እውን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም? (3)

  2. እውንበኢትዮጵያፍልስፍናወንበርየላትም?

1. ኢትዮጵያ ውስጥ ፍልስፍና ወንበር የላትም፡፡

2. ወንበር ይዞ ፍልስፍናን የሚያስተምር ሳይኖርም አካዳሚያዊ ፍልስፍና አይኖርም፡፡

3. ስለዚህ የተለየ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚባል የለም፡፡

           ትችታዊማብራሪያ

የዚህን ክርክር ትክክል መሆን ወይም አለመሆን ለመመዘን በቅድሚያ ወንበር ምንድን ነው የሚለውን ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ወንበር በሀገራችን የትምህርት ባህልና በእዚህ አግባብ መምህር ተሰይሞበትና ተማሪ ተለይቶለት የሚሠጥ የትምህርት ዓይነትን ያመለክታል፡፡ ከዘመናዊ አሰተምህር ስያሜ አንጻር ካየነው ራሱን የቻለ አካዳሚያዊ የትምህርት ዘርፍ ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ‹ፍልስፍና ወንበር የላትም› ሲባልም በአንድ የትምርህት ዘርፍነት በሀገራችን የሚሰጥ ዕውቀት አይደለም ማለት ይሆናል፡፡ አሁን ‹እውን ይህ ትክክለኛ ገለጻ ነው ወይ?› ወደ ሚለው ፍተሻችን ስንገባ ‹ወንበር ተዘርግቶለት የሚሠጥ የፍልስፍና ዕውቀት ዘርፍ በኢትዮጵያ የለም?› የሚለውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ ‹ወንበር ተዘርግቶለት የሚሠጥ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ስንል ስያሜውን ከሆነ ‹ፍልስፍና› ብሎ የሚያስተምር ሊቅ የለም ማለቱ ትክክል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የፍልስፍናን ምንነት፣ አትያይና ስልት የያዘ የዕውቀት ክፍል ወንበር ተዘርግቶለት አይሠጥም ማለት ከሆነ ግን ስህተት ነው፤ አለ፡፡ ፍልስፍናን በስሙ ጠርተው የሚያስተምሩ ሊቃውንት የሉም ማለትም ቢሆን ሙሉ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንጋረ ፈላስፋ የሚለውን መጽሐፍ ያየ ማንኛውም ሰው ምስክርነቱን እንደሚሰጠው ‹አንድ ፈላስፋ እንዲህ አለ፤ እከሌ የተባለው ፈላስፋ እንዲህ ተናገረ፣…› በማለት የብዙ ፈላስፎችን ምክርና አስተውሎቶች ይዞ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የመጻሕፍት አስተምህሮ ጉባኤያትም ቢሆን ይህ የፈላስፎች አስተሳሰብና አስተውሎታዊ ገለጻዎች እንደ ማሳያ በመሆን ጥቅም አላቸው፡፡ ስለዚህ በስያሜነት ‹ፍልስፍና ይኸ ነው› በማለት ወንበር ዘርግቶና ጉባኤ ከፍቶ የሚያስተምር ሊቅ ላይኖር ይችላል፤ ቢኖር እንኳን ቀጣይነት ያለው የወንበር ሥርዓት ተዘርግቶ እኛ ጋር ስላልደረሰ ‹እከሌ የተባለው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ፍልስፋናን ያስተማረበት ቦታና የማስተማር ስልትም ይህ ነው በማለት ማስረዳት አይቻል ይሆናል፡፡ (እዚህ ጋር የዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና ጉዳይ መነሣት ይችላል፤ ሆኖም የእሱን ፍልስፍና የሚመለከት ራሱን የቻለ ክፍል ስላለ ለጊዜው እዚህ ማለፉ የተሻለ ነው፡፡) ነገር ግን ፍልስፍና ስንል ከስያሜ አልፎ አተያዩን፣ ምንነቱንና አስተውሎቱን ከሆነ ‹ወንበር ተዘርግቶለትና ጉባኤ ተከፍቶሎት  የሚሠጥ የፍልስፍና ትምህርት የለም› ማለታችን  አግባብ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የትምህርትን ስያሜና ምንነቱን ለያይቶ መረዳት አስፈላጊ ይሆናል፡- ምንም እንኳን ስያሜው የምንነቱ ወካይ ቢሆንም፡፡

እንዲሁም ፍልስፍናን ከአውሮፓውያን አንግል ብቻ ካየነውም ለሚዛን አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ፍልስፍና ከአውሮፓውያን የፍልስፍና አተያይና አቀራረብ በተለየ መልኩ ሊገለፅ የሚችልበት መንገድ ይኖራልና፡፡ ለምሳሌ የሀገራችን የሥነ-ጽሑፍና ሥነ-ጽሕፈት ሥርዓቶች፣ የትምህርት ሥርዓት አከፋፈል ስልቶች፣ የሥነ-ዜማና ሥነ-ጥበብ አስተምህሮዎች፣ የአነጋገር ለዛዎችና ልምዶች ከአውሮፓውያኑ ይለያሉ፡፡ የሥነ-ጽሕፈት ሥርዓታችን ከፊደል ሥርዓት እስከ ሰዋሰው አግባብ የተለየ ስልትን በመከተል የተገነባ ነው፡፡ ይህንን መሠረት የሚያደረገው ሥነጽሑፋዊ ስልታችንም በራሱ የዳበረ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥነ-ጽሑፍን ያዳበርን ሕዝቦች ብንሆንም ራሱን የቻለ የሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ቤት አልነበረንም፡፡ ‹እከሌ የተባለ ሊቅ የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍ ወንበር ዘርግቶ ያስተምር ነበር› የሚል ወይም ‹ይህ ት/ቤት የሥነ-ጽሑፍ መማሪያ ነበር› የሚል የታሪክ አስረጅ በብዛት አይገኝም፤ የተጻፉ ብዙ መጻሕፍት ግን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራትም ሞልተዋል፤ በሀገራችን ብራና ዳምጠውና ቀለም በጥብጠው የሚጽፉ ብዙ ሊቃውንትም ነበሩ፡፡ ስለዚህ ያለው የሥነ-ጽሑፍ ሥርዓቱ፣ ልምዱና ምርቱ እንጂ በቅንርንጫፍነት (በዘርፍነት) ስም የሚሠጠው የትምህርቱ ክፍል አልነበረም፡፡ እና ይህንን ይዘን ኢትዮጵያዊ ሥነ-ጽሐፍ የለም ማለት እንችላለን እንዴ? የሥነ-ጽሑፍ ሥርዓት በትምህርት ዘርፍነት ባይሠጥም የበለጸገ እንደሆነው ሁሉ ፍልስፍናም ወንበር ተዘርግቶ በትምህርት ዘርፍነት የሚሠጥ ባይሆንም እንኳን የፍልስፍናው ዘይቤና ዕይታ ካለ ፍልስፍና ሊኖር አይችልም ልንል አንችልም፡፡

ከዚሁ ከወንበራዊ ፍልስፍና መኖር ጋር ተያይዞ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የሥነ ጽሑፍ ሀብታችን ነው፡፡ ሥነ ጽሑፍ በተፈጥረው የራሱ የፍልስፍና ዘይቤ ማሳያና ማስተላለፊያ ጥበብ ነው፡፡ አየለ በከሪም (ዶ/ር) Ethiopic: An African Writing System በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 3 ‘Writing systems are, indeed, rich sources of human intellectual activities, such as history, philosophy, social order, psychology and aesthetics. -‹በእውነቱየሥነጽሑፍሥርዓቶችታሪክን፣ፍልስፍናን፣ማኅበራዊሥርዓትን፣ሥነልቦናንእናሥነኪንንበመሳሰሉየሰውልጅየዕውቀትተግባራትየበለፀጉምንጮችናቸው፡፡› ካሉ በኋላም የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በሚመለከት በገጽ 10 ላይ ‘The Ethiopic writing system contains the major properties of philosophy, for it is critical, systematic, rational and holistic.- ‹የኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ሥርዓት የፍልስፍናን ዋና ዋናባ ሕሪያት የሆኑትን ስላዊ ትችትን፣ ሥርዓታዊ እሳቤን፣ የነፃ አስተውሎትንና ተጠየቃዊ መሠረትን ይዞ ይገኛል፡፡ ብለው ገልጸውታል፡፡

በጥቅሉ ኢትዮጵያ የዓለም ቀዳሚና ሳይንሳዊነቱ ተወዳዳሪ የሌለው የሥነ ጽሑፍ ሥርዓት አላት፡፡ ይህንን አስተዋይ የሆነ ሁሉ በቀላሉ ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ ስልቶች ጋር በማነጻጸር መረዳት ይችላል፡፡ ከፊደል ሥርዓቱ ጀምሮ እስከ ድረሰት ዘይቤው ድረስ ያለው የዕውቀት ድርጅት በአልቦ ፍልስፍና አልተፈለሰም፡፡ በዚህ መልክም የሥነ ጽሑፍ ዘይባችን ዳብሮ እያለ ወንበር ያለው ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም› ሊባል የሚቻልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከዳበረው የሥነ ጽሑፍ ሥርዓት የበለጠስ ፍልስፍና ምን ዓይነት መቀመጫ ወንበር ይኑራት ይባላል?

በሌላ በኩል የፍልስፍናን መሠረታዊ የጥናት ተጠየቅም ማየቱ ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በመሠረቱ ፍልስፍና ሥርዎ ቃላዊ ትርጉሙንና መሠረታዊ ጥያቄዎቹን እንደጠበቀ የሳይንስ ትምህርት መልስ ለመስጠት ያልቻለባቸውን መሥረታዊ ጥያቄዎች የሚመረምር ጥበብ ነው፡፡ በእዚህ ላይ በመመሥረትም የአካዳሚያዊ ሥርዓተ አስተምህሮ ተከፋፍሎ እያንዳንዱ ትምህርት ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ የትምህርት ዘርፍ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ፍልስፍናን መሠረቱ የማያደርግ ምንም ዓይነት የትምህርት ዘርፍ የለም፡፡ የጥንታዊ ሀገራችን የአስተምህሮ ሥርዓት ደግሞ በራሱ አከፋፈልና የአሠጣጥ ስልት የሚመራ ነበረ፤ ነው፡፡ ይህ ከሆነም የጥንታዊ ኢትዮጵያም የትምህርት ሥርዓት የራሱ ፍልስፍናዊ አከፋፈል ስልትና ጥበብን የተከተለ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሣም ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና በምንነቱ፣ በስልቱና በአተያዩ ሊለይ እንደሚችል ማስተዋል ነው፡፡ በዚህም ቢሆን ‹እና የተለየ የምንለው ወንበር ተዘርግቶለት የሚሠጥ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ የምንል ከሆነ ፍልስፍናችን የትኛው ነው?› ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡

በእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ አንጻር ካየነው እያንዳንዱ የትምህርት ክፍል የራሱ የፍልስፍና አተያይና መሠረት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ በአትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዓይነት እንደሚከተለው በአራት ዐበይት ክፍላት ይከፋፈላል፡፡

  1. ፀዋትወ ዜማ፡- ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ዝማሬ መሥዋዕትና ቅዳሴ በማለት ይከፋፈላል፡፡
  2. ትርጓሜ መጻሕፍት፡- ከስልት አንጻር የላይ ቤትና የታች ቤት ትርጓሜያት በማለት ይከፈላል፡፡ ከመጻሕፍቱ ዓይነት አንጻር ደግሞ የብሉያት ትርጓሜ፣ የሐዲሣት ትርጓሜ፣ የመጻሕፍተ ሊቃውንት ትርጓሜና የመጻሕፍተ መነኮሳት ትምህርት በማለት ይከፋፈላል፡፡
  3. ባህረ ሐሣብ ወይም የቁጥር ትምህርት፡ መርሐ ዕውርና አቡሻህር  የሚባሉ ሁለት ዐበይት ክፍላት አሉት፡፡ መርሐ ዕውር የአቅማራትን ምሥጢር፣ የአጽዋማትንና የበዓላትን ሥረዓት የሚያሰረዳ ሲሆን አቡሻህር ደግሞ ሙፃአ ፀሐይን፣ ምሕዋረ ከዋክብትን፣ የጨረቃ ብርሃን ምልዐትና ሕጸጽን የሚያሥረዳ የቁጥር ትምህርት ነው፡፡
  4. ፀዋትወ ቅኔ፡-የጥንቱ የግዕዝ ቅኔ መንገድ፣ የዋድላ፣ የዋሸራና የጎንጂ እና የጎንደር የሚባሉ አራት መንገዶች አሉት፡፡

ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው የትምህርት ዘርፎች ዝም ተብለው የተመደቡና ፍልስፍና አልባ አይደሉም፡፡ የራሳቸውን የፍልስፍና አስተምህሮ መሠረት ያደርጋሉ፤ ምናልባት ‹ክፍፍሉ ሃይማኖትን መሠረት ያደርጋል፤ ሃይማኖት ደግሞ ከፍልስፍና ጋር አይስማማም› የሚል ሙግት የሚያነሳ ተከራካሪ ሊያጋጥም ይችላል ፡፡ ለዚህ ተሟጋች ግን ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ ያላቸውን ግንኙነት በሚመለከት የቀረበውን ሃይማኖት፣ፍልስፍናእናሳይንስምንናምንናቸው?› የሚለውን ጽሑፍ ቀድሞ መጋበዝ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሃይማኖትምንነት የሚያትተውን ጽሑፍ ማሳየት አይከፋም፡፡ ከዚህ በተረፈ በሃይማኖትና በፍልስፍና ግንኙነት ዙሪያ እዚህ ማተቱ አስፈላጊ መስሎ አይታይም፤ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን የተጠቀሱትን ጽሑፎች ማየቱ የተሻለ ይሆናል፡፡

ከዚያ ባለፈ የዘርፎቹን ፍልስፍናዊ አተያይ መዳሰስ ግን አስተውሎትን፣ በአውሮፓን ዕይታ ብቻ ተሸብቦ አለመጋለብን፣ የእምነት ቅንነትንና ከራስ የግል ልምድና ፍላጎት መጽዳትን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም የአስተውሎት መታጣት ዙሪያ ገባውን በጥልቀት እንዳንቃኝ ሊያደርገን ይችላል፤ በአውሮፓው አስትምህሮት ትክክልነት ከመዘነውም መመዘኛችን አግባባዊ አይሆንም፡- ዘይት በኪሎ አይመዘንም፤ ኪሎ ሜትርና ማይልም የተለያየ መጠን ነው ያላቸው፡- ምንም እንኳ ሁሉም መለኪያዎች ቢሆኑም፡- የእምነት ቅንነትም የሌለው ሰው ወይም ሃይማኖት ተነካው ምን ይኖረው ወይም ይህ የሌላው እምነት ስለሆነ ግድ የለኝም በሚል መርህ ቀድሞውኑ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል፡- የግል ፍላጎቱ ይጋርደዋልና፤ ወይም የሃይማኖት ጉዳይ ስላለበት ከፍልስፍና ጋር ማገናኘት አይገባም የሚል መርህም ተፅዕኖ ሊፈጥርበት ይችላል ፡፡ እነዚህን የዕይታ ተግዳሮቶች ፈንቅሎ በመጣልና በመጣር ለሚመመረምር ሰው ግን የዘርፎቹ ፍልስፍና ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ፣ ከጥልቅ አስተውሎትና ከሩቅና ከቅርብ የሰዎች አኗኗርና የባህል መስተጋብር ጋር የተሳሰረ መሆኑን ይገነዘባል፣ ሃይማኖት ከፍልስፍና ጋር የተዋሐደ አስተሳሰብ መሆኑን ያጤናል፤ በመሆኑም በግልብ ፍልስፍና እና ሳይንሳዊ ግመታ ግራ ተጋብቶ ሌሎቹንም ግራ አያጋባም፡፡ እና የትምህርት ዘርፎቹ ፍልስፍና ምንድን ነው?

የእነዚህ የትምህርት ክፍሎች ፍልስፍናዊ አተያይና ጽንሰ-ሐሳባዊ መሠረት መዳሰስና በአግባቡ ያንንም ማስረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ የሙያዎቹ ባለቤት መሆንን ይጠይቃል፤ ያም ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ የአከፋፈል መሠረታቸውንና የዘመኑን ነባራዊ ሁኔታና ዕውቀት ገንዘብ ማድረግን ይፈልጋል፡፡ እናም በገዳማት ለብዙ ዘመናት ተወስነው የኖሩ ሊቃውንት የመተሩትን፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ገልጾላቸው ለሕዝቦች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አኗኗር መልካምነት የሠረቱን የሊቃውንቱን ፍልስፍና እንዴት በቀላሉ (በእንደ እኔ ዓይነት ድውይ ሰው) መግለጥ ይቻላል? አይቻልም፡፡ የእኔ ዓላማ ግን ቀሊል ነው፤ ‹የሀገራችን ባህላዊ ትምህርትን በየዘርፉ በመበለት ከፋፍሎ ማስተማር ፍልስፍናዊ መሠረት አለው፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት የሚያስተምሩበት ስልት ስለሆነ አካዳማዊ ፍልስፍና አይታወቅም ልንል አንችልም› የሚል መሠረትን ለማስቀመጥ ነው፡፡

በወፍ በረርም ቢሆን ፍልስፍናዊ አተያዩን እንናገር ከተባለ ግን የፀዋተወ ዜማን ፍልስፍና ጠቁሞ ማለፍ ይቻላል፡፡ ፀዋተወ-ዜማን በምሳሌነት ብንወስድ የፍጥረታትን እንቅስቃሴዊ ድምፅ አወጣጥና መሰተጋብራዊ የጣዕመና የሐዘናት የዜማ አገላለፅን መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው፡፡ ፍጥረታት ከፍጥረታት፣ ሰዎች ከአካባቢያቸው ፍጥረታትና አካላት፣ ሰዎች ከሰዎች፣ ሰዎች ከፈጣሪያቸውና መንፈሳዊ አካላት ጋር በሚያደርጉት የግንኙነት መስተጋር ምን ዓይነት የድምፅ ቃና እንዳላቸው የሚያሰረዳ ስልትን የያዘ የትምህርት ሥርዓት ነው፡- የዜማ ትምህርት፡፡ በእነዚህ የግንኙነት መስተጋብርም ምስጋናንም ሆነ ሐዘንን፣ ፉከራንም ሆነ ሽለላንና ዘፈንን በምን ዓይነት ቃና እና እንቅስቃሴ እንደሚገለፅ ይታወቅበታል፡፡

በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሠረት ሰው የተፈጠረው እግዚአብሔርን አመስግኖ ክብሩን ለመውረስ ነው፤ ይህ መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ በዚህ እምነት መሠረትም የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንባቸው የዜማ ስልቶችና የምስጋና እና የምልጃ ቃላቶች ተመርጠው ሥርዓት ተሠርቶላቸዋል፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ ስሜቱና አእምሮ እግዚአብሔርን ወደ ማመስገን እንዲያዘነብልና ለዚያም ደስ ብሎት እንዲተጋ የሚያደርግ ነው የዜማ ሥርዓቱ፡፡ (እዚህ ላይ ‹የሰው ልጅ እግዚአብሔርን አመስግኖ ክብሩን እንዲወርስ የተፈጠረ አይደለም› የሚል ተቃውሞ ካለ ሌላ መከራከሪያ ስለሆነ እዚህ ማተቱ ከአድማሱ ውጭ ነው፤ አይ የተባለው ትክክል ነው ‹የሰው ልጅ የተፈጠረው ለዚህ ነው› ከተባለ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አስተውሎታዊ የዜማ ስልትና እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት በመውሰድም የመመደባቸውን ሁኔታ ማድነቅ ግድ ይላል፤ ‹አይደለም› የሚለው አቋም ተመራጭ ቢሆን እንኳ የፍልስፍናቸውን አስተውሎት ማጥፋት አይቻልም፡፡) ዜማውን በዐሥሩ ስልቶች እየለዩ ያዋሐዱበትን ፍልስፋና ተመልክቶም የማይደነቅ ምን ይባላል? የዚህን ዜማ ስልት ፈጣሪና ቀማሚ ያሬድን ያላደነቀ አስተዋይ ምን ዓይነት ሰው ነው? ሌሎቹንም በዚህ መልክ መዳሰስ ይቻላል፡፡

‹ለብልህ አይነግሩ ለአንበሳ አመትሩ› በሚል ብሂል የመጻሕፍት ትርጓሜንና የቁጥር ትምህርት ፍልስፍናዊ አተያይ በዚሁ ማለፍ ብዙ ችግር አይኖረውም፡- ብዬ ገመትኩ፡፡ ከጠቀስናቸው የትምህርት ክፍሎች መካከል ልዩውን አካዳሚያዊ የኢትዮጵያ ፍልስፍና እናውጣ ካልን ግን ቅኔ (በተለይ የግዕዝ ቅኔ) ነው ማለት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የዋድላ ሊቃውንት ቅኔን ‹ጥንታዊ ፍልስፍና ነው› ይሉታል፤ የተጀመረውም እንድረም ወይም በሙያ ስሙ ዘሱትኤል በተባለ የአገው ተወላጅ በዘመነ ኦሪት ነው ይባላል፡፡ በዘመናችን የሚገኙ ታላላቅ ሊቃውንትም ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና ምንድን ነው?› ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ በአብዛኛው ‹ቅኔ› የሚል ነው፡፡ የዕውቀታቸው ዋና መለኪያም የቅኔ አዋቂነት ደረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅኔ በኢትዮጵያውያን በየትኛው ዓለም ያልተደረሰበት ልዩ የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ መጽሐፈቅኔ፤ዝክረሊቃውንት› በሚል የግዕዝ ቅኔያት ሰብስብ መጽሐፋቸው በገጽ 11-12 በሚያስደንቅ አገላለጽ እንዲህ ብለው አስቀምጠውታል፡፡

‹… በሰምና ወርቅ መንገድ ሰምና ወርቁ እንደ አንድ ሆኖ የተጣመረ በአንድ ማሠሪያ የታሠረ፤ በኅብር መንገድ ንባቡ አንድ ሆኖ ምሥጢሩ የተነባበረ፤ በአንጻር መንገድ ወይምበ ምሥጢር የተነጻጸረ፤ እንደ አፍራሽ መንገድ ወርቁ በሰም የተበጠረ፤ ቅጽል ከምሳሌው የሚየስደንቅ፤ ውስጠ ወይራው የሚራቀቅ ቅኔ በኢትዮጵያ እንጂ በሌሎች የማይገኝ ስለሆነ ነው፡፡ አይገኝም ማለታችንም በውጭ አገር ባለቅኔዎች የሚባሉት ፈላስፋዎች የጻፉትን ወደ ግዕዝ ተመልሶ ስንመለከተው፤ ነገሩ ቀዋሚ ምክሩ ጠቃሚ መሆኑ ባይካድም እንዲህ እንደ እኛ ቅኔ በሰምና ወርቅ ተጣምሮ ንባቡ አንድ ሲሆን በኅብር ተባብሮ ምሥጢር በውስጠ ወይራ ተውጦ በቅጽል ተምሳሌት አጊጦ ቁጥራቸው በበዛል ዩል ልዩ መንገዶች ሲጓዝ ስለማናየው ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቅኔ በሚገባ ተምረውና ዐውቀው የውጭ አገር ቋንቋ ለመማር ወደ ውጭ አገር ተሠማርተው ቋንቋ አጥንተው የመጡ የኢትዮጵያ ወጣቶችም ይህንን ዓይነት ቅኔ በሌላ አገር አለመኖሩን፣ ግዕዝ ያውቃሉ የሚባሉትም ሀገሮች ግዕዝን በቋንቋነቱ ጠባይ እንጂ በቅኔነቱ ጠባይ የማያዉቁት መሆናቸውን፣ የእኛን ቅኔ በሚናገሩበትም ጊዜ እንኳ የኢትዮጵያ ቅኔ የሚሉት የመልካ መልኩንና የአርኪውን ግጥም መሆኑን ነገረውናል፡፡

 ‹ቅኔ በሌላ ሀገር የማይገኝ ግዕዝ ወልዶና አሳድጎለ አማርኛ ያስተዋወቀው የደቂቀ ግዕዝ አንጎልን ለማርካት የሕሊና ሐሤት፣ የአእምሮ ትፍሥሕት የድካም መድኃኒት የሀዘን ማስረሻ፣ የፍልስፍና ማጎልመሻ ሊሆን ከልዑል እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሠጠ ሀብት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ልሳናትን ስንማር ምናልባት እርሱን የመሰለ ጥበብ እንዳለ በማለት በተቻለን መጠን ይልቁንም የግሪክንና የእንግሊዝን ባለቅኔ የሚባሉትን የቅኔያችንን ጣዕም ጠልቆ ያልቀመሰ የሚያደንቀውንና የሚያጋንነውን ግጥም ሁሉ ብናነብ በዚህ አኳኋን እንደ ኮረንቲ ሽቦ ተጣምሮ የሞሄደውን የቅኔያችንን ምሥጢር አገኛለሁ ማለት ከመሬት ቁጭ ብሎ በቀኝ እጅ ሰማይን ደግፎ በግራ እጅ  ከዋክብትን መግፋት ሆነብን፡፡

የግዕዝ ቅኔ ከሌሎች ቋንቋዎች ቅኔያት በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ልዩ ፍልስፍና ነው ለማለት የሚያስችሉ ምክንያቶችን መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ምክንያቶች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፤ አንደኛው አውሮፓውያን ቅኔን ከፍልስፍና የለዩበት ምክንያት በግዕዝም ያልተንፀባረቀ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የግዕዝ ቅኔ ከፍልስፍና ጋር ተጋብቶ የሚገኝባቸው ምክንያቶችን የሚመለከተው ማሳያ ይሆናል፡፡

ከመጀመሪያው ምክንያት ብንነሳ ቅኔን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የምንልበት ምክንያት ከጥንታዊ አስተምሮ አንጻር ስናየው በኢትዮጵያ ያለው ጥንታዊ ባህልን ያልለቀቀ ሆኖ ስለሚገኝ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ቀደምትነት ካላቸው የሰው ልጅ ጥበባት ግጥም (ቅኔ) ቀዳሚነት አለው፡፡ ብርሃኑ ገበየሁም የአማርኛ ሥነ ግጥም በሚለው መጽሐፉ በገጽ 5 ላይ ግጥም በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ፣ በዕለት ከዕለት ሕይወት የሚዘወተር የቋንቋ አጠቃቀም ጥበብ ቢሆንም እስካለንበት ዘመን ድረስ ምንነቱን የሚገልጽና ሁሉን የሚያስማማ አንድ ብያኔ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ ይላል፡፡ ከፅርዕ (ግሪክ) እስከ የሮማ ፈላስፎች ድረስ ያለውን የፍልስፍናንና የግጥም (ቅኔን) ግንኙነት ስንመለከተም ሁለቱ ዕውቀቶች፡- ፍልስፍና ቅኔ፡- የተያያዙ ስለነበሩ ለማለያየት ያጨቃጭቁ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ምንም እንኳ በግጥም የተጻፉ የፍልስፍና ሥራዎች ቢኖሩም በተለይ አብዛኞቹ ቅኔዎች የተረት መንገሪያ ስለነበሩ ለፍልስፍና ትምህርት ችግር ፈጥረው ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ፍልስፍናን ከግጥም ፈልቅቆ ለማውጣት የጣረ የመጀመሪያው ፈላስፋ አፍላጦን (ፕሌቶ) ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱን ሲያስቀምጥም የሆሜር ቅኔዎችን በመጥቀስ ከሥነ ተረት ጋር ይያያዛል ይላል፡፡ ስለዚህ በእሱ ዕይታ ቅኔ ከሥነ ተረት ጋር የተያየዘ ስለ ሆነ ፍልስፍና ከቅኔ አልፎ ጥልቀት ያለው መሆን አለበት፡፡ ይህም Man and Culture a Philosophical Anthology በሚለው የDonald P. Verene መጽሐፍ ገጽ 10 ላይ እንዲህ በሚል ተቀምጧል፡፡

’  ‹በሁለቱ በፍልስፍና እና በቅኔ መካከል የትኛው የጊዜው የበላይ ገዥ አስተሳሰብ ነው ያንንስ የሚተካው የትኛው ነው የሚለው ግጭት   የአፍላጦን ዋና ጭንቀት ስለነበር… አፍላጦን በግዜው ተደቅኖበት የነበረው ዋና ተግዳሮት ፈላስፎች የባለቅኔዎች አዲስ /ቤት ውጤቶች ነበሩ አይደሉም ወይም በአዲስ ዓይነት አስተሳሰብ ተቃኝተው ነበር? የሚለው ነበር፡፡ የአፍላጦን ፍልስፍና ዋና ጎልም የፍልስፍና አስተሳሰብ ከሥነ ግጥም  (ከቅኔየበለጠ ጥልቀት ያለው መሆኑን ማሳየት ነውና፡፡

አፍላጦን ይህንን The Republic  በሚለው ዝነኛ መጽሐፉ በ10ኛው ክፍል (መጽሐፍ) አብራርቶ ጽፎታል፡፡ አፍላጦን ፍልስፍናን ከቅኔነት ወይም ከሥነ-ተረት ለማላቀቅ ሲልም የዲያሎግ ስልትን (የእሰጥ አገባ ውይይትን) ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዚህ በጠቀስነው መጽሐፍም የአውሮፓውያን የፍልስፍና አቅጣጫ የቀየሰ መሐንድስ እስከ መባል ደርሷል፡፡ በቀለ ተገኝም የምዕራባዊያንፍልስፍና፣ሥልጣኔ፣ታሪክ በሚለው መጽሐፉ በውብ ገለጻ የፕሌቶ (አፍላጦን) ፍልስፍና ተፅዕኖው የፈላስፎችን አስተሳሰብ ሁሉ ያለመጠን ሲያስጎበድደውና ሲያንገዳፍደው ኖሯል፡፡ ይለዋል፡፡ ይህ ተፅዕኖውም ፍልስፍና ሥነተረት ከሆነው ቅኔ የተለየ ሆኖ እንዲታይ በማድረግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ተማሪው የነበረው አርስጣጣሊስም ቢሆን ከአፍላጦን ብዙም የተለየ አይደለም፡፡

ከአፍላጦን ያላነሰ በአውሮፓ አስተምህሮ ተፅዖኖ ፈጣሪ የሆነው ተማሪው አርስጣጣሊስ ደግሞ ጽንሰ-ሐሣባዊና ትግባራዊ ሳይንስ በሚለው የትምህርት ክፍፍል ስልቱ ሥነ-ግጥምን ከትግበራዊ ሳይንስ ውስጥ ይመድበዋል፡፡ ይሁንና እንደ አርስጣጣሊስ ቅኔ ምንም የትረካ መተሪኪያ ስልት ቢሆንም ከታሪክ ትርካ የተሻለ ፍልስፍና አለበት፡፡ ከላይ የጠቀስነው መጽሐፍም የአርስጣጣሊስን ሰልት በገጽ 11 እና 13 ላይ፡-

ምንም እንኳ አርስጣጣሊስ ሥነግጥምን ከመዋቅር ልምድ መንገዶቹ አንድ ብቸኛው ስልት አድርጎ ቢያስበውም ስልቱ ተግዳሮት ነበረበት፤ የሥነግጥም ዓይነቶችንና አስተያየቶችን በቅኔ ገለጻ በአመክንዮአዊ ደረጃ ከፋፈፍሏልም፤ ሥነግጥም ከታሪክ የበለጠ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ መሆኑን በመሞገትም በቅኔና በታሪክ መካከል ልዩነት እንዳለ አሳይቷል፡፡ በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይህም የአርስጣጣሊስ ሐሳብ በራሱ poetics በሚለው መጽሐፉ በምዕራፍ 1፣ 9 እና 23-25 ላይ ተብራርቶ በሰፊው ይገኛል፡፡

የ‹ቅኔ ተረት ነው› አስተሳሰብ ከአፍላጦን ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በአውጉስጠን ፍልስፍናዊ ዕይታ ላይም ተንፀባርቆ ይገኛል፡፡ በአውጉስጢን ዕይታ ከሆነ ፍልስፍና የሥነ መለኮት ዕውቀት አገልጋይ በመሆኗ ቅኔን ከፍልስፍና መለየት አለመየቱ ዋና ጉዳይ መሆን የለበትም፤ ይልቁንስ ቅኔ የሥነ ተረት መተረኪያ ስለሆነ በውስጡ ያለው የቋንቋ መሳሳት(ይጠብቃል) ችግር ብቻ ሳይሆን የሠይጣን መነጋገሪያ ቋንቋ መሆኑ ዋናው ችግር ነው፡፡ ይህም ማለት ግጥም የሥነ ተረት እምነት ግብዓት ነው፡፡ እሱ እንዳለው ከሆነ፡

 ‹የተፈጥሮ ፈላስፎች ሕዝብን ለመጥቀም ይጽፋሉ፤ ባለቅኔዎች ደግሞሕዝቡን ለማስደሰት ይቀኛሉ፤ ስለዚህ የባለቅኔዎቹ ትረካዎች ሕዝቦቹና አማልክቱ የሚደሰቱባቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሊከተሏቸው የማይገቡ የአማልክቱ ወንጀሎች መሆን አለባቸው፡፡ ስለዚህ ባለቅኔዎች ከማስደሰት ያለፈ ጥቅም የላቸውም፤ በተጨማሪም የአማልክቱን ትክክልነት ለመተረትና ለሕዝቡ ክብር ለማስገኘት ይጽፋሉ፡፡› (ዝኒከማሁ)

በዚህ ሁኔታ ቅኔ መጻፍ ከልክ ያለፈ ዝቅተኛ ጥቅም ሲኖረው ፍልስፍና መጻፍ ደግሞ በተቀራኒው ከልክ ያለፈ ጠቀሜታ አለው፡፡ በመሆኑም በሁለቱ መካከል ያለው አለመጣጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ፍልስፍና ግን የሥነ መለኮት ዕውቀት መገልገያ በመሆን ከፍተኛ ጥቅም አላት የሚል መከራከሪያ አለው፡- አውጉስጠን፡፡ በእሱ ዕይታ አንጻር ቅኔ የአምልኮ ጣዖት ማቀንቀኛ የተረት አካል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አውጉስጠስ  ከአፍላጦንና ከአርስጣጣሊስ የሚለየውም ከፍልስፍና የበለጠ የሥነ መለኮት ጥበብን በማግዘፍ ወይም ለሃይማኖት የበለጠ ቦታ በማቀዳጀት ነው፡፡

ከእሱ በኋላ በ17ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው ቪኮ የተባለው ኢጣሊያዊ ፈላስፋ ግን ‹የሥነ ግጥም ጥበብ› የፍልስፍና ባህል መጀመሪያ መሆኑን በመግለፅ ይታወቃል፡፡ ለማንኛወም ከላይ ከጠቀስነው መጽሐፍ ላይ ማሳያ ነጥብ ቀንጭበን እንመልከት፡፡

ቪኮ በሥነግጥም ጥበብ ውሰጥ ሁለት ዋና ዋና መሥመሮችን ለይቶ አሳይቷል፡፡ ከእነዚህም መሥመሮች አንደኛው ከግጥም ምሥጢረዘፍጥረት ይጀምራል፤ ከዚህም የቅኔአመክንዮ፣ ግብረገብነት፣ ምጣኔሀብትና ሥነመንግሥት ፈልቀው ይበለጽጋሉ፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ የሥነፍጠረት፣ የሥነሕዋ፣ የሥነከዋክብት፣ የዘመንጥናት እና የጆግራፊ ቅኔዎች ይካተቱበታል፡፡ ስለዚህ የትኛውም ጥናት በቅኔ ጀምሮ በሳይንሳዊ ዕድገት በመሟላት ይበለጽጋል፡፡

እንዲሁም እንደ ቪኮ ከሆነ የሰቅለ-ሕልና አስውሎትም የሚፈልቀው ከሃይማኖት መሠረትና ከግጥም ጥበብ ስለሆነ የጥበብ ምንጩ እግዚአብሔር ነው የሚለው የመከራከሪያው አንኳር ነጥብ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ቪኮ ከሌሎቹ በተለየ ለቅኔ ጥበብ ከፍተኛ ማዕረግ ሰጥቷት ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ እሱ ቅኔን ልዩና የጥበቦች ጉልላት እንደሆነች አድርጎ ቢመለከታትም አጠቃላይ የአውሮፓውያን የቅኔ ዕይታ እንደ ፍልስፍናው በአፍላጦንና በአርስጣጣሊስ ተፅዕኖ ሥር ሆኖ የበለጸገ ይመስላል፡፡

በዚህ የተነሣ በአውሮፓውያን ቅኔ (ሥነ-ግጥም) ማለት ተረት መተረኪያ መንገድ ሆኖ የተወሰደ ይመስላል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ The Arts of Learning and Communication የሚለው የሊበራል አርት መጽሐፍ በገጽ 147 የሥነ ግጥምን እውነተኛ ዓላማለ እኛ ስሜት መፍጠርና ስለሰውልጅ ሕይወት አንዳንድ ውብ እውነትን በማስገኘት ማስደሰት ነው፤ መዝናናትና ደስታን የሚሠጠንም በክርክር ሳይሆንአ ንዳንድ የሰው ተግባርን በማስመሰል ወክሎ ነው፤ ይህም ማለት ትረካን በመንገር ነው፡፡ብሎ ይገልጸዋል፡፡

ይህም በልጅነታችን ‹ተረት ተረት የመሠረት› እያሉ ወላጆቻችንና ቤተሰቦቻችን ደስ ደስ የሚሉ ተረቶችን እንደሚነግሩን ዓይነት ገለፃ ይመስላል፡፡ ለዚያም ሳይሆን  አይቀርም የኢትዮጵያ ባህላዊ ሊቃውንት ‹የውጭ ሀገር ባለቅኔዎች ቅኔ የሚሉት መልካ መልኩንና አርኬውን ሁሉ ነው› በማለት እስከማንኳሰስ የደሩሱት፡፡ የሀገራችን የግዕዝ ቅኔ ግን ከጥንት ፍልስፍና ጋር እንደተጣባ እየበለፀገ የመጣ ይመስላል፡፡ በተጨማሪም ሊቃውንቱ ብዙን ጊዜ የጥንት የግሪክና የሮማ ፈላስፎችን ምክርና እዝናት በመጥቀስ ለማስተማሪያነት ሲጠቀሙ ‹እከሌ የተባለው ባለ ቅኔ እንደዚህ ብሎ ተቀኘ› ብለው በጽሑፍ ሆነ በንግግር አይገልጹም፡፡ ይህም የውጭ ሀገራት ባለቅኔዎቹን ባለማወቅ ሳይሆን ‹ባለቅኔዎች› ብለው ለመጥራት የሚያስችላቸው ቅኔዎችን ስላላገኙባቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከአውሮፓውያን ቅኔዎች በተለይም የግዕዝ ቅኔ የተረት መተረኪያ ተደርጎ አይታይም፡- የአስተውሎት ምጥቀትና ንጽሮተ ዓለም መለኪያ እንጂ! ይህ ልዩ የግዕዝ ቅኔ ጠባይ ነው፡፡

በዚህም ወደ ሁለተኛው ምክንያታችን ስንዞር ግን የግዕዝ ቅኔ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ነው ብለን የምንከራከርባቸው አራት ዋና ዋና ምክንያቶች አንስተን መመልከት እንችላለን፡፡ አንደኛው ምክንያት የቅኔ ትርጉም ‹መጽሔተ-ጥበብ፣ ብርሃነ-ዕውቀት፣ የመጽሐፍ መነጽር፣…› እየተባለ መጠራቱ የማስተዋልና የመገልገያ መሣሪያነትን የሚያመለክት መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያኦርቶዶክስተዋህዶቤተክርስቲያንታሪክከልደተክርስቶስእስከሁለትሺህየሚለው መጽሐፍ በገጽ 130-131 ላይ ቅኔን፤

‹…የውስጥና የውጭ ሕዋሳትንና ለሕሊና አስገዝቶ በሰከነ መንፈስና በተመስጦ በተወሰነ ወይም ቁርጥ ባለሐሳብ ላይ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ የሚለውን ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ በተመስጦ ቅኔ በመቁጠር ላይያለና በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተሰወረ ሰው ቅኔ በሚቆጥርበት ወይም በሚያስብበት ጊዜ በአጠገቡ ወይም በፊቱ የሚደርሰውን ወይም የሚደረገውን ነገር እያየ አያይም፤ እየሰማም አይሰማም፡፡የቅኔ አጠቃላይ ትርጉሙ ሰው ከራሱ ከልቦናው አንቅቶ፣ አመንጭቶ ለፈጣሪው አዲስ ምስጋና ለማቅረብ በፈለገ ጊዜ ምሳሌ መስሎ፣ ከምሥጢር ምሥጢር አማርጦና አራቆ ቤት በመምታትና ግጥም በመግጠም በልቡ ውስጥ ያለውን ዕውቀትና የአእምሮውን ርቀት ወይም ምጥቀት የሚያሳውቅበት፣ የዕውቀቱን ደረጃ ለሌላው የሚገልጽበትና የሚያስረዳበት፣ የሚሰማውን ምልቡና የሚያነቃቃበት፣ የሚያራቅቅበትና የሚመስጥበት ድርሰት እንደ ሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ በማለት ያስቀመጠዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የግዕዝ ቅኔ ትምህርት ከሌሎች ሀገሮችና ቋንቋዎች በተለየ መልኩ የሰዋሰው ሥርዓትን ግሥ በመግሠሥና ዐብይና ንዑስ አግባባትን በመለየት መመርመን በቅድመ ሁኔታነት የሚጠይቅ፣ ሊቃውንቱም የሰዋሰው ትምህርትን ቀድመው በመማር የሚቀኙት መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰዋሰው ሥርዓቱ የቅኔው የደም ሥርና አጥንት ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሰው ነፍሱም ነው፡፡ ስለዚህ ቅኔውን ከመቀኘት በፊት የግሥ እርባታ እርባ ቅምርንና የዐቢይ፣ የንዑስና የደቂቅ አግባባት ሥርዓቶችን ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የቅኔውን ሙያና መንገዶችንም መረዳት፣ ከዐ.ነገር ምሥረታ እስከ ቅኔው አወቃቀር ስልት ያለውን ድርጅት ማወቅ አስፈላጊው ነው፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ  የቋንቋ ዕውቀታቸውን ካደራጁና ነገሮችንና ክስተቶችን በማነጻጸርና በማቀናበር በቅኔ አስተውሎታቸውን ካዳበሩ በኋላ ቅኔውን በአግባቡ ይቀኛሉ፡፡ በዚህ መልክ ሲታይ የግዕዝ ቅኔ የግጥም ሥርዓቱና የዜማ ስልቱ ቢተውለት የፍልስፍና ጥናት መሣሪያ ከሆነው ከሥነ-አመክንዮ ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ምናልባት የሚለየው ከዓ.ነገር እውነታ ጋር ባለው አጠቃቀም ነው፡፡ በዚህም ቢሆን የተለየ የሰዋሰው አጠቃቀምና ፍሰት ስላለው፤ ያ እየተገናዘበ ቢጠና ብዙ የሚናገረው ይኖረዋል፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ቅኔ ከሌሎች ሀገራት በተለየ በኢትዮጵያ ራሱን በቻለ የትምህርት ዘርፍነት የሚሠጥ መሆኑ ሲሆን ትምህርቱ የሚሠጠውም ለሌሎች የትምህርት ዘርፎች በተለይም ለመጻሕፍት ትርጓሜያት መመርመሪያነት እንዲያገለግልም ተደርጎ ነው፡፡ ብዙዎቹ ቀድመው ዕውቀታቸውን በቅኔ ያዳበሩ ሊቃውንት የመጻሕፍት ምሥጢራትን ሰርስረው ለመረዳትና ለማሳየት የዕይታቸውን አድማስና የአስተውሎታቸውን ምጥቀትና ጥልቀት በቅኔ ዕውቀታቸው ይቆጣጠሩታል፡፡ ለዚያም ነው ቅኔን ‹የምሥጢራት መክፈቻና መቆጣጠሪያ ብርሃን፣ የዕውቀቶች ሊቀመንበር፣…› በማለት የሚጠሩት፡፡ ለዚያም ነው ሊቃውንቱ ‹ያለ ቴሌስኮፕ ከዋክብትን፣ ያለ ማይክሮስኮፕ ጥቃቅን ነገሮችን በማየት ማጥናት እንደማይቻለው ያለ ግዕዝ ቅኔ ዕውቀትም የመጻሕፍት ምሥጢራትን በአግባቡ አስማምቶ በመረዳት መተርጎም አይቻልም፤ በጨለማ ያለ ባትሪ መጓዝ ነው› የሚሉት፡፡ ስለሆነም ነው አብዛኞቹ የመጻሕፍት ሊቃውንት ለማስተማር የግዕዝ ቅኔ መማርን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚመለከቱት፡፡ ከላይ የጠቀስነው መጽሐፍም በገጽ 135 ላይ ቅኔ በሀገራችን በኢትዮጵያ ወይም በቤተክርስቲያናችን ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት ያለው ከፍተኛ የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ የቅኔ ትምህርት ደቀመዛሙርትን ተመራማሪዎች፣ ደራሲዎችና የምሥጢር ሰዎች ወይም ፈላስፎች የሚያደርግ ከሣቴ ብረሃን በመሆኑ በቤተክርስቲያን ከፍተኛ ክብርና ቦታ የተሠጠው ነው፡፡ ብሎ ይገልጸዋል፡፡

በአራተኛነት ሊወሰድ የሚገባው ምክንያት ደግሞ ዕውቀቱ የማስተዋልና የፈጠራ ችሎታ ላይ የተመሠረተና ለሚማረው ሰውም ተወዳጅነት ያለው በመሆኑ የቅኔ ትምህርትን በአግባቡ የተማሩ ሊቃውንት ነገሮችን ከነገሮችና ክስተቶች ጋር በማገናኘት ከሽነውና አስዉበው በፍጥነትና በአይረሴነት መግለጽ የመቻል ክህሎትን የሚያዳብሩ መሆናቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የግዕዝ ቅኔ ዕውቀት ማዳበር በማመራመር፣ የክርክር ሚዛንንና የመሟገት ችሎታን በማሳደግ፣ አሳማኝ ክርክርን ከሽኖና አቀላጥፎ የመናገር ተሰጥኦን በማዳበር፣ ነገሮችን በተለያየ አንግል የመመልከት ችሎታን በማላበስ፣ ወዘተ የሚሠጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ አለቃ ለማም ልጃቸው (መንግሥቱ) በልጅነታቸው መጽሐፍ መጻፋቸውን ሲሰሙ ተደስተው ‹…ቅኔ ተማር ነው እኔ የምለው፡፡ ቅኔ ለተማረ ምንም የሚያውከው ነገር የለም፡፡ ቅኔ ባትቆጥር ኖሮ የቋንቋውም ትምህርት እንዲህ አይቀልህም ነበር፡፡› ብለው ነው የመከሯቸው፡፡ (ደማሙ ብዕረኛ፤ ገጽ 97) በአጠቃላይ የሀገራችን የግዕዝ ቅኔ ትምህርት ከግጥምነት ባለፈ ባለው አገልግሎት፣ የትምህርት አሠጣጥ ሥርዓቱ (ራሱን የቻለ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ መሠጠቱ) እና የሰዋሰው ሥርዓትን ቀድሞ ማወቅ የሚጠይቅ መሆኑ ከሌሎች ሀገራት ይለዋል፤ ከሌሎች ሀገራት ቅኔያት ይልቅ ወደ ፍልስፍና ያደላል፡፡ ከፍልስፍና ዘርፎችም ውስጥ ከሥነ-አመክንዮ ዕውቀት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም ገና ጥንቱንም ከፍልስፍና ሳይለይ ኖሮ፤ እየዳበረ በመበልጸግ እኛ ጋር ስለደረሰ ነው፡፡ ስለሆነም ነው የግዕዝ ቅኔ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ልዩ ፍልስፍና ነው ብለን የምንሟገተው፡፡ ይህ ከሆነም ወንበሩ የደራና በተለየ መልኩ የደረጀ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ ማለታችን ማንም አሌ ሊለው የማይችል ሐቅ ነው፡፡

3. ዘርዐያዕቆብኢትዮጵያዊፈላስፋ? (ይቀጥላል)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply