‹የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት›፤ ማንስ ነው አይደለችም የሚል?

የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት! please read this updated aricle in PDF

እንዳውም ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› ብላችሁ ካልተሳለቃችሁብኝ የዓለም ሥልጣኔ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት የሚል አስተሳሰብ ከሰረፀብኝ ውሎ አድሯል፡፡ ምን ላድርግ የግብፅን የጥንት ሥልጣኔ ያጠኑ የግብፅ ጥናት ሊቆች(Egyptologists)  ‹የጥንቱ የዓለም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥቶ እንደተስፋፋ ሞገቱኝ!› ተስማማሁ፡፡ ስስማማላቸው ነው መሰል ‹ግብፅ የተመሠረተችው እኮ በጥንት ኢትዮጵያውያን ነው› ብለው ማስረጃ አቀረቡ፡፡ አረ ተው ብላቸው ‹የጥንቱን ከአሁኑ ጋር እያነጻጸሩ እመን አሉኝ› እስቲ ቆይ ላስብበት ብዬ የሀገር ውስጡን ትውፊቱን፣ ተረቱንና ባህሉንና መልካችንን ‹የጥንት ግብፅ ሥልጣኔ ነው› ከተባለው ጋር ሳነጻጽር ቁርጥ የራሳችን ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከዚያም ባሰብከው መሠረት ‹ውሳኔህ ከምን?› አሉኝ ‹አመንኩ ተጠመቅኩ› አልኳቸው፡፡ እናንተ ጥርጣሬ ይዟችሁ ‹የውሳኔ እጅህ ከምን? አስረዳ!› ብላችሁ ከላዬ ላይ አልወርድ ካለችሁ ‹ግራ ቀኙን ተመልክቼ የውሳኔዬን ማብራሪያ ላቀርብ ነው›!

መቼም እንዳልኳችሁ ዋና የማስረጃ ምንጮቻችን የጥንት ታሪክ ሊቆች ናቸው፡፡ እናንተም በእነዚህ ሊቃውንት ዘገባና ማስረጃ እንደምትስማሙ እገምታለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ አምጣ ካችሁኝ ግን ‹እንዴት ብዬ?› ነው መልሴ፡፡ በዚህም ቢሆን መጀመሪያ ልትጠይቁ የምትችሉት ‹ለመሆኑ ዓለም አንድ የጋራ የሥልጣኔ ምጭ አላት ወይ?› የሚል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ልገምት የቻልኩትም ሊቃውንቱም ይህንን ጥያቄ ስለሚያነሱት ነው፡፡ ሆኖም እነሱ በመጨረሻ የደረሱበት መደምደሚያ ‹የዓለማችን ሥልጣኔ ከአንድ የጋራ መነሻ ፈልቆ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ፈሷል› የሚል ነው፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስም ያስቻሏቸውን የተለያዩ ማስረጃዎችም አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ማሰረጃዎች መካከልም የሥልጣኔ ቅሪቶች፣ የሥነ ተረት ማሳያዎችና የታሪክ ፍሰቶች ወደ አንድ አቅጣጫ በመምራት ቅድሚያውን ይይዛሉ፡፡

በሥነ ምድር ጥናት የዓለማችን ሥልጣኔ ከአንድ ከተወሰነ አካባቢ ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች መነሣቱን ማረጋግጥ የሚያስችሉ ብዙ ማስረጃዎች ማግኘት ተችሏል፡፡ በዚህም የጥንት ዘመን ሥልጣኔ ማሳያዎች የሆኑት የሐውልት አሠራር፣ የግብርና አጀማመር፣ የአምልኮ ሥርዓት፣ የጊዜ አቆጣጠር፣ የባህል ውርርስ፣ የልምድ ድርጊት … ተመሳሳይነት የሥልጣኔ መነሻ አንድ ስለመሆኑ መስካሪዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ከሥነ ምድር ጥናት በተጨማሪ የጥንት ጊዜ የሥልጣኔ አጀማመርን ለመመርመር ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው የሥነ ተረት  ጥናት (mythology) ነው፡፡ በዚህም የአንድ ማኅበረሰብ ትውፊት፣ ሥነ ቃል፣ ትረካ… ከሥነ ምድር ጥናትና ከተመዘገቡ የታሪክ ማስረጃዎች ጋር በማነጻጸር ይጠናል፡፡ የሥልጣኔ ምንጭን በሚመለከት በተደረጉ የሥነ ተረት ጥናቶችም ሥልጣኔ የጋራ መነሻ ያለው መሆኑን የሚመሰክሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ለምሳሌ የጥፋት ውሃ መከሰት በብዙ ማኅበረሰብ በተረት መልክ የሚተረክ ታሪክ መሆኑ መረጋገጥ ተችሏል፡፡ በዚህ ትረካም የኖህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በቻይናም ይተረካል፡፡ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የዐሥሩ አባቶች ታሪክ ከግብፆች ዐሥር አማልክትና ከከለደዊያን ዐሥር ነገሥታት ታሪክ ጋር ተመሳስሎ ተገኝቷል፡፡ (R.Noorbergen; Secrets of the Lost Races: the most controversial view of the past since, 1977; page 10-30) ይህም ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የጋራ መነሻ መኖር ብዙ ይናገራል፡፡

ከሥልጣኔ ቅሪቶችና ከሥነ ተረት ትሪካዎች በመነሣትም የዓለም የታሪክ ፍሰት በናይል፣ በጤግረስና ኤፍራጥስ፣ እንዲሁም በኢንዱስ ሸለቆዎች እየተያያዘ መስፋፋቱን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በዚህም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥታ፣ እነ ባቢሎንን ጎንፋ በሕንድና ቻይና እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ በኢንካና ማያ ተንሠራፍታ እንደነበር መረጋገጫ ከተሰጠባት ውሎ አድሯል፡፡

ሊቃውንቱ ‹ሥልጣኔ በዚህ መልክ ከአንድ አካባቢ መንጭታ ዓለምን እንዴት ልታጥለቀልቅ ቻለች? የትኛው አካባቢስ ነው መነሻዋ?› ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ይሁንና ምርምራቸውን ወደ ጥንታዊ መሠረት ሲወስዱት ሥልጣኔ ከአባይ ሸለቆ መፍለቋን ፣ ወደ ሌሎች የዓለማችን ክፍል ለመንሠራፋትም መነሻዋ የእኛዋ ኢትዮጵያ መሆኗን የተገኙት ማስረጃዎች ሁሉ እየመሠከሩ እንዳስቸገሯቸው (የማይታበል ሐቅ እንደሆነባቸው) መስክረዋል፡፡ እዚህ ላይ ዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤል ‹እብሮነት በኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ በ1984 ዓ.ም. ባሳተሙት  ድንቅ መጽሐፋቸው ከገጽ 4-5 ያስቀመጡትን ነጥብ ብጠቅስ ብቁ ገለጻ ይሠጠናል ብዬ አምናለሁ፡፡

‹የአባይ ሸለቆ የአባይ ወንዝ ውጤት ነው፡፡ የአባይ ወንዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ሥጦታ ነው፡፡ የአባይ ሸለቆም የመጀመሪያው ጉልህ ማኅበራዊ ሕይወት የተደራጀበት፣ የተፈጥሮ ክስተቶች ግንዛቤ ያገኙበትና የሰው ልጅ ጉልህ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሥነ ምግባርና የሣይንስ ሥርዓትና ምሥጢር የለየበትና በየፈርጁ ያደራጀበት ነው፡፡ መደበኛ ግብርና ማለትም ከብት ማርባት፣ አዕዝርት መዝራት፣ የመገልገያና የማምረቻ መሣሪያዎችን  ማምረት፣ አልባሳት መሥራት፣ ከብቶችን በወተት፣ በሥጋ፣ በትራንስፖርትና በእርሻ ምንጭነት መጠቀም፣ በመስኖ እርሻ መገልገል፣ በውሃ መጓዝ፣ በአንድ አምላክ ማምለክ፣ የጽሁፍ ባህል ማመንጨት፣ የሃይማኖት ካህን ማፍራት፣ አስከሬን ማቆየት፣ የጂኦሜትሪን ሳይንስ ማዳበር ወዘተ የመሳሰሉ ሁሉ ብልጭታዎች መጀመሪያ የታዩት በአባይ ሸለቆ ውስጥ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለመጀመሪያ የሠው ልጅ በተናጠል ሳይሆን በተደራጀ መልክ በተፈጥሮ ጋር በውል የታገለበትና በኋላም የሰው ልጅ ከራሱ ጋር መታገል የጀመረው በአባይ ሸለቆ አካባቢ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡›

የግብፅ ጥናት ታላቅ ምሁር የሆነው  ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅንም በአንድ ግጥሙ፡-

‹አስቀድሞ ሰው ሲፈጠር በዘፍጥረት በአፍሪካ አገር፣

እዚህ አሁን ባለንበት፣ በኖርንበት ክልል ነበር፡፡

ቀጥሎም ቋንቋና ፊደል፣ ልሣንም የፈለቀበት፣

የዓለም የሥልጣኔ እንብርት ይህችው የኛው ጦቢያ ናት፡፡› ብሏል፡፡

(ጦቢያ አምስተኛ ዓመት ቁ.3፣ መጋቢት 1989)

ይሁንና ሥልጣኔ ከአባይ መንጭታ ወደ ሌሎች ዓለማት ተንሠራፍታለች በሚለው አቋም ዙሪያ የሚነሡ ክርክሮች ስላሉ እነሱን ማየት አግባብ ይሆናል፡፡ በዓባይ የሥልጣኔ ምንጭነት ዙሪያ የሚነሱ ሦስት መከራከሪያ አቋሞች አሉ፡፡ እነሱም፡-

  1. የአባይ ሸለቆ ሥልጣኔ የኢንዶ ኤሮፓውያን ሥልጣኔ ውጤት ነው፤
  2. የታችኛው አባይ ሸለቆ ሕዝቦች የጀመሩትንና ያዳበሩትን ሥልጣኔ የላይኛው አባይ ሸለቆ ሕዝቦች ተቀብለው እያሻሻሉ ተጠቅመውበታል፤
  3. የላይኛው አባይ ሸለቆ ሕዝቦች የጀመሩትን ሥልጣኔ የታችኞቹ አባይ ሸለቆ ሕዝቦች ተቀብለው አሻሽለውታል የሚሉት ናቸው፡፡

ከእነዚህም አቋሞች መካከል የመጀመሪያው መነሻው የዘረኛ ነጮች አመለካከት የፈጠረው ዕይታ ነው፡፡ ምክንያቱም በእነሱ እሳቤ ጥቁር ሕዝቦች አስተሳሰባቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ቀድመው ሠልጥነው ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በ19ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው ዕውቁ ፈላስፋ ሄግልስ ‹አፍሪካ ለዓለም ታሪክ ያደረገችው የሚታይ የሥልጣኔ እንቅስቃሴ ወይም የምትካፈለው የልማት አስተዋፅኦ የላትም፤… የግብፅ ሥልጣኔም የአፍሪካን መንፈስ አይጋራም፡፡› ብሏል፡፡ “ (‹A Copamnion to African philosophy›፣2004፣ ገጽ 33)

በዚህ የሄግል መርህም በመመሥረት ‹አፍሪካ የሥልጣኔ ምንጭ አልነበረችም› በሚል አስተሳሰብ ሥልጣኔ ከአውሮፓ እየተነሳች ወደ አፍሪካ ጎርፋለች የሚል አቀራረብ ምሁራኑን ሊያጥለቀልቃቸው ችሏል፡፡ ይሁንና ይህ የታሪክ አቅጣጫን ከማስቀየስ ያለፈ ማስረጃ ያለው አይደለም፡፡ ይህንንም የማስቀየስ አስተሳሰብ ዶ/ር አየለ በከሪ the mindset responsible external paradigm ይሉታል፡- አስተሳሰብ በማራገብ የጻፉትን በመሞገት፡፡  የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክም አወዛጋቢ የሆነው ቀድመው በእዚህ እይታ አቅጣጫውን ስላስቀየሩትና በየገዳማቱ የሚገኙትን የታሪክና የትውፊት ምስክሮች እንደተረት በመቁጠር ስላጣጣሏቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አቋም የአባይ ሸለቆ ሥልጣኔ ‹የኢንዶ ኤሮፓዊያን ሥልጣኔ ውጤት ነው› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱ ማስረጃ የሌለው፣ በዘረኝነት ልክፍት የተገመተ፣ ተቀባይነት እያጣ የመጣ እሳቤ ነው፡፡

የሁለተኛው አቋም መነሻ ታችኛዋ ምሥር ናት፡፡ ማለትም የሥልጣኔ አየር ከታህታይ ግብፅ ተነሥታ በአባይ ሸለቆ ወደ ላዕላይ ወደ ኑቢያና አክሱም ነፍሳለች የሚል አስተሳሰብ መነሻው ነው፡፡ ለምሳሌ አባ ጋስፕሪን ገብረማሪያም ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹ግብፃውያን ከ2500 ዓመት ከጌታችን ኢየሱሰስ ክርስቶስ ልደት በፊት ጀምረው ወርቅና ሌላ ክብር ዕቃ ለመፈለግ በኒል አባይና አትባራ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ነበር፡፡ እነሱ የመጡበት ዘመን ኦሪት ከመጻፉ በፊት ስለሆነ የአገሪቱን ስም ኩሽ ብለውት ሄዱ፡፡ … እስካሁን ድረስ በግብፅ የሚገኙት የቀድሞ ዘመን ምስሎች ብዙዎቹ ከኢትዮጵያ በወሰዱት ወርቅ የተሠሩ ናቸው፡፡ … የቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን (የኩሽ ዘሮች) ግብፃውያን ከሀገራቸው እየተሰደዱ መጥተው በኢትዮጵያውያን ውስጥ ወርቅ የሚገኙባቸውን ቦታዎች እየፈለጉ በለቀምት፣ በሌቃ፣ በማጂ፣ በጉባ፣ በሸጎሌ እስከ ኦጋደን ድረስ የሚገኘውን የወርቅ ማዕድን እየፈለጉ ቆፍረው መውሰዳቸውን ካዩ በኋላ የወርቅ ማዕድንን ጥቅም ዐወቁ፡፡ እንዲሁም እየሠለጠኑ ከድንጋይ ዘመን ወደ ወርቅ ማዕድን ዘመን ደረሱ፡፡ ከዚህ በኋላም ጥቂት በጥቂት ወደ ነሐስና ወደ መዳብ ዘመን ደረሱ፡፡› ብለው አስቀምጠዋል፡፡  

በዚህ ገለፃ መሠረት ‹የጥንት ኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ ከግብፅ የመጣ ነው፤ ግብፆች ደግሞ ኩሾች አይደሉም፡፡› ይህ (የጥንት የኩሽ ሥልጣኔ ከታህታይ ግብፅ የመነጨ ነው የሚለው) አስተሳሰብ (መርህ) ግብፆች ጥቁር አፍሪካውያን አይደሉም በሚል የ‹ኢንዶ ኤሮፓውያን ሥልጣኔ የአባይ ሸለቆ ሥልጣኔ መሠረት ነው› ወደ ሚለው የሚወስድ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ‹የታህታይ ግብፅ የመጀመሪያዎቹ ነዋሪዎች ከየት የመጡ ናቸው?› ብለን ብንጠይቅ ለመልሱ የትውፊትም ሆነ የታሪክ ቅሪት ማስረጃ የላቸውም፡፡ በተለመደው የታሪክ ዘገባ የተቀመጠው ማስረጃ የሚያሳውም ተቃራኒውን ነው፡፡ ለምሳሌ ተበታትና የነበረችውን ግብፅ በማዋሐድ አንድ አደረጋት የሚባለው ሜነስ የላዕላይ ግብፅ ፈርኦን (ንጉሥ) እንደነበረ ብዙ የተባለለት ነው፡፡

የተለያዩ የታሪክ ማስረጃዎችም ሥልጣኔ እንደ ውሃዋ ከላዕላይ ተነስታ ወደ ታህታይ መፍሰሳን እንጂ ወደ ላዕላይ መወንጨፏን አልመሰከሩም፡፡ የግብፅ ሥልጣኔ ‹ከላዕላይ ግብፅ የመነጨ ነው› የሚለው መከራከሪያም ብዙ ማስረጃዎች ያሉት፤ በጥንት የግሪክ፣ የሮማና የአይሁድ የታሪክ ጸሐፊዎች የተጠቆመ፣ የሐውልት ላይ ጽሑፎችና ትውፊቶች (ሥነ ቃሎች) ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡ በእነዚህ ማስረጃዎችም በብዛት ተገልጾ የሚገኘው ሥልጣኔ ከላዕላይ ግብፅ መፍለቋን ነው፤ የላዕላይ ግብፅ ሥልጡንነት ደግሞ ከኢትዮጵያ የተገኘ ነው፡፡

ባንድ ወቅት የግብፅ ጥናት ሊቅ የሆነው ፀጋዬ ገ/መድኅን በጦቢያ መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ፡

 ‹አፍሪካ የመጀመሪያዊቱ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን፤ የቋንቋና የፊደል፣ የጽሑፍና የአሐዝ፣ የሙዚቃና የዳንስ፣ የቅርጻቅረፅና የሥዕል፣ ወዘተ መፈጠሪያ ምድር እንደመሆኗ የመጀመሪያይቱ የዓለም ባህል እናትነቷም ዛሬ በማያፈናፍን ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ዛሬ፣ የማንነቷ ጥያቄም ግልጥ ያለ መልስ ያገኘው በዚህ በሳይንሳዊ እውነታ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ …

ቅድመ-ታሪክ ጻሐፍት (antiquity historians) እንደነ ፕሉታርክ እንደነ ፕሊኒ ያሉ፣ ኋላም እንደነ ዲዮርዳኖስና እንደነ ሄሮዶቶስ ያሉ፣ ገና የግሪክና ሮማ ሥልጣኔዎች ከማበባቸው በፊት በካም አበው ሥልጣኔ ላይ ተመሥርተው የሰውን ዘር የሥልጣኔ አመሠራረት መመዝገብ የጀመሩት፡፡ ከደቡብ ምሥራቅ ሜዲቴራኒያ ማዶ እስከ ማዳጋስካር ባሻገር፣ ከሕንድ ውቅያኖስ በመለስ እስከ ቀይ ባህር ግራና ቀኝ ያለው ዝርያ፣ ካምም (ኩሽም) አልነው ጥቁር ግብፅ፣ ሳቢያም አልነው ኢትዮጵያ፣ ሀበሻም አልነው ኑቢያ፣ የአንድ የካም ዘር ግንድ ልጅ፣ የአንድ አጥንትና ደም ወንድምና እህት መሆናቸውን ደጋግመው ዘግበውታል፡፡….  በማለት አብራርቷል፡፡ (ጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁ.11፣ 1990)

ፀጋዬ በሌላ የጦቢያ ላይ ጽሑፉ ደግሞ ዦዥር ፖዠኔን በመጥቀስ፡

 ‹የካም እናት አቴቴ፣ የዛሬ ዐሥር ሺህ ዓመት በፊት፣ ከኢትዮጵያ ወደ ጥንታዊት ጥቁር ግብፅ ወረደች፡፡ ከዚያም ‹ããስ› (ኢሲስ) በኋላም ‹እሴት› (እሰይ) እየተባለች ወደ ግሪክና ሮማ (ላቲን) ተሻግራ ከአምስት ሺህ ዓመት በላይ ተመለከች፡፡ ባለብዙ ሺህ ስመ ውዳሴ (ዌዲሴ odyssey) ተባለች፡፡ ‹ኢስስ› ጌታ የሱስ ከተወለደ በኋላ እያደር ወደመረሳት ደረሰች፡፡ ቀጥሎም እመቤታችን ማሪያም የእመ ፀሐይ (ኢሲስ) አድባርን እጅግ ብዙ ስመ ውዳሴዎች እመ ብርሃን እየተባለች ወረሰች፡፡› ብሏል፡፡ (ጦቢያ መጽሔት አምስተኛ ዓመት ቁ.3 1989)

ማስረጃዎቻችን በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰኑ እንዳይመስሉ ስለ ኢትዮጵያ የጥንታዊ የታሪክ ምንጭነት አንዳንድ የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች የሠጧቸውን አስተያየቶች እንጥቀስ፡፡ ከእነዚህ ጥንታዊያን ምሁራን መካከልም የቢዛንታንያ ጆኦግራፊ ባለሙያ የሆነው እስጢፋኖስ የሰጠው አስተያየት ሊታለፍ የማይገባው ነው፡፡ እስጢፋኖስ ‹ኢትዮጵያ በመሬት ላይ ከሚገኙ ሀገሮች ሁሉ አምላክን ማምለክና በሕግ ሥርዓት መመራት የተጀመረባት የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን ዜጎቿም ማምለክንና በሕግ ሥርዓት መመራትን የጀመሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡› የሚል ቃል አስፍሯል፡፡

በዚህ ዙሪያ Ethiopia and the Origin of Civilization እና  Wonderful Ethiopians of Ancient Cushite Empire  የሚሉ መጻሕፍት ሰፊ ማብራሪያ ይሠጣሉ፡፡ እነሱን መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መጽሐፎቹ እኛ እንደተረት እየቆጠርን የተውነውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግብፅ፣ ከግሪክ፣ ከሮማ፣ ከዕብራውያንና ከሌሎች ሀገሮች ጥንታዊ ጸሐፊዎች ማስረጃዎችን በመሰብሰብ በማስቀመጥ የሞገቱ ናቸው፡፡

‹ኢትዮጵያ የዓለማችን የሥልጣኔ ምንጭ ናት› ብለን ስናወራ ንግግራችን አሁን ካለችው ኢትዮጵያችን ጋር ብቻ የተያያዘ ክልልን የሚያመለክት አይደለም፤ ከዚያም በላይ ሦስት አህጉራትን ጭምር ያካልል እንደነበር ነው ማስረጃዎቹ የሚመሰክሩት፡፡ እንዲሁም በጥንት ጊዜ ‹ኢትዮጵያውያን› የሚባሉት ጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ነበሩ፡፡ በጥቅል ሲቀመጥ የጥንት ኢትዮጵያ ከህንድ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ ያለውን ክልል ያጠቃልል ነበር፡፡ ከሀገራችን የታሪክ ምንጮች መካከል መሪ ራስ አማ በላይ ‹የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ› ከሚለው መጽሐፋቸው ካስቀመጡት መረዳት የሚቻለው ‹እስያ› የሚለው የአህጉር መጠሪያም የተወሰደው እፄ ሰንድቅ አልማ ከተባለው የኢትዮጵያ መሪ ሲሆን ትርጓሜውም ‹ታላቅ ሀገር› ማለት ነው (የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፣ ገጽ 41)፡፡

በዚህ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ነገዶች እንዴት በተለያየ አካባቢ ተበታትነው እንደሚገኙና መለያቸው ምን እንደሆነ ተብራርቶ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ስለ ባቢሎን፣ ስለ ሞርታኒያ፣ ስለ ታንዛኒያና የመሳሰሉት አገሮች በኢትዮጵያ ነገዶች እንዴት እንደተመሠረቱና እንደቀኑ ማስረጃ ይሠጣል፡፡ የኢትዮጵያ ስምም ኢትኤል ከሚለው የመልከጼደቅ ልጅ መሰየሙን ያብራራል፡፡ ትርጉሙንም ሲያስቀምጥ ‹ኢትኤል ማለት የአምላክ ሥጦታ፤ ኢትኦጵ ማለት ደግሞ የወርቅ ሥጦታ ማለት ነው› በማለት ይገልጻል፡፡ ኢትኤል ግዛት መሥርቶ መኖር የጀመረበት የግዮን ሥፍራም ‹ዮጵ› በሚባለው ወርቅ የከበረ ስለነበረ የእሱን ስም ‹ኢትዮጵ› የሚስቱ ስም ‹ሲና›ን ደግሞ ‹ኢንቆዮጳግዮን› ብሎ ቀይሯል፡፡ ከዚያም ‹ኢትኤል ግዮን ወንዙን ለወንዝ አጠራቅሞና ሰብስቦ እስከሚገናኝበት ያለውን ምድር ሁሉ በስሙ ኢትዮጵያ እንዲባል አድርጓል፡፡› (የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ፤ ገጽ 26)፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት ዘሮቹም በየሔዱበት ሥፍራ መሠረታቸውን ሳይለቁ ኢትዮጵያውያን እየተባሉ ተጠርተዋል፡፡ በዚህ የተነሣም ይመስላል ሦስት አህጉራት በአንድነት ኢትዮጵያ የሚል ስም ይጠቀሙ የነበረው፡፡

በዚህ ዙሪያም ከሰፈሩ ማስረጃዎች መካከል ሰር ዋሊሰ ባጅ የተባለው የጥንት ግብፅ ጥናት ተመራማሪ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለው የመጀመሪያ ክፍል መጽሐፉ መግቢያ ‹ሆሜርና ህሮዶቶስ የሱዳንን፣ የግብፅን፣ የአረብ፣ የጳላስጣይንና የእስያን እና የህንድን ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ብለው ይጠሯቸዋል፡፡› ብሏል፡፡ ይህንን የበለጠ ሲያብራራ ‹የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎችና የጂኦግራፊ ሊቃውንት ከግብፅ እስከ ህንድ ባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩትን ሕዝቦች በሙሉ ኢትዮጵያውያን በማለት ይጠሯቸው ነበር፤ ስለሆነም በዚህ ክልል የሚኖሩት ባለጥቁር ቆዳ (ጥቁር) ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ እነዚህን ኢትዮጵያውያንንም ምሥራቃውያንና ምዕራባዊያን በማለት በሁለት ይከፍሏቸው ነበር፤ ምሥራቃውያን የሚሏቸው እስያውያኑን ሲሆን ምዕራባውያን የሚሏቸው ደግሞ አፍሪካውያኑን ነበር፡፡› ብሎ አስቀምጧል፡፡ ባጅም ይህንን ያቀረበው ጋሽ ፀጋዬ እንደጠቀሰው የጥንቶቹን የግሪክን ሄሮዶቶስንና ኢፎሩስን፣ የሮማ ታሪክ ጸሐፊ ስትራቦን፣ የባዛንታይን ምሁር እስጢፋኖስን፣ … የመሳሰሉትን የጥንት የታሪክ ምንጮች መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ስለ አፍሪካ ስያሜም ተጨማሪ ነጥብ ማንሳት እንችላለን፡፡ አፍሪካ የሚለው አህጉርም ‹አፋር› ከሚለው ቃል ተወስዶ ሳይታወቅ በፊት መጠሪያው ‹ኢትዮጵያ› ነበር፡፡ በጥንት የአፍሪካ ባህል፣ ሥነ ልሳንና ሥነ ሰብ ጥናት የታወቀው ከላይ የጠቀስነው ምሁር ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ስለ አፍሪካ ስያሜ በጦቢያ መጽሔት ተጠይቆ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

‹አፍሪካ የተሰኘው የአህጉሪቱ ስም እንኳን የመነጨው ከካማውያን ፊደልና ስም ነው፡፡ አፍ ማለት ‹ምድር› ወይም በምድር ላይ ያለ ‹በቀልት› ማለት ነው፡፡ አፍ-ራካ ወይም አፍ-ሪካ ማለት ‹የእግዚአብሔርና የፀሐይ ንጉሥ ምድር› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አፋር ወይም አፈር የተባለው የአፋር ስም፣ ኦል-ኦፍ ወይም ዎል-ኦፍ ወይም ዘራፍ የምንለው የፉከራ ቃላችን፣ የዘር ግንዳችን መነሻ አፍሪካ መሆኑን በመንፈስ ኩራት ለመግለፅ ነው፡፡›  (ጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁ.11፣ 1990

ምንም እንኳን አቀራረቡና የመረጃ ምንጫቸው ቢለያይም ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ መረጃ አግኝተው ያቀረቡት መሪ ራስ አማን በላይም አፍሪካ የሚለው የአህጉሪቱ መጠሪያ ከአፋር እንደተወሰደ ይስማማሉ፡፡ እሳቸው፡-

‹ኦፊር የአፍሪካውያን አባት ለዛሬዎቹ አፋሮች አባት ነው፡፡ በኦፊር ስም ከዛሬው አውሳ የሚገኝ ወርቅ ኦፊር ይባል ነበር፤ ዋና ከተማው ተርሴስ ነው፤ እርሱም በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የታወቀ ወርቅ ስለነበረ የኦፌር ወርቅ ክቡር ነበር፤ በኦፌር ሀገሩን አፍሪቃ ሰዎችን አፍሪካኖ ይሉዋቸዋል፡፡› በማለት አስቀምጠውታል፡፡ (አብርሂት  2000 ዓ.ም. ገጽ 52)

በዚህ አገላለፅና ማስረጃ መሠረት አፍሪካ የሚለው ሰም ‹አፋር› ከሚለው መጠሪያ የተወሰደ ከሆነና አፋርም በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑም እሙን ከሆነ፤ እንዲሁም የጥንት አፍሪካ ስም በኢትዮጵያ የሚጠራ ከነበረ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ምንጭነት የሚቃወመው ማን ነው? አላዋቂ ወይስ ሌላ?

አረ! ጎበዝ አንዳንድ ጊዜ እንኳን የራስ የሆነን ነገር ማክበርና መመርመር ይልመድብን፤ ቢያንስ አይጎዳንም፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ችግር ግን የራሳችንን ጥንታዊ ታሪክ መጥላት ይመስለኛል፡- ለነገሩ ወደን ሳይሆን ኋላቀርነታችንን በማየትና በተመረገብን የአውሮፓ ማዕከላዊነት አስተምህሮ የተነሣ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ይህንን በዚህ ላቁምና ለሚቀጥለው ገዜ በኢትዮጵያ ነገዶች ዙሪያ የምለው ይኖረኛል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ማን ነው? የዚያ ሰው ይበለን!

Please follow and like us:
error

4 COMMENTS

Leave a Reply