የጥቁር አፈር ትሩፋት

( የኮተቤው የሻው ተሰማ)

ይኼ ያፈር አዋይ– ይኼ ያፈር ነዋይ…

ይኼ ያፈር ጌታ– ይኼ ያፈር ጎታ- ይኼ ያፈር ሲሳይ…

ይኼ ያፈር ወገን– ይኼ ያፈር ተገን …

ነፍስና ሥጋውን አፈር ያበጃጀው…

አክሊሉን ተክሊሉን አፈር ያቀዳጀው…

አፈር ይመገባል– ወዳፈር ይገባል፡፡

ካፈር ውስጥ ይወጣል– አፈሩን ይረግጣል፡፡
ባፈር ይጫወታል– ላፈር ይሟገታል፡፡

ላፈሩ ይዘፍናል– ላፈር ይዘምራል፡፡

 

ይኼ ያፈር አዋይ– ይኼ ያፈር ነዋይ…

ላፈሩ ይሞታል– ላፈሩ ይገላል፡፡

ባፈሩ ይምላል– ባፈሩ ይሣላል፡፡

ባፈሩ ያቅራራል– ባፈር ይፎክራል፡፡

አፈር ላይ ይጥራል– አፈር ይቋጥራል፡፡

አፈር ለብሶ ውሎ፣ አፈር ለብሶ ያድራል፡፡

አፈር ይናዘዛል– ባፈሩ ይመካል፡፡

አፈሩን ይገዛል– አፈሩን ያመልካል፡፡

ላፈሩ ይሰግዳል– ላፈር ይማገዳል፡፡

 

ሎሌ ነው- ጌታ ነው፤ ለጥቁር አፈሩ፡፡

ፍጡር ነው- አምላክ ነው፤ ለጥቁር አፈሩ፡፡

ምርት ነው- ጥሪት ነው፤ ለጥቁር አፈሩ፡፡

 

ይኼ ያፈር አዋይ– ይኼ ያፈር ነዋይ…

በነቢብ በግብሩ– አፈር ነው ነገሩ፡፡

በሞት- በህላዌ፣ በነፍስ- በሥጋው፤

መክሊቱ ተመኑ፣ አፈሩ ነው ዋጋው፡፡
በደግ- በክፉ ፣አፈሩ ናት ትርፉ፡፡

ለማወቅ ቢጥሩ– ጥቁር ነው ምሥጢሩ፡፡
ቀና ቢለው ቢያዩ– ጥቁር ነው ሰማዩ፡፡
ከወንዞች ሲሳዩ– ጥቁር ነው ዓባዩ፡፡

ሲምሱት ከሥሩ– ጥቁር ነው አፈሩ፡፡

ሲገልጡት ከጅስሙ– ጥቁር ነው ቀለሙ፡፡
አጥንቱና መቅኔው– ጥቁረቱ ነው ቅኔው፡፡

ካፈር ዘር ተዘርቶ– ከጥቁር ተመርቶ፤

ጥቁር እንደወለደው– አፈር ነው (እ)ሚወስደው፡፡
ይሁንና አጅሬው፣ በዚህ አይታማም…

ጥቁረቱን– መክሊቱን፣ መቅኔውን- ቅኔውን፣ ጅስሙን አያስማማም፡፡

(የጥቁር አፈር ትሩፋት)

Please follow and like us:
error

Leave a Reply