ለጥቅል ዕይታ ይህንን አልኩ እንጂ ኢትዮጵያዊያን ክርክርን የማናቅና የመተቻቸት ባህል የሌለን ሕዝቦች አይደለንም፤ እንዳውም በተቃራኒው የዳበረ የራሳችን የትችትና የክርክር ባህል አለን፤ ካለወቅንም የትችትና የመከራከር ባህል የለንም ብሎ ከመተቸት በፊት ያለውን ማየት ያስፈልጋል፤ ይቀድማልም፡፡  ሌላው በግሌ የታዘብኩትና የብዙ ተችችዎች የትችት ማጠንጠኛ መነሻ የ1960ዎቹ ትውልድ እንቅስቃሴ መሆኑ ነው፡፡ እንደእኔ ግንዛቤና አረዳድ ግን ትክክል አይመስለኝም፤ የ1960ዎቹ የተማሪ ምሁር ትውልድ የሚወክለው ራሱን እንጂ ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችውን ኢትዮጵያ አይመስለኝም፡፡ ድፍረት ባይሆንብኝ ከ1960ዎቹ ባኋላ ያለው አብዛኛው  የተማረ ምሁር የሚባለው ትውልድ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ባህል በተለያየ ሁኔታና አስተሳሰብ ስለተገነጠለ ከዚያ ትውልድ በኋላ ያለውን ልምድ በመያዝ የእኛ ኢትዮጵያውያን ባህላችን ይህ ነው ማለት አግባብ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የራሳችን የሆነ የመተቻትና የክርክር ባህል ያዳበርን ሕዝቦች ስላልሆንንና የመተቻቸት ልማድ ስለሌለን ነው የራሳችን ፍልስፍናም የሌለን የሚሉትን የምንተቻቸው የተነሱበትን ጭምር በመቃወምና ጥንት ከነበረን ልምድ አንጻር በማየት ነው፡፡ አሁን ወደ ክርክር ባህላችን ማሳያዎችን ወደ ማቅረብ ልግባ፡፡

1)  ትችትና ክርክር በሀገራችን በእረኛ፣ በቡና የመጠጣት ሥርዓት በሚደረጉ ጨዋታዎች፣ በየቀዬው የሽማግሌዎች ውይይትና ሸንጎዎች የሚታዎቅና የዳበረ ማኅበራዊ ልምድ ነው፡፡ የድሮ የሀገራችን እረኛ የአሁን ግዜ የመጽሔትና የጋዜጣ ሐያሲ ማለት ነበር፤ የዘመኑን ሁኔታና የአገዛዙን ሥርዓትና አኳኋን በመተቸትና በማወደስ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚሄስ ነበር፡- እረኛ፡፡ በነገሥታቱም ቢሆን ‹እረኛ ምናለ› የሚባለው ትችቱ እንዳይረሳና እንዲስታዋል በግጥም ከሽኖ ስለሚናገር ነው፡፡ ‹ወፍ አለች› የሚባለው የትችት ባህልም በቀላሉ የማይታይ የፍትህ ማረቂያ ነበር፡፡ ከነበረን የባህልና የቴክኖሎጂ ሁኔታ ወይም ከዘመኑ የሥልጣኔ ደረጃ አንጻር ከዚህ የበለጠም ነፃና ገለልተኛ ትችት ከየትም አይመጣም፡፡  ምናልባት ይኸ ለፍስፍና ዕውቀት መኖር ዋስትና የሚሆን ላይሆን ይችላል፡፡

