የሸቃዩ ትዝብት

(በካሣሁን ዓለሙ)

ሽቀላ የጀመርኩት መጽሔቶችን ጮኾ በመሸጥ ነው፤ የመጽሔት ሽቀላን ታሪክ አረሳውም፤ ብዙ ነገሮችንም ታዝቤበታለሁ፤ ምሁራን የሚያነቡትንም ለማወቅ ችያለሁ (ምሁራን የሚያውቁት በማንበብ አይደል!)፡፡ መጽሔት ስሸቅልም ቶሎ  ቶሎ ሸጬ ትርፋማ ለመኾንም የሚያስችለኝን  የማሻሻጫ ዕውቀት አዳብሬያለሁ፤ ሳነብ ግን ስልትን እጠቀማለሁ እንጂ ዝም ብዬ አልሸመድድም ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ ከመጽሔቱ ላይ የምፈልገው እውቀት መጽሔቱን ለማሻሻጫነት እንጂ ከዚያ ያለፈው አይመለከተኝም፡፡

ዕወቀትም የማሻሻጫ መሣሪያ እንደኾነም ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ የአንድን መጽሔት ርዕስ ‹ጥሩ አድርጎ በካርቶን፣ በተመረጡ ቃላት ወይም የቃላቱን አጻጻፍ በማሳመርና በማጉላት ማስጮህ› የሚጠቅመው ያየው ሰው እንዳያልፈው ለማድረግ ነው፤ ስለዚህ የመጽሔቱን (ወይም የጋዛጣም ሊኾን  ይችላል) ርእስ ማስጮህ ዕወቀት ነው፤ የጩኸቱም ግብ በብዛት እንዲሸጥ ለማድረግ ነው፡፡ ሌላም ምሳሌ ላንሳ አንድ መጽሔት አዘጋጅ የተሻለ ዕውቀት ያለቸውን ሰዎች በመጠየቅ ወይም በማጻፍ ካካተተ በብዛት ይሸጥለታል (ለምሳሌ ጦቢያ የተባለው መጽሔት ዋና ማሻሻጫ ፀጋዬ ገብረመድኅን (ሎሬቱም ኾነ አርአያው) እንደነበር አስታውሳለሁ)፤ ይህም ማለት የዐዋቂው ሰዉየ ዕውቀት ለማሻሻጨነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ነው፡፡ ደግሞስ ድለላ (የገበያ አፈላላጊም ይባላል)፣ የማስታወቂያ ሥራ የመሳሰሉ ሥራዎች ድግሪ የተመርቁ ሰዎች የሚሠማሩባቸው አይደሉም እንዴ! ከእነዚህ የበለጠ የዕውቀት አሻሻጭነት ምሳሌ ሌላ ምን ያስፈልጋል? ስለዚህ እኔም የመጽሔትን ዕውቀት ለማሻሻጫነት መጠቀሜ ትክክለኛ ዐዋቂነት ነው፡፡ ከማይሠራበት ብዙ ዕውቀትም የኔ የማሻሻጫ ዕውቀት ሳይሻል አይቀርም፡፡

ዕውቀትን ለማሻሻጫነት ስጠቀምም በመጀመሪያ በመጽሔቱ ላይ ወይም ውስጥ የካርቶን ሥዕል መኖሩን እሾፋለሁ፡፡ የካርቶን ሥዕሉን ካገኘሁም እሱን በምን ዓይነት አጠራር መሸጥ እንዳለብኝ እዘጋጅበታለሁ፡- የካርቶን ሥዕሉን መልዕክትና ያሣሣል ጥበቡን ተረዳሁ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የካርቶን ሥዕል ኖረም አልኖረም ለሽያጭ የሚስቡ ርዕሶችን መርጬ በማንበብ በራሴ አባባል እንዴት መግለጽ እንዳለብኝ እዘጋጃለሁ፡- የመጽሔቱን ዋና ነጥብ አገኘሁት ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ለገዥዎቼ ብርቅ በመኾን ከጠዋቱ 1፡30 እስከ 3፡00 ሰዓት እና ከሰዓት በኋላ ከ10:00 እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ብቻ በመሸጫ ቦታ ላይ እገኛለሁ እንጂ ከሌሊት እስከ ምሽት ሳላቋርጥ አልጮህም፡- ምክንያቱም የጊዜ አጠቃቀሜ የመጮህ ጉልበቴን ይቆጥብልኛል፤ አንብቤ ለመሸጥ ይጠቅመኛል፤ የድምፅ ብክለትንም ቀንሸበታለሁ፡፡ እስቲ ማሳያ እንዲኾነኝ የተወሰኑ ምሳሌዎችን ልጥቀስ፡፡

በመጀመሪያ በዚያን ጊዜ የነበረውን የካርቶን ሥዕል ልግለጽ፡፡ የዛሬን አያድርገውና በዚያን ጊዜ የነበሩ መጽሔቶች ሕግ አልነበራቸውም፡- ልቅ ነበሩ፡- መንግሥት አይፈሩ፤ መሪ አያከብሩ፤ መጽሔቱን ጥሩ የሚያሻሽጠው ከኾነ የማይጽፉት ነገር፣ በካርቶን ሥዕል ያማይሥሉት ያማይቀርጹት ጉድ አልነበረም፤ ስለኾነም የካርቶን ሥዕልን በመጠቀም በፈለጉት በየትኛውም ነገር ላይ የማሾፍ ነጻነት ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ በጊዜው የነበሩትን ትልቅ ሰው፡- የኢትዮጵያ መሪ፡- አንዳንድ ጊዜ ድመት፣ የሜዳ አህያ ፣ የሚዋጋ በሬ ፣ እባብ ፣ ጥንቸል፣ የቄራ ከብት አራጅ ፣ ባለ ቀንድ ወታደር፣… እያደረጉ በመሳል ያሾፉባቸው ነበር፡፡ እነዚህ የካርቱን ሥዕሎች ደግሞ ለእኔ ገበያ በጣም ጠቃሚ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አንድ መጽሔት የኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ለማሳየት የኢትዮጵያ መሪ ላም ሲያርድ የአሜሪካ፣ የግብጽና የሌሎች አገሮች መሪዎች ደግሞ ላሚቱን በገመድ ጥለው የሚያሳይ ካርቶን ሥሎ አወጣ፡፡ አቤት ይህንን መጽሔት ተጨማሪ ማንበብ ሳያስፈልገኝ በካርቶኑ ሥዕል ብቻ እንደጉድ ቸበቸብኩት፤ ለእኔ ያስፈለገኝ ‹ተመልከቱት ኢትዮጵያን እንደላም ጥለው አንገቷ ላይ ሲያርዷት› ማለት ብቻ ነበር፡፡

የገረመኝ ግን ኢትዮጵያውያን ነን እያሉ፣ አገራቸው እንደላም ስትታረድ እንደማልቀስ ፣ እንደማዘን ይልቁንም እንዳስደናቂ ነገር ብርቅ አድርገውት ከኔ መጽሔት ለመግዛት መሻማታቸው ነው፡፡ ደግሞ እኮ ‹ኢትዮጵያ አገራችን እናታችን ናት፤ ኤርትራም የእሷ ራስ ናት› ብለው ያወራሉ፤ ለመኾኑ ለእናታቸውም ዝም ብለው እንደዚህ ነው የሚደነቁት ማለት ነው? ለነገሩ ገርመውኝ እንጂ  ለኔማ እንደዚያ መቅረቡ ጠቅሞኛል፤ የካርቶን ሥዕሉ በዚያ መልክ ባይቀርብ ኖሮ መቼ በደንብ እሸቅለው ነበር?  መጽሔቱም እንኳን በዚያ መልክ አወጣ፣ እነሱም ከሚጣሉ ይልቁንም እንኳን ተደነቁ፤ ተገርመውም እንኳን በወረፋ ገዙኝ፤ ኤርትራም እንኳን ተቆረጠች፤ ጥሩ መሸቀል ችያለሁና!

ስለ ኤርትራ ጉዳይ ሳነሳ መጽሔት ለመሸጥ የነበረው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ መግለጽ ግድ ይለኛል፡፡ ኤርትራ መገንጠሏም ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ መክፈቷም ለነበረው የመጽሔት ሽያጬ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶልኛል፡፡ እዚህ ላይ ግን የሁለቱ አንድነት ተቆርቋሪዎች ከኾናችሁ ‹የኤርትራ መገንጠልና ከኢትዮጵያ ጋር መዋጋቷ እንዴት ጠቃሚ ነበር ትላለህ?› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡

 አልገባችሁም ይኾናል እንጂ እንኳን ለእኔ ለሲ.ኤን.ኤን እና ለቢ.ቢ.ሲ እንዲሁም ለአሜሪካ ሬዲዮና ለጀርመን ሬድዮ እንደጠቀማቸው ሰምቻለሁ፤ እንዲሁም ለመሣሪያ ሻጮች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መኾን  መቻሉን፣ ለሕዝብ ቁጥር ቀናሾችም ብዙ ሰውን በማሳነስ ያደረገውን አስተዋጽኦ ማነው የሚክደው? ለምሳሌ ለዜነኞች ስንት ጥቅም ነው ያስገኘው? ስለ ጦርነቱ ስንትና ስንት ዜና ነው በየቀኑ የተነበበው? እንግድህ ሬድዮና ቴሌቭዥን ሥራቸው ወሬ ከሆነ፣ ጦርነቱ ደግሞ በዕየለቱ ጥሩ የወሬ ምንጭ ከነበረ ለተሰሚነታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት አይደለም እንዴ?

 በጦርነቱስ ስንት ሰው ነው ያለቀው! የሕዝብ ብዛትን ለመቀነስ ለተቋቋሙ ድርጅቶች (አካላት) ሳይለፉ ቀነሰላቸው ማለት አይደም ወይ? ቆይ!

ሌላው ደግሞ ጦርነቱን ለማሸነፍስ ሁለቱም አገሮች ስንትና ስንት መሣሪያ ነው በዓይነት፣ በዓይነቱ የገዙት? (መቼም አንደኛቸውም የመዋጋትን እንጂ መሣሪያ የመሥራት አቅምን እንዳላደበሩ ይታወቃል)፤ አንድ ግዥ ሲደረግ ደግሞ ለሻጩ ገቢ እንደሚያስገኝ፣ ለገዥው ግን ወጪ እንዳለበት የማያውቅ ማነው? እና! የመሣሪያ ሻጮችን ከፍተኛ ተጠቃሚነት ማን ነው የሚክደው? ለእኔም መጽሔቱን ‹እንደ ጉድ› በመሸቀሌ እንደዚያ ነው የተጠቀምኩት፡፡

ምናልባት ለተዋጊዎቹ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ የመሣሪያ መግዢያ ብዙ ብር ስላስወጣቸው፣ ዜጎቻቸውን ስላስጨርሳቸው፣ አንድነታቸውን ስለበተነባቸው አልጠቀማቸው ይኾናል እንጂ ለእኔ ብዙ መጽሔት በማሸጥ ‹ዐመድ ዐመዱን› ስላስነከሰኝ በጣም በጣም ባለውለታዬ ነው፡፡ እኔ ስለነሱ ምን አገባኝ! ከፈለጉ አንድ ሰው (እኔ) እስከምቀር ድረስ ይዋጉ፤ ደግሞስ ‹ለኤርትራና ኢትዮጵያ እንደሰው የረከሰ የለም› ይባል የለ! የረከሰ ነገርም ዋጋው አነስተኛ ነው፤ ዋጋ የሌለው ነገር ደግሞ ቢጠፋም አይጎዳ፡፡ ሆኖም ምናልባት እነሱ ቢጎዱ እንኳን ለእኔ የነበረውን ጠቀሜታ እንዳታጣጥሉብኝ፡፡

እስቲ የኤርትራ ጉዳይ ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር እንድትገነዘቡልኝ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ፡፡ ‹ወያኔና ሻዕቢያ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታ ነበር› አሉ፤ ‹የወያኔው መሪ የኤርትራን መገንጠል መደገፉን ከኹሉም አገሮች በፊት ለተባበሩት መንግሥታት አሳወቀ›፤ ‹ወያኔና ሻዕቢያ ‹ኤርትራ ነጻነት ወይስ ባርነት?› የሚል የተንኮል ጥያቄ ለኤርትራዊያን አቅርበው ኤርትራን ገነጠሉ፡፡›… አረ አላስታወሰውም እንጂ በጣም ብዙ ነው፡፡ በጦርነቱም ጊዜ ቢኾን ‹ሻዕቢያ ወያኔ ስለከዳው በኢትዮያ ላይ ጦርነት ከፈተ፡፡› ‹ኢትዮጵያ ጦርነቱን ብታሸንፍም ጦሩ አሰብን እንዳይዝ መሪው ከለከሉ›…  እየተባለ ይጻፍ ስለነበር ገበያ ስቦልኝ ነበር፡፡

አንዳንደዬ ግን እንደ ታዛቢ ነገሩን ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ለምሳሌ እንደ እኔ እንደ እኔ ‹ኢትዮጵያ ኤርትራን ቅኝ ገዝታታለች› መባሉ አያስገርምም፤ ምክንያቱም ‹ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያን አይደሉም› ተብሏልና፤ ኢትዮጵያዉያን ሳይኾኑ ናችሁ ከተባሉ፤ አብረው መኖር ሳይፈልጉ እንዲኖሩ ተደርጎ ከነበረ፤ ይህንንም ወያኔና ሻዕቢያ ካመኑበት፤ ‹ቅኝ ግዛት› ማለታቸው ስህተት አይኾንም፤ ቅኝ ግዛት ማለትም የራስ ያልሆነን አገር ተቆጣጥሮ መግዛት ማለት ይመስለኛል፡፡ በዚህ መሠረት ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያን ካልነበሩ፤ ኋላ ግን በግድ በኢትዮጵያ ሥር እንደኾኑ ከተደረገ ‹ቅኝ ገዝታታለች› መባሉ ስህተት አይሆን፤ ለዚህ ደግሞ ሻዕቢያ ለመገንጠል በሚል ብዙ ዓመት ተዋግቶበታል፤ እና አምኖ ስንት የተዋጋበትን ተሳስተሃል ማለት ራሱ ስህተት አይሆንም?

‹የወያኔው መሪም ከኹሉም አገሮች በፊት ኤርትራ ትገንጠልልን› ማለቱ ምን ይደንቃል? ከሌሎቹ ይልቅ የሚቀርበውና የሚተዋወቀው መሪ እሱ አይደለም ወይ? እና! ለሚያውቁትና ለሚቀርቡት ቀድሞ መድረስና ማገዝ ምኑ ነው ነውሩ? ‹ነጻነት ወይስ ባርነት ማለታቸውስ ምኑ ያስገርማል? ዓላማቸው መገንጠል አይደለም ወይ? ሻዕቢያዎች ለመዋጋት የተነሱትና የተዋጉት፣ ወያኔዎቹም ያገዟቸው ለነጻነት አይደለም ወይ? ሕዝቡንስ የሚመሩት እነሱ አይደሉም ወይ? ምኑ ነው የተንኮል ጥያቄ የኾነው? ነው ሕዝቡ እነሱን እንዲመራቸው ተፈልጎ ነው?

ሕዝብ እንዲመራቸው ማድረግ ነበረባቸው ከኾነ ‹የማይመስል ወሬ ለሚስትህ አትንገር› የሚባለው ተረት አልገባችሁም ማለት ነው፤ ሰውን ያለ ጠባዩና ተፈጥሮው ‹ሁን!› ማለት ሞኝነት ነው፤ ‹ሕዝብ› ስም ከተሰጠው ምን ዐነሰውና ነውና መሪ ካልኾነ የሚባለው? ሕዝብ መሪ መኾን  የሚችለውስ የት አገር ነው? በእውነታው የበግ መንጋ ራሱን አይጠብቅም፤ ሕዝብን ‹መሪነህ› ማለትም ‹የበግ መንጋ ራሱን ይጠብቅ› ማለት ነው፡፡ ደግሞም ‹ወያኔና ሻቢያ እኮ ጫካ አበጅተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲዋጉና ሲወጉ የኖሩት (ካልወጉ ይቅርታ) ሥልጣንን ለራሳቸው ወስደው ለመጠቀም እንጂ መልሰው ለኢትዮጵያ ሕዘብ ለመስጠት አይደለም› ሲባል ሰምቻለሁ፤ ስታስቡት ለወጉት ሕዝብ ሥልጣንን የሚሰጡት ምን ዓይነት ሞኝ አደረጋችኋቸው? ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ እንዳውም ‹የኢትዮጵያን ሕዘብ ያለ ክፍያ ለመግዛት ነው› የተባለው የተግባር ምስክር ያለው ይመስለኛል፡፡ ‹ለምን ይዋሻል?›

‹ሻዕቢያ ወያኔ ስለከዳው ነው ጦርነት የከፈተው› ማለትም አያስገርምም፤ እና ከከዳው ወዳጅ ይሁነው እንዴ? መካካድ ባለበት መጣላት እንደሚኖር ግልፅ ነው፤ ሁለቱ ደግሞ የኤርትራና የኢትዮጵያ ባለቤቶች መሆናቸው ይታወቃል፤ ስለዚህ ሻዕቢያ ከወያኔ ጋር ከተጣላ የወያኔ የኾነችውን ኢትዮጵያን መውረሩ አያስደንቅም፤ እንዲያ ካልኾነማ ወዳጅ እንጂ ጠላት አይኾንም ነበር፤ ነው ሻዕቢያ የምትሉት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን ይውረርና ወያኔን አጥፍቶ ይግዛችሁ? የማይኾን  ነገር ነው፤ ‹የአራት ኪሎ ተቀያያሪ ገዥ ከበዛ ችግርም አብሮ ይበዛል እንጂ ይቀንሳል ብላችሁ ባትገምቱ ይሻላችኋል› ባይ ነኝ፡፡

የኢትዮጵያ ጦር አሰብን ለመያዝ ሲል መሪው መከልከላቸው ግን አከራካሪ ነው፤ በኔ ግምት ግን አንደኛ ምናልባት መሪው ቀድሞም አሰብን ላለመንካት ቃልኪዳን የነበራቸው ሊኾን  ይችላል፤ ቃላቸውን ማክበራቸው ደግሞ አግባብ ነው ወይም አሰብ ኤርትራ ስትገነጠል ይዛው ስለሄደች የኤርትራን የባለቤትነት መብት ላለመንካት (ተንኳሽ ላለመኾን) ብለው በማሰብ ወይም አሰብን በመያዝ ተጨማሪ ጭቅጭንና ጦርነትን ከመጋበዝ (አሰብ አሳብ እንዳይኾንባቸው) መተው ይሻላል በሚል ግምት ወይም በሌላ ባልታወቀ ምክንያት ብለው ሊኾን  ይችላል ‹አሰብን አትንኩ! ተመለሱ› ያሉት፤ አንዳንዶች ግን ‹የናታቸው ሥጋ አድልቶባቸው ነው› ይላሉ፤ እኔ ይኸንን ‹ውሸት ነው› ባልልም፤ ‹እውነት ለማድረግ› ይከብደኛል፤ ያልከበደው ይመን፡፡ ቢኾንስ ከእናታቸው ሥጋ መገኘታቸውን ማን ይክዳል?

ለነገሩ እኔ ምን አገባኝ! የኔ ቁም ነገር የኤርትራ መገንጠልና ጦርነት መቀስቀስ ለመጽሔት ሽቀላ የነበረውን ከፍተኛ ጥቅም መናገር ነው፤ ተናገሬለሁ፤ መጽሔት ገዥዎቹ ሲፈልጉ የማያስደንቀው ይድነቃቸው፤ ሳይፈልጉም የሚያስደንቀው ጉዳይ ምንም አይምሰላቸው፤ ምን አገባኝ! ሲፈልጉ ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ ናቸው እያሉ እንደድሮው ይኑሩ፤ ወይም መለያየታቸውን አምነው አንድ ለማድረግ ይጣሩ፤ ካልፈለጉም ተለያይተናል በማለት ሲዋጉ ይኑሩ፤ መሪውም ቢኾኑ (የኢትዮጵያ ባለቤት እሳቸው ናቸውና) ካስፈለጋቸው አሰብን ይያዙ ካላስፈለጋቸውም ይተውት፤ ካሻቸውም ባድሜንም ይጨምሩላቸው፤ ከደበራቸው ቀይ ባህር የግመል ሽንት ነው ይበሏቸው፤ ምን አገባኝ! ለእኔ! የመጽሔት ሽቀላዬ በቂዬ!

ለነገሩ ለመጽሔት የነበረው ሥራ ጠቃሚ የማሻሻጫ ርዕስ የነበረው የኤርትራ ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡ በኢሕአዴግ ተቆጥተው ጫካ ገብተዋል የተባሉ ተቋዋሚዎችም ጥሩ ማሻሻጫ መኾን ችለው ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ‹አርበኛ ነኝ› የሚል ግንባር ጎንደርን ‹ጦርነት በጦርነት አድርጓታል› ተብሎ መጽሔቶችም ያንን ዜና እየያዙ መውጣት አበዙ፡፡ የሚታተመውም የመጽሔት ኮፒ በጣም ብዙ ስለነበር ለእኔም ተመችቶኝ ነበር፡፡ ለዚህ ዓይነት ርዕስ ደግሞ እኔ አሻሻጡን ስለምችልበት ‹ጎንደር ጦርነት አለ› የሚለውን ርዕስ ‹ዐዲስ አበባ› አደረስኩት፡፡ ምክንያቱም አርበኛው ጎንደር ጦርነት የጀመረው ዐዲስ አበባን ለመያዝ ጭምር መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ የገረመኝ ግን የጦርነቱ አርበኛ እንኳን ዐዲስ አባባ ሊድርስ ይቅርና እዚያው መሬት ውስጥ ይግባ ወይም ጫካ እየሠራ ይኹን ሳያሳውቅ ተሰውሮ ቀረ! የት እንደደረሰ ዐላወቅኩም፡፡ ዋሽቶ እኔንም ውሸታም ስላደረገኝ ግን አብሽቆኛል፡፡ ስገምት ግን በድሮ የአርበኞች ስም ጦር መሣሪያ የሚሸጥ ሰው ያስወራው ይመስለኛል (የጦርነት ወሬ በመንዛት ጦርነት መቀስቀስ፤ ከዚያም ብዙ መሣሪያ መሸጥ፤ በእሱም ትርፍ በትርፍ መኾን ብሎ ሊኾን  ይችላል ያወራው፤ ማን ያውቃል!)፤ ግን ምን አገባኝ ችሎታው አይደለም ወይ?

በዚያን ጊዜ ‹አርበኛ ነኝ› ባዩ ግንባር ብቻ ሳይኾን ኦነግ የሚባል ዝነኛ ግንባራም ነበር፤ እሱም ቢኾን ገበያ ይስብ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ‹ጮማ መሸቀያ ይኾነኛል ብዬ› የሰፍይ ነበልባል የሆነ ጋዜጣ ላይ የወጣውን ‹ኦነግ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም አለ› ስል ሰው እየፈራ ይኹን እያፈረ አልገዛ ብሎኝ ነበር፤ ታዲያ ‹ለምን ቀረብ አላደርገውም› በማለት ‹ኦነግ የተባለው ተቃዋሚ ድርጅት ዐዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ፊንፊኔ ለማድረግ መዘጋጀቱ ተገለጸ› ስል ሰው ኹሉ ወይ ፈርቶ ወይም ዐዲስ አበባን የብቻው ለማድረግ ጎምጅቶ ተሻማበት፡፡

ሳስበው ግን ‹ኦነግ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም› አለ የተባለው በማን እንደሆነ እንጃ! ራሱ ከሆነ ማንን ተቀይሞ እንደኾነ አላወቅኩም!፡፡ አላሳምን ስላለኝ ነው እንጂ ‹ምኒልክን ነው› ያሉኝ ግን አሉ፡- ‹ኢትዮጵያ› ማለት የ‹ምኒልክ› ማለት ነው ያለው ማን ነው? እኔማ ‹ኧረ! ለመሆኑ ለመካድ ያደረሰው ማን ‹አይደለህም በል!› ብሎ ቢያሰለጥነው ነው?› የሚል ጥያቄም አቃጭሎብኝ ነበር፡፡ አሁንም ለማመን ከብዶኝ ነው እንጂ በወሬ ወሬ ጀርመኖች ናቸው የላቲን ዜጋ እስከ መኾን ያደረሱት ሲባል ሰምቻለሁ፡፡

ግን በጋዜጣ እንደ ሰማሁት ከሆነም ኦነግ በብሔሩ ኦሮሞ ነው፡፡ ታዲያ ‹ኢትዮጵያዊ አይደለሁም› ያለው ኦሮሞነቱንም ክዶ ነው ወይስ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦሮሞ አልነበረም (ወይም ኢትዮጵያዊ አይደለም) ብሎ ሊክድ ነው? ኦሮሞ ጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው፤ ኦነግም የኦሮሞ ልጅ ከሆነ ለምን ራሱን ይክዳል? ነው የጥንቷ ኢትዮጵያ አርጅታለች ብሎ ሳትሞት ሊወርስ ፈልጎ ነው? እና ክዶ መውረስ አለ እንዴ? እኔ ግን ሳስበው ወላጅነቱን ለካደው ልጁ  ቤቱን የሚያወርስ አባት ያለ አይመስለኝም፡፡

 ኦነግ ‹ዐዲስ አበባ የኔ ፊንፊኔ!› ማለቱም ይገርመኛል፤ ትንሽ እንኳን የታሪክ ዕውቀት ካለው አንደኛ ዐዲስ አበባ የሚለውን ስም የሠጡት እቴጌ ጣይቱ መሆናቸውን የሚያውቅ ይመስለኛል፤ ጣይቱ ደግሞ ኦሮሞ ናቸው ተብሎ የተጻፈ ታሪክ በመጽሄት ላይ አንብቤያለሁ፤ እሳቸው ስያሜዋን ከሰጧት ኦነግ ‹ፊንፊኔ› እያለ የሚጠራው የእሱ ያልኾነ ኦሮሞ የሠጠውን ስያሜ አልቀበልም ማለቱ ነውን? ሁለተኛም ‹ፊንፊኔ› የሚለው የቦታ ስያሜ የሚመለከተው የፍል ውሃ አካባቢን እንጂ ሰፊዋን ዐዲስ አበባ አይወክልም ይባላል፤ ይህ ከሆነ ሰፊውን የዐዲስ አበባ ከተማ ‹ፊንፊኔ› ማለት ዐዲስ ስም ማውጣት አይሆንም ወይ? ነው የዐዲስ አበባ አካባቢ በሙሉ በፊትም ፊንፊኔ ተብሎ ይጠራ ነበር? በሌላ በኩል ዐዲስ አባባ ኢትዮጵያውያን አገራችን ብለው የሚኖሩባት ከተማም እንደኾነች አያውቅም እንዴ? ‹አረ! ኢትዮጵያውያን ይቀየሙኸል፤ እሽ አይሉህም› የሚለው ሰው እንዴት አጣ? ነው ኢትዮጵያዊይነትን ስለጠላ ኢትዮጵያውያንም ሰው መስለው አልታይህ አሉት?

ለነገሩ እሱ ከፈለገ ምንም አይሁን፤ የፈለገውንም (ቢፈልግ ጀርመናዊ ካሻውም ላቲናዊ) ይኹን እኔ ምን አገባኝ፤ መብቱ ነው፤ ፍራቴ ግን ‹እንኳን የዐዲስ አባባ ጎዳናን ሰማዩንም ቀና ብለህ እንዳታይ› እንዳይለኝ ነው፡፡ ከዐዲስ አበባ ጎዳና እንዳያባርረኝ ብዬ ነው እንጂ! ከፈቀደልኝ ይመቸው፡፡

‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም› ከሚሉት ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያ አጨቃጫቂ ታሪክም ቢኾን  ጥሩ የነበረው ገበያን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም› የሚሉት አለመሆን መብታቸው ስለሆነ ነው መሰል ብዙም አላስቆጡም፤ ታሪኩን ባሳጠሩት ላይ ግን ጭቅጭቁ ደርቶ ነበር፤ ሽቀላየም እንደዚሁ፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያን ጠልተው የ‹ቅኝ ገዥ ፍለጋ› አውሮፓ ሲሄዱ ቅር ያለው ሰው አልነበረም፤ ቢኖርም ደፍሮ የተናገራቸው የለም፡፡ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት ተብሏል መባሉ ግን አንድ ሰሞን አስቆጥቶ ስለነበር በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ በብዙ መጽሔቶች ይጻፍ ነበር፡፡ ከሚወጡ ጽሑፎች መካከልም ‹‹የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት› ማለቱን ምሁራን ተቃወሙ›፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ3000 ዓመታት በላይ እንደኾነ የታሪክ ምሁራን አረጋገጡ› የሚሉት የተለመዱና ብዙ ሰሚንም የሚስቡ ነበሩ፡- የታሪክ ምሁራንም በዝተው ነበር፡፡ ለነበረው አሠራርም አመችተውኝ ስለነበር ብዙ ሸቅየባቸዋለሁ፡፡

በእውነት እኔ እንደታዘብኩት ከኾነ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው› መባሉ በጣም ያናድዳል፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የሚኖር የአንድ ሰው አያት ከፍ ቢል ቅድም አያቱ ኢትዮጵያዊ አልነበሩም ማለት እኮ ነው! ኢትዮጵያ ሳትኖር ኢትያጵያዊ ተብለው መጠራት ይችሉ ነበር? ኢትዮጵያ ከነበረች ደግሞ ያለ ታሪክ ዝም ብላ ተቀምጣ ነበር ይባላል እንዴ? ካልተባለ የኢትዮጵያ ታሪክ በመቶ ዓመት ብቻ መወሰኑ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሊያስቆጣቸው እንደሚችል ማወቅ ነበረበት፤ ባለ መቶ ዓመቱ፡- መቼም ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ እንዳላት የሚከራከር ሰው ‹ኢትዮጵያዊ ቅድመ አያት ነበረኝ› ብሎ አይከራከርም! ስለዚህ ወይ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን አያቶች መኖር ቀንቷል ወይም የታሪክ ዕውቀት የለውም ማለት ይቻላል፤ ወይም ፀረ-የኢትዮጵያ ታሪክ  ሰው ነው፡፡

 ባለ መቶ ዓመት ባለታሪኩን ጉዳይ ያለ-ቢዝነስ ሳስበው ነው እንጂ ከነበረው ሥራ አንጻር ካየነው የመቶ ዓመት ታሪክ መደረጉ በጣም ጠቅሞኝ ነበር፤ ምክንያቱም ‹መቶ ዓመት ነው› ባይባል በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ በየመጽሔቱ በብዛት ተጽፎ ገበያን መሳብ ዐይችልም ነበር፤ ደግሞስ ታሪክ ቢረዝም ካልሠሩበትና ካልተማሩበት ምን ይሠራል? ለጉራ ነው? (ለነገሩ ጉራም ወኔ ነው፤ ወኔ ያለው ሰው ደግሞ ትልቅ ነገር ይሠራል! ስለዚህ ታሪኩን የሚያውቅ ጉረኛ ሰውም ወኔ ይኖረዋልና መናቅ የለበትም፡፡)

የኢትዮጵያ ታሪክ ከተነሣም የአድዋ ድል እንዲሁ በቀላሉ ዝም ተብሎ መታለፍ የለበትም፡፡ እንዳውም አንዳንድ ሰዎች ‹ኢትዮጵያና የአድዋ ድል አንድ ናቸው‹ ብለውኛል፡፡ እውነት ስለመኾኑ እኔ ምን አገባኝ፤ መጽሔት እንደ ጉድ ስለማሸቀሉ ነው እንጂ! ባይኾን የአድዋ ድል ሲከበር ለእኔ ያደረገልኝን ከፍተኛ ጠቀሜታ ልናገር፤ እንዳውም የተከበረ ዕለት ያገኘሁትን ሳስበው ምናለ ሁልጊዜ ቢያከብሩት እላለሁ፡፡

 በእዚያ ዕለት በየመጽሔቶቹ ‹የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያንና በቅኝ ግዛት ለነበሩ ህዝቦች ኹሉ የነጻነት ተምሳሌት መኾኑን ምሁራን ገለጹ› ይባላል፤ ዝርዝሩን ለማየት ሰው ኹሉ ይገዛል፡፡

የአድዋ ድል ግን ይኸን ኹሉ ጥቅም አስገኝቶ ከኾነ እውነትም ታላቅ ነው፤ ለተጨቆኑ የነፃነት ተምሳሌት ከመኾን  የበለጠ ምን ትልቅ ውለታ አለ? ግን የሚያናድደኝ ለምን የአፍሪካም ኾኑ ሌሎች አርአያ የሆናቸው ሕዝቦች እንደማያከብሩት፤ ምሁራን ነን ባዮቹም ይህንን ለማስከበር አለመጣራቸው ነው! የሚያከብረው ቢበዛ እኮ የእኔም ገቢዬ ይጨምርልኝ ነበር፡፡

የአድዋ ድል ግን አንድ ቀን እኔንም ድል አስደርጎኛል፤ አንድ ፀረ-አድዋ የኾነ ጽሑፍ ‹የአድዋ ድል ለዐፄ ምልሊክ የሕዝቦች መጨቆኛ ኾኗቸዋል› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ይዞ ወጣ፤ እኔም ‹እንደዚህ ለየት ብሎ መውጣቱ ጥሩ ነው፤ የማይስማሙ አሳቦችን በማፋጠጥ ገበያ ያደራል› ብዬ፤ ‹መጨቆኛው የአድዋ ድል› እያልኩ መጮኽ!፤ ጮኸቴን የሰሙ የአድዋ ተቆርቋሪዎች ተሰብስበው በመምጣት የአባቶቻቸውን የድል በዓል አክብረውብኝ፤ የአድዋ ዕለት የነበረ ጣሊያን አድርገውኝ ሄዱ፤ ‹ጣሊያ ገዳይ› ብለው ሳይፎክሩብኝ እንደማይቀርም እገምታለሁ፡፡ መቼም ሰው መስማትና ማንበብ ወይም ማወቅ የሚፈልገው ስሜቱን እንጂ የሐሳቦችን መለያየት አይደለም ብዬ፤ መጽሔቴንም ከሥሬ፣ ድል እንደተመታ ሠራዊት ቁስለቴን ተሸክሜ ለተወሰነ ቀናት ካካባቢው ጠፋሁ፡፡

 ‹የአድዋ ድል ለዐፄ ምኒልክ የመጨቆኛ መሣሪያ ኾኗቸዋል› ያለው ግን ማን እንደኾነ እንጃ! እኔ ያገኘሁት ከመጽሔት ነው፡፡ ምናልባትም ‹ይህን ያለው የጣሊያን እርዝራዥ ሊኾን  ይችላለል ወይም ነጭ መሪው ሳይኾን  በመቅረቱ የተቆጨ ‹ነጬ-ብርቁ› ሰው ሊኾን  ይችላል› የሚሉት ልክ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ ግን ይኸ የኔ ጉዳይ ነው ወይ?

 ከአድዋ ድል ጋር ተያይዞ ደግሞ የምኒልክ ታሪክ አለበት፡፡ ለምሳሌ ‹አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን አንድ ባያደርጓትና በአድዋ ጣሊያንን ድል ባያደርጉ ኖሮ የጥንቷም ኾነች የአሁኗ ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር፤ አፍሪካም ከቅኝ ገዥዎቿ ነፃ መውጣት አትችልም ነበር› የሚል ጽሑፍ በአድዋ በዓል እለት እንደጉድ አሸቅሎኛል፡፡

እንዳው ግን ሰው ኹሉ የንጉሥ አምላኪነት ጠባይ ስላለበት ‹ምኒልክ! ምኒልክ!› ይላል እንጂ ‹የአድዋን ድል ‹የኢትዮጵያ ኩራት› ያደረገው ብዙ ኢትዮጵያውያንና ብሔር ብሔረሰቦች የከፈሉት መስዋዕትነት ነው› ሲባል በቴሌቭዥን ሰምቻለሁ፤ ተመልክቻለሁ፡፡ግን አንድን ድል በመሪው መጥራት ልማድ ነውና አጠራሩ ስህተት አይደለም የሚሉትንም ቢኾን  የሚቃወም ዕውቀት የለኝም፡፡ አረ! እንዳውም፡-

‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፣

ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሀበሻ፡፡›

 እያሉ የሚያወድሱም ሰዎች መኖራቸውን አርጋግጫለሁ፡፡ ስታዘብ ግን ከዕንቁላል አልፎ፣ ከዶሮሞ አልፎ፣ ከከብትም አልፎ፣… የሰው ደም የሚያስገብሩ መከሰታቸውን ወይም መኖራቸውን አልሰሙም መሰለኝ!

ግን እውነት ለመናገር ይች ግጥም በቃል ለመያዝ ቀላል ስለኾነችና ምኒልክን ለሚያወድስ ስለምትስብ ለእኔ ሽቀላ በጣም ጠቅማኝ ነበር፤ በሽቀላ ጊዜ የ‹ፍቅራቸው› አውሊያ ያለበት ሰው ግጥሟን ሰምቶ አያልፍም፤ ቢያንስ አንድ ይወስዳል፡፡

አቤት የኢትዮጵያን ታሪክ ሳስታውስ ብዙ ነው ትዝ የሚለኝ፤ ድሮውንስ የታሪክ ወሬ ብዙ አይደል? በተለይ የኢትዮጵያ ብዛቱ እስከ ጭቅጭቁ ማለቂያ የለውም፡፡ እንዴት ሰው በራሱ ታሪክ መስማማት አቅቶት ይጨቃጨቃል? እንደእኔ ግምት ግን ወይ ተጨቃጫቂዎቹ ወይም መጨቃጨቂያው የተሳሳቱ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከሚያጨቃጭቁ የታሪክ ማሳያዎች መካከል ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ተገዝታለች አልተገዛችም ስለተባለው፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የፊውዳል ጭቆና ስለመኖሩ፣ ዐጼ ምኒልክ ተስፋፊ ነበሩ ወይስ ወራሪ ወይስ ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ እምዬ ስለተባለው፣ ዐጼ ኃ/ሥላሴ ተንኮለኛ ናቸው ወይስ ብልህ መሪ ይባል ስለነበረው፣ ስለ ደርግ መንግሥት አረመኔያዊ አገዛዝና የኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ስሜቱ፣ ስለ ‹ወያኔ› ኢትዮጵያን በዘር መከፋፈልና የብሔሮችን መብት ማስከበር ፣ ከዚያም አልፌ ስለ አክሱም ፣ ስለ ጎንደር፣ ስለላሊበላ… የተጻፉ ጽሑፎች ለሽቀላ ያደረጉት የነበረውን ጠቀሜታ ከጠቀስኩ ‹ጉድ ይህ ኹሉ ታሪክ ነበረ› ነው የምትሉት፡፡

እዚህ ላይ ግን የታሪክ ባለውለታዎቼን ላስታውስ፤ ታሪክን በሚመለከት ለሽቀላዬ አስተዋጽዖ ያደረጉልኝም ምሁራን ናቸው፤ ከተለያየ ሥፍራ መጽሔቱን ለመግዛት ሲመጡ እኔ ጋር ይገናኛሉ፡፡ እዚያም ሲከራከሩ እኔ ጆሮዬን ጣል አድርጌ የመሸቀያ ታሪክ እማራለሁ፡፡ በተማርኩት መሠረትም ሽቀላዬን አጧጡፋለሁ፤ ታሪኩን እነሱ ለወሬ እኔ ለቢዝነስ ተጠቀምንበታል፡፡ የእነሱ ክርክራቸው ሲካረርም የእኔ ገበያዬ ይደራል፤ በዚህ ዓይነት ስልትም ብዙ የታሪክ መጽሔቶችን ሸቅያለሁ፡፡ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ጥሩ ቢዝነስ አሠርቶኛል፤ ሌሎችም ከወሬ ባለፈ ቢያውቁበት ብዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ እኔም የታሪክ ነገር በዚሁ ይብቃኝ እንጂ ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ ታሪክ ረዥም ስለኾነ ስለእሱ ኹሉ አወራለሁ ካልኩኝ ሉሲ ጋር የሚደርስ የዝግመተ ለውጥ ዕድሜ ያስፈልገኛል፤ ምሁራንም ይቀየሙኛል፤ በተለይ ባለመቶ ዓመቶቹ፡- ይህን ያህል ታሪክ መቼ አስተማርንህ ብለው፡፡

…….

Please follow and like us:
error

Leave a Reply