የኦሮሞ ብሔርተኝነት ተፈታታኝ ተግዳሮቶች

(ዩሱፍ ያሲን፣ ‹ኢትዮጵያዊነት፣ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት›፣ 2009፣ ገጽ 254-267፤ ጽሑፉ ትንሽ እረዘም ቢልም በትግስት አንብቡት፤ በተለይ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ጥሩ ግንዛቤ ይሠጣል፡፡)

“ምንም እንኳን የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቀሴ የኢትዮጵያን አንድት ፈላጊ ኃይሎች ዘወትር የሚያባንን ክፉ ቅዠት ሆኖ ቢታይም እንቅስቃሴውን ተብትበው የያዙት የራሱ ተፈታታኝ ትግዳሮቶች እንዳሉትም መዘንጋት የለበትም፡፡ እስቲ ዋናዎቹ ናቸው ብዬ የገመትኳቸውን እዚህ ላይ ገረፍ ገረፍ እናድርጋቸው፤ ከሁለት እይታ አንጻር፡፡ ተግዳሮቶቹን ብሔርተኛ እንቅስቃሴው ዓላማው አድርጎ ከተነሳው መዳረሻ ግብ ወይም የኦሮሞ ነጻ ሪፐብሊክ ምሥረታን ከማሰናከላቸው አንጻር በመመልከትና በሌላ በኩል ደግሞ ተግዳሮቶቹ ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንድትቀጥል ካላቸው ፋይዳና አበርክቶ አኳያ በማየት፡፡ የአንዱ ዓላማ መሠናክል የሌለኛው ትልም ስኬት አጋዥ ፋክተር ሆኖ ያገለግላልና፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዋና ዋና ተፈታታኝ ናቸው ብዬ የገመትኳቸው ተግዳሮቶች፤

  1. የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አተገባበርና መዘዞቹ፣
  2. ወደ ቀድሞ ባሕላዊ ትድድራቸው የመመለሱ ጉዳይ፣
  3. የተጠቃሽ ተፎካካሪ ባላንጣ አፈጣጠር፣
  4. የኦሮምማ አይዶሎጂ፣
  5. የኦሮሚፋና የአማርኛ አጠቃቀምና ፉክክር፣
  6. የሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረስ፣
  7. አካባቢያዊና ዓለማቀፍ ኩነቶች ናቸው፡፡

ተራ በተራ እንያቸው፡፡

በአንድነት ጎራ የተሰለፉት ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል የሚሹና መበታተኗ የሚያሳስባቸው ወገኖች ሁሉ ተቃውሞ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች የኦሮሞን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አካሄድ የሚቃወሙበት የራሳቸው ምክንያቶች ይኖሯቸዋል፡፡ ለኦሮሚያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት (Self-Determination) ስትቆም እግረ መንገድህን የሌላውንም እጣ ፈንታ ጭምር እየወሰንክለት መሆኑነን መገንዘብ ሊያስፈልግ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተቃውሞ ከነዚህ ወገኖች የሚሰነዘር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችም የእነዚህን ወገኖች ሥጋት መገንዘብም ሊያስፈልጋቸው ነው፡፡ እንዴት? ማለት ያባት ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች የራሳቸውን የወደፊት ዕድል በራሳቸው መወሰን ይሻሉ፡፡ ልክ እንደማንኛውም ስብስብ፡፡ የኦሮሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ በሚኾንበት ወቅት ኦሮሞው እንደ አንድ ስብስብ የራሱን የወደፊት ዕድል ብቻ አይደለም የሚወስነው፡፡ እግረ መንገዱን የበርካታ ኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦችን እጣ ፈንታም ጭምር ነው የሚወስነው፡፡ በምርጫ ካርዱ አማካይነት ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ እድል አግኝተው በሪፈረንደም ለነጻ ኦሮሚያ ድምጻቸውን የሰጡለት ማለቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ካርታ ልብ ብላችሁ ተመልከቱት፡፡ በኦሮሚያ መሃልም ሆነ በሰሜን የአማራ፣ የአፋር፣ የትግራይና የቤንሻንጉል ክልሎች አሉ፡፡ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልና የጋንቤላ ክልሎች ይገኛሉ፡፡ ኦሮሞዎች ለነጻ ኦሮሚያ ድምጻቸውን የሰጡ ዕለት የእነዚህ ሕዝቦችና ክልሎች ዕድልም ጭምር ይወስኑላቸዋል ማለት ነው፡፡ ከላይ ያሉት አራት ክልሎች ከታች ካሉት ሁለቱ ክልሎች ጋር (አብሮ ለመኖር) ቢፈልጉ እንኳን በአንድ አገር በአብሮነት የመኖር ዕድል በተግባር ከወዲሁ ተነፈጋቸው ማለት ነውና፡፡ በኦሮሞዎቹ ውሳኔ ምክኒያት፡፡ በደቡብና በምዕራብ ያሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰሜን ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ የመኖራቸው ፍላጎትና ዕድል በኦሮሞዎች ድምጽ ብቻ ተወሰነ ማለት ነው፤ በሌላ አገላለጽ፡፡ በምሳሌ ላስረዳ፡፡ የወላይታ ሕዝብ ከአማራና ከአፋር ጋር በአንድነት ተጠቃሎ የሚኖርበት መንግሥት መመሥረት ቢመኝ እንኳን አይቻለውም፡፡ የኦሮሞ ሪፐብሊክ ምሥረታ ኢትዮጵያን በሰሜንና በደቡብ ለሁለት ይከፍላታልና፡፡ ደቡብ ያሉ ብሔረሰቦች ሰሜን ካሉት ጋር በግዘታዊ አንድነት ለመኖር የነበራቸው ሐሳብና ፍላገት መና ሆኖ ይቀራል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ያልመከሩበትን ውሳኔ አለመቀበል ደግሞ የነዚህ ሕዝቦች መብታቸው ነው፡፡ አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነቱን ለመቃወም በተቃራኒው ውድቅ ለማድረግ ለአፀፋ መልስ መንቀሳቀሱም መብታቸው ነው፤ መቼም፡፡

በተራቸው ይህንን ያልወሰኑትን አለመቀበል መብታቸውን በመጠቀም የኦሮሞን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እኛንም ይመለከተናል ሊሉ ነው፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የኦሮሞ ጉዳይ ብቻ ላይሆን ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በደቡብና በሰሜን የሰፈሩት ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ውሳኔም ጭምር እንጂ፡፡… ስለዚህ ለሁሉም የሚያስማማ ሰላማዊ መፍትሔ ካልተገኘ በተለያዩ አናሳ መንግሥታት መካከል ወደማያበራ ሽኩቻ፣ ብጥብጥና የተጧጧፈ ቁሩቁስ ሊያመራ ይችላል ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል የኦሮሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰኑ ተግባር የእርስ በርስ ጦርነት ስጋት ሆኖ ጦሱ ለሁሉም የሚትርፍ አገራዊ ጉዳይ ሆኖ ቁጭ ይላል ማለት ነው፡፡ አገራዊ መበጣበጥ ማለቱ ሳይቀል አይቀርም፡፡ ተግዳሮት ቁጥር አንድ፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኞች እንቅስቃሴ ሐበሾች ከሚሏቸው በሰሜን ካሉት እንጂ ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በሰላም አብሮ ለመኖር ችግር ስለማያጋጥመው የአብሮነት ፎርሙላ ማግኘቱ አይገድም የሚል ክርክር ሊቀርብ ይችላል፤ ይህንን ስጋት ውድቅ ለማድረግ፡፡ ሲቀርብም እንመለከታለን፡፡ ‹ሐበሻ› ካልሆኑት ብሔረሰቦች ጋር ወደፊት በአንድነት ስለምንኖርባት አገር የምንደራደረውና የምንስማማው ግን ኦሮሚያ ሪፐብሊክን ከመሠረትን በኋላ ነው መባሉም አያስኬድም፡፡ የብዙዎችን ቀልብ ሊስብ የሚችል አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል አሳማኝ አቀራረብ አይደለምና፡፡ ሕይወት ሊኖረው እንደሚችል አንድ አማራጭ መቅረብ መቻሉ አጠራጣሪ ነውና፡፡ ‹ሐበሻ› ካልሆኑት ጋር የሚኖረው የአብሮነት ፎርሙላ ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡ ለኦሮሚያ ሪፐብሊክ ምሥረታ በውሳኔ ሕዝብ ከተረጋገጠ በኋላ አይደለም፡፡ ርእሰ ጉዳዩ ከተወሰነ በኋላ የሚደራደሩበት መናኛና ዝልዝል ነገር አይደለምና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት መፈታት ይኖርበታል፡፡ በነገራችን ላይ ለነዚህ (ሐበሻ ላልሆኑት) ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተፎካካሪ ባላንጣ ሓበሻም አማራም ላይሆን ይችላል፡፡ እንዳውም በተቃራኒው ተፎካካሪ ባላንጣቸው ራሱ ኦሮሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦሮሞዎች ከሁሉም የተሻለ ታሪካዊና የቅርብ ግንኙነት አለን የሚሉት ከሲዳማ ብሐየረሰብ ጋር ነው፡፡ ኦሮሞ በታሪክ ሂደቱ በመስተጋብሩ ከእሱ ውጭ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ሲዳሚቲ ብሎ የሚፈርጀውና የሚጠራው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ተጠቃሽና ተፎካካሪ ባላንጣው ማን እንደመሆነ አመልካች ነው ለሶሻል አንትሮፕሎጂስቶቹ፡፡ በኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይሎች አባባል ሓበሻ ካልሆኑት ኢትዮጵያውያን ስብስቦች ጋር አብረን ለመኖር እንችላለን ብሎ መተለምና ይህንን ከእሱ ጋር በቅድሚያ ተነጋግሮ በስምምነት በመድረስ ወደ ተግባር መቀየሩ በጣም ለየቅል የሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሐበሻ ከተባሉት ጋር በአንድ መንግሥት ማዕቀፍ አብሮ የሚያናኑራቸው አሳማኝ ምክንያት በግልጽ አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን ከቀሪዎቹ ጋር በምን አይነት የአብሮነት ቀመር መኖር እንደሚቻል የቅድሚያ ስምምነት አለመገኘቱ ለኦሮሞ ብሔርተኝት ራሱን የቻለ ተግታሮት ነው፡፡ ተግዳሮት ቁጥር ሁለት፡፡

ይህ ክርክር ወደ ሌላኛው ተዛማጅ ሙግት ያመረናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአንዳንድ ብሔርተኛ ወገኖች፣ ኦሮሞ ግንድ እንጂ ቅርንጫፍ አይደለምና ኦሮሚያን እንመሠርታለን እንጂ አንገነጠልም ሲባል ሳይገነጠሉ ሌላ አዲስ መንግሥት ማቋቋም እንዴት እንደሚቻል ግልጽ አይደለም፤ ለብዙዎቻችን፡፡ ለአንዳንዶችም ኢትዮጵያ ስሟ ብቻ ወደ ኦሮሚያ ይቀየራል የሚል ትርጉም ነው የሚሰጠው አባባሉ፡፡ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አባላት ሁሉ በሞጋሳ ወይም በጅምላ ጉዲፈቻ ይወስዳሉ ወይም ኦሮሞዎች ጋር ይዋሃዳሉ ማለት አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ እንደ አገር ኦሮሚያ ትባል የሚል ሐሳብ አልፎ አልፎ ይሰማል፡፡ ይህም ለኦሮሞ ወገኖቻችንም ሆነ ለቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ግራ የሚያጋባ የግብ መዳረሻ ንድፍ ነው፡፡ በተለይ የሁሉም ስምምነት ካልታከለበት ራሱን የቻለ ተግዳሮት ነው፡፡ ተግዳሮት ቁጥር ሦስት፡፡

ለኦሮሞ ብሔርተኞች እንደ መልካም አርአያና አብነት የሚመለከቷቸው በቅርቡ ነጻነታቸውን የተቀዳጁት ገረቤት ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ሁሉም የራሱን ጎጆ ቀልሶ በሰላም ለመኖር የተደረጉ ሙከራዎችን ለመድገም የሚያስመኙ ምሳሌዎች ሆነው አልተገኙም፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያም ሆኑ ሁለቱ ሶዳኖች በሰላም በጎን ለጎን ጉርብትና መኖር እስካሁን አልተቻለም፡፡ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ስለባልና ሚስት አለመግባባት እንደሚያንጎራጉረው፤

…አብሮ መኖር ካላልን፣ እስቲ እንሞክረው ደሞ ተለያይተን…

ዓይነቱ የመፍትሔ ሐሳብ በመለያየት በቀላሉ የሚገላገሉት ጉዳይ ሆኖ አልተገኘም የአዳዲስ መንግሥታት ምሥረታ፡፡ መቼም አገር መገነጣጠል በትዳር ጥንድ ውስጥ እንደሚያጋጥመው ያልተመቸው ወገን የራስ ጎጆ ቅለሳ ሊቀል አይችልም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደ መልካም አገነጣጠል አብነት የተወሰደው የቼክና ስሎቫክ ሁለት ሕዝቦች በተረጋጋ ሥነ ሥርዓት ፍቺውን አጠናቀው የቸክ ሪፐብሊክና ስለቫኪያ ግን ለጎን በጉርብትና ኑሯቸውን የቀጠሉበት በአፍሪካ ቀንድ ሲሠራ አላየንም፡፡ በሱዳንም ሆነ በኤርትራ እስካሁን ሰላማዊ ጉርብትና አልተሳካም፡፡ በመሆኑም የሚበረታቱ አብነቶች አይደሉም፡፡

የኦሮሞ የነጻነት ተጋድሎ ዋና ምንጭ በሆነው በአፄ ምኒልክ ማስገበርና መስፋፋት አማካይነት የኦሮሞ መሬት በሐበሻ ቅኝ ግዛትነት የመያዙ ትረካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ‹ወረራ› የተያዙትን መሬቶች የማስመለስ አፀፋ ጊፊትና የወራሪነት ክስ ተደቅኖበታል፡፡ አፄ ምኒልክ በ16ኛው ምዕተ ዓመት በኦሮሞዎች የተወረሩ መሬቶችን ነው በተራቸው እንደገና የመለሱትና ከግዛታቸው ጋር ያዋኸዱት የሚል አፀፋ ሙግት አጋጥሟል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛ ወገኖች ኦሮሚያን ነፃ የማውጣት ተልኳቸውን ከአፄ ምኒልክ የ19ኛው ምዕተ ዓመት ቅኝ ግዛታዊ የአፀፋ ሙግትና እሰጥ አገባ የሚገጥሟቸው፡፡ አንዱ በቅኝ ግዛትነት ያዝከን ስላለው ሌላኛው ‹በታሪክ አጋጣሚ ቅድመ አያቶችህ ካያቶቼ በወረራ የነጠቁትን የራሴን መሬት ብቻ ነው መልሼ የወሰድኩት ብሎ ክርክር ይገጥመዋል፤ የአፄ ምኒልክን ግዛተ አፄ መስፋፋትና *ላ… የወሰደውን የአባቴን መሬት ለመውሰድ እየጣርኩ ነው› ማለታቸውን መሠረት በማድረግ፡፡ ይህ ሙግትና ክርክር ዛሬ እንደገና ነፍስ በመዝራት እንደተጋጋለ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከቦታው ያልተንቀሳቀሰ ወገን ወይም ስብስብ የለም፤ በረዥም ታሪካችን፡፡ በአንድ የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ሁሉም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ፈልሷል፤ ሌላውን ገፍቶ ከመሬቱ አስለቅቋል፤ አፈናቅሏል፡፡ በዚህ ክርክርና የአፀፋ ክርክር መጠመድ ማለት ጎን ለጎን በመልካም ጉርብትና በሰላም መኖሩ ቀርቶ በምትኩ ለብዙ ዓመታት በማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥና ቁርቁስ ውስጥ የሚገቡ ተገዳዳይ ትናንሽ አሃዶችን ለመፍጠር መሞከር ነው፡፡ አስፈሪው ስጋት እሱ ነው፡፡ ለማንም ወገን አዋጪ የማይሆን አተረማማሽ አማራጭ፡፡ ተግዳሮት ቁጥር አራት፡፡

አንድ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ከራሱ ማንነት በተፃራሪነት ተፋጦ የቆመ ተፎካካሪ ተጠቃሽ ጠላት ምስል ያበጃጃል…፡፡ በኦሮሞ ብሔርኛ ትግል ሂደት ውስጥም ይህንኑ ነው የምንመለከተነው፡፡ በትግል ሂደት በየታሪክ መጋጠሚያ ላይ ጥርስ የገባ ተፋጣጭ ተፃራሪ ማንነት ተፈልጎ መፈረጁ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሚፋጠጡ ሁለት ማንነቶች ናቸው፡፡ ይህም በየጊዜው እንደሚለዋወጥ አስተዉለናል፡፡ የችግሩ አንዱ መንስኤ ተለዋዋጭነቱ ነው፡፡ የትክክለኛው ባለጊዜ ተፎካካሪ ማንነት አሻሚ የመሆኑን ጉዳይም ተገንዝበናል፡ የማንነት ድንበሮችም ቋሚ ሳይሆኑተለዋዋጭና በየጊዜው የሚታደሱ ናቸው፡፡ የሚታደሱትም በኅበራዊ መስተጋብሮች አማካይነት ነው ይሉናል የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች፡፡

ሐበሻነትን እንደ ተፎካካሪ የጠላት ምስል ማቅረቡ ራሱ የሚደቅነው ተግዳሮት አለ፡፡ ሓበሻ የሚለው ስያሜ ትርጉም አሻሚነት አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው፡፡ ሓበሻ እንደ ተፎካካሪና ተጠቃሽ ባላንጣ ከተቆጠረ፤ የቃሉ ፍች ለብሔርተኞች ግልፅ መሆን ይኖርበታል፡፡ በኦሮሞ ትረካ ተፎካካሪና ተጠቃሽ ባላንጣዎች እየተቀያየሩ መጥተዋል፡፡ በአንድ ወቅት ነፍጠኛ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ሐበሻ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም አሁን የመንግሥት መዘውርን ተቆጣጥሮ የኦሮሚያን ሃብት በመዝረፍ ላይ ያለው ሌላ ወገን ነው ከሚለው ግንዛቤ በመነሳት ይመስለኛል፡፡ የተመረጠው ሐበሻ የተባለው ተፎካካሪ ጠላት ምስል አማራና ትግራዊን አጣምሮ በአንድነት እንዲይዝላቸው ተፈልጎ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ አጠራሩ የጠላትን ወይም የተፎካካሪን ጎራ ከማጉላቱ በተጨማሪ በርካታ ፍቺና ትርጉም በማካተቱ ትክክለኛ ትርጉሙ አሁንም ለሁሉም አሻሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ስያሜ በተለይም ዛሬ ዛሬ በዲያስቦራው አካባቢ የኦርትራ ከበሣ ትግርኛ ተናጋሪዎችን አካታች የሖነ ባሕላዊና ቅርስ ውርሳዊ አቃፊ ደጋፊ መለያ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው፡፡… ተፎካካሪ የባላጋራ ምስል በደበዘዘ ቁጥር ብሔርተኛ እንቅስቃሴው ከዓላማው በስተኋላ ሊያሳልፈው የሚችለው ኃይል ቁጥር በዚያው መጠን ያንሳል ነው አስተምህሮው፡፡

የዛሬ 19 ዓመት ገደማ በከተብኩት… ‹ሓበሻ ማን ነው፤ማንስ ነው ያልሆነው?› የጦቢያ መጽሔት መጣጥፍ ስምንት ትርጉሞችና ፍቺዎች እንዳሉት ለማስረዳት ሞክሬ ነበር (ጦቢያ ቅጽ 5 ቁ. 4፣ 1989 ገጽ 33)፡፡  እንደዚህ ዓይነት ባለ ብዙ ፍቺና አሻሚ ንባበ ቃል ለተፎካካሪ ባላንጣነት ማገልገል መቻሉ ደግሞ ሲበዛ አጠራጣሪ ነው፡፡ የአይዶሎጂ ጉዳይም እንዲሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ሆነ አዲሱ የሐበሻ አካታችነት ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የሚያዋህድ የአስተሳሰብ ርዕዮታለምና አሰባሳቢ መጠሪያ ለመሆን ከበቁ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ነን የምንለው ምልዓተ ሕዝብ በአንድ ላይ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ይሰለፍባቸዋል፡፡ በሌላ አባባል፣ ለኦሮሞ እንቅስቃሴ ወገን ይቀንስበታል፤ የጠላትን ጎራ ያጠነክርበታል፡፡ ኦሮሙማ ለኢትዮጵያ አቻ ተፊካካሪ አይዶሎጂ ሆኖ ነጥሮ መዉጣት መቻሉ ላይ ነው ጥያቄው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት እንደ አይዶሎጂ ትክክለኛው ይዘቱ ምን እንደሆነ የራሱ ችግር ያለበት አመለካከት መሆኑ አሌ ባይባልም ከኦሮሙማ ጋር ሲነጻጸር አቃፊ ደጋፊ ማንነቱ ይበልጥ አሰባሳቢ መሆኑ ግን ሊካድ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ዳር ድንበሩ በማያሻማ አኳኋን ታውቆ የተሳለ ተፎካካሪና ተፋጣጭ ‹ሌላኛው› ባላንጣ በመሆን የሚያገለግል ማንነትም ሆነ አይዶሎጂ የመፍጠር ችግር እንዳጋጠመው አስተውለናል፡፡ ይህ ደግሞ እስካሁን ያልተሳካ ተግባር ነው፡፡ ተግዳሮት ቁጥር አምስት፡፡

ኦሮሚፋ በየትኛው ፊደል ይጻፍ የሚለው ክርክር እልባት የተበጀለት ይመስላል፤ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ አዲስ ለተቋቋመው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) አመራር ኦሮሚኛ በግእዝ ፊደል እንዲጻፍ የጠየቀበት ግልጽ ደብዳቤ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ዛሬ በኦሮሞዎች መሃል የኦሮምኛ በላቲን ፊደል መጻፍ አማራጭ ከቶም አነጋጋሪ አይመስልም፡፡ ራሳችንን ካላተለልን በስተቀር የምትለዋን ሐረግ ልጨምር መሰለኝ፡፡ ዛሬ ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች አመዛኙ የሚጻፉት በላቲን ፊደል ነው፡፡ ኦሮሚፋ የላቲንን ፊደል ከመምረጡና በእሱ ከመጻፉ በፊት ይህ አማራጭ እንደ ፀረ አገር የሚቆጠርበት ዘመን ያከተመ ይመስላል፡፡ ዛሬ ጥያቄው ኦሮሚፋ በየትኛው ፊደል ይጻፍ ሳይሆን ቋንቋው የሥነ ጽሑፍና የአገልግት ቋንቋ በመሆን ለአገሪቷ ሁለተኛ ኦፊሴላዊ ቋንቋነት የሚበቃባቸው አግባቦች እንዲመቻቹለት ነው፤ የብሔርተኞቹ ፍላጎት፡፡ በዚህ ዓቢይ አገራዊ ጉዳይ ላይ የአንድነት ኃይሎች ትክክለኛ አቋም ግልጽነት የጎደለው ነው ቢባል ከእውነት አራቅንም፡፡ ስለዚህ ይበልጥ አነጋጋሪው ርእሰ ጉዳይ ቋንቋው ወደፊት ሊያጋጥሙት የሚችሉትን አደናቃፊ መሰናክሎች መጠራረግ የሚቻልበት መንገድ ነው፡፡ በኦሮሞ ብሔራዊ እንቅስቃሴ አራማጆች አስተሳሳሪና አገናኝ ሊባሉ ከሚችሉት እሴቶች አንዱና ዋነኛው የኦሮምኛ ቋንቋ ተጋሪዮስ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ቋንቋ መግባቢያ ብቻ አይደለም፡፡ የማንነት መገለጫም ጭምር እንጂ፡፡ በኢትዮጵያ የቋንቋዎች አጠቃቀም የማንነት ዋና ቀራጭነቱ በሚገባና በማያሻማ መልኩ ይታያል፡፡ ባለፉት ዘመናት የኢትዮጵያ መንግሥታት በአንድ ግለሰብ መሪ ወይም ንጉሥ እንደተጠረነፉት ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ሕዝብ ወካይነት መታወቃቸው አሌ የማይባል ነው፡፡ ለኦሮሞ ብሔርተኞች ደግሞ የኦሮሞ ቋንቋንና የብሔረሰብ ወገንተኛነትን የማደራጀት መርሃቸው በማድረግ የሁለተኛ ቋንቋነት ክብርና ማዕረግ ቢቀዳጅ እንኳ ከአማርኛ ጋር መወዳደርና መፎካከር መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ በብሔራዊ ቋንቋነት አማርኛን መተካት መቻሉ ደግሞ ለጊዜው አይታሰቤና የትየለሌ ነው፡፡

በአልጀሪያ ዓረብኛ ፈረንሳይኛን በቅጡና በወጉ ለመተካት ለብዙ ዘመናት እንደተሳነው ማለት ነው፡፡ ከ54 ዓመት አገራዊ ነጻነት በኋለ እንኳን የ132 ዓመታት ቅኝ ግዛትነት ካልቸራዊ ቅርስ ውርስን መተካት በአልጀሪያ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያውም አልጀሪያውያኑ ዓረብኛን የመሰለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመደበ ቋንቋ ባለቤት ሆነው፡፡ ለአገሪቱ አረባዊ ብሄርተኝነትና ማንነት ይህንኑ የቅኝ ግዛትነት ቅርሰ ውርስ ማሽቀንጠር አለመቻላቸው አንድ ተግባራዊ ተግዳሮት ሆኖ ነው እስከ ዛሬ የዘለቀው፡፡ ይህም ገና ለረዥም ጊዜ የሚቀጥል ጉዳይ ይመስላል፡፡ ኢንፓየር ስለፈረሰ ብቻ በአንድ ጀምበር መነቀል የሚቻል ጓዝ ቀላል ቅርሰ ውርስ አልሆነም፤ ቋንቋዎችን መተካት፡፡ ፈረንሳይ ቅኝ ግዛታዊ ኢምፓየሯን በእውንና በተጨባጭ ከአጣች በኋላም ጭምር ፈረንሳይ እሴታዊ (የባሕላዊ) ኢምፓየርነቷን እንዳለ ቀጥላለች የሚባለው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ ዓይነተኛ ምሳሌ ተደጋግሞ የሚጠቀሰውን ‹ፈረንሳይና ቋንቋ ከቅኝ ገዥዎቼ የነጠቅኩት የጦር ምርኮዬ ነው› ያለውን አል ካቲብ ያሲን የተባለውን እውቁ አልጀሪያዊ ጸሐፊ አባባል ማጤን ሊያስፈልግ ነው፡፡ እንደ አልጀሪያውያን ከ1956-1962 በተካሄደ ደም አፋሳሽ ተጋድሎ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛትነት ነፃነቱን በውድ ዋጋ ያስመለሰ ሕዝብ የለም ማለት ያስደፍራል፡፡ አገሪቷ የአንድ ሚሊዮን ሻሂ (ለአገሩ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠ ፃድቅ ሰው) አገር የምትሰኘውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

ኦሮሚፋ የአገሪቷን ሁለተኛ ቋንቋነት ሥፍራ (Status) ቢቀዳጅም እንኳ ቅሉ ይህንን ቦታ በቀላልና በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆናጠጥ መቻሉ አጣራጣሪነት አንዱ የኦሮሞ ብሔርተኞች የዘወትር የራስ ምታትና ስጋት ነው፡፡ የቁጥር በላይነት ባለቤቶች ቢሆኑም ቅሉ የካልቸር በላይነት መቀዳጀት መቻላቸው አጠራጣሪነት ምንጩ አማርኛን ለዘመናት ከተቆጣጠረው ካልቸራዊ ገዥ መሬት በቀላሉ ማስለቀቅ የመቻሉ ምናልባትነት ነው፡፡ ከነጻ ኦሮሚያ በስተቀር የእነሱ የካልቸር በላይነት የሚረጋገጥበት ቦታ ሊኖር አይችልም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱ ፅንፍ የረገጡ ብሔርተኞች እንዳሉ ይታመናል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ የነደፉትን የኦሮሞ ሪፐብሊክ ምሥረታ አቋም የሙጥኝ ማለታቸውና ይህ የቋንቋና ብሎም የካልቸር ቀዳሚ ሥፍራ መቀዳጀት አስመልክቶ በፅንፈኛ ብሔርተኞች ላይ ያደረሰው ጥርጣሬ ነው፤ የስጋቱና ከነጻነት መለስ ሌሎች አማራጮችን አለመቀበሉ ግትርነት ምንጭ፡፡ ተግዳሮት ቁጥር ስድስት፡፡

ኦሮሞ በአገሪቷ ደረጃ አብላጫ ቁጥር ያለው ስብስብ ብቻ ሳይሆን አብላጫ ሙስሊሞችን ያቀፈ ብሔረሰብ ነው፡፡ ትክክለኛው ቁጥር ቢዋዥቅም ኦሮሞ ከፍተኛ የእስልምና አማኞችን በውስጡ ያካተተ ማኅበረሰባዊ አሀድ መሆኑ ከቶ አያጠያይቅም፡፡ ከጠቅላላ ሙስሊም ውስጥ በያዙት አብላጫና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም የወደፊት አቅጣጫ የሚወስኑት የኦሮሞ ሙስሊሞች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ያለ እነሱ ምርኩዝነት ሊያድግና ሊስፋፋ ስለማቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡… በአገራችን የማንነት ፖሊተካ የብሔረሰብ ማንነት ከሃይማኖታዊ ማንነትና ወገንተኛነት ብሔረሰባዊ ወገንተኛነት እየተፎካከረው መሆኑን ልብ ማለታችን አይቀርም፡፡ ከሙስሊም ሕበረተሰብ ለዲናቸው (ለሃይማኖታቸው) ቅድሚያ የሚሰጡ እየተበራከቱ፣ ባንፃሩ ደግሞ የብሔረሰባቸው ማንነት የሚበልጥባቸው እያነሱ ናቸው ወደማለቱ መደምደሚያ ባንደርስም የሃይማኖቱ ማንነት የበለጠ ግምትና ትርጉም እየተሰጠው የመጣበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ልብ እንላለን፡፡… ‹አላህ ለሙስሊም ወንድምህ ምን ሠራህ ብሎ ይጠይቀኝ ይሆናል እንጂ ለኦሮሞው ምን ሠራህ ብሎ አይጠይቀኝም› እንዳለው አማኝ አክቲቪስት ዓይነቱ ግለሰብ የትኛውን ማንነቱን እንደሚያስቀድም አነጋጋሪም፣ አጠያያቂም አይደለም፤ ግልጽ ነው ማለቱ ይቀላል፡፡

እስልምና እንደ አንድ ሁሉን ጠቅልል የእምነት ዘይቤ በመሠረቱ ለማንኛውም ብሔርተኛ ዝንባሌ ራሱ ተግዳሮት ሆኖ ይቀርባል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነትም እንዲሁ መጋፈጥ ያለበት ተፎካካሪ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የብሔረሰብ ማንነት ተቆናጦ የነበረውን ቦታ አሁን ደግሞ ሃይማኖታዊ ማንነት እየተቆጣጠረ መምጣቱን ልብ ማለት የግድ ተመራማሪ መሆን አያሻም እላለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በተራው በኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ የራሱን ተፅእኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡ የግድ ነው ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከላይ የተመለከትነው የቀድሞ የኦነግ ደጋፊ አክቲቪስት ዓይነቶቹ ብቻ አይደለም ለሙስሊማዊ ግደታቸው ቅድሚያ የሚሰጡት፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እስላማዊ መነቃቃትንና አዲሱን የሕዝበ ሙስሊሙ ማንነት ያለ ኦሮሞ ሙስሊም ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማሰቡ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ከሃይማኖታዊ ሙስሊማዊ ማንነት ጋር ውድድር ውስጥ ገብቷል ማለትም ያስደፍራል፡፡ ከኦሮሞ ብሔረሰብ በምሥራቅና በምዕራብ የሚኖረው አብላጫው ክፍል በእምነቱ ሙስሊም ነው ብለናል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ከወቅታዊው የሙስሊም መነቃቃት ጋር ያለው ተያያዥነት፣ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንንም የግድ ከግምት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለብሔርተኞቹ አሉታዊ ጎን አያጣም፡፡ ቅድሚያ ለሃይማኖቱ ወይም ለዲኑ የሚሰጥ ከሆነ ግለሰቡ አገራዊ ወይም ብሔረሰባዊ ማንነቱ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጫና ይኖራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ማንነት ላይ የበላይነት እየተቆናጠጠ መምጣቱን መካድ የማይቻል እውነታ ነው፡፡ እስልምና የኣማኞቹን ወንድማማችነት ስለሚሰብክና ስለሚያስቀድም ሁለቱ ማለትም እምነትና ብሔርተኝነት አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት ይጣረሳሉ፤ ይወዳደራሉ ዲኔን (ሃይማኖቴን) አስቀድማለሁ፤ ብሔሬን አስቀድማለሁ በሚሉት መካከል በሚጧጧፈው ግብግብ ውስጥ እንበለው፡፡ እነዚህን አስታርቆ መጓዙ ፖለቲካዊ ብልህነትን ይጠይቃል፡፡ ከሁሉ አቀፍ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ይልቅ የኡማው ወይም የሕዝበ ሙስሊሙን መብቶች ለማስከበሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ምእመን ደግሞ ለነጻ ኦሮሚያ መሥራቾች ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ መሰናክልም ነው፡፡

ከወቅታዊ የዓለማችን ችግሮች አንዱ ሆኖ የሚያተየውን የኢራቅን ኩርዶችን ብሔርተኛ ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰደው፡፡ ኩርዶቹ በእምነት እረገድ ልክ እንደ ኢራቅ ዓረብ ሙስሊብ ብቻ ሳይሆኑ ባመዛኙ ሱኒም ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ከዓረቦቹ አለያይ ስንጥቅ አድርገው የሚመለከቱት የኩርድ ቋንቋ ስብስብነታቸውን እንጂ ዛሬ ኢራቅ የተዘፈቀችበት የሱኒ-ሺዓ እርኩቻ አይመለከተንም ባዮች ናቸው፡፡ እዚያ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡም አይታዩም፡፡ በኢራቅ የሱኒ ሺዓ እርኩቻ ሃይማኖታዊ መገለጫዎች የኩርድ ብሔርተኛ እንቅስቃሴን አይመለከትም ማለት ነው፡፡ የኮርድ ብሔርተኞች አሰላለፍ አያሻማም ማለት ነው፤ በሌላ አባባል፡፡ በአገራችን የኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይሎች ኦሮሞ በቋንቋ ስብስብነቱ ብቻ እንዲሰለፍ ሙከራ ሲያደርጉ ቢታዩም ቅሉ ይህንን አሰላለፍ መስመር ማስጠበቅ ስለመቻላቸው ርግጠኖች አይደለንም፡፡ የኢራቅ ኩርዶች የቋንቋ ስብስብነት ማንነት ቁልጭ ብሎ እንደሚገለጸው ይህ በአገራችን ኦሮሞ ብሔርተኛ አሰላለፍ ረገድ ግልጽ ሆኖ አይታይም፡፡ ፖለቲካንና ሃይማኖትን (ፖሊቲሳይዝ) እስልምና እና ብሔርተኝነት መካከል በበርካታ ቦታዎች የተከሰተ አለመጣጣም ነው እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡…

ዛሬ ዛሬ፣ በአገራችን የሙስሊም ወገን ጥያቄና ቅሬታ ከጠቅላላው የኦሮሞ ቅሬታና የመብት ጥያቄዎች ጋር እየተመሰሰሉ የመጡበት ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ይህን ደግሞ ለአገሪቱ አንድነት አሉታዊምም አዎንታዊምም ሊያሳርፍ የሚችል የእምነት ስብጥር አድርገን ነው የምንመለከተው፡፡ በቁጥር ደረጃ አመዛኙ የኦሮሞ ሕዝብ በሃይማኖቱ ሙስሊም ነው ብለናል፡፡ ከኦሮሞ የሙስሊም ድርሻ እስከ 65% ድረስ ነው አንዳንዶቹ፡፡ 47% ነው ይላል የማዕከላዊ እስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት አሐዝ፡፡  የእስላማዊ ሃይማኖት ማንነት መገለጫዎች የበላይነት እየተቆናጠጡ ከመጡ የኦሮሞን ብሔርተኛ እንቅስቃሴ የሚደግፍ አካሃድ ሊሆን አይችልም የሚል ግምት አለ፡፡ በሌላ በኩል ሙስሊማዊ ወገንተኛነት ወደ ሙስሊም ጠቅለል መንገሥት ምሥረታ ጥያቄና ትግል ያመራል የሚል ግምት የለም፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሕዝበ ሙስሊሙን አስገንጥዬ አዲስ አገር እመሠርታለሁ ባይ የሃይማኖት ፖለቲከኛ መኖሩ በእጅጉ አጣራጣሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች በአንድ መንግሥት ሥር ለመጠቅለል የሚታገል አደረጃጀት ይኖራል ብሎ ማሰብ መቼም አዳጋች ነው፤ ከኢትዮጵያ መገንጠልን እንደ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያነገበ ሙስሊማዊ ፖለቲካ ኃይል ይኖራል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ አገራዊነት የሕዝበ ሙስሊሙን መብት ለማጎናጸፍ መሞከር እንጂ፡፡ ይህን ማለት ግን ኡማው ወይም ሕዝበ ሙስሊሙን አንድ አድርጌ በአላህ ሕግ ደንብ አስተዳድራለሁ የሚል ምኞትም ሆነ ትልም በልቡ ያደረ ወገን ሊኖር አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ሊኖር ይችላል፡፡ የአብዛኛው ሕዝበ ሙስሊም ድጋፍ አሰባስቦ ዓላማውን እግቡ ማድረስ ይሳካለታል ወይ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው አጠራጣሪው፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው በአላህ ፊት የሚጠየቀው ለሕዝበ ሙስሊሙ ወገንህ ምን ዋልክለት ተብሎ እንጂ ለተወለደበት ስብስብ ወይም ብሔረሰብ ምን አደረግክለት በመባል እንዳልሆነ እስካላመነ ድረስ ቅድሚያ ታማኝነቱ ለየትኛው ማንነት መገለጫ እንደሚሆን አጠያያቂ አለመሆኑ ሥዕሉን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡ በሌላ በኩል በኢሕአዴግ መር ሥርዓት በብሔረሰብ እንጂ በሃይማኖት መደራጀት የተፈቀደ አይደለም፤ በሌላ አባባል ክልክል ነው፡፡ በሙስሊሙ ዙሪያ የምንመለከታቸው ሃይማኖታዊ መነቀቃቶች ባመዛኙ በትውልድ ወይም በብሔረሰብ ማንነት ኦሮሞ የሆነውን ሙስሊም ወገን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ እስላም ወይም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ለይቶ የማይመለከት እስላም ለማንኛውም የቋንቋ (ብሔረሰብ) ማንነት የስጋት ምንጭ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ሐጂ ነጅብ መሐመድ ‹ኢስላም ከጎሣኛነት ጋር ሊጣመር አይችልም› በማለት በቅርቡ በሚኒሶታ የተናገሩት አቧራ አስረጅ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ በተለይ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ የደቀነው አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለአክራሪው ሙስሊም አማኝ፣ ወደ ገዳ ሥርዓት እመለሳለሁ ባይ ብሔርተኛ ኦሮሞ ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን በመሠረቱ የ‹ባዕድ አምልኮ› አቀንቃኝ ከመሆን አይዘልም፡፡ የኦሮሙማ ርዕዮተ ዓለም ከኢትዮጵያዊነት፣ ከሐበሻነት፣ ከአማራነት ብቻ ሳይሆን ከኢስላሙማ ጋርም ደጋግሞ ሲጋጭ መመልከታችን የሁለቱ ማንነት መገለጫዎች መጣረስ የሚያስከትለው አሳሳቢ አይቀሬ ውጤት ነው፡፡ ተግዳሮት ቁጥር ሰባት፡፡

በመጨረሻም ወደ ኦሮሞ ባህላዊ ትድድርና አምልኮ እንመለሳለን ባይ ብሔርተኛ ወገኖች ጉዳይ አለ፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ትድድርና ሃይማኖት በሚሉበት ጊዜ ደግሞ በተለይ ገዳና ዋቄፊና ማለታቸው ነው፡፡ ሁለቱን እንደገና ለመመለስ የሚያስቡና የሚታገሉ ካሉ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንደገና የመመለሱ ምኞት ለብሔርተኛ ስሜት ኮርካሪ መቀስቀሻ ከመሆን የሚዘል አይመስልም፡፡ ወደ ገዳና ዋቂፊቻ እንመለስ ባዮች ዛሬ በኦሮሞ ኅብረተሰብ ውስጥ ሚዛን የሚደፋ ኃይል አይደሉም፡፡ በተለይም በሙስሊም ወገን፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ አማኝ ሙስሊም አንድን ግለሰብ ወይም ስብስብ ለምን ወደ እስልምና መራኸኝ ብሎ የመክሰስም ሆነ የመወረፍ ጉዳይ የሚታሰብ አይደለምና፡፡ እንዳውም ያሰለመው ወገን እንደ መንገድ አመልካች ባላውለታው መመልከቱ አይቀሬ ነው፤ በእኔ አመለካከት፡፡ አስተማሪው ሐቀኛውን የአላህ መንገድ ስላመለከተ ምስጋና የሚገባው ሆሆተ ፅድቅ አመልካች ነውና፡፡

የእስላሚያ ኦሮሚያ መሥራቾች ይበልጡኑ ወደ እስልምና እንጂ ወደ ዋቂፊቻ ፊታቸውን ይመልሳሉ ብሎ ማመኑ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲያውም ኦሮሞ በእስልምና አጠንጣኝነት እንዲደራጅ ይገፋፉ ነበር ማለቱ ያስኬዳል፡፡ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የኦሮሞ ነፃነት እስላማዊ ግንባር መሥራችና መሪ ጃራ አባ ገዳ (አብዱል ከሪም አህመድ ኢብራሂም) ይህንን ዓላማ ከሚራምዱት አንዱ ነበሩ፡፡ እስላሚያ ኦሮሚያ በሚለው አደረጃጀት ሥር ነጻነቱ ኦሮሚያ በእስላማዊ ሕግ እንድትተዳደር የነደፉት እቅድ ካልሆነ በስተቀር ዋቂፊቻና ገዳ ሥርዓትን ለማስመለስ ሊታገል የሚችል ኃይል መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህንን እንደ አንድ ፖቲካዊ አጀንዳ ወይም ፕሮግራም አንግቦ የሚታገል ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡ አንዳንዶቹ ወደ ቀድሞ መመለሱን እንደ ዓላማ ማንገብ ብቻ ሳይሆን ከእነ አካቴውም የኢአማኝነት ምልክት አድርገው ስለሚመለከቱት አይቀበሉትም፡፡ እንዳውም ባላቸው ኃይል ሁሉ ይዋጉታል ማለት ወደ እውነታው ይበልጥ ያደላል፡፡ በተለይም በኦሮሞው ዲኑን አጥባቂ ሙስሊም ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፡፡ ትክክለኛው የእስልምና ብርሃን ፋና ጠባቂ ፀጋ አመላካች (ሁዳ) አድርገው የሚቆጥሯቸውን አስተማሪዎቹን ለምን እምነቴን እስልምና አስቀየራችሁኝ ብሎ አይወርፍም፤ አይከስምም፡፡ በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት በእየዕሑዱ በእየቅዳሜው እንባ ለእንባ እየተራጩ ከፍተኛ የእምነት መነቃቃት የሚያሳዩትም ራሳቸው ‹ጌታን ያገኙና ያገኛቸው› ምሩቃን አድርገው የሚመለከቱ እንጂ ወደ ቀደም የአያቶች ‹ባዕ አምልኮ› ለመመለስ የሚዳዱ አይመስሉም፡፡ ከኦሮሞ አማኝ ወደ ቀድሞ ገዳ ሥርዓትና ዋቂፊና የመመለሱ  በአማራጭነቱ ግምት ውስጥ ወደማይገባበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ብሎ መናገር አያዳግትም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ምንም እንኳን የዐፄ ምኒልክ ግዛት መስፋፋት ዘመቻ ውጤቶች የቆየው ታሪካችን፣ ባህላችን አስተዳደራችን አጠፉት የሚለውን መደምደሚያነ ግንዛቤ ተንተርሶ ቅኝ ግዛትነቱን ውድቅ ለማድረግ የተሳሳተ ትግል ሊሆን ይችላል እንጂ በአጠቃላይ ከዘመቻው በፊት የነበረውን ባህል፣ ትድድርና ሥርዓት ዳግም የመመለሱን ሂደትና ተግባር እንደ አንድ አማራጭ የነደፈና በምር የተያያዘ የኦሮሞ ፖለቲካዊ ኃይል ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ዛሬ ገዳ እንደ አንድ ሥርዓተ ትድድር እንደገና አንሠራርቶ ዳግም በእግሩ እንዲቆም ማስቻሉ አነጋጋሪ ነው፡፡ ወደ ባህላዊ እምነቱ የመመለሱ ጉዳይ ከብሔርተኛ ኖስታልጂያ የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያኑ ኦሮሞ አማካይ አማኝ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬም አላስብም፡፡ ተግዳሮት ቁጥር ስምንት፡፡

ምንም እንኳን በፕሮፌሰር መኩሪያ ቡልቻ የወደፊቱ የነጻ አገር ገላጭ ምልክቶች ተደርገው የሚቆጠሩት የኦሮሚያ ካርታ፣ ክልል ቅርፅ፣ ባንዲራና አርማ የመሳሰሉ ምልክቶች ሁሉ መልክ እየያዙ መምጣቸውን ቢያበስሩም፤ለብሔርተኛ ወገኖቻቸው የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ምሥረታ መሳካት ገና ገና ብዙ የሚጎድለው ንድፍ ነው፤ በእኔ አመለካከት፡፡ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሳይሆን በቅርቡ ኤርትሪያና ደቡብ ሱዳን ነጻነታቸውን ካወጁበት ሁኔታ እንኳን ለመድረስ ብዙ የሚቀረው ዕቅድ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ሲደመሩ እንደ ኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ከባድ ተግዳሮቶች የተደቀነበት ፕሮጀክት የለም ማለት ያስኬዳል፡፡ ይህ እምብዛም የሚያጠያይቅ አልመሰለኝም፡፡ እስካሁን ስምንት ተፈታታኝ ተግዳሮቶችን ከቅርቡ ዳስሰናል፡፡ ተግዳሮቶቹ ግን በነዚህ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ በርካታ ናቸው፡፡

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶው ‹በ1983 የአገሪቷ አስተዳደር ከአንድ ገዢ ቡድን ወደ ሌላ የተሸጋገረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኢምፓየርነት ሥርዓት ግን አልተቀየረም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ እስከዛሬም ከትናንቱ ኢምፓየርነት ባሕርይዋ አለመላቀቅ የኦሮሞ ሆነ የሌሎች ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ያሳያል፤ ብሎ በመግቢያው ከተንደረደሩ በኋላ ከዛሬ 41 ዓመት በፊት የኦነግ መሥራች የነበሩትን በርካታ አባላት ያካተተው አዲሱ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ አንድነት ማዕቀፍ ሥር ከሌሎች ጋር ለመሥራት መወሰኑን ይገልጻል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ልክ የብርጋደል ጀኔራል ከማል ገመቹ ቡድን ተመሳሳይ አቋም ይፋ ካደረገ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ይህ የኦሮሞን ነጻነት ወይም ነጻ ሕልውና ያላት አዲስ አገር ፈላጊዎች እንደሚያልሙት በቅርብ የሚሆን አይመስልም፡፡ ይህ ተጨማሪ ተፈታታኝ ተግዳሮት እንደሚደቅን አያጣያይቅም፡፡ ከዚህ በላይ ከተመለከትናቸው አገራዊ መሰናክሎች አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በኦሮሞ ብሔርተኞች ፍላጎት ላይ ድባባቸውን ያጠላሉ ነው፡፡ የእነዚህ አቋም በአገር ቤት ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የተዋሀሃዱት የኦሮሞ ድርጅቶች አቋም ጋር ሲነጻጸር ለኦሮሞ ብሔርተኞች በቀላሉ የሚታይ አቀበት ነው፡፡ ይህም ባንጻሩ ለኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች የማይናቅ ተጨማሪ ብርታት የሚሰጥ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ተግዳሮቶችን ከማጠቃለላችን በፊት ኦሮሞ በቁጥር የበዛ፣ በአካባቢው ሃብት የላቀ ከሆነ ለምን የኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይል ተገንጥሎ የራሱን መንግሥት የመመሥረትን አማራጭ ብቻ የሙጥኝ ይላል ለሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ በብሔርተኛ ኃይሉ በኩል አሳማኝ ምላሽ እስካሁን አላገኘንም፡፡ አቶ ሌንጮ ለታ እንደሚሉት እንደቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ይገነጠላል ወይስ ሁላችንንም ጠርንፎ ይቆጣጠረናል የሚል ስጋት አያንገላታቸውም፡፡ እንዳውም የኦሮሞ ብሔርተኞች የአንድነት አራማጆቹ ከዚህ ከሚያንገላታቸው መንታ ልቦና ራዕይ አልባነት ነፃ የሚወጡበትን ቀን ይናፍቃሉ፤ በጉጉት ይጠባበቃሉ እንጂ፡፡ ምክንያቱም እነሱ አገራዊ ልበ ልቦና ገዝተው በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሕይወት መጫዎት የሚገባቸውን ሚና እንደሚያመለክታቸው የዘወትር ምኞታቸውም ፀሎታቸውም ስለሆነ ነው፡፡ የኢምፓየሪቷን መፍረስ አስፈላጊነት ከመወትወት ባሻገር ኦነግም ሆነ ሌሎች ብሔርተኛ ድርጅቶች የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሥር ለመኖር የሚቻልበትን ሁኔታ አስረዱን ብለው ለሚሞግቷቸው የኢትዮጵያ ብሔርተኞች አሳማኝ ምክንያቶች መደርደር ሊኖርባቸው ነው፡፡ ኦሮሚያ በሕዝባ ብዛት፣ በእምቅ ሃብቷ ራሷን የመቻል አቅሟን ከመተማመኑ እርግጠኛነት ባሻገር ሊጠቀሱ የሚችሉ አሳማኝ  ምክንያቶችን ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኛ ኃይልም የኢትዮጵያዊነትን አይዶሎጂያዊ ይዘት በቅጡና በወጉ ማስረዳት መቻል ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ያለው የአሰባሳቢ ማንነት ሚና መጫወት የሚጠበቅበት እስከሆነ ድረስ፡፡ እነዚህ እሰጥ አገባዎችና ውስጣዊ ቅራኔዎችና ተፈታታኝ ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው የኦሮሞ ብሔርተኛ ትግል በጠቅላላው በኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ ጫና እንሚያሳርፍ ማንም የአገሪቷን እድገት የሚከታተል ታዛቢ አይስተውም፡፡ …”

 

Please follow and like us:
error

Leave a Reply