የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት፡- እውነት ወይስ ተረት? (2)

…የቀጠለ

በኢትዮጵያ ሥልጣኔ የሚንፀባረቅ የታሪክ አተያይ ችግር

‹የኢትዮጵያ የዓለም ሥልጣኔ ምንጭነት› መከራከሪያ ምናልባት ከተጠራጣሪዎች መሠረታዊ ጥያቄ ሳይነሣ አይቀርም፤ ‹ይህንን የታሪክ ፍሰት ወደ ኢትዮጵያ ያመጣኸው ማስረጃዎች አስገድደውህ ነው ወይስ ለራስ ቅድሚያ የመስጠት አባዜ ማስረጃዎቹን እየጎተትህ እንድታመጣ አደረገህ?› የሚል ጥያቄ ልታነሡ ትችላላችሁ፤ ጥያቄው ብዙ የታሪክ ሊቃውንት በጥርጣሬ የሚጠይቁት፤ አንዳንዶቹም ከመጠርጠር አልፈው በየት/ቤቱ ‹ማስረጃዎችን የግድ እየጎተቱ መስክሩልን የሚሉ› በሚል ሐሜት የሚያስተምሩት ነው፡፡

በእዚህም ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል፤ አንደኛ የማስረጃዎቹን ተአማኒነትና ቀዳሚነት አንጥሮ ማየት፤ ሁለተኛም አንድ የታሪክ ምሁር የታሪካዊ ዳራና አተያይ ችግር ያለበት መሆን አለመሆኑን መለየት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ ማስረጃና አተያይ (Evidence & Perspective) ወሳኝ ኩነቶች መኾናቸውን ያዙልኝ፡፡

በታሪክ  ላይ የሚነሣ የእሰጥ-አገባ ክርክር ደግሞ መቼም ቢሆን አይቆምም፤ እንኳን ተጥሎ የተረሳና አቅጣጫው ተቀይሮ የኖረ የጥንት ታሪክ ይቅርና ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻልበት አንድ ምዕት (መቶ) ዓመት ያልሞላው ታሪክ እንኳን ስንት ጭቅጭቅ ይስተናገድበታል፡፡ ኾኖም ታሪክን ያለ ማስረጃ ማጥናትም ሆነ መከራከር አይቻልም፤ ለጥንት ሥልጣኔዎች ደግሞ የታሻሉ ማስረጃዎች መሆን የሚችሉት ቀድመው ተመዝግበው የሚገኙና ሥልጣኔው መከሰቱን የሚመሰክሩ ቋሚ ቅሪቶች ናቸው፤ እነዚህ ግን የመዝገብ ማስረጃዎች ሳይኾኑ የተረት፣ የቅሪተ አካልና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በዘመኑ የፋሽን የታሪክ አፈራረጅ ብቻ ሳይሆን በጥንታዊው የታሪክ ማስረጃዎች መገኘትም መገዛት አስፈላጊ ነው፡፡

በታሪክ ምሁራን ዘንድ የሚታየው ችግር የፍረጃ ተገዥነትና የአተያይ ፋሽን ተከታይነት ይመስላል፡፡ ይህም ማለት አንዳንዱ ‹የዘማናዊነትን (Modernism) የታሪክ አቀራረብ ነው የምደግፈው› ሲል ሌላው ‹የድኅረ-ዘመናዊነትን (Post-Modernism) አተያይ ነው ትክክል› ይላል፤ እነዚህ አተያዮች ደግሞ የራሳቸው የፍልስፍና መሠረት አላቸው፡- አንዱ የሌላው ኮናኒ ባላንጣ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ኹለተኞቹ የመጀመሪያዎቹን የአውሮፓ ማዕከላዊነት አቀንቃኝ ሲሏቸው፤ የመጀመሪያዎቹ ሁለተኞቹን ደግሞ ‹አፍራሽ ኃይሎች› ይሏቸዋል፤ ኾኖም መሥፈርቶቹ የእኛ አይደሉም፤ የተሰጡን ናቸው እንጂ፡፡

ይኹንና እነዚህን አቋሞች በሚደግፉ የታሪክ ምሁራን የተነሣም ጭቅጭቁ ይደራል፤ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜያት የሚጻፉ የትግራይ፣ የኦሮሞና የአማራ ምሁራን የታሪክ ማስረጃዎች አቀራረባቸውና የዕይታ ዳራቸው በድኅረ ዘመናዊያን የታሪክ አተያይ የተቃኘ ነው፤ አካሔዱም አለኝ በሚለው የማስረጃ ማዕቀፍ በመሸበብ የተለመደውን ታሪክ በራሱ ቅኝት አፍርሶ መሥራት ነው፤ በመኾኑም የአማራው ምሁር የአማራ ሥልጣኔ፣ ታሪክና ባህል ባለቤትነት፣ ኦሮሞውም የኦሮሞ ሥልጣኔ፣ ታሪክና ባህል የበላይነት፣ የትግሬውም የትግሬ ሥልጣኔ፣ ታሪክና ባህል ዋና ባለቤትነት፣… አድርጎ ለማስቀመጥ ከእነሱ አተያይ ውጭ ያለውን ኹሉ ይኮንናሉ፤ የራሳቸውን ደግሞ ብቸኛው ወይም ዋና የአካባቢው የታሪክ፣ የሥልጣኔና የባህል ባለቤትና ባለመብት አድርገው ይሞግታሉ፤ በዚህም የጋራውን ይዘነጉታል፤ ወይም ያፈርሱታል፡፡

በሌላ በኩል ከእነ አለቃ ታዬ፣ ከዚያም ከእነ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ጀምሮ የነበረው የታሪክ ቅኝት ደግሞ በአብዛኛው በዘመናዊነት የታሪክ ቅኝት የታቀፈ ነበረ፤ ታሪኩ ኹሉ ከሰለሞናዊ የንግሥና ሥርዓት ጋር ይያያዛል፤ ይህንን ታሪክ ከአውሮጳ ቅኝት ጋር ለማስማማት የሚጥር ይመስላል፤ እንዲሁም ቅኝቱ የአውሮጳን የታሪክ ሥፈርት ይዞ፣ በመሥፈርቱ መሠረት የተስማማውን ‹እውነት›፣ የማይስማማውን ደግሞ ሐሰት እያለ በመፈረጅ ያስቀምጣል፡፡ ከዕይታ አንጻር ሲቃኙ ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፊዎች የሚባሉት ኹሉ በዚህ ቅኝት የሚታቀፉ ናቸው፤ ለምሳሌም የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን መጽሐፎች ማየት ይቻላል፡፡

የዘመናዊነትና የድኅረ ዘመናዊነት የታሪክ ቅኝት የፈጠረውን ግጭት በዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ማስተዋል ይቻላል፡፡ የታሪክ ምሁራኑ የዘመናዊነትን የታሪክ ቅኝት ይዘው ለማስተማር ሲጥሩ ወጣቱ ደግሞ የተሰበከውን የድኅረ ዘመናዊ የታሪክ ቅኝት ይዞ ስለሚመጣ በተማሪና በመምህራን መካከል አለመጣጣም መፈጠሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ በአገራችን የታሪክ ቅኝት ላይ የተፈጠረ አደጋ ነው፤ የመምህራኑም የዘመናዊነት መሥፈርት በችግር የተተበተበ ነበር፡- በመጀመሪያውኑ አተያዩና መሥፈርቱ የእኛ አልነበረምና፤ የድኅረ ዘመናዊነት አተያይም ቢኾን የባሰ አደጋን ይዞ የመጣ ነው፡- ‹የእኔ የእኔ› ባይነትን ያላብሳልና፡፡

በዚህ የተማረረ ሌላው ሦስተኛው ምሁር ደግሞ ‹አቋም መያዝ አይመቼኝም› ብሎ በአውላላ ሜዳ ላይ ይንቀዋለላል፤ የዚያንም የዚያንም ይጠቋቁማል እንጂ ለምስክርነት አይበቃም፡፡ አንዳንድ ደግሞ አለ ‹ጎጥ› ይዞ የሚተኩስ፤ ለዚህ ዓይነት ለጎጠኛ ሰው ደግሞ ከመሸገበት መንደሩ ውጭ ከተራራው ወዲያ ያለው ዐይታየውም፡፡ በአጠቃላይ በጎጠኛም ሆነ በዘመነኛ፣ በድኅረ-ዘመናይም ሆነ በገለልተኛ የእነዚህ የአተያዮች የመለያየት ችግር በማስረጃዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሣርፍ ልብ በሉልኝ፡፡

ሌላው በታሪክ ሊቃውንቱ የሚንፀባረቅ ችግር ‹የነጭ ልብስ› አምላኪነት ነው፤ የአውሮፓ ሥሪት ‹ነጭ ለባሽ› ስለሆኑም የሀገራቸውን ጥበብ ‹ዝተቱን፣ ሸማውን፣..› ይጠየፉታል፤ ብርድ ከሚከላከልላቸው ‹ሸማ› ይልቅ ምንም የአስፈላጊነት ትርጉም የሌለውን ከረባት ማንጠልጠል ይቀናቸዋል፡፡ ምን ማለቴ ነው በነጭ አሳሾች የተጻፉ መጽሐፎችን እንከን እንደሌለባቸው የገለልተኛ ሰው ምስክር አድርገው ሲወስዱ፤ በየገዳሙና በየቤተ-መንግሥቱ፣ እንዲሁም በባህላዊነት በሀገራችን ሰዎች ተቀናብረው የቀረቡ የታሪክና የትውፊት ማስረጃዎችን ለማየት ግን ብዙ ፈቃደኞች አይደሉም፤ የሚገርመው ግን እነዚህን ጽሑፎች የሀገራቸው ሊቃውንት ‹ነጮች ሀገራችንን ለመያዣ ኢንዲመቻው የጻፏቸው ናቸው› ቢሏቸው፤ ‹ከየእረኛው በስማ ወሬ ያጠራቀሟቸው የታሪክ ማዛነፊያ ጽሑፎች ናቸው› ብለው ቢመክሯቸው ‹ከፈረንጅ በላይ ልታውቁ ነው› ብለው እንቢ ብለዋቸዋል፡፡

ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም፤ ሌላውን ሁሉ ትተን የመሪ ራስ አማን በላይ ‹የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ› የሚለው መጽሐፍ በምሁራን የተሠጠውን ቦታ ማየት ብቻ ጥሩ ምስክር መሆን ይችላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንድ ፈረንጅ የዚህን መጽሐፍ ታሪክ ቢዘግበው ስንት የሀገራችን የታሪክ ምሁራን ምርምር ለማድረግና ለማብራራት ይራኮቱበት ነበር፤ ነገር ግን በኢትዮጵያዊ (በጥንታዊ ግእዝ ወይም በሳባ) ቋንቋ የተተጻፈውን በኢትዮጵያዊ ሰው በባህላዊ አቀራረብ በመዘጋጀቱ ትኩረት ሠጥቶ የጥናት አስተያየት የሠጠበት ሰው (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሣ በስተቀር)  አላየሁም፤ ፕሮፈሰር ፍቅሬ ቶሎሣም ይህንን መሠረት አድርገው መጽሐፍ በማዘጋጀታቸው ትላላቅ ከሚባሉ ሊቃውንት ሳይቀር ነቀፋ ቀርቦባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የውጭ ተመልካች በመሆን ማርቲን በርናል ‹ጉራጌኛ ከግእዝ ይቀድማል› የሚል አስተያየት ቢሰነዝር ምሁሮቻችን በድገፋና በተቃውም ሲራኮቱ ነበር፤ በዚህ መልክ ለራሳቸው የታሪክ ምንጮች ዓይን አጥተው ሌሎች በነገሯቸው ላይ ተመርኩዘው ሲያጨበጭቡ ትውልዱን ግራ አጋብተውት ይገኛሉ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልክ በየገዳማቱ ያሉትን ማስረጃዎች የሚሰበስብና የሚመረምራቸው ሰው በመጥፋቱም (የእነ ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ-ሥላሴ ውለታ እንደተጠበቀ ኾኖ)፤ አንድም በተረትነትና በሃይማኖት መጽሐፍትነት ስለተፈረጁ ብቻ ተመራማሪ አጥተው ምሥጥ የበላቸው ብዙ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ‹የጥንታዊት ኢትዮጵያን የሥልጣኔ ጀማሪነት ተረት ተረት ነው› በማለት የሚፈርጁት ምሁራን የጠቀስናቸው ተጽዕኖዎች እንደሚኖሩባቸው መገንዘብ ያስፈልጋል ለማለት ነው፤ አንድ ቀድሞ መከላከያ ነጥብ ያዙልኝማ!፡፡

ሌላው ከመነሻው ሳይሆን ከመድረሻው ጀምሮ መራኮትም የማይለቀን አባዜ ይመስላል፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያውያኑን ማንነት በፊት ‹የትኛው ሥፍራ የምንገኝ ምን ዓይነት ሕዝቦች ነበርን? አሁን ያለው ማንነታችንስ እንዴት ተገኘ?› የሚሉ ጥያቄዎቹን አንስቶ ከምንጩ መስተጋብሩን ከማየት ይልቅ ዛሬ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ ‹እኛ እንደዚህ ነን፤ እነሱ ግን እንዲህ ናቸው› ብሎ በድፍረት በመፈረጅ መራኮት ትልቅ ጉዳይ መሆኑ ነው፤ ይህ ደግሞ የአንድ ቤተሰብ አባላትን በቋንቋ በመለያየታቸው በመከፋፈል የማይገናኙ ዘሮች እርጎ ማስቀመጡ ነው፡፡ ‹ለመሆኑ ‹እኛ› እና ‹እነሱ› የሚለው ፈሊጥ እንዴት ተፈጠረ? በእዚህ አስተሳሰብ ላይ ተመሥርቶስ መበየን አግባብ ነው ወይ?› የሚል ጥያቄ ማንሣት እንደ ምንፍቅና ይወሰዳል፡፡ በዚህ መልክ አንዳንዱ ‹ሊቅ ነኝ› ባይ ጥንትና ዘንድሮን ማገናኘት ሲያቅተው የጥንቱን ለእናትና ለአባቱ ሰጥቶ የዘንድሮን ‹እኔ ብቻ› ብሎ የአሁን ቤተሰቦቹን ብቻ ‹በእኛነት› ይደመድማል፤ ከእሱ ቤተሰቦች ውጭ ያሉትን ሕዝቦች ደግሞ ‹እነሱ› ብሎ በጠላትነት ከአካባቢው ያባርራቸዋል፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ችግርም መስተጋብር የሌለው የታሪክ ንጠላን በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ፈጥሯል፤ ይህም ማዶ ለማዶ መሽጎ መጠዛጠዝን እንጂ ወንዙን መሻገሪያ ድልድይ ሊያሠራ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ቀድሞኑ የጋራቸው የኾነውን መሠረታቸውን ማወቅ ቢችሉ ኖሮ መገናኘት የሚያስችላቸውን ድልድይ ለመሥራት እንጂ የታክ ጦርነት ለመግጠም አይተጉም ነበር፡፡ ስለዚህ ማዶና ማዶ ከመመሸጋችን በፊት ያለውን አንድነታችን መፈለግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አሁን ጥያቄው ‹መነሻችንን ለማሳየት እና የሥልጣኔ መነሻ መሆናችንን ለመመስከር ምን ያህል ማስረጃዎቻችን ብቁ ናቸው?› የሚል ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ወደ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት ክርክር ስናመጣው በአእምሯችን መጀመሪያ የሚፈጠረው ጥያቄ ‹ማስረጃዎቹን ጎትተን በማምጣት ነው፤ ወይስ ራሳቸው ማስረጃዎቹ ዘግቡን ብለው ጠርተውን ነው የምናወራው?› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ማስረጃዎቹን የግድ እኛ ጎትተን በማምጣት ከሆነ ‹የሥልጣኔ ምንጭ ነን› የምንለው ስህተት ነው፤ ‹ያሉት ማስረጃዎች ዘግቡን› ብለውን ከሆነ ግን ‹ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ ናት› ብለን መሟገታችን አግባብና አስፈላጊም ነው፤ ከራስ ጋር የተያያዘን የማንነት መሠረትና ማሳያን መናገርም ነውርነት የለውም፤ ግደታም ነው፤ እና ማን ይናገረው? እኔ እዚህ የምሟገተው ‹የጥንት ሥልጣኔ የታሪክ ማስረጃዎች ኢትዮጵያ የዓለም የሥልጣኔ መነሻ መኾኗን ይመሠክራሉ› በሚል ነው፡፡ በዚህም የማስረጃዎቹ መኖር እርግጥ ከሆነ፤ እኔም ያንኑ ተጠቅሜ መከራከሬ አግባብና ትክክል ይሆናል፤ ዝም ማለቴ ግን ‹ግደለሽ›፤ ‹ለማንነቱ ትርጉም የማይሠጥ ደንታቢስ› ያስብለኛል፡፡

‹አንተ ራስህ ምን ያህል ማሳመን እችላለሁ ትላለህ?› የሚል ጥያቄ ከተነሣ፤ የአቀራረብ አቅምና የተቀባዩ ሁኔታ ይወስነዋል፡- ከቻልኩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ቀናኢ ምሁራንን ከንቅልፍ ከቀሰቀስኩ፤ ካልቻልኩም ያቅሜን ያህል ከጮኽኩኝ ይበቃኛል፡፡ ደግሞ ዓለማዬ ‹እስከ ማመን ያደረሰህ ምክንያት ምንድን ነው?› ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመስጠት ብዙም አያልፍም፡- ‹እኔን አሳምኖኛል እናንተስ እንዴት ታዩታላችሁ?› ማለቴ ነው፡፡

ይቀጥላል… ይቆየን! ያቆየን!

Please follow and like us:
error

Leave a Reply