ካምስተኛው ጉባዔ- ያባቶች ጨዋታ፡- ያለቃ የማነ ብርሃን ቅኔያዊ የጨዋታ ተረብ/ትችት

 

አበው የአገራችን ሊቃውንት በንግግር ለዛቸው የተካኑ፣ በጨዋታቸውም ተራው ሰው ሳያውቅ የሚተርቡና የሚተራረቡ፣ አባባላቸው በአእምሮ ላይ የሚጻፍ እንጂ የማይዘነጋ ነበሩ፤ ናቸውም፡፡ በተለይ የሚያዩትንና የሚታዘቡትን ነገር ሁሉ በጨዋታና በቀልድ እያዋዙ የሚገልጹበት ስልት ልዩ ነው፡፡ ይህንንም አለቃ ገብረ ሐና ‹አምስተኛው ጉባኤ› ብለው እንደሰየሙት መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው (‹አምስትኛው ጉባኤ› የሚል ርእስ በሰጡት በመጀመሪያው መጽሐፋቸው) አብራርተው ገልጸውታል፡፡ ለማሳያም የሚሆኑ አለቃ ገበረ ሐናን የመሰሉ ሊቃውንት ሞልተዋል፤ ከነዚህም መካከል አለቃ የማነ ብርሃን አንዱ ናቸው፡፡

‹‹አለቃ የማነ ብርሃን በጎንደር ፊት በር ሚካኤል፣ በተለይ ፋኖ ተብሎ በሚጠራው አቋቋም ምስክር የነበሩ ናቸው፡፡ ታላቅ ሊቅና ንግግር አዋቂ ሲሆኑ በሰውነታቸው ቅርፅ ግን ብዙ ጉዳ የደረሰባቸው ነበሩ፡፡ እግራቸው የተቆለመመች አንካሳ፣ ጀርባቸው ላይ ደግሞ ጉብር ያለባቸው ሆነው፣ መዘዋወር የሚችሉት በበቅሎ ሲሆን ሰውም በመጫን ተሸክሞ ነበር ኮርቻ ላይ የሚያወጠቸውና የሚያወርዳቸው፡፡ እኝህ ሊቅ ከተተራረቧቸው ትንሽ የቅኔ ትችቶች የተወሰኑትን እንመልከት!

  1. ‹እርስዎ በሰው ጫንቃ የሚኖሩት እስከ መቼ ነው?›

እናም እኒሁ ሊቅ በአንድ ወቅት ከርሳቸው በከፋ ሁኔታ አካለ ስንኩል ሆኖ በብርኩማ የሚሄድ የመሬት/የርስት ተቀናቃኝ ነበራቸውና ከርሱ ጋር ሙግት ገጥመው በነበረበት ወቅት በበቅሎ ተቀምጠው ወደ ፍርድ ቤት ሲሄዱ የርስት ተቀናቃኛቸውም ቀጠሮውን አክብሮ ለመገኘት በብርኩማ መሬት ለመሬት እየተሳበ ሲሄድ በኋላ ደረሱበትና

‹አቶ መኮንን! መሬት እንደያዝክ ቀረህ አይደል?› አሉት

አቶ መኮንንም ሲመልስ ‹እኔ መሬት ብይዝ እንዳቅሜ ሠርቼ ነው የምበላ፣ እርስዎ በሰው ጫንቃ የሚኖሩት እስከ መቼ ነው?› በማለት አሳፍሯቸዋል፡፡

  1. ‹ገና ሻኛ ላወጣ ነው›

ሌላ ጊዜ ደግሞ መምህር ዕፁብ የተባሉ የቅኔ መምህር እግራቸው ላይ ትንሽ እብጠት መታየት በመጀመሩ፡

‹ዕፁብ! በውነት ጎንደር ላንተ ተስማምተሃለች፤ ወፍረህ ስንጥቅ ልትል ደረስህ እኮ!› ሲሏቸው፤

መምህር ዕፁብም ‹ምን ይኸ ብቻ ገና ሻኛ ላወጣ ነው› አሏቸው፤ ባለቃ የማነ ጀርባ ላይ ያለውን ጉብር ለመንካት የተነገረ መሆኑ ነው፡፡

  1. ‹እጀሰብ ይሆናል ሲሉ ሰምተን›

ራስ ቢትወደድ አንዳርጋቸው መሳይ የጎንደር ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ በነበሩ ጊዜ የአለቃ የማነ ብርሃ ተጓዳኝ ሆነው በፊት አውራሪነት ማዕረግ የሚጠሩ አንድ ሰው የአሽሙር ቃል ሲናገሩ ተሰምቶባቸው፣ በቦክስ አስመትተዋቸው በመኖሪያ ቤታቸው ታመዋል ተብለው ተኝተው ነበር፡፡ ይህንን የሰሙት አለቃ የማነ ብርሃንም ሊጠይቋቸው ሄደው ‹ፊት አውራሪ ምን ሆኑ ምን አገኘዎት?› ሲሏቸው፤

‹የጨጓራ ህመም ተነሥቶኝ ነው› አሉ፤

አለቃ የማነ ግን በፊታውራሪ ላይ የደረሰውን ያውቁ ስለነበር ‹እሱስ በቀላሉ የሚድን ነው፤ እኛ ግን እጀሰብ (የሰው እጅ) ይሆናል ሲሉ ሰምተን ደንግጠን ነበር› አሏቸው፡፡

  1. የመምህር በላይ የቡፌ ግብዣ ዝግጅት

ሌላ ጊዜ ደግሞ መ/ር በላይ የተባሉት (የኋላ ሊቀ አእላፍ) የዘመኑ ሁኔታ የገባቸው አዛውንት ነበሩ፡፡ … ታዲያ እኑህ ሊቅ የቡፌ ግብዣ አዘጋጅተው ሊቃውንትን ሲጠሩ፤ አለቃ የማነ ብርሃንም ከተጋባዦቹ አንዱ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያ የቡፌ ግብዣ በኢትዮጵያ እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ፣ አለቃ የማነ ብርሃን በአሽሙር ተችተው ተናገሩ፡፡ መምህር በላይም የዋዛ ሰው አልነበሩምና

‹አለቃ! እኛ እኮ ይህን የቡፌ ግብዣ ያዘጋጀነው አዲሱን የሥልጣኔ አሠራር ለሕዝባችን ለማስተዋወቅ ነው እንጂ እርስዎ እግር አምጣ ካሉኝ፤ ችግር የለም ከእግራምጣ የተሠራ ሞሰብ ምልቷል› በማለት ያችኑ እግረ አንካሳነታቸውን በመንካት አሣቁባቸው (ይባላል)፡፡ (በአዲስ አበባ ብሂል ‹ግራምጣ› የሚለውን ቃል በጎንደር ብሂል ‹እግራምጣ› ይሉታልና ነው፡፡)

  1. ‹አባይ ማደሪያ የለው›

ዐባይነህ የተባለ የባህር ዳር ከበሮ መች ደብተራ አለቃ የማነ ብርሃን ከሌሎች የጎንደር ካህናት ጋር ማኅሌት ለመቆም ወደ ባህር ዳር ሲመጡ አይቶ ‹ጎንደሮች ሁሉም ባንድ እግር ወደ ባህር ዳር ገቡ/መጡ› ብሎ አፊዞ ነበርና፤

በሌሊት ማኅሌታዊ አገልግሎት ላይ መሪጌታ ዓባይነህ ከበሮውን ይዞ ሲንጎራደድ ዓይተው፣ ብድራቸውን ለመመለስ ስላጋጠማቸው ‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል› አሉት፡፡

  1. ‹ሁሉም ባንድ እግር እንዲሄድላቸው ይፈልጋሉ›

አንድ ጊዜ መምህር በላይ (ሊቀ አእላፍ) የመንግሥት ሠራተኞችንና ባለሥልጣኖችንም ሁሉ የሚያሣትፍ ‹የተዝካርና ድግሥ በገንዘብ ይለወጥ› የሚል ታላቅ ዐውደ ርእይ (የውይይት መድረክ) ከፍተው ነበር፡፡ በዚያ ጉባኤ ላይ አለቃ የማነ ብርሃን ተቀዳሚ ተናጋሪ ሆነው ‹የጥንቱ ባህላችን ሳይለወጥ በድግሥ እንጂ ተዝካር በገንዘብ ሊለወጥ አይገባም› ብለው ነበር፡፡

ሌሎች ተናጋሪዎች ግን ‹ተዝካር በድግሥ ከሆነ አንድ ካህን ለራሱ ብቻ ይበላል፤ ይጠጣል እንጂ ሚስቱና ልጆቹ የሚያገኙት ምንም ነገር የለም፡፡ በገንዘብ ቢለወጥ ግን በደመወዝ መልክ ተተምኖ ለቤተሰብ ጭምር የሚደርስ ይሆናል› የሚል ሐሳብ በሰፊው አቀረቡ፡፡

አለቃ የማነ ብርሃን በዚህ (በሌሎቹ ንግግር) አልተደሰቱም ነበርና እንደገና ንግግራቸውን ለማጠንከር እጃቸውን ሲያወጡ ‹እርስዎ ቀደም ብለው ድርሻዎትን ተናግረዋልና ሌሎች ይናገሩ› ተባሉ፤ የማዘጋጃ ሠራተኛ የሆነ አንድ ሰው እጁን አንሥቶ ግን ‹አለቃ የማነ ብርሃን የሚፈልጉት እኮ ሁሉም በአንድ እግር እንዲሄድላቸው ነው› በሚል የአግቦ ንግግር ሲያሥቅባቸው፤ ‹ገና አሁን አገኘኸኝ ክንዴ› አሉ አለቃ!

  1. ‹አየኸው ሲያቅራራ›

አለቃ የማነ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ዐራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የባለወልድ ቤተ ክርስቲያ ማኅሌት ለመቆም ሲገቡ፤ ሊቃውንቱ ቅኔ ማኅሌቱን ሰፍተው ይዘውት የጎንደርን ቀለም ለመናገር ዕድል ስለተነፈጋቸው ‹አዬ ሸዋ! የአርበኛ አገር! ዐየኸው ሲያቅራራ› በማለት መተቸታቸው ተሰምቷል፡፡

  1. ‹እገር ዘወርዋራ›

እዚያው ጎንደር ለረጅም ጊዜ ሲማር የነበረ አንድ የሸዋ ተወላጅ ሰው ግን አለቃ የማነ ብርሃን የሸዋን ሊቃውንት ደረጃ ዝቅ በማድረግ ሲተቹ ሰምቶ ‹አለቃ! መቼም እግር ዘወርዋራ ስለሆኑ አንድ ቀን ወደ አዲስ አበባ ሄደው የሸዋን ሊቃውንት ማየተዎ አይቀርም› ብሎ ነበር፡፡ (ፍሬ ነገሩ ያለው ‹እገር ዘወርዋራ› ከሚለው ቃል ላይ ሆኖ ያችው እግራቸው በመቆልመም የተዘዋወረች መሆኗን ለማሳየት ነው፡፡)

  1. ‹አረ! በተሰቀለው ይሁንብህ!›

አለቃ የማነ እንኳንስ ለባዳ ለቤተሰባቸው እንኳ ምህረት የለሽ ተራቢ በመሆናቸው የገዛ ወንድማቸውንም ዐይኑሥውርነት ለመግለጥ ‹አንተ ዝም ብለህ አብርሆን ለአዕይንትየ (ዓይኖቼን አብራልኝ) የሚለውን መዝሙር ድገም› ብለዋቸው ነበር፡፡

ወንድማቸውም የዋዛ ሰው ስላልነበሩ በሰጡት መልስ ካለቃ የማነ ብርሃን እግሮች አንደኛዋ አጥራ ወደ ላይ የተሰቀለች መሆኗን ለመግለጥ ‹እረ! በተሰቀለው ይሁን! አንተ ሰው ተወኝ እባክህ!› አሏቸው፡፡

  1. ‹ይህች ሸራፋ ደጋገመችኝ›

መምህር (የኔታ) ክፍሌ የሚባሉ የመጀመሪያ የበአታ አቋቋም ምስክር የነበሩ ናቸው፡፡ ታዲያ በብሕትውና የሚኖሩ የጸሎት ሰው እንጂ ዋዛ ፈዛዛና ቧልት ወይም ተረብ የሚወዱ አልነበሩም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አለቃ የማነ ብርሃን ባሉበት ግብዣ ላይ ተገኝተው በሸራፋ ጽዋ ጠላ ተቀድቶላቸው ጎንጨት እያሉ ሲያዳምጡ፣

አለቃ የማነ ብርሃን በአግቦ ሲነኳቸው ‹ለእኔ ጎንደር ክፍሌ አይደለም፤ ክፍሌ የሰው አገር ነው› በማለት መምህር ክፍሌ የሸዋ አገር ሰው (የቡልጋ ተወላጅ እንጂ ጎንደሬ አለመሆናቸውን) ይገልጣሉ፡፡

መምህር ክፍሌም ሳይወዱ በግድ መልስ ለመስጠት ተነሳስተው ሳለ አስተናባሪው ‹ይጠጡ እንጂ የኔታ! አንድ አይያዝም እኮ› ሲላቸው፤ ‹እሺ ወንድም ዓለም ይህች ሸራፋ ደጋገመቺኝ እኮ!› አሉ፡፡ የአለቀ የማነ ብርሃንን አካለ ጉዳተኛኘት መግለጣቸው ነበር፡፡››

እንግዲህ እነሆ በዚህ ዓይነት አለቃ የማነ ብርሃን ለሌሎች ሁሉ ምህረት የለሽ ሲሆኑ፣ እሳቸው ደግሞ በአካል ጉዳተኛነታቸው ለተቺዎች ምሁራን ሁለንተናቸው የተጋለጠ ነበር፡፡ እንደ አለቃ ገብረ ሐና እልኸኛ ሆነው ‹እከሌ ይቀየምብኛል› ሳይሉ እንዳገኙ በማንኛውም ሰው ላይ የሚሰነዝሩት ትችት አጸፋው ተመልሶ በራሳቸው ላይ ሲከነበልባቸው ይበልጥ ተጎድተውበታል፡፡

(ምንጭ፡- መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው፣ ‹ሁለገብ ትምህርት ሰጭ የአእምሮ ማዝናኛ› ገጽ 161-163)

Please follow and like us:
error

Leave a Reply