የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት፡- እውነት ወይስ ተረት? (3)

የዓለም ሥልጣኔ አንድ የጋራ መነሻ አለው? የት?

በዓለማችን የሥልጣኔ መነሻ አጨቃጫቂ ነው፤ ማንኛውም ሰው የእኔ ነው የሚለውን ከፍ ከፍ ማድረግ ስለሚወድ ኹሉም በመሰለው ወደ ራሱ ይጎትተዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ወደ ራሳችን የሳብን መምሰሉ አይቀርም፤ አሳማኝነቱን ለታሪክና ለቅድመ ታሪክ ማስረጃዎች እና ለታሪክ ፍሰት መስተጋብር፣ እንዲሁም ለአንባቢው እንተወው፡፡ ዋና የማስረጃ ምንጮቻችን ሊሆኑ የሚችሉትም የጥንት ታሪክ ሊቆችና ከአባቶቻችን የተገኙ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እናንተም በእነዚህ ሊቃውንት ዘገባና ማስረጃ እንደምትስማሙ እገምታለሁ፤ የአባተቻችንም የታሪክ ማስረጃዎች አክብራችሁ እንደምትመረምሩ እምነቴ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አምጣ ካላችሁኝ ግን ‹እንዴት ብዬ?› ነው መልሴ፤ ባይሆን የሊቃውንቱን ዘገባ በራሴ ግንዛቤና አተያይ እየመረጥኩና እየተቸሁ ለማቅረብ እጥራለሁ፡፡ በዚህም ቢኾን መጀመሪያ ልትጠይቁ የምትችሉት ‹ለመኾኑ ዓለም አንድ የጋራ የሆነ የሥልጣኔ ምንጭ አላት ወይ?› የሚል ሊኾን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ልገምት የቻልኩትም ሊቃውንቱም ይህንን ጥያቄ ስለሚያነሱት ነው፡፡

በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሁለት ዓይነት አቋሞች እንዳሉ ነው የሚታወቀው፤ አንደኛው ሥልጣኔ በአምስት[1] የተለያዩ ሥፍራዎች ለየብቻ መፍለቋን የሚሞግት ሲሁን ሁለተኛው ደግሞ ‹የሥልጣኔ ምንጯ አሐድ (አንድ) የጋራ ሥፍራ ነው› የሚል ነው፡- ከሥፍራ አንጻር፤ ሥፍራው ደግሞ በዚያ የሚኖርቱን ሕዝቦች (ማኅበረሰብ) ይወክላል፡፡ የመጀመሪያው መሟገቻ በማስረጃ የተደገፈና ትክክል ከሆነ ‹ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ ናት!› ያልነው ሐሳብ ገደል ይገባል፤ ባይኾን ‹ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከተጀመረባቸው ሀገሮች አንዷ ናት› የሚል የክርክር መነሻ ሊኖረን ይችላል፤ ትክክለኛው ባለ ማስረጃ አቋም ሁለተኛው ከሆነ ግን ክርክራችን መነሻ ይኖረዋል፤ የሚቀረው ‹አንዷ የሥልጣኔ ምንጭስ ኢትዮጵያ ናት ወይስ ሌላ ሀገር?› የሚል ይሆናል፡፡

  1. የብዙህነት የሥልጣኔ ምንጭ ንድፈ-ሐሳብ

የዚህ አቋም መሟገቻ  የዓለም የሥልጣኔ መነሻዎች የሚላቸው ግብፅ (በዓባይ ወንዝ)፣ ሜሶጶጣሚያ (በኤፍራጤስና ጤግሮስ ወንዞች)፣ ቻይና (በያንግትዝ ሸለቆ)፣ ሕንድ (በኢንዱስ ሸለቆ) እና ኢንካና ማያ (በደቡብ አሜሪካ) ናቸው፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች የጥንታዊ ሥልጣኔ ቅሪቶች የተገኙባቸው፤ የጥንቱ ሥልጣኔ ማስመስከሪያ ሥፍራዎች ናቸው፡፡

ይህ ከሆነ የሚኖረው ጥያቄ አንደኛ ‹ሥልጣኔያቸው ተመሳሳይነት ነበረው፤ ወይስ የተለያየ ነው?› የሚል ሲሆን በሁለተኛ ደረጃም ‹የየትኛው ሥልጣኔ ቀዳሚነት አለው?› በሚልም ይጠየቃል፡፡ እነዚህ ሁለት ጥያቄዎችም የሥፍራን፣ የጊዜንና የሕዝቦች መስተጋብርን በመጠቆም ተያያዥነት አላቸው፤ ከእነዚህ ሥልጡን ከነበሩ ሥፍራዎች አንዱ ከሌላው ጋር ተመሳሳይነት ኖሮት ቀዳሚነት ያለው ከነበረ፤ ቀዳሚ የሆነው ለዳኅራዊው ሥልጣኔ እንደ ምንጭነት መወሰዱ ምክንያታዊነት ይኖረዋል (ምሉዕ ባይሆንም)፤ ተመሳሳይነት ኖሮት ሁሉም በተመሳሳይ ዘመንም የተከሰቱ ከሆነ አንድነቱን ያመጣው ምክንያት መመርመር ይኖርበታል (ምናልባት በሰው ልጆች ባሕርያዊ ተፈጥሮ ተመሳሳይነት የተነሣ ነው ወይስ ሌላ ሊያመሳስለው የሚያስችለው ምክንያት ይኖረዋል በሚል)፤ እንዲሁም በእነዚህ ሥፍራዎች ሥልጣኔያቸውን አበልፅገው የነበሩት አንድ ዓይነት ሕዝቦች ናቸው ወይስ የተለያዩ የሚለው ጥያቄ አብሮ ይከሰታል፡፡ በእነዚህም ጥያቄዎች ‹ተመሳሳይ የሥልጣኔ አሻራዎች የተከሰቱት ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ ተመሳሳይነት የተነሣ ነው ወይስ ከእነሱ ውጭ የሆነ በእነዚህ ሥፍራዎች የተሠራጨ ሥልጡን ሕዝብ ኖሮ ያ መሥርቶት ነው?› በሚል ተጨማሪ ምክንያቶችና ማስረጃዎች መኖራቸው ይፈተሸበታል፡፡

ከማስረጃዎች ምስክርንነት የተነሣ በእዚህ አቋም ዙሪያ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በተለያየ መንገድ የተገኙት ማስረጃዎች እንደሚመሰክሩት ከሆነ በዚያ ዘመን የነበረው የዓለም የሥልጣኔ ባህል ተመሳሳይነት የተንፀባረቀበት ነበር፡፡ ታዲያ ይኸ ለምንና እንዴት ሊኾን ቻለ? ማለትም በአምልኮ ሥረዓት፣ በግብርና አሠራር፣ በሐውልትና በግንባታ አሠራር፣ በሥነ-ጽሑፍና በፊደል ሥርዓት፣ ወዘተ የጥንት ሥልጣኔዎች የተመሳሰሉት ለምንድን ነው? እንዴትስ በዚያን ዘመን በነበረው ሁኔታና ቴክኖሎጂ የባህል መወራረስ አጋጠመ? የባህልና የንግድ መስተጋብርስ ሊከሰት ቻለ? የሥልጣኔ አቅጣጫና መገለጫው ተመሳሳይ መኾኑ ብቻ ‹ለምን? እንዴት ሊሆን ቻለ?…› የሚሉ ጥያቄዎችን ያግተለትላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ ደረጃዎቻቸውም ተቀራራቢነት ይታይባቸዋል፤ የተጀመሩበት ዘመናት መቀራራብና መከታተልም የሚያመለክተው የእነዚህ ሥፍራዎችን የሥልጣኔ ተመጋጋቢነትና ተወራራሽነት ይመስላል፡፡ እንደገናም የንግድ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚገልጹ ማስረጃዎችም አሉ፤ ይህ ከሆነም ሥልጣኔ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተያያዘችና እየተስፋፋች ሄዳለች ማለት ይቻላል፤ ራሷን ችላ በተለያየ ሥፍራ መብቀሏን አያስረግጥም፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የሥልጣኔ መነሻ የተባሉ ሥፍራዎች (በግብፅ፣ በህንድ፣ በቻይና፣ በባቢሎን፣ በደቡብ አሜሪካ) የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎቻቸው ያሁኖቹ ነዋሪዎች ሳይሆኑ ጥቁር ሕዝቦች ነበሩ፤ ይህ ከሆነ እንዴት በሁሉም ሥፍራ ይህ ሊከሰት ቻለ? ጀማሪዎቹ ጥቁሮች ከነበሩ እንዴት ኋላ ሥልጣኔያቸው ተቋረጠ?

‹ጥቁሮች ነበሩ› የሚለው ግን ጭቅጭቅ እንዳለበት መረዳትም ያስፈልጋል፤ ‹የጥቁር ሕዝቦች ምሁራን የጥቁሮችን የሥልጣኔ ቀዳሚነት ለማሳየት የፈጠሩት መከራከሪያ ነው› የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ ግን የጥቁሮችን የሥልጣኔ መሥራችነት የሚመሠክሩ ብዙ የጥንት ታሪክ ማጥኛ ማስረጃዎች እንዳሉ ማበል አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ሕንድ የአርያን ዘሮች አሸንፈው ሳይቆጣጠሯቸው በፊት የሕንድን ሥልጣኔ የመሠረቱት ጥቁሮቹ እንደነበሩ ታሪካቸው ይመሠክራል፤ የአሜሪካ ቀይ ሕንዶች ነጮች ሔደው ሳይቆጣጠሯቸው በፊት ገናና ሥልጣኔን ገንብተው እንደነበር የሐውልትና የቅርሳቅር፣ እንድሁም የሥነ ጽሑፍ ምሥክሮቻቸው ያስረዳሉ፤ መካከለኛው ምሥራቅን በሥልጣኔ ያቀኑት የኩሽ ልጆች መሆናቸው ይታወቃል፤ ግብፅንም እንደዚሁ፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰቱ ሥልጣኔዎች ጀማሪዎቹ ጥቁር ሕዝቦች ናቸው የሚለው መከራከሪያ በቀላሉ የሚሸነፍ አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ግን ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች የአፀፋ ተሟጋቾቹ የሚሰጡት ማብራሪያ ቢኖርም አጥጋቢ አልሆነም፡፡ አንዳንዶቹም የዝግመተ-ለውጥን የዘመን መገመቻዎች ተጠቅመው ‹የዕድሜ ማራዘሚያ› በመውጋት የሥልጣኔ ዘመናቸውን ‹የሩቅ፣ ሩቅ!› ለማድረግ የሞከሩ ሞልተዋል፡፡ የዝግመተ-ለውጥን ግመታ ምናልባት ‹ሲያዘግም ቅርቡ ሩቅ ሆኖበት ሊሆን ይችላልና እንተወው፡- ዝግመተ-ለውጥንም ቢሆን አምነን ከተቀበልነው ግን ለራሱ ሲል የእኛው ምስክር ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን!!![2] (እነ ድንቅነሽ-ሉሲ ምን ሊሠሩ!)

እሱን እንኳን ብናልፈው በእነዚህ በተባሉት የሥልጣኔ መነሻዎች ውስጥ ተንፀባርቀው የሚገኙት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ አሻራዎች ሥፍራ አልተሰጣቸውም፡፡ ለምን? ጥያቄው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የጥንት ኢትዮጵያውያን ኃያልነትና ሥልጡንነት በጥንታዊያን ግብፆች ሔሮግሊፊክና በሕንዶች ሳንስክሪት ጽሑፎች ተጠቅሶ ይገኛል[3]፤ በግሪኮችና በሮማዊያን ጸሐፍት በተረት መልክም ይሁን በታሪክነት ተዘግቧል፤ እንዳውም ከዚያ ባለፈም ኢትዮጵያውያን ነገሥታትንና ንግሥቶችን እንደ አምላክ ማምለክ ሁላ እንደነበረ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኦሲሪስ (Osiris)፣ ዚየስ (Zeus) እና አፖሎ (Apollo) የተባሉት የጣዖታት ስሞች ከኢትዮጵያ ነገሥታት የተወሰዱ ናቸው[4] ይባላል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያውያንን ግዛት ስፋትና የሥልጣኔ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ የጥንት ታሪክ የካርታ መረጃዎችም ይገኛሉ፡፡ እና ይህ ሁሉ ከሆነ ለምን ቢያንስ ከአምስቱ ወይም ከስድስቱ የሥልጣኔ ምንጮች ውስጥ ኢትዮጵያ ሳትካተት ቀረች? ምክንያቱን የሚያውቁት ንድፈ-ሐሳቡን ያስቀመጡት ምሁራን ናቸው፡፡

እኛ ግን መጠርጠር እንችላለን፤ ‹ምን አልባት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ለእነዚህ ሥልጣኔዎች መሠረታቸው እንደሆነ ስላወቁ ወደ አንድ የጋራ መነሻ እንዳይወስደን ብለው ይሆን?› ብለን እንጠይቃለን፡፡ ወይም በአጸፋተ-ዘረኝነት ዕይታ ‹ምናልባት ኢትዮጵያውያኑ ጥቁር ሆነው ስላገኟቸው፤ ንድፈ-ሐሳቡን ያቀረቡት ምሁራን ደግሞ ነጮች ሆነው (ወይም የነጮች ቅጂዎች ሆነው) ጥቁር ሠልጥኖ ነበር ማለት ከብዷቸው (ቀፏቸው) በማወቅ ከሥልጣኔ ተጋሪነት ያስወገዱት ይሆን?› በማለትም እንገምታለን (የመገመት መብታችንን በመጠቀም)፡፡ በሌላ አገላለፅ የሥልጣኔ ብዙህነት መነሻ ንድፈ-ሐሳብ ኢትዮጵያን ከሥልጣኔ ተጋሪነት ስለሚያገል ከዚህ ጽሑፍ ዓላማም ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ስለዚህ የእዚህ አቋም ሙግት በመልስ አልባነቱ ትተነው (ዝግ በር ፖሊሲ እንደ ዐፄ ፋሲል) እንለፍና ይልቁንም ሚዛን የሚደፋውን የሁለተኛውን አቋም መሟገቻ እየዳሰስን ይኸኛው የመጀመሪያው አቋም ምን ያህል ችግር እንዳለበት እንረዳዋለን፡፡

  1. አሐዳዊ የሥልጣኔ ምንጭ ንድፈ-ሐሳብ

ይህንን አቋም የሚያራምዱት ሊቃውንት በመጨረሻ የደረሱበት መደምደሚያ ‹የዓለማችን ሥልጣኔ ከአንድ የጋራ መነሻ ፈልቃ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ፈሳለች› የሚል ነው፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስም ያስቻሏቸውን የተለያዩ ማስረጃዎችም አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ማሰረጃዎች መካከልም የሥልጣኔዎቹ ቅሪቶች፣  የሥነ ተረት ማሳያዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች፣ የታሪክ ፍሰቶች ወደ አንድ አቅጣጫ በመምራት ቅድሚያውን ይይዛሉ፡፡

ከእነዚህ ማስረጃዎች ከማያታችን በፊት ጭቅጭቁ ወደ ኋላ የበለጠ እንጎትተው ካልን ግን የአሐዳዊነት ሥልጣኔ አስተሳሰብ ከሰው ልጆች ከአንድ የጋራ ዘር ተቀድቶ መምጣት አለመምጣትም ጋር ይገናኛል፤ የሰው ልጅ አንድ የጋራ መገኛ ዘር ካለው፤ የተገኘበት አካባቢና ማኅበራዊ ኑሮን ማሻሻል የጀመረበት ሥፍራ ከሥልጣኔ መነሻ ጋር ይያያዛል፤ ባይያያዝ እንኳን መነሻውን ይጠቁማል፡፡ የሰው ዘርን ስናስተውለው ደግሞ አንድ የጋራ መነሻ ያለው ይመስላል፡፡ አንደኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንደሚያመለክተው ሰዎች በሙሉ ከአዳም የተቀዱ ናቸው፤ ሁለተኛው በመዋለድ ሕግ ብናስተውለው የሰዎች ብዛት ከትንሽ ቁጥር እየበዛ መምጣቱን ይገልጽልናል፤ ምክንያቱም ከወላጁ ይልቅ የተወላጁ ቁጥር ይበልጣልና፤ ይህንን ይዘን ወደ ጥንት ብንጓዝ አንድ ወንድና አንድ ሴት ጋር ያደርሰናል፤ ‹እነሱስ (ሁለቱ) ከየት መጡ?› የሚል ካለ ሌላ ጥያቄ ስለሆነ እናልፈዋለን፡፡ ሦስተኛም የሰው ልጆች ሁሉ በተለያየ ሥፍራ ቢኖሩም እኩል የማወቅ ዕድልን ካገኙ የማሰብ አቅማቸውና በሰውነት የአፈጣጠር ሁኔታቸው ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነው፤ በማወቅ ደረጃ ከሰው ሰው መለያየት በሁሉም ማኅበረሰብ ይገኛል፤ ይህም አንድ የጋራ መነሻ እንደነበራቸው፤ ነገር ግን በአካባቢያዊ ክስተቶችና መስተጋብሮች የተነሣ የተወሰነ የሰውነት ቅርጽና የመልክ ልዩነት እንደተከሰተ መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅ በራሱ በድንገት በተለያየ ሥፍራ ሊበቅል የሚችልበት ዕድል ማግኘት እጅግ ሲበዛ ውስን ይሆንነት (limited possibility) ስላለው ከአንድ የጋራ የሰው ልጅ መነሻ መጣ ካላልን አስተሳሰባችን ትርጉም አልባ ይሆንብናል፡፡ ይህም ማለት የሥልጣኔ ብዙህነት ንድፈ-ሐሳብ ከሰው ልጅ አመጣጥ ጋር ስናገናኘው የሚያስኬድ አይመስልም፤ ይልቁንስ የሰው ልጆች መነሻ ዘር አንድ መሆንና የሥልጣኔን ምሥጢር መረዳት ሥልጣኔውን ወደ ተለያየ ሥፍራ ይዞ በመሔድ ማስፋፋትን፤ ከዚያም በጋራ የማኅበራዊ መስተጋር የተነሣ የተለያየ ሥፍራ የሚገኙ ሕዝቦች ሥልጣኔን የበለጠ ሊወራረሱና አንዱ የሌላውን ሥልጣኔ እየኮረጀ ሊያበለጽገው ይችላልና፡፡

በሌላ በኩል እላይ ባነሣነው ‹ቀድመው የሠለጠኑት ጥቁሮች ናቸው ብሎ መከራከርም የዘረኝነት ሌላው ግልባጭ ነው› ካልተባለ በስተቀር በእነዚህ ሥፍራዎች ቀድመው ሠፍረው የነበሩት ጥቁሮች መሆናቸው ጥልቅ ትርጉም ይሠጣል፡፡ አንደኛ በሁሉም ሥፍራ ሥልጣኔን የመሠረቱት ጥቁሮች ከነበሩ የዚያ ሥፍራ ሥልጣኔ አሁን በሥፍራው ከሚኖሩት ሕዝቦች ጋር አይገናኝም ማለት ነው፤ ይህ ከሆነም አንድ የሥልጣኔን ምሥጢር ያገኘ ሕዝብ በፈጠረው እንቅስቃሴ በእነዚህ ሥፍራዎች ሥልጣኔዎቹ ተመሥርተዋል የሚል መላምትን ይጋብዛል፡፡ እንደገናም ‹ጥቁር ማሰብ አይችልም› የሚለውን አስተሳሰብ እና የዳሪውንን የዝግመተ-ለውጥ እሳቤ ውድቅ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የሥልጣኔዎቹ መሥራቾች ጥቁሮቹ ከሆኑ የማሰብና የመጠበብ ችግር የለባቸውም ማለት ይሆናል፤ በአስተሳሰባቸው ምጥቀትም የሥልጣኔን ምሥጢር ተረድተውም ቀድመው መሠልጠን ከቻሉም፤ የዳሪውን የዝግመት ለውጥ ንድፈ-ሐሳብ ማዝገም አይችልም፤ የአማኑኤል ካንትም ጥቁር ‹ከእንስሳት የተሻለ ከሰው ግን ያነሰ ሰው ነው› የሚለው የቀለም መከራከሪያም አይሠራም፡፡ በዋናነት ግን በእነዚህ ሥፍራዎች የሥልጣኔ አሻራቸው የሚገኘው የጥቁር ሕዝቦች ከሆነ የእነሱ ቀድሞ የመገኘት ምሥጢርና ምክንያት መመርመር እንዳለበት ይጠቁመናል፤ በሁሉም ሥፍራዎች ተመሳሳይ ማስረጃዎች ከተገኙም የሥልጣኔን መነሻ በብዙህነት ከመፈረጅ ይልቅ አንድ የጋራ መፍለቂያ እንደነበራቸው እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡

አሁን ወደ አሐዳዊያን የሥልጣኔ መሠረት ማሳያዎች እንመለስ፤ በሥነ ምድር ጥናት (Archaeology)፣ በሥነ-ሰብእ ጥናት (Anthropology) እና በሥነ-ልሣን ጥናት (Linguistic) የዓለማችን ሥልጣኔ ከአንድ ከተወሰነ አካባቢ ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች መነሣቱን ማረጋግጥ የሚያስችሉ ብዙ ማስረጃዎች ማግኘት ተችሏል፡፡ በዚህም የጥንት ዘመን ሥልጣኔ ማሳያዎች የኾኑት የሐውልት አሠራር፣ የግብርና አጀማመር፣ የአምልኮ ሥርዓት፣ የጊዜ አቆጣጠር፣ የባህል ውርርስ፣ የልምድ ድርጊት፣ የፍደላት አቀራረፅ፣ የሥነ-ጽሑፍ ሥርዓት፣ የሥነ-ድምፅ ልማድ… ተመሳሳይነትና ተያያዥነት የሥልጣኔ መነሻ አንድ ስለመኾኑ መስካሪዎች ኾነው ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ እንዴት ተመሳሳይ ሐውልት በኑቢያ (እና በአክሱም) እንደተሠራው በደቡብ አሜሪካም ተሠርቶ ሊቆም ቻለ? እንዴትስ በእነዚህ በተራራቁ ሥፍራዎች ያሉ ሐውልቶች የአሠራር ጥበባቸው ሊመሳሰል ቻለ? እንዴትስ እነዚህ ማኅበረሰቦች ተመሳሳይ የሆኑ የቤት እንስሳትን ማልመድ ቻሉ? በእንስሳት የማረስ ሥርዓታቸው ሊመሳሰል የቻለበትስ ምሥጢር ምንድን ነው? ለምሳሌ የህንድ ገበሬዎችና የኢትዮጵያ ገበሬዎች የአኗኗር ሥርዓት ተመሳሳይ የሆነው በምን ምክንያት ነው? እንዲሁም የፊደላት ሥዕላዊ አቀራረፅ፣ አደራደርና የአጻጻፍ ሥርዓታቸው መመሳሰል ይንጸባረቅበታል፣ ምንጩ አንድ ካልሆነ እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ?… ጥያቄዎቹ በሥነ-ምድር ጥናቶች በተገኙ ማስረጃዎች እየተደገፉ ሲመረመሩ የጋራ መስተጋብር እንደነበራቸው ያረጋግጣሉ፡፡[5]

የቋንቋዎቻቸው ሥርዓቶችና የአነጋገራቸው ልማዶች ሲፈተሹ ዝምድናቸውን ያጸድቃሉ፡፡

ሌላው የጥንት ጊዜ የሥልጣኔ አጀማመርን ለመመርመር ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው የሥነ ተረት  ጥናት (mythology) ነው፡፡ መጀመሪያ መታወቅ ያለበት ተረት የሚፈጠረው የተከሰተ ነገር ከጊዜ ቆይታ የተነሣ እየተጋነነ ወይም ከሌላ ታሪክ ጋር እየተደባለቀ ሲነገር ነው፤ ሌላ ችግሩ እንዳለ ኾኖ የቆዩ ሕዝቦች ታሪክ መንገሪያና ማንነት ማወቂያነቱ እሙን ነው፤ ለዚያም ነው የሥነ-ተረት ጥናት አንድ የጥንት ሥልጣኔ መመርመሪያ ስልት የሆነው፡፡ በዚህ በሥነ-ተረትም የአንድ ማኅበረሰብ ትውፊት፣ ሥነ ቃል፣ ትረካ… ከሥነ ምድር ጥናትና ከተመዘገቡ የታሪክ ማስረጃዎች ጋር በማነጻጸር ይጠናል፤ ከሥነ-ሰብእ ጥናትና በሥነ-ልሣን ጥናት ትክክለኛው እየተበጠረ ይለያል፤ ከዚያም ያለው የጋራ መስተጋብርና ልዩነት ይመረመራል፤ ይተነተናል፡፡ የሥልጣኔ ምንጭን በሚመለከት በተደረጉ የሥነ ተረት ጥናቶችም ሥልጣኔ የጋራ መነሻ ያለው መኾኑን የሚመሰክሩ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ የጥፋት ውሃ መከሰት በብዙ ማኅበረሰብ በተረት መልክ የሚተረክ ታሪክ መኾኑ መረጋገጥ ተችሏል፡፡ በዚህ ትረካም የኖህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃ ጋር ተመሳሳይ በኾነ መልኩ በቻይናም ይተረካል፡፡ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የዐሥሩ አባቶች ታሪክ ከግብፆች ዐሥር አማልክትና ከከለደዊያን ዐሥር ነገሥታት ታሪክ ጋር ተመሳስሎ ተገኝቷል[6]፡፡ ይህም ‹እንዴት አንድ ዓይነት ሊኾን ቻለ?› በሚል ጥያቄ መነሻነት ሲመረመር ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የጋራ መነሻ መኖር ብዙ ይናገራል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አንጻር ስንመለከትም በጥፋት ውሃ የተነሣ ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ያለው የሰው ዘር መጥፋቱን፤ ከጥፋት ውሃም ኖኅና ቤተሰቦቹ መትረፋቸውን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ከአዳም እስከ ኖኅ ያለው ታሪክ የሥልጣኔ አጀማመር መከራከሪያ ሊሆነን አይችልም፡፡ በዘፍጥረት ምዕ. 9፡ ቁ. 18-19 ላይ ስለ ኖኅ እንዲህ በሚል ተመዝግቦ እናገኛለን፤ ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው። የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች። ይላል[7]:: ከእነዚህ የኖህ ልጆችም በተለይ የካም ልጆች የያዙት ሥፍራ ሥልጣኔ ተመሥርቶ የተስፋፋበት ነበር፤ እነሱም በኃያልነታቸው የተመሠከረላቸው እንደነበሩ ይገልጻል፡፡[8] ለምሳሌም የካም የመጀመሪያ ልጅ ኩሽ ኢትዮጵያን፤ ምጽራይም ግብፅን (ምሥርን) ያቀኑ ናቸው፤ የኩሽ ልጅ ናምሩድ ደግሞ ባቢሎንን ገንብቷል፡፡ በተለይ ናምሩድን በሚመለከት እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆንን ጀመረ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደ ናምሩድ ተባለ።› የሚል ገለጻ እናገኛለን፡፡ የናምሩድን ገናናነትና አነዋወሩን በሚመለከት መሪ ራስ አማን በላይ ከኢትዮጵያ ወደ ባቢሎን ሄዶ ከተማን እንደገነባና በባቢሎን ግንብ መፍረስ የተነሣም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ግዛቱን አስፋፍቶ እንደኖረ ገልጸውታል[9]፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣኔያቸው የተመዘገበላቸው የዓለማችን ክፍሎችም እነዚህ የካም ዘሮች[10] የሠፈሩባቸው ሥፍራዎች ስለሆኑ (በተለይ ባቢሎንና ግብፅ) እነሱ  በዚያን ዘመን በሥልጣኔ ማማ ላይ ወጥተው የበላይነትን ይዘው እንደነበር እንረዳለን:: ይህም ማለት ፕራሚዶችን አሁን ሱዳን በሚባለው (በጥንት ጊዜ ሱባ ከዚያ በኋላም ሳባ፣ ሜርዌ (ኑብያ)) መገንባት የጀመሩትና ወደ ግብፅ ያስፋፉት፣ ከዚያም አልፈው ባቢሎንን የመሠረቱት የኩሽ ልጆች ናቸው::

እንዲሁም የኩሽ ወንድም የሆነው ከነዓንን በአሁኑ የመካከለኛው ምሥራቅ እስያ (እስራኤል፤ ፍልስጥኤም እና ሌሎቹን ጨምሮ) ግዛቱን አስፋፍቶ እንደነበር እንመለከታለን[11]፡፡ ስለዚህ እነዚህ የካም ዝርያዎች በሠፈሩበት በዓባይ ተፋሰሶችና በመካከለኛው ምሥራቅ እስያ ሥልጣኔያቸው ገናና እንደነበር መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ ከሴም ዘሮች መካከል የሚታወቁት የአብራሃም ዘሮችም ቢሆኑ ሥልጣኔንና ሥርዓትን የተማሩት ከግብፆች[12]፣ ከኢትዮጵያውያን[13]ና ከከነዓናውያን[14] እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ ከተገኙ የሥነ-ምድር ጥናቶችና የሥነ-ተረት የባህል መስተጋብሮች ጋር አገናኝተን ስንመለከት የሥልጣኔ መነሻ እዚህ አካባቢ እንደነበር ይጠቁመናል፡፡

ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክሮች፣ ከሥልጣኔ ቅሪቶችና ከሥነ ተረት ትሪካዎች በመነሣትም የዓለም የታሪክ ፍሰት በናይል፣ በጤግረስና ኤፍራጥስ፣ እንዲሁም በኢንዱስ ሸለቆዎች ተያይዛ ተስፋፍታለች ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት የሥልጣኔ አገኛኘቷ አንድ የጋራ መነሻን ምክንያት ያደርጋል፤ ከሆነም የሥልጣኔ አየር የነፈሰችው ከአንድ ከተወሰነ አካባቢ ተነሥታ ነው ማለት ይሆናል፡፡

‹ከየት አካባቢ?› ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የሠጠው አንደኛ ሥልጣኔ በግብፅ  ከሌሎቹ ቀድማ የመገኘቷ ምሥጢር፤ ሁለተኛ የተገኙ ማስረጃዎችም የግብፅን መሠረትነት ማመልከታቸውና ሜሶጶጣሚያን ማስከተላቸው[15] ነው፡፡ ይህ ከሆነም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥታ፣ በሜሶጶጣሚያ ተንፈራጣ ወይም እነ ባቢሎንን ጎንፋ በሕንድና ቻይና እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ በኢንካና ማያ ተንሠራፍታ እንደነበር ማረጋገጫ አላት ማለት ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ የክርክር ነጥብ ነው፤ በሚከተሉት መከራከሪያዎች እየጠራ ይሔዳል፡፡

[1] በስድስት የሚሉም አሉ፡- በእነዚህ ምሁራን መካከል እንደ አንዳንዶቹ አከፋፈል ከሆነ ሥልጣኔ የጀመረው በሜሶጶጣሚያ፣ በግብፅ፣ በቻይና፣ በሕንድ፣ በማዕከላዊ ኤንዴስ እና በሜሶ-አሜሪካ ነው፤ ሌሎች ደግሞ ሜሶጶጣሚያ፣ ኢንዱስ፣ ሻንግ ሸለቆ (ቢጫ ወንዝ)፣ ሜሶ-አሜሪካ እና ኤንዴያን ደቡብ አሜሪካ በሚል ይከፋፍሉታል፡፡ በየትኛው ቢሆን ግን ሥልጣኔ በተለያዩ የዓለማችን ክፍላት ወንዝን ተደግፋ መብቀሏን ነው ለማስረገጥ የሚፈልጉት፡፡

[2] እንዳውም በዝግመተ-ለውጥ የሉሲን ታሪክ (ከ3.2 ሚሊዮን ዓመት) ጠቅሰን፣ አያቷን ሰላምን (ከ4.5 ሚሊዮን ዓመት በፊት) አስመስክረን፤ በአዋሽ ሸለቆ የተገኙትን አፅሞች ነፍስ ዘርተንባቸው መጠቃቀስ እንችላለን፡፡

[3] Drussilla D. Hounstoun, p.22-23

[4]  Ibid

[5] ይህንን የጥንታዊ ሥልጣኔ መነሻ አንድ መሆን የሚመሠክሩ ብዙ ማስረጃዎች በኑቢያ (በሱዳን)፣ በአክሱም (በየሃ)፣ በግብፅ፣ በምዕራብ አፍሪካ፣ በሕንድ፣ በሜሶጶጣሚያ (ኢራቅ)፣ በአረቢያ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በሜክሲኮ፣ …  ይገኛሉ፤ የበለጠ ለማወቅ የፈለገም Ethiopia and the Origin of Civilization በሚል ርእስ የተጻፈውን በዮሐንስ ጃክሶን  መጽሐፍ  የጠቀሳቸውን  የሚከተሉትን ማስረጃዎች መመርመር ይችላል The Voice of Africa, by Dr. Leo Froebenius; Prehistoric Nations, and Ancient America, by John D. Baldwin; Rivers of Life, by Major-General J. G. R. Forlong; A Book of the Beginnings by Gerald Massey; Children of the Sun and The Growth of Civilization, by W. J. Perry; The Negro by Professor W.E.B. DuBois; The Anacalypsis, by Sir Godfrey Higgins; Isis Unveiled by Madam H. P. Blavatsky; The Diffusion of Culture, by Sir Grafton Elliot Smith; The Mediterranean Race, by Professor Sergi; The Ruins of Empires, by Count Volney; The Races of Europe, by Professor William Z. Ripley; and last but not least, the brilliant monographs of Mr. Maynard Shipley: New Light on Prehistoric Cultures and Americans of a Million Years Age. (See also Shipley’s Sex and the Garden of Eden Myth, a collection of essays, the best of the lot being one entitled: Christian Doctrines In Pre-Christian America.) These productions of Mr. Shipley, have been issued in pamphlet form in the Little Blue Book Series, published by Mr. E. Haldeman-Julius, of Girard, Kansas.

[6] R.Noorbergen; Secrets of the Lost Races: the most controversial view of the past since, 1977; page 10-30

[7] ኖህ ከጥፋት ውሃ በኋላ ያረፈበት  አርመንያ ውስጥ የሚገኝ የአራራት ተራራ ነው ቢባልም ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጣና ሐይቅ አካካቢ ከሚገኝ ‹አራራት› ከሚል ተራራ ነው እንጂ አርማኒያ አይደለም የሚል ክርክር ያቀርባሉ፤ ይህ ራሱን የቻለ የክርክር መድረክ ነው፤ ስለዚህ ማለፉ የተሻለ ይመስላል፡፡

[8] ይህንንም በዘፍጥረት በምዕ.10፣ ቁ. 1-9 ላይ ‹የካምም ልጆች ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው። የኩሽም ልጆች ሳባ፥ ኤውላጥ፥ ሰብታ፥ ራዕማ፥ ሰበቃታ ናቸው። የራዕማ ልጆችም ሳባ፥ ድዳን ናቸው። ኩሽም ናምሩድን ወለደ፤ እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆንን ጀመረ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደ ናምሩድ ተባለ።

[9] መሪ ራስ አማን በላይ በ1985 ዓ.ም  ባሳተሙት  ‹የጥንቷ የኢትዮጵያ  ትንሣኤ ታሪክ›  በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 22-23 የሚከተለውን የታሪክ አስረጅ አስቀምጠዋል፡፡

‹‹የካም ልጆች ኩሽ፣ ምሥር፣ ፉጥ፣ ከነዓን ናቸው፡፡ ካም ኩማኤል ተብሎ የኖረበት ዘመን ሰባት መቶ ሰባ ሁለት ነው፡፡ እነርሱም በአራራት ዋሻ ሳለ ዕድሜን ጠግቦ ሞተ፡፡  ታላቁ ልጅ ኩሽም ከኤፍራጥስ እስከ ኤርቶር ባሕር ድረስ ድንኳን አስተከለ፤ ልጆችንም ወለደ ስሙም ኤልዘቦ ተባለ፤ ያ(ኔ)ም ሃገር የወርቅ ሃገር ስለሆነ በስሙ ኤልዘቦ አለው፡፡

የኤልዘቦ ልጆች ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራእማ፣ ሰበቅታ ናቸው፡፡

ሳባም ሳቢስ ሃርዋዲኤል ተብ በአዜብ መኖሪያውን አደረገ ሳቢስ የክህነት ስም ኑናኤል የተባለውን ኑባኩግ ወለደ ኤታን የንጉሦች አባት አበመለክስ የተባለው ናምሩድን ወለደ፤ ናምሩድም በምድር ላይ ታላቅ ንጉሥና ኃያል ሆነ አበመለክስ የተባለው ናምሩድ በምድር ላይ ኃያል በሆነ ጊዜ ግዛቱን ከግዮን እስከ ኤፍራጥስ በአለው ሕዝብ ላይ ጣለ እንዲሁም አላቸው በሲናኦር አገር ከተማን እንሥራ ብሎ አወጀ፤ ከዚያም ካልኔቱ አርካድ ኤሬክን አሥራ ሦስት ከተሞች በተሠሩ በሰባ አምስተኛው ዓመት የሰው ልጆች ቋንቋ ተደባልቆ አንዱን አንዱ አልሰማው አለ ሁሉም ለየብቻው ዐዲስ ቋንቋ ፈጠረ፤ ሁሉም ለየብቻው ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ተሰደደ በዚያም ጊዜ ናምሩድ ከተማዋን ባቢሎን አላት፤ ከዚያም ሎጆቹን ይዞ ወንድሙ ንአሰርን አስከትሎ ወደ ነነዌ ሄደ፤ ከዚያም ካላህን ሠራ፤ አበመለክስ የተባለው ናምሩድ የመንግሥቱን ዙፋንም በነነዌና በካላህ መካከል ተከለ ስሙንም ሬሴን አለው ሬስንም ታላቁ ከተማ ተባለ፤ ይህችም የረሆባት ሕዝቦች ተማ ናት፡፡››

[10] የዓለማችን የሰው ዘሮች በሙሉ የካም፣ የሴምና የያፌት  ዘሮች በሚል ተከፋፍለዋል፤ እስካሁን ድረስ ይህንን ክፍፍል መጠቀም የተለመደ ነው፤  ቋንቋም ሳይቀር በዚህ ድልድል ስለተከፈለበት እንጂ ይህንን የምንጠቀመው የሰው ዘሮች ቢከፋፈሉም በተለያየ መስተጋብር ተደበላልቀዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ነጭ›፣ ‹ጥቁር› እና ‹ቢጫ› የሚል የቀለም ድልደላም የክፍፍሉ አካል ሆኗል፡፡

[11] ይህንንም ‹ከነዓንም የበኵር ልጁን ሲዶንን፥ ኬጢያውያንንም፥ ኢያቡሳውያንንም፥ አሞራውያንንም፥ ጌርጌሳውያንንም፥ ኤዊያውያንንም፥ ዐሩኬዎንንም፥ ሲኒንም፥ አራዴዎንንም፥ ሰማሪዎንንም፥ አማቲንም ወለደ። ከዚህም በኋላ የከነዓናውያን ነገድ ተበተኑ። የከነዓናውያንም ወሰን ከሲዶን አንሥቶ ወደ ጌራራ በኩል ሲል እስከ ጋዛ ድረስ ነው፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ፥ ወደ አዳማና ወደ ሰቦይም በኩልም ሲል እስከ ላሣ ድረስ ነው።› ይገልጻል፡፡

[12] ግብፅ በስደት 450 ዓመት ኖረው ወደ ከነዓን መመለሳቸው የታወቀ ታሪክ ነው፤ በዚህ ወቅትም ብዙ ነገሮችን ከግብፅ እንደተማሩ መገመት ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ግብጾች በዚያን ጊዜ በተለያየ ዘርፍ በሥልጣኔ በልፅገው ነበርና፡፡ በተቃራኒው ከዚያ በፊት ግን ዕብራውያን ምንም ዓይነት ሥልጣኔና ግዛት የሚዘረጉበት የተረጋጋ መሠረት አልነበራቸውም፡፡

[13] የእሥራኤላውያንን አባት የባረከው የመካከለኛው ምሥራቅ እስያ ገዥ የነበረው መልከጸዴቅ እንደሆነ ይታወቃል፤ መልከጸደቅ ደግሞ የኢትዮጵያውያን አባት የሆነው የኢትኤል (ኢትኦጵ) አባት ነው፤ እሱም የናምሩድ የልጅ ልጅ ልጅ (ኩሽ ናምሩድን ይወልዳል፤ ናምሩድ አዳማን፤ አዳማም ቄናን፣ ቄናም መልከጸዴቅ የተባለውን ጌሬራን ይወልዳል) ሙሴን የአስተዳደር፣ የውትድርና እና ሌሎች ሥርዓቶችን ያስተማረው አማቹ ዮቶር (ራጉኤል) ነው፡፡ (ይህንን የበለጠ ለመመርመር የፈለገ የመሪ ራስ አማ በላይ ‹የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ› የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 22-37 ይመልከት፡፡)

[14] በዚያ ዘመን መካከለኛው ምሥራቅ እስያ የሚባለው በከነዓናውያን  ቁጥጥር ሥር እንደነበረ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ መረዳት ይቻላል፡፡

[15] በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት (በዩንቨርስቲና በሌሎች የከፍተኛ ት/ቤቶች) በሚሠጠው የታሪክ ትምህርት ሜሶጶጣሚያ ከዓለማችን ቀዳሚዋ ሡልጡን ናት፤ ይሁንና ይህ አስተሳሰብ አሁን አሁን እየተቀየረ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ማርቲን በርናል Black Athena በሚለው በሁለተኛ መጽሐፉ መግቢያ ላይ ባስቀመጠው ንጽጽር የግብፅን የመንግሥት አመሠራረት 3600 ከክ.ል.በ. ሲያደርገው የሜሶጶጣሚያን መንግሥት ግን 2600 ከክ.ል.በ. ያደርገዋል (ገጽ xxix-xxxiii)፤ (በዚህም የግብፅ ሥልጣኔ ከሜሶጶጣሚያ አንድ ሺህ ዓመት ቅድሚያ እንደነበረው መረዳት ይቻላል)፡፡ ሌሎቹም የግብፅ ጥናት ሊቆች ብዙ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ማስረጃዎችን አቅርበውበታል፤ ስለሆነም በትምህርት ቤት የተመርነው የሥልጣኔ አጀማመር የጥንት ታሪክ ክስረት አጋጥሞታል፡፡

Please follow and like us:
error

1 COMMENT

Leave a Reply