እውን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም?

አንድ ጊዜ ፍቅሬ ቶሎሳ(ዶ/ር) የተባሉ የጦቢያ ምሁር Ethiopian needs spiritual leaders በሚል ርዕስ (The Eye on Ethiopia and The Horn of Africa vol. XXXV NO. 126 nevember 2006) ባወጡት ጽሑፍ ላይ:

‹ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ተረትና ሥነ ጽሑፍ ብዙም እውቀት የሌላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ መሪዎችና አብዮተኞች የምዕራባውያን ታሪክ፣ ባህል፣ ፍልስፍና እና ሥነ ጽሑፍ ሊቆች ነበሩ፡፡ ለዚህም ይህ ጥሩ ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ይሆናል፡፡ ሁለት ኢትዮጵያን ሊቆች የጦፈ ጨዋታ ይዘዋል፤ በመሃል በኢትዮጳያ ታሪክ ዙሪያ ሰፊ ዕውቀት ያለው አንደኛው በምዕራባውያን ትምህርት ዶክተር የሆነውን ጓደኛውን ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ የምዕራባዊያን ፍልስፍና ሊቅ የሆነው ዶክተር ግን መልሶ በሚያስደንቅ ሁኔታ ‹ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ፍልስፍና አላት?› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ የታሪክ ምሁሩም ‹በክላውድ ሰምናር የተጻፉት እነዚህ ሁሉ መጻሕፍት ምንድናቸው? ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና አይደለም እንደ የሚናገሩት? ደግሞስ ኢትዮጵያ ፍልስፍና የላትም ብለህ ካመንክ  አንተ የፍልስፍና ምሁር አይደለህም? ፍልስፍና እንዲኖራ ለምን አንተ ራስህ የፍልስፍና መጽሐፍ አታዘጋጅም?…› ብሎ አፋጠጠው፡፡ ነገሩ ግልፅ ነው፡፡ የፍልስፍናው ምሁር ስለ ጀርመን ፈላስፎች ሄግልና ማርክስ በጥልቀት ያውቃል እንደ እነ ዘርዓ ያዕቆብና ወልደሕይወት ስላሉት ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች መኖር ግን የሚያወቀው ጉዳይ ላይኖር ይችላል፡፡ይህም አንድ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ሳወራ ይህንን የማያውቅ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ‹የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ደግሞ ምንድን ነው?› ብሎ የጠየቀኝን መቼም መርሳት አልችልም፡፡ ይህ ምሁር ግን ከላይ እንዳለው የፍልስፍና ምሁር ስለ አውሮፓውያን ስልጣኔ በቂ ዕውቀት ያለው የሚባል ነበር፡፡ እንደሱ ከሆነ በእውነቱ  ኢትዮጵያ ነበራት ተብሎ ሊወራ የሚችል ምንም ዓይነት ሥልጣኔ አልነበራትም በሚል እምነት ተሞልቷል፤ ሥልጣኔ ያለውና የፈለቀው ከምዕራብ ብቻ ነው፤ ስለዚህ የትኛውም ሥልጣኔ የምዕራባዊያን ሥልጣኔ ላይ ጥገኛ ነው በማለት ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡…›  በማለት ያስቀመጡት ለዚህ ርዕስ ጥሩ ማሳያ መግቢያ ይሆነናል፡፡

የአለንበት ዘመን ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው፡፡ የትኛውንም ነገር ጠይቆ መከራከርና መመርመር የተለመደም ነው፡፡ የሀገራችንም የዕውቀት ባህል ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ዛሬ እንደ ድሮው  ‹ለምንና እንዴት ይህንን ጥያቄ ታነሣለህ?› ተብሎ ሳይሆን መልስ የሚሠጠው ‹በዚህ ምክንያት የጥያቄህ ምልስ ይህ ነው› በማለት ነው፡፡ በመሠረቱ በድሮም ጊዜ ቢሆን የሊቃውንቱ ክርክር የማይዳስሰው ጉዳይና የዕውቀት ክፍል አልነበረም፤ ከአሁኑ ዘመን ጋር የሚለያየው በአስተውሎት አቅጣጫውና መመዘኛው ነው እንጂ፤ የተለያዩ ደረጃዎችም ነበሩት፡፡ እንዲሁም የድሮዎቹ የሀገራችን ልቃውንት ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው› ብለው ሲጀምሩ የአሁኑ ጊዜ ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር አለ ወይ ብሎ ይሞግታል፡፡ የድሮዎቹ የሀገራችን ሊቃውንት ዕውቀትን የእምነታቸው ማጥበቂያና አምላካቸውን ማድነቂያ ሲያደርጉት የዘመናችን ዕውቀት ግን የሚያምነውም በዕውቀቱ አረጋግጦ ነው፤ ዋና ማወቂያውም ምንፍቅና (skepticism) ነው፡፡ ስለዚህ የእዚህ ዘመን ፍልስፍና በአብዛኛው ‹እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ቢሠራው ነው?› ብሎ አይደነቅም፤ ‹ማነው ደግሞ እሱ?› ብሎ ያፋጥጣል እንጂ፡፡ ለማንኛውም ይህንን ልተወውና ‹እውን ኢትዮጵያዊ ፍለስስፍና የለም ወይ?› ብዬ ወዳነሳሁት ጥያቄ ልመለስ፡፡

ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያን የጥንታዊ ሥልጣኔ እንድንፈትሽ የሚያደርገን የክርክር በር ከፋች በመሆኑ መልካምነት ያለው ይመስላል፤ ሆኖም ሥልጣኔያችን መሠረታዊ ፍልስፍናና አተያይ የሌለው ስለሚያስመስል ደግሞ አደጋን ያዘለና ማንነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መስሎ ይታያል፡፡ ይሁንና ካለንበት ነባራዊ ሁኔታና ከሚነሱ ጥያቄዎች አንጻር የተለያዩ መከራከሪያ ነጥቦችን ለማየትና የኢትያጵያ ፍልስፍና የምንለው የተለየ አተያይ ካለም አንጥሮ ለመረዳት ጥያቄውን አንስቶ መወያየት አስፈላጊ መሰሎ ተሰማኝ፡፡ ስለሆነም ደፍሬ የመሰለኝን ዕይታና አስተሳሰብ ለመንጸባረቅ ይህንን ጥያቄ ለማንሳት ተገደድኩ፡፡

በመሠረቱ ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና› ካልን በፍልስፍና አተያዮች ከሚዳሰሱ የዕውቀት ክፍሎች ውስጥ አንድ የተለየ ዕይታ ማለታችን ነው፡፡ ስለሆነም ከመሠረታዊ የፍልስፍና ወሰነ ትርጉም (Definition) ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፡፡ ወሰነ ትርጉሙን የሚቃወምና ጭብጡን የሳተ አተያይ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ስምም የሆነ ከሆነ ደግሞ በዚያ ውስጥ ሆኖ ከሌሎች የፍልስፍና አስተምሮዎች የሚለይበትን ነጥብ አንስቶ የተለየ የፍልስፍና አተያይ መሆኑን ማሳየት ይገባል፡፡ በዚህ መልክ መታየት ከቻለም ከሌሎች ሀገሮች ፍልስፍናዊ አተያይ የተለየ የፍልስፍና ዕውቀት በኢትዮጵያ አለ ማለት ይሆናል፡፡

በዚህ በኩል ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ ብለው የሚከራከሩትም ሆነ የለም ብለው የሚመግቱት የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎችና ምክንያታቸው መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ እኔ እዚህ የምከራከረው አንደኛውን ወገን ደግፌ ነው፤ ‹የተለየ ኢትዮጵያዊ ፍልሰፍና አለ› የሚለው መከራከሪያ የምደግፈው አተያይ ነው፡፡ ስለዚህ ‹የለም› የሚለውን መከራከሪያ የምቃኘው በአጸፋዊ መልስ እይታ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ‹ለምን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናን የአውሮፓ መዛግባተ ቃላትና ዕውቀተ መዛግበት አያውቁት ወይም አልመዘገቡትም?› የሚል አተያይ ያለው ጽሑፍ በዚህ ገጽ ላይ ለጥፌ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ላቀርብ የቻልኩትም ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ› የሚለው መነሻ ሐሣብ ትክክል እንደሆነና ተቀባይነት እንዳለው በማሰብ ነው፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ ወይ?› ተብሎ ከተጠየቀ ግን አውሮፓዊያንን ለምን አልመዘገባችሁልንም ብለን መውቀስ አንችልም፤ በመጀመሪያ የራሳችን የምንለው ፍልስፍና ያለን መሆኑን ዐውቀንና እነሱም አንዲያውቁት ማሳወቅና ማስረዳት፤ ከተቻለም መከራከር ይኖርብናል፡፡

ለማንኛውም በመጀመሪያ ‹ፍልስፍና ምንድን ነው?› ከሚለው እንነሳ፡፡ በመሠርዎ ቃላዊ ትርጉሙ እንደሚታወቀው ከሆነ ‹ፍልስስፍና ‹ፍቅረ ጥበብ› ማለት ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ አስተውሎታዊ መደነቅ ነው፡፡ መደነቅም የመፈላሰፍ መሠረቱ ነው፤ በዕውቀት ተስተውሎም እውነት ጋር ለመድረስ ይጣርበታል፡፡ እውነት ፍልስፍና ለማግኘት የሚተጋባት የመደነቅ ጉልላት ናት፡፡ ስለዚህ የትኛውም የፍልስፍና ዓይነት፤ የፍልስፍና ዘውግና አተያይ፤ እንዲሁም የፍልስፍና ወንበር ይህንን መሠረታዊ የፍልስፍና ፅንሠ ሐሣብ መሠረቱ አድርጎ ይፈሳል፡፡ ሕዝባዊም ሆነ ተቋማዊ ፍልስፍና ከዚህ መሠረት አይወጣም፡፡ ይህ ትክክል ከሆነ ሌላው ገለፃ ማብራሪያው ነው፡፡ እና ይህንን መሠረታዊ ወሰነ ትርጉም የጠበቀ የዕውቀት አተያይና ምርምር በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ የለም ወይ? የለም የሚሉትስ ምን የመከራከሪያ መረጃና ምክንያት ይዘው ነው የሚሟገቱት? አለ የምንል ከሆነስ የለም የሚሉትን ወገኖች ለምን ሊታያቸው አልቻለም? የጠቀስነውን ትርጉም መሠረት ያደረገ የፍልስፍና አተያይ አለ የምንለውስ በምን መከራከሪያ? ደግሞስ ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት የባህል መገለጫዎች ያሏት ውስብስብ ሀገር ናት የራሷ ፍልስፍና አላት የምንለው በየትኛው ላይ ተመሥርተን ነው?…

ከሁሉም በፊት ግን የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንሰራፋቱ በፊትና የፍልስፍና ትምህርትን ከተማሩ ባህላዊ ምህራን ዘንድ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም ብሎ የተከራከረ ኢትዮጵያዊ ምሁር መኖሩን አልሰማሁም፤ አላየሁም፡፡ እንዳውም ከዚህ በተቃራኒው የአውሮፓን አስተምህሮ ከኢትዮጵያውያን የባህላዊ አስተምህሮ ጋር ለማጣጣምና ለማዋሀድ የጣሩ ምሁሮች ብዙ መሆናቸውን ነው የታዘብኩት፡፡ ለምሳሌም ‹የፍልስፍና ትምህርት ቁ. 1 እና 2›፤ ‹የፍልስፍና መግቢያ አንድ እና ሁለት› የሚሉ መጻሕፍትን ያዘጋጁት የማነ ገብረ ማሪያም(ዶ/ር)፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ እና ‹ብፁዓን ንጹሐነ ልብ›፡ ስለ ክርስቲያን ሥነ ምግባር መሠረት የሚሉ መጻሕፍት ያዘጋጁት እጓላ ገ/ዮሐንስ(ዶ/ር)፣ የምዕራባዊያን ፍልስፍና ቁ. 1 በሚል የሩስልን መጻሐፍ የተረጎሙት በቀለ ተገኝ፣ … የምዕራባውያ ፍልስፍና ከኢትዮጵያ አስተምህሮ ጋር ለማዋሐድ የጣሩ ናቸው፡፡ በመሠረቱ እነዚህን እንደማሳያ አነሣሁ እንጂ በዘርዓ ያዕቆብ መጽሐፍ ላይና በባህላዊ ማስረጃዎች በመመሥረትም ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› እያሉ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፎችን ያዘጋጁ እንደ እነ ክላውድ ሰምናር እና ቴዎድሮስ ኪሮስን የመሰሉ ምሁራንም አሉ፡፡ በአሁን ጊዜም ቢሆን በየመጽሔቱና በየጋዜጦቹም የሚሟገቱ ጻሐፍት ሞልተዋል፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ‹ኢትዪጵያዊ ፍልሰፍና የለም› የሚል መከራከሪያ ይዘው ብቅ ያሉ ምሁራን መሞገት ጀምረዋል፡፡ በዚህ በኩል አንድ የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮችን ፍልስፍና ተረጎምኩ ያለ ልጅ ‹ኢትዮጵያውያን ምንም ፍልስፍና የለንም› የሚል መግቢያ ጽሑፍ አቅርቦ አይቼ ገርሞኝ ነበር፡፡ የወጣቱ ልጅ አለማወቅ ነው ብለን ልናልፈው እንችላለን፤ የባሰው ግን ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተብለው የሚጠሩ አንዳንድ የፍልስፍና ምሁራንም ይህንን ሐሣብ ሲያንጸባርቁና ለ‹የለም› ጥብቅና ቆመው ሲታዩ አስተሳሰቡን እንድናጠነው እንገደዳለን፡፡ እነዚህ ምሁራን ‹መከራከሪያዎቻቸው ምንድን ናቸው?› ብለን በመጠየቅ ጥቅል ሐሣቦቹን አንስተን መሟገትም አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ለማንኛውም ‹ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም› የሚሉትን መከራከሪያ ነጥቦች በዝርዝር ከማየታችን በፊት አሳባቸውን በጥቅል እናስቀምጠው፡፡ ተችዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ‹በአፍሪካ ውስጥ የአንዱ ሀገር ምሁር ከሌላው ጋር ተዋውቆ ሲከራከርና ሲተቻች አይታይም፤ በአደባባይ የመናገር ልምድም የለም፡፡ በአውሮፓ ውስጥ ግን ፍልስፍና ሊዳብርና ሊያንሠራራ የቻለው አንዱ ከሌላው ጋር በሚያደርገው የደብዳቤ ልውውጥ፣ የሥራዎች መተቻቸትና ቀጣይነት ባለው የፍልስፍና አስተምህሮ ልምድ የተነሣ ነው፡፡ ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን እንኳን በአህጉር ደረጃ በአገር ደረጃም ቢሆን ይኸ ልምድ የለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የፍልስፍና አስተምህሮ ልምድ ቀድሞውንም ስለሌለ አስተሳሰቡ አላደገም፤ ሁለተኛ እንዳጋጣሚም አንድ ሰው በተፈጥሮው ፍልስፍናዊ አተያይ ኖሮት ያንን ማንጸባረቅ ቢጀምር እንኳን የመተቻቸት ባህሉ አለመኖር አስተሳሰቡ እንዲቀጥልና እንዲዳብር አያደርገውም፡፡ እነዚህ ሁለት ሁኔታዎችም ተደጋጋፊና ተያያዥ ሆነው በአፍሪካ ውስጥ ዕውቀት እንዳይዳብር አድርገዋል፡፡ ለሁኔታዎቹ መቀጠልና አለመቀረፍም በአፍሪካ ሥነ ጽሑፍና የመጻፍ ልምድ አለመኖር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚያም ነው አፍሪካ ጨለማው አህጉር እየተባለ የሚጠራው፡፡

ምንም እንኳን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ሥርዓት ያላት ብትሆንም አጠቃላይ የሀገራችን ትምህርት በሃይማኖት ዶግማ የታነቀና መሻሻልን የማያውቅ ሥርዓት ሸሸብቦ ስለያዘው የተለየ የፍልስፍና አተያይ አስካሁን የጻፈ ምሁር አልተገኘም፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በፍልስፍና ዙሪያ መጽሐፍ በማዘጋጀት ቦግ ብሎ እልም ብሏል የሚባለው በ17ኛው መ/ክ/ዘ በነበረው ዘርዓ ያዕቆብ ነው፡፡ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ ለማጎልበት በጣረው ተማሪው ወልደ ሕይወት ነው፡፡ ይሁንንና የእነዚህ ሁለት ሰዎች ሥራዎች ብዙ ጥያቄዎች አሉባቸው፡፡ ለምሳሌ ፍልሰፍናቸው ኢትዮጵያዊ መንፈስ የሌለው ነው፤ ለዚህም ደግሞ በዚያን ግዜ ምሲዮኖች በኢትያጵያ በብዛት ስለነበሩ መጽሐፎቹን እነሱ ጽፈዋቸው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ይጋብዛል፤ እንዲሁም ሥራዎቻቸው ቀጣይነት ያልነበረቻው መሆናቸው በኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተዋል ብለን ለመሟገት አሳማኝ አያደርጉልንም፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያም ውስጥ ፍልስፍናን እንደ ትምህርት ወንበር በመዘርጋት ያስተማረ ምሁር አለ ለማለት ምንም ዓይነት ማስረጃ ማግኘት አይቻልም፤ አንደዘርዓ ያዕቆብ ያሉትን ብንጠቅስ እንኳን፤ የኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ስለመሆኑ ማረጋገጪያ መስጠት አይቻልም፤ የእሱ ትምህርትም ቢሆን ሥርዓት ተበጅቶለት እየተሠጠ እኛ ጋር መድረስ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ፍልስፍናን ወንበር ዘርግቶ የሚያስተምር ሳይኖር፤ እንዲሁም የአስተምህሮው  ወንበር  ቀጣይነት በሌለበት ምሁራዊ ፍልሰፍና መኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የተለየ ‹የአፍሪካ› ወይም ‹የኢትዮጵያ› ሊባል የሚችል ፍልስፍና የለም፡፡›

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት መከራከሪያዎች አሳማኝ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መፈተሸና የራስን አስተያየት ማቅረብ ለጠቅላላው ኢትዮጵያው ፍልስፍና ክርክር ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክል መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን በተናጠል እየመዘንን ማየት ይኖርበናል፡፡

(ይቀጥላል)

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply