የቅኔና የፍልስፍና ፉክክር (፭)፡- ቅዱስ አውጉስጢን

በካሣሁን ዓለሙ

መግቢያ

ቅኔ ከፍልስፍና ጋር ባለው ጉንኙት ዙሪያ የምናደርገውን ምርመራ በግሪክ ፈላስፎች ዙሪያ ተሸከርክረን፣ ባለፈው ሣምንት የአርስቶትልን ክርከር ዐይተን ነበር ያቆምነው፤ ለዛሬው ቅዱስ አውጉስጢን (St. Augustine) ዕይታ እንቃኛለን፡፡

ቅ.አውጉስጢን የተወለደውና የተማረው በሰሜን አፍሪቃ ነው፤ የኖረበት ዘመን እ.ኤ.አ ከ354- 430 ዓ.ም ነው፡፡ ክርስቲያን ሳይኾን በፊት በሚላን እና በካርቴጅ አስተማሪ እና የት/ቤቶቹ ቀዳሚ ሊቀመንብር ነበር፤ ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ግን ወደ ሰሜን አፍሪቃ ተመልሶ የመኖኮሳት ማኅበርን መሠረተ፡፡ ከዚያም ክህነት ተቀብሎ በሂጶ ጳጳስ ኾነ፡፡ ቅ. አውጉስጢን በተለየ የሚታወቅበት ሥራው የእግዚአብሔር መናገሻ (The City of God) በሚለው መጽሐፉ ነው፡፡

ሊቁ አውጉስጢን ቀድሞ ባለቅኔ ነበር፤ እንዳውም በቅኔው ተወዳድሮ በማሸነፍ እሰከ መሸለም ደርሶ እነደነበር ይነገራል፤ ኋላ ግን ክርስቲያን ሲኾን ያ ኹሉ መውደስ ለባድዕድ አምልኮ የሚቀርብ መኾኑን ተረዳ፡፡ ስለዚህ ቅኔን ገሸሽ በማድረግ ወደ ማራከስ ዞረ፤ ፍልስፍናንም የክርስትና ሃይማኖት ገረድ አድርጎ በመቅጠር፣ የፕሌቶ የቅኔና የፍልስፍና ንትርክ ቀይሮ በቅኔና በሃይማኖት መካከል የሚደረግ ‹የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ›  ፉክክር አድርጎ ሞገተ፡፡

NT; (c) Kingston Lacy; Supplied by The Public Catalogue Foundation

በአውጉስጢን ላይ ተፅእኖ ያሳደሩ ሦስት ሰዎች አሉ፡- ፕሌቶ፣ ፕሎጢኑስ (Plotinus) እና ማርቆስ ቫሮ (Marcus Varro) ናቸው፡፡ ፕሌቶ ቅኔን በቅጅ ቅጅነትና በተረትነት በመፈረጁ ‹አደገኛ› የሚል ‹ታፔላ› ለጥፎቦታል፤ አውጉስጢንም እንደ ፕሌቶ ቀድሞ የባዕድ አምልኮን አወዳሽ ባለቅኔ ስለነበር፤ ክርስቲያን ከኾነ በኋላ ቅኔን በማንከዋሰስ ከፕሌቶ ጋር ተስማማ፤ በዚህ የተነሣም የፕሌቶ አወዳሽ ለመኾን በቃ፡፡ የThe City of God የሚለው መጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍልም ለፕሌቶ ውደሳ ያሽጎደጎደበት ነው፡፡ አውጉስጢን ለፕሌቶ ውዳሴው በማሽጎድጎድ የቸረው ቅኔን በቅጅ ቅጅነትና በተረትነት አወራርዶ ስላቃለለ እና በአደጋነት ስለፈረጀ ነው፡፡

ሌላው የፕሌቶ አስተምህሮ ፕላቶናዊያንን አስገኝቷል፤ አውጉስጢን ወደ ክርስትና ሲቀየር ስብዕናውንና አስተሳሰቡን የቀየሩትና ተጽዕኖ ያደረጉበት እነዚህ ፕላቶኒያውያን ሲኾኑ በተለይ ፕሎጢኑስ እና ቫሮ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሐሳቢያን ተፅእኖም በአውጉስጢን የፈጠራና የአስተውሎት ችሎታ እየተሸከረከረ ወደ የቅኔ እና የሃይማኖት ፉክክር አድርሶታል፡፡

የፕሎጢኑስ ተፅእኖ

አውጉስጢን መጀመሪያ ከክርስትና ጋር ሲገናኝ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ቃልም እግዚአብሔር ነው› የሚለው የዮሐንስ ወንጌል ጥቅስ በፕሎጢኑስ እና በደቀመዙሙሩ ፖርፊሪ (Porphyry) እየተተረጎመ ተብራርቶ አገኘው፡፡ ቃል ደግሞ በፅርዕ (በግሪክ) ሎጎስ ስለሚባል የቃልም ትርጉም አመክንዮ (ምክንያተ ነገር) ማለት መኾኑ ተረዳ፤ የምክንያት ትስስርም ከቅኔ የበለጠ ከሰማያዊ ፍልስፍና ጋር እንደኾነ በማየትም በምክንያት ለምትመራው ፍልስፍና የበለጠ ክብር ሰጠ፡፡

ፕሎጢኑስ የፈላስፎችና የባለቅኔዎች ሥራ በከፍተኛው የማሰላሰል ደረጃ ላይ ሊገናኝ (ሊገጣጠም) ይችላል ይላል፤ ልዩነቱን የሚፈጥረው ማሰላሰልን በዕውቀት (በሥልጠና) የመደገፍ ኹኔታ ስለኾነ ለባለቅኔዎች፣ ለሙዚቀኞችና ለሌሎች የአርት ሰዎች ፊት ለፊት ከሚታየው ክስተት ባለፈ ያለውን መስተጋበር እንዲያስተውሉ፤ እዚያ ማዶ (ከአካባቢያቸው ባለፈ) ያለውን ራዕይ እንዲይዙ ይመክራል፡፡

ስለ ተረት በጥልቅ አስተውሎቱ ፕሌቶን ራሱ ‹የተረት ጸሐፊ ነው› ብሎ ይሞግታል፡- ፕሎጢኑስ፤ ይህ የፕሌቶ ተረትም በማስደነቅ ምሥጢር ይዞ የየትኛውንም አስተሳሰብ ጥልቀትና ስፋት ለመመርመር መነሻ ይኾናል፤ ይህንንም ማወቅና መረዳት የምንችለው ዘይቤያዊ ስልቶችን (በማመሳሰል፣ በማነጻጸር፣ በመወከል፣…) በመጠቀም መኾኑን ሞግቷል፡፡

ፍልስፍናዊ አሰላስሎትም ባለቅኔውን የቅኔን የተፈጥሮ ገላጭነት እና ተፈጥሮ የምትፈልገውን መያዝ እንዳለበት እንዲገነዘብ ያደርገዋል ይለናል፡፡ ስለዚህ  ቅኔ (አርት) እንደ ፕሌቶ ተፈጥሮን አስመስሎ መቅዳት ብቻ ሳይኾን ከተፈጥሮ ምንጭ ፈልቆ መፍሰስም በመኾኑ ቅኔ ራሱ የህልው (እውን) ነገር ተፈጥሮን መረዳት እስከቻልነው ድረስ መግለጫና መመርመሪያ ጥበብ መኾኑን ሞግቷል፡፡ በሙግቱም ተፈጥሮ በከፍተኛው ደረጃ እውን ነገርን እንድንረዳ የምታደርገው ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ጠብቃ እንደኾነው፤ የአርትን (የቅኔን) ምንነትም በተመሳሳይ መልኩ መረዳት ይገባናል ይላል፡፡

ለፕሎጢኑስ  እውነት በቁስአካል፣ በነፍስ፣ በአእምሮ እና በአሐድነት ላይ ያርፋል፤ በዚህም የምትገኝ እውነትም ከመልካምነት ጋር የተዋሐደች ናት፡፡ አሐድነት የኹሉም ምንነት መሠረት ነው፤ አእምሮ ደግሞ የመኾን ኑባሬ እውንነት ነው፡፡ ነፍስም በኹለት ትከፈላለች፡- የዓለም (የኹሉም) ነፍስ  እና የግለሰቦች (ዝርዝር) ነፍስ በሚል፤ እሷም የአካላችን (የሥጋችን) አንቀሳቀሽ ኃይል ናት፤ አካላችን ደግሞ የቁስ አካል ሥሪት ነው፤ ቁስአካልም ከኹሉም ሥር የሚገኝ ያዥ (ንጣፍ) ነው በማለት ይተነትናል፡፡

በዚያም ላይ ‹እሺ የሕይወት ከፍታው ምንድን ነው?› ብሎ ይጠይቅና  መልሱን ‹አእምሮ› በማለት ይሰጣል፤ አእምሮ እኛን ወደፊት የሚገፋፋንን (የሚያንቀሳቅሰንን) የሰዎችን ነፍስ ጠባያት እና የእግዚአብሔርን ሕሊና ጠባያት አዋሕዶ መያዙን ይሞግታል፤ ስለኾነም በከፍተኛ ሕይወት የሚገኝ ትልቁ ሥጦታ የሶቅራጥስ እሰጥ አገባ ነው ይለናል፡፡ በዚህ ሥጦታ ነፍስ ኹሉንም ነገር ትመረምራለች፣ ሕሊናም ከአድማሱ ወዲያ ያለውን ኑባሬ ሳይቀር ጠልቆ ያያል፤ ከኹሉም ግን ምርጡ የፍልስፍና ክፍል የእሰጥ አገባ ስልት ነው ይለናል፡- ፕሎጢኑስ፡፡

‹እንዴት ግን በዚህ መልክ ጥልቅ የኾነውን የከፍታ ዕውቀት ገንዘብ ማድረግ ይቻላል?› ሲባል፤ መልሱ በዘይቤ ወይም በምሳሌ ስልት አእምሯችን እየተምዘገዘገ የምሥጢረ ፍጥረትን እና የግብረገብን ከፍታን መጥቆና ሰርጎ በመግባት የኑባሬ ምሥጢር፣ የጥልቀት መዳረሻ፣ የንፅሕና ጥግ፣ የኹሉም ነገር መሠረት፣… የኾነውን ነገር መመርመር/መፈተሽ ይችላል ይለናል፡፡

ደረጃ አውጥቶ ሲያስቀምጥም የከፍታውን ጫፍ መልካምነት አድርጎ ዝቃጩን ሥፍራ ደግሞ ቁስ አካል ያደርገዋል፤ መልካምነት ከመጠበብም የሚበልጥና የኹሉም ነገር ከፍታ ነው ይላል፡፡ የፍልስፍና እና የቅኔ መደነቅም ከቁስ አካል ጋር ተያይዞ ከሚገኝ ውበት ጋር ከኾነ ይጠፋል፤ በመልካምነት ተውህቦ ከኾነ ግን ይዘልቃል የሚል ክርክር ነበረው፡- ከታች ወደ መልካምነት ጫፍ ሲያወጣ፡፡ ስለኾነም ቅኔ ከተውህቦ፣ ከዜማና ከጥበብ ንድፍ ይጀምራል፤ ይኽም ቅኔ ከዝቅተኛው ወደ ከፍተኛው ዕይታ መምጠቅ እንዳለበት ይከራከራል፡፡ በአጠቃላይ ግን የፕሎጢኑስ ትልቁ ተፅእኖው አውጉስጢን ወደ ክርስትና እንዲመለስ እና ፍልስፍናን የሃይማኖት ገረድ ለማድረግ ማስቻሉ ነው፡፡

ማርቆስ ቫሮ

የፕሌቶ ተፅእኖ ብቻ ሳይኾን ቫሮም ያደረገው የአማልክት ምደባም ለአውጉስጢን ትልቅ ግብዓት ኾኖታል፡፡ ቫሮ የሚታወቀው አማልክትን በየግብራቸው መሠረት በመከፋፈል ነው፤ በዚህም 20 (12 ወንዶች እና 8 ሴቶች) አማልክትን ለይቶ አቅርቧል፡፡ እነዚህን አማልክትም በሦስት ምደባዎች ጠቅልሎ አስቀምጧቸዋል፡- የሥነ-ተረት፣ የሲቪል እና ከተፈጥሮ አማልክት በሚል፡፡ የሥነ ተረት አማልክት ከባለቅኔዎች ሥራ ጋር ሲያያዙ፣ የሲቪል ደግሞ ከከተማ ሕዝብ ተግባራት ጋር የተያያዙ ናቸው፤ በሰው ሠራሽ ድሪጊቶች (ለምሳሌ በትያትር) ይገለጻሉ፤ የተፈጥሮ አማልክት ደግሞ ከፈላስፎች ተግባራት ጋር የተቆራኙ ሲኾኑ በተፈጥሮ ጠባይ የሚገለጹ ናቸው በሚል ተከራክሯል፡፡

የሰው ሠራሽ ነገሮች የሚገለጹት በአርት ሥራ ሲኾን ከእውነት በጣም የራቁ ወይም ሐሰተኞች ናቸው፤ ቀጥታ ከተፈጥሮ ጋር የሚገናኙት ግን ለእውነትነት በጣም የቀረቡ ናቸው ይላል፡፡ ሰው ደግሞ ከሐሰት ይልቅ እውነትን መምረጥ ስላለበት የተፈጥሮን ጥበብ የሚያጠናው ፍልስፍና ከቅኔ የበለጠ ክብር ሊሠጠው ይገባል ይለናል፤ ስለዚህ በተረትነት ከተፈረጀው ከቅኔ ይልቅ ከተፈጥሮ የሚቀዳው ፍልስፍና የተሻለ እውነት ያለው ነው፡- ለአውጉስጢን፡፡

ኾኖም አውጉስጢን ቅኔ ስለ አማልክት ተረት በጥልቀት የሚያወራ የሐሳብ ቤት በመኾኑ ይስማማል፤ ግን ደግሞ ሐሰተኛ አማልክትን እንጂ እውነተኛ አምላክን አይገልጽም ባይ ነው፡፡ የዚህን ምክንያት አውጉስጢን ሲገልጽ ቅኔ የሚያቀነቅነው የምድራዊ እና ሰው ሠራሽ አማልክትን ተግባራት ስለኾነ እና ባለቅኔዎች የሚቀኙት በጋኔን መንፈስ እየተመሩ ስለኾነ ከእውነተኛው አምላክ ጋር አይገናኙም፡፡ ለአውጉስጢን በተፈጥሮ አማልክት ጋር ሲለሚገናኝ ፍልስፍና ለእውነት ከሌሎች የበለጠ ቅርብ ነው፤ አንዱን አምላክ ከሌላው ለመለየትም ትልቅ ሚና ይጫወታል፤ ምድራዊ አማልክቱ ግን እርስ በራሳቸው ስለማይስማሙ ምድራዊ ፍልስፍና እውነተኛውን አምላክ ለማወቅ አያስችልም፤ ትክክለኛው አምላክ የመጨረሻው እውነት መኾን አለበት፤ ይህም የተገለጸው በክርስትና ሃይማኖት ነው ይላል፤ ለእሱ ክርሰቲያን የሰማያዊት ከተማ ባለርስት ነው፡፡

የምድራዊ ከተማ ለሐሰተኛ አማልክት ሲያገለግል ሰማያዊ ከተማ ደግሞ የእውነተኛው አምላክ መገለጫ ነው፤ ሐሰተኛ አምላክ በባለቅኔዎች ሲገለጽ እውነተኛው ደግሞ በነበያት ይገለጻል፡፡ የምድራዊ ፈላስፎች ለባለቅኔዎች ምላሽ ሲሰጡ የክርስትና ፈላስፎች ደግሞ ለነበያት ትንቢት መልስ ይሰጣሉ፤ የምድራዊ ከተማ ፍልስፍናንም ይገነዘባሉ፤ ምክንያቱም እውነተኛው እግዚአብሔር የሚናገረው በነቢያት ነውና ብሎ ሞገረቷል፡፡ እውነተኛው አምላክም ኹሉንም ነገር የሠራ፣ የእውነት ገላጭ እና ደስተናን ሰጪ (አዳይ) ስለኾነ ‹እውነተኛ ፈላስፋ የእግዚአብሔር አፍቃሪ ነው› የሚል ክርክር አቅርቧል፡፡ ኾኖም እውነተኛው አምላክም ለዓለሙ የተገለጸው በፈላስፎች፣ በባለቅኔዎች ወይም በሲቪል ሰዎች ሳይኾን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡

አጠቃላይ

ለአውጉስጢን ታላቅ ክብር ያለው ጥበብ ሃይማኖት ነው፤ የዕውቀቶች ኹሉ መዳረሻ ለሃይማኖት ማገልገል መቻል ነው፤ ፍልስፍና ከተፈጥሮ ጋር የተናበበችና በምክንያት የምትመራ ስለኾነች ለክርስትና ሃይማኖት መልካም አገልጋይ መኾን ትችላለች፡፡ የሥነ ተረት ሥነ መለኮት ግን የባለቅኔዎች የባዕድ አምልኮ ማቀንቀኛ ስለኾነ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር አይስማማም፤ ይህም የቅኔን ፉክክር እንደ ፕሌቶ ከፍልስፋ ጋር ሳይኾን ከሃይማኖት ጋር በማድረግ የክርክሩን ዓይነት ቀይሮታል፡፡ አውጉስጢን በዚህ በሥነ-ተረት አስተሳሰቡ በተለይ ከአርስቶትል ጋር አይስማማም፤ ምክንያቱም አርስቶትል ቅኔን በተረትነት አይነቅፍም፤ የተረትን አስፈላጊነትም ይሞግታል፡፡ በአጠቃላይ ግን አውጉስጢን ቅኔን ለጣኦት መውደስ የምታወረድ፣ ፍልስፍናም የሃይማኖት ገረድ አድርጎ ተከራክሯል፡፡

ፍልስፍናም የሥነ መለኮት ዕውቀት አገልጋይ በመሆኗ፣ ቅኔን ከፍልስፍና መለየት/አለመየቱ ዋና ጉዳይ መኾን የለበትም፤ ይልቁንስ ቅኔ የሥነ ተረት መተረኪያ ስለኾነ በውስጡ ያለው የቋንቋ ስህተት ብቻ ሳይኾን የጋኔን (የሠይጣን) መነጋገሪያ ቋንቋ መሆኑም ዋናው ችግር ነው፤ ይኽም ማለት ቅኔ የሥነ ተረት እምነት (አማልክት) መተረኪያ ነው፡፡

 እሱ እንዳለው ከኾነ፡-

የተፈጥሮ ፈላስፎች ሕዝብን ለመጥቀም ይጽፋሉ፤ ባለ ቅኔዎች ደግሞ ሕዝቡን ለማስደሰት ይቀኛሉ፤ ስለዚኽ የባለቅኔዎቹ ትረካዎች ሕዝቦቹና አማልክቱ የሚደሰቱባቸው የእግዚአብሔር ወገን የኾኑ ሰዎች ሊከተሏቸው የማይገቡ የአማልክቱ ወንጀሎች መኾን አለባቸው፡፡ ስለዚኽ ባለቅኔዎች ከማስደሰት ያለፈ ጥቅም የላቸውም፤ የአማልክቱን ትክክልነት ለመተረትና ለሕዝቡ ክብር ለማስገኘት ይጽፋሉና፡፡

በመኾኑም ለአውጉስጢን ቅኔ መጻፍ እጅግ ዝቅተኛ ጠቀሜታ ሲኖረው፣ ለሃይማኖት የሚጠቅም ፍልስፍና መጻፍ ደግሞ በተቀራኒው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ ምክንያቱም ፍልስፍና የሥነ መለኮት ዕውቀት መገልገያ በመኾን ከፍተኛ አገልግሎት ይሠጣልና፤ ቅኔን ግን የአምልኮተ ጣዖት (የባዕድ አምልኮ) ማቀንቀኛ የተረት አካል በማድረግ ይደመድማል፡፡ በመሆኑም ለአውጉስጢን በቅኔ እና በፍልስፍና መካከል ያለው አለመጣጣም ከፍተኛ ነው፤ በተለይም ፍልስፍና የሃይማኖት አገልጋይ በመኾኗ ፉክክሩን በቅኔና በሃይማኖት መካከል አድርጎ ያጦዘዋል፤ ከእነ ፕሌቶ የሚለየውም የፍልስፍናን ለሥነ መለኮት መመርመሪያ መኾን በማግዘፍ ወይም ለሃይማኖት ከኹሉም የበለጠ ቦታ በማቀዳጀት ነው፡፡

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply