የአበው የክርክር ጥበብ፡- አለቃ አያሌው እንደ ማሳያ

(በካሣሁን ዓለሙ)
ALEQA AYALEWክርክር የሰው ልጆች የአስተሳሰብ መሞረጃና ማቃኛ ዘዴ ነው፡፡ ይህም ዘዴ አንድን የይገባኛል ጥያቄ በማስረጃ አስደግፎ በምክንያት ማረጋገጥን ወይም መቃወምን ይመለከታል፤ ስለሆነም ክርክር በአንድ በሚያስማማና ተቀባይነት ባለው ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ መደምደሚያው ትክክል መሆኑን የሚረጋገጥበት የሙግት ጥበብ ነው፡፡ ክርክር ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፤ እነሱ ካልተሟሉ ክርክር አይኖርም፡-
አንደኛ የሚያከራክረው ነጥብ መቋጫ (መደምደሚያ-Conclusion)፣
ሁለተኛ ነጥቡን የሚያግዝ ማስረጃ መኖር (መንደርደሪ-Premise)፤
ሦስተኛ በትክክልም የመንደርደሪያው ማስረጃ(ዎች) በተጠየቅ መደሚደሚያውን ማገዙ(ዛቸው) (ስምምነት ካለው መንደርደሪያ ላይ ተነሥቶ በአግባቡ መደምደሚያው ላይ መድረሱ- Logical inference) እጅግ ወሳኝ የክርክር ጅማቶች ናቸው፡፡
ስለዚህ ክርክር አንድ የጋራ ስምምነት ያለው ማስረጃ በመነሻነት ከሌለው ወይም መደምደሚያ ካልተሰጠበት ወይም የቀረቡት ማስረጃዎች መደምደሚያውን በአግባቡ ካልደገፉ ንትርክና ንዝንዝ እንጂ ክርክር አይሆንም፡፡ እነዚህን አስፈላጊ ነገሮች ያሟላ ክርክር ግን የሥነ አመንክዮ ክርክር (Logical Argument) ይሆናል፤ የሥነ አመክንዮ ዕውቀትም የሚቃኘው በዚህ አስተሳሰብ ላይ ነው፡፡
እስቲ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ የተለመደ ምሳሌ እንመልከትለ፡-
ሁሉም ሰው ማች ነው፡፡ (መንደርደሪያ ፩)
ካሣሁንም ሰው ነው፡፡ (መንደርደሪያ ፪)
ስለዚህ ካሣሁን ማች ነው፡፡ (መደምደሚያ)
በዚህ ክርክር ‹ሁሉም ሰው ማች ነው› ተብለናል ይህንን ፉርሽ ሊያደርግ የሚችል የተለየ ዕውቀት ከሌለን በስተቀር በአሳቡ መስማማታችን የግድ ነው፤ በሁለተኛው ዓ.ነገርም ‹ካሣሁን ሰው ነው› ስንባል ስለምናውቅ ‹አዎ ትክክል ነው› ብለን ለመቀበል እንገደዳለን፡፡ በእነዚህ በሁለት የመንደርደሪያ ማስረጃዎች ላይ ከተስማማንም መደምደሚያችን ‹ካሣሁንም ሟች ነው› መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ሁለቱ መንደርደሪያዎች የዚህ ክርክር መደምደሚያን በአግባቡ ለማስረገጥ (ለማጠየቅ) የቀረቡ ናቸው፡፡ በእኛ ሀገር የተጠየቅ ልጠየቅ ስልት ከሆነ ክርክሩ ውርድ መንዛት ላይ የሚገኝ ነው፡- ማለትም ‹ሁሉም ሰው ሟች ከሆነ፤ የካሣሁንንም ሰው መሆን ከተስማማን፤ የካሣሁንንም ማችነት መስማማታችን የግድ ነው›፡፡ በዚህ የተነሣም ይህ ክርክር ስምምነት ያላቸው መንደርደሪያዎችን ይዟል፤ በዚያ ላይ ተመሥርቶም ትክክለኛ መደምደሚያ ሰጥቷል፡፡ ይህም ማለት ሦስቱን አስፈላጊ ነገሮች አማልቷል (የመንድርደሪያው እና የመደምደሚው ይገባናል ጥያቄዎች (claims) በአግባቡ ተናበዋል)፤ ስለሆነም ይህንን ክርክር ያቀረበ ተከራካሪ መርታት ይችላል፡፡ (ስለ ክርክር የበለጠ ማብራሪያ መግኘት የፈለገ ‹መሠረታዊ ሎጂክ እና ሐጸጽ› የሚለውን መጽሐፌን መመልከት ይችላል)
የእኛ ሀገር ሊቃውንት ደግሞ በዚህ ዓይነት የሥነ-አመንክዮ የክርክር የተካኑ ነበሩ፤ ናቸውም፤ በተለይም የተጠየቅ ልጠየቅና የበልሃ ልበልሃ የክርክር ክህሎቶቻቸው ይህንን ይመሰክራሉ፤ ያደረጓቸው ሙግቶችም ሲመረመሩ ጠቢብነታቸውን፣ ብልጠታቸውንና አስተዋይነታቸውን ማሳያዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጥበባቸው የተረሣ ቢመስልም ማሳያዎቹ ግን አልጠፉም፤ ከሥነ-አመንክዮ ዕውቀት ጋር ተነጻጽሮ ያለው የሥነ-አመንክዮዊነት ደረጃና የስልት ዓይነት ባይታወቅም አስደናቂነት ያለው የክርክር ጥበብ እንደሆነ ግን በጥቅል ዳሰሳ መረዳት ይቻላል፡፡
የተነሣነው የአበውን የክርክር ጥበብ በአለቃ አያሌው ምሳሌነት ማሳየት ስለሆነ የተወሰኑ የክርክር ጥበቦችን ከሊቁ የክርክር ጥበብ ጋር እያስተያየን እንመልከት፡፡ ካለቃ አያሌው የክርክር ጥበባትም በተለይም ካቶሊካዊ የሆኑት ዶ/ር አባ አየለ ተክለሃይማኖት ለመመረቂያ ያቀረቡትን Dissertation ወደ አማርኛ መልሰው ‹የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባህርያት አካላዊ ተዋህዶ የምታምነው ትምህርት› በሚል ርዕስ ላሳተሙት መጽሐፍ መልስ የሰጡበትን ስልት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ እንደኔ ግንዛቤ በዚህ በአለቃ አያሌው መልስ አሠጣጥ ዙሪያ ሁለት የክርክር ጥበቦችን ተመልክቻለሁ፡፡ እነሱም፡-
አንደኛ ‹በራሱ ክትክታ ራሱን መምታት›
ሁለተኛ የተለመደው የተጠየቅ ልጠየቅ ስልት ናቸው፡፡
እነዚህን ነጥቦችም በመጽሐፋቸው ዙሪያ እየተሽከረከርን እንመልከታቸው፡፡ የመጀመሪያው አንድ የቀረበን አሳብ በማፍረስ ወይም አሳቡን ውድቅ በመደረግ ትርጉም አልባ የማድረጊያ ጥበብ ሲሆን፤ የአለቃ አያሌው መምህርና የቅርብ ሰው የሆኑት ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬም ‹ኩክሐ-ሃይማኖት› እና ‹መድሎተ-አሚን› በሚሉ መጽሐፎቻቸው ተጠቅመውበታል፤ የአለቃም ‹መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና› የሚለው መጽሐፋቸው በዚህ ስልት የቀረበ ነው፡፡ ሁለተኛው ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ጠበቆች የመሟገቻ ጥበብ የነበረ ነው፤ በተለያዩ የሀገራችን የሃይማኖት ጉባዔያትና ቆየት ባሉ በአንዳንድ ባህላዊ የፍርድ ችሎቶች ተንፀባርቆ ይገኛል፡፡
(1) ‹በራሱ ክትክታ ራሱን መምታት›
የክትክታ ዱላ በገጠር አካባቢ ጎበዞች የሚይዟት ጠንካራ ዱላ ናት፤ ጎበዞች የሚባሉት አንድ ጠብ በተነሣ ጊዜ በአብዛኛው በምከታ እየተከላከሉ ባላጋራቸውን የሚያሥጨንቁ ናቸው፡፡ ብዙን ጊዜ በጠብ ላይ እያሉ የዱላ መሠበር አጋጥሟቸው እንዳይጎዱ ጠንከር ያለ በትር (ለምሳሌ ከወይራ፣ ከትለም፣ ከክትክታ ወይም ከሌላ ዛፍ፣ እንጨት) አዘጋጅተው አርቀውና ወልውለው ይይዛሉ፡፡ ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ጠንካራ በትር ሳይዙ ቀርተው ፀብ ከተነሣ በእጃቸውም ቢሆን መክተው የባላጋራቸውን ዱላ በመንጠቅ ያበራዩታል፡፡ አንድ የመመከት ልምድ የሌለው ሰው የተወለወለች ጠንካራ ዱላ ይዞ ከተጣላም መክቶ የመመለስ ችሎታ ያለው ጀግና የገልጃጃውን ዱላ ቀምቶ በዚያ ይዞ ልክ ያስገባዋል፡፡ አንዱም እንደዚሁ የራሱን የክትክታ ዱላ ተቀምቶ ስለተደበደበ ‹በራሱ ክትክታ ራሱ ተመታ› ተብሎ ተተርቶበታል፡፡ ይህንን ስልት ነው እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ እና አለቃ አያሌው ወደ የመጽሐፍ ክርክር መድረክ ያመጡት፡፡
ይህንን የእነ አለቃን የክርክር ስልት ቀደም ካሉ የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ክርክሮች ጋር ካያያዝነው ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የ‹መጽሐፈ-ምሥጢር› መጽሐፍ አቀራረብ ጋር (መጽሐፉ በአማርኛ ተተርጉሞ በገበያ ላይ ይገኛል ወይም ‹ሶፍት ኮፒውን› በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ድረ-ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል) እና ከእጨጌ በትረ-ጊዮርጊስ ክርክር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አቀራረብ የመናፍቃኖቹን መሞገቻ ነጥቦች እያነሣ እነሱንም ከአሥራው መጽሐፍ (ከመጽሐፍ ቅዱስ) እና ከሊቃውንት ክርክሮች እየጠቀሰ ስህተታቸውን ማሳየት ነው፤ ተከራካሪዎችን የሚመታውም ያነሱትን ነጥብ ‹እንዲህ ያልከው!› በማለት ተነስቶ ነው፡፡
እንዲሁም በአፄ ፋሲል ጊዜ በካቶሊኮችና በኦርቶዲክሶች መካከል በተደረገ የጉባኤ ክርክር እጨጌ በትረ-ጊዮርጊስ አልፎንሱ ሜንዴዝን የረቱት ራሱ ባነሳቸው ጥያቄዎች ነበር፤ ክርክሩም አጭር ስለሆነ እንጥቀሰው፡፡
የአልፎንሱ ሜንዴዝ ጥያቄ፡
• ‹የአብ የባሕርይ ልጁ ሞተ የሚለው ገጸ-ንባብ ከምን ይገኛል?›
የእጨጌ በትረ-ጊዮርጊስ መልስ፡-
• ‹ጠላቶቹ ስንሆን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ይቅር አለን ይልብሃል› (ሮሜ 5፡- 10) መልሱ ትክክል ስለሆነ አላከራከረም፡፡
የአልፎንሱ ሜንዴዝ ሁለተኛው ጥያቄ፡
• ‹የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው?›
የእጨጌ በትረ-ጊዮርጊስ መልስ፡-
• በዚህን ጊዜ መብራት በጉባዔው ፊት አስበርተው ‹የዚህ መብራት ፊቱ ወዴት ነው?› በማለት መልሰው ጠየቁት ይባላል፡፡ በዚህም መልስ ስላጣ ተረቶበታል፡፡