2)  ክርክር በኢትዮጵያውያን የትልቅነት መለኪያ ያዋቂነት ማስመስከሪያ ልምድ የነበረ እንጂ የማይታይና የማይታወቅ የፍልስፍና ስልት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ከጭቃ ሹምም ሆነ ከንጉሥ ዘንድ ቀርቦ ሐሣብን በተመጠነና በጣፈጠ ቃላት በማቅረብ ንግግር አዋቂነትንና የመከራከር ችሎታን ማስመስከር የትልቅነት ማሳያ ነበር፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ መመራመር ሳያስፈልግ በቅርስነት የሚታወቁትን ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችን ማየት በቂ ነው፡፡ እነዚህን የንግግር ለዛዎችና ያላቸውን የመልከት ዕምቅነት ሳናስተውላቸውም ቢሆን በእየዕለት ንግግራችን የምንጠቀምባቸው ስለሆኑ ልለፋቸው፡፡ በክርክር ጊዜ ያለውን የሙግት ፈሊጣቸውንና የአመላለስ ቅልጥፍናቸውን አስደናቂነት ግን ምሳሌ ጠቅሶ ማለፍ ግድል ይለኛል፡፡ ይህንንም ‹ኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕግ፡ ሌባ ሻይ› መጽሐፍ ያዘጋጁት ከበደ ሀብተማሪያም(ፊታውራሪ ዶ/ር) ‹የበልሃ ልበልሃ ሥርዓቱ በጽሑፍ የተመዘገበ ይመስል በአእምሯቸው      ቀርፀው ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ከፈገግታና ከደም ግባት ጋር የሚሰጡ ወይንም የሚያስተምሩ የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶች በዚህ አጋጣሚ ሳይደነቁና ሳይመሰገኑ አይታለፉም፡፡› (ገጽ 47) ካሉ በኋላ ፈርሳዊው ዶር ማረብ ‹ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯቸው ጠበቆች ናቸው፡፡› (ገጽ 50) ከማለቱም በተጨማሪ የሙግት ሥርዓቱ በፊልም ሳይቀረፅ በመቅረቱ መቆጨቱን ጠቁመዋል፡፡ የሚገርመው ግን እኛ በባህሉ ኑረናልና የራሳችን ልማድ ነው የምንለው ምንም ሳይመስለንና ሳናስተውለው የምንኖር መሆናችን ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሀገራችን አስቸጋሪ ጥያቄ በመጠየቅ ባላንጣን ማሳጠትና አሳፍሮ መርታት አንድ ስልት ነበር፡፡ ዋናው ችሎታን ማሳየትና አዋቂነትን ማስመስከር ነበርም፤ በዚህ ውስጥም የዕውቀት ውድድርና አስተውሎት አለበት፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ጠበቃ ተከሣሹን በአላዋቂነት አፋጦ መልስ በማሳጣት ለመርታት የሚከተለውን አስቸገሪ ጥያቄ፡-

‹የሰማይ ኮከብ ስንት፣

የምድር አንብርት ወዴት› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡

ተከሳሹም መልሱን ደግሞ በፍጥነትና በግጥም ወዲያው አቅርቦ አዋቂነቱን ማስመስከር አለበት፡፡ መላሹም፡-

‹‹የሰማይ ኮከብ ስንት› ላልከው

አንድ ቁናን ጤፍ ቆጥረህ ድረስበት›

‹የመሬት እንብርት ወዴት› ላልከው

እነሆ! አንተ የቆምክበት›› በማለት በፍጥነት መልስ ሰጠው፡፡ የዚህ ዘመን ምሁር ቢሆን ኖሮ ምን ይመልስ ነበር? ማጣቀሻ ሲያገላብጥ በጭንቀት ይሞት ነበር፡፡

(ኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕግ፡ ሌባ ሻይ፤ገጽ 40)

በክርክር በኩል ያላቸውን ችሎታና የአቀራረብ ፍሰት ጥንቁቅነት ለመታዛብም ሁለት የታወቁ የክርክር ማሳያዎችን እንመልከት፡፡ አንደኛው የሕዝባዊ ነገር አዋቂ ሙግት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሊቃውንቱ የሃይማኖት የጉባኤ ክርክር ነው፡፡

  1. አንድ ጊዜ ‹ሁለት ሰዎች በርስት ምክንያት ተጣልተው ሲሟገቱ ከኖሩ በኋላ አንደኛው ይረታል፡፡ የተረታው ግን ቂም ይዞ አንድ ቀን በምሽት መንገድ ላይ ጠብቆ ይገድለዋል፡፡ ምን እንኳን እሱ እንደገደለው ቢታወቅም ሲገድለው ያየ ሰው ባለሞኖሩ ጉዳዩን ወደ ዳኛ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡ የሟች ወንድምም በአፈርሳታ (በአውጫጭኝ) ጉዳዩን ለማግኘት ቢጥርም ሳይሳካለት ይቀራል፡፡ ሆኖም የሟቹ ወንድም ዝነኛ ጠበቃ ስለነበር ተጠርጣሪውን ሰው ብሎ እዳኛ ጋር በማቅረብ በሙግት እውነትና ሐሰቱን ለማውጣት ቆርጦ ይነሳል፡፡ ተጣርጠሪውም በክስ በአፈ ቀላጤ ችሎት ላይ ከቀረበ በኋላ የሟች ወንድም ዳኛን አስፈቅዶ ሙግቱን በተጠየቅ ሥርዓት ይጀምራል፡፡› በሙግቱ መጨረሻም ወርድ የነዛባት ክርክር ይች ናት፡-

ከሳሽ ‹ተጠየቅ›

ተከሳሽ ‹ልጠየቅ›

ከሳሽ ‹ሰውን በግፍ የገደለ ወንጀለኛ ነው ይቀጣል፡፡›

 ተከሳሽ ‹አዎን ይቀጣል›

ከሳሽ ‹ባንተና በወንድሜ በአቶ ዘርፉ መካከል የርስት ሙግት ነበር፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ነበር›

ከሳሽ ‹በዚህ የተነሣ ከወንድሜ ጋር ጠበኞች ነበራችሁ፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ነበርን›

ከሳሽ ‹በመጨረሻም አቶ ዘርፉ ረታህ፡፡›

ተከሳሽ ‹አዎን ረታኝ›

ከሳሽ ‹ስለረታህ ቂም በቀል ይዘህ ሌሊት እመንገድ ላይ ጠብቀህ የገደልከው አንተ ነህ፡፡›

ተከሳሽ ‹አረ! ባዛኝቷ ምን በወጣኝ እባክህ!›

ከሳሽ ‹ስትገድለው ያዩህ የዓይን ምስክሮች አሉ፡፡›

ተከሳሽ ‹አረ! ማንም የለም!›

ከሳሽ ‹እማኞች ንቁ!› ይላል፡፡

ከሳሽ ይህንን የተናገረው የመጨረሻዋን ቃል ልብ ብለው እንዲያጤኑለት ነው፡፡ ይህንንም በመመርኮዝ እንዲህ ብሎ ውርድ ነዛ፡፡

‹ሰውን በግፍ የገደለ ወንጀለኛ መሆኑን አምነኸል፤

ከወንድሜ ጋር ሙግት እንደነበርህና በመጨረሻም እንደረታህ አምነሃል፤

በዚህም ቂም ‹ወንድሜን ገድለኸዋል› ስትባል አሌ ብትልም፤

‹ስትገድለው ያዩህ ሰዎች አሉ› ብልህ ‹አረ ማንም የለም› ስላልክ ወንድሜን እንደገደልከው እውነቱን አውጥተኸልና በነፍሰ ገዳይነት መቀጣት እንዳለብህ ሰጋር በቆሎ እሰጥ!› አለ፡፡

(ሽበሺ ለማ፣ ተጠየቅ)

እዚህ ላይ ዳኞች ምንም ይፈረዱ የክርክሩን ፍሰትና ድብቅ ድርጊቶችን የማውጣጣት ስልት ስናይ ምን ያህል ኢትዮጵያውን የዳበረ የሙግት ልምድ እንደነበረን መገንዘብ ቀላል ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን በብዙ የሀገራችን ክፍሎች ዘመናዊ ትምህርትና የፍርድ ቤት አሠራር የጥንቱን እያጠፋውና በነበር እያስቀረው ቢሆንም በአንዳንድ ሥፍራዎች ‹የተጠየቅ ልጠየቅ› እና ‹የበልሃ ልበልሃ› ክርክሮች ልምድ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ማሳያዎች አሉን፡፡ ለምሳሌ በመንዝ አካባቢ እስከ ቅርብ ጊዜ ይሠራበትና እዛፍ ሥር እየተሰበሰቡ መሟገት የተለመደ እንደነበር በዚያ አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ በማስተማር ላይ የቆየ ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ ስለዚህ የተጠየቅ ልጠየቅን ሥርዓት የመሰለ የሙግት ባህል እያለን ክርክር የማይታወቅ አድርጎ መናገር ስህተት ነው፡፡

  1.  የጉባኤያት ክርክሮችም የኢትዮጵያዊያንን አሰተውሎታዊ የሞሟገት ችሎታዎች የሚያሳዩ ናቸው፤ የተጻፉ ማሳያዎችም አሉ፡፡ በተለይ ሊቃውንቱ በንግግር ለዛቸው የተካኑ ነበሩ፡፡ ሊቃውንቱ የሙግታቸውን ፍሰት በማር ማገጃ ስልት ጠብቀው፣ የንግግራቸውን ፍሬ ነገር በሞገሰ ቃል ከሽነውና በጣዕመ ነገር አጣፍጠው በቅልጥፍና የመግለፅና የተሟጋቻቸውን ብልት መተው የመጣል ልዩ ችሎታ ያላቸው ነበሩ፤ ናቸውም፡፡ ለዚህም በታሪክ ተመዝግበው የሚገኙትን ክርክሮች ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌም በ1878 ዓ.ም. በቦሩ ሜዳ ሊቃውንቱ ስለ ሁለትና ሦስት ልደት የሃይማኖት ጉዳይ ካደረጉት ክርክር መካከል አንዱ ይህንን ይመስላል፡፡

…ከተዋሕዶዎች ወገን የሆኑት መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ‹ቀረኝ› ብለው በመጠየቅ ክርክራቸውን ያቀረቡት በዚህ መልክ ነበር፡፡

‹የንጉሥ ገንዘብ ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመዝገብ ይጻፋል፡፡.

‹አዎ ተሰፍሮ፣ ተቆጥሮ በመዝገብ ይጻፋል፡፡›

‹በመዝገብ ከተጻፈው ያጎደለም፣ ያተረፈም ይቀጣል፡፡›

‹አዎ ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›

‹የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል፡፡›

‹አዎ! የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል፡፡›

‹ከመጽሐፍ ቃል ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›

‹አዎ! ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›

‹መጽሐፍ ነአምን ክልኤተ ልደታተ (ሁለት ልደታትን እናምናለን) ብሎ በአሐዝ ወስኖ ተናግሯል፡፡›

‹አዎን! ነአምን ክልኤተ ልደታተ ይላል፡፡

በዚህ ጊዜ ጠያቂው በዚህ መልክ ውርድ ነዙ፡-

‹ከመጽሐፍ ቃል ያተረፍ ያጎደለም የሚቀጣ ከሆነ፤

 መጽሐፍ ጠንቅቆ ነአምን ክልኤት ልደታተ ብሎ ከተናገረ፤

አንተ ከዚህ አልፈህ ተርፈህ ሥስት ልደት እያልክ ስታስተምር ከተገኘህ ትቀጣለህ፡፡›

(አባ ጎርጎሪዮስ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ገጽ 80-81)

ይህ የክርክር ስልት ምን ያህል በሊቃውንቱ ሰርፆ እንደሚገኝና በጽሑፋቸው ሳይቀር እንደሚንጸባረቅ አለቃ አያሌው ታምሩ አንድ ጊዜ ያቀረቡትን የመከራከሪያ ጽሑፍ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ነው፤ አንድ ሰሞን ‹ፊያሜታ› በሚባል ጋዜጣ ‹ድንግል ማሪያም ወላዲተ አምላክ ትባላለች አትባልም› የሚል ክርክር ተጧጡፎ ነበር፡፡ በመሀል አለቃ አያሌው አንድ ሰው ለጻፈው ምላሽ ሲሰጡ በሚከተለው አቀራረብ ሙግታቸውን አቀረቡ፡፡ አንዳንድ ማስተካከያ ተደርጎበት አቀራረቡ ይህንን ይመስላል፡፡

‹መጽሐፍ ቅዱስን ታምናለህ?›፤

-መልስህ ‹አዎ› ወይም ‹አላምንም›

‹በመጽሐፍ ቅዱስ ታመንክ ኤልሳቤጥ ማርያምን ‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?› በማለት የተናገረችው በውስጡ ተጽፏል፤ አልተጻፈም?›

-መልስህ ‹ተጽፏል› ወይም ‹አልተጻፈም›

‹ከተጻፈ ኤልሣቤጥ ‹ጌታዬ› ያለችው አንተ ‹አምላኬ› ብለህ የምታምነውን ነው፤ አይደለም?

-መልስህ ‹ነው› ወይም ‹አይደለም›

‹ነው ካልክ ‹ታዲያ ድንግል ማርያም ለምን ያምላክ እናት አትባልም?›

-መልስህ አዎንታ ወይም አሉታ ብቻ ይሁን ሀተታ አያስፈልግም፡፡

ይህም የሙግት አቀራረብ አለቃ ራሳቸው ምን ያህል በክርክር ክህሎት የዳበረ ችሎታ እንደነበራቸው፤እንዲሁም ዘመናዊ ዕውቀት ሳያዳበሩ በባህላዊ የሙግት ሥርዓት ማንንም መርታት የሚያስችል የክርክር ፍስትን ገንዘብ ያደረጉ ሊቃውንት መኖራቸውን እንድናጤን ያደርገናል፡፡ ከዚህ የበለጠም የክርክር ባህልን ማደበር ምን እንደሆነ ለእኔ አይገባኝም፡፡ እንደባልና ሚስት ንዝንዝ ትዝ ሲል የመወቃቀስና መጨቃጨቅ ባህል ማለት ይሆን እንዴ? ነው የክርክር ወሰን (አድማስ) ሳያበጁ ሁሉንም መስደብና መንቀፍ ነው ትችት? እንዳውም እንደ እኔ አረዳድ ከሆነ ሊቆጨነንና ልናውቀው የሚገባን የሚያስደንቅ የሙግት ባህል የነበረን ሕዝቦች መሆናችን አለመስተዋሉ ነው ይመስለኛል፡፡

‹ያባቶች ጨዋታ እንዴት ነበር ድሮ፣

ሲወዱም ሲጠሉም አስቦ መርምሮ፡፡› እንዲሉ ነበር፤ ባይሠበር፡፡

3)  ይህም ብቻ ሳይሆን በቅኔ መተቻቸትና መከራከር የተለመደ ነው

በመሠረቱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይከባበራሉ እንጂ የሚያደርጉትን የቅኔ ዘረፋና ነጠቃ ላየና ላስተዋለ ምን ዓይነት አስተውሎትና ፍጥነት ያላቸው እንደሆኑ ይረዳል፡፡ ለምሳሌም ሠረገላ ብርሃንና ካሣ ጉዱ (የፍቅር እስከመቃብሩ ጉዱ ካሣ) የተባሉት የቅኔ ሊቆች በዲማ ጊዮርጊስ ባደረጉት ፉክክር የነበረውን ሁኔታ አለቃ ለማ የገለጹት እንዲህ ብለው ነበር፡፡

‹ሁለቱ ሊዛረፉ ቀረቡና፤ ሊማሩ ጀምረዋል፡፡ ዛዲያ ካሣ አንዱን ዘለቀ፡፡ በሁለተኛው ላይ ‹እም–እም–እም› መልስ፤ ማለት አበዛ፡፡ ዛዲያ ሠረገላ ብርሃን፡-

ወክልኤቱ ጌጋይ ቃለ መውደስ

አክአብ ካሣ ጉዱ እስከ ማእዜኑ ተሐነክስ›

(በሁለቱ በደል ኃጢያት፣ የመውደስ ቃል ካሣ ጉዱ- አክአብ እስከ መቼ ታነክሳለህ?)

አለ፤ መውደስ ነው፤ መጽፊያው ነው፡፡ ድማ ነዋ፤አለቃ ተጠምቆና መምር ዕንግዳሸት ኻንድ ቤት ተማሪው ሁሉ ሞልቶ፤ እኔ እያለሁ አደለም ወይ ይኸ?›

(መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ፤ ገጽ 89-90)

 ምናልባት የአለቃ ለማ መደነቅ ለሌላው ላይሰማ ይችላል፤ የዘረፋ ፉክክሩን መንፈስ ላየና በሕሊናው ለሣለው ሰው ግን ድንቅ የዕውቀት መለኪያ መሆኑ ይገባዋል፡፡ በተለይ አለቃ ‹እም–እም–እም› አለ ያሉትን የገለጹት ‹ካሣማ የድማ ደብተራ ነው፤የሽማግሌ ልጅ ነው፤ ዛዲያ ካሣ ጉዱ ይሉታል፤ የሙገሣ ስሙ ነው፡፡› በማለት መሆኑን ሲረዳ የቅኔ ፍክክሩ በእነማን እንደነበረ ይገባዋል፡፡ አንድ ጊዜ በሙዚክ ሜይ ዴይ የመጻሕፍት ንባብና ውይይት ክበብ በዚሁ ‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ› በሚለው መጽሐፍ ላይ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ስለ አለቃ ለማ ቅኔዎች እንዲያስረዱ ተጋበዥ አቅራቢ የነበሩት ሊቀ ኅሩያን በላይ ስለሁለቱ ስለ ሠረገላ ብርሃንና ካሣ ጉዱ ሌላ ቅኔ በመጥቀስ ጭምር ከፍተኛ የዘረፋ ፉክክር ያደርጉ እንደነበር በመደነቅ ነበር ያስረዱት፡፡

የቅኔ ዘረፋን ካነሣሁ የቅኔ ነጠቃንም ሁኔታ በጥቆማ ልጥቀስና ልለፍ፡- የዕውቀት ውድድር አካል ነውና፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ትምህርት በመውደድ ከትውልድ ሥፍራዬ ወጥቼ 40 ዓመታትን ቅኔ በማፍቀር ስማርና ሳስተምር ቆይቻለሁ የሚሉት ታላቁ የቅኔ ሊቅ ንቡረዕድ ክፍለ የሐንስ የተናገሩት ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ‹ቅኔ ተነጥቀው ያውቃሉ ወይ? › ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ‹‹ሊቃውንቱ ስለሚያከብሩን የኛን ቅኔ ለመንጠቅ አይቸኩሉም› ካሉ በኋላ አንድ ጊዜ የገጠማቸውን ሲናገሩ ‹አንድ ጊዜ ስቀኝ ምሥጢሩ ቦግ እሚልበት ጋር ስደርስ አንድ አባት ፈጥነው ነጠቁኝ ሆኖም እኔ ‹እረ ምሥጢሩ ከተራራው ወዲያ ነው› ብያቸው ወጣሁት፤ ከዚያም ሊቁ ‹እውነትም ከታራራው ወዲያ! እውነትም ከተራራው ወዲያ!› ብለው አደነቁ፡፡ የእኛ ቅኔ ከዋድላው፣ ከዋሻራውም ከተለያየ መምህር ከዚያም ከዚህም ተወስዶ ስለተዋሐደ በቀላሉ አይደረስበትም›› ነበር ያሉት፡፡ (ጥቅሱ በ1995 ከሐመር መጽሔት ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ- በተዘክሮ የተወሰደ ነው) ለቅኔ ነጠቃም ምን ያህል ፍጥነትን፣ ምሥጢር ማስተዋልን፣ ታሪክ ማወቅን፣ የድርጊቶች ተያያዥነትንና የቋንቋ ዕውቀትን ሊጠይቅ እንደሚችል በዓይነ ሕሊና መሣል ነው፡፡ ከዚህ የበለጠም ፉክክር ያለበት ዕውቀት ምን ዓይነት ይሆን?

አንድ አካባቢ ያሉ ወይም የተለየ የእምነት አመለካከት ያላቸው ሊቃውንት ከሌሎች ጋር የሚከራከሩትና ዕውቀታቸውንና የእምነታቸውን ዕርቱዕነት የሚያሳዩትም በሚቀኙት ቅኔ ነው፤ ቅኔ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ግጥም ብቻ ሳይሆን ታሪክን፣ አስተውሎትንና የዕውቀት ደረጃን መለኪያ ነው፡፡ ለዚያም ነው ‹የካህን ዐዋቂነቱ የሚለከው በቅኔው ነው› የሚሉት፡፡  ለዚህ ማሳያ የሚሆን ሁለት የታወቁ የቅኔ ሊቃውንት ያደረጉትን የቅኔ ምልልስ እንመልከት፡፡ አንድኛው ሊቅ የታወቁት ዐራት ዓይና ጎሹ የቅባት አስተምህሮን የሚደግፉ ሲሆኑ ሌላው ደግሞ የዲማው ሊቅ ቄስ ገበዝ ኑርልኝ የተዋህዶዎችን እምነት ይደግፋሉ፡፡ የመጀመሪየውን ቅኔ ዐራት ዓይና ጎሹ ጽፈው ለድማ ጊዮርጊስ ማህበር ልከውታል ይባላል፡፡ እነሆ ቅኔው፡-

ኢትጥፍዐ ንዴተ ሥጋ ተዋሕዶተ ቃል ምስለ ሥጋነ እመ ሐተትነ በልብ ይእዜ እንበለ ማኅየዊ ቅብዐት፤

ወኢይኩን በዐውደ ሮምያ በይነዝ ሑከት፤

ይክልኑ በእግር ተሐውሶ ኀበ ፍኖተ ላዕል ወታሐት፤

ነፍስ ዘአልቦ ሥጋ ምውት፤

ወጽልመተኑ ያሴስል እም ዓይን ማኅቶት፤

ዘላዕሌሁ ኢሀለወ ዘይት፡፡ 

ትርጉም፡-

ከልብ ብንመረምር ማኅየዊ (አዳኝ) ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ቅብዐትነት ማለት ክብርነት በቀር በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐትነት ነው እንጂ ቃል ከሥጋችን ጋራ መዋሐዱ የሥጋ ንደትን አላጠፋውም፡፡ ስለዚህም በሮማ ዐደባባይ ሑከት እንዳይሆን ነፍስ የሌለው የሞተ ሥጋ በእግር ከላይ ወደ ታች ሊመላለስ ይችላልን? በላዩ ላይ ዘይት የሌለበትስ መብራ ከዓይን ጨለማን ሊያርቅ ይችላልን?

በተዋሕዶዎች በኩል ቄስ ገበዝ ኑርልኝ ደግሞ  ለአራት ዓይና ጎሹ ቅኔ መልስ የሚሆን የሚከተለውን  ቅኔ ተቀኝተው ልከውላቸዋል፡፡

ኢየኀሥሥ ለአብርሆ ቅብዐ ዘይት ፀሐይ ዘላዕለ ኩሉ፤

ወዘየዓቢ ፀሐይ ከማሁ ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ ክብርነ፤

ኢየኀሥሥ አምጣነ ፀሐይ ዘያበርህ ለነ፤

ወኢይትሐወክ ብዙኅ በዝንቱ አርዮሳዊ ዘኮነ፤

ከመ ቃል ብርሃነ ኀበ ኢዘምነ፤

ዐይኑ የኀሥሥ ካልአ ዐይነ፤

ወብርሃን ካልአ ብርሃነ፡፡

ትርጉም፡-

ከሁሉ በላይ ያለ ፀሐይ ላብራ ባለ ጊዜ ዘይትን ለቅብዓትነት አይፈልግም፤ እንደዚሁም ከዚህ ዓለም ፀሐይ የሚበልጥ ኢየሱስ ክርስቶስም ለእኛ የሚያበራ እውነተኛ ፀሐይ እንደመሆኑ መጠን ለእኛ ክብር የሚሆን መንፈስ ቅዱስን አይሻም፡፡ በዚህም ያርዎስ ወገን የሆነ ሰው እንዳይታወክ ዐይን ልይ ባለ ጊዜ ሌላ ዓይን ይሻልን? ብርሃንስ ልገለፅ ባለ ጊዜ ሌላ ብርሃ ይሻልን?

(መ/ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ መድሎተ አሚን ገጽ 194-195)

እነዚህ ቅኔዎች የጠቀስኳቸው የቅኔዎችን ምሥጢር በመፍታት ለማሳየት አይደለም፡- ላደርግ ብልም አቅሜ አይፈቅድልኝም፤ ቢፈቅድልኝም እንኳን እዚህ መተንተኑ አግባብ አይደለም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሊቃውንቱ ብሶታቸውንና ደስታቸውን፤ ነቀፌታቸውንና ምስጋናቸውን ባጠቃላይ የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ሁኔታና የሚያምኑበትን ዕይታ… የሚያቀርቡት በቅኔያቸው ነው፡፡ የእኔ ዋና ዓላማ ሊቃውንቱ የአዋቂነት መለኪያቸው በሆነው የግዕዝ ቅኔ በመተቻቸት የእምነታቸውን ትክክልነት የሌሎቹን ግን መሳሳት ያሳዩበት እንደነበር ለመጠቆም ነው፡፡ ይህንን ያህልም የመተቻቸት ባህል ያላቸው ሊቃውንት ያሏትን ሀገር መተቻቸትን ‹ስለማናውቅ ነው› ፍልስፍና የሌለን ማለት ስህተት ነው ማለቴ ነው፡፡

4)  የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሃይማኖትን መሠረት ያደርጋሉ እንጂ ለእያንዳንዷ ሐሣባቸው ምክንያትን የሚሹ፣ ሙግትን በተለያየ አንግል በመቃኘት የሚከራከሩና በነገር አስተውሎት የተካኑ መሆናቸውን በተለያየ መንገድ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እንደ ማሳያም የጻፏቸውን መጻሕፍት መቃኘት ጠቃሚ ነው፡፡  ለምሳሌም የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ‹መጽሐፈ ምሥጢር› መጽሐፍ የሙግት አቀራረብ ማየትና ነገሮችን በተለያየ አንግል አጋጭቶ የማስታረቅ ስልትን በአንድምታ ትርጓሜያት መጻሕፍት መመልከት በቂ ነው፡፡ ብዙ ዝርዝር ማብራሪያ ውስጥ ሳንገባም ይህንን ለማረጋገጥ የፈለገ ሰው መጽሐፎቹን በማየት የራሱን ምስክርነት መስጠት ይችላል፤ ለምሳሌም ‹መጽሐፈ ምሥጢርን› የተመከተ ምሁር የራሱን ፍርድ ይስጥ ከማለት ያለፈ ምን ማለት ይቻላል? ምክንያቱም በመጽሐፉ የሥነ መለኮት ፍልስፍናና ሥነ አመክንዬአዊ ክርክር በሚያስደንቅ ሙገታ ቀርቦ ይገኛልና፡፡

በአጠቃላይ ከ1950ዎቹ በኋላ የተለመዱትን የጋዜጣና ሌሎች ክርክሮችን አይቶ ከዚያ ጋር በማነጻጸር፤ እንዲሁም በአውሮፓውያን የትችት ልምድ ሚዛን በመመዘን የክርክርና የመተቻቸት ባህል የለንም ብሎ በመደምደም፤ የራሰን ወግና ባህል ማጣጣልና ትርጉም ማሳጣት፤ በዚህ ላይ ተመሥርቶም የራስን ሀገር ዕውቀትና አተያይ ፍልስፍና አልባ አድርጎ ማየትና ማሳየት ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች ተነስተን የሚኖረን መደምደሚያ ይህንን ይመስላል፤

  • ፍልስፍና በሙግትና በነገር አዋቂነት ይበለፅጋል እንጂ አይመሠረትም፡፡ የፍልስፍና መሠረቱና መነሻው መደነቅና አስተውሎታዊነት ነው፡፡
  • ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንትና ተሟጋቾች ደግሞ በተፈጥሮቸው ማስተዋልና መደነቅ ብቻ ሳይሆን ነገር አዋቂነት፣ ተሟጋችነትና መጣኝነት መለያ ሀብታት ናቸው፡፡ ነገር አዋቂነትና ተሟጋችነት የትልቅ ሰውነት መለኪያ ስለሆነም የክርክርና የሙግት ባህል የለንም ማለት ስህተት ነው፡፡
  • በዚህ የተነሣ የመተቻቸትና የመከራከር ባህል ስለሌለን የራሳችን ፍልስፍና የለንም ማለት አያስኬድም፤ ስህተት ነው፡፡

2. እውን በኢትዮጵያ ፍልስፍና ወንበር የላትም? (ይቀጥላል)

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply