እግዜርን ጠርቶ የለም ማለት መኖሩን በግማሽ መመሥከር

(በካሣሁን ዓለሙ)

በዚህ ዘመን እንደ ኢ-ኣማኝ ማስረጃ ሳይኖረው የሚቦርቅ ተጨቃጫቂ ዐላየሁም፡፡ አንድ ጊዜ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ‹ፍልስምና ፫› በሚለው መጽሐፉ ላይ አንዱን ኢ-አማኝ ነኝ ባይ ‹ስለ እግዚአብሔር አለመኖር ምን ማስረጃ አለህ?› ብሎ ሲጠይቀው ‹ኢ-አማኝ ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅበትም፤ አለ የሚል ነው ማቅረብ ያለበት› በማለት መልስ መስጠቱን አንብቢያለሁ፤ ይህች መከራከያም የተለመደች መሆኗን አውቃለሁ፡፡ ከሰሞኑም አንድ ጓደኛዬ ተመሣሣይ አስተያየት አቀረበልኝ፡- ‹‹እግዜር› አለ ብሎ የሚከራከር ሰው ‹አለ› ያለውን ነገር የማብራራት ሸክሙን የሚወስድ መሆኑ ነው፡፡ ቃል እና ሃሳብ ሆነው በማኅበረሰቡ ውስጥ የምናገኛቸውን ነገሮች ሁሉ ‹አሉ› የሚለው ሰው ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡››ይላል በሣጥኔ ውስጥ የተላከልኝ መከራከሪያ፡፡

እንደኔ እንደኔ ያለመሳረጃ መከራከር በተለይም ማስረጃ ያለውን ትቶ ማስረጃ እንደሌለው እያወቁ ለዚያ ጥብቅና ቆሞ እሞግታለሁ ማለት የእንቆቅልሽ ጨዋታ ይመስለኛል፡፡ የማይገባኝ ነገርም ኢ-አማንያን አቋም ይዘው የመከራከራቸው ነገር ነው፤ ጥብቅና መቆም እኮ! ለአመኑበት ነገር መመስከር ነው፡፡ አቋም ከሌላቸውና ‹መከራከር አንችልም› ካሉም መዘባረቅ የለባቸውም፤ እየተከራከሩና ‹እግዚአብሔር የለም› ለሚለው ለኢ-አማኝነት ጥብቅና ቆመው ከሆነ ‹ማስረጃ አቅርቡ› መባላቸውም አግባብ ነው፤ ሊያቀርቡ ይገባል፤ ያለበለዚያ ኢ-ኣማኝነት ትክክል ነው ብለው የሚከራከሩበት ምክንያት ምንድን ነው? ማስረጃ የለኝም ግን ትክክል ነኝ ብሎ ክርክር ምንድን ነው? ስለዚህ ‹እግዚአብሔር የለምን› አምነውበት እየተከራከሩ ስለሆነ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፤ ምክንያታዊም መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የሚከራከሩት ማስረጃ ሳይኖራቸው ከሆነ ‹አንድትም ብጣቂ ማስረጃ ብትሆን ከተገኘች ለመቀበልና እምነታቸውን ለመቀየር ይገደዳሉ ማለት ነው፤ ምክንያቱም የሚከራከሩት ስለህልውና ነውና፡፡

እስቲ በሣጥኔ ውስጥ ደረሰኝ ያልኩትን መከራከሪያ በአግባቡ እንፈትሸው፡፡ የዐረፍተ ነገሩ አስተሳሰብ የተመሠረተው ‹ሳይኖሩ በቃል ደረጃ አሉ የሚባሉ ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ ‹እግዜር› የሚለው ቃል ይጠቀሳል የሚል ይመስላል፡፡ ስለዚህ ‹በህልውና ሳይኖር ስም ተሰጥቶት የሚገኝ ነገር አለ ወይ?› የሚል ጥያቄን እናንሳ፤ምክንያቱም ለእግዜር አለመኖር እንደማሳያ የሆነው ያለ ህልውና ስም ተሰጥቷቸው የሚገኙ ነገሮች መኖር ነው፤ ስለዚህ አስተሳሰቡን ቀድሞ መቃኘት ያስፈልጋል፤ መልሱ በአጭር ሲቀመጥም ‹የትኛውም ስም የተሰጠው ነገር ህልውነት አለው› የሚል ይሆናል፡፡ በመሠረቱ ይህ የሥነ-ህላዌ (Ontology) ምርምርን የሚጠይቅ ጉዳይም ቢሆንም፤ ምሳሌ በመጥቀስ ለማየት መሞከር አይከፋም፤ ለምሳሌ የሒሳብ ቁጥሮች፣ ረቂቅ የሆኑ ‹እውነት›፣ ‹ፍትህ›ና ፍቅርን የመሰሉ ቃሎች፣ ረቂቅ የመናፍስት ስሞች ህልውና የሌላቸው ይመስላሉ፡፡ ህልውና ባይኖራቸው ኖሮ ግን ስም አይወጣላቸውም ነበር፡፡ ለምሳሌ ቁጥሮች ከምናያቸውና ከምንቆጥራቸው ነገሮች ተረቀው ነው፤ ሒሳብ በረቂቅነት የሚጠቀምባቸው፤ ለማሳያም አንድ ሰው፣ አንድ እንስሳ፣ አንድ ልጅ፣ አንድ ድንጋይ ፣ ወዘተ ስንል መጥነን እየተናገርን ነው፡፡ ይህንን ቁጥር እንጠይቀው ካልን ግን ‹አንድ ሰው ማን?›፤ ‹አንድ እንስሳ የትኛው?›፣ ‹አንድ ድንጋይ ምን ዓይነት?›፣ ወዘተ እያልን ብዙ ተያያዥ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን፡፡

ለምሳሌ ‹አንድ ሰው› ተብለናል፣ ሰው ግን የሚቆጠር፣ የሚዳሰስና የምንጨብጠው ነገር ነው ወይ? ‹ሰው› የሚለው ቃል እኮ ሁሉንም የሰው ዘሮች፡- ያሉትንም፣ የሞቱትንም፣ የሚፈጠሩትንም፡- የሚወክል ረቂቅ ቃል ነው፡፡ ሰለዚህ ‹ሰው› የማይጨበጥ ባሕርያዊ ስም ነው፤ ለመቁጠር አንችልም፤ ቁጥር ተለክቶና ተወስኖ የሚረዱት ወካይ ነው፤ ሰው ደግሞ ረቂቅና ልንጨብጠው የማንችል የብዙ ተቆጣሪ ሰዎች የጋራ ባሕርይ ነው፡፡ ‹አንድ ሰው› ስንልም መጠኑን ‹አንድ› የሚለው ቁጥር ባይወስንልን ኖሮ የማይጨበጥ ባሕርይን ወክሎ ይቀር ነበር፤ ‹አንድ ሰው› የሚለውም ቢሆን ልጅ ይሁን ሽማግሌ የምናቀው ነገር የለም፡፡ ጠለቅ እናድርገው ካልን ‹ለመሆኑ ሰው የሚባል ነገር አለ ወይ?› በማለት ብንጠይቅ ጭቅጭቃችን ይጨምራል፤ አንዱ ‹እንዴት የለሁም ትለኛለህ?› ብሎ ሊያፈጥ፤ ሌላው ‹አንተስ፣ እኔስ፣ የጥንት ወላጆቻችንስ፣ የምንወልዳቸው ልጆቻችንስ ሰዎች አይደሉም ወይ? ሁሉን ሰው ብለን ከጠራንስ ህልውናውን የት አገኘነው?› ብሎ ሊሞግት ይችላል፡፡ ጥያቄዎቹን የበለጠ እንጎርጉራቸው ካልን ሌሎችን እየሳቡ ይመጣሉ እንጂ ክርክሩ መቋጫ አይኖረውም፤ መፍትሔውም የህልውና ምሥጢርን መረዳት ነው፤ የድንጋይንም ሆነ የሌሎች ነገሮችን ባሕርያዊ ስም በዚህ መልክ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህ ከሆነ ‹ቁጥር የሌለ ነገር ነው›፤‹ሰውስ የሌለ ነገር ነው› ማለት እንችላለን? ድንጋይንስ?… ቁጥር የሌለ ነገር አይደለም፤ ሰውንም የለም ማለት አንችልም፤ ድንጋይንም የለም ብለን መናገር ስህተት ነው፤ ሌሎቹንም እንደዚሁ፡፡ ሰው የሚለው ስም ባሕርያዊ ስም ነው ብለናል፤ ባሕርይ ደግሞ በአካል ውስጥ ተሠውሮ ምንነትን ወይም ማንነትን የሚያስነብብ ነገር ነው፡፡ ለዚያም ነው በልጁ በማሙሽም ሆነ፣ በአባትዬው በከበደ፣ በእናትዬው ጫልቱም ሆነ በጆን ወይም በሙሃመድ ውስጥ ‹ሰውነት› ባሕርይ ሆኖ የሚኖረው፤ አንደዚሁም ቁጥርም የምጣኔ ባሕርይ ማንበቢያ ነው፤ ስለዚህ አንድ ስንል በብዙ ነገሮች ውስጥ ሆኖ የመጠኑን ልክ ያስነብበናል፡፡ የሒሳብ ስሌትም የተወሰደው ከዚህ አስተሳሰብ እንጂ የሌለ ነገርን ፈጥሮ አይደለም፤ ምናልባት የሒሳብ ስሌቶችንና ቁጥሮችን በደብተር ላይ እያየን ስላደግንና በዚያም ላይ ተመሥርተን ስለምንሠራ ህልውነትን የማይወክሉ መስለውን ይሆናል እንጂ የህልው ነገር ወካይና ቅጂዎች ናቸው፤ የ‹ሌለ ነገርን› የሚያነብም ሆነ የሚረዳ ማንም የለም፤ ረቂቅ ሆነው ለእኛ የሌሉ የሚመስሉን ነገሮች ሁሉ በባሕርያዊ ምንነታቸው ማንበቢያ ስለሆኑ ነው፤ እነሱ ባይኖሩም ነገሮቹን አሁን ባለው ሁኔታ መረዳትና መጠቀም አንችልም ነበር፡፡

‹ይህ ከሆነ ለምሳሌ ‹ፍትህ›ና ‹ፍቅር› ያልናቸውም በአካል የሚገኙ ነገሮች ናቸው ልንል ነው?›ብሎ የሚጠይቅ ወይም በህቡቅ ጥያቄው የሚብላላበት ሰው ሊኖር ይችላል፡ ሁለት ነገሮችን ልብ እንበል፤ አንደኛ ‹ህልውነት የሌለው ስም› የለም፤ ሁለተኛ ‹ባሕርይ ያለ አካ አይገለጽም፤ ስለዚህ አካል ሳይኖር ባሕርይ አይኖርም፤ ባሕርይ የሌለው አካልም የለም›፡፡ ይህ የተፈጥሮን አጠቃላይ ሁኔታ ያገናዘበ መሠረታዊ ፍልስፍና ነው፤ ነቂሀ-ኅሊናንም አንቅቶ ማስተዋልና መመንጠቅን ይጠይቃል፡፡ (1) በዚህ መሠረታዊ መርሆ ተስማምተን ከተነሣን፤ (2) ‹ህልውነት የሌለው ስም ከሌለ፤ (3) ‹ፍቅር› እና ‹ፍትህ› የሚሉ ቃላትም ስሞች ከሆኑ፤ (4) ህልው ነገርም ‹ባሕርይና አካል› የሚኖረው ከሆነ፤ (5) ባሕርይ የህልው ነገሩ ማንበቢያ፣ አካል ደግሞ ተነባቢው ከሆኑ፤ ተለያይተውም ካልተከሰቱ፤ (6) እንደ ‹ፍቅር› እና ‹ፍትህ› የመሳሰሉ ቃላትም ባሕርያዊ ስሞች ከሆኑ አካል ያላቸው ህልው ነገሮች ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ በአጭሩ ፈጥነን በመሮጥ ስንመጣ ነው፡፡ ‹ፍቅር› እና ‹ፍትሕ› የመሳሰሉ ስሞችን ለመረዳት ተፈጥሯቸውንና መገለጫቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሯቸው ረቂቅ፤ የሚገለፁትም በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መልኩ ነው፤ ምሥጢረ-ህላዌን መመርመር የሚጠይቁም ናቸው፤ ምክንያቱም ቃላቱ የተግባራት ባሕርያዊ ስሞች ናቸው፤ በተለያየ አካላት ወስጥ በግብር ይነበባሉ፤ ወይም ግብርን ያነባሉ፤ ያለ እነሱ መኖርም ተግባራትን፣ ምግባራትን፣ የአኗኗር ሁኔታን ማወቅ አይቻልም፤ ይህም ሰውን ‹ሰው› በሚለው ባሕርይው ለይተን እንደምናነበው፤ ‹ድንጋይን› በድንጋይነት ባሕርይው እንደምንለየው፤ ‹ፍትሕ› እና ‹ፍቅር› የመሳሰሉትን ባሕርያዊ ስሞችም ተግባራዊ ክንውኖችን ያነቡልናል፤ ሥራው ትክክልና አግባብ መሆኑን፣ ተግባሩ መወደዱን ወይም ማስደሰቱን ይገልፁልናል፤ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በተግባራት ውስጥ ሳይኖሩ የተግባሩን የአተገባበር ሁኔታ መረዳት አይቻልም፤ እነዚህ ነገሮች የሚገለፁት በተግባራዊ ክንውን ከሆነም ተግባራዊ ክንውንም የሚያከናውነው ነገር ሳይኖር በራሱ አይከሰትም፡፡ በዚህ መልክ የትኛውም ተግባር ያለ አከናዋኝ ወይም ተግባሪ የማይከሰት ከሆነ፤ ተግባራትም የሚታወቁት በክንውኑ ማንበቢያ ነገሮች (ፍቅር፣ ፍትሕ…) ከሆነ፤ የሚከሰቱት ህልው በሆነና ባለ ነገር ላይ ነው ማለት ነው፤ ይህ ከሆነም ህልው የሆነ ነገር ባይኖር ምንም ዓይነት ስም አይሰጥም ነበር፡፡

እዚህም ላይ ቢሆን ተከራካሪው መሞገቱን ላያቆም ይችላል፤ ‹ታዲያ የታለ አካላቸው?› ብሎ፤ ይህንን ከጠየቀ ግን እስካሁን ድረስ ዋና ነጥቦችን አልተረዳም ማለት ነው፤ ለምሳሌ ቁጥርን ‹አንድ› ስንል ይኸኛው ብለን መወሰን አንችልም፤ የቁጥር ባሕርይ የሚገኘው ሁሉም ፍጥረት ውስጥ ነው፤ ሰው ውስጥ እንዳለው ሁሉ እንስሳ፣ ድንጋይ ወይም ሌሎች ነገሮች ውስጥሁሉ አለ፤ በዚህ የተነሣ ቁጥርን በአንድ በሰው ወይም በሌላ ብቻ ወስነን መረዳት ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ በነቂሀ-ኅሊና ላስተዋለው የትኛውም ስም ያለው ነገር ሁሉ ከህልውና የሚቀዳ መሆኑን መረዳት ይችላል፡፡ ሆኖም እዚህ የጠቀስናቸው ‹ፍትህ› እና ‹ፍቅር› የሚሉ ስሞች ‹ሰው› ከሚለው ስም ይለያሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ አካላቸው በግልፅ የማይገለፅ ነገር ግን በብዙ ነገሮች በደረጃና በምጣኔ የሚንጸባረቅ ናቸው፤ ‹ሰው› የሚለው ባሕርያዊ ስም ግን የሰው ልጅ ዘርን ብቻ የሚመለከት ስም ነው፤ የሰው ልጅን ከሌሎች መለያ ነው፤ በሌላ አገላለፅ ‹ሰው› የሚለው ስም ከፍጥረታት ውስጥ የአንዱ ፍጥረት ዓይነት የወል ባሕርያዊ ስም ነው፡፡ ቁጥር ግን አቅሙ ኖሮን ልንቆጥረው በምንችል የትኛውም ነገር ውስጥ ይገኛል፤ ያለ ቁጥር ውሳኔ ምንንም ነገርን ወስነን መረዳትና መናገር አንችልም፤ የሚያነበውም የሚነበበውም በየትኛውም ነገር ውስጥ ነው፤ ከምንምነት እስከ የትየለሌነት ያለውን እኛ ከቻልን ያስነብበናል፡፡ እንደዚሁም ‹ፍቅር› እና ‹ፍትሕ› የመሳሰሉ የትግበራ ሁኔታ ማወቂያ ስሞችም ሁሉም ነገር ውስጥ ይኖራሉ፤ የእነሱ ሥራ የአፈጻጸሙንና የአከሳሰቱን ሁኔታ ማስነበብ ነው፡፡ ስለዚህ ‹ፍትሕ› እና ‹ፍቅር› የመሰሉ ነገሮች የሉም ማለት ቁጥር የለም ከማለት የተለየ አንድምታ የለውም፤ በመኖራቸው ከተስማማንም የርቅቀታቸው ጉዳይ የፍጥረታትን ደረጃና ምዳቤ መረዳትን ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ ለዚህም የነገሮቹን ምጣኔ፣ ሁኔታና ምዳቤም መለየት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ከተገነዘብንም ህልውነት የሌለው ስም የለም በማለታችን ተስማማን ማለት ነው፡፡

‹እግዚአብሔር› የሚለው ስም በአካሉ ረቂቅነት በባሕርዩም ከሁሉም ነገሮች ምጡቅነት ያለው ነው፤ በእሱም ውስጥ እነ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ እውነት፣ ቅድስና እና የመሳሰሉ የግብር ባሕርያዊ ስሞች ይነበባሉ፤ እሱንም ያስነብባሉ፤ ምክንያም የእነሱም ፍጽምና መቋጫው እሱ ነው፤ እንዲሁም ስሙ ብቸኛ የሆነ ተጋሪ የሌለው የአንድ አካል መጠሪያ ነው፤ ሌላውን ውዝግብ አንተወውና ‹እግዚአብሔር› የሚል ስም መኖሩ ብቻ የመኖሩ ዋና መስካሪ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ያተትኩት ምን ያህል ውስብ ነገርን እያነሳን እንደሆነ ለማሳየት ነው፤ አሁን ግን ወደ ‹እግዜር የለሞች› እንመለስ፡፡

እንደ እኔ ግንዛቤ ከሆነ ‹እግዚአብሔርየለም› ማለት ለመኖሩ ግማሽ ማስረጃ ማቅረብ ነው፤ ‹እግዚአብሔር የለም› በማለት የሚከራከር ሰው በመኖሩ ቢያስ በግማሽ አምኗልና፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ‹የሌለ ነገር› ስም አይኖረውም ብለናል፤ኢአማኒያን የሚከራከሩት ግን ‹እግዚአብሔር› ብለው በመጥራት ነው፤ስለዚህ ‹እግዚአብሔር› በማለት ስም ሠጥቶ እንደገና ‹የለም› ብሎ መከራከር እርስ በራሱ የሚጋጭ ክርክር ነው፡፡ መቼም ቢሆን ህልውና ወይ ከስም ጋር እኩል ይከሰታል ወይም ነገሩ ከተከሰተ በኋላ ስም ይወጣለታል እንጂ፤ ህልውና የሌለው ነገር ስም የለውም፡፡ በሌላ በኩል ግን ‹የለም› ከሚለው ቃል ውጭ ህልውና የሌለውን ነገር ስም በመስጠት መከራከር ይቻላል ካሉ፤ ጠቅሰው ማስረዳት አለባቸው፤ ኢ-አማኞች ግን ይህን ለማስረዳት ምክንያት ወይም ተጠየቅ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ምናልባት ‹የለም› የሚለው መከራከሪያ የሚሠራው ከሥፍራና ከጊዜ ሁኔታ ጋር አብሮ ለሚለዋወጥ አካል ከሆነ፤ ይህ የመወሰን ችግር ስለሆነ አማንያን ‹እግዚአብሔር› የሚሉትን አይመለከትም፤ ስለዚህ ኢ-ኣማንያንም ‹እግዚአብሔር የለም› የሚሉት በጊዜና በሥፍራ ውስንነት ከሆነ፤ ‹እግዚአብሔር አለ› በማለት የሚከራከሩትን ስለማያቅፍ ክርክራቸው አማንያን ‹አለ› በማለት የሚመከራከሩለትን እግዚአብሔር አይመለከትም ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ እዚያው ኢ-አማንያን እርስ በራሳቸው ‹የራሳቸውን እግዚአብሔር› ወስነው ይጨቃጨቁ እንጂ አማንያን ከሚጠሩት እግዚአብሔር ጋር እያያዙ አያጭበርብሩ፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ‹እግዚአብሔር የለም› በማለት መከራከራቸው የሚመሰክረው መቃወማቸውን እንጂ ምክንያታዊ መሆናቸውን አይደለም፡፡ ማለትም ኢ-አማንያን ‹እግዚአብሔር የለም› ብለው ሲከራከሩ ‹እግዚአብሔር መኖሩ ይታመንበታል፤ እኛ ግን አናምንበትም› ማለታቸው ነው፡፡ በሌላ አባባል ‹እግዚእብሔር አለ፤ ግን አላምንበትም› እንደ ማለት ነው፤ በዚህ አገላለፅ ደግሞ የምንረዳው እግዚአብሔር መኖሩ ከተቃውሞው እንደሚቀድም ውይም እንደሚሰፋ ነው፤ ይህም ማለት አባባሉ የሚገልፀው በመኖሩ ውስጥ ያልተስማሙበት ተቃውሞ መኖሩን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ‹የለም› ያስባላቸው ስለሌለ ሳይሆን ሌሎች የሚመሠክርቱን መቀበል ስላልፈለጉ ነው ማለት ነው፤ ይህም የሚያምኑትን(አማኞቹን) መቃወማቸው እንጂ አለመኖሩን ማሳያ አይሆንም፤ የእነሱን ትክክልነትም አይመሠክርም ምክንያቱም መቃወም ካለ ነገር ውስጥ ችግሮችን መንቀሻና መስተካከያ ስልትን ማመልከቻ እንጂ ‹ያለመኖር› ማስረጃ መሆን አይችልም፤ አንድ ነገር ሳይኖርም ተቃውሞ አይቀርብበትም፡፡ እንዲሁም ‹የለም› የሚለው መከራከሪያ ትክክል ነው የሚሉ ከሆነም ማሳመኛ ሊሆን የሚችል ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይላቸዋል፡፡ በጥቅሉ ግን ኢ-አማንያን ‹እግዚአብሔር የለም› ሲሉ ቢያንስ በግማሽ በመኖሩ መስማማታቸው መበምክንያት የሚያስቡ ከሆነ ግን በዚህ በውስብስብና በጥበብ በተሠራ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ዓለሙን አለመጠየቃቸው ይገርማል፤ ለመሆኑ ጽንፈ-ዓለም ያለ ምክንያት ተሠርቷል ወይ? የዚህን ጥያቄ መልስ ለመስጠት ቢሞክሩም ግማሹ ምክንያታቸው ይሟላላቸዋል፤ እስቲ በድፍራት ተንጠራርተው ‹እግዚአብሔር የለም› ከማለታቸው በፊት የጽንፈ-ዓለሙን አሠራር ለመመርመር ይሞክሩ፡፡

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply