እግዚአብሔር ለምን ሰው ኾኖ መገለጥ አስፈለገው?

ለአዳም ካሣ በመክፈልና የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍትሕ በመጠበቅ ሞትን ለመሻር የተደረገ መገለጥ

* * *

የተወለደ ከአዳም፣

መሬት ያልገዘ የለም፡፡

ግብሩን መገበር አቅቷቸው፣

ገና ብዙ ዕዳ አለባቸው፡፡[1]

* * *

ለክርስቶስ በስብዕና መገለፅ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በአዳም መሳሳት የተነሳ በሰው ልጆች ላይ ያረፈውን የሞት ፍርድ በመሻር ለማስቀረት ሲኾን በሞት መሻርም የእግዚአበውሔር ትክክልኛ ፍርድ ሳይዛባ እንዲፈፀም ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳይበሉ ያስጠነቀቃቸውን ዕፀ በለስ በመብላት ትዕዛዙን በመሻራቸው ሞት የሚባል ዕዳ በሰው ልጆች ኹሉ እንደመጣባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ‹የተሳሳቱት አዳምና ሔዋን ለምን ልጆቻቸው የሞት ቅጣት ተቋዳሽ ይሆናሉ?› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃ ከኾነ ግን አዳምና ሔዋን የተሳሳቱ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ናቸው፤ኹሉም በዓለም ላይ በመዋለድ የተራባው የሰው ዘር ደግሞ ከእነሱ የመጣ ነው፡፡ ይህም የኾነው ስህተት ፈፅመው የሞት ፍርድ ከተላለፈባቸው በኋላ ስለኾነ ማንም ከእነሱ የተወለደ ዘር ኹሉ የእነሱን ሀብትና ማንነት ይወርሳል፡፡ ከእነሱ የተገኘው ሀብትም በስህተት ላይ የተመሠረተ የስብዕና ማንነት ሲኾን የእሱም መቋጫም ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ልጆቻቸው ወይም ዘሮቻቸው በሙሉ በስህተት የመጣ የሞት ፍርድ ተካፋይ ናቸው፡፡ ያለበለዚያ በእነሱ ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ልጆቻቸው መውረስ የለባቸውም ከተባለ  የእነሱን የስብዕና ማንነትም ልጆቻቸው መውረስ የለባቸውም፡፡ እንዲሁም በአዳምና ሔዋን የተወከለው የሰው ዘር በሙሉ ነው እንጂ የሁለት ሰዎች የመሳሳት ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ልጆቻቸውን በአብራካቸው ውስጥ በመያዝ ወክለው ትዕዛዙንና ፍረዱን ተቀብለዋል፤ ፍርዱም የተላለፈው ለሰው ልጅ ኹሉ ነው፡፡ ልጆቻቸው የእነሱ ዝርዝር ማንነቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሞት ፍርድ የተላለፈው በአዳምና በሔዋን ከእነ ልጅ ልጆቻቸው ነው፡፡

የሞት ፍርድ የተላለፈው ደግሞ አዳምና ሔዋን ክፉና ደጉን ከምታሳወቀው ዕፀ በለስ በመብላታቸው በመኾኑ ሞት የመጣባቸው በማወቃቸው ነው ማለት ነው፡፡ ‹ምን በማወቃቸው?› ‹ክፉና ደጉን ነዋ!› መልሱ ነው፡፡ ይህን በቀጥታ ሲወስዱት አደናጋሪ ይመስላል፤ አዳምና ሔዋን ከመሣሣታቸው በፊት ዕውቀት አልነበራቸውም፣ ስለዚህ የበሉትም ባለማወቃቸው ነው በማለት፤ ዕወቀት ስላልነበራቸው ተጠያቂ መኾን የለባቸውም የሚል አንድምታን ያሰማል፡፡ በዚህ አተያይ ላለመኾኑ ግን ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው እናገኛለን፡፡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው በማወቃቸውና የሚያገናዝቡ በመሆናቸው ነው እንጂ ለማያውቅ አካል ጠብቅ ተብሎ ትዕዛዝ አይሰጠውም፡፡ ስለዚህ አዳምና ሔዋን ምንም ሳያውቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ካጠፉ በኋላ ማወቅ ቻሉ ማለት ስህተት ነው፡፡

እና መጽሐፍ ቅዱስ ‹አዳም ክፉና ደጉን በማወቅ ከእኛ እንዳንዱ ኾነ› በማለት ዕፀ በለሰን ከበሉ በኋላ አዳምና ሔዋን ክፉና ደጉን ለይቶ የማወቅ ሀብትን ገንዘብ ማድረጋቸውን ይናገር የለም ውይ? ተብሎ ይጠየቅም ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ለማያውቅ አካል ጠብቅ ተብሎ ትዕዛዝ አይሰጥም ብለናል፡፡ ሁለቱ እንዴት ይስማማሉ? የሚል ጥያቄንም  ያስነሳል፡፡

ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፡፡ ትክክለኛው መልስም አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን ከመብላታቸው በፊት የነበራቸው ዕወቀት ክፉና ደጉን አመዛዝኖ በማወቅ ላይ የተመሠረተ ሳይኾን ትክክለኛውንና መልካሙን ነገር በማወቅ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነበር፡- የማገናዘብና የማመዛዘን ዕውቀታቸውም በክፉና በደግ፣ በመጥፎና በጥሩ፣… መካከል ሳይኾን በአንድ በኩል ብቻ ደግ ደጉን፣ ጥሩ ጥሩውን፣ ፍቅር ፍቅሩን፣… ማወቅ ነበር፡፡ ዕፀ በለሰን ከበሉ በኋላ ግን የክፉን፣ የመጥፎንና መሰል እኩይ ተግባራትንና የእነሱ ውጤት የኾነውን ህልውናን ማጣት (ሞትን) ጭምር ማወቅ ቻሉ፡፡ ምክንያቱም የክፉ ነገር መጨረሻ የኾነውን ህልውና ማጣትን ማለፍ የሚችል የደግነት ማንነትና ዕወቀት ስለሌላቸው ይህንን የክፋትና የመጥፎ ነገሮች ኹሉ ጉልላት የኾነውን ሞትን በዕውቀትም በግብርም ሲያውቁ በዚያው ካምላካቸው እየተለዩ ለመቅረት ተገደዱ፡፡ ስለኾነም አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔር ትዕዛዝን በመተላለፍ ዕፀ በለስን ሲበሉ ገንዘብ ያደረጉት ዕውቀት ክፉውንና መጥፎውን የዕውቀት በኩል ነው እንጂ በትክክልና በጥሩ በኩል ያለውን ጭምር አይደለም፡፡ የትዕዛዙም አንድምታ ‹በክፉነትና በመጥፎነት የሚታወቅ ዕውቀት አለ፤ የእሱም ውጤቱና መቋጫው ሞት ነው፤ ይህ ዕውቀትም በዚህች ዕፅ ላይ ይገኛል፤ ስለዚህ ኹሉንም ስትበሉ ይች ዕፅ ግን ትቅርባችሁ፤ ለእናንተም አይጠቅማችሁም፤ ሞትን ታሳውቃችኋለችና፡፡› የሚል ነው፡፡ ይህ የክፉው ክፍል ዕውቀት ደግሞ አዲስ የተጨመረ በመኾኑ ከደጉና ከትክክለኛው ዕውቀት ጋር ማነጻጸሪያ ሊኾናቸው ችሏል፤ ከስህተት በኋላ ያለቸው ዕውቀት በዚህ መልክ የተቃኘ ስለኾነም ‹ክፉና ደጉን የሚያሳውቅ› ዕውቀት መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ክርክሩ የሚኾነው ክፉን ማወቃቸው አስፈላጊና ጣቃሚ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ነው፡፡

ልብ ብለን ካስተዋልነው የተለያየ ልምድና ባህልና ተፅእኖ ስላበት እንጂ የሰው ልጆች ተፈጥሯቸው ክፉ ነገርን አይመርጥም፤ የትኛውም ሰው ልጅ ሲወለድለት ደስ ይለዋል፤ ሲሞትበት ግን ያዝናል፡፡ ሞት የክፋት ኹሉ መጨረሻ (ህልውናን ማጣት) ሲኾን መወለድ ደግሞ ህልውናን ማግኘት መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ከሞት ያነሱትን ስቃዮችና መከራዎችም ቢኾን የሰው ልጅ ይቃወማቸዋል እንጂ ፈልጎ በመምረጥ አይጠቀምባቸውም፡፡ ፈልጎና መርጦ ቢተገብራቸው እንኳን በጫናዎች የተነሣ ነው የሚኾነው፡፡ ይህም የሰው ልጅ ከክፋት ተፈጥሮ ጋር ተፈጥሮው አብሮ የማይሔድለት ፍጡር መኾኑን ይመሰክራል፡፡ ይህ የማይፈለግና ከተፈጥሯችን ጋር አብሮ የማይሔድ ዕውቀት ክፍል ነው በአዳምና በሔዋን ታውቆ የሰው ልጆችን ሊስማማን ያልቻለው፡፡

* * *

ዘአምላክየ (ቅኔ)

አናኒ አምላክ ዘኢይትዐወቅ ሀገሩ

አነመ ልብሰ ተቀንዎ በእዱ ወእግሩ፤

አዳም ወሔዋን ደቂቁ እስመ በተዐርቆ ነበሩ፡፡

ትርጉም፡-

ሀገሩ የማይታወቅ ሸማኔ አምላክ

በእጅና በእግሩ ልብስ መቸንከርን ሠራ፤

ልጆቹ አዳምና ሔዋን ተራቁተው ነበርና፡፡[2]

* * *

እንግዲህ አዳምና ሔዋን በመሳሳት ዕፀ በለስን በመብላታቸው የተነገራቸው ትዕዛዙ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ኹሉን በማወቅ ላይ ስለሚመሠረት መፈፀሙ የግድ ነው፡- ልክ ዓለመ-ፍጥረቱን በትዕዛዙ ፈጥሮ እነደሚያኖረውም፡፡ ስለዚህ ትዕዛዙ ሊፈፀም የግድ ነበር፡- ይህችን ዕፀ በለስ ከበላችሁ ትሞታላችሁ የሚለው ተዕዛዝ፤ ተፈጸመባቸው፡- ሞቱም፡፡ ይሁንና አዳምና ሔዋንም መሳሳታቸውን ዐውቀዋል፤ ዐውቀውም ዝም አላሉም፤ አምላክ እንዲምራቸው ለምነዋል፡፡ ከእግዚአብሔር የሞራላዊነት ጠባያት አንዱ ደግሞ መሓሪነት ነው፡፡ ስለዚህ ሲለምኑት ሊምራቸው ይገባል፡፡ ፍረዱን ሽሮ? ከባዱ ጥያቄ ያለው እዚህ ጋር ነው፡፡

በሰው ሰውኛ መሐሪነት ባለበት ትክክለኛ ፍርድ አይኖርም፤ ትክክለኛ ፍርድ ከተሰጠም ምህረት ሥፍራ ያጣል፡፡ ትልቅ አጠያያቂና አጨቃጫቂ የሚኾነው ደግሞ እግዚአብሔር ቀድሞ ኹሉን የሚያውቅ መኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ ቀድሞውንም አዳምና ሔዋን ተሳስተው እንደሚፈርድባቸውና ምህረትም እንደሚጠይቁት ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን እያወቀ የፈረደውን ፍርድ ከመሐሪነት ጠባዩ ጋር እንዴት ያስማማዋል?

በዚህ ላይም ጥያቄዎችን አንስተን በመጠየቅ መልሳቸውንም እንፈልግ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚሳሳት እያወቀ አዳምን ለምን ፈጠረው? ከፈጠረውና ከተሳሳተስ በኋላ አጠፋህ ብሎ መቅጣቱ ትክክል ነው ወይ?  ትክክል ነው ካልነስ እግዚአብሔርን መሐሪ አምላክ ነው ማለት እንችላለን?

ለእነዚህ ጥያቄዎችም አማራጭ መፍትሔዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከአንዱ በሰተቀር ግን ሌሎቹ መልስ ሰጪ መፍትሔዎች መኾን አይችሉም፡፡ እስቲ እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡

v  መፍትሔ1፡- ‹በመጀመሪያውኑ አዳምን ሳይፈጥረው መቅረት ነበረበት፡- ምክንያቱም ባይፈጠር መሳሳት አይችልም፤ ተሳስቶም በመከራ ከመሰቃየትና ከመሞት አለመኖሩ ይሻለዋል፤ ለማሰቃየትና ለመግደል ለምን የሰውን ዘር መፍጠር አስፈለገ?› የሚል መከራከሪያ፡-

ü  ይህ ግን ከአዳምና ከሔዋን አንጻር ስናየው መፍትሔ የሚሠጥ አማራጭ መኾን አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ከስህተት በኋላ ላለው ለአዳምና ሔዋን ሕይወት መፍትሔ የሚሰጥ  ሳይኾን ቀድሞ መኾን ስለነበረበት የሚያወራ ነው፡፡ መፍትሔ የሚፈልግ አጨቃጫቂ ጉዳይ የተነሳው ደግሞ ከስህተት በኋላ ላሉበት ሕይወት ነው፤ ለዚያውም ከስህተት በፊት ወደ ነበሩበት ሕይወት ለመመለስ፡፡ በተጨማሪም ለአዳምና ለሔዋን ከመፈጠራቸው የበለጠና ከመኖራቸው የተሻለ ሕይወት ሊኖር የሚችል ነገር የለም፡-በህልውና ከመኖር የተሻለ ነገር አይኖርም፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን የእግዚአብሔር ኹሉንም ማወቅ የፈቃድ ምርጫቸውን ኹሉ የማያግድ መኾኑንም ነው፡- ፈቃዳቸውን ማገድ አለበት የምንል ከኾነ ደግሞ እንደ ማሽን፣ ከዚያም ቢሻል እንደ እንስሳት ለምን አልኾኑም ማለታችን ነው፡፡ የራሳቸው ፈቃድ ሊኖራቸው ይገባል የምንል ከኾነም በፈቃዳቸው ከእነሱ ተፈጥሮ ውጭ ያለ ነገርንም ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደሚሳሳቱ እያወቀ መፍጠር አልነበረበትም ማለት አንድም በህልውና ከመገኘታቸው አለመገኘት ይሻላቸው ነበር ማለት ነው፤ ሌላም በህልውና ቢኖሩም ሊሳሳቱ የሚችሉበት የፈቃድ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም ነበር ማለት ይሆናል፡፡ በአዳምና በሔዋን አንጻር ሲታይ ግን ቢሳሳቱም እንኳን ተፈጠሩ ከህልውና የሚበልጥ ነገር የለምና፡፡ የእግዚአብሔር ዕውቀትም ቢኾን ከመሳሳታቸው እስከ ንስሐቸውና መዳናቸው ጭምር ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ስለዚህ ማለት ያለብን እንደሚሳሳቱ እያወቀ መፍጠር አልነበረበት ሳይኾን በመሳሳታቸው የመጣባቸውን ቅጣት (መከራና ሞት) ከመሓሪነቱ ጋር እንዴት ያስማማዋል? የሚል መኾን ይኖርበታል፡፡ መልስ ያለው መፍትሔ ማግኘት የምንችለው በዚህ መልክ ማየት ስንችል ነው፡፡ ስለዚህ አዳምና ሔዋን ተሳስተው ላሉበት ሕይወትም ይህ አማራጭ መፍትሔ መኾን አይችልም፡፡

v  መፍትሔ2፡- አዳም በሌላ አካል (በእባብ፡- በሰይጣን) ቀስቃሽነት ስለተሳሳተ ያንን ቀድሞ ማጥፋት  ወይም አዳምን እንዳያሳስተው መከልከል ነበረበት የሚል አማራጭ፡-

ü  ይህም መፍትሔ የሚሰጥ አማራጭ አይደለም፡፡ አንደኛ አዳም የሌላ አካል ምክርን ከሚያውቀው ትዕዛዝ  አብልጦ ማክበር አልነበረበትም፡፡ ሁለተኛም አዳም የተሳሳተው በፈቃዱ መርጦ ነው፤ በእሱ ፍላጎት የመረጠውን ደግሞ ሌላ አካል ተጠያቂ ሊኾንበት አይችልም፡፡ ያ እንዲሳሳት ምክንያት የኾነው በአሳሳችነት የራሱን ፍርድ ማግኘት አለበት ማለት ትክክል ይሆናል፤ አዳም ግን ከጥፋተኝነት ነፃ ሊኾን አይችልም፡፡ የሌላ አካል ተፅዕኖ አዳምን ከተጠያቂነት ነፃ የማያደርገው ከኾነ ደግሞ የእዚያ ነገር መኖር ወይም አለመኖር ምክንያት ኾኖ ከወቀሳ አያድነውም፡፡ እግዚአብሔር ያ አካል እንዲኖር መፍቀድ አልነበረበትም ወይም አለመፍጠር፤ ከፈጠረውም ማጥፋት ነበረበት ሌላ የክርክር አቅጣጫ ነው፡፡ ያ አካል ለአዳም መሳሳት ምክንያት እንጂ አስገዳጅ አይደለምና፡፡  በተጨማሪም ከስህተት በኋላ አምላክ ፈታሒነቱ በመጠበቅ እንዴት የምህረት መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አይገልፅም፡፡ ስለዚህ ይህም አማራጭ መፍትሔ መኾን አይችልም፡፡

v  መፍትሔ3፡- መሓሪ አምላክ ከኾነ ዝም ብሎ ‹ይቅር ብየሃለሁ› በማለት አዳምን ቢምረው ምን ችግር አለው? በማለት የእግዚአብሔርን መሐሪነት ጠባይ ብቻ በመውስድ ፈታሒነቱን የመሰረዝ መፍትሔ፡-

ü  ይህ አማራጭ ምንም እንኳን አዳምና ሔዋን ከተሳሳቱ በኋላ ያለውን ችግር በማየት አንደ አማራጭ የተወሰደ ቢኾንም፤ መፍትሔ መኾን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር መሐሪ ብቻ ሳይኾን ትክክለኛ ፈራጅም ነው፡፡ ያለበለዚያ የመሐሪነት ጠባዩን ብቻ የምንመለከት ከኾነ አምላክን በፍርዱ አላዋቂና ተለዋዋጭ እናደርገዋለን፡- ይህ ደግሞ ያላዋቂነት ግንዛቤ ነው፡፡ አንዱን መርጦ ሌላውን መሰረዝም የእግዚአብሔርን ጠባያት በከሀሊነት ባህርዩ አንድ መኾናቸውን አለማስተዋል ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አማራጭ የእግዚአብሔርን ጠባያት ሚዛን በመጠበቅ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም፡፡

v  መፍትሔ4፡- በአዳም ላይ የተላለፈው ፍርድ ተፈጽሞበት ሞትን የሚያስቀር አካል ተገኝቶ፤ እሱም ክሦ ሲያስታርቀው (የአስታራቂ ሽማግሌ መገኘት)፡-

በዚህ አማራጭ መሠረት አዳም አምላኩ የሠጠውን ትዕዛዝ በማፍረስ የሞት ፍረድ ተላልፎበታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ መሳሳቱን አውቆ ተሳሳትኩ በማለት ምህረት ከአምላኩ ጠይቋል፤ በዚህ የተነሳም አንደኛ የተፈረደው ፍርድ ተግባራዊ መኾን አለበት፣ ሁለተኛ ደግሞ አዳም ምህረት ማግኘት አለበት፡፡ ስለዚህ ለመፍትሔው  የፍርዱ ተግባራዊነት እንደተጠበቀ ኾኖ አዳም ምህረት እንዲያገኝ የሚያደርግ አስታራቂ ሽማግሌ (አስማሚ አካል) መገኘት አለበት፡፡

ከዚህ በፊት ከተመለከትናቸው ከሦስቱ ይህ የተሻለ እና ትክክለኛ አማራጭ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የአምላክን ትክክለኛ ፈታሒነት ከመሐሪነቱ ጋር ያስማማል፤ በኹል ዐዋቂነቱም ላይ ጥያቄ አያስነሣም፡፡ ምክንያቱም የአዳም ስህተት በአስታራቂው ካሣ መፍትሔ እንደሚሠጠው ቀድሞ የታወቀ ነውና፡፡ ይህ ትክክል ከኾነም አስታራቂው ማን መኾን ይችላል? ምናልባት መልአክ?

ከመላዕክት መካከል ይህንን መኾንም ኾነ መፈጸም የሚችል የለም፡፡  ምክንያቱም እንደሚባለው ከኾነ መልአክት መሞት አይችሉም፤ የተሰጠው ፍርድ ደግሞ ሞት ነው፤ በሌላ በኩል የበደለው ሰው እንጂ መልአክ አይደለም፡፡ ሰው ደግሞ የበደሉ ተካፋይ ነው፡፡ እና ማን ይሁን?

ማንም ይሁን ይህ አስታራቂ፡-

ü  ሰው መኾን አለበት፡፡ ምክንያቱም የበደሉት አዳምና ሔዋን ሰዎች ናቸውና፡፡ እነሱን በመወከል ምህረት ለማግኘት መለመንና ለይቅርታ የሚኾን ካሣም መክፈል አለበት፡፡ ካሣውም በሰው ልጆች ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ የሚያስቀር መኾን አለበት፤ ሞትን ሞቶ በመግደል፡፡ ይህንን ካልቻለም የሞት ፍርድ እንደጸና ይኖራል፤ እግዚአብሔር ፍርዱ ተለዋዋጭ አይደለምና፡፡ ስለዚህ የሞት ፍርድን ራሱ በመሞት የሰው ዘር በሙሉ ከዕዳው ነፃ እንዲወጣ ማድረግ የሚችል ሰው መኾን አለበት፡፡

ü  የሞት ካሣን ሲከፍልም ሞትን ድል ነሥቶ በመነሣት የሞት ፍረድ መቅረቱን ማሳየት አለበት፤ ማለትም ራሱ ሞቶ መቅረት የለበትም፤ የሞት ዕዳ መቅረቱን ማረጋገጥና ማብሰር አለበት እንጂ፡፡ ሞቶ ለመቅረትማ የአዳምና ሔዋን ዘሮች ኹሉ እየፈጸሙት ኖረው የለም! ሞትን አሸንፎ ድል በማድረግ ማሳየት ካልቻለ ምን ዋስትና ይኖረዋል?

ü  ቅዱስ መኾን አለበት፡፡ ያለበለዚያ በእርኩሰት ተዘፍቆ በአምላክ ፊት በመቅረብ ማስታረቅ አይችልም፡፡ ማለት የበደሉ ተካፋይ መኾን አይኖርበትም፤ ከኾነ የሞት ካሣን በመክፈል አዳምን ከእነ ዘሩ ማስታረቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ ከአዳም የሚወረሰው ኀጢያት ተካፋይ መኾን የለበትም፡፡ ይህ ከኾነም አስታራቂው የረከሰውን የአዳምን ተፈጥሮ ከእነዘሮቹ መቀደስና ማደስ የሚችል መኾን አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ራሱ ቅዱስ ኾኖ መገኘት ይኖርበታል፡፡

ü  አምላክ መኾን ይኖርበታል፡፡ ቅዱስ በመኾን ሞትን ድል ሊነሳ የሚችል የሰው ዘር አልተገኘም፤ የለምምና፡፡ በተጨማሪም አዳም አምላኩን ምህረት የጠየቀው መፍትሔ እንዲፈልግለት ወይም በራሱ በደሉን ተሸክሞ ካሣ በመክፈልም ቢኾን እንዲምረው ነውና፡፡ ከኹሉም በላይ አዳም እግዚአብሔርን ፍጠረኝ ሳይለው በሌላ አካል አሳሳችነት እንደሚሳሳትና ምህረትም እንደሚጠይቀው እያወቀ ስለፈጠረው ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ የረከሰውን የአዳም ተፈጥሮ ኃላፊነት ወስዶ መቀደስና ማደስ፣ እንዲሁም  የሰው ተፈጥሮ ገንዘብ ማድረግ የማይሳነው  እግዚአብሔር ራሱ ብቻ ስለኾነ አስታራቂው አምላክ ሊኾን የግድ ነው፡፡

ü  ስለዚህ በጥቅሉ አስታራቂው በደል ቀርቶ ዕርቅ እንዲፈፀም ሁለቱንም አምላክንም ሰውንም መወከል አለበት፡፡ ስለዚህ በዚህ አማራጭ መሠረትም ክርሰቶስ አምላክ ኾኖ ሳለ ሰው በመኾን አዳምና ዘሮቹን ከሞት ፍርድ ነፃ ለማውጣት (ለማዳን) መጣ፡፡ ለምን?

ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መሥፈርቶችም የሚያሟላ ኢየሱስ  ክርስቶስ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ፡-

i.      አስታራቂ ሽማግሌ የኾነ ካህን ነው፡፡ በመኾኑም መሥዋዕትና የይቅርታ ልመናን (ምልጃን) የሰው ዘሮችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ አቅርቧል፡፡ ስህተት አንድ ጊዜ በአንዱ አዳም ተፈፅሞ ኹሉንም የአዳም ልጆች ባለ ዕዳ እንዳደረጋቸው ኹሉ የክርስቶስም መሥዋዕትና ልመና በአንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ተፈፅሞ ኹሉንም የአዳም ዘሮች በመወከል ምህረት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ii.      መሥዋዕቱም ራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹ይቅር በላቸው› እያለ ሞትን በመሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠው ራሱ ነበርና፡፡ ሞት ድል ተነስቶ ሳይቀርም ማስታረቅ አይችልም ነበር፤ ሞት መቅረት የሚችለው በመሞት ነበር፡፡ ለሌላው ሲሉ መሞት ደግሞ መሥዋዕትነት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ክርስቶስ ራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠው፡-በመሥዋዕትነት፡፡

iii.      ይቅርታ ሠጪም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው የኾነው አምላክነቱን ትቶ ሳይኾን በመስቀል ላይ ኾኖ ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዓለምን ሞልቶ ይገኝ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርንም ይቅርባይነት ወክሎ እርቁን ማፅደቅ ነበረበትና፤ አፅድቋል፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ሞቶ በመነሣቱ ዕርቅ ተፈጸመ ወይም ተፈጽሟል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በስብዕና የተገለፀው ካህን (መሥዋዕት አቅራቢ) ፣መሥዋዕት (በመስቀል ላይ በመሰቀል) እና መሥዋዕት ተቀባይ (ይቅርታን ሰጪ) ኾኖ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነው ሰው ከአምላኩ ጋር በክርስቶስ ታረቀ የሚባለው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጥ ያስፈለገበት አንዱና ዋናው ምክንያት የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ እንደተጠበቀ ሞትን ሽሮ አዳም የአምላኩን ምህረት እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡

* * *

ሚበዝሁ ( መምህር ዘደበጋ ሚካኤል ደንበያ፣አክሊሉ ወርቅነህ)

በይነ ጣዕዋሃ ሐንካስ፣

ትትበላዕ ላሕም አአምሥጦ ዘይትከሃል

ወለዘተበልዐት ላሕም መድኃኔ ዓለም ተመሰላ፣

አኮኑ ተቀትለ በዘበልዐት ሔዋን ፍሬ ዕፀ በለስ ሰግላ፡፡

ትርጉም፡-

ማምለጥ የሚቻላት ላም፣

ስለ አንካሣ ጥጃዋ ተበላች፤

የተበላችውንም ላም መድኃኒያዓለም ተመሰላት፣

ሔዋን የሾላ ፍሬ ዕንጨትን በበላች ተገድሏልና፡፡[3]


[1] ኅሩይ ወ/ሥላሴ፤ ወዳጀ ልቤና ሌሎችም፣ ገጽ 36

[2] የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ ገፅ 260

[3] የግእዝ ቅኒያት የሥነ ጥበብ ቅርስ 3፤ ገፅ 7

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply