የቅኔ ዘፍልሱፍ መጽሐፍ መግቢያ

 ፍልስፍና ከትምህርቶች ኹሉ ተወዳጁ ዕውቀት ነው፤ ተወዳጅ ሊኾን የቻለውም የተፈጥሮ (ፍጥረታት)፣ የሰውየእግዚአብሔር ቅኔያዊ መስተጋር ስለሚመረመርበት ነው፡፡ ማለትም የተፈጥሮ ምንነትና መስተጋብር፣ የሰው ልጆች የዕውቀት፣ የባህል፣ የግብረገብነት፣ የአስተዳደር አመሠራረት፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ህላዌና ከፍጥረቱ ጋር ያለው መስተጋብር እየተጠየቀ ስለሚመረመርበት፣ የሳይንስ ዘርፍ ዕውቀቶችም መሠረትና ጥልቀት መዳረሻ ተደርጎ ስለሚወሰድ፣ መሠረታዊ ጥያቄዎቹም ዘመን የማይሽራቸው በመኾን መልሳቸውን ለማግኘት የብዙዎችን ሊቃውንት የአእምሮ ምጥቀት ፈትነው በተግባር ያልተመለሱ ስለኾነ፤ በሌላ በኩል የሰው ልጆች ደግሞ በተፈጥሯቸው የዐዋቂነት ከፍታ አድናቂዎች በመኾናቸው፣ ይኽንን ምጥቀት እየጠየቀ የሚያጠናው ፍልስፍና ዋና ተወዳጅ ዕውቀታቸው ኾኖ ይኖራል፡፡

 IMG_20171028_185337

ፍልስፍና ተዋዳጅ ዕውቀት ቢኾንም በማኅበረሰብ ዕይታ መለያየት፣ በልማድ መዳበር፣ በአካባቢያዊ ተጽዕኖና በዘመኑ የሥልጣኔ ደረጃ የተነሣ የተለያየ ደረጃና ዓይነት ይኖረዋል፡- በአንዳንድ ማኅበረሰብ በዘልማድ አኗኗር ብቻ ሲንፀባረቅ፣ በአንዳንዶቹ ዘንድ ግን የዕውቀት ደረጃ መለኪያና መዳረሻ የኾነ ክብር ያገኛል፡፡ ደረጃውን የማኅበረሰቡ የሥልጣኔ አመጣጥ (የታሪክ አመዘጋገብ፣ የተመዘገበ የዕውቀት ክምችት መኖርና የቅብብሎሽ ትስስር)፣ የአስተውሎት ዳራ እና የሐሳብ አደረጃጀት ይዘት ይወስነዋል፡፡ አካባቢያዊ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞም የጠቀስነው የሥልጣኔ አመጣጥ መያያዝ፣ የተመዘገበ ታሪክ ያለበት አካባቢ መኾን፣ እንዲሁም ከሌሎች ጋር የሚደረግ የግንኙነት መስተጋብር፣ ይኽንን ወርሶና አበልጽጎ የሚገኝበት አካባቢ የመገኘት ኹኔታ፣… ዕውቀታዊ አደረጃጀቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ በተቃራኒው ከተባሉት ነገሮች መራቅና የዕውቀቱ ከቀደሙት ትውልዶች ጋር አለመያያዝ አሉታዊ ተጽዕኖውን ያጎላዋል፡- ማኅበረሰቡንም ዘልማዳዊ ዕውቀት ይቆጣጠረዋል፡፡

ኾኖም ዕውቀት በተፈጥሮው ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው አካባቢ እየተሠራጨ በመሔድ ይሻሻላል፤ ዕውቀትን በአንድ አካባቢ ብቻ ወስኖ ሊያስቀረው የሚችል ነገር ስለማይኖርም የዕይታ አንጻሩን (አንግሉን) እየቀያየረና ከዘልማድ ጋር እየተዋሐደ ይበለጽጋል፡፡ ስለኾነም ነው የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ በግብፅ፣ በሜሶጶጣሚያ፣ በሕንድና በላቲን አሜሪካ (በማያ፣ በአዜቲክስና በኢንካ) ተሠራጭቶ የበለጸገው፡፡ በተለይ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን በጥንታዊያን ግብፆች ላይ ያሳደሩት የዕውቀት ተፅዕኖ እንደ አምላክ እንዲታዩ ጭምር አድርጓቸው ነበር፤ ከዚያም የግብፆቹ የዕውቀት ሀብት ለግሮኮች ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጉ የማይታበል እውነት ነው፤ የግሪኮች የዕውቀት ክምችት ደግሞ በሮማውያን ተወርሷል፤ ከዚያም አረቦችና አውሮጳውያን እያበለፀጉ ተቀባብለው ለዓለም በትነውታል፤ በተለይ አውሮጳውያን በቴክኖሎጂ ፈጠራ በመታገዝ የዕውቀት ክምችታቸውን በምክንያት እያበጠሩ፣ በጥቅመኝነትና በቁሳዊነት መራህያን ወስነው ዓለምን በእነሱ ይትባህል መርተውታል፤ እየመሩትም ይገኛል፡፡ በዚኽ ዓይነት የዕውቀት ፍሰትና ሥርጭት ነው ሥልጣኔ በዓለማችን የተስፋፋው፤ ዕውቀትም በተለያየ ደረጃ የበለፀገው፤ ፍልስፍናም የኋላ ደጀንና ዋና አዛዥ ጣቢያ በመኾን እስከዛሬ የኖረው፡፡

ምንም እንኳ አገራችን ኢትዮጵያ መሬቷ ብቻ ሳይኾን የዕውቀት ክምችቷም ከቀጥታ ቅኝ ግዛት የተጠበቀ ቢመስልም ለእኛ የደረሰን የሀገራችን የዕውቀት አደረጃጀት ከጠቀስነው የመወራረስ መስተጋብራዊ መሠረተ-አሚን (Principle) የሚለይ አይደለም፡- ገና ከጥንቱ ሌሎች ከእኛ ሲወስዱ፣ እኛም ከሌሎችም የወረስናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከተከማቸው የአገራችን ዕውቀትም እየተዳፈነ ሳይደርሰን የቀረም ያለ ይመስለኛል፤ በተለይ ምሥጢራዊ ጥበባትን በሚመለከት መሬት ውስጥ ተቀብረው የቀሩ ብዙ ጥበባት ሊኖሩን እንደሚችሉ ይታመናል፤ እኔም እንደዚያ ይሰማኛል፡፡ ቢኾንም የሀገራችን ፍልስፍናም ከጥንት ሥልጣኔያችን ጋር ተያይዞ ከሌሎች የዕውቀት አደረጃጀቶች ጋር እየተገናዘበና እየተዋዋሰ፣ እንዲሁም እየተቃረነ የበለፀገም፣ አንዳንዴም እየኮሰሰ ከዘመናችን የደረሰ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ጥንታዊ ይዘቱን ሳይለቅ፣ ከሌሎች ያገኛቸውን የሃይማኖት፣ የግብረገብና የንጽሮተ ዓለም ዕሴቶች እያዋሐደ ያለንበት ዘመን መድረስ ችሏል፤ በሌላ በኩል በጦርነትና በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ የድርቅና የበሽታ ተግዳሮቶች (ችግሮች) የተነሣ የዕውቀት ክምችቱና አደረጃጀቱ እየተሸረሸረ፣ ሊቃውንቱ ያለተተኪ ሲያልፉ ዕውቀታቸው በዘልማድ እየተተካ ለመሔድ የተገደደም ይመስለላል፤ ኾኖም መሠረታዊ አስተምህሮው ግን እንደተዳፈነ እሳት ሳይጠፋም ሳይለማም ከዘመኑ ጋር እየተናበበ ያለንበት ዘመን ደርሷል፡- የዜማና የአንድምታ ትርጓሜ ስልቶች መሻሻል እንደተጠበቀ ኾኖ፡፡

ይኽ ተቋርኗዊ አመጣጡ (የጠፋው ጠፍቶ፣ የለማው ለምቶ፣ የተወረሰውም ከነበረው ጋር ተስማምቶ) እንደተጠበቀ ኾኖ ግን አስተምህሮው መሠረታዊ ይትበሃሉን ጠብቆ ከዘመናችን ለመድረስ ችሏል፡፡ በዚኽ ላይም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ያበረከተችው አስተዋፅዖ ወደር የለውም፤ ለምሳሌም የቅኔ ፍልስፍና ጥንታዊ ይትበሃሉን እንደጠበቀ፣ የፊደልና የሰዋሰው ሥርዓቶችም ሥነ-ፍጥረታዊ ተፈጥራቸውን ሳይለቁ አመክንዮአዊ ስልታቸውን ጠብቀው ለእኛ እንዲደርሱን የማድረጓ ውለታ እጅግ ላቅ ያለ ነው (የእኛ የወራሾቹ ችግር እንዳለ ኾኖ)፤ ለእኛ መድረሳቸው ብቻ ሳይኾን ልብ ብሎ ላስተዋላቸው የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ ምጥቀት የሚመሰክሩ ጥበባት ናቸው፡፡ ይኽንን ያስተዋለው እጓለ ገብረ ዮሐንስ ትዝብቱን ‹ሳያደንቁ ለማለፍ አይቻልም› በማለት ጀምሮ ‹ኢትዮጵያውያን በክርስትና ክንፍ ላይ ኾነው አየር አየራት ወጥተው እመቀ እመቃት ወርደው የነገሮችን ባሕርይ ለመመርመርና ለመረዳት የሕሊና ጥረት አድርገው ከብዙ የሐሳብ ትክክለኝነትና ጽርየት ደርሰዋል፡፡[1] ብሎ ገልጾታል፡፡

በተለይ የቅኔ ጥበብ በዓለም አቀፍ ደረጃም የኹሉም ጥበባት ቀዳሚ መኾኑ እንደተጠበቀ ኾኖ በኢትዮጵያ ደግሞ ጥንታዊነቱ ብቻ ሳይኾን መሠረታዊነቱም የተጠበቀ ጥበብ ኾኖ ይገኛል፡- የፍልስፍናው ይትበሃል ገና በአግባቡ ያልታየና ያልተመረመረ ቢኾንም:: የኹሉም ጥበባት መሠረት የኾነ ልዩ ዕውቀት በመኾኑ የቅኔ ጥበብ ለኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ስውር መግለጫ፣ ውስብስብ መፍቻ፣ ጥልቅ ሐሳብን ሰርስሮ ማውጫ፣ የተሻለውን ሐሳብ ማማረጫ፣ ንጥር ሐሳብን ማረጋገጫ፣… በመኾኑ ሰፊውንና ውስብስቡን አእምሮ ለምሥጢር በማስገዛት የተፈጥሮን ኅብርነት፣ ዕምቅነትና ለዛዊነት መፍቻ ጥበባቸው ነው፡፡ ስለኾነም የፍልስፍናን ዕውቀት ምጡቅነትና መሠረታዊነት ከኢትዮጵያዊ ዕይታ አንጻር በመቃኘት ስንመረምረው ከቅኔ ጋር የተቆራኘ ኾኖ ይገኛል፡፡ ስለኾነም ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ሊቃውንት ንጽሮተ ዓለም አንጻር ሲቃኝ ቅኔያዊ ተፈጥሮን ገንዘብ  ስላደረገ ፍልስፍና ራሱ በቅኔ መቃኘቱን ይነግረናል፡፡

በመሠረቱ ፍልስፍናም በተፈጥረው ከቅኔነት የተለየ ጥበብ አይደለም፡፡ የፍልስፍና መራሂው የተፈጥሮን ቅኔነት መመርመር ነው፡- የቅኔነት ምሥጢር በተፈጥሮ ውስጥ በኅብርነት፣ በምቅነት፣ በዜማ፣ በሰሐቢነት፣… ተጽፎ ይገኛልና፤ መፈላሰፍ ማለትም ይኽን የተጻፈውን ቅኔ አንብቦ መፍታትና ምጢራዊ ጥበቡን አውጥቶ (ገልጾ) ማሳየት ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ የተሠራችው በእውነት መሠረት፣ በዕውቀት ሥርዓትና በመልካምነት ተውህቦ ስለኾነ፤ እኔም የፍልስፍናን ቅኔነት ለማሳየት በፍልስፍና ሥርወ-ቃላዊ ትርጉም ላይ ተመሥርቼ ‹ጥበብ የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ› መኾኗን በማሳየት፣ ቅኔዊ ተዋሕዶዋ የፍልስፍናን ፍቅር መኾኑን/ ማስገኘቱን ለመሞገት ጥሬያለሁ፡፡

እውነት፣ ዕውቀትና መልካምነት ደግሞ መሠረታዊ የፍልስፍና ማጠንጠኛዎች በመኾናቸው የእውነትን ቅኔነት ፈቶ ማሳየት፣ የዕውቀትን ጥልቀትና ምጥቀት ማስረዳት እና የመልካምነትን ዋጋ እና መስህብ መግለፅ፣ በተለይም የሦስቱን መስተጋብር መፈልቀቅና ምሥጢራቸውን መፍታት አእምሮን ይፈትናል፡፡ ይሁንና ሰው እንደቻለው ስለኾነ የቅኔነቱን ዳራ ለማሳየት የአቅሜን ሞክሬያለሁ፡፡

የመጽሐፉ ዋና ዓላማም የፍልስፍናን ቅኔነት በመሞገት ኢትዮጵያዊ ይትበሀል አላብሶ ለማሳየት ሰለኾነ በዕይታው፣ በይዘቱና በስልቱ ከተለመደው ይለያል የሚል እምነት አለኝ (ለራስ ሲቆርሱ)፡፡ ይለያል ስል ምን ማለቴ እንደኾነ የመጽሐፉን ይዘት በመግለጽ የዐስተሳሰቡን ሥዕል ላሳይ፡፡

መጽሐፉ በአጠቃላይ አራት ምዕራች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ምእራፍ የፍልስፍናን ምንነት ለመመርመር ይሞክራል፤ በዚኽም ‘ፈላስፋ ማን ነው?’ የሚል ሙግት በማቅረብ ጀምሮ የፍልስፍናን ፍቅረ ጥበብነት በመተንተን ስለ ቅኔነቷ የክርክር መሠረት ይጥላል፤ ጥበብ ቤቷን በሰባት አዕማዳት አቁማ በእውነት ዓለትነት፣ በዕውቀት ግድግዳና ማገርነት እንዳቆመች እና በመልካምነት ተውህቦ እንደተሠራች ይቃኛል፤ የጥበብ ጥልቀቷና ምጥቀቷም እስከ እግዚአብሔር አንድነት ሦሰትነት፣ እስከ ክርስቶስ ሰው ኾኖ መገለጽ እንደሚደርስም ይሞግታል፡፡

ምዕራፍ ኹለት ከጥበብ ይዘቶች መካከል መሠረት የኾነችውን የእውነትን ምንነት ይተነትናል፤ ከፍጽምናዋ እስከ ተነጻጻሪነቷ ያለውን የእውነት ቅኔነት ምሥጢር በመፍታት እና ከምንነቷ እስከ ዋጋዋ ያለውን ዕንቆቅልሽ በመቃኘት ይሞግታል፡፡ ለጠጥ በማድረግም የምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) እና የምሥጢረ ፍጥረትን (Metaphysics) ጥያቄዎች ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አስተምህሮ አንጻር በመጠኑ ለመመልከት ይሞክራል፡፡

ቀጥሎ በምዕራፍ ሦስት የሥነ-ዕውቀት (Epistemology) ምንነት፣ ስፋትና ምንጭ ሙግቶች ተዳሰዋል፡፡ በዚኽም የዕውቀት ምንነት ከእውነት፣ ከእምነትና ከአመክንዮ (ምክንያት) ሥሪቶቹ ተመሥርቶ ተተንትኗል፤ በዚያ ላይ በመመሥረትም የፍልስፍና፣ የሃይማኖትና የሳይንስ መስተጋብርም የዕውቀትን ስፋትና ዕይታ እንዴት እንደሚወስኑት ተቃኝቷል፡፡ እንዲሁም የልቦናን የዕውቀት ምንጭነት፣ የአእምሮን የግንዛቤ መድረክነትና የስሜት ሕዋሳትን የውጫዊ ዓለም (መረጃ) አንባቢነት በመሞገት ‹የዕውቀት መፍለቂያው ከየት ነው?› የሚለውን ጥያቄን ለመመለስ ተሞክሯል፡፡

ምዕራፍ አራት ስለመልካምነት የጥበብ ሥሪት የሚሞግት ክፍል ነው፤ በዚኽም መልካምነት ከልቦና ብቻ ሳይኾን ከሕሊና ጋር ያለውን መስተጋብርና አስፈላጊነቱን ከሥነ-ምግባር ተውህቦ አንጻር በመቃኘት፣ የፈጣሪን የልቦናን ሕግጋት አመንጭነት በመሞገት የጥበብ ቤት ሥራን በማጠናቀቅ ይቋጫል፡፡    ከዚያም የመጽሐፉን መደምደሚያ ሐሳብ በማቅረብ ያሳርጋል፡፡

[1] እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ 2003፣ ገጽ 71

Please follow and like us:
error

Leave a Reply