አልፎንሱ ሜንዴዝ መጀመሪያ የጠየቀው ‹የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ሞተ የሚል ቃል አምጡ› የሚል ነው፤ ‹ቅ.ጳውሎስ እግዚአብሔር በልጁ ሞት ይቅር አለን፤ ይልብሃል› ተብሏል፤ ከዚህ ውጭ የሚቀረው አንደኛ ‹ጥቅሱ በትክክል የተጠቀሰው ነው ወይ?› የሚል ነው፤ ለዚያ ደግሞ በአግባቡ ተጠቅሶ አግኝቶታል፤ ሁለተኛ በትክክል የተጠቀሰ ቢሆን እንኳን ትክክለኛ መልስ ነው ወይ?› የሚል ይሆናል፤ ለዚህም ቢሆን ‹በልጁ ሞት› በሚል ተዘግቷል፤ እግዚአብሔር ሌላ ልጅ አለው ካልተባለ በስተቀር ትክክለኛ መልስ መሆኑ እርግጥ ነው፤ ቃሉም ሁሉቱም ወገኖች የተስማሙበት የቅ.ጳውሎስ ቃል ነው፤ ስለዚህ ‹የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ አልሞተም› የሚል ክርክር ማቅረብ የሚችልበት መንገድ አይኖርም፡- አልፎንሱ ሜንዴዝ፡፡ የሁለተኛው የክርክር ጥያቄ ለፈተና የቀረበ ጥያቄ ይመስላል፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያውያን የተለመደ የክርክር ስልት ነው (ለተከራካሪየቸው ያልተለመደ ወይም ያልጠበቀውን ጥያቄ በመጠየቅ መልስ አሳጥቶ መርታት ዐዋቂነትን አስመስክሮ መርቻ ስልት ነበር)፤ አልፎንሱም የተጠቀመው ያንን ስልት ነው፤ ግን ደግሞ ለምን ዓይነት ጥያቄ እንዴት መልስ መስጠት እንዳለባቸው ለሚያውቁት ለኢትዮጵያ ሊቃውንት ጥያቄው መርቻ መሣሪያ ሆኗቸዋል፡፡ በግልፅ እንደሚታየው በሁለቱም ክርክሮች አልፎንሱ ሜንዴዝ የተረታው ባነሣቸው ጥያቄዎች ነው፤ ሙግቱን ለመርታት ያስቹልኛል ያላቸው መከራከሪያዎች ለራሱ መረቻ ስለሆኑት አልፌንሱ በራሱ ክትክታ ራሱ ተመቶበታል ማለት ይቻላል፡፡
በዚህም የተደነቀ አንድ የጎንደር ባለቅኔም የሚከተለውን ቅኔ ተቀኝቷል፡፡
‹ረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ፣
ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ፡፡›
ትርጉም፡
‹ብትሯን አገኘናት ሮምን የምታደክም፣
በንባብ ተወልውላ (ተጠርባ) የተቀረጸች በትርጉም፡፡›
ባለቅኔው በራሱ ክትክታ ራሱ ተመታ ማለቱ አይደለም ወይ?
ወደ አለቃ አያሌው የክርክር ጥበብ ስንመለስ፤ ከርዕሱ መነሣት እንችላለን፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ዶ/ር አባ አየለ የመጽሐፉን ርዕስ ‹የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባህርያት አካላዊ ተዋህዶ የምታምነው ትምህርት› ሲሉ የሚጠቁመው በክርስቶስ ሁለት ባሕርያት መኖራቸውን በአንድ አካል ግን ተዋህደው እንደሚገኙ፤ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያንም ይህንን እንደምታምን ነው፡፡ ከተዋህዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ብሎ ማመን ግን የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን እምነት ሳይሆን የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን እምነት ነው፤ ሁለቱ አቤያተ-ክርስቲያናት በዋናነት የሚለያዩትም በዚህ እምነት (ነጥብ) ነው፤ ስለዚህ ዶ/ሩ የካቶሊክን ትምህርት የኦርቶዶክስ እምነት (አስተምህሮ) አድርገው ስላቀረቡ አለቃ ‹መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና› (1953 ዓ.ም) ብለው መልስ ሰጥተዋል፤ ይህም ትክክለኛ ርእሳዊ መልስ ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የዶ/ሩ መጽሐፍ ርዕስ ‹ተኩላዊ ጠባይን› የተላበሰ ነበርና፤ ማለትም ዶ/ሩ የካቶሊክ እምነትን (አስተምህሮ) በኦርቶዶክስ ስም ደብቀው አቅርበውበታልና፡፡
በሌላ በኩል ዶ/ር አባ አየለ በአዎንታ አስበውትም ይሁን በአሉታ ሆን ብለው አለቤታቸው ገብተው የኢትዮጵያን ሊቃውንት ላስተምራችሁ ብለዋል፤ ያለቤቱ ገብቶ ‹ባለቤት ነኝ› የሚል ደግሞ ሌባ ነው፤ ስለዚህ አለቃም ቤታቸው የገባውን ሌባ የያዘውን ክትክታ በመንጠቅ በሩን ዘግተው የመቀጥቀጥ ተግባር እንዲፈጽሙ ዕድል ሰጥተዋቸዋል፤ ‹እንዴት?› ለሚል ሰውም አለቃ የዶ/ሩን ጽሑፍ መስመር በመስመር እተከተሉ ዋጋ የማሳጣት ወይም የማረም ስልት በመጠቀም መልሳቸውን ማቅረባቸው ምስክር ይሆናል፡፡ እስቲ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሥስት ምሳሌዎችን መዘን እንመለከት!
1ኛ. ዶ/ር አባ አየለ የሚሠጧቸውን ምክንያቶች በማጣረስ ማፍረስ፤ ለምሳሌ ዶ/ሩ የኢትዮጵያ ቤ/ክን ከካቶሊክ ቤ/ክን የተለየችበትን ምክንያት ብለው የጠቀሷቸውን በመልቀም፡-
፩‹እውነቱን መናገር አቅቶት አሥሩን ይቀባጥራል፡፡ በዚህ ምዕራፍ (…) ብቻ ብዙ ምክንያቶች ለዋዉጧል፡
• (ሀ) የትምህርት ልዩነት
• (ለ) የሃይማኖት ልዩነት
• (ሐ) የሥርዓት ልዩነት
• (መ) የሀገር ርቀት
• (ሠ) እስላሞችና የእስክንድሪያ ሊቃነ ጳጳሳት የፈጠሯቸው የውጭ ጉዳዮች
• (ረ) አለማወቅ
• (ሰ) አለመለየት
እስከ ሰባት ተራ ቁጥር ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ባንዱም እንኳ አሳቡን ሊወስን ስለአልቻለ እነሆ ዓባይነቱ እየተገለጠ ሄዷል፡፡ አልተለያዩም ቢል ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያና የሮማ ቤተ ክርስቲያ አለመቀላቀላቸው የተገለጠ ነገር ሆነ፡፡ መለየታቸውም በሃይማት ምክንያት መሆኑን እንዳይናገር እውነት መመስከር ሆነበት፡፡ ከእውነትም ለመራቅ ቢሞክር ብዙ ምክንያት መፍጠር ግድ ሆነበት፤› ይላሉ አለቃ በመልሳቸው (ገጽ- 69)፡፡
አለቃ በዚህ ክርክር አንዱን አብስለው ምክንያት መሆን እንደሚችልና እንደማይችል ሳያረጋግጡ በግምትና በቢሆንስ የተለያየ ምክንያት መዘርዘር አግባብ አለመሆኑን አሳይተዋል፡፡ ለምሳሌ እሳቸው እንዳሉት ሁለቱ አቤያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት አልተለያዩም ከተባለ ስለ ልዩነት የሚያወሩት አብዛኞቹ ምክንያቶች አስፈላጊ አይሆኑም፤ መከራከር የሚቻለው ስላሉ ጥቃቅን ልዩነቶች (ለምሳሌ አንዳንድ የሥርዓት ልዩነቶች፣ የአስተምህሮ አለመሟላቶች/መለያየቶች…) ነው፤ አለቃ እንዳሉት ደግሞ ልዩነታቸው በሃይማኖት ከጀምረ፤ የሚጠቀሱት የሥርዓትና የአስተምህሮ ልዩነቶች በዚያው ውስጥ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ይህ ከሆነም አሥር መላምት መደርደር ትርጉም አይኖረውም፡፡
፪ስህተትነቱን በቤተ-ክርስቲያን አስተምህሮ በማረም፤ ለምሳሌ፡-
• ዶ/ር አባ አየለ ‹ኢትዮጵያውያን ባሕርይና አካል ለሚሉ ቃላት የሚሠጡት ትርጉም ተራቅቆ የሌለበትና የተራ ሕዝብ ትርጉም ነው› ካለ በኋላ ‹አካል ሲሉ ግዙፍ ሥጋ ገላ ወይንም ቁመት ማለትን ያሰማሉ፤ ባሕርይ ሲሉም ስሜት የአለው ሥጋ ማለት ያንድ ሕያው ሆኖ የቆመው ግዙፍ ሥጋ ጠባይ ማለትን ያሰማሉ፡፡› ላሉት በማረም መልክ ሲመልሱ፡
• ‹አካል ሲባል ግዙፍም ሆነ ረቂቅ የባሕርይ መገለጫ ነው፤ ባሕርይ ሲባል ግዙፍም ሆነ ረቂቅ የአካል መገኛ መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም ባሕርይ በየዐይነቱ፣ በየስልቱ፣ በየመልኩ ጠንቅቆ ለማወቅ መገለጫውን አካልን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ባሕርይና አካል ሳይለያዩ የተለያዩ ናቸው፡፡› ካሉ በኋላ ሕጽጽነት አለበት ባሉት ምሳሌ ሲያስረዱ ‹አንድ ሰው አሳቡን ለሌላው ሊገልጥና ሊያስረዳ ቢፈልግ በልቡ የሚንቀሳቀሰውን አሳብ በጽሕፈት ይገልጸዋል፤ ያ ጽሑፍ በልቦና የነበረው አሳብ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ምስክሩም በጽሕፈት ተገልጦ በዐይነ-ሥጋ የሚታየው አካሉ ነው፡፡ ስለዚህም የፊደል መምህር ረቂቃነ ባሕርይ ፊደላትን ከሰሌዳ ላይ በተገለጠው አካላቸው ለተማሪዎች ያስታውቃቸዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ባሕርይ ጥንት፣ አካል ግን መገለጫ ስለሆነ ባሕርይ የሌለው አካል፣ አካል የሌለው ባሕርይ አለመኖሩን አውቆ አካላዊ ቃለ እግዚአብሔር የአዳምን አካሉን አካል ባሕርዩን ባሕርይ አድርጎ አዳም ሊቀበለው የሚገባውን መከራ ተቀብሎ አዳምን ከነልጆቹ እንዳዳነ ማወቅ ይጠቅመዋል› በሚል አርመውታል፡፡
በዚህ ማሳያ የተነፀባረቀው ዶ/ር አባ አየለ ያልተስተካከለ ወይም የተሳሳተ ፅንሠ-ሐሳብን ለክርክራቸው መጠቀማቸው ነው፤ ይህንንም አለቃ በማረም መልክ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በክርክር መንፈስ ስንቃኘው ዶ/ር አባ አየለ የተሣሣተ መረጃን/ማስረጃን ለክርክራቸው አቅርበው ነው የሚሞግቱት ማለት ነው፤ ምናልባት ዶ/ር አባ አየለ ትክክለኛ መስሏቸው ጠቅሰውት ቢሆን እንኳን የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንቱ የማይቀበሉት እምነት ከሆነ ክርክሩ ከመነሻው ‹ትስማሙበታላችሁ/ አይ አንቀበለውም› በሚል የነጥብ ጠርዞች ላይ ለመሽከርከር ይገደዳል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ገና ከክርክሩ መነሻ ስምምነት የለም ማለት ነው፤ ይህ በሆነበትም መከራከሪያቸው በመሳሳቱ ‹የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን በክርስቶስ ላይ ያላት እመነት እንዲህ ነው› በማለት ማብራራት አይችሉም፤ ገና በመነሻው በፅነሠ-ሐሳብ ደረጃ አልተግባቡምና፤ መነሻ ሳይኖረው በሩጫ ተወዳድሮ አሸናፊ የሚሆን ሯጭ የለም፡፡ ለዚያም ነው አለቃም ‹እኛ እንዲህ አንልም እንዲህ እናምናለን እንጂ› በማለት እርማት የሠጡት፡፡
፫ዶ/ሩ ባቀረቡት ማስረጃ በመመሥረት ጥቅሉን በዝርዝሩ እያጣረሱ፣ እያመሣከሩ በመተቸት፤ ለምሳሌ፡-
• ዶ/ር አባ አየለ ‹ኢትዮጵያውያን ባሕርይ የሚለውን ቃል ተራቅቆ በሌለው በግዙፍ ትርጉሙ ስለሚሰሙት በክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉ ማለት ባንድ ሰው አራት እግሮች፣ አራት ዓይኖች ይገኛሉ ማለትን ያህል ጆሮን የሚቀድ የሆነ የማይሰማ ባህል መስሎ ይታያቸዋል› (ገጽ፣ 158-159) ላሉት ሲመልሱ
• ‹በክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉ ማለት፣ በኢትዮጵያውያ ዘንድ ላንድ ሰው አራት እግር፣ አራት ዐይን አሉት ማለትን ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል ሲል የተደነቀበት እኔንም ገርሞኛል፡፡ የሚያስደንቀው ሁለት ባሕርያት አሉ ብሎ ሁለት አካላት የሉም ማለቱ ነው እንጂ፤ ሁለት ባሕርያት ካሉ ሁለት አካላት መኖራቸው፣ ሁለት አካላትም ካሉ ለየአንዳንዱ ሁለት ሁለት፣ የሁለቱም ሲደመር አራት እግር፣ አራት እጅ፣ አራት ዐይን መገኘታቸው የማያጥራጥር ነውና የሚያስደንቅ አይደለም፡፡› ብለዋ፡፡ (ገጽ 161)
ይህ ሦስተኛው ነጥብ ትችታዊ መልስ ነው፤ የተነሣውን ነጥብ ወይም በዶ/ር አባ አየለ የተሠነዘረው ትችት ምንም እርባና እንደሌለው አድርጎ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በዚህም አለቃ የተሳካላቸው ይመስላል ምክንያቱም ያቀረቡት ትችት አሐዛዊ ማሳያን በመጠቀም ነው፤ ስለሆነም ትችቱን በመተቸት ማቃለልና ትርጉም እንደሌለው አድርጎ ማሳየት የአለቃ የመከትከቻ ዱላ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በእነዚህ ሦስት ማሳያዎች እንደምናስተውለው አለቃ የዶ/ር አባ አየለን መጽሐፍ ከወዲያ ወዲህ እያነጸሩ፣ የተሳሳተውን እያስተካከሉ፣ ያልጣማቸውን እያጣጣሉና እየተቹ መልስ መስጠት ችለዋል፡፡ ማለትም አለቃ የዶ/ር አባ አየለን የመከራከሪያ ዱሉ (ክትክታ) እየተቀበሉ፤ የዶ/ሩን ክርክር በክትክታው መደብደብ ችለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ዶ/ሩ ማድረግ የሚችሉት እንደአለቃ ለተሠጠው መልስ ሙሉ መልስ ሰጥቶ ወይም የአለቃ መሠረታዊ መከራከሪያ ምንም ትርጉም እንደሌለው አሳይቶ ማፍረስ እና የራሳቸውን ክርክር ማሻሻል ነው፡፡ ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ይመስላል፤ ለማንኛውም መገምገም የሚቻለው ዶ/ር አባ አየለ በዚያኑ ጊዜ መልስ መስጠት ችለው ቢሆን ነበር፡፡
በጥቅሉ ግን ይህ ‹በራሱ ክትክታ ራሱን መምታት› ያልነው የክርክር መንገድ የአለቃ ሙሉ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ስልት ነው፡፡ ይሁንና ይህንን ስልት ለመጠቀም እንደ አለቃ ዓቢይና ንዑስ ሐሳቦችን ለይቶ የመከራከር ጥበብ፡ ሥርና ቅርንጫፉን በመለየትና በማያያዝ መግለፅ መቻል፤ በተለይ ደግሞ ‹የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር ጥበብን ገንዘብ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ያን ሳያደርጉ አንድን የክርክር ሐሳብ ‹እከተክታለሁ› ብሎ መነሣት በተገላቢጦሽ መከትከቻን አቀብሎ የባሰ መደብደብና መሠባበር ይሆናል፡፡
(2) የተጠየቅ ልጠየቅ ስልት (ጥበብ)
(በዚህ የክርክር ስልት ዙሪያ አንድ ተክለማርያም ፋንታዬ የተባሉ ሊቅ ‹የተጠየቅ ልጠየቅ ሙግት ሥነ አመንክዮን ቀጥታ የሚተካ ዕውቀት ነው› በሚል በ1953 ዓ.ም. ርዕሱን ‹ተጠየቅ› ብለው የሰየሙት መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ የሽለሺ ለማ ‹ተጠየቅ› የሚለው መጽሐፍም የተደረጉ ክርክሮችን በማሳየት መልካም ነው፡፡ እነሱን መመልከት ጠቃሚ ይሆናል፡፡)
የተጠየቅ ልጠየቅ የክርክር ጥበብ ልዩ የሀገራችን በተለይም የኢ/ኦ/ተ/ቤ ሊቃውንት የክርክር ስልት ነው፡፡ ይህንን የክርክር ጥበብ አለቃም በጽሑፍ በማምጣት ተጠቅመውበት ይገኛል፡፡ በጥበቡ ምን ያህል የቤ/ክ ሊቃውንት ተክነውበት እንደሚገኙ በ1878 በቦሩ ሜዳ በሊቃውንቱ መካከል የተደረገው ክርክር እና የአለቃ የክርክር አቀራረብ ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌም በቦሩ ሜዳው ጉባኤ ከተዋሕዶዎች (ሁለት ልደት ብለው የሚከራከሩ) ወገን የሆኑት መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ‹ቀረኝ› ብለው በመጠየቅ ክርክራቸውን ያቀረቡት በዚህ መልክ ነበር፡፡
‹የንጉሥ ገንዘብ ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመዝገብ ይጻፋል፡፡.
‹አዎ ተሰፍሮ፣ ተቆጥሮ በመዝገብ ይጻፋል፡፡›
‹በመዝገብ ከተጻፈው ያጎደለም፣ ያተረፈም ይቀጣል፡፡›
‹አዎ ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›
‹የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል፡፡›
‹አዎ! የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል፡፡›
‹ከመጽሐፍ ቃል ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›
‹አዎ! ያተረፈም፣ ያጎደለም ይቀጣል፡፡›
‹መጽሐፍ ነአምን ክልኤተ ልደታተ (ሁለት ልደታትን እናምናለን) ብሎ በአሐዝ ወስኖ ተናግሯል፡፡›
‹አዎን! ነአምን ክልኤተ ልደታተ ይላል፡፡
በዚህ ጊዜ ጠያቂው በዚህ መልክ ውርድ ነዙ፡-
‹ከመጽሐፍ ቃል ያተረፍ ያጎደለም የሚቀጣ ከሆነ፤
መጽሐፍ ጠንቅቆ ነአምን ክልኤተ ልደታተ ብሎ ከተናገረ፤
አንተ ከዚህ አልፈህ ተርፈህ ሥስት ልደት እያልክ ስታስተምር ከተገኘህ ትቀጣለህ፡፡›
(አባ ጎርጎሪዮስ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ገጽ 80-81)
ይህን ክርክር ልብ ብሎ ላስተዋለው የሊቃውንቱን የክርክር ጥበብ አምቆ ስለያዘ ጥበባቸው ምን ያህል የመጠቀ እንደነበር ይመሰክራል፤ ስለሆነም መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ባልተጠበቀና ማንም ሰው ሊቀበለው በሚችል መነሻ ተነሥተው ወደ ውርድ መንዛት ተንደርድረዋል፤ የፈለጉት ነጥብ ላይ ሲድረሱም ውርዳቸውን ነዝተው የክርክራቸውን ትክክልነት አሳይተውበታል፡፡ በመጀመሪያው መንደርደሪያ በዘመናችን የመንግሥት ገቢና ወጪ ተመዝግቦ እንደሚታወቀው በዚያ ዘመንም የነገሥታት ሀብትና ንብረት በመዝገብ ይታወቅ እንደነበር ይጠቁማል፤ ስለሆነም ተጠያቂው ሊስማማ ችሏል፤ ባይሆን ኖሮ ተጠያቂው ተከራካሪ አይቀበልም ነበር፤ የተስማማው በመሬት የሚታይ ሐቅ ስለሆነበት ነው እንጂ መረታት ፈልጎ አይደለም፡፡ በመጀመሪያው ስለተስማማም በጀት ያጎደለ ወይም አላግባብ ያወለ ወይም በሙስና የመንገሥትን ንብረት ያባከነ በኦዲተር ተመርምሮ እንደሚጠየቀው/እንደሚቀጣው ከተመዘገበው የቀነሰም የንጉሥ የግምጃ ቤት ኃላፊም መቀጣቱ የግድ ነው፤ ስለሆነም ተጠያቂው በሁለተኛውም መንደርደሪያ መስማማት ግድ ሆነበት፡፡
ተጠያቂው በእነዚህ በምድራዊ መንግሥታት/ነገሥታት አሠራር ስለተስማማም የሰማያዊውን ንጉሥ የሃይማኖት ገንዘብ በመጽሐፍ መመዝገብ መስማማት ግድ ሆነበት፤ ያለበለዚያ ‹የምከራከረው ከመጽሐፍ ውጭ ባለ ማስረጃ ላይ ተመሥርቼ ነው› ሊል ይገደዳል፤ ያ ደግሞ አያስኬደውም፤ እንዳውም ክርክሩን ‹መጻሕፍትን ትቀበላለህ/አትቀበልም?› ወደሚል ክርክር ስለሚያዞረው በማጣረሱ በማር ሊታገድበት (ሊቀጣበት) ይችላል፤ ወይም ‹ፍጆታ!› በመጠየቅ ‹የምከራከረው በመጽሐፍ ከሚገኝ ማስረጃ (ተከራካሪዎቹ በጋራ ከሚያውቁትና ከሚስማሙበት) ውጭም ጭምር ነው› የሚል ክርክር መክፈት አለበት፤ ይህም ሌላ የክርክር ነጥብ ነው፤ ስለዘህ ‹ፍጆታ!› ቢጠይቅ እንኳን ተመልሶ ይገባታል፡፡ እንድሁም ነገሥታቱና የታደሙት ታዛቢዎች የሚጠብቁትም የክርክሩን ትክክለኛ አካሄድ ስለሆነ ተጠያቂው ወደ ሌላ አቅጣጫ ውልፊት እንዲል አይፈቅዱለትም፤ ጥያቄውን የሚያቀርበው ተከራካሪም ‹አንድ ስጠይቅህ አንዷን ሁለት ስጠይቅህ ሁለቷን ከዚያ ካለፍክ ማር ያግድህ ብሎ ነው ክርክር የሚጀምረው፤ ተጠያቂው ‹ልክ ነው!› ወይም ‹ልክ አይደለም!› ከሚል መልስ ከወጣ አይለቀውም፤ ስለሆነም ነው ተጠያቂው ትክክለኛ መልሱን ‹አዎ! የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቆጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል› በማለት የተስማማው፤ በሌላ በኩል ‹በመጽሐፍ ተጽፏል› ሲል ተፈጥሮን በጠቅላላም አካቶ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ተሟጋቾቹ የተስማሙበት ነጥብ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ከተስማማም ቀጠዩ መጽሐፍ ላይ ምን ተጽፏል የሚለው የጠያቂው ተከራካሪ ፋንታ ነው፤ የፈለገውን በሐዝ የተደገፈ የመከራከሪ ዋና ነጥብ ‹የተመዘገበው ‹ሁለት ልደት› ይልብሃል› አለው፤ በመጽሐፍ እንዳለ ተጠያቂውም ስለሚያውቅ ተስማማ፤ በዚህም ላይ ነው ጠያቂው ተከራካሪ ውርድ ነዝቶ ያጠቃለለው፡፡
ውርድ መንዛት ቀጥታ የሥነ-አመንክዮ ክርክርን የሚወክል ነው፤ ከላይ የተነዛውን ውርድ እንደገና እንመልከተው፡
ከመጽሐፍ ቃል ያተረፍ ያጎደለም የሚቀጣ ከሆነ፤ (መንደርደሪያ ፩)
መጽሐፍ ጠንቅቆ ነአምን ክልኤተ ልደታተ ብሎ ከተናገረ፤ (መንደርደሪያ ፪)
አንተ ከዚህ አልፈህ ተርፈህ ሥስት ልደት እያልክ ስታስተምር ከተገኘህ ትቀጣለህ፡፡ (መደምደሚያ)
የእኛን አባቶች የክርክር ጥበብ በልዩነት አስደናቂ የሚያደርገው በሙግታቸው አብስለው ስምምነቱን ጨርሰው የክርክሩን ፍሬ ሐሳብ የሚስቀምጡ መሆናቸው ነው፡፡ ተጠያቂው በክርክሮቹ ፍሰት ቀድሞ ስለተስማማ ከመረታት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም፡- ‹መስማማቴ ስህተት ነበር› ካላለ በስተቀር፤ ተሳስቻለሁ ካለ ደግሞ መረታቱን በራሱ ጊዜ መሰከረ ማለት ነው፤ ወይም ‹ተሳስቻለሁ› በማለቱ ‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ› ይልብሃል ይሉታል፡፡ የመጀመሪያው መንደርደሪያ እንደሚገልጸው ያጠፋ ይቀጣል፤ የጥፋት ደመወዙ (ውጤቱ) ቅጣት ነው፡፡ ለዚያም ነው ‹ልትቀጣ ይገባሃል› የሚል መደምደሚያ ሊሠጥበት የቻለው፡፡
ይህ የክርክር ጥበብ ነው በአለቃ አያሌው ታምሩም ክርክር ላይ ተንፀባርቆ የምናገኘው፡፡ እስቲ ሁለት የአለቃን የተጠየቅ የክርክር ማሳያዎች እንመልከት፤ የመጀመሪያው ከጋዜጣ የተወሰደ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እላይ ከጠቀስነው መጽሐፋቸው የተጠቀሰ ነው፡፡
1ኛ. በ1992 ዓ.ም. በፕሮቴሳታንቶችና በኦርቶዶክሶች መካከል ‹ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መባሏ ትክክል ነው/ አይደለም?› በሚል በፊያሜታ ጋዜጣ ላይ ክርክርና ንዝንነዝ ጦፎ ነበር፤ በመሃል አለቃ አያሌው በክርክሩ ውስጥ ገቡ፤ በተለይም አንድ ፕሮቴስታንት (ሠይፈ ሥላሴ የሚባል ይመስለኛል) ለጻፈው መልስ ሲሰጡ የሚከተለውን መከራከሪያ አቀረቡ፡፡ የሙግቱ አቀራረብ አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገውበት የሚከተለውን ይመስላል፤
• ‹መጽሐፍ ቅዱስን ታምናለህ?›፤
-መልስህ ‹አዎ› ወይም ‹አላምንም›
• ‹በመጽሐፍ ቅዱስ ታመንክ ኤልሳቤጥ ማርያምን ‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?› በማለት የተናገረችው በውስጡ ተጽፏል፤ አልተጻፈም?›
-መልስህ ‹ተጽፏል› ወይም ‹አልተጻፈም›
• ‹ከተጻፈ ኤልሣቤጥ ‹ጌታዬ› ያለችው አንተ ‹አምላኬ› ብለህ የምታምነውን ነው፤ አይደለም?
-መልስህ ‹ነው› ወይም ‹አይደለም›
• ‹ነው ካልክ ‹ታዲያ ድንግል ማርያም ለምን የአምላክ እናት አትባልም?›
-መልስህ አዎንታ ወይም አሉታ ብቻ ይሁን ሀተታ አያስፈልግም፡፡
በዚህ የአለቃ ክርክር ተጠያቂው በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምን መሆኑ ተጠይቋል፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ካላመነ በወንጌል አያምንም ማለት ነው፤ በወንጌልም ካላመነ በአምላክ በሥጋ መገለጥ አያምንም ማለት ነው፤ በዚህም ካላመነ ደግሞ የሰው ዘር የሆነችው ድንግል ማርያም አምላክን ወልደዋለች ብለው መከራከር አይችሉም፤ ስለዚህ በመጀመሪያ በዚህ እንደሚስማማ ማረጋገጥ ስላስፈለጋቸው አለቃ፤ ‹በመጽሐፍ ቅዱስ አምናለሁ ወይም አላምንም የሚል መለስ ስጥ› የሚል ጥያቄቸውን አቀረቡ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ካመነም ኤልሣቤጥ ‹የጌታዬ እናት› ያለችውን ጥቅስ ያውቀው እንደሆነ ማረጋገጥ አስፈልጓቸዋል፤ ምክንያቱም ባለማወቅ ወይም ባለማስተዋል ሊሳሳት ይችላልና፤ ካወቀ ‹ኤልሣቤጥ ‹የጌታዬ እናት› ያለችው በእናቱ ማሕጸን ውስጥ እያለ ስለሆነ፤ እሱም ‹አምላኬ! ጌታዬ!› እያለ የሚያመሰግነው እሱን መሆኑን ማረጋጥ አለባቸው፤ እሱ የሚያመሰግነው እሱኑ ከሆነ ደግሞ የአምላክ እናት የምትባለው በዚህ ነው ማለታቸው ነው፤ ማለትም ተጠያቂው ተከራካሪ ከገባው አለቃ የሚሉት፡
• ‹መጽሐፍ ቅዱስን ካመንክበት፤
• በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ኤልሣቤጥ ኢየሱስ በማሕጸን እያለ ማርያምን ‹የጌታዬ እናት› ብላ መጥራቷ እርግጥ ከሆነ፤
• አንተም ‹ጌታዬ! አምላኬ!› እያልክ የምታመሠግነው እሱን ከሆነ፤ ማርያም የአምላክ እናት ለምን አትባልም?› ነው፡፡
በዚህ ክርክርም ተያቂው ተከራካሪ ወይ በተጠቀሰው የጥቅስ ቃል አላምንም ካላለ ወይም አጠቃላይ በአምላክ በሰውነት መገለጥ አልስማማም ካለለ ወይም እምነቴ ኢ-አማኝነት (Atheism) ነው ብሎ ካልተከራከረ በስተቀር የአለቃን ክርክር ውድቅ አድርጎ የሚረታበት መንገድ የለም፡፡ የተጠየቀው ተከራካሪ ደግሞ ፕሮቴስታንት ነው፤ የእኛ ሀገር የፕሮቴስታንት እምነት አማኞች ደግሞ ‹መጽሐፍ ቅዱስን አምኖ በመቀበል ‹ከእኛ በላይ ላሣር› ባዮች ናቸው፤ ስለዚህ በተጠቀሰው ጥቅስ ስለሚያምን፤ እግዚአብሔርም በሥጋ መገለጡን ስለማይክድ ‹እንቢየው!› ካላለ በስተቀር መረታቱን መቀበሉ የግድ ነው፤ ምናልባት ‹ነጥብ የማይገባው› ከሆነም የጥቅስ ፋይል እያዥጎደጎደ ሊንጣጣ ይችላል፤ አለቃን የሚረታ መልስ ግን አይሆንም፤ ‹ሐተታ አያስፈልግም› ያሉትም ለዚያ ነው፡፡
2ኛ. ከዶ/ር አባ አየለ መጽሐፍ አለቃ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይነት ያቀረቡት መከራከሪያ ማሳያ ሊሆን የሚችል ተጠየቃዊ ሙግት ነው፤ እንዳውም እሳቸው ኢትዮጵያዉያን እንዲፈርዱላቸው የፍርድ ጥያቄ ነው ያቀረቡተ፡፡ ለማንኛውም ክርክሩ እነሆ!
• ‹(ሀ) የሰው ባሕርይ አካል የለውም ሊባል ይቻላልን?
• (ለ) ለአምላክ ባሕርይሳ አካል የለውም ይባላልን?
• (ሐ) ባህርያት የአምላክ፣ የሰው ተብለው ከተለዩና ሁለት ከተባሉስ ሁለት አካላት የሉምን?
• (መ) የባሕርያት ሁለትነት ከታመነስ የአካላት ሁለትነት የሚካደው የትኛውን ሽሮ ነው?
ከእነዚህ ጥያቄዎች በኋላ የሚከተለውን ውርድ ነዙ፡-
 እንግዲህ ከ‹ሀ› እስከ ‹መ› የተሰጡትን ጥያቄዎች ከመረመራችሁና ከአበጠራችሁ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፡-
1. ካቶሊካውያን በክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉ ካሉ፤ አካል የሌለው ባሕርይ የለምና ሁለት አካላት ማለታቸው ነው፤ (ማለቷ)
2. እንዲህም ከሆነ ሃይማኖታቸው የንስጥሮስ ነው፤ ይህም ሁኔታ በሥላሴ 4ኛ ተመላኪ መጨመር ነውና ክህደት ነው፤ (ማለቷ)
3. አንድ አካል ካሉም አንድ ባሕርይ ማለት ይገባቸዋል ማለቷ እውነት ነው፡፡› (ገጽ 75-76)
ይህ የአለቃ ክርክር ‹ባሕርይ የአካል መሠረት ሲሆን አካል ደግሞ መገለጫው ነው› በሚለው መሠረታዊ የባሕርይና የአካል ጽንሣተ-ሐሳብ አፈታት ላይ ይመሠረታል፡፡ በዚህ የምሥጢረ-ህላዌ (Ontology) ፍልስፍና መሠረትም አለቃ ከላይ እንደገለጹት አካልና ባሕርይ ተለያይተው አይገለጹም፤ ያለ አካል ባሕርይ አይታወቅም፤ አካል ሳይኖረውም የሚታወቅ ባሕርይ የለም፡፡ ይህ በሀገራች ሊቃውንቱ ሲመራመሩበትና ሲከራከሩበት የኖሩት መሠረታዊ አስተምህሮና እምነት ነው፡፡ ስለዚህ ባሕርይና አካል ተለያይተው የማይከሰቱ፤ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸው መሠረታዊ አቋም ነው፡፡
በዚህ መሠረትም አለቃ ላነሡት ‹የሰው ባሕርይ አካል የለውም ሊባል ይቻላልን?› ለሚለው ጥያቄ መልሱ የሚሆነው ‹አይቻልም› መሆኑ ግድ ነው፤ ለሁለተኛውም ‹ለአምላክ ባሕርይሳ አካል የለውም ይባላልን?› ጥያቄም ቢሆን ‹አይባልም› በማለት መመለስ ግድ ነው፡፡ ለሁለቱም ጥያቄዎች ይህንን መልስ የሠጠ ሰው ደግሞ የሰውና የአምላክ የሆኑ ሁለት ባሕርያትና ሁለት አካላት መኖራቸውን መቀበሉ የማያመልጠው ነገር ነው፡፡ በዚህ ላይ ነው አለቃም ውርድ የነዙት፤ የመደምደሚያ ሐሳቡም ‹ወይ እንደ ንሥጥሮስ ክርስቶስ በተዋህዶ አልከበረም፣ ስለዚህ መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፤ ሥጋም (ሰውነትም) የሰውን ሥራ ያከናውናል ብለህ ተከራከር፤ አለያም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካላት በተዋሕዶ አንድ አካል፤ ከሁለት ባሕርያትም በተዋህዶ (ገንዘብ በመደራረግ) አንድ ባሕርይ ሆኗል ብለህ እመን እንጂ የህልውናን መሠረታዊ አስተሳሰብ የሚቃረን ያለ አካል የተገኘ ባሕርይ አለ አትበል› የሚል ነው አንድምታዊ ክርክራቸው፡፡
ምንም ይሁን ምን አለቃ በአባቶቻቸው የተጠየቅ ልጠየቅ የክርክር ስልት የተካኑ እንደነበሩ ምሳሌዎቹ ጥሩ ማሳያ መሆን ይችላሉ፡፡ አለቃ በዚህ የክርክር ጥበብ ሊካኑ የቻሉትም ቀድሞውን የተጠየቅ ልጠየቅ ክርክር የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የመሞገቻ ባሕል/ልማድ ስለነበርና እሳቸውም ከእነሱ ስለወረሱ ነው፤ ይህም ጥበብ ከቅኔና ከመጽሐፍ አንድታ ጋር በጣም የተቆራኘ ይመስላል፤ ይህም ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ይህ የአበው ጥበብ መረሳቱና አለመጠናቱ የሚያስቆጨው፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply