የቅኔና የፍልስፍና ፉክክር ፩

በካሣሁን ዓለሙ

ቅኔና ፍልስፍና ጥንታዊ እና የዓለም ገዥ ዕውቀቶች ናቸው፤ በገዥነታቸውም በፈላስፎች ዘንድ ፉክክርና አታካራ አለባቸው። ስለ የቅኔ ፍልስፍና ስናወራም በቅኔና በፍልስፍና ዕሳቤዎች ውስጥ ያለ ያስተሳሰብ መስተጋብር፣  ክርክር እና ታሪካዊ አታካራ መናገራችን ነው፤ መስተጋብራቸውም አንዱ በሌላው ውስጥ/ላይ በሚያደርጉት አስተዋፅኦና ተፅእኖ ይወሰናል፤ በዚህ ደግሞ በተለያዩ ዕይታዎችና አስተሳሰቦች የተቃኙ ክርክሮች መደረጋቸው አይቀርም፡፡ ምንም እንኳ የቅኔ እና ፍልስፍና የአስተሳሰብ መነሻ መደነቅ ቢኾንም በስልታቸው የተለያዩ ፅንሳተ ሐሳብ ናቸው፤ ቅኔ በሰምና ወርቅ ወይም በኅብርነት ስልት ዕውቀትን ሲመረምር ፍልስፍና በምክንያት (በአመክንዮ) ይመራል፤ በእነዚህ ስልቶች ልዩነት የተነሣም በኹለቱ የዕውቀት አተዋወቅ ዙሪያ አታካራዎች መፈጠራቸው አያጠራጥርም፡፡

የአገራችን የቅኔና የፍልስፍና መስተጋብር በቅኔ የበላይነት ይመራል፤ ቅኔነቱም በሰምና ወርቅ ወይም በኅብርነት ስልት ላይ ያጠነጥናል፤ ኅብርነት ደግሞ ተፈጥሮ የተሠራችበት ጥበብ ስለኾነ ቅኔነት የሌለው ፍጥረት አይኖርም፤ በቅኔነት ሳያመሠጥሩ የሚያስቡት ሐሳብም ተራ ጉዳይ እንጂ ጥልቀት አይኖረውም፤ አስደናቂነቱ አነስተኛ ነውና፤ የማያስደንቅ ነገርም አእምሮን ሰብስቦ አይመስጥም፤ በሐሳብም አምጥቆ አያመራምርም፡፡

የቅኔ መሠረታዊ መነሻውና መድረሻው መደነቅና ማስደነቅ ነው፤ የሚያስደንቀውን በኅብርነቱ፣ በምዕምቅነቱ፣ በለዛዊነቱ፣ በዜማው፣… አማካይነት ነው፡፡ ኅብርነቱም (ሰምና ወርቅነቱ) ሥውሩን በግልጽ፣ አማናዊውን በጥላ/በምሳሌ፣ አንዱን ነገር ከሌላው ጋር በማነጻጸር፣… አንዱን ሐሳብ በሌላው ላይ አሣፍሮ በማጓጓዝ እሩቅ፣ ሥውር፣ ረቂቅና አይታሰቤ የኾኑ አስተሳሰቦችን በማሳየትና በማስገኘት ያመራምራል፡፡ ዕምቅነቱም ብትንና ውስብስብ የኾነውን የተፈጥሮ መስተጋብርና ህላዌ በማዋሐድና አጣጥሞ በማያያዝ የሐሳብ ስብሰባን (ውሕደትን) እና ብተናን (መዘርዘርን) በማቀናበር የአሐድነትን እና የብዙህነትን ተያይዞት ምሥጢር ይፈታል፤ የዚህ መነሻና መዳረሻም መደነቅ፣ መገረም ነው፡- ዕፁብ ውእቱ፡፡

በሌላ በኩል ፍጥረት ኹሉ በእንቅስቀሴና በመለዋወጥ መስተጋብር ውስጥ ይኖራል/ይገኛል፤ የእንቅስቃሴው መስተጋብርም ድምፅና ዜማ አለው፤ ስለኾነም ፍጥረት ኹሉ በዜማ የተቃኘ ህላዌ ያለው ስለኾነ ዜማው ለሰው ልጅ በሚስማማና በሚመስጥ ጥበብ ሲቃኝ በተመስጦ ያስደስታል፤ ይህም የተፈጥሮ ቅኔነት አስደናቂ ምሥጢር ማሳያ ነው፡፡ በኅብርነት፣ በዕምቅነት፣ በዜማ፣… መስተጋብር ውስጥም ውበት አለ፤ በውበት ውስጥ ደግሞ የመልካምነት ቅንብር ይታያል፤ በዚህ ቅንብርም ለዛዊ አመሥጥሮ ይነበባል፡፡ በእነዚህ መስተጋብር የተሠራው ይህ የተፈጥሮ ቅኔነትም የሰው ልጆችን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እየተደነቁ እንዲኖሩ ያደረገ ምሥጢር ነው፡፡

ይህም ተፈጥሮው ቅኔን በአንድ በኩል ከፍልስፍና ጋር ሲያስማማው፣ በሌላ በኩል ግን ተፎካካሪው ኾኖ ንትርክ ውስጥ እንዲገባም ያደርገዋል፡፡ የሚያስማማው ማስደነቁ እና ምሥጢርን በእውነትነት መፈልቀቁ ሲኾን ንትርኩን ደግሞ የኅብርነት ተፈጥረው ይፈጥረዋል፡፡

ፍልስፍና ልክ እንደ ቅኔ መሠረቱ/መነሻው መደነቅ ሲኾን ግቡም የተደነቀበትን ነገር ጠይቆ ማረጋገጥ ነው፤ የጥያቄውን መልስ ለማግኘትም የተጠየቅን ምክንያት ወይም አመክንዮን ይጠቀማል፤ ስለኾነም ዋና ስልቱ ምክንያታዊነት (አመክንዮአዊነት) ነው፡፡ ‹ለምን?› የምክንያታዊነት ማጠንጠኛ ጥያቄ ናት፤ ለዚህ መልስ ‹መሠረታዊ ሎጂክ እና ሕጸጽ› በሚለው መጽሐፌ መግቢያ ላይ ‹የሰው ልጅ አእምሮ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አእምሮውም በምክንያት ይመራል፡፡ የምንኖርበት ዓለምም ምክንያት ዓልባ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡› በሚል አስቀምጬ ነበር፤ ምክንያቱም ዓለምና የሰው ልጅ አእምሮ የሚናበቡት በጋራ ምክንያታዊ ሥሪት ነውፍጥረት በምክንያት ተሠርቷል፤ አእምሮ ደግሞ ይህንን ሥሪት ማንበብና መረዳት የሚያስችል ጥበብ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ፍልስፍና በምክንያት ዘዋሪነት በማጠንጠን ከእውነት እስከ መልካምነት ያለውን የዕውቀት መስተጋብር ለማጥናት አመክንዮን መራሂው አድርጓል፤ ይህ ደግሞ ምሥጢረ ፍጥረትን (Metaphysics)፣ ሥነ ዕውቀትን (Epestimology) እና ሥነ ዕሴትን (Axiology) ያጠቃልላል፡፡

‹የፍልስፍና አተዋወቅ ስልት የሚያጠነጥነው በዚህ መልኩ ከኾነም ከቅኔ ጋር ያለው መስተጋብር ታዲያ የት ነው ያለው?› የሚል ጥያቄ ይነሣል፤ ወይም ‹የምክንያታዊነትን እና የሰምና ወርቅነትን የተለያየ አተያይ ኾነው እያለ እንዴት አስማምተነው ነው ‹የቅኔ ፍልስፍና› የሚል ፅንሰ ሐሳብ የፈጠርነው?› የሚል ጉምቱ ጥያቄ አፍጦ ይመጣብናል፡፡

ፍልስፍና እና ቅኔ ልክ ሕይወት እንዳላቸው ፍጥረታት አድርገን ብንወስዳቸው፤ ፍልስፍናን በእፅዋት ብንመስለው፣ የእንስሳትን ምሳሌ ቅኔ ይወስዳል። እፅዋት በተፈጥሯዊ ሕጋቸው የሚራቡት ባሉበት ኾነው ቋሚ የኾነ ሥርዓታቸውን ጠብቀው ነው፤ እንስሳት ድግሞ ወደዚያ ወደዚህ በመዘዋወር/በመንቀሳቀስ የመኖር ሥርዓት ተስጧቸዋል፤ ኹለቱም ግን ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት በመኾን አንድነት እና ስምምነት አላቸው፤ የአንድኛው ተፈጥሮም በሌላው ውስጥ ይገኛል፤ አንዱ ያለሌላው መኖራቸውም ትርጉም አይሠጥም። ፍልስፍና እና ቅኔም በኅብርነት እና በምክንያታዊይነት ዋና ስልታቸው ባይስማሙና የተለያዩ ቢኾኑም በመደነቅ መሠረት ላይ በመቆማቸው እና እውነትን (ምሥጢርን) ማግኘት (መግለጥ) ዋና ዓላማቸው በማድረጋቸው ግን ይፋቀራሉ፡፡ ቅኔነት በአንድ ነገር ላይ ብቻ አይገተርም፤ ዘወር ዘወርወር እያለ ያማርጣል፤ ያነጻጽራል፤ ሐሳባትን ያፎካክራል፤ ያጣላል፤ ያስማማል፤ እስከቻለው ድረስ ተንቀሰቅሶ የተፈጥሮን ምሥጢር ይፈትሻል… ። ፍልስፍና ደግሞ ሕግጋቱና መርኾቹ ቋሚዎች ናቸው፤ በእነሱ መሠረትም ተፈጥሮን ይመዝናል፤ ከእሷ ጋር የሚስማሙ ሐሳቦችን በመበጠር ይመረምራል፤ ‹ምን›፣ ‹ለምን›፣ ‹እንዴት› በሚሉ የጥያቄ ባትሪዎቹ እየተፈተሸ ከሕግጋቱና ከመርኾቹ ጋር ስምም የኾኑትን ሐሳቦች እያጎለመሰ፣ ያልኾኑትን እየተፋና እያስወገደ የተፈጥሮ ምሥጢር ይመረምራል፡፡ ኹለቱም ቅኔ እና ፍልስፍና የሚመረምሩትም የተፈጥሮን ቅንብር ነው፤ ተፈጥሮ የተቀናበረችው በኅብርነትም በምክንያትም ነውና።

የሰው ልጅ ዕውቀት የሚመሠረተው በተፈጥሮ ቅንብር ላይ ነው፤ የተፈጥሮ ቅንብር ደግሞ የተሠራው በምክንያት ነው ብለናል፤ በምክንያት የተሠራችው ተፈጥሮ (ፍጥረት በሙሉ) ደግሞ ነጠላ ሥሪት ብቻ የላትም፤ ስለዚህ በኅብርነት፣ በዕምቅነት (በአሐድነትና በዝርዝርነት)፣ በለዛ፣ በዜማ… የተሠራች ናት፡፡ በአተዋወቅም የማይታወቀውን ማወቅና መገመት የምንችለው በሚታወቀውና በምንረዳው ነገር አንጻሪነት ነው፤ የዕውቀት መዋቅራዊ መስተጋብር የሚገናኘው በአንጽሮት ነውና፤ የዕምቅነትና የማፍታታት (መዘርዘር) ምክንያታዊ መስተጋብርን በአእምሮ ጂምናስቲክ በማፍታት እና አንዱን በሌላው በማንጸር የቅኔያዊነት ገንዘብ ይኾናል፡፡ ዜማም ቢኾን አግባባዊ የተፈጥሮ መስተጋብርን ካላገኘ አይስብም፤ አይመስጥም፤ ስለዚህ ዜማም እንዲመስጠንና እንዲያስደስተን ምክንያታዊ ጥበብን ይሻል፡፡ ይህ መስተጋብራዊ ማጠንጠኛም የቅኔና የፍልስፍና ስልቶችን በአተያያቸው ለይቶ በተፈጥሯቸው ያገናኛቸዋል፤ ይህንን የቅኔ እና የፍልስፍና መስተጋብርን ማጣጣም ደግሞ ‹የቅኔ ፍልስፍናን› ወይም ‹የፍልስፍና ቅኔን› ይፈጥራል፡፡

እዚህም ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ ያስፈልገናል፤ ‹የቅኔ ፍልስፍና› ስንል ቅኔነትን በፍልስፍና መቃኘት ሲኾን ‹የፍልስፍና ቅኔ› ማለታችን ግን በተቃራኒው ፍልስናን በቅኔ መነጽር መመርመር ይኾናል፤ በኹለቱ መካከል የአተያይ ልዩነት አለ፡፡ የቅኔነትን  ፍልስፍና የምንቃኘውም የተፈጥሮን ኅብራዊ፣ ዕምቃዊ፣ ዜማዊ፣ ምሳሌያዊ፣… ሥሪት ከምክንያታዊ መስተጋብር ጋር በማንጸርና አንዱን በሌላው አሳይነት በመመርመር ይኾናል። በዓለማዊ ኑሯችን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅመን ኑሯችን እንደምናቀለው፣ ጉዟችን/አሠራራችንን እንደምናፈጥነው፣ ድምፅን ከርቀት ጠልፈን እንደምንሰማው፣ ሥውርንና ሩቅን መመልከቻ ተጠቅመን እንደምናየው፣… ይህንን በርቅቀት ደረጃ፣ በመንፈሳዊነትና በግዙፍነት፣ በስፋትና በጥበት፣… በጥቅሉ በተዋሕዶ ተፈጥሮ የተሠራውን የዓለም ምሥጢር የምንመረምረው በቅኔ ይኾናል፡፡

ፍልስፍናን የምንቃኘው በቅኔ መነጽ ከኾነ ደግሞ የፍልስፍናን ድንቀታዊ አመሠራረትና መስተጋብራዊ ሥሪት ከቅኔያዊ ተፈጥሮ አንጻር መመርመር እና ያለውን መስታጋብርና ተቃርኖ ማየትና ማሳየት ይኾናል፡፡ የዕያታ መለያየትና የልዩ ትኩረት ጉዳይ ካልኾነ በስተቀር በኹለቱም በኩል የሚመረመረው የተፈጥሮ ምሥጢራዊነት ነው፤ የሰው ልጅ ያን ጥበብ እንዴት እንደሚያውቅና እንደሚመረምር ነው፤ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ያለውን መስተጋብር ነው፤… ፡፡

ብዙ ሊቃውንት ደግሞ ቅኔና ፍልስፍናን አስማምተውም ይኹን አጣልተው በመመርመር ዘመናትን ፈጅተዋል፤ ወደፊትም ይቀጥላሉ እንጂ አእምሯቸው እስካለ ድረስ ምርምራቸውንና መጠበባቸውን የሚያቆሙ አይመስሉም፡፡ ይሁንና አንዳንዶች ፍልስፍና ላይ ብቻ ሙጭጭ በማለት የቅኔነት ዓይነ ሥውራን ሲኾኑ ሌሎች ደግሞ በቅኔነት እንጠበባለን ብለው ፍልስፍናን ይዘነጋሉ፤ አስታራቂ ሽማግሌ የኾኑትም ፍልስፍና እና ቅኔ መልካም ትዳር ካልመሠረቱ መልካም ጥበብ (ልጅን) አይወልዱም ብለው አሸማግለው በማስታረቅ በኹለቱ ሩካቤ የሚገኘውን ጥበብ/ልጅ ለመሳም እንደጓጉ አሉ፤ በእነሱ ዕይታ ያለኹለቱ መልካም ጋብቻና ሩካቤ ያልተወለደ ጥበብ ወይ ድቃላ ነው ወይም ከተፈጥሮ ውጭ በኾነ ኃይል በታምራዊ ክስተት የተገኘ እንጂ በተፈጥሮ ሥርዓት የተገኘ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ በተቃራኒ ጎራ የሚገኙ ደግሞ በሙግትና በትችት ሲነታረኩ የሚኖሩ ናቸው፤ ባለቅኔዎቹ ፈላስፎቹን ‹ቅኔው ከሌላቸው እንዴት ያመሥጥሩት› (ለምሳሌ የአገራችን ባለቅኔዎች) ብለው ጥበባቸውን ሲያናንቁ፤ ፈላስፎቹ ደግሞ በተቃራኒው ለባለቅኔያዊያኑ ‹ተረታዊያን!› ‹ኢ-ምክንያታዊያን›፣… እያሉ እንዳጣጣሏቸው ዘመናትን ፈጅተዋል፡፡ ብቻ! ንትርካቸው ብዙ ነው፤ ለማስታረቅም ሽማግሌዎቹ አልቻሉም፡፡

በምዕራባዊያን የቅኔ ትርጓሜን ለመወሰንም አስቸጋሪ ነው፤ ለቅኔ የሚሠጡት ትርጓሜም በተረትነት ከመፈረጅ ጀምሮ ልዕለ ፍልስፍና አድርጎ እስከመውሰድ የሚደርስ ሰፊ ውዝግብ አለበት፡፡ በዚህ የተነሣም አንዳንዶቹ ፈላስፎች ቅኔን እንደ ተረት መተረኪያ አድርገው ሲወስዱት (ፕላቶ፣ አውጉስጢን…)፤ ሌሎች ደግሞ በተቀራኒው የጥበባት ኹሉ ጉልላት ያደርጉታል (ቪኮ፣ ካንት፣ ኒቼ፣…)፤ ቅኔና ፍልስፍና ፀበኞች አድርገው ‹በማከሻከሽ› የተከራከሩም አሉ (ፕላቶ)፤ በክርክራቸውም ዐዲስ የዕውቀት መስክ ፈጠርን ብለው ሞግተዋል፡፡ በዚህ የተለያየ ዕይታ እና ፍረጃ የተነሣ የቅኔን እና የፍልስፍናን ግንኙነት ይኸ ነው ብሎ ወስኖ ለመተርጎም ያስቸግራል፡፡

ምዕራባዊያን ሊቃውንት ፍልስፍናን የጥበባት መሠረት አድርገው ይወስዱታል፤ ለፍልስፍና ከሚሰጡት ልዩ ትኩረትና ክብር አንጻርም ‹የትኛውን ያስቀድማሉ ወይም ያስበልጣሉ? ፍልስፍናን ነው ቅኔን?› ብለን ብንጠይቅ በታሪካቸውና በአስተምህሮ አፈራረጃቸው እንደሚታየው በአብዛኛው ‹ለፍልስፍና› እንደሚያሉ አያከራካሪነት የለውም፡፡ የልዩነቱ መሠረትም ፍልስፍና የተፈጥሮ ሥርዓታዊ ተጠየቅ ላይ ሲያተኩር፤ ቅኔ ግን የጥንት ጥበብ ሥነ-ተረታዊ ዕሳቤ ተደርጎ በእነ ፕላቶ ስለተፈረጀ ይመስላል፤ በተለይም ቅኔ በቋንቋ ዘይቤያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮች የሚገለጽ መኾኑና ለኅብራዊነት ተገዥነቱ እንዳልጠራ የነዳጅ ድፍድፍ የተደበተ ዕውቀት አድርጎታል፡፡ አውሮጳውያን ደግሞ የተፈጥሮን ሥርዓታዊ ሥሪት ሲመረምሩ ኅብርነቷን ትተው ተጠየቃዊ ቅንብራ ላይ ብቻ በመቸከላቸው (የትኩረት ማዕከላቸውን የነጠላ ሥርዓታዊ ቅንብር በማድረጋቸው)፤ ቅኔን አሳንሰው ፍልስፍናን አግዝፈው ለመመልከት ተገደዋል ማለት ይቻላል፤ ይህ የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ የተቀረጸበት ልማድ ነው፤ የዓለምም ዕውቀት ፍሰት በዚያ ተቃኝቷል፡፡

ይህን ሐቅ እጓለ ገ/ዮሐንስ ከአገራችን ቅኔ ጋር በማነጻጸር ትዝብቱን ሲገልጽ ቅኔ ወይም ግጥም በፈረንጆች ቀላል ነገር ነው፡፡ ኹሉም የሚረዳው ለተራ ሕዝብ የሚኾን ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት… የፍልስፍና ሕዝባዊ አቀራረብ ግጥም ይባላ› ይለናል (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ 1953፣ ገጽ 71)፡፡ እነዲሁም በምዕራባዊያን የፍልስፍና ትምህርት በላቀ ደረጃ ልዩ ትኩረት የሚሠጠው ዕውቀት ሲኾን ቅኔ ግን የግለሰቦች ሥጦታና ተሰጥኦ ጉዳይ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በዚኽ የተነሣ ከግሪኩ ፈላስፋ ከአርስጣጣሊስ (አርስቶትል) ጀምሮም እስከ 20ኛው መ/ክ/ዘ ድረስ ፍልስፍና በአውሮጳ ነግሦ የሚወልዳቸውንም የሳይንስ ቅርንጫፎች ‹አባታችሁ እኔ መኾኔን እንዳትረሱ› በሚል የተመራማሪዎቻቸውን የደረጃ ከፍታ በእሱ ስም በማሰየም ‹የዚኽ ትምህርት የፍልስፍና ዲግሪ› በማለት አስጠብቆ ኖሯል፡፡ ቅኔ ግን በአርት ጥበብነት የሚገኝ ‹የእነ ደሳለኝ) መዝናኛ ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፡፡

ቅኔ ያለ ፍልስፍና መቀኘት የቃላት ጨዋት የሚፈጥረው ተረትና ቅዠት ነው፤ ፍልስፍናም ያለቅኔ ምሥጢር አልባ ጥበብ ይኾናል፤ አንዱ ያለ ሌላው ሲገለጽ ጥበብነቱ ጎደሎ ይኾናልና የሚል ሙግት ግን እየተንፀባረቁ መምጣታቸውን መታዘብም ይቻላል፡፡ የአገራችን የቅኔና የፍልስፍና መስተጋብር በቅኔ የበላይነት ሲመራ የኖረ ሲኾን በምዕራባዊያን ያለው የኹለቱ ታሪካዊ ግንኙነት ግን የሚመሰክረው የፍልስፍናን መሪነት እና የአታካራ ጡዘት ነው፡፡

የአገራችን የቅኔ ሊቃውንት መሠረታዊ የቅኔ ፍልስፍና እና የምዕራባዊያኑን የአተካራው ጡዘት በየትኞቹ ፈላስፎች ምን ዓይነት ዕይታ እና አስተሳሰብ እንደነበረ በቀጣይ እንመለከታለን፡፡

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply