ወልዱ ዘምናለሽ ተራ

‹ምናለሽ ተራ ምናለሽ ተራ
‹በሌለ የለም› ታታሪነት
ሀገር የምታስጠራ
የመርካቶ ኩራት
የዓለም አውራ፡፡›
እያልሁ ሁልጊዜ እዘፍንላታለሁ፤ እዘምርላታለሁ፡፡ ምክንያም እናቴ ናታ!
እንደ! ተወልጄ ራሴን ያገኘሁት እኮ! መርካቶ ምን አለሽ ተራ ነው፡፡ አዎ! መርካቶ “ምናለሽ?” ስትባል እኔን በጭድ ተራ ማኽፀኗ ዱብ አድርጋ አቀረበች፡፡ እኔም በጭን ጎዳናዎቿ ላይ እየተንፈላሰስኩ ቤንዝን ጡቶቿን ጠብቼና ጎማዎቿን ሞቄ አደኩ፡፡ ምናለሽ ተራ “የሌለ የለም ብቻ ነው፡፡“ በሚለው ልዩ ‹ትምሮዋ›ና ምክሯም ቀረፀችኝ፡፡ ይህ ትምርዋም በውስጤ ሰረጸኝ፤ እንዳልለያትም ‹ፎንቃዋ› ያዘኝ፡፡ ስለኾነም የሌለው ነገር እንዲኖር አደርጋለሁ እንጂ ከእሷ መለየት ማለት ‹መደየም› ይመስለኛል፡፡
በእናቴ ቤት በምናለሽ ተራ እድሜዬ ለሥራ እንደደረሰም በመጀመሪያ በ‹ቅፈላ› ሽቀላ ተሠማርቼ ነበር፡፡ የተዋጣልኝ የልጅ ‹ቀፋይ› ሆኜ ነበር፡፡ ባቀፋፈሌም ስልተኛ ነበርኩ፤ በዋናነትም ፍቅረኛሞችን ብቻ እጠይቃለሁ፤ አቀፋፈሌንም ቢኾን አንጀት ይደርሳል እንጂ ጆሮ ጠልዞ በሰልቸት አይቀርም፡፡ ፍቅረኞችን ስቀፍልም በሴቷ በኩል ከኾነ “ቆንጅት! እናንተንስ አይለያችሁ፤ ስለ ፍቅር አምላክ?” እላታለሁ፤ ፍቅር ካላት በፍቅር አምላክ አትጨክንም፤ ‹ታሽረኛለች›፤ ‹ኮይን› ባይኖራት እንኳን በፍቅረኛዋ ‹ታስገጨኛለች› እንጂ ዝም ብላ ‹አትመርሽም›፡፡ በወንዱ በኩል ከኾነም “ስለ ቆንጅት? ስለ ፍቅር አምላክ?” እለዋለሁ፤ እሱም ወይ በውለታነት ቆጥሮ ወይም ‹ሸም ቆንጥቶት› ያለውን አውጥቶ ያሽረኛል፡፡ ምክንያቱም ፍቅረኛሞችን “ስለ ማርያም ፣ ስለ ገብርኤል…” ብሎ መቀፈል መሰልቸቱን ነቄ ብያለኋ! ፍቅረኛሞች ከኾኑ የሚያመልኩት የፍቅርን አምላክ ነው፡፡
ያኔ! በ‹ቅፈላ› ማንም ተፎካካሪ አልነበረኝም፤ ምክንያቱም አቀፋፈሌ ነዋ! ኾኖም በቢዝነሱ ብዙ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ አብረውኝ የሚኖሩ ቋንጣ፣ ዶዮና ባሪያው የሚባሉ ‹ጀለሶች› ነበሩኝ፤ እነሱም መቀፈል ሲያቅታቸው እኔን የ‹ጨብሻ›ና “የኡፋ” ቀላቢያቸው አደረጉኝ፡፡ በረጃጅም እጆቻቸው እየሰበሰቡ በሰፋፊ ጉሮሯቸው የሚያስገቡትን የ‹ቡሌ› መጠን አልቻልኩትም፤ እነሱንም እያደነቅኩ መኖርም ሰለቸኝ፡፡ ለምሳሌ ዶዮ አንድ ፌስታል ኡፋ ብቻውን ‹ሲጥ› ያደርጋል፡፡ ቅፈላ ደግሞ አይኾንለትም፤ ከቅፈላ ይልቅ ‹እንክብክብ› ይችላል፡፡ ክፋቱ በእንክብክብ ያገኘውን ‹ሳቢ› ‹እብስ› አድርጎት ይመጣል፡፡ የተገኘውን እኩል ተሰልፎ ለማጥቃት ግን ማንም አያህለውም፡፡
ቋንጣ ቡሌ ሲደፍቅ እጁ አይበቃውም፤ መቀፈል ደግሞ ብዙም አይችልም፡፡ ቡሌ ቅፈላ ግን የእጁ ነው፤ ወይ ከምግብ ቤቶች በኮንትራት ቆሻሻ በመድፋት ኡፋውን ይሰበስባል ወይም ከእኔ ‹ኮይን› ተቀብሎኝ አንድ ወይም ኹለት ፌስታል ይሸምታል፡፡ ኮይን ለመቀፈል ከተሠማራ ግን ቅፈላውን ትቶ ‹ቺኮችን› መጥበስ ይወዳል፡፡ በዚህም ብዙ ጊዜ ‹ተቦቅሷል›፡፡ ‹ጋያ› ሳይነፋ እና ‹በርጫ› ሳያደርስ አይውልም፡፡
ባሪያው ቅፈላም፣ ኡፋ መሰብሰብም አይኾንለትም፡፡ የሚኾንለት ድርቶ መስፋት ነው፤ ለኹላችንም አንዳንድ ድርቶ ሰፍቶልናል፡፡ ኹላችንም እሱ የሠፋልንን ድርቶ አንድ ላይ በመደራረብ ለብሰን እናድር ነበር፡፡ ቡሌ በመድፈቅ ግን ከዶዮ አያንስም፤ በተለይ ኡፋው ካነሰ የጎረሰውን በግራ እጁ ለመዋጥ እየገፋ በቀኙ መዳፉን ሞልቶ ይሰበስባል፡፡ በዚህ የተነሣ ከእሱ ጋር ‹ሻሞ› ለመሰለፍ የሚፈልግ አልነበረም፡፡
ቅፈላን በደንብ የምችል እኔ ስለነበርኩ ለ‹ጀለሶቼ› የ‹ኮይን› ምንጫቸው ነበርኩ፡፡ በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ ፊልም የምንመለከትበትን ሒሣብ የማወራርደው፤ ኡፋ ሲጠፋ የእናት ጉርሻ ‹ኮይን› የምዘጋው፤ የሲጋራ፣ የጨብሲ፣ የበርጫና የሌሎችን ወጪዎች ሳቢ የምዘጋው እኔ ነበርኩ፡- በተለይም በ18 ቀበሌ የምንመለከተውን እስፔሻል፣ የሕንድና የአሜሪካ ፊልም በእኔ እጅ ነበር፡፡ እያደር ግን የነሱ ሳቢ ዘጊ እኔ ብቻ መኾኔ ድብርት ለቀቀብኝ፡፡ በተለይም እነሱ እስፔሻላቸውን እየኮመኮሙ ‹አንቺ ቀፍይ› እያሉ ‹ሸም የማይቆነጥጣቸው› ስለኾኑ አስደበሩኝ፡፡ “ፋራያችኹን” ፈልጉ ብዬ ከዚያ አካባቢ ‹መርሽሁባቸው›፡፡ ለጊዜውም እናቴን ምናለሽ ተራን ትቼ ወደ ሰባተኛ ሰፈር ለመሰደድ ተገደድኩ፡፡
እዚያም ሰው መኾን አምሮኝ ሊስትሮ ጀመርኩ፡፡ ሰው መኾን ግን አልቻልኩም፤ ሰው መኾን ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሊስትሮ ወንበሬን ወንዶች የ‹ሸሌ› ቤት ወረፋ መጠበቂያና ማስቀየሻ አደረጉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የሽንት መጣጭ መኪና መሰልኳቸው መሰለኝ ቦርሽልን በማለት የሸኖ ቤታቸውን በጫማቸው ይዘው መጥተው አፍንጫዬን ከማሽተት አስኮረፉት፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ እዚያ አካባቢ ጉልቤ ሊስትሮዎች ተፎካከርከን ብለው ቡርሽ መለማመጃ አደረጉኝ፡፡ ከዚያም ‹ሰፈሬ ማሪኝ› በማለት ምናለሽ ተራ ተመልሼ ‹ከች› አልኩ፡፡ በምናለሽ ተራ እኮ ከጀለሶቼ ማስመረር ውጭ ማንም ዝንቤን እሺ አይለውም፡፡ ከዚያም ሥራ ቀይሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡
በልጅነቴ ስቀፍል ብዙውን ጊዜ የ‹ቺኮች›ን ቦርሳ ‹መከለም› አበዛ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንዷ ቦርሳዋን ለመያዝ ተጠይፋው ስታሰቃየው አይቻት አላስችል ቢለኝ “ልያዝልሽ” አልኳት፡፡ “‹ድክሞ› ብሎኛል” ስትለኝ ጊዜ ተቀበልኳት፡፡ በቦርሳዋም ጥሩ ሳቢ አገኘሁ፤ እንደልቤም በአሜሪካና በሕንድ ፊልም፣ በበርጫና በጨብሲ ተዝናናሁ፡፡ አንድ ቀን ደግሞ አንዷ ‹ጩባ› በአንገቷ ላይ ተሸክማ ታወዛውዘዋለች፤ ‹መንጩ› አድረኳት፡፡ ከዚያ በኋላ በምናለሽ ተራ ታዋቂ “ላቦሮ” ኾንኩ፡፡
“የላቦሮነት” ሥራ በፊት በፊት ያበላ ነበር፡፡ ዛፓም አያስቸግርም ፤ ተቀናቃኝም አልነበረበትም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን ‹ጉልቤዎቹ› እነ ቋንጣ፣ ዶዮና ባሪያው አስቸገሩኝ፡፡ አንዲት ቦርሳ ይዤ “ተቄ” ስል እየተከታተሉ ይቀበሉኝ ጀመር፡፡ ጭራሽ እኔን እየተከተሉ ‹በጋቢና ተሣፈር›፣ ‹የኋላ ወንበር ተቀመጥ› እያሉ በየትኛውም ሰው ኪስ ዘው እንዲል ‹አጃኳሚዎች› ኾኑ፡፡ በዚህም ‹ሙዳችን› አብሮ ሊሔድ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የእኔ ደንበኛች ‹ቺኮች› ናቸዋ! እነሱ ግን እኔ እንቢ ስላቸው ራሳቸው የኹሉንም ወንድ ኪስ እንደፍራለን ብለው ጥርሳቸውን አጡ፤ ፊታቸውም ታርሶ፣ ታርሶ ላቦሮነታቸውን ገጠሬ ሳይቀር አወቀባቸው፡፡ ‹መንጩ ማድረግ› ሲያቅታቸውም እኔ አንዲት ቦርሳ ይዤ ‹ተቄ› ስል ወይም ‹ጩባ› ላፍ አድርጌ ‹ሽል› ስል ተከትለው ‹ቴባ! ቴባ!› እያሉ በመካፈል አሠለቹኝ፡፡
ለምሳሌ አንድ ቀን የተቀመመች ምግብ ቤት አጠገብ የአንዷን ‹ቺክ› ቦርሳ ‹መንጩ አድርጌ› ተቄ ስል ለካ ከኋላዋ ልጁቱን የተከተላት ልጅ ኖሮ አሯሯጠኝ፡፡ እኔም የምገባበት ሳጣ በሞሰብ ተራ ወረድ ብሎ ያለው የብረት ተራ ሸኖ ቤት ወረፋ የያዙትን ‹ተቅማጥ›፣ ‹ተቅማጥ› ብዬ አንዱ የሸኖ ክፍል ዘው አልኩኝ፡፡ የሸኖ ሰልፈኞችም ስለገባቸው የሚያሯርጠኝ ልጅ እንዳይገባ ‹ወረፋ ያዝ› ብለው አስቆሙልኝ፤ በዚህ አጋጣሚም ልጁ ከሰልፈኞች ጋር ሲጨቃጨቅ ከሸኖ ቤቱም በጓሮ በኩል በመዝለል በወንዙ ‹ተቀነጠስኩ›፡፡
ከዚያም ዘወር ብዬ ቦርሳውን ክልም ሳደርገው ‹አመዱን›፣ ‹ቸንቶውን›፣ ‹ደቹን›፣ ‹ቢጫውን› ሳቢ አጭቋል፤ ‹ፈንዱ› አልኩኝ፡፡ ይኹንና እነ ዶዮ በጎን ተከታትለውኝ ኖሮ ‹ቴባ› ብለው ተካፈሉኝ፤ በሸኖ ቤት ላስቀየሱኝም ‹ስቦጭቅ› አንድ ‹አመድ› ከምናምን ብቻ ተረፈኝ፡፡ ልክ እንደዚህ እኔ ስንት ተሰቃይቼ ያገኘሁትን ሳቢ እየተቀበሉ ሲያስቸግሩኝ ሥራው ራሱ እያስጠላኝ መጣ፡፡ በተጨማሪም በምናለሽ ተራ “ላቦሮነት” የሚሠሩ “ጮካዎች” በዙ፡፡ በዚህ የተነሣ ቺኮችም የቦርሳ መያዢያቸውን ቀየሩ፡፡ በግልገል ሱሪያቸው ውስጥ እየቀረቀሩ ለሚገዙት እቃ ዋጋ ለመክፈል ሲቸገሩ ብዙዎችን አየኋቸው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ማንም በሞጨለፈው “ዛፓ” ኹሉ እኔን “ውለድ” እያለ ባልወለደ አንጀቱ የገረፋ መሰልጠኛው አደረገኝ፡፡ ስለዚህ “ላቦሮነት” እርም ብዬ ተውኩት፡፡ እሱን ትቸም በድንችና ሽንኩርት ተራዎች ‹የጉርጎራ› ሥራን ጀመርኩ፡፡
እኔ ድንችና ሽንኩርት ተራዎች በመሄድ የጉርጎር ሥራን ሳልጀምር በፊት በየተራዎቹ ብስባሽ መንገድ በመዝጋትና በመሸተት ሻጮችንና ገዥዎችን አስቸግሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገዥዎችም ኾኑ ሻጮች አንድ ድንች ወይም ሽንኩርት አምልጧቸው መሬት ከወደቀ በይሉኝታ አያነሱትም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን እኔ በዚያ አካባቢ ‹ሳንዣብብ› ነጋዴዎቹ አዋጥተን እንገጨኸለን ጥረገው አሉኝ፡፡ እኔም ቆሻሻውን ኹሉ ከአካባቢው ፀዳ ፀዳ ካደረኩ በኋላ የሚወድቁ ድንቾችንና ሽንኩርቶችን እየጠበቅኩ በመልቀም አጠራቀምኳቸው፡፡ ከዚያም ወደ ማታ አካባቢ ዋናው አስፋልት ላይ ወስጄ በመዘርገፍ በቅናሽ ዋጋ ሸቀልኳቸው፡፡ ከዚያ በኋላማ! ሸቀላው ጣመኝ ሽንኩርትና ድንችም እንኳን በመሬት ወድቀው ሊሰበስቡ ይቅርና መሬት መንካትም አቃታቸው፡፡ ከአየር ላይ እየቀለበኩ ሸቅልኳቸዋ! በዚህም ድንችና ሽንኩርት ገዝተው መመገብ የማይችሉ ሰዎች ከእኔ በርካሽ በመግዛት ጥፍጥናውን ለመዱት፡፡ ገና የመሸጫ ሰዓቴ ሳይደርስም በአስፋልት ላይ ሰልፍ ለመያዝ ይጠብቁ፤ ሰዓቱ ሲደርስም ለመግዛት በሻሞ ይቧቀሱ ጀመር፡፡
በተለይ ሳቢዬ እየጎለመሰ ከሄደ በኋላ በጉርጎራ ሰበብ ኹለት ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ጀመርኩ፡፡ በሌሊት ተነሥቼ ለድንችና ሽንኩርት አውራጆች ሲጋራ እሸቅላለሁ፡፡ አውራጆቹም ለሲጋራቸው ሲሉ ከተሸከሙት ላይ እያሾለኩ ወይም በአይሱዙ መኪናዎቹ ላይ የፈሰሰውን እየለቀምኩ ስወስድ ‹እስታ› ይላሉ እንጂ ‹አይገግሩብኝም›፡፡ እኔም እየተከታተልኩና እየተንጠላጠልኩ የጎረጎርኩትን ድንችና ሽንኩርት በአሠርኳቸው እጅጌዎቼና በታጠቅኩት ወገቤ ዙሪያ እያስገባሁ እቀረቅራለሁ፡፡ ከዚያም በከረጢት በመቆጠር ከአንዱዋ ቸርቻሪ ጋር አስቀምጣለሁ፡፡ ትንሽ ቆይቼም ከአውራጅ ወዛደሮቹ የሲጋራ ኮይኔን እሰበስባለሁ፡፡ ስለዚህ ሲጋራ የጉርጎራ ሥራዬን በአግባቡ ለማከናወን፤ ጥሩ ሳቢ ለማግኘትም አስችሎኛል፡፡ በዚህም የጉርጎራ ሥራዬን ተዝናንቼ መሥራት ችዬ ነበር፡፡
ዶዮ፣ ቋንጣና ባሪያው ደግሞ በጉርጎራ ሥራዬ ጥሩ ኮይን ማግኘቴን ሲሰሙ ቅናት አቃጠላቸው፡፡ በየቀኑ እየመጡም ‹የሲጋራ ግጪን›፣ ‹የኡፋ ቻይን›፣… እያሉ መቀፈል ‹አሪፊነት› አደረጉት፡፡ እንቢ ስላቸውም ለአካባቢው የሽንኩርትና ድንች ነጋዴዎች የበፊቱን ‹የላቦሮነት› ሥራዬን እየቀደዱ አስፎገሩኝ፡፡ በዚህ የተነሣ ቸርቻሪዎቹ እንዳልጠጋቸው ‹ገገሩብኝ›፡፡ በዚያ ላይ ብዙ ጎርጓሪዎች ስለተፈጠሩ ተፎካከሩኝ፡፡
በፊት ድንችና ሽንኩርት ሻጮች የወደቀውን ለማንሳት ተጠይፈው በብስባሽ ሽታ ተቸግረው እንዳልነበር እኔ የፈጠጠውን እየጎረጎርኩና የወደቀውን እየለቀምኩ በወረፋ ስሸቅለው ሲያዩ ጊዜ አንዲት ድንች ወይም ሽንኩርት ለመውደቅ ከጆንያው ብቅ ስትል ወይም ከወደቀች ለመውሰድ በሻሞ መጣላት አበዙ፡፡ ከእኔ ይገዙ የነበሩ ድሆችም ድንችና ሽንኩርት መመገብ ሲለምዱ ጊዜ ጣማቸው፤ በጉርጎራ ሥራም ላይ ተሰማሩ፡፡ ጭራሽ ይባስ ብለው የሕጻን ልጆቻቸው ጥርስ ማብቀያ አደረጉት፡፡
ሕጻኖቻቸው ገና ቆመው መሄድ ሲጀምሩ የተቀቀለ ድንች ያቀምሷቸዋል፡፡ ማውራት ሲጀምሩ የጉርጎራን ዝና እያወደሱ ይቀዱላቸዋል፡፡ በዚያውም ድንችና ሽንኩርት ተራ በማምጣት ለቀማና ጉርጎራ ያስከልሟቸዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ልጆቹ በአይሱዙ የጭነት መኪናዎች ላይ እየተንጠለጠሉና በተጫኑ ኩንታሎች መካከልም እየተሸለከለኩ በመጎርጎር አከፋፋይ ነጋዴዎችን አስመረሩ፡፡ በእነሱ ድርጊትም የእኔ የጎርጓሪነት ስሜ ጠፋ፡፡ በአካባቢውም ‹ውር!› እንዳልል ተወሰነብኝ፡፡ በዚህ የተነሣ የድንችና የሽንኩርት ተራ የጉርጎራ ሥራዬን ለመተው ተገደድኩ፡፡
ከዚያ በኋላ ‹ምን አዳረቀኝ› በማለት ምንም ተቀናቃኝ የሌለበትን የእንክብክብ ሥራ ጀመርኩ፡፡ በመርካቶ ውስጥ በመሽከርከር የተለያዩ እቃዎችን እንደ ዶዮ ማንከብከብ ሥራዬ ኾነ፡፡ የእንክብክብ ሥራም በፊት በፊት ያዋጣ ነበር፡፡ በቀን ቢያንስ አራት ወይም አምስት ‹ወረቀት› አይጠፋውም፡፡ ይህን ያህል ሳቢ ካገኘሁም አልቸገርም፡፡ ምክንያቱም ባገኘኋት ኮይን ቁርሴን ሁለት ሽልጦ ‹በቸላ› እገዛና በሚጥሚጣ እነፋለሁ፡፡ ከዚያም ሠራ ሠራ አድርጌ ምሣ ሰዓት ሲደርስ ‹በቸላ› ምናለሽ ተራ ከምትገኘወቅ እናት ቤት በእጄ ሣህንነት አምስት ጉርሻዎች እቀበላለሁ፡፡ ያ ማለት በቃ! ዝግ ነው፤ እንክብክብ ራሱ ይቀላል፡፡ ማታም ቢኾን ‹አንቡሌ ቤት› ‹ቅንጥብጣቢ› ስላለ ‹በየካ› አወራርዳለሁ፡፡ በዚያውም የሁለት ሦስቷን ብርሌ አንገት በመያዝ እሞጨሙጫለሁ፤ እንሳሳማለን፡፡ ኤዲያ! እርካታ ያለ እዚያ ነው እንጂ! አዳርም ቢኾን ‹በቸላ› በሽበሽ ነበር፡፡ ከፈለኩ ጎጃም በረንዳ ወይም አሜሪካ ግቢ ትኋንና ቁንጫ ‹እቅፎ አድርጌ› ሞቆኝ ደቀሼ አድር ነበር፡፡
ጎጃም በረንዳና የአሜሪካ ግቢ አድር የነበረበትን ጊዜም ሳስታውሰው ልዩ ትዝታ አለው፡፡ ያን ጊዜ እኔ ከምናለሽ ተራ በረንዳ አዳሪነት አልፌ ቤት የገባሁበት ወቅት ነበር፡፡ ጎጃም በረንዳም መሬት ላይ ‹ቸላ› እየከፈልኩ በማደር ቤተኛ የኾንኩበት ቤት ነበር፡፡ እዚያ ቤት የምናድረውም መጀመሪያ ከባሉካዎቹ ሽቦ አልጋ ሥር እስከ በሩ ድረስ ‹ቸላ› ‹ቸላ› የዘጋነው ገብተን በአንድ ጎናችን ብቻ ትንኋንና ቁንጫ ሾልከው እንዳያልፉ አድርገን እንተኛለን፡፡ በዚህ መኝታችን ተባዮች መብላት የሚፈቀድላቸው ከአንድ በኩል ብቻ ነው፤ ተከላካይም የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም እጅን አሾልኮ ማከክም ኾነ መዳጥ ስለማይቻል የፈለጉትን ያህል መቦጨቅ መብታቸው ነው! ተባዮቹ ግን መተላለፊያ በማጣት መንገድ እየጠበባቸው የሸዋዚንገርን፣ የቻርኖሪስን፣ የሬንቦን የጦርነት ፊልም ይሠሩብናል፡፡ እዚያ ቤት የሚያድሩት ደግሞ አብዛኞቹ ‹ጮካ›፣ ወዛደር፣ ‹ቁጭ በሉ›ና ቀፋይ የሆኑ ሰካራሞች ስለነበሩ እንቅልፋቸው ወፍራም ነበር፡፡ ትንፋሻቸውም ብርድን ከቤት ጠርጎ ያስወጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የሚያስወጣ ሰካራምም ያጋጥማል፤ ሆኖም እሱኑ ራሱን እናስወጣዋልን እንጂ ዝም የሚለው የለም፡- መበከሉ ግን አይቀርም፡፡ እያደር ግን መኝታው ለእኔ ‹ሙድ› የሌለው ኾነብኝ፡፡
ትንሽ ቆይቶም የመደቀሻ ደረጃዬን በማሻሻል ቆጥ ላይ ወጣሁ፡፡ ይኹንና የቆጥ መደቀሻ፡-
 አንደኛኛ የሣር ፍራሽ ስለኾነ የቁንጫ፣ የቅማልና የትኋን አፎች ይጨምርበታል፤
 ሁለተኛኛ ሣሩም ቢኾን ወፋፍራምና በስሱ የተጎዘጎዘ ስለኾነ ቆዳ ይልጣል፤
 ሦስተኛ በቆርቆሮውና በግድግዳው መጋጠሚያ የሚገባው ብርድ ከፍተኛ ስለኾነ አይቻልም፡- ይፎደፉዳል፤
 አራተኛ በቆጥነት የተረበረበው አጠና ቀጫጭን ስለኾነ እየተልመጠመጠ ከአኹን አኹን ተሠብሮ ሾለኩ የሚል ፍርሀትን ያመጣል፤
 በተጨማሪም ዋጋው ‹የካ› ስለኾነ ከመሬቱ ይወደዳል፡፡
ስለዚህ ቆጥ ላይ ማደርን ትቼ ከባሉካዎቹ አልጋ ጠርዝ ላይ ተደርቤ እንድደቅስ ተፈቀደልኝ፡- ጠባይ ነዋ!፡፡ ከዚያ ግን በወዲያ በኩል የአልጋ ጠርዝ ትተኛ የነበረች የባሉካዎቹ ልጅ ‹ከእሱ ጋር ካልኾነ› ብላ አቅጣጫ በመቀየር መጣችና እኔ ጋር ተወሽቃ መደቀስ ጀመረች፤ ‹ãኸ! ልትደፍሪኝ ነው› ብዬ ከቤቱ ጠፋሁ፡፡ እሷ እንዳታገኘኝም ለጊዜው ወደ አሜሪካ ግቢ ተቀየስኩ፡፡ ከተረሳሳልኝ በኋላም ግን ጎጃም በረንዳዬ ተመለስኩ፡- ምን ታመጣለች?
እዚህ ላይ ከተወሰነ ጊዜ ቆይታ በኋላም ጎጃም በረንዳ ሳድር ያጋጠመኝን ሳስታውስ የቺኮችን ቀልብ የመሳብ ኃይል እንዳለኝ አሳውቆኛል፡፡ በዚያን ጊዜ እንክብክብ ጥሩ ኮይን ይገኘው ስለነበር የአስተዳደር እድገቴን በማሻሻል ‹ዱ ወረቀት› እየከፈልኩ አልጋ ለማየት ፈለኩ፡፡ አስቤም አልቀረሁ አንድ ሰው ብቻ የምታስተኛ አልጋ ያለችበት ጠባብ ቤት ውስጥ ገባሁ፡፡
ስለ አልገዋ አከራዬ እንደነገሩኝ ከኾነ በፊት በቁንጅናቸው ጊዜ ቢዝነስ ይሠሩባት ነበር፡፡ በቢዝነስ ሥራቸውም አኹን እቤት ያለችውን ቺክ ወለዷት፡፡ ልጅቱ እያደገች ስትመጣ ግን የአልገዋ ቢዝነስ እየቀዘቀዘ፤ መጠኗም እየጠበበ መጣ፡፡ በዚህም እናትና ልጅ ችግር ገጠማቸው፡፡ ችግራቸውን ለመቋቋም ግን አንድ ዘዴ ቀየሱ፡፡ ይኸውም ከልጃቸው ጋር ተስማምተው ቀን ቀን እነሱ በየተራ ሊደቅሱባት ማታ ማታ ደግሞ ሊያከራዩዋት ወሰኑ፡- ቀን የሚከራይ ስለማይኖር፡፡ በዚህ ሰዓትም ከእኔ ጋር ተገናኝተን አከራዩኝ፡፡ ኾኖም እናትና ልጅ ውጭ ለማደር ተገደዱ፡፡
እኔም ታሪካቸውን ስሰማ ስላሳዘኑኝ ሴትዮዋን ‹አልገዋ ከበቃች ልጅቱ ከእኔ ጋር ተደርባ ትተኛ፡፡› አልኳቸው፡፡ ይህንን ያልኩት ስላሳዘነችን ነው እንጂ ከቺክ ጋር መደቀስ አለመድኩ?
እሳቸውም ተደስተው ‹እንዳውም ከወንድ ጋር መተኛት ትለምድልኛለች፡፡› ብለው ተስማሙ፡፡ አልጋዋን ስንሞክራት እውነትም በቃችን፡፡ ከዚያም ከልጅቱ ጋር ስንደቅስ! ስንደቅስ! እናትዋን ሳይቀር አስቀናናቸው፡፡ ችክ ‹እቅፎ› አድርጎ ማደር መጣሙን ያወቅኩት ያን ጊዜ ነው፡፡ እያደር ግን እናቷ በቅናት ነቀሉ፡፡ እሳቸውም ‹እኔ ብቻዬን ሁልጊዜ ውጭ ከማድር እየቀየርሽኝ አንዳንድ ቀን እኔም አብሬ ልደር› አሏት፡፡ ልጅቱ ግን ከእኔ ጋር ከደቀሰች በኋላ መነሳት ያቅታት ጀመር፡፡ ትንሽ ቆይቶማ እኔው ራሴ ‹ፎንቃ› ይዞኝ ቁጭ!፤ ከልጅቱ? በእሷ ‹ፎንቃ› የተነሣም በአካባቢው እያንዣበብኩ እስከመዋል ደረስኩ፡፡ እናቷ ግን በአካባቢው ‹ውር› እንዳላል በሰፈሩ ጉልቤዎች አስወቁኝ፤ ጭራሽ ጉልቤዎቹ አጅበዋት እንዲዞሩ አደረጓት፡፡ እኔም በእሷ ፎንቋ ተለክፌ የለ? እንክብክብ እንዴት ልሥራ?
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማንከብከብም አላዋጣ አለኝ፡- ፈላጊው በዛ፡፡ በፊት በፊት ዕቃ ለመሸከም ‹ቅብርር›፣ ‹ጅንን› እንዳላልኩና እንዳላማረጥኩኝ እንኳን ተንቀባርሬ ልተወው ይቅርና የማንከበክበውም አጣሁ፡፡ ምክንያቱም ወደ መርካቶ ዕቃ ለመግዛት የሚመጡ ሰዎችን ገና ከታክሲ ሳይወርዱ ‹እኔ ልያዝላችሁ› የሚሉ ወዛደሮች በዙዋ!፡፡ እነ ዶዮ፣ ቋንጣና ባሪያውም እንደ እኔ ወዛደር መስለው ‹የማስቀየስ ላቦሮነትን› አጧጧፉት፡፡ የእናት ቤት ጉርሻም ሽሚያው በዛበት፡፡ በፊት “በቸላ” ዝግ እንደዘጋሁበት “የካ” የሚከፈለው ለሽታ ኾነ፡፡ ለሽታ ለሽታማ! በሸራተን አላልፍም ብዬ ተውኩት፡፡ አንድ ቀንም ‹የጥሩ ምግብ ሽታማ! ሸራተን ‹ጥግቦ ብዬ› እመጣለሁ› ብዬ በሆቴሉ በር ባልፍ፣ ብመላለስ ሸራተን መዓዛ አልባ፤ ሽታ የለሽ ሆኗል፡፡ ኋላ ስሰማ የምግብ ሽታው ኮይን ማስገባት ስለቻለ እዚያው በግቢው መሸቀሉን ሰማሁ፡፡ ጊዜ ማረሳሻ የሚኾነኝ አንቡላም ቢኾን ተወደደ፡፡ እሱንም ቢኾን በ“ቸላ” አንገት እንዳላጫወትኩበት ማሩ በአፌ እንዳልዘነበ፤ ወለላው በጉሮሮዬ እንዳልተንቆረቆረ፣ በቂጥ የለሽ ጆሯም ብርጭቆ ስኳር በጥብጠው “ብር ከቸይ” አስገቡት፡፡ ማር የነካው አንቡላም ማግኘት ትዝታና ምኞት ኾነ፡፡
(ይቀጥላል…)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply