የጥበብ መጀመሪያ መደነቅ ወይስ እግዚአብሔርን መፍራት?

(በካሣሁን ዓለሙ)

የሀገራችን የጥበብ አረዳድ ‹እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው› በሚለው በጠቢቡ ሰለሞን መርህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ደግሞ ‹መፈላሰፍ በመደነቅ ትጀመራለች› በማለት ገልጽዋል፡፡ እነዚህ የጥበብ መሠረታዊ መርሆች የሚጣረሱና የማይስማሙ ይመስላሉ፡- ‹‹ፈሪ› ነው፤ ‹ተደናቂ› ጥበበኛ!?› በሚል ጥያቄ ተነሥቶ የጥበብ መሠረቱ ‹መደነቅ› ነው ወይስ ‹መፍራት› በሚል ማጠንጠኛ ላይ ይሽከረከራል፡፡ ‹ገለጻዎቹስ በምሥጢር የሚገናዘቡ ናቸው የሚጻረሩ?› የሚል ጥያቄም አብሮ አለ፡፡

ካስተዋልነው ግን የሶቅራጥስ ገለጻ ከሰው ልጅ ዕውቀትን መሻትና ምርምር ናፋቂነት አንጻር የተቃኘ ሲኾን የሰለሞን ደግሞ ከሰፊውና ከምጡቁ ከእግዚአብሔር ማንነትና ከሰው ጋር ከሚያደርገው መስተጋብር ጋር ይገናዘባል፡፡ ችግር የሚፈጠረው በአንድኛ ዕይታ ዙሪያ ብቻ ተሸብቦ በመገተር እንጂ (በተለይ ሶቅራጥስኛ ላይ ተገትሮ መቅረት ልማድ ኾኗል) ኹለቱም በዕይታ አንግላቸው ቢለያዩም በአስተውሎታቸው የሚገናዘቡ ይመስላሉ፡፡

ለሶቅራጥስ በተፈጥሮ ምንነትና በሰዉ ማንነት መደነቅ የፍልስፍና አስተሳሰብ ወይም መጠበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህም አንድ የቅኔ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉባዔ ቃና ቅኔ ሲቀኝ ባመሠጠረው ምሥጢር ተደንቆ በደስታ እንደሚፍነከነከውና ሌላም ቅኔ ለመቀኘት እንደሚሻቅለው ዓይነት መኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ እንደሶቅራጥስ ከኾነ አንድ አስተዋይ ሰው ከራሱ በመነሳት ምርምር ሲጀምር የተፈጥሮ ውስብስብነት፣ ስፋት፣ በሥርዓት ተያያዥነትና ተመጋጋቢነት እየደነቀው ተጨማሪ ምርምርን ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት ፈላስፋነትን ያጎናጽፈዋል፡- ‹ወደ ራስ ማንነት መዋጥ መሰልቀጥ› እንዳለው ገጣሚው ሰለሞን ደሬሣ፡፡

ለእኔ ግን የሰለሞን የጥበብ ገለጻ ከሶቅራጥስ የበለጠ የሚጠልቅ፤ የሚረቅ ይመስለኛል፡- ይህ ነጥብ በዓለም ጥቅም ናፋቂነት ለተሸበቡ እንደማይገለጽም ይገባኛል፡፡ ባይኾን የሰለሞን ይጠልቃል ያልኩበትን ምክንያቴን ላስቀምጥ፡፡

የሰለሞን ገለጻ አንደኛ በሰውኛ የዕውቀት ዕይታ ብቻ ላይ የሚያተኩር ወይም የሚያጠነጥን አይደለም፡- ከእግዚአብሔር ማንነትና አፈጣጠር ላይ ተነሥቶ ከሰው ልጅ ዐዋቂነት ጋር ያለውን መስተጋብር ይቃኛል፡- ስለዚህ ‹ጥበብን ከእግዚአብሔር አንግል ማየቱ (መጀመሩ) ትክክል ነው ወይስ አግባብነት የለውም?› የሚል ጥያቄ ነው እንድናስቀድም የሚጋዘን፤ ይህን ጉዳይ ወደፊት እናየዋለንና እንለፈው፡፡ ኹለተኛም እንደኔ እንደኔ ከኾነ ‹እግዚአብሔርን መፍራት› የሚለው ቃል የያዘው ምሥጢር ጥልቅና ሰፊ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ብንመለከት ሶቅራጥስ የመደነቅን ጥበብ የሚጀምረው በራሱ ነው፤ ስፉህንና ልዩውን ውጫዊ አካል (እግዚአብሔርን) ዘንግቷል፤ ስለዚህ የሰው ልጅ ጥበብ ውስን በመኾኑ የጠቢቡም የፍልስፍና ድንቀት በውስን ክስተትና ውስብስብነት ዙሪያ ያጠነጥናል፤ እንዳውም በሶቅራጥስኛ (ራስህን ዕወቅ በሚለው መርሁ) ብቻ ከተመለከትነው የአጽናፈ-ዓለሙን ስፋትና ውስብስብ ተፈጥሮ ማወቅ እንደትርፍ ነገር ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሰው ደግሞ ዕውቀትን ለመሰብሰብ የሚሞክረው ከውጫዊ ነፀብራቅና ነባራዊ ኹኔታ ነው፤ ስለኾነም እስከ እግዚአብሔር ወይም ከእግዚአብሔር መለስ በአእምሮ ላይ ሳይሥሉ ዕውቀትን መወሰን የማሰብ አቅም እጥረትም ይመስላል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስብስባዊነት ጀምሮ መደነቁ ባይነቀፍም በሌላ በኩል ያለውን ክፍል በመዘንጋት ላይ ስለተመሠረተ የሶቅራጥስኛን ‹ትክክለኛ ድንቀት›  በሙሉ ልብ ለመቀበል የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ እንዲሁም የሥነፍጥረት ክስተትና የሰው ማንነትም ከውጫዊ አካል ጋር መስተጋብር አለው የምንል ከኾነም ሰለሞን ጥበብን ከእግዚአብሔር መጀመሩ አግባብና የበለጠ ጥልቅ ይኾናል፡፡ ይህ ከኾነም የሶቅራጥስ መደነቅ በሰለሞን መጠበብ ወስጥ ሊካተት ይችላል፤ የሰለሞን ገለጻ የሚያጠነጥነው እግዚአብሔር ከሥነ-ፍጥረቱና ከሰው ልጅ ጋር የሚያደርገውን መስተጋበር በአእምሮ በመሣል ነውና፡፡

ይህንን ብልም ዋናው የክርክር ነጥብ ‹እግዚአብሔርን ለምን እንፈረዋለን? ፍርሐት እንዴት የመጠበብ መነሻ ይኾናል?› ከሚል ጥያቄ ላይ ነው፡፡ ‹ፈሪ ለእናቱ› እንዲሉ፤ ይህች ‹እግዚአብሔርን ለምን እንፈረዋለን?› የምትለዋ ጥያቄ ናት የጥበብ መነሻ፡- ለጠቢብ ሰለሞን፡፡ ምክንያቱም ጥያቄዋን የሚያነሣ ተመራማሪ አርፎ አይተኛም የእግዚአብሔርን ማንነትና ሥራውን ለማወቅ ይከጅላል፤ ይጥራልም፤ ንዝህላል ወይም ትንሽና ትልቅን ወይም መጋቢና ተመጋጋቢ ሐሳብን መለየት ያቃተው ሰው ካልኾነ በስተቀር ጥያቄዋን ማሰላሰሉ አይቀርም፡፡ ሰነፉ ለጥያቄዋ ‹እሱ ደግሞ ማን ኾኖ ነው የምፈራው?› የሚል የትቢት ጥያቄ አንስቶ መልሱን በግርድፉ ሊያልፈው ይችላል፡- ይህ ደግሞ ፈጣንና ተፈጣሪን ያለመለየት ወይም ሸክላው ሸክላ ሠሪውን ‹አንተ ደግሞ ማን ኾነህ ነው እንደዚህ አድርገህ የምትሠራል?› ብሎ ጠየቀው እንደማለት ነው፡- ቅ.ጳውሎስ እንዳለው፡፡ የቻለውን ያህል መርምሮ መልሱን ለማግኘት የሚጥር አስተዋይ ግን የእግዚአብሔርን የድንቅ ባሕርይ ባለቤትነት፣ ስፋቱን፣ ጥልቀቱን፣ … እስከቻለው ድረስ ነቂሐ-ኅሊናውን አምጥቆ ይመረምራል፡፡ እንዲሁም የሥራውን ስፋት፣ ብዛት፣ ወስብስብነትና ያለውን ሥርዓታዊ መስተጋብርና ተመጋጋቢነት እየጠየቀ ይመረምራል፡፡ በዚህም ላይ ከአእምሮው በላይና አስተሳሰቡ ሊደርስበት የማይችል ብዙና ወስብስብ ነገር መኖሩን እየተገነዘበ በእግዚአብሔር ሥራ በመገረም ይደነቃል፡፡ ከዚያም አልፎ የእሱን ማንነትና የዕውቀት ምጣኔ የእግዚአብሔር ከኾነው ጋር እያነጻጸረ ግርምቱን ይጨምራል፤ ይህም የእሱ ውስንነትና ዐላዋቂነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ርቀት፣ ያላቅሙ መንጠራራቱን ስለሚያስገነዝበው በመደነቁ ወስጥ እግዚአብሔርን መፍራት ይፈጠርበተል፡፡

እግዚአብሔርን መፍራት በውስጡ ጥበብን ይጭርለታል፤ ምክንያቱም መጀመሪያ እኔ ማን ነኝና ነው ድንቅ ሥራ ከማድነቅ ባለፈ የረቂቅና ጥልቅ ጥበብ ባለቤት የኾነውን የእግዚአብሔርን ማንነት መመርመር የምችለው?› ብሎ ይጠይቃል፤ (የራሱን ማንነት ከእግዚአብሔር ጋር በማነጻጸር ፈራ፤ ተደነቀ ማለት ነው)፤ ይህም እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር የሚያደርገውን መስተጋበር ወደ መመርምር እንዲያዘነብልና በዚያ ዙሪያ እንዲተጋ ያደርገዋል፡- እግዚአብሔርን ለማወቅ ሥራውን ማወቅ ወደሚል ያዘነብላል፡፡ የሚፈራውም እግዚአብሔርን እንጂ ሥራውን ስላልኾነ፤ ፍርሐቱ ከእግዚአብሔር መለስ ፈጣሪ ከፍጥረቱ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ብቻ ሳይኾን የፍጥረቱን ምንነትና የእርስ በርስ መስተጋብርና ተመጋጋቢነት፣ እንዲሁም ሥርዓታዊ አኗኗር ለመመርመር ይጥራል፡፡ ጥረቱም ከፍጥረት አፈጣጠር እስከ አነዋወሩ ያለውን ሁኔታ፣ የርስ በርስ መስተጋበርና የራሱም ተፈጥሯዊ ማንነት በመመርመር መደነቅን ይፈጥራል፤ በዚህ ዙሪያም ይፈላሰፋል፡፡ በዚህ መልክ በሚያደርገው መጠበብም የፍልስፍናው ደረጃ ይገለጻል፡፡ ለዚያም ነው ሰለሞን ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው› ያለው፤ በውስጡም የሶቅራጥስ የመደነቅ ጅማሮ አብሮ አለበትና፤ ለእሱ (ለሰለሞን) መደነቁ እግዚአብሔርን በመፍራት ወስጥ የሚገኝ አንድ ነገር ነው፡፡ ይህ ከኾነም መደነቅ በኹለቱም ውስጥ አለ፤ ምንም እንኳን የዕይታ አንግላቸው ቢለያይም (ከራስ በመጀመርና ከእግዚአብሔር አንጻር በማየት) የኹለቱ ጠቢባን አገላለጽ ተመጋጋቢ እንጂ የሚቃረን አይደለም፡፡ ይህ ስለኾነም ይመስላል የኢትዮጵያ ሊቃውንት የሶቅራጥስን የመደነቅ መርህ ቢያውቁም መጠበባቸውን እግዚአብሔርን በመፍራት የሚጀምሩት፡- ውስንነታቸውን በመረዳት እና በእግዚአብሔር ህላዌ በማመን፤ ስለሚመራመሩ፡፡

Please follow and like us:
error

Leave a Reply