የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት፡- እውነት ወይስ ተረት? (4)

…የቀጠለ

ባይ! ዓባይ!…

ከዚህ በላይ እንደጠቆምኩት ሊቃውንቱ ‹ሥልጣኔ በዚህ መልክ ከአንድ አካባቢ መንጭታ ዓለምን እንዴት ልታጥለቀልቅ ቻለች? የትኛው አካባቢስ ነው ቀደምት መነሻዋ?› ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ይሁንና ምርምራቸውን ወደ ጥንታዊ መሠረት ሲወስዱት ሥልጣኔ ከዓባይ (ከግዮን) ሸለቆ መፍለቋን፣ ወደ ሌሎች የዓለማችን ክፍል ለመንሠራፋትም መነሻዋ የእኛዋ ኢትዮጵያ መሆኗን የተገኙት ማስረጃዎች ኹሉ እየመሠከሩ እንዳስቸገሯቸው (የማይታበል ሐቅ እንደኾነባቸው) መስክረዋል፡- የዓባይ ወንዝ በርዝመቱ አንደኛ እንደሆነው የሥልጣኔ መነሻነቱም ረዥም ነው፡፡

ሊቃውንቱ ሥልጣኔዓባይ መንጭታ ወደ ሌሎች ዓለማት ተንሠራፍታለች በሚለው አቋም ለመስማማት ቢሞክሩም ‹የዓባይንስ ሥልጣኔ ማን መሠረተው?› በሚለው ላይ ክርክሮች ተነሥተዋል፤ የክርክሩ ማጠንጠኛም ‹በዓባይ ሥልጣኔ ዙሪያ በጣም የታወቀው የግብፅ (የፎርዖኖቹ) ሥልጣኔ ነው፤ ግብፅ የምትጠቁመው ደግሞ የዓባይን ታህታይ ክፍል ነው፤ ይህ ከሆነ የጥንቱ የግብፅ ሥልጣኔ እዚያው ፈለቀ ወይስ ከዚያ ውጭ ከነበረ አካባቢ ፈልቆ ነው ግብፅ ያጥለቀለቃት?› የሚል ጥያቄ አፍጥጦ መጥቶባቸዋል፡፡ የዚህ ጥያቄ ችግር የበለጠ ሲጨምርም ሌላ ጥያቄ ይወልዳል፤ ‹የግብፅ ሥልጣኔ ከእሷ ውጭ ባሉ ሕዝቦች መሥራችነት የተጀመረ ከሆነ ምኑን የሥልጣኔ ምንጭ ኾነችው?› የሚል ሌላ የተጠየቅ ጥያቄን ያስከትላል፡፡ እነዚህ ተባባሪ ጥያቄዎችም በዓባይ የሥልጣኔ ምንጭነት ዙሪያ የሚነሱ ሦስት የመከራከሪያ አቋሞችን (መላምቶችን) ይፈጥራሉ፡፡ እነሱም፡-

  1. የዓባይ ሸለቆ ሥልጣኔ የኢንዶ ኤሮፓውያን ሥልጣኔ ውጤት ነው፤
  2. የታችኛው ዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች የጀመሩትንና ያዳበሩትን ሥልጣኔ የላይኛው ዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች ተቀብለው እያሻሻሉ ተጠቅመውበታል፤
  3. የላይኛው ዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች የጀመሩትን ሥልጣኔ የታችኞቹ ዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች ተቀብለው አሻሽለውታል የሚሉት ናቸው፡፡

ከአማራጭ መላምቶቹም ‹የግብፅ ሥልጣኔ የተመሠረተው በሌሎች ከሆነ ሌላ ቀደምት የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ አለ› የሚል መከራከሪያ ይወለዳል፡፡ ኾኖም ሊቃውንቱ በእነዚህ መላምቶች ላይ ተከራክረውም አንደኛውን በማጽደቅ ተባብረዋል፤ ምክንያቱም የተገኙት ማስረጃዎች ሁሉ ወደ አንደኛው በማድላት ‹ዓባይ ከላዕላይ ወደ ታህታይ ፈሶ የግብፅን ሕይወት እንደሆናት ሥልጣኔንም አምጥቶ አበልፅጓታል› የሚል መከራካሪያ ሠልጥኖባታል[1]፡፡ ‹ሥልጣኔ ከታህታይ ነው የመጣው ማለት ውኃ አሻቅቦ ይፈሳል› ከማለት ጋር ተመሳሳይ ነው የሚል ሙግት ተደንቅሮ ሊቃውንቱን ፈትኗቸዋል፤ ለማንኛውም ለንጽጽር እንዲመቸን አቋሞቹን በተወሰነ ደረጃ እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡

  • ሥልጣኔ ከኢንዶ-እስያ ወደ ላዕላይ ዓባይ

የዚህ አቋም መከራከሪያ ‹የግብፅን ሥልጣኔ የጀመሩት ከእስያ (በተለይ ከሜሶጶጣሚያ) የመጡ ሕዝቦች ናቸው፤ ስለዚህ ግብፅ ዋናዋ የሥልጣኔ መነሻ ተደርጋ ልትወሰድ አይገባትም› የሚል ነው፡፡ በግልጽ አነጋገር  እዚህ መከራከሪያ  ‹የሜሶጶጣሚያ ሥልጣኔ ከግብፅ ይቀድማል፤ ሜሶጶጣሚያ ደግሞ የነጮች ሥልጣኔ መነሻ ናት› የሚል ስውር አቋምም አለው፤ ይህንን ግን የዘረኛ ነጮች አመለካከት የፈጠረው ዕይታ ነው እንጂ እውነታነቱ ሚዛን አይደፋም፡፡ ይህንን የምንለው ወደን ሳይሆን የአስተሳሰቡ መነሻ የፈጠረው ተጽዕኖ ዝም ብሎ ለማለፍ ስለማያስችል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የዘረኝነት አመለካከትም የፍረጃ አደጋ ስላለበት ነጻ ኾኖ ለመከራከርም ያስቸግሯል፤ ‹ጭቃ ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ መለዳደፍ የማይቀር ነው› እንዳሉት ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ነጭ ኮት የለበሰ ሰውንም ‹ኮትህ ነጭ ነው› ማለት አማራጭ የለውም፡፡ ቀድሞ ችግሩ የተፈጠረው ደግሞ ‹ከዚያኛው ቤት› ነው፤ ምክንያቱም በእነሱ እሳቤ ጥቁር ሕዝቦች አስተሳሰባቸው ዝቅተኛ ስለኾነ ቀድመው ሠልጥነው ነበር ማለት አይቻልም፡፡

ለዚህም ሁለት የታወቁ ፈላስፎቻቸው የጻፉትን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በ19ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው ዕውቁ ፈላስፋ ሄግልስ አፍሪካ ለዓለም ታሪክ ያደረገችው የሚታይ የሥልጣኔ እንቅስቃሴ ወይም የምትካፈለው የልማት አስተዋፅኦ የላትም፤… የግብፅ ሥልጣኔም የአፍሪካን መንፈስ አይጋራም፡፡› ብሏል፡፡[2] ለዚህሔግል አስተሳሰብ መነሻ ከሆኑት መካከል ታላቁ ፈላስፋ አማኑኤል ካንት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፤ ለካንት ጥቁር ሕዝብ ግማሽ ሰው እንጂ ሙሉ የማሰብ ስብእና የለውም፤ ስለዚህ ጥቁር ሊሆን የሚችለው እንደ እንስሳ በማሰልጠን የጉልበት ሠራተኛ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ሔግልም የግብፅን ሥልጣኔን ቢያይም የማያስብ ሠልጥኖ ነበር ለማለት ከበደው፤ የሚያየውን ለማመን ተቸግሮ ለሚያስቡት ለነጮች ሰጣቸው፡፡ የእነዚህ የአውራ ሊቃውንት አስተሳሰብ ደግሞ ምን ያህል የመምራትና የመቅረጽ ኃይል እንዳለው ለመገንዘብ ሌሎቹ ፍልስፍናዎቻቸው ያላቸውን ክብደት ማየት ብቻ ይበቃል፡- ካንትም ካንት ነው፤ ሔግልንም ሔግል ማለት በቂ ነው፡፡

በእነዚህ (እና መሰል) ፈላስፋዎች እሳቤ በመመሥረትም አውሮፓውያን ‹አፍሪካን የሥልጣኔ አልባነት› ስላረጋገጡ አህጉሪቱን ምን እንዳላት እንዲመረምሩና ሕዝቡንም ለማሰልጠን እንዲተጉ አነሳሳቸው፡- ቢያስ የጉልበት ሥራን ለማቀላጠፍ እንዲችሉ፡፡ ‹አፍሪካውያን መሠልጠን የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም› በሚል አስተሳሰብም ሥልጣኔ ከአውሮፓ እየተነሳች ወደ አፍሪካ ጎርፋለች የሚል አቀራረብ ምሁራኑን ሊያጥለቀልቃቸው ችሏል፡- እንደ ቅኝ ግዛታቸው ማለት ነው፤ የቅኝ ግዛት አሳብ መነሻውም ይህ ነው፡፡ እንዲሁም በጥንት ሥልጣኔ ውስጥ ምንም ዓይነት የሥልጣኔ አሻራን በአውሮፓ ውስጥ ስላጡ ሜሶጶጣሚያንና ግሪክን አመጋግበው ግብፅን ተቀጥላ አደረጓት፤ ጥቁርነቷንም ክደው የግድ በነጭ ሸማ ሸፈኗት፡፡ በእውነታው ግን የግብፅም ሆነ የሜሶጶጣሚያ ሥልጣኔ የጥቁሮች የምስክር ሐውልቶች እንጂ እነሱን አያውቃቸውም፤ እነሱ የዚያን ጊዜ በበረዶ ሀገር ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ነበር፡፡ እዚያ ደግሞ ምስክር ሊሆናቸው የሚችልም ምንም ነገር ስላልሠሩ ከዋሻ ወጥተው የወረሩትን እኛ ነው ብለው ለመከራከር በቁ፡፡ ግሪኮችም ቢሆኑ የሥልጣኔ ባለቤት የሆኑት ከግብፅ የሠረቁትን ጥበብ የእኛ ነው በማለታቸው መሆኑ ማረጋገጫ ከቀረበበት ከርሟል (Stolen Legacyን ይመለከቷል)፡፡

የዚህን አስተሳሰብ ምክንያት፣ ስልትና ያመጣውን ውጤት ዶ/ር ላጵሶ ጌ.ድሎቦ ከ‹አውሮፓውያን የማንነት ችግር› ጋር አያይዘው እንዲህ አብራርተውታል፡፡

‹… ከዚህ ቀደም ስለኛ ሲነግሩን የነበሩ አውሮፓውያን ማንነትን በግልፅ እንመርምር፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ አውሮፓ የማንነት (Identity) ችግር ያለበት አህጉር ነው፡፡ …

 ከዘመናት በኋላ… አውሮፓውያን ሳይንስና ቴክኖሎጅን አስፋፍተው በየብስ ያቃታቸውን በባሕር ተጉዘው ዓለምን በቅኝ ግዛትነት ያዙ፡፡ አፍሪካን የባሪያ ገበያ፣ የምዕራብ ንፍቀ ክበብ አህጉራትን አውስትራሊያንና ኒውዚላንድንም መኖሪያቸው አደረጉ፡፡ ከዚህ በኋላ የማንነት ጥያቄ ተነሳ፡፡ ጀርመኖች፣ አንግሎሳክሰኖችና ፍራንኮች ባርበሪያንስ ስለነበሩ ከዚያ የተገኘ ሥልጣኔ ስላልነበር ፊታቸውን ወደ ግሪክ ሥልጣኔ አዞሩ፡፡ ይህንን ያደረጉት የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ ከሮማውያን ሕግን፣ ከግሪኮች ዴሞክራሲን ወሰዱ፤ ያም ስላልበቃቸው ክርስትናን አጠነከሩ፡፡

የግሪክን ሥልጣኔ ሲመረምሩ ከግብፅ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሆኖ አገኙት፤ ግን አምነው መቀበል አልፈቀዱም፡፡ ምክንያቱም ባሪያ አድርገው የገዙትን አፍሪካዊ፣ የሰው ዘር አይደለም ብለው የካዱትን ሕዝብ የሥልጣኔ ምንጭ ነው ብለው ለመቀበል አዳገታቸው፡፡  ሆኖም ሥስት የጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔዎችን አግኝተዋል፡፡ የግብፅ፣ የኑቢያና የአክሱም ሥልጣኔዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሥልጣኔዎች አፍሪካዊ ሥልጣኔዎች ናቸው ብለው ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ ይህን ያልተቀበሉት የሚያካሂዱትን የባሪያ ንግድ የሚቃረን በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አውሮፓውያን አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ፡፡ በመግባታቸውም ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በመፋቅ አቢስኒያ በሚል ስያሜ ተኩት፡፡ የአንድን ነገር ሕልውና ለማጥፋት መጀመሪያ መጠሪያውን መቀየር የተለመደ አካሄድ መሆኑን ካርል ማርክስ በአንጽንዖት መግለጹን እዚህ ላይ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ካደረጉ በኋላ አውሮፓውያኑ የፈጠራ ታሪካችውን አስተማሩን፤ የነፃ የትምህርት ዕድል ሰጡን፡፡ እኛም ያስተማሩንን አጠናን፡፡ ያንን ለሌሎችም ማስተማር ጀመርን፡፡ የአርኮሎጂ ዕውቀት እየሰፋ ሲሄድ ግን የተማርነው ትምህርት ስህተት ሆኖ ተገኘ፡፡ ሥነልሳን የሴም ቋንቋዎች በአረቢያ፣ በባቢሎን ከመነገራቸው በፊት ፊኒቃውያንና አይሁዳውያን ከመገኘታቸው በፊት ቢያንስ ከ10ሽህ ዓመታት በፊት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ይነገሩ እንደነበር አረጋገጠ፡፡ ቋንቋዎቹ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሄዱት ከአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ተነስተው  እንደሆነም አሳየ፡፡[3]

ዶ/ር ላጲሶ የገለጹትን የአውሮፓውያንን የታሪክ ቅሰጣ ስልት ቀድመው ከተረዱት የሀገራችን ሊቃውንት መካከል አለቃ አስረስ የኔሰው አንዱና ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ በየገዳማቱ በመዞር መርምረው እስኪረዱ ድረስም ይህ ቅሰጣ ትክክለኛ አቅጣጫ መስሏቸው እንደነበርም አልሸሸጉም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎችን በዚህ ቅያስ ተታለው እንደነጎዱ ገልጠዋል፡፡

‹የሮማውያን አሳብ የኢትዮጵያን ጥንታዊ መሠረቷን እያጠፋን ስንጽፍ ማንኛውም ዓለም የእኛን አሳብ ከተቀበለን በኋላ በኢትዮጵያም የሚወለዱ ልጆች በዓለም የሚገኘውን ታሪክ እየተከተሉ ይለምዱትና በኛ ሐሳብ ለመሄድ ይችላሉ በማለት አሳባቸውን በዚህ ወስነው ስለተነሱ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ከብራና መጽሐፍ አገኘነው እያሉ፤ በፈረንሳዊ ጽሑፍ እያሳተሙ ለዓለም ባለታሪኮች ሁሉ ስለ አስተላለፉት ያነን መሠረት የሌለውን ጽሑፍ የሌላው አገር ሰው ይቅርና የኢትዮጵያ ልጆች እንኳ እውነት እየመሰላቸው ያንን እየገለበጡ ለወጣቶች ሲያቀርቡ ይገኛሉ፡፡…

ለተጻፈው ታሪክ መደገፊያ የሚኾን በታላላቆቹ ገዳማት አገኝ እንደሆነ በማለት በተላላቆቹ ገዳማት እንደተቻለኝ እየተዘዋወርኩ ከመረመርኩ በኋላ የነሱን ታሪክ የሚደግፍ ጥንታዊ ጽሑፍ ሳላገኝ ስለቀረሁ…›[4] በማለት ሐሳባቸውን ከገለጹ በኋላ በሌላ ገጽ ላይ ደግሞ

‹… እነ አለቃ ታዬን፣ እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይን፣ አታለውበት እንደነበር ጽሑፋቸው ያስረዳናል፡፡ ይህም ጽሑፍ የዮቅጣን ልጆች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር የሚል ጽሑፍ ስላዩ ሐሰት አይጻፍም መስሏቸው በመታለል የነሱን ተከትለው በታሪክ መጽሐፋቸው ስለጻፉት ነው፤ በሀገራችን የሚገኙ ጸሐፊዎች ሁሉ ይህንን ጽሑፍ እየተከተሉ ጽፈው የሚገኙ ብዙዎች ናቸው፤ እኔም ራሴ እንደዚሁ ተከትዬ በታሪክ መጽሐፌ ጽፌው ነበር፡፡ ግን ሳይታተም በመቆየቱ የተሻለ መንገድ ለመስጠት ያባ ጋስፓሪን መጽሐፍ አገለገለኝ፡፡›[5]

የአለቃ አስረስ የኔሰውን መጽሐፍ መሠረት አድርገው የጻፉት ዶ/ር አየለ በክሬም ይህንን በአውሮፓውያን የተደረገውን የማስቀየስ አስተሳሰብ external paradigm ይሉታል፡- አስተሳሰብ በማራገብ የጻፉትን በመሞገት፡፡

‹በእውነቱ የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ደቡባዊ አረብ ነው የሚለው አስተሳሰብ የሚያግዘው ማስረጃ መታጣት ተሰናስሎ ርዕዮታዊ እይታ ላይ ያርፋል እንጂ ታሪካዊ መሠረት ላይ አይደለም፤ ይህም በ19ኛው መ/ክ/ዘ የቄሣራዊ አውሮፓውያን ፈጠራ እንቆቅልሽ መሆኑን ማረጋገጫ ነው፡፡ አፍሪካንም የአውሮፓውያን ቀጣይ ቅኝ ግዛትነት እውነት ለማድረግ ብቻ ሳይኾን ለአዲሱ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተፈበረከ ፈጠራ ነበር፡፡›[6]

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክም አወዛጋቢ የኾነው ቀድመው በእዚህ እይታ አቅጣጫውን ስላስቀየሩትና በየገዳማቱ የሚገኙትን የታሪክና የትውፊት ምስክሮች እንደተረት በመቁጠር ስላጣጣሏቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አቋም የዓባይ ሸለቆ ሥልጣኔ ‹ምንጩ የኢንዶ ኤሮፓዊያን ሥልጣኔ ነው› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱ ማስረጃ የሌለው፣ በዘረኝነት ልክፍት የተገመተ፣ ተቀባይነት እያጣ የመጣ እሳቤ ነው፡፡

ዕይታው ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ግን የታሪክ ማስረጃዎችን ከዓለማዊ ጎራም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምስክሮች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በሚቀጥሉት ንዑሳን ርእሶች እንመለከታቸዋለን፡፡

  • ሥልጣኔ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያን

የዚህ የሁለተኛው አቋም መነሻ ታችኛዋ ምሥር (ግብፅ) ናት፤ ማለትም የሥልጣኔ አየር ከታህታይ ግብፅ ተነሥታ በዓባይ ሸለቆ ወደ ላዕላይ ወደ ኑቢያ፣ ፑንት፣ ደአማትና አክሱም (በጥቅሉ ኢትዮጵያ) ነፍሳለች የሚል አስተሳሰብ መነሻው ነው፡፡ ለምሳሌ አባ ጋስፕሪን ገብረማሪያም ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹ግብፃውያን ከ2500 ዓመት ከጌታችን ኢየሱሰስ ክርስቶስ ልደት በፊት ጀምረው ወርቅና ሌላ ክብር ዕቃ ለመፈለግ በኒል ዓባይና አትባራ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ነበር፡፡ እነሱ የመጡበት ዘመን ኦሪት ከመጻፉ በፊት ስለኾነ የአገሪቱን ስም ኩሽ ብለውት ሄዱ፡፡ … እስካሁን ድረስ በግብፅ የሚገኙት የቀድሞ ዘመን ምስሎች ብዙዎቹ ከኢትዮጵያ በወሰዱት ወርቅ የተሠሩ ናቸው፡፡ … የቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን (የኩሽ ዘሮች) ግብፃውያን ከሀገራቸው እየተሰደዱ መጥተው በኢትዮጵያውያን ውስጥ ወርቅ የሚገኙባቸውን ቦታዎች እየፈለጉ በለቀምት፣ በሌቃ፣ በማጂ፣ በጉባ፣ በሸጎሌ እስከ ኦጋደን ድረስ የሚገኘውን የወርቅ ማዕድን እየፈለጉ ቆፍረው መውሰዳቸውን ካዩ በኋላ የወርቅ ማዕድንን ጥቅም ዐወቁ፡፡ እንዲሁም እየሠለጠኑ ከድንጋይ ዘመን ወደ ወርቅ ማዕድን ዘመን ደረሱ፡፡ ከዚህ በኋላም ጥቂት በጥቂት ወደ ነሐስና ወደ መዳብ ዘመን ደረሱ፡፡› ብለው አስቀምጠዋል፡፡

አሁን የታሪኩን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ‹አባ ጋስፕሪን ይህንን ለማለት ያስቻላቸውን ማስረጃ ከየት አመጡት? ነው ያለ ማስረጃ ነው እንደ ልብወለድ የሚዘግቡት?› ብለን ስንጠይቅ፤ መሠረት የሌለው የፍረጃ ዘገባ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ አባ ጋስፕሪን ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ፣ በቅንነትም ይሁን በክፋት የገለፃቸው መሠረት ‹የጥንት ኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ ከግብፅ የመጣ ነው፤ ግብፆች ደግሞ ኩሾች አይደሉም፡፡› እያሉን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ግብፆች የኩሽ ወንድም የምጽራይም ዘሮች ናቸው፤ ይህም ማለት ሁለቱም የካም ልጆች ናቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከምጽራይም ልጆች ይልቅ ኃይልነታቸው የተገጸው የኩሽ ልጆች የእነ ናምሩድ ነው፡፡ ‹በሌላ መረጃዎችስ ምን ያህል አሳቡን የሚደግፍ ነገር ይገኛል?› ከተባለም ጥያቄው በእንጥልጥል ይቆማል እንጂ አያራምድም፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው ግን የመነሻ አስተሳሰቡ የሥልጣኔን መነሻ ደቡብ አረቢያ (ሚሶጶጣሚያ) በማድረግና የግብፅን ሥልጣኔ ተከታይ አድርጎ በመውሰድ ላይ ይመሠረታል፡፡ በሌላ በኩል ይህ (የጥንት የኩሽ ሥልጣኔ ከታህታይ ግብፅ የመነጨ ነው የሚለው) አስተሳሰብ (መርህ) ግብፆች ጥቁር አፍሪካውያን አይደሉም በሚል የ‹ኢንዶ ኤሮፓውያን ሥልጣኔ የዓባይ ሸለቆ ሥልጣኔ መሠረት ነው› ወደ ሚለው የሔግል የዘረኝነት ሙግት የሚያዘነብል ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ‹የታህታይ ግብፅ የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎች ከየት የመጡ ናቸው?› ብለን ብንጠይቅ ለመልሱ ከላዕላይ ግብፅ የእነሱም ቀደምት መነሻቸው ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ነበር ከማለት ያለፈ ሌላ የትውፊትም ኾነ የታሪክ ቅሪት የሆነ ማስረጃ አይገኝም፡፡

እንዲሁም በተለመደው የታሪክ ዘገባ የተቀመጠው ማስረጃ የሚያሳየውም ከዚህ መላምት ተቃራኒውን ነው፡፡ ለምሳሌ ተበታትና የነበረችውን ግብፅ በማዋሐድ አንድ አደረጋት የሚባለው ሜነስ የላዕላይ ግብፅ ፈርኦን (ንጉሥ) እንደነበረ ይታወቃል፡፡ እንዳውም በጥንት ጊዜ የነበሩ ግብፆች በላዕላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንን የሚመለከቷቸው በአማልክት ሀገር የሚኖሩ ሰዎች እንደኾኑ አደርገው ነበር፡፡ ለምሳሌ አትሸፕሱት የተባለችው የግብፅ ንግሥት፣ የ‹ፑንት› ምደርን (የኢትዮጵያ ምድር) የአባቷ ቅድስት አገር አድርጋ ነበር የምትቆጥራት፡፡ ባጠቃላይ የተለያዩ የታሪክ ማስረጃዎች ሥልጣኔ እንደ ውሃዋ ከላዕላይ ተነስታ ወደ ታህታይ መፍሰሷን እንጂ ወደ ላዕላይ መወንጨፏን አልመሰከሩም፡፡

  • ሥልጣኔ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ከዚያም….

የግብፅ የጥናት ሊቆች ‹ግብፅን ማን አሠለጠናት?› ብለው ላነሱት ጥያቄ፤ የጥንት ኢትዮጵያውያን ‹እኛ!› ብለው መልስ ሰጥተዋቸዋል፡፡ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን ተብለው ይጠሩ የነበሩትን ሕዝቦች ታሪክ ሲመረምሩም መነሻ ቤታቸውን እዚሁ አለንበት የዓባይ መነሻና ተፋሰሱን አድርገው፤ ግብፅን አሠልጥነው፣ በጎረቤቶቻቸው በእስያና በሌሎች አህጉራት ተንሠራፍተው፣ አሁን የህንድ ውቅያኖስና የአትላንቲክ ውቅያኖስ የሚባሉት ቀላያትን (ውቅያኖስ) በስማቸው አስጠርተው በመርከቦቻቸው እየቀዘፉ፣ በጥበቦቻቸው እየመረመሩ የሥልጣኔው በር ከፋች በመሆን፤ ዓለምን ተቆጣጥረውት እንደነበር የማያብሉት ጥንታውያ ማስረጃዎች ምስክር ሆነው አግኝተዋቸዋል፡፡ ይህንን የበለጠ ጠልቆ መመርመር የፈለገ ጎግልን ይጎልጉለው የሥልጣኔን ፍሰት ከጥንት ካርታ ጋር አያይዞ ያቀርብለታል፡፡

ይህም ማለት ‹የግብፅ ሥልጣኔ ከላዕላይ ከኢትዮጵያ የመነጨ ነው› የሚለው መከራከሪያ ብዙ ማስረጃዎች ያሉት ነው፤ በጥንት የግሪክ፣ የሮማና የአይሁድ የታሪክ ጸሐፊዎች የተጠቆመ፣ የሐውልት ላይ ጽሑፎችና ትውፊቶች (ሥነ ቃሎች) ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ጋር በመገናዘብ ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡ በእነዚህ ማስረጃዎችም በብዛት ተገልጾ የሚገኘው ሥልጣኔ ከላዕላይ ግብፅ መፍለቋን ነው፤ ታህታይ ግብፅ ግን ከላይ እየጎረፈ በመጣላት ጥበብ ተጠቅማ ነው የሥልጣኔ መስኖዋን ያስፋፋችው፤ የላዕላይ ግብፅ ሥልጡንነት ደግሞ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ነበር፡- ‹አራት ነጥብ!› አሉ ጠቅላያችን ሲጠቀልሉ፡፡

እዚህ ላይ ዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤል ‹አብሮነት በኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ በ1984 ዓ.ም ባሳተሙት ድንቅ መጽሐፋቸው ከገጽ 4-5 ያስቀመጡትን ነጥብ ብጠቅስ ብቁ ገለጻ ይሠጠናል ብዬ አምናለሁ፡፡

‹የዓባይ ሸለቆ የዓባይ ወንዝ ውጤት ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ሥጦታ ነው፡፡ የዓባይ ሸለቆም የመጀመሪያው ጉልህ ማኅበራዊ ሕይወት የተደራጀበት፣ የተፈጥሮ ክስተቶች ግንዛቤ ያገኙበትና የሰው ልጅ ጉልህ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሥነ ምግባርና የሣይንስ ሥርዓትና ምሥጢር የለየበትና በየፈርጁ ያደራጀበት ነው፡፡ መደበኛ ግብርና ማለትም ከብት ማርባት፣ አዕዝርት መዝራት፣ የመገልገያና የማምረቻ መሣሪያዎችን  ማምረት፣ አልባሳት መሥራት፣ ከብቶችን በወተት፣ በሥጋ፣ በትራንስፖርትና በእርሻ ምንጭነት መጠቀም፣ በመስኖ እርሻ መገልገል፣ በውሃ መጓዝ፣ በአንድ አምላክ ማምለክ፣ የጽሁፍ ባህል ማመንጨት፣ የሃይማኖት ካህን ማፍራት፣ አስከሬን ማቆየት፣ የጂኦሜትሪን ሳይንስ ማዳበር ወዘተ የመሳሰሉ ኹሉ ብልጭታዎች መጀመሪያ የታዩት በዓባይ ሸለቆ ውስጥ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለመጀመሪያ የሰው ልጅ በተናጠል ሳይኾን በተደራጀ መልክ በተፈጥሮ ጋር በውል የታገለበትና በኋላም የሰው ልጅ ከራሱ ጋር መታገል የጀመረው በዓባይ ሸለቆ አካባቢ መኾኑ ተረጋግጧል፡፡›

ይህ የዶ/ር ኃይሌ ገለጻ በብዙ ሰነዶች የተደገፈ፣ በተለይም በግብፅ ጥናት ሊቃውንት የሚቀነቀን ነው፡፡ ለምሳሌም እነ ዱርሲላ ሆስቶንን፣ የእነ ዮሐንስ ጃክሶንን፣ የእነ ቸክ አንታ ዶዮፕን፣ የእነ ቻንስለር ዊሊያምስን፣ የእነ ማርቲን በርናልን፣… ሥራዎች መመልከት ይቻላል፡፡ የብዙ ብዙ ማስረጃዎችን ከጥንታዊያ ዶሴዎች (ዶክመንቶች) በመልቀም አቅርበውልናል፤ ማስረጃዎቹም ‹ጥንታዊት ኢትዮጵያን እያወደሱ ከምሥጢራዊ ሕዝቦች መኖሪያ ምድርነት እስከ የአማልክት ማደሪያ ቅድስትነት አድርሰዋታል፤ እግዚአብሔር ራሱስ ሕዝቦቹ የሆኑትን እሥራኤላዉያን ‹ለእኔ እናንተ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁንምን?› አይደለም እንዴ ያላቸው?

ከሀገራችን ታሪክ ጸሐፊዎች ግንባር ቀደም የሆኑት ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ምንም እንኳን በአሁኑ ዘመን የታሪክ ሊቃውንት ተቀባይነት የለውም በማለት ቢያጣጥሉትም በጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግብፅ ይቀድማል ተብሎ መመዘገቡን ገለጽዋል፡፡ ማጣጣላቸውን የአመለካከት ጉዳይ ስለሆነ ብንተወዉ የሚባለውን ግን እንደሚከተለው ነው ያቀረቡት፡-

ነገር ግን የታሪክ አባት የሚባለው ስመ ጥሩው ሔሮዱትስ ወደ ግብፅ መጥቶ ዓባይንም ጎብኝቶ በጻፈው የታሪክ መጽሐፉ እንደዚሁ ዲዮዶር የሚባለው የሮማ ታሪክ ጸሐፊ ከግብፅ በፊት ሥልጡንና ገናና የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗን፤ እሷም ግብፅን ወራ መያዟን ግብፅንም Ú¥(18) የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደገዟት፤ ራሷ ኢትዮጵያ ግን በማንም ተገዝታ የማታውቅ አገር መሆኗን፤ ነገሥታቱም ሕዝቡም በጣም ሥልጡን፣ ደግ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ሰላማዊ፣ በጦርነት ጊዜ ዠግና ጎበዝ መሆናቸውን እያጋነኑ ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያም በአገር (ጊኦግራፊ) አቀማመጧ ከፍተኛ (ላዕላይ) ግብፅግን ወደታች (ታሕታይ) ዓባይም ከላይ ከኢትዮጵያ ወደ ታች ወደ ግብፅ እየፈሰሰ እንደሚያጠጣት አፈርም እያቀበለ እንደሚመግባት፣ እንደዚሁ እንደ ውሃው አወራረድ ሥልጣኔን ለግብፅ የሠጠጭ ኢትዮጵያ መሆኗን እነዚሁ የታወቁት የጥንት ጸሐፊዎች እነሱንም የተከተሉት ሁሉ አስፋፍተው ጽፈዋል፡፡ በኋላ ግን ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ ያገኘችውን ሥልጣኔ አስፋፍታ እንደገና የ፲፰ና የ፲፱ኛው ዲናስቲ ነግሥታት ኢትዮጵያን መልስው እንደገዙ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አይለው እንደገና ግብፅን ይዘው የ፳፭ኛውን ዲናስቲ (ሥርወ መንግሥት) እንደመሠረቱና እንደገዙ ተጽፏል፡፡› ብለው አስቀምጠዋል፡፡[7]

ባንድ ወቅት የግብፅ ጥናት ሊቅ የኾነው ፀጋዬ ገ/መድኅን በጦቢያ መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ፡

 ‹አፍሪካ የመጀመሪያዊቱ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትኾን፤ የቋንቋና የፊደል፣ የጽሑፍና የአሐዝ፣ የሙዚቃና የዳንስ፣ የቅርጻቅረፅና የሥዕል፣ ወዘተ መፈጠሪያ ምድር እንደመሆኗ የመጀመሪያይቱ የዓለም ባህል እናትነቷም ዛሬ በማያፈናፍን ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ዛሬ፣ የማንነቷ ጥያቄም ግልጥ ያለ መልስ ያገኘው በዚህ በሳይንሳዊ እውነታ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ …

ቅድመ-ታሪክ ጻሐፍት (antiquity historians) እንደነ ፕሉታርክ እንደነ ፕሊኒ ያሉ፣ ኋላም እንደነ ዲዮርዳኖስና እንደነ ሄሮዶቶስ ያሉ፣ ገና የግሪክና ሮማ ሥልጣኔዎች ከማበባቸው በፊት በካም አበው ሥልጣኔ ላይ ተመሥርተው የሰውን ዘር የሥልጣኔ አመሠራረት መመዝገብ የጀመሩት፡፡ ከደቡብ ምሥራቅ ሜዲቴራኒያ ማዶ እስከ ማዳጋስካር ባሻገር፣ ከሕንድ ውቅያኖስ በመለስ እስከ ቀይ ባህር ግራና ቀኝ ያለው ዝርያ፣ ካምም (ኩሽም) አልነው ጥቁር ግብፅ፣ ሳቢያም አልነው ኢትዮጵያ፣ ሀበሻም አልነው ኑቢያ፣ የአንድ የካም ዘር ግንድ ልጅ፣ የአንድ አጥንትና ደም ወንድምና እህት መኾናቸውን ደጋግመው ዘግበውታል፡፡….  በማለት አብራርቷል፡፡[8]

ፀጋዬ በሌላ የጦቢያ ላይ ጽሑፉ ደግሞ ዦዥር ፖዠኔን በመጥቀስ፡

 ‹የካም እናት አቴቴ፣ የዛሬ ዐሥር ሺህ ዓመት በፊት፣ ከኢትዮጵያ ወደ ጥንታዊት ጥቁር ግብፅ ወረደች፡፡ ከዚያም ‹ኧስ ኧስ› (ኢሲስ) በኋላም ‹እሴት› (እሰይ) እየተባለች ወደ ግሪክና ሮማ (ላቲን) ተሻግራ ከአምስት ሺህ ዓመት በላይ ተመለከች፡፡ ባለብዙ ሺህ ስመ ውዳሴ (ዌዲሴ odyssey) ተባለች፡፡ ‹ኢስስ› ጌታ የሱስ ከተወለደ በኋላ እያደር ወደመረሳት ደረሰች፡፡ ቀጥሎም እመቤታችን ማሪያም የእመ ፀሐይ (ኢሲስ) አድባርን እጅግ ብዙ ስመ ውዳሴዎች እመ ብርሃን እየተባለች ወረሰች፡፡› ብሏል፡፡[9]

ማስረጃዎቻችን በጣም አስተማማኝነት አላቸው፤ ካስፈለገም ስለ ኢትዮጵያ የጥንታዊ የታሪክ ምንጭነት የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች የሠጧቸውን አስተያየቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ጥንታዊያን ምሁራን መካከልም የቢዛንታንያ ጆኦግራፊ ባለሙያ የኾነው እስጢፋኖስ የሰጠው አስተያየት ሊታለፍ የማይገባው ነው፡፡ እስጢፋኖስ ‹ኢትዮጵያ በምድር ከሚገኙ ሀገሮች ኹሉ አምላክን ማምለክና በሕግ ሥርዓት መመራት የተጀመረባት የመጀመሪያዋ ሀገር ስትኾን ዜጎቿም የአምልኮ ሥርዓትንና በሕግ ሥርዓት መመራትን የጀመሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡›[10] የሚል ቃል አስፍሯል፡፡

በዚህ ዙሪያ Ethiopia and the Origin of Civilization እናWonderful Ethiopians of Ancient Cushite Empire (2ኛው ፒራሚድ ገንቢዎቹ ኢትዮጵያን በሚል ርዕስ በአማርኛ ተተርጉሟል) የሚሉ መጻሕፍት ሰፊ ማብራሪያ ይሠጣሉ፡፡ እነሱን መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መጽሐፎቹ እኛ እንደተረት እየቆጠርን የተውነውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግብፅ፣ ከግሪክ፣ ከሮማ፣ ከዕብራውያንና ከሌሎች ሀገሮች ጥንታዊ ጸሐፊዎች ማስረጃዎችን በመሰብሰብ በማስቀመጥ የሞገቱ ናቸው፡፡

 

[1] ለምሳሌ የታሪክ አባት የተባለው ሔሮዱተስ መዝግቦ ያስቀመጣው ማስረጃ የሚወራ የግብፅ ሥልጣኔ ምንጯ ኢትዮጵያ መሆኗን ነው፡፡

[2] ‘The Philosophy of History’, 2001, p. 117; ‘A Copamnion to African philosophy’, 2004፣ p. 33

[3] ዶ/ር ላጵሶ ጌ. ድሎቦ፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረቶችና መሣሪየዎች፡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የመነሻና የማንነት ግንዛቤ፣ (1999)፤ ገጽ 10-11

[4] አስረስ የኔሰው፣ ትቤ አክሡም መኑ አንተ፤ገጽ 122

[5] ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 132

[6]  The lack of evidence to support the south Arabian origin of Ethiopian history, in fact, places the proportion squarely into the realm of ideology and not of history. It is our contention that the paradim was an invention- an invention of 19th century imperial Europe. It was invented to facilitate the continued colonization, and present necolonization, of Africa by Europe or imperialism. (Ayele Bekrie, Ethiopic: an African writing system, p.34)

[7] ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ፣ አክሱም ዛጉዬ፤ ገጽ 42

[8]  ጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁ.11፣ 1990 ዓ.ም.

[9] ጦቢያ መጽሔት አምስተኛ ዓመት ቁ.3 1989

[10] J. Jackson,  (1939), Ethiopia and the Origin of Civilization,

Please follow and like us:
error

Leave a Reply