የዕውቀት መፍለቂያው ልቦና፣ ሕሊና ወይስ የስሜት ሕዋሳት?

‹ልቦናን› ስናነሣ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ ‹የዕውቀት መፍለቂያው ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ ነዋ! የዕውቀት ምንጩን ማወቅ ደግሞ ጭንቅ ነው፤ ምክንያቱም የዕውቀት የመገኛ ምንጩና አገኛኘቱ በትክክል መታወቅ ከተቻለ የማይታወቅ ነገር አይኖርም፡፡ የማይታወቅ ነገር ከሌለም ፍጹማዊ ዕውቀትን ገንዘብ ማድረግ ይቻላል፡፡ ፍጹማዊ ዕውቀትን ገንዘብ ማድረግ የሚችለው ግን ልዕለ ኃያል የኾነው እግዚአብሔር እንጂ በችሮታ የሚያገኘውን ዕውቀት በቅደም ተከተል፣ በመርሳትና በማስታወስ እየመረጠ የሚያገናዝበው የሰው ልጅ አይደለም፡፡ ለብዙ ሰው ዕውቀት በምንጩ የተወሳሰበ ስለሚመስለው በአግባቡ ለይቶ ለማሰብና የተሻለ አስተሳሰብን ገንዘብ ለማድረግ ይቸገራል፡፡ በሌላ በኩል የሚያውቀው ዕውቀት የተደበላለቀበት ሰው ምንጩን ካላወቀ ‹ከየትና እንዴት› የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይቸገራል፤ ‹ከየት› የመረጃ ምንጭ፣ ‹እንዴት› ደግሞ የማወቂያ ዘዴ (ስልት) ነውና፡፡ ይህ ከኾነም ማንኛውም ተመራማሪ ቢያንስ የተቻለውን ያህል የዕውቀቱን አገኛኘት መለየት ይገባዋል፡፡

ጥያቄውን ጠበብ ስናደርገው ‹ዕውቀት በውስጣችን ተጽፎብን ነው የተፈጠርነው ወይስ በመሰብሰብ ያጠራቀምነውን ነው ማወቅ የምንችለው?› የሚል ይመጣብናል፡፡ ‹ከውስጣችን ተጽፎብን የተፈጠርን ከኾነ ያንን የተጻፈብንን ዕውቀት በምን እና እንዴት ነው የምንገነዘበው? ከውጭ የምንሰበስበው ከኾነም እንዴት በሕሊናችን ውስጥ ተሰብስቦ በመግባት ልንረዳው ቻልን? ነው ከውስጣችን የተጻፈብን እና ከውጭ በስሜት ሕዋሶቻችን የምንሰበስበው በመናበብ ነው ዕውቀትን እንድናውቀው የሚያደርጉን?›

የሕፃን ልጅ አንጎል፣

የልጆች አዕምሮ፣

የጻፉበትን ይይዛል፣

የነገሩትን ይቴፓል፡፡ [1]

ይህ ግጥም ዕውቀት ተሰብሳቢ መኾኑን ነው የሚገልጸው፤ ሕፃናት ዕውቀት ስላልተጻፈባቸው ከተወለዱ በኋላ በስሜት ሕዋሳታቸው የሚሰበስቡትን በማጠራቀም ዐዋቂዎች ይኾናሉ የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን የዕውቀት ምንጭ› ክርክር ዋናው የፍልስፍና የክርክር ሞተር ነው፡- የዕውቀቱን መኪና የሚያሽከረክረው ሹፌር (ፈላስፋ) እንዲበርም እንዲንቀረፈፍም የሚያደርገው የዚህ ሞተር ኹኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ሕፃናትን እንደ ነጻ ወረቀት በመቁጠር የጻፉባቸውን በማጠራቀም ዕውቀታቸውን ያዳብራሉ ማለት የክርክሩ መቋጫ መኾን አይችልም፡፡

በተለመደው ፍልስፍና አንጻር እንመርምር ካልንም በሦስት ከፍለን (፩. የሰው ልጅ ዕውቀት ተጽፎበት ተፈጥሯል፣ ፪. እየሰበሰበ ያጠራቅማል፣ £. ከኹለቱም ነው በሚል) እናከታክትበታለን፤ መከታከቱ ወገን በመለየት ስለኾነ ስንቶች በውገና ቢዋጉበትም አልተሸናነፉበትም፤ ስለዚህ ስምምነቱን ላናገኘው ከምንዛቁን እንለፈውና፤ ቀጥታ ወደ ሀገራችን ሊቃውንት አስተምሀሮ እንሳበው፡፡ አሽ! የሀገራችን ሊቃውንት ‹የሰው ልጅ ዕውቀቱን ከምን? እንዴት? ያገኛል› ይላሉ? አላችሁ!

እንደሀገራችን ሊቃውንት አስተመህሮ ከኾነ (እኔ የተገነዘብኩ የመሰለኝ) የሰው ልጅ በተፈጥሮው ዐዋቂ ተደርጎ የተፈጠረ ነው፤ ስለኾነም የዕውቀቱ ምንጭም ከተጻፈበት ከልቦናው ይፈልቃል፤ ይህም የዕውቀቱ መሠረት ከሕገ-ልቦናው ጋር የተገናኘ ነው፤ ይህ ከልቦናው የሚፈልቅ ዕውቀት በሕሊና ሲነበብ (‹ጎሣ ልብዬ ቃለ ሠናዬ› እንዲል) ግን በምክንያት ይመራል፤ ሕሊናችን እስከሚያነበው ድረስ ግን ዝም ብሎ ተጽፎ ይቀመጣል እንጂ ተነቦ ሊታወቅ አይችልም፤ ሕሊና ደግሞ ከልቦና የፈለቀውን ቃል ያገናዝባል፡፡ ሕሊናችን ዕውቀትን አንብቦ እንዲረዳም ከውጭው ዓለም ጋር ከሚያገናኙት ከማንበቢያዎቹ ከስሜት ሕዋሳት ጋር መስተጋብር መፍጠር መቻል አለበት፤ ስለዚህ ሕሊናችን የውስጣችንን የዕውቀት ጽሑፍ (መዝገብ) በስሜት ሕዋሳት አመካይነት ከተቀበለው ጋር አስማምቶ በትክክል ሲያነበውና መልሱንም በአግባቡ ሲመልስ የተስተካከለ ዕውቀት ይኖረናል፤ ያለ በለዚያ ግን በልቦናችን የተጻፈውም አይገለጽልንም፤ ከውጭው የምንሰበስበውም ተተርጉሞና ተናቦ አይታወቅም፤ ዕውቀታችንም ሕጸጽ የተፈጸመበት ይኾናል፤ የተሟላ ወይም የተስተካከለ አይኾንምና (በፊደል ቅንብር የሚጻፍ ቃል ከሕሊና እንደሚፈልቀው፤ የሕሊና ዕውቀት የሚፈልቀው ከልቦና ነው፤ የስሜት ሕዋሳት ደግሞ እንደ ፊደል መጻፊያ ቀለማት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ሐሳብ ተገልጾ ሊነበብ የሚችለው ኹለቱ በውስጥ በልቦና የሚፈልቀው እና የውጭውን ዓለም ማንበቢያዎቹ የስሜት ሕዋሳት ሲገናኙ ነው፤ ምክንያቱም የዓለም ምሥጢር በልቦና ስለተጻፈ ውጫያዊው መረጃ ይህንን ጽሑፍ እንዲነበብ ያደረግልናል፤ ማንበቢያው ደግሞ ሕሊና ነው፤ የሕሊና ሚዛናዊ ተጠየቃዊነትም የውጭውን ከውስጡ ጋር አስማምቶ ማሰብ ነው፡፡ ከኹለቱም ዋናው የዕውቀት ምንጭ በሕገ-ልቦና ላይ የተጻፈው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የዕውቀትና የሕግ መዝገብ ነው፡፡ የሰው ልጅ ኹሉ በሕገ-ልቦናው የጋራ ተፈጥሯዊ ሕግ ወይም መርህ ተጽፎበታል፤ ጽሑፉም ከመለኮታዊ ሕግጋትና ዕውቀትም  ይቀዳል፣ በሕሊና ተንፀባርቆም ይታሰባል፤ ተፈጥሯዊ ጽሑፉም በሕሊና ተንፀባርቆትና ውጫዊ ግንኙነቶች እየተብላላ መስተጋብር ይፈጥራል፤ መስተጋብሩም ከመሠረቱ ጋር ሲስማማ በሕሊና ምክንያታዊነት በደረጃና በቅደም ተከተል እየተለየ የሚገናዘብ ሐሳብ (ዕውቀት) ይኾናል፤ የሕሊናም ተግባር የውጭውን መረጃ በልቦና ከተጻፈው ጋር ማስማማት ነው፡- ብለናልና፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ የተፈጠረው የአጽናፈ-ዓለም ዕውቀትና ሕግጋት በልቦናው ተጽፎበት ብቻ ሳይኾንም ‹በአንክሮ በተዘክሮ› አጽናፈ-ዓለሙን እንዲመረምር ጭምር ሰብሳቢና አናባቢ የሕሊና ሕዋሳት ይዞ ነው፤ ስለኾነም ሕሊናው ከውጫዊ ዓለም የሚያገኘውን የትኛውንም መረጃ በልቦናው ከተጻፈው ጋር በማስማማት ይተረጉማል፡፡

የሰው ልጅም ከውጫዊው ዓለም ጋር መስተጋብር ስለሚያደርግ፤ ዕውቀቱም የዚህ መስተጋብር ማከናወኛ መንገዱ ነው፤ መስተጋብሩም በሕሊና እንደ ፊደል መዝገብ ጎልቶና እንድንዘክረው ተመዝግቦ ይኖራል፡፡ እጓለም ‹ሕሊና እና ፊደል ይዛመዳሉ፡፡ ያስገኝና ተገኝ ግንኙነት አላቸው፡፡ ሕሊና የመፈተሸ፣ የመመርመር፣ የመምረጥ፣ የአመክንዮ (ካወዛሊታስ) ችሎታ ነው፡፡› [2]ይላል፡፡ ስለዚህ በልቦናችን ውስጥ የተጻፈብን የተፈጥሮ ምሥጢር እየተዘከረ ከውጭ በምናገኘው ቀለም (መረጃ) ጎልቶ አንድናሰላስለውና በፊደልነት (የሐሳብ ቅርጽ) ጎልቶም እንድናነበው ያደርገናል፡- ሕሊና፡፡ ነገር ግን የውጭው መረጃ የተበተነና ብዙ ስለኾነ፤ የመረጃ መሰብሰቢያና መላኪያ የስሜት ሕዋሶቹ ኹኔታም ውስን፣ የቅደም ተከተል ተገዥነት ስላለባቸው እንደ ስሜት ሕዋሳቱ ተፈጥሮና አገልግሎት በየፈርጁ እየተሰበሰበ ወደ ሕሊናችን የሚገባውና በግብረ መልስ የሚወጣው የዕውቀት መስተጋር ተቆጣጣሪና በሥርዓት የሚመራው ይፈልጋል፡፡ ‹ምክንያት የሥርዓት ግንባታ ነው› የሚባለው የውስጣዊ (የልቦናን) የዕውቀት ምንጨት ከውጫዊ መረጃ ጋር በትክክል እያነበበ ስለሚያስማማውና ስለሚየሳውቅ ነው፡፡ ‹ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደ እሳት› እንደተባለውም የውጭ ዕውቂያችን በውስጣችን የተጻፈውን በመቀስቀስ ከውስጥ ተቀጣጥሎ በሕሊና አቀናባሪነት መስተጋብር ይፈጥራል፤ ከውጭ ደግሞ በስሜት ሕዋሳት አማካይነት እየተሰበሰበ ውስጥ ካለው የልቦና ምንጭ ጋር ተገናዝቦ  እየተስማማ ይታሰባል፤ ይተገበራል፡፡ ስለዚህ ሕሊና ከውጭ በስሜት መስኮቶች የተሰበሰበ መረጃ ከልቦና ሕግጋት ጋር በመናበብ ወደ ሐሳብነት የሚቀየሩበት የምክንያት፣ የሥርዓትና የውሳኔ መድረክ ነው፡፡ ሕሊና ውስጣችን ባለው (በተጻፈው) የልቦና እሳት አማካይነት ጥሬውን እያበሰለ ወይም በምክንያት ፈጭቶና አድቆ እያረቀቀ በሥርዓት የተቀናበረ ሐሳብ (ዕውቀት) ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ሐሳብ ከልቦና ከተጻፉ ሕግጋትና ሥርዓት ይመነጫል፤ ይህ ምንጨቱ ግን ከውጫዊ የክስተቶች መስተጋር ጋር ካልተናበበ አይገለጽም፤ ከውጭዊ ክስተቶች ጋር መስተጋበር በመፍጠር ወደ ሐሳብነት ለመቀየርም የሕሊና ዳኝነት ያስፈልገዋል፤ ስለኾነም ሕሊና በልቦናችን የተጻፈብን የዕውቀት ሕግጋት ከውጫዊ ዓለም ክስተቶች ጋር በማናበብ በሐሳብነት እንድናውቀው ማድረጊያ ወይም የውስጣችንን ተፈጥሮ ከውጫዊው ተፈጥሮ ጋር አገናኝቶ ማስተዋወቂያ መድረክ ነው፡፡ ስለዚህ ውጫዊ መረጃ (ዕውቀት) በልቦናችን የተጻፈው የዕውቀት ምሥጢር በሕሊና እንዲተረጎም የሚደረገው በዚህ ዓይነት ቅኔያዊ  (መስተጋብራዊ) አተረጓገም ነው፡፡

ከልቦና የሚፈልቅ ዕውቀት ሲባል ብዙ ሰዎችን ግር ያሰኛቸዋል፤ እንዳውም አንድ ኢትዮጵያዊ የፍልስፍና ምሁር በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና (ስለ ዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍና) ጽሑፍ ሲያቀርቡ ‹ኢትዮጵያውያን ሰው በልቡ ያስባል እንላለን› በማለታቸው መጨቃጨቂያ (መሣቂያም የሚሉ አሉ) ኾነው እንደነበር  ሰምቻለሁ፡፡ እንደ እኔ ግንዛቤ ችግሩ ያለው የልቦና እና የሐሳብን ግንኙነት ካለመረዳት የመጣ ይመስለኛል፤ ልብ ማለት ‹ለበወ› ከሚለው ግሥ የሚገኝ ሲኾን ‹ልብ አደረገ (አስተዋለ)፣ የጥልቀት መነሻ ኾነ ወይም ‹መመንጫ፣ መፍለቂያ› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቤተክርስቲያን በምሥጢረ-ሥላሴ አስተምህሮ አብ በልብነት፣ ወልድ ደግም በቃልነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስ ይመሰላሉ፤ ይህም ምሳሌ የሚሠጠው ወልድ (ቃል)ና መንፈስ ቅዱስ (መንፈስ)፣ ከአብ (ከልብ) የፈለቁ ወይም የወጡ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፤ በዚህም ወልድ ይህንን ምክንያታዊ ዓለም በመፍጠር እና ሰው ኾኖ በመገለጽ እግዚአብሔርንና አጽናፈ ዓለምን እንድናውቅ አድርጎናል፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የሕይወት ምሥጢርን ይገልጻል፡- ነው እምነቱ፡፡ ይህ የሥላሴ ኩነታዊ ምሥጢርም አንደኛ የልቦናነት አፍላቂነት፣ ሕሊናም ከልቦና የፈለቀውን ከውጫዊ ዓለም ጋር ማገናኛ መድረክ መኾኑን ያሳያል፤ ኹለተኛም አብ ወልድ እንዳልኾነ የሐሳብ ማብለያና ማገናዘቢያ መድረክ ሕሊና እንጂ ልቦና አለመኾኑንም ይመሰክራል፤ ‹ጎሣ ልብየ፣ ቃለ ሠናየ› እንዳለው ዘማሪው ዳዊት የኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት የልቦናና የሕሊና ጉንኙነት ከዚህ ጋር የተናበበ ነው፤ ስለዚህ ምሁሩ በዚህ መልክ ቢያቀርቡት ትክክል የሚኾኑ ይመስለኛል፤ ቀጥታ በልብ እናስባለን ማለታቸው ተለምዷዊ አነጋገርን የተከተለ ይመስላል፡፡

ምናልባት ‹ልብ በል› ማለት ‹አስተውል!› ማለት ስለኾነ፤ እንዲሁም ‹ልቦና ማለት ‹ማስተዋያ. ወይም በጥልቀት መረጃ(መረዳት)› ማለትን ስለሚገልጽ  ልቦና ማለት ማሰቢያ መስሏቸው ሊኾን ይችላል፤ እንዲሁም ፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብ ልቦና! ልቦና! ሲል ማሳቢያን ከአእምሮ ነጥቆ ለልብ የሰጠ መስሏቸውም ይኾናል፡፡[3] አባባሉ ግን ልቦና የሰው ልጅ የተፈጥሮ ሕግጋትና ሥርዓት የተጻፉበት ስለኾነ፣ እንዲሁም የውጫዊውን ዕውቀት ትክክልነት በሕሊና አማካኝነት እያገናኘ በማናበብ ውሳኔ የሚሰጠው ሕሊና የሚፈርደው ከተፈጥሯዊ ሕግጋት ጋር በትክክል በማናበብ ስለኾነ ‹በልቦና ከተጻፈብህ ከተፈጥሯዊ ሕግጋትና ሥርዓታት ጋር በአግባቡ አገናኘው› ለማለት እንጂ ማሰቢያህን ወደ ልብ ቀይር ማለት አይደለም (‹አብ ወልድ እንደማይኾነው ወልድም አብ አይኾንም› እንዲሉ)፤ ለዚያም ነው በብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ተደርጎ የሚወሰደው ዘርዓ ያዕቆብ በሐተታ መጽሐፉ በብዛት ‹ልቦናዬ አልተቀበለው› ወይም ‹ከልቦናችን ጋር ይስማማል› በማለት ዋናው የዕውቀት ሚዛኑን ልቦና ያደረገው፤ አበውም ‹ልብ ያሰበውን› ሲሉ ምሥጢሩ ልብን የዕውቀት ምንጭ ወይም የጥልቀቱ መዳረሻ ልቦና መኾኑን መግለጣቸው እንጂ ማሰቢያችን አእምሯችን ሳይኾን ልባችን ነው ማለታቸው አይመስለኝም፤ ‹ማሰቢያችን አእምሯችን ሳይኾን ልባችን ነው› የሚሉ ቢኾን ኖሮማ ‹አእምሮ› (ማወቂያ) እና ‹ሕሊና› (ሐሳብ) የሚሉ ቃላትን ከዕውቀት ጋር አያይዘው ባልፈጠሩ ነበር፡፡[4] በመኾኑም በልቦናችን የሚገኘው በተፈጥሮ የተጻፈብን ዕውቀትና ሕግጋት ሲኾን በምክንያት እየተለየ የሚገናዘብ ዕውቀት የሚኾነው በሕሊና መድረክ ከውጫዊ ዓለም ጋር መስተጋብር ሲፈጥርና ሲስማማ ነው፡፡ ስለዚህ የልቦናንና የሕሊናን ልዩነት እና መስተጋብራዊ ግንኙነት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ይህ የማወቂያ ጉዳይ በአሁኑ ዘመን ፈላስፎችም ጭቅጭቅ አለበት፡- ‹ዕውቀትን ማወቅ የምንችለው ወይም የሰው ልጅ የሚያስበው በአንጎሉ ነው ወይስ በልቡ? ወይስ በሌላ ውስጣዊ አካሉ?› የሚለው ጥያቄ አጨቃጫቂ እየኾነ መጥቷል፡፡ ቀደም ካሉ ፈላስፎችም ታላቁ ፈላስፋ አማኑኤል ካንት የምክንያትን ውስንነት በመግለፅ የሰው ልጅ በሐሳቡ ሊደርስበት የማይችል ሥውር ነገር (Noumenon or Thing-in-itself) መኖሩን ይከራከራል፤ የሕግጋት፣ የደስታ፣ የደግነት ኹሉ ምንጭ መልካም ፈቃድ መኾኑንም ይገልጻል፡፡ የእሱን መከራከሪያ መሠረት በማድረግም ሾፐንሐወር፣ ፌርደርኪ ኒቼ፣ ሄደገር፣… የመሳሰሉት ታላላቅ ፈላስፈች የምክንያትን ውስንነት ተቀብለው ፈቃድን ገዥ በማድረግ ተከራክረዋል፡፡ ለምሳሌ ሾፐንሐወር ‹ዓለምን እንዳሳብ፣ እንደፈቃድ› በሚለው መጽሐፉ ዓለም የተሠራው በፈቃድ ነው፤ የሚጠቀለለው በፈቃድ ስለኾነ ፈቃድ የሌለው ነገርም አይኖርም በማለት ተከራክሯል፤ ምክንያትንም ከፈቃድ  በጣም የተወሰነ ክፍል መኾኑን ተከራክሮበታል፡፡ ኒቼ ደግሞ ፈቃድ ወደ ኃይል መወጣጫ መሰላል ነው በሚል ከሰው ኹሉ የላቀ ሰውን ማስገኛው ከምክንያት ይልቅ የልቦና ፈቃድ መኾኑን ገልጽዋል፡፡ ሄደገርም በተመሳሳይ የምክንያትን ውስንነት በራሱ በምክንያት አገልጧል፡፡ ይህም የሐሳብ ዋና ሞተር የኾነው ምክንያት በዚህ መልክ ሲጣጣል፤ የስሜትና የፈቃድ አማራጭነት እየጎለመሰም ሄዷል፡፡ (ይህንን በማየት ይመስላል ሴነጋላዊው ፈላስፋ ሴንጎር ‹የአፍሪካውያን ፍልስፍና በስሜት ላይ የተመሠረተ ነው› የሚል መከራከሪያ በማቅረብ ስሜትን ለአፍሪካ ምክንያትን ለግሪክ በመስጠት የተሟገተው (በሱ ቤት መብለጡ ነው))፡፡ ይህንን በማለፍ ደግሞ ፍቅር የልብ ስለኾነ ማሰቢያችን ዋናው ልባችን ነው የሚል ክርክር ያላቸውም አሉ፤ ‹የማዳምጠው ልቤ የሚነግረኝን ነው› ብሏል አንዱ (ልብ ጆሮ ኾነ እንዳትሉ)፡፡ በየትም ይሁን ዋናው ነገር ‹ሐሳብ መሠረቱ የት ነው?› የሚለው አጫቃጫቂ መኾኑን መረዳት ነው፡፡ አሁን ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና የልቦናን ምሥጢር መመርምራችንን እንቀጥል፤ ለእኛ ግን በልቦናችን ሕግጋትና ሥርዓታት ስለተጻፉበት የሐሳብ ማፍለቂያ ይኾናል እንጂ ማገናዘቢያና የተጠየቅ መድረክ አይደለም፡፡

‹ለበለጠ መረጃ› እንዲሉ የልቦናን ምሥጢር ከልብ ደምን ማመንጨት ጋርም በማነጻጸር መረዳትም ይቻላል፤ ምክንያቱም ደም ከልብ እንደሚመነጨው ልቦናም ለሐሳብ መፍለቂያ ነውና[5]፡፡ ከልብ የሚመነጨው ደም በዝውውሩ አንጎልንም ጭምር ኹሉ መቆጣጠር ይችላል፤ አንጎል ደግሞ የተጣራውንና ተስማሚውን እየለየ ደም በሰውነት ውስጥ በአግባቡ እንዲሠራጭ የሚያደርገው አዛዡ፣ ሚዛን ጠባቂውና የእንቅስቃሴው ተቆጣጣሪ ነው፡፡ የሚገርመው ግን አንጎል ሥራውን የሚያካናውነው ይህንን ደም በነዳጅነት እየተጠቀመ መኾኑ ነው (በማቀጣጠያነት)፤ የሰው ልጅ የደም መነሻ መዘውሩ ያለው ግን ልቡ ውስጥ ነው፡፡ ሐሳብም እንደዚሁ ነው፤ መፍለቂያው ልቦና ሲኾን በምክንያት እየተብላላ በሥርዓት የሚገናዘበው ደግሞ በሕሊና ነው፤ ስለዚህ ምክንያታዊ ዕውቂያችን የሚመሠረተው በሕሊና ግንዛቤ ነው፤ ከግንዛቤ ያለፈው የልቦና-ሕሊና መስተጋብር ይሰማናል እንጂ በምክንያት አንገልጸውም (ለምሳሌ ፍቅር)፤ እንኳን ልቦናችን ፈጣን የሰውነታችንን መስተጋብር የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ባሰላስሎሻዊ ዕውቂያ አንጻር ለእኛ ዝም ያለ ነው፡- በመታሰብ አይገለጽም፤ በውስጣችን ምን እየተከናወነ እንደኾነ አገናዝበን የማወቅ ዕድላችንና አቅማችንም ውስን ነው፤ የትኩረት አቅጣጫችን አይደለም፤ ያለ አብሰልስሎሻዊ ዕውቂያ ሥራውን ይሠራል፤ ክፍሉም የትውስታዎች ማብላሊያና መዋቀሻ ሸንጎ ሳይኾን እንደ መንግሥት በግልፅ ሳይታይ ኹሉን በሥውር የሚመራ ነው፡፡

ይህም ማለት የደም ዝውውር በአንጎል ቁጥጥር እየታዘዘ የሰውነት አካሎቻችንን ኹሉ ደማችንን እንደሚያዘዋውረው፤ ሕሊናችንም በመስኮቶቹ የስሜት ሕዋሳት አማካይነት የውጭውን ዓለም እያነበበ፣ በሐሳብነት ቀይሮ ከልቦናችን ሕግጋት ጋር እያገናዘበ አግባባዊ ዕውቀትን በማስገኘት ትክክልነቱን ለይቶ በመፍረድ ጠብቆልን ይኖራል፡፡ ስለኾነም ይሰማናል እንጂ የልቦናችን የሐሳብ ምንጨት ምንነቱንና ከአእምሯችን ጋር ያለውን መስተጋብር ማወቅ አንችልም፤ ግን መስተጋብራዊ መናበባቸው ከተስማማ መልካምነቱ ይሰማናል፤ ሕሊናችንም አይወቅሰን፤ እንዳወም በትክክልነቱ እርካታን ይሠጠናል፡፡ ስለኾነም ልቦና የሕግጋትና ሥርዓት ተፈጥሯዊ ጽሑፍ ያለበት በሕሊና መስተጋብር አማካይነት ከውጫዊ የሕግጋትና ሥርዓት መረጃዎች ጋር ተናቦ የሚተረጎም ታላቅ ቅኔ ያለው የምሥጢራት ኹሉ ጥልቁ ምሥጢር ነው፡፡

[1] K=l ¯KS<& u#›T`— Y’ ÓØU$ w`H’< Ñu¾G< እ”ÅÖkc¨<  Ñê 49::

[2] ‹ብፁዓን ንጹሐነ ልብ› ስለ ክርስቲያን ሥነመግባር መሠረት፣ ገጽ 56

[3]  ዘርአ ያዕቆብ የፍልስፍና ሚዛኑን ልቦናውን አድርጎታል ማለት ይቻላል፤

የተወሰኑ ምሳሌዎችን ማየት ይቻላል፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔርን የለመነውም ‹ልቦና ስጠኝ› ብሎ ነው (ገጽ 16)፤ ምክንያቱም የተፈጥሮን ሕግ ትክክልነት የሚመሰክረው ልቦናው ነው፤ ይህንንም ‹የተፈጥሮንም ሕግ ከመረመርን የተረጋገጠ መኾኑን ልቦናችን በግልፅ ይነግረናል› በማለት ገልጾታል (ገጽ 27)፡፡ የፈጣሪን መኖር በሚመለከት ‹ፍጡር አለፈጣሪ ሊገኝ እንደማይችል፣ ፈጣሪ እንዳለ ግን እውነት ነውና፤ ይህ የምናየው ኹሉ ፍጡር እንደኾነው የሰው ልቦና ያውቃል፡፡ ሰዎች ኹሉ በዚህ ይስማማሉ› በማለት ፍጥረቱን በማየት የፈጠሪውን መኖር ያመሠጥራል (ገጽ 24)፡፡ የተነገራቸውን ተቀብለው የሚኖሩትን ሊቃውንት ሲተችግን ‹ከፊተኞቻቸው በሰሙት ልባቸው ረግቷል፡፡ እውነት ወይም ሐሰት መኾኑን አልመረመሩም› ይላል (ገጽ 18)፡፡ የሚያስበው ወይም የሚመረምረው ቃል ከልቦናው ጋር መናበቡን ‹ልቦናችን ይነግረናል› (ገጽ 21)፣ ‹ልቦናችን ያስተምረናል› (ገጽ 22)፣… በማለት ሲገልጽ አለመስማማቱን ደግሞ ‹ልቦናዬ አልተቀበለውም›፣ ‹ከልቦና ጋር የማይስማማ› (ገጽ 27)፣ ‹ልቦናችን ዝም ይላል› (ገጽ 28)፣… እያለ ይገልጻል፡፡ በጥቅሉ ለዝርአ ያዕቆብ የኹም ነገር መለኪያ ልቦና ነው፤ ይህንንም ለተማሪው ለወልደሕይወትም ‹አንተ ግን መጻሕፍትን ከመረመርካቸው እግዚአብሔር እውነት እንድንፈልግበት ከሰጠን ከልቦናችን ጋር እማይስማማ ክፉ ጥበብ ታገኝባቸዋለህ› (ገጽ 47) በማለት ልቦናውን ሚዛን አድርጎ እንዲመረምር እንዳስተማረው ይነግረናል፡፡ ኾኖም በዘርአ ያዕቆብ አቀማመጥ የልቦና እና የሕሊና ልዩነትና ግንኙነት ግልጽ ኾኖ አልተለየም፤ ስለኾነም ይህ ነጥብ ሰፊ ምርምርንና አስተውሎትን የሚጠይቅ ነው፡፡

[4] እንደኔ አረዳድ የቀድሞ ሊቃዉንት ግንዛቤያቸዉ ጥልቅና ምጡቅ በመኾኑ ለእያንዳንዱ ነገር የሚሰጡት ወይም የሰጡት ስያሜ ራሱ ጥልቅ ፍልስፍናቸዉን የጠበቀ ነዉ፤ ‹ልቦና›፣ ‹አእምሮ›፣ ‹ሕሊና›፣ ‹አንጎል›ና የመሳሰሉ ስያሜዎችም ፅንሳባቸው ዝም ብሎ የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ልቦና ከልብ ጋር የተያያዘ መኾኑ ግልጽ ነው፤ አእምሮ ደግሞ ማወቂያ ማለት መኾኑና በአንጎል ውስጥ የሚገኝ ማሰቢያ እንደኾነ ይታወቃል፤ ሕሊና ሲባል ደግሞ የአእምሮ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ወይም የሐሳብ ግንዛቤ ማለት ነው፤ ስለኾነም ሐሳብ ከልቦና የሚፈልቅ ቢኾንም የሕሊና ገንዘብ ነው፡፡

[5] አንጎል የአእምሮ (አእምሮ ማለት ማወቂያ ማለት ነው) ቤት ሲኾን ሕሊና የፍርድ ውሳኔ ሰጭ የአእምሮ አካል ነው፤ ብዙውን ጊዜ አእምሮና ሕሊና አንድ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በአንድ ምሁር ዕይታ ሕሊና የምንለው ‹ምጡቅ (ንቁ) አእምሮ› (conscious mind) ነው (ዜጋ መጽሔት፣ 2ኛ ዓመት ቁ.5፣ ጥር 1993)፡፡ ስለዚህ አንጎል የሕሊና መኖርያ እንደኾነው፤ ልብም የልቦና መገኛ ነው፤ አንጎልና ልብ ቁስ አካላት ሲኾኑ ሕሊና እና ልቦና መንፈሳዊነት ያላቸው ነገሮች ናቸው፡- ሐሳባዊ የኾኑ፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply