የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ (Appeal to people Fallacy- Argumentum ad populum)

(በካሣሁን ዓለሙ)

‹በመጠን፣ በመልክ፣ በቋንቋ፣ በአስተዋይነት፣ በቀለምና በአኗኗር ኹኔታ ሰው ቢለያይም በጠቅላላ ፍላጎታዊ ገመድ በመታሠር ግን አንድ ይኾናል፡፡› እንዲሉ፤ እያንዳንዱ ሰው መፈቀርን ይሻል፤ የተከበረ ዋጋ ያለው ሰው ኾኖም መወደስን ይፈልጋል፤ ዝናንም ይናፍቃል፡፡ እነዚህ ፍላጎቶችና የመሻት ሞተሮችም ሕዝብን ለአንድ ለተፈለገ ጉዳይ መቀስቀሻነት አስተወፅኦ አላቸው፡፡ ብዙ የሚፈልገውን ነገር በመጠቀምም የተፈለገውን ሕዝብ ወደ ራስ ዓላማ ጎትቶ ማስገባት ይቻላል፡፡ ማንኛውም ሰው በእነዚህ ፍላጎቶች የተወጠረ በመኾኑ ፍላጎቱን ቀስቅሶ ኅብረት አንድነት ለመፍጠርም ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በተለይ አንዳንድ ሰው በአብዛኛው ኅብረተሰብ የተደገፈ ከመሰለው በስሜት ተነድቶ ሳይመረምር ተሳታፊ መኾን ይፈልጋል፤ ምክንያቱም ከተወደደው፣ ከተከበረውና ዋጋ ካለው ሰው ጋር በመተባበር ፍቅርና ክብርን መካፈል የማይፈልግ ሰው የለምና፡፡

የሰው ልጅ ፍላጎት ኃያል ነው፡፡ አስተሳሰቡን እንደ ጎማ በመወጠር ማሽከርከር ይችላል፡፡ በፍላጎት ነፋስ ተሞልቶ የሚጓዝ ሰውም በሚጓዝበት አስፋልት ሌላ መንገደኛ ሰው ቢገጭም እንኳን ‹ሰውየው የተገጨ መንገድ በመዝጋቱ ነው› ይላል እንጂ ሰው በመግደሉ አይፀፀትም፡፡ በሱ ፍላጎት መኪና የሚሳፍራቸው ሰዎችም ቢኾኑም በተመሳሳይ/በጋራ የመፈቀር፣ የመከበር፣ የመደነቅ፣… ፍላጎቶች ተስበው የሚሳፈሩ ናቸው፡፡ ቀስቃሹ ወያላም ‹ፈጣን የሞላ!› ብሎ ሲያሳፍራቸውም፤ ሹፌሩም ያከንፋቸዋል፤ ተሳፋሪዎቹም ለመድረስ ይቸኩላሉ፡፡ በዚህ ፍጥነትና የችኮላ ጉዞ ታዲያ መኪናው ሰው ቢገጭም ተሳፋሪዎች የሾፌሩ ጠበቃና ደጋፊ ይኾናሉ እንጂ ለተጎዳው ሰው አብዛኞች የሚያዝኑ አይኾኑም፡፡ ዓለማችንም በዚህ ዓይነት የፍላጎትና ሞተር ባላቸው መኪና ሰዎች የምትሽከረከር ናት፡፡

የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፤ በኹለት ዓይነት መንገዶችም ይፈጸማል፡፡ አንደኛው በቀጥታ ሲኾን ሌላው ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ነው ተፈጻሚ የሚኾነው፡፡ የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ በቀጥታ የሚፈጸመው ተከራካሪው የቅስቀሳ ተሳትፎውን በቀጥ ከሕዝቡ ጋር በመገናኘት ሲፈጽም ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገውም ሕዝብ በተሰበሰበበት በቀጥታ ንግግር በማድረግ ወይም በሌላ ስልት (ለምሳሌ ቴሌቪዥን፣ የፌስቡክ የቀጥታ ሥርጭት፣… ) ታዳሚውን ወደ ራሱ ዓላማ በመሳብ ሊኾን ይችላል፡፡ ዓላማውም የታዳሚውን አስተሳሰብና ግንዛቤ በስሜት ወጥሮ ወደ ራሱ ፍላጎት በማምጣት ተባባሪው ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ አዶልፍ ሒትለር ‹የቴክኒኩ አባት› የኾነ ሰው ነበር ይባላል፡፡ በ2ኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ሕዝብን ከዓለም የተለየ ምርጥ እንደ ኾነና ዓለምን መግዛት የሚገባው ሕዝብ መኾን እንዳለበት አድርጎ በመቀስቀሱ አብዛኛው የጀርመን ሕዝብ ከእሱ ዓላማ ጋር እንዲያብር አድርጎታል፡፡ በዚህ የተነሣም ሒትለር ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ አይሁዳዊያንን ሲጨፈጭፍ የጀርመን አብዛኛው ሕዝብ ተባባሪው ኾነ እንጂ ተቃዋሚው አልኾነም፡፡ መሶሎኒም ቢኾን እንደ ጓደኛው ሐትለር ተመሳሳይ ስልት ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ሲያውጅ ‹ክብር ያለህ የጣሊያን ሕዝብ ሆይ እንዴት ባልተማረና ባልሠለጠነ ጥቁር ሕዝብ ተሸንፈህና ተዋርደህ ትቀመጣለህ› በማለት የጣሊያን ጦር በዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ መሸነፉን እንደ ውርደት በመቁጠር ቀስቅሶበታል፡፡ በዚህ የተነሣም የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያዊያንን በመርዝ ጭስ ሲፈጅና ዐዲስ አበባ ላይ በመትረጌስ ሲጨፈጭፍ አብዛኛው የጣሊያን ሕዝብ ሐዘኑን አልገለጸም፡፡ አመለካከቱን የተቀሰቀሰበት የፍላጎት ነፋስ የወጠረው ጎማ ያሽከረክረው ነበርና፡፡ ይህንን ከአገራችን የብሔር ፖለቲከኞች ጋር በማያያዝ መተንተን ይቻላል፤ በራሳችሁ ከሚደረጉ ንግግሮች ጋር አያይዙት፡፡

በነገራችን ላይ የፖለቲካ ተመራጮችም ቢኾኑ ይህንን የቅስቀሳ ታክቲክ ይጠቀሙበታል፡፡ እያንዳንዱ መራጭም እንደተባለው መተማመንን፣ ደስታ ማግኘትን፣ ክብር መጋራትን፣ መደነቅንና መታወቅን ስለሚፈልግ የቀረበውን ሐሳብ ወኔው ተቀስቅሶ ይቀበለዋል፡፡ ‹ግን እውን የቀረበው ሐሳብ ጭብጥ በማስረጃዎች ተደግፏል፤ ተጠየቃዊ ፍሰቱስ ሠምሯል?› ቢባል ምናልባት በሥነ-ልቦና ጫና መፍጠር ካልኾነ በስተቀር ተቃራኒውን ሊኾን ይችላል፤ ሐሳቡ አመክንዮአዊ አግባብነት ካለው ግን ሕጸጽ አይፈጸምበትም፡፡

ይህ የቀጥታ ሕዝብ ቅስቀሳ ክርክር ሕጸጽ በንግግር ብቻ ሳይኾን በጽሑፍም ይፈጸማል፡፡ በዚህ የአንባቢውን ስሜት ወጥረው ወደ ተፈለገው ግብ የሚያመጡ የስሜት ጫና እና ክብደተ-ዋጋ የተሸከሙ ቃላትን (ሐረጋትን) መርጦ መጠቀም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ‹የነፃነት ታጋይ› ከተባለ ነፃነተን የሚወድ ኹሉ ከታጋዩ ጎን አብሮ ይሰለፋል፤ ሻዕቢያ ‹ነፃነት ወይስ ባርነት?› ብሎ ምርጫ በማሳጣት ኤርትራን እንደገነጠለው ማለት ነው፡፡

የሚከተሉት ስልቶች የቀጥታ ሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ የሚፈጸምባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

  1. ከባለ ዕድል ጋር ማበር (Band wagon)

አስረጅ፡- ‹90% የሚኾኑት የዓለም ሳይንቲስቶች በዳሪዊን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ትክክለኛነት ይስማማሉ፡፡› ከተባለ አንዱ ሳይንቲስት ‹የዚህ ንድፈ ሐሳብ ስህተት የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለኝ› ብሎ ቢከራከር የሚሰማው የለም፡፡ መርሁ ‹እንደ ንጉሡ ያጎንብሱ› በሚል ጊዜ ከሰጠው ጋር ተደምሮ መክንፍ ነውና፡፡

  1. የብዛት ተቀባይነት (Consensus Gentium)

የዓለም ሕዝብ የተስማማበትን ጉዳይ እንዴት ብለው ይቃወሙታል? ኹሉም ወይም አብዛኛው ሕዝብ ያመነበትን ነገርስ አይስማሙበትም?

አስረጅ፡- ‹እግዚአብሔር አለ፤ ምክንያቱም የዓለም  ብዙዉ ሕዝብ በዚህ ይስማማልና፡፡› በዚህ ገለጻ የቀረበው ስለ እግዚአብሔር መኖር ማስረጃ ሳይኾን ስለ ብዙ ሰው ማመን ነው፤ ‹ይህን ያህል ሕዝብ ከተስማማ አንተም ተስማማ› እንደማለት ነው፡፡ አሁን ካለው ነባራዊ ኹኔታ ጋር አያይዘን ብንገልጸው ‹አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተደመረ አንተ ከለውጡ ጋር የማትደመርበት ምክንያት ምንድን ነው?› መርሁ ‹ብዙሓን ይመውዑ!› የሚል ነው፡፡

  1. የወል ተግባር (Common practice)

‹አንድን ተግባር አብዛኛው ሕዝብ በጋራ የሚሠራው ከኾነ ትክክል ነው› እንደማለት ነው፡፡

አስረጅ፡- ‹መዘሞት መጥፎ ተግባር አይደለም፤ምክንያቱም ኹሉም ሰው የሚፈጽመው ተግባር ነውና፡፡

  1. የጓደኛ ድፊት (Peer Pressure)

‹ጓደኞችህ ትክክል ነው ብለው ተስማምተውበት እንዴት አንተ ትለያለህ?› የሚል አንድምታ አለው፤ ማለትም በጓደኛ ይሉኝታ በመታሠር ‹ትክክል ነው› ብሎ መቀበልን ያሳያል፡፡

  1. ኅብረት መፍጠር (Plain Falks)

‹አንድ ሕዝብ ነን› ወይም ‹በብሔራችን እንተባበር› እንደማለት ነው፡፡

ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው የቀጥታ የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ ዓይነቶች ሌላው ሰው ወይም አብዛኛው ኅብረተሰብ ተስማምቶበት የሚያደርገውን ወይም ያመነበትን ነገር ‹ትክክል ነው› ብሎ መቀበል ይገባል የሚል ይዘት የሚያፀባርቁ ናቸው፡፡ ኾኖም (ብዙ) አብዛኛው ሕዝብ ስለደገፈው ወይም ስላመነበት ብቻ አንድ ነገር ‹ትክክል ነው› ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በድሮ ጊዜ ‹መሬት ዝርግ ናት፤ ከፀሐይም ትበልጣለች›ተብሎ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ይታመን ነበር፡፡ ይህ እምነት ግን መሬትን ዝርግ አድርጎና ከፀሐይም አስበልጦ አላስገኛትም፡፡ ምክንያቱም መሬት ክብ መኾኗ በተለያዩ ማስረጃዎች ተረጋግጧል፤ ፀሐይምመሬትን ከ99% በላይ እንደምትበልጣት ታውቋል፡፡ ስለዚህ ብዙ ሕዝብ ስላመነበት ትክክል ነው የሚል የክረክር ይዘትና አመለካከት የማያስኬድ ሊኾን ይችላል፡፡

ኹለተኛው የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ የሚፈፀምበት መንገድ የተዘዋዋሪ ቅስቀሳ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም ቡድን ኅብረተሰቡን በመቀስቀስ ከእሱ ሐሳብና ዓላማ ጋር እንዲያብር የሚያደርገው ኅብረተሰቡ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ ኅበረተሰብ ጋር የቀጥታ ተሳትፎ ያላቸውን በኅብረተሰቡ የሚወደዱ፣ የሚከበሩ፣ የሚታመኑና የሚደነቁ ሰዎችን ወይም ነገሮችን በመሣሪያት በመጠቀም ኅብረተሰቡ ዓላማውን ደግፎ እንዲተባበረው ወይም እንዲፈጸምለት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተለይ ይኸኛው የሕዝብ ቅስቀሳ ስልት በማስታወቂያ ሥራዎች የጠለመደ ነው፡፡

ለዚህም የሚያገለግሉ ሦስት ዋና ዋና ስልቶች አሉ፡፡

  1. ከባለ ዕድል ጋር ማበር (Bandwagon Argument)

ሐሳቡን ሲያስተውሉት ‹አንተ ምርቱን ካልተጠቀምክ ይቀርብኸል፤ ከተጠቃሚው ኅብረተሰብም ትለያለህ› የሚል ይዘት አለዉ፡፡ ከዚህ ኹሉ ሕዝብ ተለይተህ ከምትቀር አንትም ተጠቀም› እንደ ማለትም ነው፡፡ ይህ በፍጥነት ገዥ ለማግኘት ይረዳል፡፡

አስረጅ፡- ‹የጥርስ ብሩሽ መጠቀም ከፈለክ አኳፍረሽነ ግዛ፤ ምክያቱም 90% የሚኾኑት የጥርስ ቡርሽ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን ይጠቀሙበታልና፡፡ እና ይኸ ኹላ ሕዝብ የመረጠው ከኹሉም የተሻለው ቢኾን አይደለም ወይ?›

  1. ከዝነኝነት ጋር ማያያዝ (Appeal to Vanity)

ምርትን ከዝነኝነት ጋር በማያያዝ ማስተዋወቅን ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ በጣም ታዋቂ አትሌትን፣ ሙዚቀኛን፣ የእግር ኳስ ተጨዋችንና የመሳሰሉትን በመጠቀም የምርት ማስታወቂያ ዓነት ነው፡፡ ዋና ሐሳቡም ‹ዝነኛ የኾነውን ሰው የምትወደው፣ የምታከብረውና የምትከተለው ከኾነ እሱ ይህንን ይጠቀማል፤ አንተም ብትጠቀም አድናቂው መኾን ይገለጻል፤ የዝናው ተካፋይም ትኾናለህ› የሚል ነው፡፡ የዝናው በረከትም ይደርስሃልና ተሳተፍ!

አስረጅ፡- ‹ኃይሌ ገ/ሥላሴ ተጫምቶት የሚሮጠው ጫማ የአዲዳስ እስኒከር ጫማ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጥ ጫማን የሚፈልግ የኃይሌ አድናቂ ኹላ የአዲዳስ እስኒከር ጫማን መርጦ ይገዛል፡፡›

  1. መጀነን (Appeal to Snobbery)

‹የማንም ልቅምቅም የሰው ልጅ አያውቅም› እንዲሉ አራዶች፤ መጀነንም የሚያንፀባርቀው ‹ጥሩ ነገር የሚመርጥ ሰው ኹሉ ደህና ዋጋ ከፍሎ ክብር ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበትን ምርት (ዕቃ) ይገዛል እንጂ ዝም ብሎ ትርኪ ምርኪ ነገር በቅናሽ ዋጋ ገዝቶ አይጠቀምም› የሚል ሐሳብን ነው፡፡

አስረጅ፡- ‹የምርጦች ምርጥ መናኸሪያ ሸራተን ዐዲስ ሆቴል በዘንድሮ 2000 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሚሊኒየም ዘመን መለወጫ በዓል ልዩ ዝግጅት አዘጋጅቷል፡፡ ይህንን ለኹለተኛ ጊዜ ደግመው የማያገኙትን የዘመን መለወጫ በዓል 5000 ብር ከፍለው ከእኛ ጋር ተደስተው ያሳልፉ፡፡›

ከዚህም በተጨማሪ የታዋቂ ድርጅቶችን፣ ጋዜጦችን ወይም ባለሙያዎችን ምስክርነት መጥቀስ የተለመደ የማስታወቂያ ሥራ ስልት ነው፡፡ ለምሳሌ በብዙ የመጻሕፍት ሽፋን ላይ ‹ምርጥ ተሸጭ›፣ ‹ተወዳጅ›፣ ‹አስደሳች›፣ ‹ልብ አንጠልጣይ› እና የመሳሰሉትን የተዋቂ ሰዎች ወይም ጋዜጦች/ድርጅቶች ምስክርነትን እናገኛለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ገለጻዎችም ዓላማቸው የገዥውን ስሜት በመሳብ ወጥሮ የተባለውን ምርት/ዕቃ እንዲገዛ ማድረግ ስለኾነ በአብዛኛው የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ ይፈጸምባቸዋል፡፡

ተዘዋዋሪ የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ የሚፈጸመው በማስታወቂ ሥራ ብቻ አይደለም፤ በተለያዩ ተግባራትም እንደሚፈጸም ማስተዋል ያስፈልጋል፤ በሃይማት ስብከት፣ በፖለቲካ ቅስቀሳም በበዝዛት ይንፀባረቃል፡፡ በአጠቃላይ ግን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ስልት የሚፈጸም የሕዝብ ቅስቀሳ ሕጸጽ ይዘቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ የይዘቱ መዋቅርም ‹አንተ መወደድ፣ መደነቅ፣ መፈቀር፣ መከበር፣ አንድነት ወይም የደኅንነት ጥበቃ ማግኘት ትፈልጋለህ፤ ስለዚህ ይህንን የምነግርህን ተክክል (እውነት ብለህ ተቀበል፣ ተግብር› የሚል ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ዓላማውም የታዳሚውን አወንታዊ ወይም አሉታዊ ስሜቶች በማራገብ የሥነ ልቦናውን እሳት አቀጣሎ ወደ ራሱ ፍላጎት መማረክ ነው፡፡ ስለዚህ የቀጥታ የሕዝብ ቅስቀሳ ዘዴ የተሰበሰበውን (በቀጥታ የተገኘውን) ሕዝብ ስሜት ወጥሮ አፋጣን መልስ በመስጠት የአንድንት ጥንካሬና ደኅንነት እንዲጋራ ማድረግ ነው፤ ከጠንካራው አንድነትና የደኅንነት ጥበቃ ራሱን ለማግለል የሚፈልግ ሰው እንደ ጉዱ ካሣ ‹ጉድ!› መባልና በኅብረተሰቡ መጠላትን ስለሚፈራ ‹አሜን!› ብሎ ይቀበላል፡፡ በተዘዋዋሪ ስልትም ብንሄድ መንገደዱ ነው እንጂ የሚለየው መድረሻው አንድ ነው፤ መንገዱም የተለየው በእጅ አዙር በሌሎች ስለሚጠቀም ነው፤ ሌሎቹ የግቡ ማድረሻ መሣሪያዎቹ ናቸው፡፡

ጎበዝ! እዚህ ላይ ታዲያ ይጠነቀቋል፤ ‹የሰው ልጅ አንድነትና ደኅንነትን፣ እንዲሁም መተባበርን፣ መደነቅን፣ መከበርንና መታወቅን መፈለጉ ስህተት ነው› አልተባለም፡፡ ነገር ግን ቁም ነገሩ ‹እነዚህን የሰው ልጅ ፍላጎት ማጠንጠኛዎች በመጠቀም ስሜቱን ወጥሮ ለግላዊ አመለካከትና ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋል አመክንዮአዊ ተግባር አይደለም፤ ነዚህም የማስረጃን ትክክል አለመኾን በስሜት ቅስቀሳ በመጠቀም ኅብረተሰቡ በስሜት መኪና ብቻ ተሳፍሮ እንዲጓዝ ማድረግ ማስረጃውን ከጭብጡ ጋር አብሮ እንዲሔድ አስለማያደርግ ስህተት ነው፤ ስለኾነም ሕጸጽ ይፈጸምበታል፡፡› የሚለው ነው፡፡ ‹የቸኮለ ጅብ ቀንድ ይነክሳል› እንደሚባለውም በስሜት ተወጥሮ የሚነዳ ኅብረተሰብም ጥፋቱ ተሸፍኖበት የሕጸጽ ተግባራትን እየፈጸመ የተወሰኑ ሰዎች መጠቀሚያ ኾኖ ሊኖር ይችላል፡፡

ለሚቀጥለው ‹የአህያውን ትቶ ዳውላውን› ሕጸጽ እንዴት እንደሚፈጸም እናያለን፤ እስከዚያው ይቆየን! ያቆየን!

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply