የኢትዮጵያ ጀግኖች እንዲህ ተወድሰው ነበር፤ ዛሬስ?

 

 አጥንቱን ልልቀመው

አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣

ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣

ስመኝ አድሬያለሁ ትንትና ዛሬ፣

ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ፡፡

 

ተሰበሰቡና ተማማሉ ማላ፣

አሉላ ተትግሬ ጎበና ተ/ሸዋ/፣

ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣

አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሊያስተኩስ፣

አገሬ ተባብራ ታልረገጠች እርካብ፣

ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ፡፡

 

አራቱ ጉባኤ  ይነሡልንና፣

መኮንን ደረሶ አሉላ ጎበና፣

አገራችን ትማር አሁን እንደገና፡፡

ጎበና፣

ከፈረስህ ጋራ ተነስ እንደገና፡፡

(ዮፍታሔ ንጉሤ፤ 1927)

 *  *  *

 

 የኢትዮጵያ ድምፅ (?)

 

ደግሞ አንድ ጊዜ ስሙኝ ልንገራችሁ፣

ታላቆቹ ልጆች እንዳይሥቁባችሁ፣

አብረውን ነው ያሉ ሞቱ እንዳይመስላችሁ፡፡

 

ገና ሳስባቸው ልቤን ጨነቀው፣

እስኪ ስማቸውን በተራ ላንሣው፡፡

 

ይህ የልብ እመሜ ጥቂት ቢሻለኝ፣

ቶሎ ና ቴዎድሮስ አንተ ደግፈኝ፡፡

 

በግራ በቀኝህ ጠላት መቶብሃል፣

በፊትም በኋላ ደመኛ ከቦሃል፣

በል ተነሣ ታጠቅ ሞት ባንት ያምርብሃል፡፡

 

አሁንም ሙትልኝ ታጠቅ እንደገና

መቼም መች አይገድህ ሞት በጅህ ነውና፡፡

 

ቴዎድሮስን ልጄን ማንም አይደፍርህ፣

አንት ካልሞትህ በስተቀር ራስ በራስህ፡፡

 

ዮሐንስን ጥሩ እሱ ይያዘኝ፣

እስኪ ካሣን ጥሩ በል አንተ ያዘኝ፣

ቴዎድሮስን ወስዶ ከሣ አንተን ሰጠኝ፡፡

እጅግ ደስ ይለኛል ያንተ ስም ሲነሣ፣

የቁና ዐፈር ንፉግ አንተ ነህ ወይ ከሣ፡፡

 

ዮሐንስ ካሣህን ማን ሊችለው ነው፣

ከዘውድ ይልቅ ሞትክን አንት የመረጥኸው፡፡

እንዳንት ለድርጎ አፈር ንፉግ ሰው የለም፣

በደምበር ላይ ብትሞት አይደነቅም፡፡

 

በል ዕረፍ ዮሐንስ ጥራው አሉላን፣

ያንተ ግርፍ ነውና ያውቃል ዐመሌን፡፡

 

ይኸው ነጋ አሉላ ምጥዋ ገሥግሥ፣

አልወድም ባዕድ ሰው ከባሕር መለስ፡፡

 

ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ፣

አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡

 

ተኩላው ብዙ ነበር ምጥዋ ያለው፣

በነጋ በነጋ አሉላ አረደው፤

እነዚህ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው፣

አሉላ አነጣረህ ቶሎ አወራርዳቸው፤

አሉላ ፈረስህ እንዴት ሆዳም ነው፣

እንኳን ወንዛ ወንዙ ባሕርም አይገታው፡፡

 

እንዴት ነህ አሉላ የተዳሊ በር፣

አምስት ሺህ ገዳይ በአንድ ቀን ጀምበር፡፡

 

ክፉ ህልም አይቼ ሌት አልተኛሁኝ፣

አሁን ግን ተነጋ ጥቂት አረፍኩኝ፡፡

 

አሉላ አባ ነጋ መንገሻን ጥራው፣

ያባቱ ነውና ጋሻዬን ስጠው፡፡

አይከፈት በሩ መግቢያ መውጫችን፣

በል ተንሥ መንገሻ ግጠም በርበሩን፡፡

ይህንን ጎሽ ጠላ ማንም አይቀመሰው፣

 መንገሻ ዮሐንስ አንተ ገፍተው፡፡

 

ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ መጥተህ እይ፣

አኩስም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡

 

ምኒልክ ዝም አልክ ወይ ተኩሎች ከበውኝ፣

ረብልኝ ወዲያ እንዳይጮሁብኝ፡፡

 

ይህ ጫሂ አይጩህብኝ ሰው አይታወክ፣

ያላንት ዳኛ የለም ዳኛው ምኒልክ፡፡

ዐድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑ ለት፣

ምኒልክ ጎራደህ ወረደ ባንገት፡፡

 

ምኒልክ ወንድምህ እንዲህ ፈጣን ነው፣

መሪው አንተ እያለህ መኮንን ቃኘው፣

የጣሊያኖች ድርድር በገና ቢያምረው፣

መኮንን ወንድምህ በሾተል ቃኘው፡፡

 

እጅግ አንዣበበ ልናየው ፈራን፣

ልንገርህ ምኒልክ ሰጉድ ጋሻህን፡፡

 

ወንድምህን መኮንን የሚለው ሰው ማነው፣

እኔስ ባስተውለው ድንግል ባላገር ነው፤

በጣም ያሣፍራል ባሌጌ እንዳየኸው፣

ይህ ራስ መኮንን ውብ ገበሬ ነው፤

አላጌ ላይ ዘርቶ መቀሌ ዐጨደው፣

ዐድዋ ላይ ከምሮ መረብ ላይ ወቃው፡፡

ዐድዋ ገበያ ላይ ከጎንህ ነበርሁ

እኔም እኮ እናትህ መልካም ገበየሁ፡፡

 

ክብር ለመኮንን ሸመታ ረከሰ፣

ከዳጉሳው ይልቅ ጥሩ እህል ታፈሰ፡፡

 

እነዚህን በጎች ምን በታተናቸው፣

ተኩላው እጅግ በዝቷል አንት ኃይሌ አንድርጋቸው፡፡

 

ሁሉም መንገድህ ነው መሪም አያሻህ፣

አንተ አሠማራቸው አቦዬ በሻህ፡፡

 

ምኒልክ ዐድዋ ላይ አጥብቀህ ጠራህ፣

እስከ አውሳ በር ድረስ ተሰማ ድምፅህ፡፡

 

ዋናውስ በሽታ ምንም አልጎዳቸው፣

ካገገሙ ወዲያ ግርሻ ገደላቸው፡፡

 

ዳርጌና ጎበና መከዳ እያሉህ፣

ከዙፏንህ ዳኛው ማናነቃንቆህ፡፡

 

በመድፉ ጢስ ብዛት ሲጨልም አገር፣

ጎራደህ አበራ ከዳር እስከ ዳር፡፡

 

እንዳይጠፋኝ ስምህ እንዳልዘነጋህ፣

 አንተ ወልደ ጊዮርጊዘስ ዘወትር ላውሳህ፡፡

 

መድፋቸው ተርቦ አፉን ከፍቶ ቢያየው፣

አባተ አባ ይትረፍ ጥይት አጎረሰው፡፡

 

ብዙ ሰው አለቀ አድዋ ላይ በሰይፍ፣

ለምሳሌ እንዲሆን አንድ ሰው ይትረፍ፡፡

ምኒልክ ጥራልኝ ቶሎ ጣይቱን፣

እኔን ለመደገፍ ትችል እንደሆን፡፡

 

ምነዋ ተኮሰኝ ጣይቱ ገላሽ፣

እንዴት ነደሽ ይሆን አድዋ ላየሽ፣

እኔም በጣም ሞቀኝ አጥብቀሽ ተኩሽ፡፡

 

ገና ጣይ ስትወጣ እንዲህ ያላበው፣

ቀትርማ ቢሆን የት ሊገባ ነው፡፡

 

ወሌ የጣይቱን አይቶ ብርታቷን፣

ውሃም አልመረጠ ጠጣው ድፍርሱን፡፡

 

ፈክራ ፈክራ ምንም አልቀረች፣

አልፋ ከሴቶቹ ወንድ አሰለፈች፡፡

 

መድፉ መትረየሱ ምንም አልጎዳቸው፣

እንደ ጎመን ዝልቦ ጣይ አዛለቻቸው፡፡

(ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ፤ 1928)

 

(ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ፣ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ፤ ገጽ 76፣100-103)

Please follow and like us:
error

2 COMMENTS

Leave a Reply