የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭነት፡- እውነት ወይስ ተረት?

(በዚህ ርዕስ በሚቀርቡ ተከታታይ ጽሑፎች የሚከተሉት ነጥቦች ማጠንጠኛ ይኾናሉ፡፡)

  1. የታሪክ አተያይ ችግር
  2. የዓለም ሥልጣኔ አንድ የጋራ መነሻ አለው?
  3. ‹ኢትዮጵያ› የሚለው መጠሪያዋ ከምን/ከየት መጣ?
  4. ከግብፅና ከኢትዮጵያ ሥልጣኔ የትኛው ይቀድማል?
  5. የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥፋት ከየት እስከ የት ነበር?
  6. የኢትዮጵያ ሕዝቦች እነማን ናቸው?
  7. ኢትዮጵያ ለዓለም ሥልጣኔ ያበረከተችው ምንድን ነው?
  •    እንደ መግቢያ

እንዳውም ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› ብላችሁ ካልተሳለቃችሁብኝ የዓለም ሥልጣኔ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት የሚል አስተሳሰብ ከሰረፀብኝ ውሎ አድሯል፡፡ ምን ላድርግ የግብፅን የጥንት ሥልጣኔ ያጠኑ የግብፅ ጥናት ሊቆች (Egyptologists)[1] ‹የጥንቱ የዓለም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥቶ እንደተስፋፋ ሞገቱኝ› ተስማማሁ፡፡ ስስማማላቸው ነው መሰል ‹ግብፅ የተመሠረተችው እኮ በጥንት ኢትዮጵያውያን ነው› ብለው ማስረጃ አቀረቡ፡፡ ‹ኧረ ተው!› ብላቸው የጥንቱን ከአሁኑ ጋር እያነጻጸሩ ‹እመን አሉኝ› እስቲ ቆይ ላስብበት ብዬ የሀገራችንን ትውፊቱን፣ ተረቱንና ባህሉንና መልካችንን ‹የጥንት ግብፅ ሥልጣኔ ነው› ከተባለው ጋር ሳነጻጽር ቁርጥ የራሳችን ኾኖ አገኘሁት፡፡ ከዚያም ባሰብከው መሠረት ‹ውሳኔህ ከምን?› አሉኝ ‹አመንኩ ተስማማሁ› አልኳቸው፡፡ እናንተ ጥርጣሬ ይዟችሁ ‹የውሳኔ እጅህ ከምን? አስረዳ!› ብላችሁ ከላዬ ላይ አልወርድ ካለችሁ ‹ግራ ቀኙን ተመልክቼ የውሳኔዬን ማብራሪያ ላቀርብ ነው፤ እነሆ!›!

ምናልባት ገና በመጀመሪያው ‹ሥልጣኔ ራሷ ምንድን ናት?› ብሎ የሚጠይቅ ነገር ሰንጣቂ ሰው አጋጥሞን እንዳንቸገር፤ ምንነቷን በጥቅል መልክ መናገር አይከፋም፡፡ ሥልጣኔ በጥቅል አነጋገር በጊዜው ካለ ማኅበረሰብ የተሻለ ኑሮ መኖር መቻል ነው፡፡ ከሥርዎ-ቃሉ አመጣጥ ስንነሣ የሥልጣኔ ምንነትን እጓለ ገብረ-ዮሐንስ ‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ› በሚለው መጽሐፋቸው ዲልማንን ጠቅሰው እንዳብራሩት ከሥልጣን (Authority) ጋር  ይያያዛል፤ እንደሳቸው  ከሆነ civitia ከሚለው ከላቲኑ አመጣጥ ትርጉም ጋር በማነጻጸር ሲገልጹ የላቲኑ ቃል ከተሜነትን ያመለክታል፤ ከገጠር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ማግኘትን  ያንጸባረቃል ማለት ነው፤ በሌላ በኩል  ግን የእኛን ‹ሥልጣኔ› የሚለውን ብንመለከተው ‹‹በአንድ ነገር ላይ ሥልጣን ማግኘት መያዝ ማስገበር ማለት ነው፡፡ ‹እስመ አንተ ሥሉጥ ላዕለ ኩሉ› በሁሉ ላይ ሥልጣን፤ ገዥነትን ያለህ ነህና›፤ ‹አግብርት ሠሉጠ ላእለነ› ባሮች በእኛ ላይ ሥልጣን አገኙ›› የሚለውን በመጥቀስ ገልጸዋል (እጓለ ገብረዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 32)፡፡ ይህም ማለት ሥልጣኔ የሚለው ቃል ገዥነትን፣ ሥልጣን ያለው መሆን፣ ልቆና ተሸሎ መምራትና ማስተዳዳር መቻልን ይገልጻል፡፡ ሥልጣኔ ስለሚለው ቃል ‹ኢትዮጵያ ቃል ለዓለም ማበደር ቢኖርባት የመጀመሪያ መሆን ያለበት ይህ ነው› ብለዋል፡፡

በተለይ ሊቁ የሥልጣኔን ምንነት በሚከተለው ገለጻ አምቀውና አሟልተው ገልጸውታል፤

  ‹‹ሥልጣኔ ማለት መጀመሪያ ሰው በሕሊናው ውስጥ ያሉትን ሀብታት መርምሮ ተረድቶ መሪነቱን ካወቀ በኋላ ዝቅተኛውን የስሜት ወይም የፍትወት ዓለም አርቆ ገርቶ ለሕሊናው ያስገበረ እንደሆነ በራሱ ላይ ሥልጣን ያለው የሆነ እንደሆነ የሚሰጠው ቅጽል ነው፡፡ ሁለተኛ በዙሪያው ያሉትን ሥነ-ፍጥረቶች ለራሱ እንዲያገለግሉ ለማስገበር የሚያደርገው ጥረትና ከዚያም የሚገኘው ውጤት ሥልጣኔ ይባላል፤ በመጀሪያው በኩል ያደረገው ምንም እንኳን የሚያጠራጥር ቢሆንም በሁለተኛው በኩል በጣም ርቆ ሔዶአል፡፡›› (ገጽ 36-37)

ስለዚህ ሥልጣኔን በአሁን ዘመን አስተሳሰብ ብንመነዝረው በኢኮኖሚ በልፅጎ፣ በፖለቲካ የተሻለ የመወሰን አቅምን አዳብሮ እና በዕውቀት አቅም በልጦ መገኘት አድርገን ልንወስደው እንችላለን፤ በድሮው ጊዜ ግንዛቤ ደግሞ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ አኗኗር ከሌሎች መሻልን ይገልጻል፤ መንፈሳዊ ክፍሉ የሃይማኖት አምልኮና ሥርዓት መሻሻልን፣ የሞራልና የሥነ-ምግባር ደረጃ መብለጥን ሲያመለክት፤ ሥጋዊ ክፍሎ የአሠራር ጥበቦችን፣ የአስተዳደር ሥርዓትን፣ የግንባታ፣ የሥነ-ጽሑፍ፣ የቅርጻ-ቅርጽ እና የአሣሣል መሻሻልን፤ በፍልስፍና፣ በትምህርት ሥርዓት መብለጥን ያመለክታል፡፡ በሌላ አገላለፅ ሥልጣኔ ከታሪክ ክሰተት ውስጥ የተሻለ አኗኗርን ገንዘብ ያደረገ ማኅበረሰብ ደረጃን የሚመለከት የዘመኑ የገዥነት ደረጃ ነው፡፡

ሀብታሙ አለባቸው ግን ሥልጣኔ ከዘመናዊነት ጋር በማነጻጸር ሥልጣኔን የጥንት የከተሜነት አኗኗር ሲያደርገው ዘመናዊነትን ደግሞ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ በአውሮጳ ተከስቶ ዓለምን እየመራ ያለ ሥርዓት እንደኾነ ይከራከራል፡፡ የሀብታሙ የሥልጣኔ ትርጉም የአገራችንን (ለምሳሌ የእጓለን) ሳይኾን የምዕራባዊያኑን መሠረት ያደረገ ነው፤ ዘመናዊነት በአገራን ‹ዘመነ› ከሚለው ቃል የወጣ ነው፤ ይህ ደግሞ ከጊዜ ጋር የተያያዘ ትርጓሜ ይኖረዋል፤ ስለዚህ ዘመናዊነት በጊዜ ሂደት የመጣ የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ ስለኾነም ሥልጣኔ የሥልጣን ባለቤት መኾንን፣ ዘመናዊነት ደግሞ ባለጊዜነትን የሚገልፅ ፅንሰ ሐሳብ መኾኑ መረዳት ጠቃሚ ይኾናል፡፡ አሁን ዙሪያ ገባውን መሽከርከሬን ልተወውና ወደ ዋናው ጉዳዬ ልግባ!

ይቀጥላል… ይቆየን! ያቆየን!

[1] የግብፅ ጥናት ሊቆች (Egyptologists) የሚባሉት ግብፅን የዓለም የሥልጣኔ መነሻ ናት በሚል የሚከራከሩ ምሁራን ናቸው፤ ለምሳሌ ከሀገራችን ምሁራን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ኢጂፕቶሎጂስት ነው፡፡

 

Please follow and like us:
error

1 COMMENT

Leave a Reply